tewodros tsega
ቴዎድሮስ ጸጋ

ሀገራችን ከገባችበት ውርደትና ዝቅጠት ነጻ መውጫ ሰዓቷ ደርሷል። ለእኔ፣ ሊነጋ ሲል አይጨልምም፤ ዐይኔ ከቶም ጥቁሩን ድቅድቅ ጭልማ ለማየት አይፈቅድም። ይልቅስ፣ ዐይኖቼ ከዋሻው ጫፍ ያለው ብርሃን ነው የሚታያቸው። ሊነጋ ሲል ያቅላላል ወጋገኑ፤ ወገግ ብሎ ይታያል። ይህንን የምለው የሰነፍ ግብዝነት ይዞኝ አይደለም። የዘመን አቻዎቼን ሩቅ ሕልም፣ በግፍ በየወህኒው የተጣሉ እውነት ናፋቂ ብርቱ ድምፆች፣ የሀገሬ አርሶ አደሮች፣ ሰላማዊ እምቢተኝነት… ነው ተስፋዬን ከፍ ያደረገው።
የዘመን አቻዎቼን ለሀገራቸው ያላቸውን ሩቅ ሕልም፣ ተስፋ እና ምኞት በደንብ የታዘብኩት፤ ብርቱው ኦቦ በቀለ ገርባ እና የትግል አጋሮቹ የመድረክ አመራሮች፣ እንዲሁም የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው፣ ለሦስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት ቀን ላይ ነበር። ምንም እንኳ የተከሳሾቹ ጉዳይ በዝግ ችሎት እንደሚካሄድ አስቀድሜ ባውቅም፤ ለተከሳሾች ሞራል ሊሆን ከቻለ በሚል ከሰዓት የሚካሄደውን ችሎት ከውጭ ሆኜ ለመታደም በጠዋት ነበር ከቤቴ የወጣሁት።
ሰዓቱ እስኪደርስም የግል ጉዳዮቼን ሳከናውን ዋልኩ። መድረሱ ያልቀረው ሰዓት ደርሶ ወደዚያው በማምራት ላይ ሳለሁ፣ ተያይዘን ወደ ፍርድ ቤቱ እንድንሄድ ጠዋት ላይ የደወልኩላት የዞን ዘጠኝ አባልና እስር ያልበገራት ጀግናዋ ማሕሌት ፋንታሁን ደወለችልኝ።ከሆነው ካፌም ተቀጣጥረን፤ የሁለታችንም ወዳጅ ከሆነው አስማማው ኀይሉ ጋራም ተገናኘን።
ሦስታችንም የቀረበልንን ቡና ፉት እያልን፤ ወደ ፊት እና ወደ ኋላ እየተመላለስን፤ ብዙ ነገሮች አንሥተን እየጣልን እያወጋን ወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮች ጎራ አልን። የወጋችን ዋና ፍሬ ሐሳብ ያጠነጠነው በኦሮሚያ ክልል እየተቀጣጠለ ያለውና ዓለም አቀፍ ፖለቲከኞችን፣ የሚዲያ አካላትንና፣ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችን መሳብ የቻለው ሕዝባዊ አመፅ ላይ ነበር። ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ ሌላውን ክልል ቢያዳርስ ጥቅም እና ጉዳቱ ምንድነው? የሚለውም አጨቃጫቂና አከራካሪ ሐሳብ የሚጠቀስ ነው።
በእርግጥ በዚያች ጥቂት ደቂቃ ሁላችንም ለሀገራችንና ለሕዝባችን ያለንን በጎ ሐሳብ እንደ አቅምቲ አስቀምጠናል። ቢሆንም ግን ‹‹አብዮቱ›› እንዳይጠለፍ ያሰጋኛል የሚለው በማስረጃ የተደገፈው የአስማማው ሐሳብ አሸንፎ ወጣ። አስማማው ሐሳቡን ሲያቀርብ፣ምክንያታዊ መፍትሔዎችን ሲደረድር ለተመለከተው፤ ከጥቂት ወራት በፊት ከእስር የተፈታ አይመስልም፤ ረዘም ያለ ጥናት እና ምርምር ውስጥ የቆየ ጉምቱ ሰው ይመስላል።
አብዮቱ እንዳይጠለፍ ምሁራን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ማድረግ አለባቸው? ለተደጋጋሚ ጊዜ ኢሕአዴግን የሥልጣኑ ጉዳይ እንጂ የሀገርና የሕዝብ ጉዳይ ከቶውን እንደማያስጨንቀው፤ ሥልጣኑ ካልተነካ በስተቀረ ብሔራዊ ጥቅም፣ የዜጋ ደኅንነት፣ የሀገር ሕልውና …ጉዳዮች ግድ እንደማይሉት በተግባር ጭምር አይተናል። ሌላው ቢቀር አሁን እንኳ ከአራቱም አቅጣጫ የሀገሪቱ ሕዝቦች በከፋ ረሃብ ሲሰቃዩ፣ የወያኔዎች ጭንቀት እንዴት የሥልጣናችንን ዕድሜ ልናስረዝም እንችላለን? የሚለው መፍትሔ የማያገኙለት ራስ-ወዳድነት የተናወተው ሐሳብ ነዉ።
ጭውውታችንን ሳንቋጭ ወደ ፍርድ ቤቱ ግቢ አመራን፤ በግቢው የሚከወኑትን ድርጊቶች መከታተል ጀመርኩ፤ አንድ ትዕይንትም ትኩረቴን ሳበው፤ ኢንጅነር ይልቃል፣ ከኦቦ ቡልቻ ደመቅሳና ከሌሎች ሰዎች ጋራ ተቃቅፎ ፎቶ ይነሣል። ያለምንም ማጋነን ይልቃልና ቡልቻ አብረው ሲታዩ ግርማ ሞገሳቸው ከሩቁ ጎልቶ ይወጣል። በእርግጥ ሁለቱን ፖለቲከኞች የዚያን ሰዓት ትኩር ብሎ ላያቸው፤ የማያቋርጥና የሚያብብ ሀገራዊ ተስፋ በጉልህ ፊደላት ተጽፎ ያነባል። ይልቃል ወጣት ነው፤ ያውም ተስፋ የተደረገበት። ኦቦ ቡልቻ ደግሞ በሥስት ዐሥርት ውስጥ ያለፉና በከፍተኛ የመንግሥት ኀላፊነት አገራቸውን ያገለገሉ ናቸው። የዚያን እለት የነበራቸው ግንኙነት መከባበር፣ ቅንነትና፣ ትህትና የተሞላበት ነበር።
አምናለሁ፤ እነኚህ ፖለቲከኞች አልያም እነርሱን አርአያ የሚያደርጉ ወጣቶች ልክ እንደዛው ቀን አብሮ ፎቶ ከመነሣት አንድ እርምጃ ከፍ ብሎ አብሮነታቸው መተቃቀፋቸው ለአንድ ዓላማ ሀገርን ሊጠቅም እንደሚችል። ተስፋም አለኝ፤ ይልቃል እና መድረኮች በቅርቡ ተቀራርበው እንደሚሠሩ።
በእርግጥ ያለንበት ጊዜ ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሳዛኝ ጋሬጣዎች ከፊታችን የተደቀኑበት ነው። ዕለት ዕለት የማያቋርጠው የንጹሐን እስር፣ መንግሥታዊ ሕግ-አልባ ጭፍጨፋ፣ ረሃብ፣ እልቂት፣ ስደት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የግፈኞች ዐይን ያወጣ ዝርፊያ እና ስርቆት፤ ለእኛ እንዳይታየን የሕዝብን ሚዲያ በመጠቀም አምባገነኑ መንግሥት እና ደጋዎፊቹ በምንግዴነት ቢጠቀሙበትም፤ ተስፋ አደርጋለሁ!
በእርግጥ ከአምባገነን መንግሥታት የወል ባሕርይ አፋኝ ሥርዓትን አስፍኖ፤ ዜጎችን እያስጨነቁ ከመግዛት ጎን ለጎን አንዱ ሚዲያውን አፍኖ መያዝና የራስን በሬ ወለደ ፕሮፓጋንዳ በባዶ ሜዳ መልሶ በራስ ታማኝ ሰው መንዛት ነው። በሕክምናው የሙያ ዘርፍ ledocian የሚባል መደኃኒት አለ። የአንድ ታካሚ ያልተፈለገ አካል እንዲወገድ አልያም ኦፕራሲዮን ለማድረግ በመጀመሪያ ታካሚው ledocian መወጋት ግድ ይለዋል፤ ታካሚው መድኃኒቱን ተወግቶ ካልደነዘዘ ሕመም ይሰማዋልና። አምባገነን መንግሥታትም ሕዝቦቻቸውን አደንዝዞ ለዓመታት ለመግዛት የሚጠቀሙት የደናቁርት መፍትሔ ከዚህ ጋር እጅጉን ይቀራረባል። ለአብነትም ገቢውን ከሕዝብ ከሚሰበሰብ ግብር ካደረገው ኢብኮ ጀምሮ እስከ ክልል ቴለቭዥኖች፤ ከዛም መልስ እስከ አፍቃሬ መንግሥቱ ኢቢኤስ ድረስ፤ ፕሮግራሞቻቸውን ተከታለን እንደ ሆነ ተግባራቸው ይሄው ነው።
አዎ! ሕዝቡ ከእውነት ዜና ጋር እንዳይገናኝ የተቻላቸውን ያህል ከመጣራቸውና ከመትጋታቸውም በላይ፤ ሕዝቡን ለማደንዘዝ የሀገሪቱን ገጽታ ቀይረው ለማሳየት ይጥራሉ። የእነኚህን የቴሌቭዥን ጣቢያዎች የተከታተለ – እውነትን ከወደደ – በፕሮግራሞቹ መገረሙ አልያም መበሳጨቱ አይቀሬ ነው። የሀገሪቱን ኑሮ የማይወክል አንዱ ድራማ ሳያልቅ ሌላው ብቅ ይላል። አንዱ የመዝናኛ ፕሮግራም ሳያልቅ ሌላኛው በአናቱ ይመጣል። እንደ ኢያሪኮ ዓይነት አዙሪት በጣቢያዎቹ ፕሮግራሞች በስፋት ይታያል።
በእነኚህ የቴሌቭዥን (ራዲዮ) ጣቢያዎች ዜና የሚተላለፈው አንድ የአፋር ነዋሪ ውሃ አጥቶ ለዘመናት በጥም ሲሰቃይ አልያም በጤና ኬላ እጦት በበሽታ ሲሞት ሳይሆን፤ አንድ ቧንቧ ወይም የማይረባ አነስተኛ መደኃኒትና ቁሳቁሶች የሌሉት የጤና ጣቢያ ክሊኒክ ሲመረቅ ነው። እንዲሁም አንድ የሀረርጌ ወይም የሱማሌ ተወላጅ በረሃብ ሲሞት ሳይሆን፤ መንግሥት አንድ ሺኅ ኩንታል ዕርዳታ ሲሰጥ ነው። ይሄ ተግባር ሚዛናዊ ለመሆን ጣር ከሚለው ከሚዲያው ሕግ ጋር የሚጋጭ ቢሆንም፤ የድሮ ‹‹ኢቴቪ›› የአሁኑ ‹‹ኢቢኮ›› የመንፈስ ወንድሞቹን ከጎኑ በማሰለፍ ያለ ገላጋይ ለዘመናት ከዚህ ሕግ ጋር ሲጣላ ኖሯል። እየተጣላም ነው።
ለኔ እንደሚታየኝ ገዢው ፓርቲ ለሀገሩ የሚያስብ ግለሰብ፣ ለሕዝቡ የሚሠራ ጥሩ መዋቅር ያለው ተቃዋሚ ፓርቲ እንዳይኖር ካለም በእንጀራ ልጆቹ በኩል ተፈረካክሶ ሽባ እንዲሆኑ በእሱ ልክ እንዲያስቡና ካሉበት የስብእና ከፍታ በእሽቅድድም ወደ ቁልቁለት እንዲወርዱ ያለመታከት ሠርቷል፤ በጋሼ መሥፍን አባባል፣ ‹‹ዳገቱ ላይ ሰው እንዲጠፋ››። ነገር ግን ለገዢው ፓርቲ ሤራ አልበገርም ያሉ ጥቂቶች ሀገር አልባ ሆነው ከሀገር ወጥተው በሰው ሀገር በስደት እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል። ስደትን ወደጎን ያደረጉና በዓለማቸው የጸኑ የቁርጥ ቀን ልጆች፤ ያለርህራሄ ወደ ሰፋፊ የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ተወርውረዋል። እስር፣ ስቃይ፣ ሞት… ያልፈሩ ብርቱዎች ዛሬም የገዥውን የብረት በትር ሳይፈሩ ስለ ነገ ይጨነቃሉ። መጪው ጊዜ ግን ሀገሬ የጠፋው ሊገኝባት፣ የተፈረካከሰው ሊጠገንባት፣ ቁልቁል የወረደው ተመልሶ ከፍታ ላይ ጉብ ሊልባት ምንም አማራጭ ሳይኖር ግድ ብሏል።

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *