‹‹ስለታሰርኩ፣ ስለተደበደብኩ፣ ጉዳትና ጫና ስለደረሰብኝ በቃኝ ብዬ አገሬን እና ሕዝቤን አልተውም!››

አቶ  ሀብታሙ አያሌው

 

ልጁ አሁንም ብርቱ ነው፡፡ ‹‹በሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ አንድ ሙከራ አድርጌ እስር ስለገጠመኝ ተስፋ አልቆርጥም›› ባይ ነው፡፡ ደጋግሞ ‹‹ከእነማን ጋር ነው ስታገል የነበረው?›› በማለት የቀድሞ የአንድነት የትግል አጋሮቹ ላይ ጥያቄ ያነሳል፡፡ ‹‹የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁን አንቀፅ አራት በመተላለፍ አንድነት ፓርቲን ሽፋን በማድረግ የሽብር ድርጅት አመራሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር አመጽ ለማነሳሳት ሞክሯል›› ተብሎ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ጋር ክስ ተመስርቶበት በነሐሴ 14 2007 በከፍተኛ ፍርድ ቤት በነፃ ቢሰናበትም አቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍ/ቤት ያነሳው ይግባኝ ተቀባይነት በማግኘቱ ከደጅ ሆኖ ጉዳዩን የመከታተል ዕድል ተነፍጎ በእስር ቆይቷል፡፡ የካቲት 4 2008 ሰበር ሰሚ ችሎት በጠቅላይ ፍርድ ቤት በእግድ የተላለፈባቸው ውሳኔ ተቀባይት የሌለው በመሆኑ ከደጅ ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ወስኖለታል፡፡ ከ17 ወራት የእስር ቤት የመከራ ጊዜ በኋላ ወደ ቤተሰቦቹ ከተመለሰው ሀብታሙ አያሌው ጋር አቤል ዓለማየሁ ቆይታ አድርጓል፡፡

 

‹‹ስለታሰርኩ፣ ስለተደበደብኩ፣ ጉዳትና ጫና ስለደረሰብኝ በቃኝ ብዬ አገሬን እና ሕዝቤን አልተውም!››

አቶ ሀብታሙ አያሌው

 

እንኳን ለቤትህ አበቃህ!

አመሰግናለሁ! ደስታዬ ግማሽ ነው፡፡ ተመሳሳይ ክስ የተመሠረተብን ጓደኛቼ የሺዋስ አሰፋ፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ አብርሃ ደስታ፣ [ፍርድ ቤት ደፈራችሁ ተብለው የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው] ዮናታን ወልዴ፣ ዘላለም ወርቃገኘሁ፣ ባህሩ ደጉና ሌሎችም በርካቶች አሁንም ያሉት በእስር ቤት ነውና እነሱን ሳስብ ደስታዬ ግማሽ ይሆናል፤ ግማሽ ሀሳቤም እነሱ ጋ ነው፡፡ ከቤተሰቦቼ እና ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመገኘቴ ግን በጣም ደስ ብሎኛል፡፡

መቼም የእስር መልካም ስለሌለው ‹‹ቆይታህ እንዴት ነበር?›› አልልህም፡፡ ግን እስኪ ከፋፍለን እንመልከተው፡፡ ከየት ነበር የያዙህ?

የተያዝኩት ፍላሚንጐ አካባቢ ሰንሻይን ሕንጻ የሚገኘው አቢሲኒያ ባንክ ውስጥ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ በአሜሪካ ስድስት ከተሞች ላይ ቅስቀሳ ያደረግ ስለነበር ወደዚያው የሚሄዱ ስድስት ሰዎች ነበሩ፡፡ የእነሱን ፓስፖርት ይዤ አስቀድሞ ክፍያ መፈፀም ስለነበረበት ቅፅ እየሞለሁ እያለሁ ባስገራሚ ሁኔታ ባንኩን መጥተው ወረሩት፡፡ እኔ አንድ ተራ ሰው ነኝና ይሄ ሁሉ የወታደር ኃይል እኔን ለመወስድ ይመጣል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ [የባንኩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ትመስለኛለች] ሲይዘኝ ተደናግጣ ‹‹ምን ሆነህ ነው?›› ብላ ስለጠየቀችኝ ሦስት ቀን ታስራ ተለቅቃለች፡፡

ከዚያስ ወዴት ወሰዱህ?

ብርበራ ለማካሄድ ወደ ቤት ይዘውኝ ሄዱ፡፡ ለተጠረጠርኩበት ጉዳይ እኔን የሚመለከት ማስረጃ በፍፁም ሊኖርም፣ ሊገኝም አይችልም፤ አልተገኘምም፡፡ ከዚያ ወደ ወንጀል ምርመራ  (ማዕከላዊ) ወሰዱኝ፡፡  በእዚያ አራት ወራት አሳልፌያለሁ፡፡

በማዕከላዊ ቆይታህ ጭለማ ቤት መታሰር፣ የስቃይ ምርመራን መጋፈጥ አጋጥሞሃል?

የሕግ አማካሪዬ የነበሩት አቶ ተማም አባቡልጉ የጥብቅና ፈቃድ ሲታገዱና ችሎት መቆም ሲከለከሉ የእኔን ጉዳይ ኃላፊነት ወስደው ከያዙት አቶ አምሐ መኮንን ጋር አጠቃላይ የማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ጊዜዬ ምን እንዲመስል፤ የገጠሙኝ ችግሮች ለየትኛው የሕግ አካል በአግባቡ መቅረብ እንዳለባቸው ተነጋግረን የተዘጋጀ ሰነድ ስላለ ወደፊት እሱን  እናቀርባለን፡፡ ገና የፍርድ ሂደቱ ስላላለቀ እዚያ የተፈጠሩ እና የደረሱ ነገሮች በሙሉ ሂደቱ የሚመራን ከሆነ ወደ ፍ/ቤት የምናቀርባቸው ይሆናል፡፡ ዝርዝር ጉዳዩን ወደፊት የምንገልፀው ይሆናል፡፡

የቂሊንጦ ቆይታህም በተመሳሳይ ለፍርድ ቤት የሕግ ጥያቄ የምታቀርብበት ነው?

በቂሊንጦ ቆይታዬም በፍርድ ቤት ሂደቶች ውስጥ በመፈታት፣ በመለቀቅ ጉዳይ ላይ የተፈጠሩብኝ ስህተቶች፣ ባቀረብኳቸው ክርክሮች ፍርድ ቤት በነጻ ካሰናበተኝ በኋላ ያለመለቀቄ ጉዳይ [ክስም ያቀረብኩበት ጉዳይ ነው] አሁንም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከለቀቀኝ በኋላ ከአርብ (የካቲት 4/2008 ዓ.ም.) እስከ ሰኞ ድረስ ለአራት ቀናት ያለ አግባብ ለምን እንደተጉላላሁ ሳይነገረኝ ማክሰኞ ውጣ መባሌን አስመልክቶ የማነሳቸው ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡ እንደ አንድ ዜጋ ‹‹ደኅንነቴ ተጠብቆ መኖር እችላለሁ ወይ?›› የሚለውን ጥያቄ ውስጥ የከተተ ስለሆነ ከጠበቃዬ ጋር ተነጋግረን ወደፊት ማብራሪያ የምንሰጥበት ይሆናል፡፡

ከእስር ተፈትተው የወጡ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም ሲያወሩ እንደምሰማው (እንደምናነበው) በወኅኒ ቤቶች ውስጥ አስገራሚ የክስ ዓይነቶችን እንደሚመለከቱ እና ሰዎችን እንደሚያገኙ ይነግሩናል፡፡ የታዘብከው አለ?

በጣም የገረመኝ በርካታ ሕዝብ በፀረ-ሽብር አዋጁ አማካኝነት እየተከሰሰ መሆኑ ነው፡፡ ብዙዎቹን ክሶች ከመመልከቴም ባለፈ የሕግ ድጋፍ የማያገኙ ሰዎች ድጋፍ በመስጠት የበኩሌን ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ [ሀብታሙ የተማረው የሰው ኃይል አስተዳደር ቢሆንም በእስር ወቅት ባዳበረው የሕግ ዕውቀት ለእስረኞች ድጋፍ ያደረግ ነበር፡፡] ክሳቸውን ዓይቶ ማማከር፣ የክርክር ማቆሚያ ማዘጋጀት፣ የክስ መቃወሚያ ማቅረብ፣ በመስቀለኛ ጥያቄ ዐቃቤ ህግን መፈታተንና ሌሎችን ጉዳዮች ጊዜ እስካጣ ድረስ አግዛቸው ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የተረዳሁት አብዛኛዎቹ ክሶች ዜጎች ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ምንም ማስረጃ ሳይቀርብባቸው በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ሥርዓት ሕግ 27/2 አማካኝነት [ከተከሳሽ የሚገኝ የእምነት ቃል ተፈጻሚነት ይኖረዋል] የተገኘ ነው እየተባለ በኃይል ተደብድበው በሚገኝ ቃል ‹‹አምኗል›› እየተባለ ብይን እየተሰጠበት መሆኑ ነው፡፡ ውሻዋን ‹‹ፍየል ነኝ ብላ አምናለች›› ብሎ ፖሊስ አቅርቧታል ተብሎ እንደሚቀለደው ማለት ነው፡፡

በሽብር የተጠረጠራችሁ ታሳሪዎች ከፍርድ በፊት ነጻ ሆናችሁ የመታየት ሕገ-መንግሥታዊ መብታችሁ እንደሚጣስ ይነገራል፡፡ ውብሸት ታዬ ‹የነጻነት ድምጾች› በሚለው መጽሐፉ ምን ያህል መገለል እንደሚደርስባቸው በዝርዝር ገልጿል፡፡‚

በትክክል! የጊዜ ቀጠሮ ማረሚያ ቤት በሽብር ተከሰህ ከገባህ በማንኛውም ኮሚቴ ላይ መሳተፍ አትችልም፡፡ ሕክምና ስትወጣ የሚደረግብህ ቁጥጥር ጥብቅ ነው፡፡ የቤት አስተዳደር ሆነህ እንኳን መሥራት አትችልም፡፡ ሰዎች ከአንተ ጋር ቀርበው እንዲያነጋግሩህ አይፈቀድም፡፡ ቃሊቲ ያሉ እስረኞች ደግሞ የሚጠየቁበት ሰዓት በጣም የተገደበ ነው፡፡

መንግሥት የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴ ጀምሬያለሁ ሲል በማረሚያ ቤቶች ላይ እንደዚህ አይነት ግልጽ የሕግ ስህተቶችን ያርማል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ የሚገርመው ግን የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴው ሲጀመር በሽብር የተከሰሱ ሰዎች ላይ ጫናውን በማጠንከር እንደ ጥፋተኛ እየተቆጠርን የሚደርስብን መገለል እየጨመረ ሄዷል፡፡

በሰበር ሰሚ ችሎት አቃቤ ሕግ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረባችሁትን ይግባኝ በደጅ ሆናችሁ እንድትከታተሉ ውሳኔ ቢያሳልፍም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እናንተን ለመፍታት ዳተኝነት አሳይቷል፡፡ ይህን ስታይ የአገራችን የሕግ ስርዓት ወዴት እየሄደ ነው እንድትል አላደረገህም?

በአጠቃላይ የፍትህ ስርዓቱ የከፋ ደረጃ ላይ ለመድረሱ ማሳያው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔን እንኳን ለማክበር አለመቻሉን ነው፡፡ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ተረድተው እሰሩ ሲባሉ የማሰር፣ ፍቱ ሲባሉ የመፍታት ተግባራቸውን አይወጡም። የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብት በመጠበቅ የማረም እና የማነፅ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ሳይሆን በሽብር ተጠርጥረን በመግባታችን ብቻ እኛን እንደ አገሪቱ ከባድ ጠላት የመቁጠር እና የማግለል ሥራ እየሠሩ ነው። የሕግ የበላይነት እየተተገበረ አይደለም።

ወደኋላ መለስ ልበልና አንዳንድ ነጥቦችን ላንሳ… የገዢውን ፓርቲ መለያ አውልቀህ የተቀላቀልክበት የተቃውሞው ጎራ (ተፎካካሪ ፓርቲዎች) የራሳቸውን ለፓርቲ ወንበር (ሥልጣን) ከማስጠበቅ ባለፈ ረዥም ጉዞ የሚያስኬድ ራዕይ፣ ግብ፣ ቁርጠኝነትና አቅም  የላቸውም ተብሎ ይተቻል። የአጭር ጊዜ ተሞክሮህ በአስተያየቱ እንድትስማማ የሚያደርግ ነው?። [በቂ የማሰላሰያ ጊዜ ስለነበረህ ይህንን እንዴት ታየዋለህ?]

ያነሳኸው ሰፊ እና ራሱን የቻለ ጥናት የሚያስፈልገው ነጥብ ነው። የተቃውሞ ጎራው ስብስብ ጥርት ያለ ዓላማ ይዞ፣ ግልፅ ብሎ የወጣ የፖሊሲ አማራጭ በማቅረብ ረገድ ያሉበት ድክመቶች አከራካሪ አይደሉም። ‹‹ድክመቶችን ለማረምም ሆነ ዘመናዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲመጣ የኛ ትውልድ የተሻለ አሰተዋጽኦ ማበርከት ይችላል›› ብለን እንቅስቃሴ ጀምረን ነበር። ቅጥ አምባሩ የጠፋውን ከስም ያልዘለለ ዴሞክራሲ ወደ ተግባር በማምጣት ሕዝቡ መብቱን በሚገባ እንዲያንሸራሽር የሚያደርግ ሥርዓት እንዲመጣ ግፊት ስናደርግ ነበር። ይህን ስናደርግ ግን ዋጋ እንደሚያስከፍለን እናውቀው ነበር።

ይህ አቋምህ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ውስጥም እያለህ የነበርህ ነው?

ከገዢው ፓርቲ ጋር በቆየሁባቸው ሁለት ዓመት በማይሞሉ ጊዜያት ውስጥ ለአገር አይጠቅሙም ብዬ የማስባቸውን መሠረታዊ ችግሮች በልዩ ሁኔታ አውጥቼ እታገልባቸው ነበር። በዴሞክራሲ ማዕከላዊነት ስም ግለሰቦች በአምባገነንነት የሁሉም ነገር አድራጊ ፈጣሪ ሆነው የወጡበት እና መሠረታዊ የፖሊሲ ችግሮች ያሉበት ፓርቲ በመሆኑ እነዚህ እንዲቀረፉ መከራከሪያዎቼን አቀርብ ነበር።

እነዚህ ችግሮች እንዳሉ ካወቅክ ለምን ፓርውን ተቀላቀልክ?

አንድን ነገር ተሳስቷል ብለህ የምታስብ ከሆነ ስህተቱን ለማስተካከል የምትችለው የሂደቱ አካል በመሆን ነው። ሌላው ደግሞ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን ከመቀላቀሌ በፊት ይሄ ነው የሚባል የፖለቲካ የጀርባ ታሪክ አልነበረኝም።

ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ ከነበርኩበት ደቡብ አፍሪካ ወደ አገር ቤት የተመለስኩት የምርጫ ክርክር በተጋጋለበት በ1997 አጋማሽ ላይ ነበር። በወቅቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የለውጥ ሥርዓቱ አካል እንደነበረው ሁሉ እኔም የዚሁ ደጋፊ ነበርኩ። ቅንጅት ከተፈረካከሰ በኋላ ወደ መደበኛ የራሴ ሕይወት ተመልሼ እኖር ነበር። በ1999 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ‘የአዲስ አበባ ፎረም’ በሚመሠረትበት ጊዜ እዚያ እንድገኝ በፎረሙ ተጋብዤ ቆይታ ካደረግኩ በኋላ በ2001 ዓ.ም. ፖርቲውን እንድቀላቀል ጥያቄ ሲቀርብልኝ የፓርቲውን ፕሮግራም እና ፖሊሲ ዓይቼ ሁለት ዓመት ላልሞላ ጊዜ አብሬያቸው ቆይቻለሁ።

ከገባሁ በኋላ የመሬት ፖሊሲን ጨምሮ የማልስማማባቸውን ጥያቄዎች ማንሳት የማይሞከር፣ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍልና የሚያስፈርጅ መሆኑን ተረዳሁ። ሀሳቤን ከመቀበል ይልቅ ጫፍ የመርገጥና የማግለል ሁኔታዎች ገጠሙኝ። በሂደት የፓርቲው ዓላማ ሄዶ ሄዶ ኢትዮጵያን ለአደጋ ያጋልጣታል የሚል ድመዳሜ ላይ ስደርስም በዚህ ፓርቲ ውስጥ ከዚህ በላይ መቆየት በታሪክም ተጠያቂ ያደርጋል ብዬ ስላመንኩ በገዛ ፈቃዴ ለቅቄ ወጥቻለሁ።

ቅድም ወዳቋረጥከው ጥያቄ ልመልስህ። ወደ ተቃውሞው ክበብ…

የተቃውሞ ጎራው አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረሱ በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት እንችላለን። በገዢው ፓርቲ ጡጫ ተደብድቦ የተፈረካከሰ ድርጅት ባለበት አገር ሙሉ ለመሉ የፖርቲዎቹ ችግር ነው የሚል ድምዳሜ ላይ አልደርስም። ቅድም እንዳልከው በማሰላሰያ ጊዜዬ ሳስባው ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ሀሳብ ይዤ የነበረ ቢሆንም ‹‹ከእነማን ጋር ነበር የተሰለፍኩት?›› የሚል ጥያቄ ያጭርብኛል።

እዚህ ላይ ላቋርጥህና… ሀብታሙ አጠገቡ (አንድነት ፓርቲ ውስጥ) በነበሩት አጋሮቹ [አላቸው ብሎ በሚያምነው] ለዘብተኛ አቋም እና የፖለቲካ አስተሳሰብ ደስተኛ አልነበረም፤ ብዙዎቹ የአመራር አባላት በወጣቶች መተካት አለባቸው የሚል አቋምም ነበረው ይባላል።

ይህ በተቃውሞ ጎራው ብቻ ሳይሆን በገዢው ፓርቲ በኩልም ያለ ችግር ነው።

ለጥያቄዬ ቀጥተኛ ምላሽ ስጠኝ። [ሳቅ]

ልመጣልህ ነው። በገዢውም ሆነ በተቃዋሚዎች መሀከል መሠረታዊ ከሚባሉ ችግሮች አንዱ በስልሳዎቸ አደገኛ የተተበተበ ፖለቲካ ውስጥ የተጠመዱ ሰዎች ሁለት ጫፍ ላይ ቆመው የማይታረቅ ልዪነት ይዘው የሚሄዱ መሆናቸው ነው። ፍፁማዊ የሆነ ጫፍ የረገጠ ጥላቻ ይዘው ስለሚሄዱ በማንኛውም መልኩ ሊገናኙበት የሚያስችል ዕድል የለም።

ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት መምጣት አለበት ብለን ለተነሳን ሰዎች ሁለቱም መንገድ አጣብቂኝ ነው። ገዢው ፖርቲ የተሻለ አስተሳሰብ ይዘን ስንመጣ ሕዝቡ ሊከተለን ስለሚችልና ያየዝነው አማራጭ ከግራ ዘመሙ ወደ መሀከል የመጣ ስለሆነ ሁሉንም ሕዝብ [የግል ሆነ የቡድን መብት ጠያቂውን] የሚያቻችል በመሆኑ በሁለቱም ወገን ስጋት ሆነን ታየን።

ቀጥታ ወደ ጥያቄህ ስመጣ… በተቃውሞው ካምፕ ውሉ ያለየለት ስብስብ አለ። የስልሳዎቹ ትውልድ ያረጀ አመለካከት የያዙ ሰዎች ነበሩ። አንድ ጫፍ ላይ ከመቆም ውጪ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ወደፊት ሊገፋ የሚያስችል፣ ሊከፈል የሚገባ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ አልነበሩም።

ወደፊት እየተራመድን ሕዝቡን ማሰለፍ ስንምጀምር ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. እንደተለየ ጠላት ዓየን። የማይገባንን ስም ሰጥቶም ወደ ወኅኒ ቤት ጣለን። ተቃዋሚው ጎራ (አጋሮቻችን) ደግሞ ነፋስ እንደመታው የሳሙና አረፋ ብትንትናቸው ጠፍቶ ወደሚገቡበት ገቡ።

ሀብታሙ ችኩል ነውለውጥ በአንድ ጀምበር (በአጭር ጊዜ) የሚመጣ ይመስል እንቅስቃሴው ስሜታዊነት ይታይበት ነበር ይሉሀል ብዙ የዳያስፖራ ሚዲያዎች ‹‹ታሪካዊ›› ሲሉ በተቀባበሉት የሰላማዊ ሰልፍ ንግግርህ ላይ ‹‹እመነኝ ኢሕአዴግ ይወድቃል›› እና ሌሎችም መልዕክቶችን በስሜት መናገርህን በማሳየነት የሚያቀርቡት አሉ።

በሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ያሰማኋቸው መፈክሮች በሙሉ ከችኩልነት የመነጩ ናቸው የሚል እምነት የለኝም። የምናስተላልፋቸው መልፅክቶች ሁሉ በፓርቲ ውይይት ላይ ቀርበው የፀደቁ ናቸው። ፓርቲው ሳያውቀው የተካሄደ ሰልፍ እና መፈክር አልነበረም።

አገላለፅ ላይ እንደ ሰዉ ማንነት ይለያያል። በርግጥ አገሬ እና ሕዝቤ ያሉበት ሁኔታ የሚፈጥርብኝ ስሜት አለ። የፍትሕ ሥርዓቱን ከለላ አድርገው ጉልበታቸውን ለሚያሳዩ ሰዎች ሕዝብ ሁሌም አሸናፊ እንደሆነ ደጋግሜ መልዕክት ማስተላልፍ እፈልግ ነበር።

ለውጥ በአንድ ጀምበር ሊመጣ እንደማይችል በሚገባ የምገነዘብ ሰው ነኝ። ፈረንጆቹ ‹‹Think big, Start small & Act now›› ይላሉ። የኔም አካሄድ ችኮላ አልበረም። በሰፊው አስበህ፣ ከትንሹ አሁን መጀመር አለብህ። ዴሞክራሲ ሂደት ነው የሚባለው ዛሬ መሥራት ያለብህን እያደረግክ ነው።

ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የሚሳሳተው እዚህ ላይ ነው። 25 ዓመት አስቆጥሮም ‹‹ዴሞክራሲ ሂደት ነው›› ይልሀል። ከ100 ዓመት በኋላም ሂደት ነው ሊልህ ነው። ሂደቶች ውስጥ ማሻሻል ያለብንን እያሻሻልን፣ መለወጥ ያለብንን እየለወጥን መጓዝ አለብን። አንድም ለውጥ ሳታመጣ ባለህበት ቆመህ ዴሞክራሲ ሂደት ነው ማለት የለብህም።

ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ብዙ ዓመት አስቆጥረዋል። ከኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. በማይተናነስ ሁኔታ የሚሰነዝሩት ሀሳብ አንተን ወደ ዳር የሚገፋ ነው። እነሱን የማይመስል የለውጥ ሀሳብ አሊያም ከሥልጣናቸው የሚያነሳ ሀሳብ ከመጣ ‹‹የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ቅልብ ነው›› በማለት ተልዕኮ ተሰጥቶህ እንደመጣህ አድርገው ያዩሀል። ይህንን አሮጌ አስተሳሰብ የያዘ ኃይል (ገዢው ፓርቲን) ተጋፍተህ ስትሠራ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ‹‹አሸባሪ›› ነው ይልሀል።

የቀድሞ አንድነት ፓርቲ ይዞት በነበረው አመለካከት ‹‹አብዛኛውን የትግል ሂደት ወደ መሀከል አምጥተን መግፋት እንችላለን›› የሚል እምነት ስለነበረኝ በትልቅ ቁርጠኝነት እየሠራሁ ነበር። በፓርቲያችን ባለፉት አምስት ዓመታት ያልነበሩ ፖሊሲዎች በአዲስ መልክ ተንትነን እያቀረብን ነበር። አንድነት እኔ በደረስኩበት ጊዜ እጅግ ለአገር የሚጠቅሙ ከምላቸው ውስን የፓርቲው አባላት (ወጣት እና የለውጥ ኃይል ከሆኑት) ጋራ ሆነን የፖሊሲ አማራጮችን ቀን ከሌት እየሠራን ነበር። ወደ ሕዝቡ ለመቅረብ ሕዝቡን የምናገኝባቸውን መድረኮች እናዘጋጅ ነበር። በርካታ ሰላማዊ ሰልፎችን በተለያዪ ከተሞች አድርገናል። በዚህ ሁሉ እንቅስቃሴ ውስጥ አንዲት ድንጋይ ተወርውራ፣ ሁከት ደርሶና ሰው ተጎድቶ አያውቅም። ግን ሽብርተኛ ተብለን ተከሰስን።

‹‹እመነኝ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ይወድቃል›› ማለቴን አሁንም እደግመዋለሁ። ደርግም ወድቋል ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ም ይወድቃል። መውደቅ ካልፈለገ አፋጣኝ ሥር ነቀል መሠረታዊ ለወጥ ማምጣት ነው። ‹‹ይህን ለማድረግ የሚያስችል ቁመና አለው ወይ?›› ካልከኝ መልሴ ‹‹የለውም›› ነው። ስለዚህ ይቺን አገር ለመምራት የሚችል፣ የነበሩትን ነገሮች የሚንድ ሳይሆን ባሉት ላይ የሚጨምር ጥሩ ያልሆኑትን የሚያሻሽል፣ ዘመናዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚያመጣ፣ ሕዝቡ ተስፋ የሚያደርገውን ትክክለኛ ለውጥ ማሳየት የሚያስችል ፓርቲ መፈጠር አለበት ብዬ አምናለሁ። የምታገለውም ለዚህ ነው።

ከአሁን በኋላ ትግሉ እንዴት፣ የትና መቼ መደረግ አለበት ብለህ ታስባለህ?

አንድ ዓመት ከሰባት ወር የጥሞና ጊዜ ቢሰጠኝም ደጅ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችል ዕድል አልነበረኝም። ስለዚህ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ጊዜው ገና ነው። መፈተሽ ያለበት ነው። ቀጣዩን የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ መወሰን ያለበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሆነ ወደ ለውጥ ሊመራው የሚችል አማራጭ ኃይል ሕዝቡ ይፈልጋል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ጥረቴ ይቀጥላል። ስለታሰርኩ፣ ስለተደበደብኩ፣ ጉዳትና ጫና ስለደረሰብኝ በቃኝ (ቻዎ) ብዬ አገሬን እና ሕዝቤን አልተውም። አገርህን እና ሕዝብህን ለማን ትተዋለህ?

ትግሉ ርዕዮተ ዓለማዊ መሆን አለበት፣ በዚህም ለውጥ ይመጣል ብለህ ታምናለህ?

ዘመናዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማለት ታዲያ ምንድን ነው? የሀሳብ ትግል ማለት  ነው። የሀሳብ ትግል ከምን ይጀምር? ወዴት ይሂድ የሚለውን ሞክረነው አሁን ለደረስንበት ደረጃ አድርሶናል። በቀጣይ ምን መሆን አለበት? የሚለውን ጊዜ ወስደን ማየት አለብን።

ስለታሰርኩ የሄድኩበት መንገድ አያዋጣም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ በጣም ችኩል መሆን ነው። አገዛዝ መጣል፣ መለወጥ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት ምንድን ነው? ዕጣ ፈንታዋ እንዴት ነው መወሰን ያለበት? የሚለውን ሁሉም ባለድርሻ አካላትን ያካተተ እንቅስቃሴ እና ጥናት ይፈልጋል። ኢትዮጵያዊ በርካታ ምሑራን በዓለም ዙሪያ ያላት አገር ስለሆነች ከችግር መውጫ መንገዱን አጥንተው ማቅረብ ይቸግራቸዋል ብዬ አላስብም።

መቼም እንደዚያ በጥልቅ ስሜት እና በቁርጠኝነት ትታገል የነበረው ራስህን ብቻ ነጻ ለማውጣት እንዳልሆነ አስባለሁ፡፡ ‹‹ትግሉ ለህዝብ ነው›› የምትለኝ ከሆነ፣ ሕዝብ፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ተዕጽኖ ፈጣሪ ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲታሰሩ ለከፈሉት መስዋትነት ዋጋ ሰጥቶ ከጎናቸው የማይቆመው ለምን ይመስልሃል?

እኛ አገር እንደ ባህል ያደገ ነገር ቢኖር… ጀግና ከፊት ይቀድምና የኋለኛው ይበተናል፡፡ አጼ ዮሐንስ የሚመሩት ሠራዊት ማህዲስቶቹን አሸንፎ ነበር፡፡ በጦርነቱ ማጠቃለያ ላይ ግን አጼው ሲመቱ አሸንፎ የነበረው ሠራዊት ንጉሡ ስለ ሞቱ ብቻ ወደ ኋላ ተመለሰ፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ውስጥ መሪ ብሎ ያመነውን ሰው የመከተል፣ መሪው የለም ብሎ ሲያስብ የመበተን ሁኔታዎች የተለመዱ ስለሆኑ ነው፡፡ አንድ ፓርቲ አመራር አባላት ላይ መንግሥት እርምጃ ወስዶ ሲታሰር ሕዝብ የመበተን በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እንደ ባህል እየተወራረሰ መጥቷል፡፡

ከሁሉ በላይ የሚገርመው ግን ለትግል አብረውህ የወጡ አካላት አንተ ስትታሰር ‹‹እኔ ተተክቼ እሠራለሁ›› የሚል ቁርጠኝነት ማጣታቸው ነው፡፡ ይህም ‹‹ከማን ጋር ነው እየታገልኩ የነበርኩት?›› የሚለውን ቆሜ እንዳየው አድርጎኛል፡፡ ምን ዓይነት ዋጋ ማን እንደከፈለ፣ ማን ከማን ጋር ይታገል እንደነበረ በሚገባ አይተንበታልም፡፡ ይህ የሚያሳየው የዴሞክራሲና የትግል ባህላችንን አለማደግ ነው፡፡ እንደ ሕዝብ ግን ከመረጃም እጥረት የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡

ስለዚህ ሕዝቡን ማብቃት ዋነኛ ተግባር ሊሆን እንደሚገባው …

አዎ! ሕዝቡን ማብቃት ላይ የቀሩ ሥራዎች መኖራቸውን ይጠቁማል፡፡

 ባለፈው ቂሊንጦ ላይ አውርተንበታል፡፡ አሁንም በግልጽ እንድትነግርኝ እፈልጋለሁ፡፡ ከታሰርክ በኋላ ከቀድሞ አንድነት ፓርቲ የትግል አጋሮችህ ባገኘኸው የአጋርነት ግብረ መልስ ደስተኛ ነህ?

በጣም ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ በጅምላ ‹‹ሁሉም የትግል አጋሮቼ›› ብዬ ከፈረጅኩት አደገኛ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እውነተኛ የትግል አጋርነት ያሳዩኝ አንድም ሆነ ሁለት አባላት አሉ፡፡ በርካቶቹ ግን ‹‹ከማን ጋር ነው እየታገልኩ የነበርኩት?›› ብዬ እንድደነግጥ ያደረጉኝ ናቸው፡፡ እኛ ዋጋ ወደከፈልንበት (እስር ቤት) ስንሄድ በጽናት ይቆማሉ ብለን የጠበቅናቸው ጉልበታቸው ቄጤማ ሆኖ ሲልፈሰፈሱ ዓይተናል፡፡ በጣም በጣት የሚቆጠሩት ደግሞ እኔንም ቤተሰቤንም ለማጽናናት የሚችሉትን ጥረት አድርገዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን አንድነት ሠርተፍኬት እና ማኅተም ሲቀማ ወደ ቤታቸው የሚገቡ አመራር አባላት ጋር ስታገል መክረሜ ገርሞኛል፡፡

ምን ማድረግ ይችሉ ነበር ትላለህ?

ሠርተፍኬት ብትቀማም ሕዝብ አልተወሰደብህም፡፡ ስለዚህ ‹‹ሰላማዊ ትግል አበቃ›› ብለህ ወደ ቤት መግባት አልነበረብህም፡፡ እኔ ችኩል የምባለው እንደዚህ አይነት ውሳኔ ብወስን ነበር፡፡ ደጅ ያሉ ሰዎች ግን አንድ ፈተና ቢጋረጥባቸው ከዚያ መውጫ መንገድ ለማዘጋጀት መጣር እና መመካከር ይገባቸው ነበር፡፡ አንድነት ለመፍረሱ የገዢው ፓርቲ ኃይል እና ጡንቻ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እኛም ለመፍረስ የተዘጋጀን ስለነበርን ነው፡፡ በአንድ ጀምበር አባላት ብለን የስብሰብናቸው ሰዎች መልካቸውን ቀይረዋል፡፡ ይሄም የአባላት ጥራት ችግር መኖሩን፣ የዓላማ ጽናት እና ቁርጠኝነት ላይ ችግር እንደነበረ የሚያሳይ ነው፡፡ በጥቅሉ ሰዎች በየእስር ቤቱ ተጥለው ሳለ ተበታትኖ ወደ ቤት መግባት መፍትሄ ሊሆን አይችልም፤ ተገዳዳሪ ጉልበትህን መጨመር እንጂ፡፡

አንባቢያን የሀብታሙ ቀጣይ የፖለቲካ ተሳትፎ ምን ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ ቢያነሱ ምላሽህ ምን ይሆናል [ክሱ እስኪያበቃ ከአገር እንዳይወጡም ገደብ ተጥሎባቸዋል]

በመሠረቱ ትግል ለማድረግ ከአገር መውጣት አይጠበቅብኝም፡፡ በአገሬ ውስጥ ነጻነት ማጣቴ እንጂ ከአገር እንዳትወጣ መባሌ አያሳስበኝም፡፡ በተለያዩ ጊዜ ሁለት ሦስቴ ከአገር ወጥቼ መመለሴን ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ከአገር መውጣት ለእኔ አጀንዳ አይደለም፡፡ ስለታሰርኩ ልገለፀው የማልችለው ከባድ መከራ ስለደረሰብኝ [ወደፊት በጣም አብራራዋለሁ]፡፡ ከአሁን በኋላ ብዬ የምቀይረው አቋም የለኝም፡፡

ቀጣዩ እንቅስቃሴዬ ፓርቲ ፖለቲካ ነው፣ ጋዜጠኛ መሆን ነው፣ አክቲቪስት ሆኜ ወይስ ልጆቹን የሚያሳድግ አባት ሆኜ ልቀጥል የሚለውን በደንብ ማየት እና መገምገም ይጠበቅብኛል፡፡ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩበት፣ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚታዩበት ኢትዮጵያ እስክትፈጠር ድረስ በሚል ፍራቻ እጄን ሰብስቤ አልቀመጥም፡፡ በተነሳሁበት የሰላማዊ ትግል አውድ ተስፋ ቆርጬበታለሁ የምልበት ደረጃ አልደረስኩም፡፡ በአንድ ሙከራ ስለታሰርኩ ወደኋላ አላፈገፍግም፡፡

ማመስገን ያለብህ ብዙ ሰዎች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ‹‹አዲስ ገጽ››ን ጨምሮ ሁሉንም የኅትመት ውጤቶችን፣ ጉዳያችንን የተከታተሉትን ሁሉ እና ቤተሰቦቼን አመሰግናለሁ፡፡ በቅርበት ያሉ ሁሉ ሊረዳው እንደሚችለው ባለቤቴ ቤተልሔም አዛናው ከባድ ዋጋ ከፍላለች፡፡ ሕጻን ልጅ ማሳደግ፣ ስንቅ ይዞ መመላለስ፣ የፍ/ቤትና የሚዲያ ጉዳይ መከታተል …ብቻ ሁሉንም ሆናለች፡፡ ማንም እንደ እሷ የለም፡፡ ብዙ ጫና ቢደርስባትም ሁሉን ማለፍ ችላለች፡፡ የትዳሬ ብቻ ሳይሆን የትግሌም አጋር ነች፡፡ ስለዚህ ከእግዚያአብሔር ቀጥሎ የማመሰግነው እሷን ነው፡፡ ጠበቃ ተማም አባቡልጉን እና ጠበቃ አምሐ መኮንንን ለማመስገን ቃላት የለኝም፡፡ አቶ አምሐ የፍ/ቤት ጉዳይ መከታተል፣ ቂሊንጦ መመላለስና ቤተሰቤን ለመከታተል ብቻ ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡ በውጪ ያሉ ኢትዮጵያንንም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡

 

 

 

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *