ይሁኔ አየለ (ዶ/ር)

 

yihayele@gmail.com

 

ልክየለሽ ውፍረትን (ኦቢሲቲ) የዓለም ጤና ድርጅት ‹‹ወረርሽኝ ደረጃ ላይ ደርሷል›› በማለት የወረርሽኝ (obesity epidemic) ደረጃ ሰጥቶታል። በተደረገ የትንበያ ጥናትም በ 2050 (እ.አ.አ) ከመቶው ሰባ አምስቱ የዓለም የበሽታ ሸክም በምንሸከመው የስብ ክምችት እንደሚመጣ ተነግሯል።

 

ውፍረት ‹‹እንዴት አምሮብሃል›› በሚባልበት ሀገር ሊያደርስ የሚችለው ጥፋት ሲታሰብ በጣም አስደንጋጭ ነው። ለዚህም በዋናነት መነሻ ይሆናል ተብሎ የሚገመተው የአመጋገብ ሥርዓት ለውጥ በሀገራችን እየተከሰተ መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው። ለውጡን በእውቀት እና በማስተዋል ካላስተናገድነው ‹‹እጦት ይሻለን ነበር›› ማለታችን የማይቀር ይመስለኛል። ለነገሩ፣ ውፍረት በለሙት ሀገሮች የድሆች መገለጫ ነው። በእኛስ? በጥናት የተረጋገጠ መረጃ ባይኖረኝም፣ የግል ትዝብቴ የሚነግርኝ፤ አስተማማኝ ገቢ ባላቸው እና (ሁሉም ባይሆኑም) በባለስልጣኖች ላይ ውፍረት መኖሩን ነው።

 

የዚህ መጣጥፍ ትኩረት፣ የትርፍ ስብ ክምችትና አመጣጡ ላይ ሳይንቲስቶች ያፈለቋቸውን ንድፈ ሀሳቦች ለአንባቢዎች ማካፈል ነው። አንባቢ ‹‹ከአስር ሚሊየን ህዝብ በላይ በረሃብ እየተሰቃየ ባለበት ሀገር፤ በጤናው ነው ስለ ውፍረት የሚያወራው?›› ይላል ብዬ እገምታለሁ። ረሀቡ ከአቅማችን በላይ ሆኖ በቶሎ ልናስቆመው ባንችልም ትኩረት ግን አልተነፈገውም። ከእኛም አልፎ ለጋሽ ሀገሮች ባለ አቅማቸው እርብርብ እያደረጉ መሆኑን አውቃለሁ። ውፍረትና መዘዙን ግን የእኔ ጉዳይ ብሎ የያዘው ያለ አልመሰለኝም።

‹‹ምን ያህልስ አንገብጋቢ ነው?›› የሚል ጥያቄም ሊነሳ ይችላል። ይህን ለማወቅ ወደ አንድ ሆስፒታል ሄዶ ሀኪም መጠየቅ ነው። ጥያቄውም የሚሆነው ‹‹ምን ያህል ደም ግፊት ያለበት፣ ስኳር በሽታ ያለበት፣ የልብና ተያያዥ በሽታ ያለበት፣ የኩላሊት በሽታ ያለበት፣ የአጥንት መሳሳት ችግር ያለበት፣ የኮሌስቴሮልና የትራይግላይሴራይድ ክምችት ያለበትና በአጠቃላይ ተላላፊ ያልሆኑና የካንሰር አይነቶችንም ጨምሮ የተጠቁ ሰዎች ምን ያህል ይሆናሉ?›› ብሎ መጠየቅ ነው። ‹‹አበዛኸው›› የሚል አንባቢ ቢኖር መልሴም ‹‹በጣም አሳንሸዋለሁ›› የሚል ይሆናል።

ከተዘረዘሩት በሽታዎች (ደዌዎች) ጀርባ ትርፍ የስብ ክምችት ተጠርጣሪ መነሻ ምክንያት መሆኑን የሥርዓተ ምግብን ሳይንስ ሀሁ የቆጠረ ሁሉ የማይስተው ጉዳይ ነው።

 

ክብደት ወለድ በሽታዎች የሚያጠቁት በአብዛኛው የዕድሜ ክልሉ ወደ አርባዎች የገቡ ሰዎችን ነው። እነዚህ ሰዎች ደግሞ በብዛት ቤተሰብ የመሰረቱና በሥራውም ዓለም ተሰማርተው ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ የሀገር ሀብት ናቸው። እነዚህን ሰዎች ማጣት ጉዳቱ ከቤተሰብ አልፎ ሀገርንም ይጨምራል። በሽታዎች በቀላሉ የማይድኑ በመሆናቸውም የቤተሰቡን አንጡራ ሀብት ብዙም ተስፋ በሌለው ህክምና ሙልጭ አድርገው ይወስዳሉ። ከዚያም ቤተሰብ ይበተናል። ይሄ ሌላው ውድመት ነው።

 

የዚህ አስከፊ ደዌ መከላከያው በአኗኗር ዘይቤ ላይ የባህርይ ለውጥ ማምጣት ነው። የባህርይ ለውጡ ደግሞ “ሳይቃጠል በቅጠል” የሚለውን የአባቶችንና የእናቶችን ፍሬያማ የሆነች ምሳሌያዊ አነጋገር ተግባር ላይ የምናውልበት ይሆናል።

 

የባህርይ ለውጡን ለማምጣት ጉዳዩን ከመነሻው ጠንቅቀን ማወቅ አለብን። ፈረንጆች ‹‹ችግሩን መገንዘብ የመፍትሄው ግማሽ አካል ነው›› እንዲሉ እኛም የበሽታውን መነሻ ማወቅ ግድ ይለናል።

 

መነሻ ይሆናሉ ተብለው በንደፈ ሀሳብ ደረጃ ከተቀመጡት ውስጥ የምግብ ዝግመተ ለውጥ፣ የአኗኗር ዘይቤ መቀየር፣ የሰውነት እንቅስቃሴ፣ ከቤተሰብ ውርስ፣ አካባቢ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለ የአመጋገብ ባህሪይ፣ የምግብ አቅርቦት፣ ቴክኖሎጂ፣ የሀሞት ከረጢት ህመምና የሆርሞን መዛባትን መጥቀስ ይቻላል:: በተመራማሪዎች ዘንድ ቁርጥ ያለ ምክንያት በውል አልታወቀም። ‹‹መነሻ ምክንያቱ ውስብስብ የሆነና የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው›› የሚሉም አሉ። ከላይ እንደተጠቆመው፣ መነሻውን በደንብ ማወቅ ለመፍትሔው አመላካች መንገድ ስለሚሆን ‹‹መነሻ ይሆናሉ›› የተባሉትን ምክንያቶች በደንብ ማየት አስፈላጊ ነው። ከዚያም ባለፈ ለእውቀትም ይጠቅም ዘንድ ተመራማሪዎች እስከአሁን ከተንደረደሩባቸው ሀሳቦች ዝግመተ ለውጥን ለዛሬ እናያለን።

 

ዝግመተ ለውጥ እንደ ውፍረት መነሻ

 

‹‹ሰቡ-ረቡ የሚሉንን ጉልበታቸውን ቄጠማ ዐይናቸውን ጨለማ አድርግልን›› የሚለው የአባቶች ምርቃት ነው። ዝግመተ ለውጥ ‹‹ሰቡ ረቡ›› ከሚለው ጽንሠ ሀሳብ ይነሳል። የሰባ በችግር ጊዜ ያጠራቀመውን ስብ በመጠቀም ችግርን በማለፍ ህልውናውን ማስቀጠል ሲችል ድንቡሽ ያላት ሴት ደግሞ በወንዶች ተመራጭ በመሆን ዘሯን ታስቀጥላለች (በአሁኑ ጊዜ የከሱት በቁንጅና እንደሚያሸንፉ አያውቁም እንዴ?) የሚል እሳቤ ያለው ይመስላል።

 

ወደ ዋናው ጉዳይ ስንገባ፤ በለውጥ ሂደት ውስጥ የሰው ልጅ ውጥንቅጥ የህይወት ጉዞ አድርጓል። በማደንና በመልቀም ኑሮውን በሚገፋበት ወቅት በጥጋብና በረሃብ ሀዲድ ላይ ዠዋዥዌ ተጫውቷል። ምግብ ሲገኝ በደንብ ይመገብ ነበር፤ ቁጠባ የሚባል ነገር አልነበረም። ተጠባባቂ ኃይል ማስቀመጥ የሚቻለው በሰውነት ውስጥ በስብ መልክ ብቻ ነበር። ስለዚህ ስብን የማጠራቀም ጸጋ የተሰጣቸው ችግሩን ሲያልፉት ያላጠራቀሙት ግን ህይወታቸው ያልፋል። በዝግመተ ለውጥ አጥኚዎች ‹‹ስብ የህልውና ማቆያ ተቀማጭ ሀብት ነው›› የሚሉት ከዚህ በመነሳት ነው።

 

‹‹ሰውነት በመጀመሪያ ያሳለፈውን ችግር በማስታወስ የማከማቸት አባዜ እንዲጠናወተው ሆነ›› የሚለውን ሀሳብ የሚደግፉ ሀሳቡን ሲያብራሩት፤ የሰው ልጅ በአዕምሮው ጎልብቶ ማምረትና ማርባት ሲጀምርና ከዚያም ለችግር ጊዜ በጎተራም ሆነ በበረት በማጠራቀምና መጠቀም ጀመረ፤ ሰውነቱ ግን ሊጠቀምበት የማይችለውን ስብ ማጠራቀሙን አላቋረጠም። ሰውም ጥሮ ግሮ ያገኘው የነበረን ሲሳይ ብዙ ሳይለፋ በቀላሉ ማግኘት ጀመረ። ሰውነትም ስብ ማጠራቀም ቀጠለ። ‹‹የተጠራቀመው ስብም የበሽታ መፈልፈያ ኢንኩቤተር ሆነ›› ይላሉ።

 

ንደፈ ሐሳቡ ለመስራቱ በድርቅ ወቅት በሀገራችን የሚፈጠረውን የእንስሳት እልቂትና የሚተርፉትን ብናስተውል ንድፈ ሃሳቡን የሚደግፍ ምልከታ እናገኝ ይሆን?

 

ይህንን ንድፈ ሀሳብ ለመፈተሽ ይመስላል ራቩሲን (Ravussin) እና ቦጋርደስ (Bogardus) የተባሉ ተመራማሪዎች በሁለት የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ቀያይ ህንዶች (Red Indians) ተብለው በሚታወቁት የአሜሪካና አካባቢዎች የሚኖሩ ነባር ሰዎች ላይ ጥናት ያደረጉት። ጥናቱ ታሳቢ ያደረገው ሰዎቹ አንድ አይነት ዝርያ ሲኖራቸው በአኗኗር ግን የተለያዩ መሆናቸውን ነው። አንደኛው ተጠኝ ቡድን በአሜሪካ አሪዞና በተባለው ግዛት ውስጥ ባለ ጥብቅ (reservation area) ቦታ የሚኖሩትን የሚይዝ ሲሆን ሁለተኛው ተጠኝ ቡድን ደግሞ በሜክሲኮ ሴራይማድሬ በተባለ ተራራማ አካባቢ የሚኖሩትን የያዘ ነው። የመጀመሪያዎቹ ብዙ ነገር የተመቻቸላቸው እና ዘመናዊ ኑሮ የሚኖሩ ሲሆን የኋለኞቹ ግን በጣም ኋላቀርና ጥንታዊ የአኗኗር ዘዴ የሚከተሉ (ለፍቶ አዳሪዎች) ነበሩ። የጥናቱ ውጤትም በጣም አስደናቂ የሆነ ልዩነት አሳየ። ሰማንያ እጅ ከመቶ የሚሆኑት የአሪዞና ነዋሪዎች ከመጠን በላይ በመወፈር በብዙ በሽታዎች (ዋናዎቹ ስኳር እና የኩላሊት በሽታዎች) ተጎድተው የተገኙ ሲሆን በሜክሲኮ አካባቢ የሚኖሩት ግን ከመቶው አስር እጅ ብቻ ውፍረት ሲገኝባቸው በበሽታ የተጠቁትም በጣም ጥቂቶቹ ነበሩ።

(ይቀጥላል)

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *