(ክፍል – 2)
ዩሐንስ ሞላ
[በክፍል 1፥ ለውጥ እንዲዘገይ አስተዋጽኦ አድርገዋል ተብለው ከታመኑ ጉዳዮች መካከል፥ የለውጥ አራማጅነትን ህልም ይዘው እየተንቀሳቀሱ፣ ‘የራስን የአስተሳሰብ አድማስ ለመለወጥ መዘግየት’፣ ‘ለራስ የሚሰጥ አጉል ግምት’፣ ‘በለውጥ ሂደት ውስጥ ዕውቅናን ማሠስ’፣ ‘ግልብነትና ትኩስ ትኩሱን ቃርሚያ’’ እና ‘ሰድቦ ለሰዳቢ መስጠት’ የሚሉ ንዑስ ርዕሶችን አንስተን በወፍ በረር ለማየት ሞክረናል። እነሆ ዛሬም በቀጣዩ ክፍል ሌሎቹን እንዳስሳለን። ምንም እንኳን ፅሁፉ በሁለት ክፍል የተወሰነ ቢሆንም፥ በየቤታችን እና ልባችን ውስጥ፥ ጥቃቅን መስለው ለውጥን በማዘግየት ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ብዙ ጉዳዮች ይኖራሉና፣ ራሳችንን እንድንፈትሽ፣ አካባቢያችንን እንድናጤን፣ እና ሁኔታውን ለመለወጥ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ይሁን።]
ርካሽ ቡድንተኝነት
በተለይ “ያወቁ፣ የነቁ” ናቸው ተብለው ቦታ የሚሰጣቸው ሰዎች፥ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ርካሽ ቡድንተኝነት ውስጥ ሲጠመዱ ይስተዋላል። የቡድንተኝነቱ ርኩሰት፥ ሌሎችን ለመጉዳትና ለማግለል፣ ፊትና ዕድል ቢሰጣቸው የለውጥ ምሶሶ አጠናካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ስለሚያጠቃ ነው። ባነበብናቸው አንድ ሁለት መጽሐፍት ውስጥ ተከልለን፥ ሌሎች ሰዎች ላይ ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት እናደርሳለን። ጥራዝ ነጠቅ የእውቀት ጋሻችንን ይዘን፥ የጥፋት ጦራችንን እንመዛለን። ለመነሳት የሚጥሩ ነፍሶችን፣ ለማወቅ የሚታትሩ ልቦችን፣ ግንዛቤያቸውን ለማስፋት የሚታገሉ ብላቴናዎችን ብቅ ሲሉ ጠብቀን፥ አቁስለን ጥልቅ እናደርጋቸዋለን። “ወፌ ቆመች” ላይ ያሉ ሰዎችን በደረት እንዳይድሁ ሳንካ እንሆንባቸዋለን። ሀሳባቸውን ሊገልጹ ሲሞክሩ፥ “እስኪ ዝም በሉ” ይባላል። የሆነ ነገር ለመጻፍ ሲጭሩ እንኳን፥ “ዘንድሮ ማንም እየተነሳ ይፈነጭበታል” ብለን የማሸማቀቅ ስራ እንሰራለን። ያው ጉዳዩም ርካሽ፣ ቡድንተኝነቱም ተራ ነውና፥ ደቀመዛሙርቶቻችን ያቀነቅኑልናል። በዚያ ሂደት ውስጥ፥ የለውጥ ሀዋርያት ቁጥሮችን እንቀንሳለን።
እኔ ያልኩት ካልሆነ… (ፍረጃ)
ጥቃቅን መንግስተኝነትም ሌላው ችግራችን ነው። በየቅያሱ ከመንግስት የምንጠይቃቸውን መብቶች እኛው ከወዳጆቻችን እንገፋ’ለን። “እኔ ብቻ ላውራ። የእኔ ብቻ ነው ልክ።” የሚል ሰው፥ መንግስትን “የመናገር መብቴን አትንጠቀኝ። አስተያየት ልስጥበት።” ይለዋል። ደግሞ በመንግስት ቂመኝነት የሚማረር ሰው፥ ወዳጁ ላይ ስር ሰደድ ቂም ይቋጥራል። …ደግሞ ወዲያ “ለውጥ፣ የሀሳብ ነፃነትና የምርጫ መብት” ጃዝ ገለመሌ እንላለን። ወዲህ ሰዎች የወደዱትን ስለመረጡ፥ ቅሬታን ከመግለፅ ባለፈ …በራስ የመስተሀልይ ልክ፣ በቀደመ ታሪክና በግል ፍላጎት ብቻ መዝነነው ተመራጮቹንም መራጮቹንም ባንድ ላይ እንወቅጣለን። ወቀጣችንን የሚወቅሱ ቢኖሩም የነገር ሰንኮፋችን እጥፉን ይዘረጋል። የሀሳብ ነፃነትም ሆነ ለውጥን መናፈቅ በመከባበር መታጀብ እንዳለበት! አለዚያ ይሄድ ይሄድና አንገቱ ጋር ሲደርስ ሲጥ ብሎ፣ እምነት ማጣት ተከትሎት፣ ‘ብዬ ነበር’ መባባልና እርስበርስ መወቃቀስን እንጂ ምንም አያስተርፍም።
የትልልቅ ምስሎች ልክፍት
ትንንሽ ሁኔታዎችንና የለውጥ መንደርደሪያዎችን አናደንቃቸውም። ልባችን ትልልቅ ለውጦችን በማሰብ ተጠምዶ፣ በመንገዱ ላይ የሚያገኛቸውን ትንንሽ ለውጦች ስለማይደነቅባቸው ሀሞቱ ቶሎ እንዲፈስ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። የማመስገንን እና የመደሰትን ጉልበት ብዙዎች እንስተዋለን። ስለዚህ ቶሎ ይደክመናል። ልባችን ትልቁን ነገር ብቻ ነውና የሚያየው፥ እዚያ ለመድረስ ያደረግናቸው ጥረቶች ምን ያህል ፈቅ እንዳደረጉን ሳናስብ፥ እዚያ አለመድረሳችንን እንረግማለን። በንጽጽር ውስጥ ሆነን ራሳችንን እንወቅሳለን። ሌሎች ሰዎች የነበሯቸውን እድሎችና፥ የማርያም መንገዶች ሳናውቅ፣ ቀድመውን ስለሆኑት ነገር እንገረማለን። ራሳችንን እንረግማለን። በአንጻሩ ደግሞ፥ ትንንሽ ምስሎችን ብቻ ይዘን እየተንቀሳቀስን በትንሽ ውጤቶች ብቻ ልባችን አርፎ ቁጭ ካለም ሌላ ችግር ነውና ሚዛኑን መጠበቅ ያሻል።
ውሻ በቀደደው…
ሌላው ማኅበረሰባዊ ችግራችን፥ በተቀደዱልን ቦዮች ሁሉ የመፍሰስ አባዜዎች ነው። ያም ይመጣል አጀንዳ ያቀብለናል፣ ተቀብለን እናቀነቅናለን። ደግሞ አጀንዳ ሲቀየርልን ቀይረን እንቀባበለዋለን። ተደጋግሞ የሚጠቀሰው “አስማተኞች እና ፖለቲከኞች የሰዎችን ትኩረት ከሚያከናውኑት ነገር ላይ ትኩረቶችን ማስቀየስ መፈለጋቸው ያመሳስላቸዋል” የሚለውን የናይጄሪያዊውን ደራሲ ቤን ኦክሪን አባባል ደጋግመን ብንጠቅሰውም፣ ጭራሽ አናስተውለውም። ስለዚህ በአስማተኞች እና በፖለቲከኞች አጀንዳ ማስጠምዘዝ መርሀ ግብር ሰለባ እንሆናለን። ሌሎችን የመከተል አባዜም አለ። “እነ ኧከሌ ካሉማ” ብለን ልክነትን በሰዎች እንመዝንና እንደናበራለን።
ዘርፈ ብዙ ማኅበረሰባዊ “ሳቦታጆቻችን”
የጎረቤት ዛፍ ጥሩ እያደገ፣ ቅርንጫፉ እየሰፋና እያበበ ሲሄድ …ከመደሰትና ያለውን የጋራ ጥቅም ከማሰብ ይልቅ፣ በጋራ ለሚቆጋን ፀሐይ ጥሩ መላ መሆኑን ከመገንዘብ ይልቅ፥ “ቅርንጫፍሽን ሰብስቢልኝ። የልጆቹን ዐይን እየጠነቆለብኝ ነው።” ….“ማነሽ… አበባሽ ደጄን አቆሸሸው። ዛፉን ቁረጪልኝ።” ….“ግንዱ ግድግዳዬን ሊሰብረው ነው። ተኛብን እኮ! ኧረ ይሄ ነገር ባጭር ይቆረጥ።” ….“ስሩ ወደቤቴ ገብቷል። ቤቴን ያፈርስብኛል ንቀይልኝ ይሄን ዛፍ።” እሪሪሪ… ይባላል። የፈረደበት ቀበሌ አለ፥ ነጠላ ጎትተው ለነገር ቅያስ ያካልላሉ። “ምናምን አርጋበት እንጂ፥ ሰው ሲጫጫ ዛፏ ብቻውን የሚወዛ” የሚሉ ሀሜቶች ሊሰሙ ይችላሉ። – አገሩ የእኛ ነው! የተተከለው የምች መድኃኒት ቢሆን እንኳን፥ “ነገ ታምሜ እፈልገውም ይሆናል።” ብሎ መራራትም የለም።
ሰው ስራው ጥሩ ከተቀላጠፈ፣ ፍላጎቶቹን ማሟላት፣ ለውጡ ፊቱ ላይ መታየት ሲጀምርና “ስራ እንዴት ነው?” ሲባል፥ ረገጥ አድርጎ “ተመስገን” ማለቱ ሲሰማ፥ ዞር ተብሎ፥ “በጤናው ነው ብለሽ ነው? ጠንቋይ ቤትማ ሳይሄድ አይቀርም።” ይባላል። ደም ያቃቡ፣ ጉቦ ያቃበሉ ይመስል፥ “ጉቦኛ ነው ስልሽ።” …“በሰው ደም ነው ቤቱን የሰራው።” ይባላል። ሌላም ሌላም …ሀሜቱ ብዙ ነው። ማነፍነፉና መሰለሉም አይቀሬ ነው። ሀሜቱ መሰረት ያለው ሲሆን፥ ደህና። ማነፍነፉና መሰለሉም የወንጀልን ጫፍ ለመያዝ ሲታለም ሸጋ ነው። ነገር ግን፥ በዕለት ተዕለት ኑሮ ሀሜቱ የሚቆሰቆሰው የምንጠረጥራቸውን ተግባራት እኩይ መሆናቸውን በማሰብ የተነሳ ሳይሆን፥ ወዳጃችን ቀና ቀና ማለት ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ መሆኑ ነው የሚያሳዝነውና ለውጥ የሚያዘገየው።
አብረን ትምህርት ቤት ያልሄድነው ሰው፥ ስለሚያውቀን ብቻ፥ በትምህርት ሲሳካልን ቅር ይለዋል። ራሱን እየወቀሰ በንጽጽር ይለፋል። አምላኩን ሲያማርር ውሎ፥ ፀሎቱም “የኧከሌ አምላክ” ይሆናል፥ – የተሳካለትን ጎረቤቱን/ወዳጁን ስም ጠቅሶ። (ይህም በቅንነት ሲሆን ክፋት የለውም።) የምንሰራው አጥተን፣ ሰማይ ምድሩ ዞሮብን ስንንከራተት፥ መላ ያላማታን ሰው፣ “ምን በልተው አደሩ?” ብሎ ያልተጨነቀና ለእርጥባን ያላግደረደረን ሰው፣ ነቃ ነቃ ማለት ስንጀምርና የበለጥነው ሲመስለው ይበግናል።
በተለይ ግቢ የሚጋሩት ከሆነ፥ የጎረቤት ቤት መታደስ ለጸብ በቂ ምክንያት ነው። ከ “አሸዋው ግቢውን አቆሸሸው” እስከ “ድንበር ነክታችኋል” ድረስ ጸብ ለመጫር በተጠንቀቅ የሚቆመው ብዙ ነው። አንድ ሚስማር ሲመታ፥ ቀበሌ ተንጋግቶ ይመጣል። መቼም ቀበሌው ጎረቤት ሆኖ አይደለም… ጎረቤት ተሯሩጦ ሄዶ ጠቁሞ እንጂ። ለክፉ ጎረቤት የእኛ ቤት አለማደስ እንጂ፣ በእኛ ቤት ማደስ ተነሳስቶ የእርሱን እንዴት ሊያደርገው እንደሚችል ማሰብ ሞቱ ነው።
እንበልና፥ ግቢ ከሚጋሩ ሰዎች መካከል፣ አንደኛው በገቢ የማይጨነቅ ቤተሰብ ለውጥ ፈልጎ “ሙሉ ግቢውን ሲሚንቶ ላድርገው። መቼስ ከልኩ አያልፍም።” ብሎ ገንዘቡን አፍስሶ ሲሚንቶ ሲያስደርግ፥ ከጎረቤቶቹ መካከል ያንዱ አባወራ ልጁን ጠርቶ፥ “ካለሸር ሲሚንቶ ላድርገው አላለም። ምን እንደሚካሄድ ነቅተህ ተከታተል። እስኪ ዛሬ እንኳን ቁም ነገር ስራ። ነፈዝ!” ብሎት ሊሄድ ይችላል። ንፍገትን እንረግማለን። ስጦታዎችን እንጠራጠራለን።
ደግሞ የሚሰራና ጥሩ ላይ ያለ ወዳጃችንን፥ በመቆርቆር ስሜት፣ ስራውን ያቃናል፣ ለመልካምነቱ ሳንካ ነው ብለን ያሰብነውን ነገር ስንነግረው፥ ቅናት ነው፣ ምቀኝነት ነው፣ ይለናል። ቀና አስተያየት መስጠትም፥ ከምቀኝነትና ከተንኮለኝነት የሚያስደምር ነገር ነው። – አይገርምም፥ የእኛ አገር እንዲህ ነውና!
ሁልጊዜ አንጻር እንፈልጋለን። እኛ ማድረግ የማንችላቸውን ነገሮች፣ ወይም ለማድረግ እየቻልን ችላ ያልናቸውን ነገሮች፥ ሌሎች ሰዎች ሲያደርጉ ስናይ ዐይናችን ደም ይለብሳል። ደስታችንን ስንገልጽ እንኳን ካንገት በላይ ነው። ከዚህ በፊት፥ አንድ ወዳጄ “ሊስትሮ፥ ‘እኔም ሰፊ እሱም ሰፊ’ ብሎ ሰርጅን ላይ የሚቀናበት አገር” ብሎ ነበር። የችግሩን ስር ሰደድነት፥ ይህ ንግግር ፍንትው ያደርገዋል።
ብዙ ጊዜ ሰው ወዳጁን የሚለካውና የሚያዳንቀው በሐዘኑ ጊዜ ከጎኑ በመኖር ባለመኖሩ ነው። በእርግጥ ስናጣ አብሮን ያለ የክፉ ቀን ወዳጅ የልብ ነው። ስናዝን የሚያጽናናም ከየትም አይገኝም። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን “ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና።” የሚል ትምህርት አለ። (መጽሐፈ መክብብ 7፥2) ሆኖም እዚህም ላይ ቢሆን፥ ለቅሶ ደራሹ ስለሚማረውና በልቡ ስለሚያኖረው ነገር እንጂ፣ ለቀስተኛው ላይ ስለሚፈጥረው በጎ ነገር ብቻ ተጨንቆም አይመስልም። ያ ለቅሶ ደራሽ፥ በግብዣችን ወቅትም፥ ድግሱን ታድሞ ከመሄድ ባለፈ ‘የደስታችን ተካፋይነቱ’ ሊፈተሽ ይገባዋል።
ምሳሌውን ነው ‘ቤት፣ ጎረቤት፣ ጓደኛ’ ያልኩት እንጂ፥ ችግሩ በየዘርፉና በየሁኔታው ውስጥ የሚስተዋል ነው። ስለለውጥ ስናስብ ‘የደስታ ተካፋይነታችንን’ ልንፈትሸው ይገባል።
እንዴት ይሻላል?
“ላለፉት 33 ዓመታት፥ ሁልጊዜ ጠዋት ራሴን በመስታወት ውስጥ እየተመለከትኩ፥ እጠይቃለሁ ‘ዛሬ የሕይወቴ የመጨረሻው ቀን ቢሆን ኖሮ፥ ዛሬ ልሰራ ያሰብኩትን ነገር ነበር የምሰራው’ ብዬ ራሴን ደጋግሜ እየጠየቅኩኝ፥ ደጋግሜ ያገኘሁት መልስ ‘አይ! አልነበረም!’ ሲሆን፥ የሆነ ነገር መለወጥ እንዳለብኝ አውቅ ነበር።” ብሎ ነበር የአፕል ካምፓኒው ስቲቭ ጆብስ። የምር፥ ዛሬ የሕይወታችን የመጨረሻው ቀን ቢሆን ኖሮስ? ታላቁ ማርቲን ሉተር ኪንግም፥ “ሰዎች እንዲጋልቧችሁ፥ ጀርባችሁን ለምጣችሁ አትመቿቸው።” ብሎ ነበር። (በረከታቸው ይደርብንና!)
በማርቲን ሉተር ኪንግኛ እንሰነባበት! – “Change does not roll in on the wheels of inevitability, but comes through continuous struggle. And so we must straighten our backs and work for our freedom. A man can’t ride you unless your back is bent.”
እስኪ ጀርባችንን ቀና እናደርግና ጋላቢ ጨቋኞቻችንን እናንሸራትታቸው ዘንድ፥ አቋቋማችንን እንፈትሽ፣ ለውጦቻችን ስለዘገዩበት ጉዳይ እንጨዋወት።
ሰላም!
Leave a comment