ተማም አባቡልጉ

በኦሮሚያ ክልል ሰሞኑን በተደረገው ሕዝባዊ የመብት ጥያቄ ከ190 በላይ ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል። ለዚህም (1) የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ (2) የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታሞዦር ሹም ሳሞራ የኑስ፤ (3) የሀገሪቷ ደህንነት ሹም (ዋና አዛዥ)፤ (4) የፌዴራል ፖሊስ ዋና አዛዥ፤ እና (5) ኢህአዴግ ኃላፊነቱን ይወስዳሉ። ስለሆነም እነዚህ ስለሆነው ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተከሰው በዓለም አቀፍ ደረጃ ወይም በሌላ ሁኔታ ላለ (ለሚቋቋም) ገለልተኛ ውሳኔ ሰጪ የፍርድ አካል ፊት ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል። ይህንን ዕውን ማድረግ ደግሞ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ ይሆናል። ይህ የሚሆነው ለኦሮሞ ሕዝብ ተብሎ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተብሎ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ እና በኢትዮጵያ ስም ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ አባይ ፀሐይንና የመከላከያ ሚኒስትሩን ያለፍናቸው፣ በኢህአዴግነት ይጠየቁ ወይም ሌሎቹ እነሱም ይከሰሱልን ይበሉ በሚል ብቻ ሳይሆን፣ በሌላ ምክንያት ነው። በተለይ አቶ አባይ የለሁበትም ያሉትን አስመልክቶ ያሉበት ለመሆኑና አሉት የተባለውን በርግጥም ያሉት መሆኑን ለማስረዳት ከሎጂክ ወዘተ. አንፃር 500 ገፅ ያለው መፅሐፍ ልንፅፍበት እንችላለን። ለሁሉም ግን የህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ በጦር ኃይል መላውን ኢትዮጵያ ከተቆጣጠረበት ጊዜ 1983 ዓ.ም ጀምሮ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልፅ ያሉትን አላልንም በማለት በአደባባይ ለመካድ የተገደዱበት የሰሞኑ የኦሮሞ ኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ ሲሆን፤ በዚህች የሕወሓት የታክቲክ ለውጥ ሊሸወድ የሚችል ኢትዮጵያዊ ባይኖርም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገሪቷን ደም መጣጮች አስቦክቶ የሚያውቀው ዛሬ ብቻ አልነበረም፤ ዛሬም ብቻ አይሆንም፤ ሊሆንም አይገባም እላለሁ። የአቶ አባይ ሁኔታ ይህንን አሳይቶናል።
ሕወሃትን መናገር ፀረ-ትግሬነት ነው ማለት፣ ትግሬ ኢትዮጵያዊ አይደለም ለማለት ካልሆነ በቀር ስለራሳችን አንድ አካል መናገር ስለሆነ ማንም ሊከለክለን አይችልም። እኔ ስለትግሬ መናገር ስለራሴ መናገር እንደሆነ አድርጌ ስለምወስድ ለዚያ የማንንም ፍቃድ አልጠይቅም። ዘረኛ እባላለሁ ብዬም አልፈራም። ነገር ግን ስለሕዝብ በደፈናውና በአጠቃላይ መናገር በራሱ አስቸጋሪና እርግጠኛ የሚሆኑበት ሊሆን ስለማይችል፣ ቢቻል ከዚያ መቆጠብ ያስፈልጋል። ሕወሓት (መሪዎቹ) በግላቸው ለሠሩት ወንጀል ሕዝብን መሸሸጊያ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸው ሊወገዝ ይገባል። ሕዝብን (ሌላውን) ጓንት አድርገው እሳት መያዝ የለመዱ አካላት ለራሳቸው እንጂ ለማንም ግድ የላቸውም። በማነካካት ፖሊሲያቸውም መሠረት በየመንደሩ ያሉትን እናቶች ሳይቀር አባል በማድረግ ስም ለእነሱ ዘረፋ መያዣነት ሊጠቀሙባቸው መፈለጋቸው ራሱን የቻለ ወንጀል መሆኑንም ሊረዱት ይገባል። የስድስት ሚሊዮን አባላት ባለቤትነትም (መንስኤና ውጤቱ) ፖለቲካ ሳይሆን ወንጀል እንደ ሆነ ወደ ፊት እመለስበታለሁ። ወንጀል የተፈፀመባቸው እነዚህ ወገኖቻችንም ጭምር ናቸው። እንደ ፀረ-ሴማዊነት (anti-semitism) ስለትግሬ መናገርን ወንጀል (ነውር) በማድረግ የፈለጉትን ወንጀል በፈለጉበት ጊዜና ቦታ በፈለጉት ሰው ላይ ፈፅሞ መሸሸጊያ እናደርገዋለን ማለትና ያንን በመፈለግ ግን አያዋጣም። የአማራ ሕዝብ በገዢ መደብ ስም ሲሰደብና ሲዋረድ በቡድን የሚጠፋ ስም ስለሌለና ዝም የተባለው ሁኔታው ወንጀል ስላልሆነም ነው። እነ ኤሊያስ ገብሩ የቡድን (የኦሮሞ) ስም አጥፍታችኋል በሚል ተከሰዋል። አማራን መስደብ ፀያፍና ነውር መሆኑን አስመልክቶ ይህ ፀሐፊ በሎሚ መፅሔት ላይ ለአንድ አማራ ነኝ ለሚሉ የክልሉ የኢህአዴግ ባለስልጣን መልስ ሰጥቷል።
ሕወሃት እራሱንና አባላቱን እንጂ የትግራይ ሕዝብን አይወክልም፤ ማንም ትግሬም ራሱን እንጂ የትግራይ ሕዝብን አይወክልም፤ አባይ ፀሐይ ትግሬ ስለሆነ ወንጀል ቢሠራብኝ ወይም አሁን እያደረገ ያለው ውሸት መናገር ስለሆነ ውሸታም ነው ብለው የትግራይ ሕዝብን ውሸታም ማለቴ የሚሆነው በየትኛው ሕግ ወይም ሎጂክ ወይም ቲዮሪ ነው? Impunity ፍለጋ ነው።
ሕወሓት በኢህአዴግ ጓንትነት መላ ኢትዮጵያን መያዙን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያውቀዋል። ይህንን መካድ ግመል ሰርቆ እየሄዱ ላለመታየት እንደ ማጎንበስ ነው። ሰሞኑን በኦሮሚያ ለተፈፀመውም ሆነ እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈፀሙት ሁሉ በሕግ ብቸኛው ባይሆንም ዋናው ተጠያቂ ሕወሃት ነው። ኢህአዴግን የመሠረተው ሕወሃት ነው። አባል ድርጅቶችን ያቋቋማቸውም እሱ ነው። አገሮችን ያቋቋመው ራሱ ነው። ይህንን ሁኔታ አንድ ፀሐፊ “ሕወሃት እ.ኤ.አ በ1991 ዓ.ም ሥልጣን እንደ ያዘ ዴዶችን (pdo’s) በመላ ሀገሪቷ በማቋቋምና እንደ አሸን እንዲራቡ በማድረግ ሥራ ተጠመደ” በማለት ገልፆታል። እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም በሀገሪቷ ከነበሩት 79 ድርጅቶች ውስጥ 70ዎቹ ዴዶችና እሱ ያቋቋማቸው ነበሩ። ዘጠኙም ሕብረ-ብሔራዊ ድርጅቶችም በእሱ ተፅዕኖ ሥር እንዲገቡ ለማድረግ ያደረገው እንቅስቃሴ መኢአድንና አንድነትን ከፍሎ በማፍረስ ተጠናቋል።
እነዚህ ሁሉ ማስረጃ ያላቸው ሊረጋገጡ የሚችሉና የሚረጋገጡባቸው ዘዴዎች (መሣሪያዎችም) የሚታወቁ እውነታዎች (factual የሆኑ) ናቸው። ኦህዴድ ባይኖር ኢሕአዴግ ላይፈርስ ይችላል። ያለ ሕወሃት ግን ሊኖርና ሊቀጥል አይችልም። ለምን? ሴኮ ቱሬ ትግርኛ መናገር ይችላል። ከሕወሃት አባልነቱ ተባሯል። ብአዴን ሆኗል። ለምን? ህወሃት ዘረኛ ድርጅት ስለሆነ አይደለምን? ይህንን ማለት እውነት መናገር (ዘረኛን ዘረኛ ማለት እውነት መናገር ነው) እንጂ ዘረኝነት አይደለም። ወደ ሕወሃት ለመግባት ዘር (የብሔር ምንነት) እንጂ ቋንቋ ብቻውን በቂ አይደለም። ኦሕዴድ ብአዴን ዴህዴን ወይም የሌላ አገር ድርጅት አባል ለመሆን ግን ቋንቋውን መቻል ብቻ በቂ ስለሆነ አባልነቱን ለመከልከል ዘርን መሠረት ያደረገ ካለ ጠባብ ይባላል። ይገመግማል። ሴኮ ቱሬ ከሕወሃት የተባረረው በዘረኝነት መሆን/ያለመሆኑ ለምን ግምገማ አልተደረገበትም? ኢህአዴግም አንድ ወጥ (አንድ) ፓርቲ የማይደረገውም የሕወሃትን የበላይነትና ድሎቹን ለማስጠበቅ ተብሎ ነው። ይህም እውነት ነው።
ሕወሃት ስለ እኔ አትናገሩ ማለት አይችልም። ያንን ለማለት የሚችለው በግልፅ ኢትዮጵያዊ ድርጅት አይደለሁም ካለ ብቻ ነው። እሱን ዘረኛ ነው ማለት ከሱ አልፎ ማንንም መውቀስ ሊሆን አይችልም። በነገራችን ላይ ማንንም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ አትችልም ወይም ብሔርህ ይለያል በሚል የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆን መከልከል የተሻሻለውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 አንቀፅ 2(2)ንና ሌሎችን መጣስ ነው። ለአባልነት የሐሳብ (የእምነት) አንድነት እንጂ ዘርና ቋንቋ ቅድመ-ሁኔታዎች አይደሉምና።
ለአንድ ፓርቲ አባልነት ከኢትዮጵያዊነትና ከሐሳብ (አስተሳሰብ) መመሳሰል ውጭ ሌላ ቅድመ-ሁኔታ ማስቀመጥ ሕገ-ወጥ ነው ማለት ነው። ኢሕአዴግ የሁሉም አባላቱ የእኩል ቤት ቢሆን ኖሮ ሀገሪቷም የሁሉም ዜጎች የእኩል ሀገር በሆነች ነበር። ስለሴኮ ቱሬ መባረር፣ ወይም በኢህአዴግ ውስጥ ስለሕወሃት የበላይነት መጠየቅ መብት እንጂ ዘረኝነት አይደለም። ስለዚህ አትጠይቁ (ስለሁኔታው አትናገሩ) ማለት ነው። ዘረኝነት አሁን ባለው ሁኔታ ኢሕአዴግ ራሱ ለፈጠራቸው ዘርፈብዙ ችግሮች መፍትሔ ለማምጣት ከፈለገ መፍረስ አለበት።
በሕግ ኦህዴድ ብአዴን ደህዴን እና ሕወሃት እንደ ቅደም ተከተላቸው ስማቸውን የወሰዱትን (የያዙትን) ሕዝብ ማለትም ኦሮሞን፣ አማራን፣ ደቡብና ትግሬን አይወክሉም። የሚወክሉት ራሳቸውንና አባላቶቻቸውን ብቻ ነው። ይህ ሕግ ነው። ፓርቲ (ድርጅት) ሕጋዊ ሰውነት ያለው ሕጋዊ ሰው ነው። አባላቶቹ በመተዳደሪያ ደንባቸውና በመመስረቻ ፅሑፋቸው ላይ የጠቀሷቸውን ዓላማዎች ለማስፈፀም ዓላማ መብትና ግዴታ (ሕጋዊ ሰውነት) በሕግ የተሰጣቸው ከአባላቶቹም ሰውነት የተለየ የራሳቸው ሰውነት ያላቸው ተደርገው የሚወሰዱ (የሚቆጠሩ) ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎች እንኳ ከስማቸው (ከስያሜያቸው) መነሻ ላይ የሰደሩትን ሕዝብ መወከል (መሆን) ይቅርና ከአባላቶቹም ማንነት የተለዩ የሆኑና በዓላማቸው የሚወከሉ (ዓላማቸውን የሚወክሉ) ብቻ የሆኑ ናቸው ማለት ነው። ስለሆነም ስለአንድ ፓርቲ መናገር በዚያ ፓርቲ ውስጥ አባል የሆነን ማንንም ሰው በተለይ መናገር አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም ማለት ነው።
ፓርቲን ማውገዝ መውቀስ ወዘተ. ማለት ዓላማውን ማውገዝ መውቀስ ወዘተ. ብቻ ነው ሊሆንና ተደርጎ መወሰድ የሚችለው ማለት ነው። ሕወሃትን ማውገዝ እና አልቀበልም ማለት በድርጅቱ መሪዎች ንግግርና ድርጊቶቹ የሚገለፅን (የተገለፀን) የድርጅቱን ዓላማዎች ማውገዝና አልቀበልም ማለትን ብቻ ያመለክታል። በድርጅቱ ውስጥ የሚበዙትን ሰዎች ብሔረሰብ ሕዝብ ይቅርና የቱንም አባል በተለይ የሚመለከት አይደለም፣ አይሆንም፣ ሊሆንም አይችልም። ይህ እውነት የሚሆነው ሁሌም ነው። በአገዛዝ ሥር አምባገነኖች መሪዎቹ ፓርቲው ወይም ድርጅቱን ሆነው ተቀባይነት የሚኖራቸው መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ድርጅቱ ሲባል ፈላጭ ቆራጭ ሰውየው (መሪው) የማለት እንደምታ እንዲሰጥ ተደርጎ እሱን ማለትን ቢያክልም ያ መሆኑ በሕግ ያለውን ሁኔታ አይለውጥም። ድርጅት (ፓርቲ) ራሱን እንጂ በተለይ ማንንም አይደለም። ይህንን ያለመቀበል እውነትን (ሕግን) መካድ (መጣስ) ሲሆን የአምባገነኖችም ሕልውና የሚቀጥለው በዚህ ክህደት ውስጥ ብቻ ነው። የፓርቲ (የድርጅት) መሪዎች ድርጅቱን መወከል ቢችሉም፤ ይህ መሆኑ የትኛውም የንግድ ድርጅት በሥራ አስኪያጁ ወይም በሌላ ሰው እንደሚወከለውና ሥራውን እንደሚሠራውና ያ ማለት ግን ድርጅቱ ሥራ አስኪያጁን ነው ማለት እንዳልሆነ ሁሉ ፓርቲው እሱን የወከለውና የቀን ተቀን ሥራውን የሚሰራው (የሚመራው) ግለሰብ (ግለሰቦች) ነው (ናቸው) ማለትን አይሆንም (አያስከትልም።)
ሕወሃትን አባይ ፀሐይን መናገር አንድና ተመሳሳይ ነገሮች አይደሉም። ሕወሃትን ወይም አባይ ፀሐይን መናገርና ስለትግራይ ሕዝብ መናገርም አንድና ተመሣሣይ ሁኔታዎች (ድርጊቶች) አይደሉም። አቶ አባይ በራሱ ችሎታ ወይም የፓርቲውን ወይም ሌላ ሥልጣኑን መከታ በማድረግ ለፈፀመው ወንጀል በግሉ ተጠያቂ ይሆናል፣ ለወንጀል ሥራ ዓላማ ፓርቲ (ድርጅት) ከመሠረተ ወይም የተመሠረተውን ድርጅት ለሕገ-ወጥ ሥራ ጥቅም ከዋለው ፓርቲውን (ድርጅቱን) ለሕገ-ወጥ ሥራ የተቋቋመ (በሕገ-ወጥ ሥራ ላይ ተሠማርቶ የተገኘ) ሕገ-ወጥ ድርጅት እንዲሆን በማድረግ እንዲፈርስ ወይም ሌላ ቅጣት እንዲያገኘው ሊያደርገው ከመቻሉም በተጨማሪ ግለሰቡንም ለወንጀል ድርጊቱ ተጠያቂ ያደርገዋል። እዚህ ውስጥ የቱም ሕዝብ የሚገባበት መንገድ የለም።
ደርግን ማሸነፍ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማሸነፍ አይደለም። በዳግማዊ ምኒልክ ዘመቻ ወቅት በ6 ዓመታት ጦርነት የተሸነፈውን ከኦሮሞ ሕዝብ አንድ በመቶ የሆነን አካባቢ ያለን ሕዝብ የሚወክለውን አባዱላን ማሸነፍ የኦሮሞን ሕዝብ ቀርቶ የአርሲን ኦሮሞ እንኳ ማሸነፍ አይደለም፣ ሊሆንም አይችልም። የተወሰኑ አካላት የፈለገውን ያህል ቢደራጁ እንኳ ሕዝብን ማሸነፍ አይችሉም፤ የሆነን ቡድን (ለምሳሌ ደርግን) ማሸነፍን (የኢትዮጵያ) ሕዝብን እንደ ማሸነፍ አድርገው የሸጡልንን ርካሽ ፕሮፓጋንዳ የገዛናቸው የተወሰነ ሕዝብን ስም ይዘው መገኘታቸውን ያንን ሕዝብ ናቸው ለማለት እንደበቂና አስፈላጊ አድርገን ከመቀበላችን የተነሳ ነው። የሚሉትን ሳይሆን የሚያደርጉትን ባለማየታችን ነው። የራሳችንን የተሳሳተ ድምዳሜ ባለማረማችን ነው መፍትሔ ያጣነውና የማናመጣው። በርግጥ በየትኛውም ሕዝብ ስም በማንም ላይ ሕገ-ወጥ ድርጊት ሲፈፀም ያንን ድርጊት አስቀድሞ መቃወም ማውገዝና መቆጣት ያለበት ያ በስሙ ድርጊቱ የሚፈፀመው የሕብረተሰብ ክፍል አባላት ሊሆኑ ይገባል። ምክንያቱም በሕግ ባይሆንም ያ ሁኔታ በሌላው ሕዝብ አዕምሮ ውስጥ ያ የሕብረተሰብ ክፍል የተባለውን ጥቃት የፈፀመበት አድርጎ እንዲቆጥር ሊያደርገው ስለሚችልና በአንድ ሀገር ውስጥ የሚፈፀምን የቱንም ግፍ መቃወም ያለዘርና ሃይማኖት ልዩነት በሁሉም ዜጋ ላይ የተጣለ ግዴታ በመሆኑ ያንን መወጣት የጥሩ ዜጋ ምልክት ስለሆነ ነው። ከሚኒልክ ድርጊት ውስጥ የሚወገዝ ካለ መወገዝ አለበት። ያንን ማድረግ (ማውገዝ) ዘረኝነት አይደለም። ያንን መከላከል ዘረኝነት ነው፤ ጭቆናም ይሆናል።
በየትኛውም መለኪያ ተቀባይነት የሌለውን ድርጊት መደገፍ ደጋፊው ሰው ያንን ድርጊት መቀበሉን ያሳያል። ከዚህ ብቻ ተነስቶ ሰውየው እንጂ እሱ በወል ስም ከነሱ የሚጋራውን የሚጠራባቸው ሰሞች (ዘር) ሁሉ የተባለውን ድርጊት ይደግፋሉ ማለትም (ሰውዬው ሁሉንም የዘሩን አባላት ይወክላል ማለት ነውና) ተመሣሣይ ስህተት ነው። እኔ ስለምኒልክ ለመናገር የማንም ፍቃድ አያስፈልገኝም። ስለዛ መናገር የራሴ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ባለፈ ጉዳይ ላይ መነታረክ በተለይ ጅልነት ነው ብዬ ስለማምን ያንን አልፈፅምም። ካለፈው ተምረን ለወደፊቱ የተሻለን ሁኔታ ለመፍጠር መስራት ግን ብልህነት ነው። ስለየቱም ነገር ማንም የፈፀመው ድርጊት (በተለይ የሀገር መሪዎች ሥራ) የሁላችንም ጉዳይ ስለሆነ ማናችንም ከማናችንም መጠበቅ ያለብን (የሚገባን) ሊሆን አይገባም። የምኒልክ ድርጊት የሚመለከተው ራሳቸውን ስለሆነ ለዚያ ዛሬ ላይ ማንም ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። ያንን የፈፀሙት ሰዎች ዛሬ የሉምና። የሕወሃት ድርጊትም በተመሣሣይ መልኩ ራሱንና መሪዎቹን ብቻ ይመለከታል። ተጠያቂነትም ከመጣና ካለ የሚመለከተው ድርጅቱንና መሪዎቹን ወይም ድርጊቱን የራሱ ያደረገን አካል (ሰው) ብቻ ይሆናል።
ሕወሃት የትግራይ ሕዝብ ነው፣ ምኒልክም የአማራ ሕዝብ ናቸው። እነሱን ይወክላሉ የሚሉትን ድምዳሜዎች ሁላችንም በተለይ ደግሞ ከትግራይና ከአማራ ብሔር የወጡ ሰዎች ልናወግዘው (ሊያወግዙት) ይገባል። ይህንን መሠረታዊ ስህተት ያለበትን ድምዳሜ (assumption) መቀበል እና በሱ ላይ ተመስርቶ ማሰብና መሥራት አሁን ላለንበት ሁኔታ አብቅቶናል። በሌለና በማይመለከተን ጉዳይ (ያለና የሚመለከተንን ጉዳይና ለጋራ ችግራችን መፍትሄ በጋራ መፈለግ ትተን) ወገን ለይተን እንድነዋጋ (እንድንጣላ) እያደረጉን ያሉት እነዚህ ድምዳሜዎች ናቸውና እነዚህን ማረም ለነገ የማይባል ይሆናል። እኔ ኦሮሞ በመሆኔ ስለምኒልክ ወይም ስለሕወሃት መናገር የማይገባኝ የሚመስላቸው ሰዎች ወይም አማራ ወይም ትግሬ ስለሆኑ የቱንም የምኒልክ ወይም የሕወሃት ድርጊት መከላከል ያለባቸው አድርገው የተቀበሉና ያንን የሚያንፀባርቁ ሰዎች ዘረኞች ናቸው። የአንድ ሀገርነትን ትርጉም ያልተረዱ ፀረ-ኢትዮጵያ አንድነት የሆኑ ናቸው። ስለምኒልክ አትናገሩ ማለት፣ ስለሕወሃት አትናገሩ የማለት (የአንድ ሳንቲም) ሌላኛው ገጽታ (ሌላኛው ግልባጭ) ነው። ምኒልክ፣ ኃይለሥላሴ፣ መንግሥቱ፣ ኃይለማርያም፣ መለስ ዜናዊ ወይም ሕወሓት ያደረጉትን፣ ያደረጉትና እያደረጉ ያሉት በሁላችንም ላይ እስከሆነ ድረስ (ያንን ያደረጉትና እያደረጉ ያሉት የተወሰነን አካል መሣሪያ እያደረጉ ቢሆንም፣ ማንም ገዢ የተወሰነን አካል ለይቶ መሣሪያ ካላደረገ ፈላጭ ቆራጭነቱን ማስቀጠል አይችልምና በዚህ ላይ ምንም ለውጥ ስለሌለው) ያለምንም የዘር የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የፆታ አመለካከት ወዘተ. ልዩነት የትኛውም ኢትዮጵያዊ ስለነዚህ የመሠለውን አስተያየት መስጠት እምነት መያዝና የማንፀባረቅ መብት ይኖረዋል። ይህንን ያለመቀበል ዘረኝነት የሚሆነው ዘርን መሠረት ባደረገ የጅምላ ድጋፍ መልክ ከሆነ ሲሆን ካልሆነም ደግሞ የሌላውን ዜጋ ስለሆነ ታሪካዊ ሁኔታና የራሱም በሆነ ሀገር ላይ ስለሆነ ክስተት የመሠለውን አመለካከት ይዞ የመግለፅን መብት መጋፋት ብቻ ሳይሆን በሀገርህ ጉዳይ ላይ እኔ ካንተ እበልጣለሁና አውቅሃለሁ ማለትም ስለሚሆን ፀረ-እኩልነት (ዜግነት) የሆነ አድሃሪ አስተሳሰብ ይሆናል። ማንም ኢትዮጵያዊ ከላይ በስም የተጠቀሱትን ገዢዎቹን ድርጊት በሚመለከት የመሰለውን አድማ መያዝና ማንፀባረቅ ቢችልም፣ የሌላውን ዜጋ ተመሳሳይ መብት በመጋፋት መልክ ግን መሆን የለበትም።
እነዚህ ገዢዎች የአማራን፣ የትግሬን ወይም የኦሮሞን ሕዝብ ናቸው ማለት ግን ማንም (በመደገፍና በመቃወም ስም) አይቻለውም። ምክንያቱም ይህንን ማለት ሕገ-ወጥ ስለሆነ ነው። ይህ ሁኔታ የሚገለፀው ምኒልክን መንካት አማራን መንካት ወይም ሕወሃትን መንካት ትግሬን መንካት አድርጎ በመደገፍም ሆነ በመቃወም መልክ በማቅረብ ነው። አባይ ፀሐይ ያደረጉት ይህንን ነው። ምኒልክ ማለት አማራ፣ ሕወሃት ማለት ትግሬ ማለት ናቸው ማለት ውሸትና ሕገ-ወጥ የሆነ ድምዳሜ ሲሆን፣ ፀረ-አማራነት፣ ፀረ-ትግሬነት፣ ፀረ-ሕዝብነትም ናቸው። ማንም ሰው ምኒልክን ወይም ሕወሃትን አትንካብኝ ይህንን ማድረግህ አማራ ወይም ትግሬን መንካት ነውና በዚህም እኔን እየነካህ ነው ቢለኝ፤ ይህንን ዘረኛ፣ ውሸታም፣ ሕገ-ወጥ፣ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ሀገርና ሕዝብ አንድነት የሆነን ግለሰብ (እምነት) በሆነው ስም በመጥራትና ያንን በመንገር ካልተቃወምኩትና ተቀብዬ ካንፀባረቅሁኝ (በማስተባበል ወይም በመደገፍ መልክ) እኔም እሱ የሆነውን እሆናለሁ።
ይህ የተባለው (የቀረበው) ስለነዚህ ምን ያገባሃል በሚል ከሌላ ወገን ነኝ ባይ አካል በተሰነዘረ አስተያየት መልክ ቢሆንም ልዩነት አያመጣም። ስለነዚህ ገዢዎች ሲነገር ሳናጠራ ቱግ የምንል ከሆነ ወይም ማንም ስለነዚህ የመሰለውን እምነት ይዞ መግለፁ ስህተት ከመሠለን ዘረኞች ነን። እነዚህ ገዢዎች በተለያየ ደረጃ የተወሰነን የሕዝብ ክፍል ጉርሻ እየሰጡና በሌላው ላይ በቁስና በስነ-ልቦና የበላይነት እንዲሰማው በማድረግ ሌላውን በመሣሪያነት ለመግዛት ቢጠቀሙበትም ያንን ሕዝብ ናቸው ማለት ግን ስህተትና ሕገ-ወጥነት ነው። በተለይም የዚያ ብሔር አባላት የሆኑ ምሁራን ገዢዎችን ከብሔራቸው ጋር አንድ አድርጎ ለሚያቀርብ ሁኔታ ትዕግስት ሊኖራቸው አይገባም። ምክንያቱም የተባለው ነገር በርግጥም በተባለው ብሔር ላይ የሕግ ተጠያቂነትን ማምጣት ባይችልም ውሸትና ሕገ-ወጥ ስለሆነ ብቻም ሳይሆን ይህ አመለካከት እውነት ተደርጎ በሌላው (በሁሉም) የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት ካገኘ ሕዝብን ጎራ ለይቶ እንዲፋጅ የማድረግ አቅም ስላለው ሁሉንም ህዝብ በተለይም ከገዢው ጋር የተፈረጀውን ሕዝብ ዛሬ በመሣሪያነት ነገ ደግሞ በተጠቂነት ሠለባ ሊያደርገው ስለሚችል ነው።
ቲዎሪ በሠፊው ሕዝብ ውስጥ ሲሰርፅ ቁስ አካል ይሆናል ማለት ይህንን ማለት ነው። ሕወሃት የትግራይ ሕዝብ ነው ማለት ፀረ-ትግራይ ሕዝብነት ነው። ሕወሃትን (ባለስልጣናቱን) መናገር የትግሬ ጥላቻ ነው ማለት ፀረ-ትግራይ ሕዝብነት ነው። ሕወሃት የኦሮሞን ሕዝብ ከነካ (ከጎዳ) ትግሬን ጨምሮ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደጎዳ ይቆጠራል። ይህንን መቃወም የሁሉም ግዴታ ነው። ያለመቃወም ፀረ-ሀገርነት ነው። ፀረ-ትግሬ፣ ፀረ-አማራ፣ ፀረ-ኦሮሞ (ፀረ-የቱም 85ቱ የኢትዮጵያ ዘር) የሆነ ሁሉ ፀረ-ሁላችንም (ፀረ-ኢትዮጵያ) ነው። ለኦሮሞ ሕዝብ መብት መቆም ለትግሬም ሕዝብ መብት መቆም ነው። ኦሮሞን መንካት ሁሉንም የኢትዮጵያ ዘር መንካት ማለት ነው። በሀገር (መብትና ነፃነት) ደረጃ ኦሮሞም ትግሬ ነው።

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *