ዮሃንስ ሞላ

‘ኧረ ልጆች ልጆች እንጫወት በጣም…’

የልጅነት ቀለብ፣ ወይም ከጎረቤት ሽልማቶች መካከል፣ አምባሻ አንዱ በነበረበት ወቅት… እንደ ሁኔታው ስሙ እየተለዋወጠም፣ ሽልጦ፣ ጋዜጣ፣ ግድግዳ፣ አጤሬራ… እየተባለ ይንቆለጳጰስ በነበረ ጊዜ፤ … እድሜ ከፍ ብሎም፣ በጉርምስና፣ ‹‹ግድግዳ እየናደ ነው››፣ ‹‹ጋዜጣ እያነበበ ነው››፣ ‹‹እየጨመጨመ ነው›› እያሉ አምባሻ ተመጋቢ ላይ መቀለድ ሳይመጣ በፊት… ብዙ ልጆች ተማጽነውና የቀራጺውን ዋጋ ከፍለው፣ በአምባሻቸው ቅርጽ ያሰሩ ነበር። ብዙም ሂሳብ የለውም፤ የልጅነት ውል ነው። ግን ለሚበሉት ነገር ምን አደከማቸው? — ልጅነታቸው? ሞኝነታቸው? የስነ-ጥበብ ፍቅራቸው? የማየት ጉጉታቸው? ቅዱስ ላሊበላ አስራ አንዱን አብያተ ክርስቲያናት የፈለፈለበት በሚመስል ትኩረትና ብልጠት፣ አምባሻዎች በከርካሚው ጥርስ ተፈልፍለው፣ በያይነት ዓይነቱ ተቀርጸው ለሆድ ሲሳይ ሆነዋል።

ሌሎች ቅርጾቹን ማሰራት ከሚፈልጉ ህፃናት በፈቃድ፣ ‹‹እምቢ›› ካሉ ደግሞ፣ በጉልበት፥ አምባሻቸውን ተቀብለው ዙሪያውን ይኮመኩሙና ለልጆቹ ቅርጽ ያወጣሉ። የአፍሪካና የኢትዮጵያ ካርታ ቅርጾች የልጅነቱን የቅርጽ ፍላጎት ተቆጣጥረውት ነበር። ስራው ቀላል ስለሆነ ህፃናት እምብዛም አይጓጉለትም ነበር እንጂ፥ ከነኮከብና ሶስት ማዕዘን ጋር፣ የሲዲ (Compact Disc) ስራም ነበር። ሲዲ ስራ አምባሻዋ ክብነቷን በደንብ እንድትጠብቅ በሚል፥ ዳር ዳሯን ተኮምኩማ፣ መሀሏ ይቀደድላት እና የሲዲ ቅርፅ ትይዛለች። መሀሏ በደንብ ተቀዶ ጎማ የምትመስልበት ጊዜም ብዙ ነው።… ‘ቀራጮቹ’ አንዳንዴም ህጻናቱ ቅርጽ ማሰራት ሳይፈልጉ ቢቀሩ እንኳን፥ በጉልበትና በማስፈራራት ተቀብለዋቸው ቅርጽ ያወጡላቸው ነበር። — እነሱስ፥ የሚቀረፅላቸውን ልጆች የማስደሰት ፍላጎታቸው? ብልጠታቸው? የመቅረፅ ፍቅራቸው? ጨዋታው ማርኳቸው? ከዳር ዳር የሚጎማምጧትአጓጉታቸው?

አልፎ አልፎ ጨዋታውን የመውደድ ነገር ቢሆንም፥ ብዙ ጊዜ ግን ብልጠት ነበረበት። አምባሻውን ተቀብሎ ቅርፁን የሚያወጣው ሰው በጥርሱ እየከመከመ፥ በልቡ ‹ከመከም’ን በልጅኛ ያንጎራጉራል። ክቡን አምባሻ፥ ከዚህ ከዚያ እየጎማመጠ፥ የአፍሪካን ካርታ ወይም የኢትዮጵያን ካርታ የመሰለውን ነገር ያስተርፋል። ባትመስልለትም፥ ጎዶሎውን በወሬና በቁጣ ይሞላላዋል። …ምናልባት የአምባሻውን ከሲሶ በታች አስተርፎ፤ ኪኒን አሳክሏት። — አይተው ሳይጠግቡት ለሚውጡት ነገር፤ ውጠውት ለማይጠግቡበት ነገር!

‘ከእንግዲህ ልጅነት ተመልሶ አይመጣም…’

አምባሻቸውን ሰጥተው፥ በቅርጽ ይሰራልኝ ሰበብ የሚያስጎምጡትና ቀለባቸውን የሚያስቀንሱት ልጆች በእድሜም በማስተዋልም ከፍ እያሉ ሲመጡ ግን ‹‹እምቢ›› ማለት ጀመሩ። ቅርጹ ሲወጣላቸው እያዩ መሳቀቅ ጀመሩ። እንባ ቅር ይላቸው ጀመረ። መጠየቅ ጀመሩ። ሩጦ ማምለጥ ጀመሩ። መደባደብ ጀመሩ።

ትዝታ እንምዘዝ! ከእለታት ባንዱ ቀን…

ታሪኩ የሚባል ልጅ ዮሴፍ ለሚባል ልጅ አምባሻውን ሰጥቶ የአፍሪካ ካርታ ሲቀረፅለት አድፍጦ ይመለከታል። ቀራጩ፥ ዮሴፍ በብልጠት ኋላ ካርታዋ እንድታንስ እና የሚውጣት እንድትበዛ፥ የሚገምጠውን በዛ ሲያደርገው ታሪኩ አላስችል አለውና፥

‹‹በቃ ዮሲ በኋላ ትጨርስልኛለህ።›› አለው።

‹‹ለምን?››

‹‹ቤት ተጠርቻለሁ›› ሳግ እየተናነቀው መለሰ።

‹‹ሌባ… ማን ጠራህ?››

‹‹አይ መጠራቴ አይቀርም›› አለ እጁን በእልህ አወናጭፎ።

‹‹አርፈህ ቁጭ በል። ያላለቀ ካርታ ወስደህ ልታሰድበኝ ነው?›› ብሎ እንደ አዋቂ በወግ ገሰጸው። ይኽኔ ታሪኩ እንደ ተቆነጠጠህፃን እሪሪ… ብሎ ለቅሶውን አቀለጠው። ዮሴፍም ፈርቶ አምባሻውን ወረወረለት። እንዲህ ዓይነት ጀብዱዎች በዙ። ሲበለጡ የነበሩ ሰዎች መባነንና ለመብለጥ መፍጨርጨር ያዙ። ለውጥ ሆነ። ነውጥም ሆነ።

‹‹የአፍሪካ ካርታ ልስራልሽ?›› ሲባሉ፥

‹‹ዳር ዳሩንም ከርክመህ ከመለስክልኝ›› የሚሉ ብልጥ ልጆች በዙ።

‹‹ቅርፅ አትፈልግም?›› ሲባሉ፥

‹‹ሞኝህን ፈልግ… ችጋራም›› ብለው የሚጋፈጡ ልጆች በረከቱ።

‹‹ና የኢትዮጵያ ካርታ ልስራልህ፤ አምባሻህን አምጣው›› ሲባሉ፥

‹‹ካርታ ሆኖ ብበላው ቶሎ አላድግ። ለምን እከስራለሁ?›› የሚሉ ንቁ ልጆች ፈሉ።

‹‹ሲዲ ልቅረፅልህ… ›› ሲባሉ፥

‹‹በምኔ ልሰማው? ይልቅ እርሳሴን ቅረጽልኝ።›› የሚሉ አሽሟጣጦች ተፈለፈሉ።

ይኼ አካሄድ ያላማራቸው ‘ህጻናት መንግስታት’ በ‹‹ጊጩ››፣ በ‹‹ቢጥም›› እና በ‹‹ወጋሁ››ጨዋታዎች የእነርሱ ያልሆነን ቀለብ የመቋደሻ መንገዳቸውን ለወጡት። … መጀመሪያ ልጆቹ ‹‹ወጋሁ››፣ ‹‹ቢጥም›› እና ‹‹ጊጩ›› (እንደየጊዜው እና እንደየሰፈሩ አንዱ) ለመባባል ተስማምተው፣ ‹‹ሽርክ… ሽርክ›› ተባብለው ትንሿን ጣታቸውን፥ ተጣልቶ እንደሚታረቅ ልጅ አገጫጭተው ይስሙና ቃል ይገባባሉ። ከዚያ ልክ የጨዋታው ደንብ ላይ የተስማማ ልጅ አምባሻውን ይዞ ሲወጣ፥ ‹‹ጊጩ›› ይለዋል፤ ገንድሶ ይሰጠዋል። ‹‹ወጋሁ›› ይለዋል፤ ቆርሶ ይሰጠዋል። ‹‹ቢጥም›› ይለዋል፤ ይሸነሽንለታል።

ቤቱ ጨርሶት አይወጣ ነገር፥ ለእኩዮቹ ካላሳየና የሌላቸውን ካላንቆላለጨ መብላት አይበሉት። ዋናው እርካታ ይጎድልበታል። የእኛ ሰው ሁለት ጊዜ ይረካል፤ ሲያገኝ እና ያገኘውን ነገር ላላገኙ ሰዎች አሳይቶ ሲጀነን። ይዞት እንዳወጣ፥ በጊጩና በወጋሁ ያጫርሱታል። ቀድሟቸው ‹‹ጊጩ ባትለኝ›› ‹‹ወጋሁ ባትል›› ‹‹ባይጥም›› እንዳይል፥ ህጻን ልጅ ምግቡ ባለበት፥ በዚያ ልቡ አለ። — በመሀል ቤት ተሰቃየ። እንደ ምንም ‹‹ጊጩ ባትለኝ›› ‹‹ወጋሁ ባትለኝ›› ማለቱን ለመደ፥ ደግሞ ሌላ ለውጥ ሆነ።

‘እርጅና መጣና…’

ይህን የልጅነት ጊዜ፥ በ2002 ዓ.ም ከሱዳን ትሪቡን ድረ ገጽ፥ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ድንበር የማካለል ሥራ ስለመጀመሩ ካነበብኩበት ጊዜ አንስቶ፥ ስለጉዳዩ በሰማሁና ባነበብኩ ቁጥር በቁጭት የማስታውሰው ነው። ባባቶች ደም ተከብሮ የኖረ ሉአላዊ መሬት፥ ማንም ተነስቶ ‹‹ጊጩ›› ‹‹ወጋሁ›› ባለ ቁጥር ተቆርሶ የሚሰጥ ከሆነ ችግር ነው። ማንም ብልጣ ብልጥ ‹‹ቅርጽ ልስራላችሁ፥ መሬታችሁን አምጡ›› ባለ ቁጥር የሚሰጥ ከሆነ ከባድ ነው። ማንም ‹‹እንቆቅልህ›› ብሎ፥ ‹‹አላውቅልህ›› ሲባል፤ ‹አላውቅ› ያለ ይጠየቅ ዘንድ ደንቡ ነውና፥ ‹‹ሀገር ስጠኝ›› ሲል፥ ሸረፍ ተደርጎ የሚሰጠው ከሆነ፥ አደጋ ነው። መቆራረሷከቀጠለ፥ መጨረሻ ላይ ተቀርፃ የምትተርፈን ኢትዮጵያ ምን ታህል ይሆን?

ስለኢትዮ-ሱዳን ድንበር የሚምታቱ መረጃዎች

በድንበር ማካለል ሰበብ ኢትዮጵያ ለሱዳን መሬት ስለመስጠቷ የሚነገረውን ወሬ መንግስት ሁልጊዜም እንዳስተባበለ ነው። ከጥንት ጀምሮም አወዛጋቢ ጉዳይ እንደሆነ አጽንኦት መስጠቱንም አይዘነጋም። ሲመቸው፥ የእኛ ገበሬዎች እዚያ ሄደው እንደሚያርሱም ያወራል። ሁሉም ነገር የጸረ-ሰላም ወልማት ኃይሎች ሴራ እና ወሬ ነው ይላል። መሬት አለመሰጠቱን አጽንኦት ሰጥቶ ለማስረዳት ሲባትል ‹‹በአንዳንድ ሚዲያዎች ሱዳን በግድቡ ላይ ባሳየችው አዎንታዊ አቋም ምክንያት፣ ሲያወዛግብ የቆየውን ሰፊ የድንበር መሬት መስጠቷ የተዘገበ ቢሆንም፣ እንኳን መሬት ሊሰጥ ይቅርና በጉዳዩ ላይ የሚደረገው ውይይትም አልተቋጨም። እስካሁንም ስምምነት ላይ የተደረሰ ነገር የለም።›› በማለት ነው። (ሪፖርተር ጋዜጣ፥ የጥር 11 2006 እትም አምባሳደር ዲናን ጠቅሶ)

መንግስት ‘አንዳንድ ሚዲያዎችን’ ለውጦ ሲጠቀምም፥ ‘አንዳንድ ቡድኖችም ሆኑ በውጭ የሚኖሩ የዲያስፖራ አባላት’ ኢትዮጵያ መሬት አሳልፋ ሰጠች በሚል የተራገበው የበሬ ወለደ መሆኑን በመግለጽ፣ ከዚህ አልፎ ግን በአገራት መካከል የሚኖርን ታሪካዊ ዳራ ማየትም ጠቀሜታ እንዳለው በማሳሰብ፣ ‹‹ከድንበር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች መኖራቸው ነባራዊ ቢሆንም፣ ከአማራ ክልል ለሱዳን የተሰጠ አንድም ቁራጭ መሬት የለም።  ከአፄ ሚኒልክ ዘመን አንስቶ እሰካሁን ድረስ የሚነሱ የድንበር ጥያቄዎች ቢኖሩም፤ በሌላ ወገን ይገባኛል የሚል ጥያቄ የሚነሳበት እድል ዝግ ባይሆንም፣ በኢትዮጵያ በኩል ግን ሉዓላዊነት የማስከበር ተግባር የመንግሥታችን ቀዳሚ ተግባር ነው።›› በማለት ነው። ‹‹ከኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ጋር ተያይዞ የሚነሳ የበሬ ወለደ ወሬ  በአመራሮች መካከል መከፋፈልን፣  በህዝብም ውዥንብርን ለመፍጠር ታስቦ  የሚደረግ ዘመቻም ነው።›› ይለናል። (ዋኢማ፥ ሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጠቅሶ፡፡)

አንዳንድ ሚዲያ ያልሆነው፣ ዳያስፖራ ያልሆነው፣ ቡድን ያልሆነው፣ በሽብር ቢከሰስም፥ ፍርድቤት ‹‹ጥፋት አላገኘሁበትም፤ ይፈታ›› ያለው፥ ግን ዛሬም በማረሚያ ቤት እምቢተኝነት ቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ የሚገኘው የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህር እና የአረና ፓርቲ አባል አቶ አብርሃ ደስታ ግንቦት 8 ቀን 2006 ዓ.ም በፌስቡክ ገጹ ላይ፥ ‹‹ድንበሩ ብዙ ውዝግብና ተቃውሞ ያለው ሲሆን የኢሕአዴግ መንግሥት ከሱዳኖች ጋር በመተባበር በድብቅ ለመከለል ተስማምቷል። እንዲህ ነው የተደረገው፥ በድንበሩ አከባቢ የሚገኙ ኗሪዎች (የኢትዮጵያና የሱዳን) ድንበራቸውን አይተው ክለላውን ይፈፅማሉ፣ ይፈራረማሉ። ለሱዳን የተሰጠው መሬት ታውቋል። ሁሉም ነገር በኢህአዴግና የሱዳን መንግስት አልቋል። አሁን ‹‹የሀገር ሽማግሌዎች›› እንዲፈርሙ እየተደረገ ነው። የሀገር ሽማግሌዎች እንዲፈርሙ የተፈለገበት ምክንያት የድንበር ክለላ የተከናወነው በኗሪዎች ነው እንዲባል ነው። ለሌላ ጊዜም ምስክር ሁነው እንዲቀርቡ ነው።በዚህ መሠረት በድንበሩ አከባቢ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ከተሞች ማይካድራና በረከት የተወሰኑ ሰዎች በካድሬዎች ተመርጠው ‹‹ኮሚቴ›› ተሰኝተው ዛሬ እንዲፈርሙ ወደ ሱዳን ድንበር ተጉዘዋል።እነዚህ ኮሚቴ ተብለው የተመረጡ ሰዎች ስለ ድንበሩ ይሁን አከባቢው እውቀት የሌላቸው፣ የአከባቢው ኗሪዎች ሳይሆኑ በቅርብ ግዜ ባከባቢው መሬት የተሰጣቸው ሰፈርተኞች ናቸው።›› በማለት አስነብቦን ነበር። ጊዜው በአምባሳደር ዲናና በምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ማስተባበያዎች መካከል ነበር።

ከዚህ ባሻገር፥ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ታህሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር ‹‹ለሱዳን ተቆርሶ የተሰጠ መሬትም ሆነ እስካሁን የተደረገ ድርድር የለም።›› ብለው ነበር። (‹‹እስካሁን የተደረገ ድርድር የለም›› ቢሉም፥ ‹‹ላለፉት አሥር ዓመታት ድንበሩን በተመለከተ ሲሠራ የቆየው የጋራ ኮሚሽን፣ በሁለቱም አገሮች መካከል ያለው ድንበር እንዲካለልና የግጭት መንስዔ የሆነውን ጉዳይ ለመፍታት እየሞከረ መሆኑን›› ግን አምባሳደር ዲና በተጠቀሰው እትም፥ ለሪፖርተር ተናግረው ነበር።)

አቶ ኃይለማርያም፣ በሱዳን ድንበር ጉዳይ ‹‹… አስቀድሞ በመሬት ዙሪያ የተደረገ ድርድር የለም፡፡ ተቆርሶ የተሰጠም ነገር የለም፡፡ ተቆርሶ ሊሰጥ የሚችል ነገርም የለም፡፡ […] ይሄ ማለት ግን የሱዳንና የኢትዮጵያ ድንበር እንዳልተካለለ ቀድሞም የሚታወቅ ነው፡፡ ዛሬም ያለ አጀንዳ ነው፡፡ […] ሁለተኛው በርካታ ኪሎ ሜትሮች ሱዳን ውስጥ ገብተው የሚያርሱ እኛም የምናውቃቸው ሱዳኖችም የሚያውቋቸው የእኛ ባለሀብቶችና ውስን አርሶ አደሮችም ጭምር አሉ፡፡ ይሄንን የማካለል ሥራ እስከምንሠራ ድረስ እባካችሁ አርሶ አደሮቻችንን አትንኩብን፣ ባለሀብቶቻችንን አትንኩብን ብለን፤ እሺ አንነካም ብለው በወዳጅነታቸው ምክንያት ዝም ያሏቸው፣ አርሰው የሚበሉ በርካቶች›› በማለት፥ በቀጥታ ‹‹ለሱዳን የሚሰጥ መሬት›› አለ ባይሉም፥ ‹‹ሱዳን መሬት ላይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስላሉ፣ እስከዛሬ ስለቻሉንና ወገኖቻችንን ስላልነኩ የመመሰጋገን፣ እነሱ ወዲህ ሳብ የማድረግ እና ድንበሩን የመከለል ሥራ መካሄዱ አይቀርም። እዚያ ገብተው የሚዘርፉ ሽፍቶች ላይም ስለሚሆነው ነገር ከደሙ ንጹህ ነኝ።›› ዓይነት ገደምዳሜያዊ ንግግር አድርገዋል።

ከዚህ በተቃራኒው፥ ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን በታህሳስ 21 ቀን 2008 ዓ.ም በዚሁ ጉዳይ በጻፈው ጽሁፍ ‹‹ለሱዳን ሊሰጡት ባሰቡት መሬት ላይ ያለውን አርሶአደርም እያፈናቀሉና እየጠረጉ መሬቱን ነጻ ሲያደርጉ ከራርመዋል፡፡ የተፈናቀሉ ገበሬዎች በጎንደር ከተማና በሌሎች ስፍራዎች ሜዳላይ ፈሰው […] በተለያየ ጊዜ ተመልክተናል፡፡ ‹‹ለምን?›› ተብሎ ሲጠየቅ የወያኔ ባለሥልጣናት ከሰባት ዓመታት በፊት ይሰጡት የነበረው መልስ ‹‹መሬቱን የሱዳን ባለሀብቶች እንዲያለሙት በሊዝ ተሰጥቷቸዋል›› የሚል ነበር።›› ይለናል። ይሄ ደግሞ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ነው። አሁን እየሰጡት ካለው ማስተባበያ ጋርም ሙሉ በሙሉ ይጋጫል።

በጉዳዩ ዙሪያ ለብዙዎች የወሬ ምንጭ ሆኖ የከረመው ‘ሱዳን ትሪቡን’ በበኩሉ፥ ጃንዋሪ 17/2016 ‹‹Ethiopia to complete border demarcation this year›› በሚል ርዕስ ድረ-ገጹ ላይ ባሰፈረው ዘገባ፥ የሱዳን እና የኢትዮጵያን ድንበር ካርታ መልሶ በመሳል (redrawing) ላይ የተሰማራው ኮሚቴ፣ ‹‹(የካርታውን ስዕል) ወደ መሬት የማውረዱ ስራም በዚህ ዓመት ያልቃል›› ማለቱን ገልጿል። በማያያዝም ‹‹በኖቬምበር 2014፥ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው፥ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሞት ተከትሎ ተቋርጦ የነበረውን የድንበር ማካለል ጉዳይ እንዲቀጥሉ ማሳሰባቸውን ገልጿል።›› በማለት ዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ሱዳንና ኢትዮጵያ የሱዳን ክልል ውስጥ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ሽፍቶች (gangs) እንቅስቃሴዎች ለማክሸፍ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ለአልጀዚራ ቴሌቪዥን መናገራቸውንም ገልጿል። ሚኒስትሩ ‹‹’አልፋሻግ’ (ለሱዳን ሊሰጥ ነው የተባለው 600 ሺ ሄክታር መሬት በጅምላ የአረብኛ አጠራሩ) የሱዳን ግዛት ቢሆንም፥ በሁለቱ አገራት መካከል ባለው ትብብርና ወዳጅነት መሰረት፥ መንግስታችን ለኢትዮጵያ ገበሬዎች እንዲያርሱት የፈቀደላቸው ነበር። ሆኖም ኢትዮጵያ ፈቃደኛ ነች። የሱዳን ግዛት መሆኑንም አምና ተቀብላለች።›› በማለት ገልጿል።›› ብሎናል። (እንግዲህ ይህ ንግግራቸው ከጠቅላይ ሚኒስትራችን የፓርላማ ንግግር ጋር ስምም መሆኑን ልብ ይሏል።)

ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ፥ የካቲት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. የአረና ፓርቲ የአመራር አባል የሆነው አቶ አምዶም ገብረስላሴ በፌስቡክ ገጹ ላይ ‹‹…እንደ መተማ ዮውሃንስ፣ ቋራ፣ ልጉዲና ሌሎች ለም መሬቶች ለሱዳን ሊሰጡ በሁለቱ መንግስታት ዝግጅት መጠናቀቁ እየተገለፀ ነው።ወቅቱ የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን ለማስረከብ ሁለቱ መንግስታት ከ17 ግዜ በላይ በድብቅ እየተደራደሩ የነበሩ ሲሆን የዚህ ድንበር ውጤትም ሱዳን በሑመራ በኩል ከነበረው ባህረሰላም የሚባለው የኢትዮጵያ ድንበር በርካታ ኪሎሜትሮች ወደ ኢትዮጵያ በመግፋት ልጉዲ በተባለው የድንበር ከተማ ኣድርገው በመትከል የሱዳን የኢሚግሬሽን ፅሕፈት ቤት (Passports Office )ኣዲስ ህንፃ ገንብተዋል።›› በማለት የ17ኛውን የሱዳን እና የኢትዮጵያ የድንበር ልማት ኮንፈረንስ ባነር (17th Sudan Ethiopia Boarder Development Conference) እና የህንጻውን ፎቶ አያይዞ ለጥፎ ነበር።

የአማራ ክልል መንግስት፥ 50ኛ ዓመቱን በማክበር ላይ ያለው የመንግስት ቴሌቪዥን (EBC) ላይ ‹‹የፕላቲኒየም የክብር ስፖንሰር›› በመሆን ይሄድለት በነበረ ማስታወቂያ ላይ የታየው ካርታ ደግሞ፥ የአማራን ክልል ከሱዳን ጋር ተዋሳኝነቷን የማያሳይ ነው። (ምስሉ ከዚህ ጽሁፍ ጋር የታተመ።) ይሄ ሁሉ ነገር ግጥምጥሞሽ ከሆነ ይገርማል።

ስንጠቀልለው

አቶ ኃይለማርያም ንግግራቸውን ባደረጉበት ወቅት ‹‹በተለይ በሱዳን በኩል ልክ የኛዎቹ እንደሚያደርጉት መንግሥታውን የሚያስቸግሩ አካላት አሉ፡፡ እነዚህ አካላት በየጊዜው ይሄን ነገር ያራግባሉ፡፡›› ብለው ነበር። ሆኖም ግን፥ የሚዲያ፣ ሀሳብን የመግለጽ፣ የመጠየቅ፣ መረጃ የማግኘት፣ እና አስተያየት የመስጠት ነጻነት በሌለበት ሁኔታ ሕዝቡ በቀጥታ በሚመለከተው ጉዳይ ላይ ያገኘውን የመረጃ ምንጭ ቢጠቀም ቢያስደንቀው እንጂ አያስወቅሰውም። ሲሆን፥ በ‹‹ብሔራዊ ቴሌቪዥኑ›› ብሔራዊ ጉዳዮቹን በግልጽ መስማት መብቱ ነበር። መንግስትም በሁለቱ አገራት መካከልም የሚደረገውን ነገር በይፋ፣ መረጃዎችን በማጠናቀር መዘገብ ይኖርበታል። ምን ተሰራ ምን፥ የግንኙነት (communication) ክፍተት በፈጠሩበት ሁኔታ ቁጣና ማስፈራራት መፍትሄ አይሆኑም።

መቼም ሀገር ምግብ አይደለች ነገር፤ ተውጣ ተሰልቅጣ አትረሳ። ነገ ከነገ ወዲያ ‘ድንበሬን፣ ወሰኔን’ ብለው ልጆቻችን ቢጠይቁን ምን እንመልስ ይሆን? ወይ ደግሞ ተጠያቂዎች አልፈውና ማስረጃዎች ጠፍተው ካለፈ በኋላ፥ መጠያየቁ ከባድ ሲሆንባቸው፥ እንዴት ይሆኑ ይሆን?…ወይስየግጭት አጀንዳ ሳያንሳቸው ጨማምረን እያሳደርንላቸው ነው? ዓይናችን እያየ፥ ጆሯችን እየሰማ በአንቀጽ 39፥ ኢትዮጵያ ከወደአንገቷ ተቀንጥሳ ኤርትራ ራሷን ማስተዳደር ስትጀምር የአሰብ ወደብ የሌላ ሆነ። …ጦር የታወጀባትና ስንት ደም የፈሰሰባት ባድመ ቆሽት በሚያበግን መልኩ ተዳረች። እነሆ ሱዳንም ‹‹ወጋሁ›› ካለች ከርሟል። ‹‹ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው›› እንጂ፥ ሽርጉዱም እንደጦፈ ነው። ድንበር መጋራቱም ስላለ፥ ዳር ዳሩ እንዲህ መከምከሙን ቀጥሏል። በሰበብ አስባቡ፥ ከመሀል ሰፍረው ‹‹መሀሉን ቀደን ሲዲ እንስራላችሁ›› የሚሉ ቢመጡስ ምን እንል ይሆን?

 

ዕንቊ(ቅል)

ከተጫወቱ አይቀር፥

‹‹እንቆቅልህ›› ካሉስ፣

ከደግ ሀገር ጌታ፣

ካ’ላዋቂ ንጉስ፤

‹‹አላውቅ›› ባለ ቁጥር፥

አፈር እንዲቆርስ፤…

..መሬት እንዲለግስ።

/‹‹የብርሃን ልክፍት›› (2005)/

 

 

 

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *