ደርቤ ችሮታው

ፈረንጆች የአዲስ ዓመት በዓላቸውን ሲያከብሩ፣ ያሳለፉትን ዓመት (2015) ገምግመው ለ2016 ያላቸውን ምኞት ሲገልጹ፣ እቅዳቸውን ሲነግሩን ወዘተ. ነበር። ለዛሬው ጽሑፌም መነሻ የሆነኝ ይሄው ጉዳያቸው ነው።

የሰው ልጅ ወደ ምድር ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ አካባቢውን፣ ጊዜውን፣ ሐሳቡን… ለራሱ እንዲመቸው አድርጎ ሲያስተካክል ቆይቷል፤ ይህም ይቀጥላል። ‹‹ለራሱ እንዲመች› ካደረጋቸው ነገሮች መካከል አንዱ የጊዜ አቆጣጠር ነው። እርሱም ጊዜን በኖረበት ዘመን በማይክሮ ሰከንድ፣ ሰከንድ፣ ደቂቃ፣ ሰዓት፣ ቀን፣ ዓመት፣ ክ/ዘመን፣ ሚሊኒየም ወዘተ. እያለ ከፋፍሎ ሲጠቀም ኖሯል። የሰው ልጅ ‹የነገሮች መነሻው› አካባቢው ነውና፤ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ጊዜን በተመሳሳይ መንገድ አልከፋፈለም፣ አልቆጠረም፤ ሊከፋፍል፣ ሊቆጥርም አይችልም። በሌላ አገላለፅ፣ ሁሉም ማኅበረሰብ ተመሳሳይ የሆነ የጊዜ መክፈያ እና መቁጠሪያ ዘዴ የለውም (ይህ ድምዳሜ ምናልባት የአሁኑን የባህል ወረራ ላይጨምር ይችላል)።
አውሮፓውያን የራሳቸው፣ ‹ምሥራቃውያን› እና ብቸኛዋ ኢትዮጵያ ደግሞ የራሷ የጊዜ አቆጣጠር አላቸው። ኢትዮጵያ መጤ የባህል ተጽእኖ የተራራ ያኽል እየከበዳ ቢሆንም፤ ከአብራኳ የወጣውን – የራሷን – የዘመን አቆጣጠር እየተጠቀመች ትገኛለች። እንደሚታወቀው፣ እኛ ዘመን የምንለውጠው በመስከረም ሲሆን፣ አውሮፓውያን ከእኛ አራት ወሮች በኋላ ነው። የሆኖ ሆኖ ግን ዛሬ ላወጋችሁ ያሻሁት ስለ ዘመን አቆጣጠር አይደለም፤ በዘመን ውስጥ ስለሚኖረን፣ ስላሉንና ስለኖሩን ምኞቶች፣ እቅዶች እንጂ።
ወዳጆቼ! አዲስ ዓመትን ባለፈው ሳምንት የተቀበሉት የዓለም ሀገሮች፤ 2015ን ፈረስ ብለው ሰይመው፣ በ2015 ውስጥ ጥሩና መጥፎ ሥራ የሠሩትን ፈረሰኛ (ጋላቢ) አድርገው ሲረግሙ፣ ሲመርቁ ሰምተናል። እንደ እነርሱ፣ 2015 (ፈረሱ) መጥፎ ዓመት ነበር። ለምን? የእርስ በርስ ጦርነት የበረከተበት፣ የስደተኞች መዓበል አውሮፓን ያጥለቀለቀበት፣ አሸባሪዎች የንጹሃን ዜጎችን ሕይወት የቀጠፉበት፣ …ብለው ምክንያቶቻቸውን ይደረድራሉ። 2016 ደግሞ የእርስ በርስ ጦርነት የማይኖርበት፣ ስደተኛ የማናይበት፣ አሸባሪ የሚባል ቡድን የማይኖርበት …ይሁን ብለው ተመኝተዋል።
ይህን ሁሉ እርግማንና ምኞት ሰማሁና ወደ ሀገሬ ስመለስ፤ ያለፈውን ዓመትና አዲስ የተባለውን አሰብኩና፣ አሮጌውን ምን ብለን ረግመን፣ አዲሱን ምን ብለን ተመኝተን ተቀብለነው? …እንዴትስ አምስተኛው ወር (ጥር 2008 ዓ.ም) ደረስን? … እያልኩ ጥያቄዎችን እየደረደርኩ፤ 2007 ዓ.ም (13ቱን ወር) እና 2008 ዓ.ም (4ቱን ወር) በዐይነ-ኅሊናዬ ተመልሼ አሰብኩት!
ወዳጆቼ! 2007 ብዙ ኢትዮጵያውያን የአፍሪካ በረሃ ራት የሆኑበት፤ በሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ የዓሣ ራት የሆኑበት (ሰባት የ33 ሰፈር ልጆች በባሕሩ ላይ በጀልባ ‹ሲጓዙ› ጀልባው ሰጥሞ ውሃ የበላቸውን ያስታውሷል)፤ ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ ሀገሮች – ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሊቢያ ወዘተ. – ወደ ዘብጥያ የተወረወሩበት፤ በሊቢያ ውድ ልጆቻችን የተሰየፉበት (እነጀማል፣ ኢሳይያስ … ያስታውሷል)፤ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ትተው የተሰደዱበት እና በሀገራቸው ደግሞ ለእስር የተዳጉበት፤ ለአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ሩሲያ፣ ጀርመን ወዘተ. ምሳሌ የሚሆን ‹እንከን የለሽ ምርጫ› ያካሄድነበት (‹እንከን የለሽ› ያልኩት፤ ከላይ የጠቀስኳቸው ምዕራብያውያን፣ የሚያካሂዷቸውን ምርጫዎች ውጤት የሚያውቁት ከምርጫው በኋላ እንደሆነና እኛ ደግሞ – ከእነሱ በተሻላ – ውጤቱን ከምርጫ በፊት ስለምናውቅ ነው)፤ ደግሞም ብዙ ጋዜጠኞችን ያስፈራራንበት፣ ያሰርንበት እና ያሰደድንበት፤ የአንደኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተገቢው መልኩ ያሳካንበት፤ በታሪካችን ታይቶ ማታወቅ ድርቅ ያየንበት፤ ሕፃናት በረሃብ የሞቱበት፤ መንግሥት ‹ረሃብ የሚባል ነገር የለም! በቁጥጥሬ ሥር አውዬዋለሁ!› ብሎ የፎከረበት ዓመት ነበር። እና በመሆኑም ፈረሰኛውን – እኛን – ሳይሆን፤ ፈረሱን እንዲህ ወቅሰን፣ረግመን፣ ታርጋ ለጥፈን ነበር። እንደውም ሰባት ቁጥር ያለበት ዓመተ-ምሕረት፣ ‹ለኢትዮጵያ አይሆንም፣ መጥፎ ነው!› ብለን፤ ሰባት ቁጥርን ወደ ኃላ መቶ ዓመት ተመልሰን በአገራችን ታሪክ ውስጥ ያለውን መጥፎ ጠበሳ አስታወሰን ነበር። እንያቸው፡-
1907
የዐፄ ምኒልክ የልጅ ልጅ – ልጅ ኢያሱ – የንግሥና ወንበር ይዘው ስለነበር፤ የሸዋ መኳንንትና የዐፄ ኃይለሥላሴ (ተፈሪ መኮንን) እና የንግሥት ዘውዲቱ ደጋፊዎች፤ ልጅ ኢያሱን የሰደቡበት፣ ያጥላሉበት፣ እበና በሕዝብ ተቀባይነት እንዳያገኙ ሤራ የተሤረበት ዓመት ነበር። (እዚህች ጋር፣ ‹‹ከሸዋረጋ የተወለደ ልጅ፤ ለሀገር አይጠቅም፣ ለራሱም አይበጅ።›› ተብሎ የተተረተባቸውን ያስታውሷል!)
1937 (አ.አ)
ኢትዮጵያ በማይጨው ጦርነት የተሸነፈችበትና የአክሱም ሐውልታችን ወደ ጣሊያን አገር ተወስዶ ሮም አደባባይ የተተከለበትና ጣሊያን የአድዋን ቁጭት ኢትዮጵያ ላይ የተወታችበት ዓመት መሆኑ አይዘነጋም።
1967
ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ለሀገራቸው ዳር ድንበር ተዋግተው ሀገራቸውን ነጻ ያወጡ አርበኞችንና የዐፄ ኃይለሥላሴ ባለሥልጣናትን የረሸንንበት፤ የ1966 ዓ.ም ድርቅ በዚህኛውም ዓመት የቀጠለበት፤ የኢትዮጵያ ክብር እና ሞገስ – የጥቁር ኩራትነት! – በዓለም ፊት ዝቅ ያለበት፣ የተዋረደበት – ዓመት ነበር። ከዚያም በተጨማሪ፤ እስካሁን ግልጽ መረጃ ባልተገኘበት መንገድ ዐፄ ኃይለሥላሴ የተገደሉበት ዓመት ነበር። በ1977 ዓ.ም እንዲሁ የኢትዮጵያ መጥፎ ታሪክ የተመዘገበበት ዓመት ነው። ይኸውም፤ ድጋሚ አሰቃቂ ድርቅና ረሃብ ያስመዘገብንበት ዓመት ነበር።
1987
የሽግግር መንግሥት አብቅቶ ‹በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት› የሚባል የውሸት ካባ የለበሰ መንግሥት የመሠረትንበት፤ ‹እኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦች… › ሳይሆን፣ ‹እኛ ብሔር ብሔረሰቦች… ›› ብሎ የሚጀምር ሕገ-መንግሥት ያጸደቅንበት ዓመት መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
1997
1997ን ስናስታውስ፤ ዴሞክራሲያዊ ሕዝብ ያለባት ነገር ግን ዴሞክራሲያዊ መንግሥት አልበቅልልሽ ያላት ሀገር፤ ዴሞክራሲያዊ ሕዝቦቿን በጥይትና እስር የምትቀጣ ሀገር …መሆኗን ያየንበት ዓመት መሆኑን፣ በትውስታ ሳይሆን ዓይናችን ላይ ያቀረረው እንባ ይመሰክራል። ይህን ሁሉ ብሶት ዘርዝረን 2007 ዓ.ምን ሸኝተን 2008 ዓ.ምን ስንጀምር ምን ብለን ተመኝተን ነበር?
አንድም ኢትዮጵያዊ የበረሃ ሲሳይ የማይሆንበት፤ የዓሣ ቀለብ የማይሆንበት፤ ሰው በሀገሩ ቀልብህ አላማረኝም ተብሎ ወደ ዘብጥያ የማይወረወርበት፤ ሀገሬ በቃኝ ብሎ መጥፎ ስደት የማይሞክርበትና የማይሰደድበት፤ ጋዜጠኛ ሐሳቡን በነጻነት የሚገልጽበት፤ አንድም ኢትዮጵያዊ ወንድሙን የማይገድልበት፤ ሰው ለሆዱ ሳይሆን ለኅሊናው የሚኖርበት፤ ውሻ ‹ጃስ!› ተብሎ ባለቤቱን የማይነክስበት …ዓመት ይሁንልን ብለን ተመኝተን ነበር።
ታዲያ ይኽ ምኞታችን በአራት ወሮች ውስጥ የት ደርሷል? ስንቱ ኢትዮጵያዊ በ2008 ዓ.ም የበረሃ ራት፣ የዓሣ ቀለብ ሆነ? ስንት ኢትዮጵያዊ ሀገሬ በቃኝ ብሎ ጥሎ ሲሄድ፣ በራሱ የአፍሪካ ሀገሮች እስር ቤት ታሰረ? ስንቱ ከፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ አለፈ? ስንቱ ከነነፍሱ ኩላሊቱ ተሰረቀ? ስንት ጋዜጠኞችና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ታሰሩ? ስንት ጋዜጠኞች ሐሳባቸውን በነጻነት ገለጹ፣ ለሕዝብ አስተማሩ፣ የሕዝብን ችግር ለአደባባይ አበቁ፣ ለሕዝብ የመረጃ አማራጭ ሆኑ? ስንት ኢትዮጵያውያን በወንድሞቻቸው ተገደሉ፣ ከሚኖሩበት ቀዬ በጎሰኝነት ተፈናቀሉ፣ ንብረታቸው ወደመ? ስንት ኢትዮጵያውያን ሆዴ በቃኝ፣ ለኅሊናዬ ልደር፣ ልኑር አሉ? ስንት ውሻ ‹ጃስ!› ተብሎ ባለቤቱን ነከሰ?
እንግዲህ ጊዜ እዚህ ደርሷል – ጥር 2008 ዓ.ም። ግን ምኞታችን የት ደርሷል? እስከ መቼ ነው ምኞታችን፣ ተግባራችን እና ጊዜ እንደ ሮኬትና የሮኬት ጭስ በተቃራኒ ሆነን የምንቀጥለው? ቀሪው የ2008 ዓ.ም ምኞታችንስ እንዴት ይሆን?
እናንተ ሰላም!

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *