‹‹ጭቆና እስካለ ድረስ የመብት ጥያቄዎችመልካቸውን እየቀያየሩ መምጣታቸው አይቀርም››
‹‹አገራዊ ጭቆናው በጠነከረ ቁጥር ፕሬሱ ከፊት ለፊት የመጀመሪያው ተመቺ ይሆናል››
soliana shimels
ሶሊያና ሽመልስ (ጦማሪ)

ለቃለ-ምልልሱ ፈቃደኛ በመሆንሽ እናመሰግናለን፡፡
እኔም አመሰግናለሁ፡፡
የዞን ዘጠኝ ጦማርያን እና ሦስት ጋዜጠኞች ከመታሰራቸው በፊት፣ ሲታሰሩ፣ በእስር ላይ እያሉ፣ ከእስር ከተፈቱ በኋላ የነበረሽን ስሜት እንዴት ትገልጪያቸዋለሽ?
ያው እስሩ የተጠበቀም ቢሆን፤ በጣም አስደንጋጭ ነበር። ምንም ያህል ሐሳቡ ቢኖርም፤ በተለይ በተግባር ሲመጣ በጣም ያደናብራል። በእስር ላይ እያሉ በጣም ብዙ የሚያስፈሩ ነገሮች ነበሩት። በመጀመሪያ ማእከላዊ ምርመራ ባሉበት ወቅት፤ በተለይ የአካል ደኅንነታቸው ሁኔታ በጣም ያሳስበኝ ነበር። በአካልም በአእምሮም በመጎዳት ከባዱ ጊዜ ያ ነበር። ከዚያ በኋላያለው ጊዜ በንጽጽር የተሻለ ነበር። ከወዳጅ፣ ቤተሰብ እና ዘመድ ድኅንነታቸውን መስማት መጀመሬ በጣም አጠናክሮኛል። በወቅቱም እነሱም በጣም በከፍተኛ ጠንካራ ሞራል ላይ ስለነበሩ፤ ከውጭ ሆነን የተቻለንን እየሞከርን ላለነው ጥሩ ብርታት ሆኖናል።
እስር ቤት፣ የታሰረውንም ከውጭ ያለውንም ወዳጅ ዘመድ በጣም ተጋላጭ እና ስሜታዊ ያደርጋል። እኔም በዛው ስሜታዊ ሒደት ውስጥ አልፌያለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች ታስረው ልንጠይቅ እና ልናበረታታ ሄደን የምናውቅ ቢሆንም፤ በራስና በራስ ሰው ላይ ሲደርስ በጣም ልዩነት አለው። እና በሕይወቴ በጣም ስሜታዊ የሆንኩበት ጊዜ ነበር። በጣም ፈታኝ ወቅት ነበር። የጓደኞቻችን የመፈታት ዜና ለእነሱ ከቀለለው በላይ ውጭ ላለነው ብዙ ነገሮችን አቅልሏል የምለውም ለዛ ነው። ብዙ ችግሮችና መስዋእትነቶች ቢከፍሉበትም፤ ዜናው እንደጓደኛ እና እንደቤተሰብ ለእኔ በግል በጣም ጫና እንደቀለለልኝነው የተሰማኝ። የቅርብ ጓደኛ ሆነህ ስታየው ዋናው የሚታይህ ነገር በሰላም መውጣታቸው እና ደኅና መሆናቸው ነው። ለእኔ ትልቁ ቅድሚያ የምሰጠው ነገርም በደኅና ያለምንም አስከፊ የአካልና የመንፈስ ጉዳት ቶሎ መውጣታቸው ላይ መሥራት ነበር፡፡ከሞላ ጎደል ስለተሳካም ደስ ብሎኛል።
ከጆማኔክስ ካሳዬ እና ከአንቺ ውጭ ሌሎቹ ታስረው ነበር፡፡ እና ጓደኞችሽን በአካል ለማግኘት አለመቻልሽ ሥነ-ልቦናዊ ጫና ይኖረዋልና እሱን ስታስቢው ምን ይሰማሻል? ጓደኞችሽ ከእስር ቢወጡም ከአስማማው ኃ/ጊዮርጊስ (ጋዜጠኛ) በስተቀር ከሀገር ለቀናቶች ወጥቶ መመለስ አሁንም አልቻሉምና ከድምፅ ልውውጥ ባሻገር በአካል ለማግኘት አለመቻልሽን ስታስቢውስ…?
እውነቱን ለመናገር በአካል አለመገናኘታችን በጣም ከፍተኛ ጉዳት ቢኖረውም፤ ከእስሩ ሁኔታ ጋር በጣም ተለማምጄ ስለነበር የአካል ርቀቱ ያን ያህል አልከበደኝም። ከአንድ ዓመት በላይ ሲታሰሩ ዋናው ደኅና መሆናቸው ነው እንጂ የራስህ ናፍቆት አይታይህም። ነገር ግን የመንቀሳቀስ መብታቸው መነፈጉ አሁንም ጭቆናው እና ጫናው መቀጠሉ በጣም ያሳስባል፤ የሚያሳዝንና የሚያናድድም ነው። መንግሥትም ቢሆን ይህንን ነገር ለምን አይተወውም እያልኩ ሁሌ እገረማለሁ። የተነፈጉት ዕድል ቢሰጣቸው ኖሮ ብዙዎች በአሁን ሰዓት ትምህርታቸውንና ያገኙትን የአቅም ማዳበር ሥልጠናዎች እየተከታተሉ ይሆን ነበር። ከእስሩ መልስ መንቀሳቀስ አለመቻላቸው በጣም የሚያስቆጭ እና በጣም የአቅም አልባነት ስሜት የሚፈጥር ነው።
አንቺም አንዷ ተከሳሽ ነሽና፤በአሁኑ ወቅት ያለው የፍርድ ሒደት በሶሊያና እይታ አንደምታው ምንድን ነው?
የፍርድ ሒደቱ እንኳ ቀልድ ነው። ብዙ የተባለበት ነገር ነው። ከእስሩ ቀን ጀምሮ ሒደቱን ለማጋለጥ እና ምንም ወንጀል እንዳልነበረ ለማሳየት ሞክረናል፡፡ የሚገርመው ግን ፍርድ ቤቱ ያንን ማንም የሕግ እውቀት የሌለው ተራ ሰው ራሱ የሚታየውን ክፍተት ለማየት አንድዓመት ከስድስት ወር ነው የወሰደበት። በዚህ ሒደት ተከሳሾች፣ ታሳሪዎች እና ጓደኞቻቸው ያለፉበት ስቃይ ሳይረሳ፤ የመንግሥት የሥራ ሰዓት፣ የአገር ንብረት፣ ጊዜ እና ገንዘብ በማይረባ ክስና የፍርድ ሒደት መባከኑ ያሳዝናል። ይህ በእኛ ክስ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ክሶች ላይ በተደጋጋሚ የሚታይ ነው።አሁን በተለይ ሕግ መማርን እስኪያስረግም ድረስ የፍትሕሥርዓቱ አሳፋሪ ሆኗል። ፍርድ ቤቶች በጣም ረጅም ጊዜ ወስደው ሰው ነጻ ነው ማለት ጀምረዋል። ሰው መለቀቁ ጥሩ ሆኖ፤ ያለወንጀል መንገላታቱ፣ መታሰሩ፣ መገረፉ፣ ቤተሰብ መሰቃየቱ፣ የአገር ንብረትና ጊዜ መውደሙ፤ ለፖለቲካ እስካዋጣ ድረስ ማንም ለአገር ሀብት እንደማያስብ ትልቅ ማሳያ ነው። ብዙ ጊዜ ጭቆናው ከመጠናከሩና በጣም አስከፊ ከመሆኑ የተነሣ፤ የፍትሕሥርዓቱ ውድቀት ላይ ነው ከማለትና የእስረኞች ስቃይ ላይ ከመቆዘም ውጭ እንደአገር ምን ማለት እንደሆነ ስንነጋገር አይታይም። የሚወጣው ገንዘብ፣ የወደቀ ሥርዓትንናቢሮክራሲውን መልሶ ተአማኒ ለማድረግ እንደአገር የሚወስደውን ጊዜ (ተሳክቶ ቢቻል እንኳ) ኢሕአዴግ ከሄደ በኃላ ራሱ የፍትሕሥርዓቱን መሥራት ትልቅ አገራዊ ራስ ምታት ነው የሚሆነው።
የወደቀስርዓትስትይ…?
የወደቀየፍትህስርዓትማለቴነው፡፡የፍትህስርዓትለአንድአገርበጣምወሳኝስርዓትነው፡፡አሁንባለውመንግስትደግሞበፍጹምከጥቅምውጪተደርጓል፡፡የፖለቲካውብቻሳይሆንኢ-ፖለቲካዊየሆኑጉዳዮችላይምየፍትህስርዓቱንየሚያምነውየለም፡፡ይሄንንለማስተካከልየስርዓትለውጥቢመጣእንኳንበጣምብዙጊዜየሚፈጅየቤትስራችንነውየሚሆነው፡፡ቢሮክራሲውንከማደስጀምሮእስከብቁእናነጻየህግባለሞያዎችማፍራትድረስበጣምብዙአገራዊስራይጠብቀናል፡፡ብዙጊዜአሁንያለውጥፋት(Damge)

ከስርዓትለውጥጋርበአንድሌሊትይቀየራልብሎማሰብዘበትነው፡፡በተለይፍትህስርዓቱላይደግሞየረጅምጊዜጉዳትመድረሱትኩረትተሰጥቶትውይይትላይሲቀርብስለማላይናእንደህግሰውምያይበልጥስለሚያሳስበኝነውማንሳትየፈለግኩት፡፡
በአሁኑ ወቅት ምን እየሠራሽ ነው? ከፌስቡክ መንደርም ጠፍተሻል፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው? ‹‹ጓደኞቿ ከተፈቱ በኋላ ጠፋች›› የሚሉም ሰዎች አሉና ምላሽሽ ምንድን ነው?
በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ ፕሮጀክቶች ላይ እሠራለሁ። በዓለም አቀፍ ደረጃበተለያዩ መድረኮች እየከፋ ስለመጣው የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እየተናገርኩም ነው። ከዚያ ውጭ ግን የጓደኞቻችንን እስር ተከትሎ የማኅበረሰብ ሚዲያውን እንደትልቅ መሣሪያ በመጠቀም ብዙ ስለቆየሁበት ትንሽ ጊዜ ለመስጠትና ‹‹ራሴን በትምህርትም መደገፍ አለብኝ›› በሚል ከፌስቡክ ራቅ ካልኩኝ ጊዜ ጀምሮ እዛ ላይ ትኩረት አድርጌ ነበር። አሁን እሱ አቅጣጫ የያዘ ይመስላል፤ ሀርቫርድዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተቀብለውኛል። የቀሩኝን ነገሮች አጠናቅቄ የሚቀጥለውን አንድና ሁለት ዓመት አሁን ከምሠራቸው የተለያዮ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ፣ ትምህርት ላይ ትኩረት አደርጋለሁ የሚል ሐሳብ ነው ያለኝ። ነገር ግን በተለያየ መልኩ ሥራዬን መቀጠሌ አልቀረም።ማኅበረሰብ ሚዲያ ላይ አለመሆኔና የእኔ ፊት ለፊት አለመታየቱብቻ ነው ልዩነቱ።
ሐሳብን የመግለጽ ነጻት በሶሊያና አንደበት እንዴት ይገለፃል?
የሕግ ሰው እንደመሆኔ፤ ሐሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትን ሕጋዊ ማእቀፍ መከበርን ባስቀድምም፤ ከሕግ መከበር ባለፈ ለአንድ አገር ወይም መንግሥት ችግሮችን ሁሉ መናገር መቻልና ሌሎች መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ መሠረታዊ እንደሆነ አምናለሁ። አሁን የምናየው ያለመግባባትና አገራዊ ውጥረት ከሚተነፍስባቸው መንገዶች አንዱ ሐሳብን በአደባባይ ሲወራና ውይይት ሲዳብር ነው። ዞን ዘጠኝ ብለን ስንነሣም ዋናሐሳባችን ውይይት እና የሐሳብ መንሸራሸርን መደገፍ ነበር። በሒደቱ ከሁሉ በላይ እኛ ተምረንበታል። በግልም በቡድንም ጥቅሙን ስለማቀውም ጭምር ነው ይህንን የምልህ።የምንሰጠው ብዙ እውቀት ኖሮን አልነበረም። ከሁሉ በላይ ግን በመናገር አስፈላጊነት ማመናችን ነው አሁን ያለው ዓይነት አስተዋፅኦ በአቅማችን ማድረግ የቻልነው።
ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የብዙ መብቶች መነሻ ነው።እሱ በመገደቡ፣ ብዙ ተያያዥ መብቶች እና አገራዊ ጥቅሞች ተገድበዋል። ሐሳብ መናገር ለችግሮች መፍትሔ ያስገኛል፤ ለውይይት ዕድል ይሰጣል፤ የተወጠሩ ጽንፎችን ያፍታታል፤ መንግሥትና ሕዝብን ያገናኛል። መልካም አስተዳደርም ማለት መንግሥት ሕዝብን ሲሰማ ማለት ነው፡፡ እናም መናገርና መጻፍን ከልክለህ፣ ‹‹መልካም አስተዳደር››፣‹‹ልማት›› በሚል ስም ቢቀየር፣ መነሻ የሆኑ መሠረታዊ መብቶች አብረው እስካልተከበሩ ድረስ፣ ዋጋ የለውም።
ሰሞኑን ስለመልካም አስተዳደር ሲወራ እሰማለሁ፤ መልካም አስተዳደር ማለት ሕዝብ የሚፈልገውን ነገር አውቆ ማድረግ ነው፡፡ ያንን ለማወቅ ዋናውና የመጀመሪያው መንገድ ደግሞ እንዲናገር መፍቀድ ነው፡፡ አትናገር ብሎ መልካም አስተዳደር ማለት ፍጹም ተቃራኒ ነገሮች ናቸው።ሐሳብን በነጻነትመግለጽ፣ ስንት ጋዜጣ አለ? ስንት ኮፒ ተሸጠ? ስንት የሬዲዮጣቢያ ተከፈተ? ከሚለው በላይ በጣም በጣም ሰፊ ማእቀፍ የሚጠቀልል ሐሳብ ነው።
ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ስላለው ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትና የነጻነት ደረጃ ንገሪን?
ሐሳብን በነጻነትየመግለጽ መብት በጣም ሐሳባዊ ተደርጎ ሲወሰድ አያለሁ። እኛ አገር መብቱን እንደቅንጦት የመቁጠር እና የጋዜጠኞች እና የጸሐፊያንጉዳይ አድርጎ የማየት ነገርም አለ። የጥቂቶች ስጋት ተደርጎም ይቀርባል። መብቱ አለ የለም የሚለው የሚያነጋግርም አይደለም። በተለይ ባለፈው 10 ዓመት የወረድንበት ቁልቁለት በጣም ግልጽ ነው። ፌስቡክ ላይ የተለጠፈ ጽሑፍ ሽብር እየተባለ ማስከሰስ በጀመረበት አገር የነጻነት ደረጃውን መናገር ራሱ አይቻልም።
በስደት የተማርኩት ነገር፤ የሠለጠኑ አገሮች የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመቀለድና የመጠየቅ መብታቸው ምን ያህል እንደጠቀማቸው ነው። ለአንድ የውጭ ዜጋ የእኛን ሁኔታ ብትነግረው አልገባ ሲለው ምን ያህል ጥልቅ ችግር ውስጥ እንዳለን ትረዳለህ። ‹‹ብዙዎቹ ጋዜጠኞች ታሰሩ››ሲባል እንደእነሱ ዓይነት ጋዜጠኝነት ተሠርቶ፣ የተደበቀ ተጋልጦ፣ ባለሥልጣናትን ተጠያቂ ለማድረግ ተሞክሮ ነው የሚመስላቸው። ፌስቡክ ላይ ‹‹መንግሥትን አልደግፍም›› ብሎ መጻፍ እስር እና ተያያዥ አደጋ እንዳለው ስትነግራቸው አልገባ ብሏቸው ተደጋጋሚ ማብራሪያ ይጠይቁኻል። ይሄ ምን ያህል ጥልቅና ለንግግር እንኳ የሚያስቸግር ጣጣ ውስጥ እንዳለን ያሳይኻል። ስደት ነገሮችን ለማወዳደር ብዙ ዕድል ስለሰጠኝ፤ በመታፈናችን የምናጣው ነገር ምን ያህል ጥልቅና ብዙ እንደሆነ ይበልጥ ተረድቻለሁ።
የዓለም የፕሬስ ነጻnት ቀን ሰሞኑን በተለያዩ የዓለም አገራት ተከብሯል፡፡ ቀኑን ባለሽበት ሆነሽ ያከበርሽበት ሁኔታ ነበር? በኢትዮጵያም ‹‹የሚዲያ ብዙኃነትን ያረጋገጠች አገር – ኢትዮጵያ›› በሚል መርሕ ቃል በመንግሥት በኩል ተከብሯል፡፡ ቃሉን እንዴት አየሽው? በዚህ ዙሪያ የምትይው ካለ?
ባለሁበት አገር ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀንን አላከበርኩም፡፡ ግን በኢትዮጵያ የዚህ መብት አለመከበር ሰለባዎችን (ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶችን) ፕሮፋይል የማድረግና የማስታወስ ዕድል ገጥሞኝ ነበር። በመንግሥት በኩል አከባበሩ ያው ቀልድ ስለሆነ ከቁም ነገርም አልቆጠርኩትም። እነሱ ሲቀልዱ እኔም ለቀልዱ እውቅና ባለመስጠት ነው የማልፈው።አንድም የመንግሥት ባለሥልጣን ሆነ ዜጋ መሪ ቃሉን ቁም-ነገር ነው ብሎ እንደማይቀበለው እርግጠኛ ነኝ። አንድ መሪ ቃሉ አገሪቷ ያለችበት ሁኔታ በትክክል ይገልጻል ብሎ የሚናገር ሰው ካለም ይገርመኛል። ያው ሥራ ስለሆነባቸው ልማታዊ መሪ ቃል መሞከራቸው መሰለኝ [ሳቅ]፡፡
በነገራችን ላይ፤በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን ‹‹መረጃ ማግኘት መሠረታዊ መብት ነው››በሚል መርሕ ቃልነው የሚከበረው። የመሪ ቃሎቹ ልዩነት በራሱ ከተቀረው ዓለም ጋር ያለንን ርቀት ያሳያል።
ዛሬም ድረስ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ይታሰራሉ፣ ይከሰሳሉ፣ በፍርድ ቤት ይንገላታሉ፣ በሰብዓዊ መብቶቻቸው በየእስር ቤቱ ይደፈጠጣል፤ እነዚህንና ሌሎች በርካታ ዘርፈ-ብዙ የሙያውን ተግዳሮቾችና ችግሮች እንዴት በጣጥሶ ማለፍ የሚቻል ይመስልሻል?
የሞያው ተግዳሮት በጋዜጠኝነት ባለሞያዎች ብቻ የሚፈታ አይመስለኝም። እስካሁንም ጋዜጠኞች ብቻቸውን ለመታገል መገደዳቸው ሥራውን አደገኛ ከማድረጉም በተጨማሪ፤ለዓላማው የሚቆሙለትን ሰዎች ቁጥር ትንሽ አድርጎታል። በሌላ ሞያ ላይ ያሉና መናገር አስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች እስካልተቀላቀሉ ድረስ፤ ለብቻው በጋዜጠኞች እና ተሟጋቾች ጥረት ብቻ የሚፈታ አይመስለኝም። በተጨማሪም መረሳት የሌለበት ነገር የጋዜጠኞች መብት ከሌላው የመብት ጥያቄ ጋር ተያያዥ መሆኑን ነው። የትልቁ አገራዊ ጭቆና አካል ነው።አገራዊ ጭቆናው በጠነከረ ቁጥር ፕሬሱ ከፊት ለፊት የመጀመሪያው ተመቺ ይሆናል። በተሻሻለ ቁጥርም ተጠቃሚ ይሆናል። እናም የጋዜጠኞች መብት እና የሚደርስባቸው ስቃይ ከአጠቃላይ አገራዊ የፖለቲካ ምኅዳሩ ጋርም ተያይዞ መታየት እንዳለበት መዘንጋት የለብንም። እንደመፍትሔ ግን ይህ ነው የሚባል አንድ መፍትሔ የለውም፡፡ አጠቃላይ የአገሪቷ የሲቪክ እና የሰብዓዊ መብት ሁኔታ እስካልተቀየረ ድረስ፤ ዋጋ ማስከፈሉ የሚቀጥል ይመስለኛል።
በፍርድ ቤት ከሀገር እንዳይወጣ እግድ ሳይወጣ ዜጎችን በነጻነት ወደፈለጉት አገር በሕግ አግባብ የመዘዋወር ነጻነታቸው በደኅንነት ኀይሎች ለምን ይቀማሉ? ከእስር የወጡ የተወሰኑ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና ጋዜጠኞችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ዘላለም ክብረት፣ ኤዶም ካሳዬ፣ ተስፋለም ወልደየስ … ከዚህ ጋር በተገናኘ ዘላላም የትምህርት ዕድም አምልጦታል፤ ለሽልማትም መገኘት አልቻለም፤ ባለሽበት ቦታ ሆነሽ ይሄ ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት እንዲወገድ ያደረግሽው ነገር ይኖር ይሆን ወይስ ልታደርጉ ያሰባችሁት ነገር አለ?
ቅድም እንዳልኩት ከእስሩ ቀጥሎ ከፍተኛ ችግር እየሆነ ያለው የቁም እስሩ ነው።ሥራ መፈለግ ከባድ ነው፡፡ እስካሁን የአራት ሰዎች የጉዞ ዕድል ተሰናክሏል።ለትምህርትም ለሽልማትም፤ እንዲሁም በፊት የምንሠራውን የአክቲቪዝምሥራ ለማጠራናከር በነጻነት መንቀሳቀስ አለመቻሉ በጣም ያሳዝናል። በተቻለ መጠን መግለጫዎች ወጥተዋል፤ በተለያየ አጋጣሚም መናገራችንን አላቆምንም። ብዙ ጊዜ ‹‹መንግሥት በቀለኛ እና ቂመኛ ነው›› ሲባል የምንሰማውን ነገር በተግባር በእኛ ጉዳይ ላይ መመልከት ትችላለህ። ያው የተጣሰ መብት እስካለ ድረስ መጠየቁ፣ መጮሁ እና ተደጋግሞመነሣቱ አይቀርም።
ጊዜው የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ መጠን፤ የኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ ሚዲያ የመጠቀም ልምድ እያደገ መሆኑ በተግባር ይታያል:: ከሌሎች አፍሪካ አገራ ጋር ስታነጻጻጽሪው ዕድገቱን እንዴት ታይዋለሽ? በሀገራችን ላይ ማኅበራዊ ሚዲያ ተግባራዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው? የጥላቻ ንግግሮች መብዛታቸውስ እንዴት ይታያል?
የእኛ ማኅበረሰብ ሚዲያ አጠቃቀም እንደምታውቀው ከብዙ አገሮች ጋር አንጻር ሲታይ በጣም ዝቅተኛው ነው። ጎረቤቶቻችን ኬንያ እና እነታንዛኒያ ላይ ለመድረስ ገና ብዙ ይቀራል። ይህ ታዲያ በኢንተርኔት መሠረተ-ልማት ብቻ ሳይሆን፤ በኢንተርኔት ነጻነትዋጋ በኩል ጭምር ነው። ነገር ግን በዚያ ተግዳሮት ውስጥም ሆኖ የማኅበረሰብ ሚዲያ እኔ የዛሬ ስምንትና ሰባት ዓመት ከማውቀው በጣም ተቀይሯል። አሁን ተጠቃሚውም ተናጋሪውም በዝቷል። ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ‹‹ምኅዳሩ ተበላሸ፣ እንደድሮው አይደለም›› እያልን የምናማርር ቢመስልም፤ ብዙ ተጨማሪ ሰዎች መጠቀማቸው፣ ብዙዎች መናገራቸው ሌሎች እጅግ በጣም ብዙዎች ደግሞ መስማታቸው በጣም በበጎ ነው የምወስደው።አሁን የማኅበረሰብ ሚዲያው ሚናው በጣም ከፍ እያለ መጥቷል። ተጠቃሚ በጨመረ ቁጥርም ተጽእኖው ይጨምራል፡፡ በንጽጽር የእኛ ዕድገት ደካማም ቢሆን አሁን ያለውን ሚና እውቅና መስጠት ያለብን ይመስለኛል።
የጥላቻ ንግግሮችን በተመለከተ፤ አብዛኛውን የማኅብረሰብ ሚዲያ ተጠቃሚ የሚታይ ትልቅ ክስተት አይመስለኝም።ሚልየን የሚጠጋ ተጠቃሚ ነው ያለው፡፡ ከዛ አንጻር የጥላቻ ንግግር በስጋት ደረጃ የሚቀመጥበት ቦታ ደርሷል የሚል ግምት የለኝም። መርሳት የሌለብን ነገር፤ከማኅበረሰብ ሚዲያ በፊት ምንም ዓይነት ነጻ የመናገሪያ ምኅዳርና ዕድል በፍጹም ያልነበረን ነን እንደ ማኅበረሰብ። መጻፍ፣ መናገር፣ ተሰብስቦ መወያየት በጣም ጥቂቶች ብቻ የሚያደርጉት ወይም የሚፈቀድላቸው ማኅበረሰብ ነን። ስለዚህ የማኅበረሰብ ሚዲያ በጣም አዲስ ልምድ ነው። እያንዳንዱ ሰው የፈለገውን የመናገር፣ የመከታተል፣ ሐሳብ የመስጠት ሙሉ ነጻነት አለው። ይህ ነጻነት ለእኛ አዲስ እንደመሆኑ መጠን፤ የሚያስደነግጡና የጥላቻ ንግግር የሚመስሉ ቢኖሩም፤ ከዚህ ትልቅ አውድ አንጻር ከታየ፣ እንደውምደኽና ነን ነው የምለው። ይህን የምልህ የጥላቻ ንግግር የሚለውን ትርጉም ‹‹የማይባሉ፣ በማኅበረሰብ ተቀባይት የሌላቸው›› በሚል ቀለል ያለ ትርጉም ውስጥ ዐይቼው ነው። በሕግና በንድፈ-ሀሳብ ከሄድን የጥላቻ ንግግር በጣም ጥልቅ ትንታኔ የሚጠይቅና በተለያዩ የሕግ ማእቀፎች የተለያየ ትርጉምና ዝርዝር ውይይት የሚፈልግ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሶሻል ሚዲያ ላይ የሚወጡ ጽሑፎችን ለመቆጣጠር ረቅቅ ሕግ ማውጣቱ ይታወቃል:: ይህ የመናገር ነጻነትን አፋኝ ሊሆን እንደሚችልም ይገመታል፡፡ (ከታየው ልምድ አኳያ) የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ላይ የቀረበበት የአሸባሪነት ክስ በፌስቡክ ገጹ ላይ በጻፋቸው ጽሑፎች ነውና ቀጣይ ስጋቱን እንዴት ታይዋለሽ? የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ጡመራ ከባድ አደጋ ላይ አልወደቀም?
በጣም በጣም ከባድ አደጋ ላይ ነው።የማኅበረሰብ ሚዲያ እና ጡመራ ከዓመታት በፊት በንጽጽር ሐሳብን ለመግለጽ አደጋው ከኦፍ ላየንየተሻለ ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር። አሁን ያ በጣም በፍጥነት ተቀይሯል።የመንግሥት ትችትን የመታገስ አቅም (Tolerance of critics) በጣም አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ አሽቆልቁሏል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ብታይ እንኳ ለውጡ ግልጽ ነው። አሁን ኢንተርኔት ከጋዜጣና ከሕትመት ሚዲያ ጋዜጠኝነት እኩል አስጊ እየሆነ ነው ብዬ ነው የማስበው። ይህንን ሒደት በግልጽ አቅጣጫ የቀየረው ከእኛ እስር ጋር ተያይዞ ነው። ከዚያ በኋላ ያለው ነገርም እየከፋ እንጂ እየተሻሻለ አልመጣም።
የዮናታን ተስፋዬን ክስ ያየሁ ዕለት ‹‹ለምን ሕግ ተማርኩ?›› የሚል ማማረር ውስጥ ገብቻለሁ።በኢትዮጵያውስጥ የሕግ ባለሞያ መሆን ካለመሆን ጋር ምንም ልዩነት የማይታይባት እየሆነ ነው። ባለሞያዎቹም፣ በተለይ ዐቃቢያነ ሕጎቹ፣ ሕግ መማር ለምን እንደሚያስፈልጋቸው አይገባኝም። ብዙዎቹን ክሶች በቅርብ እከታተላለሁ። እናም እያንዳንዱ ክስ አንገት የሚያስደፋ፣ የሚያስቆጭ እና ሞያ የሚያረክስ ነው።አሜሪካ ኤምባሲ በር ላይ ሰልፍ ያደረጉ ወጣት የኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የቀረበው ክስ፣ ዮናታን ላይ የቀረበው ክስ፣ እነአቶ በቀለ ገርባ ላይ የቀረበው ክስ የመሳሰሉትን ማንሣት ይቻላል፡፡
የአዲሱን ሕግ መምጣት በሁለት መንገድ ነው የማየው።አንደኛው በአጠቃላይ የኢንተርኔት እንቅስቃሴውን መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደስጋት ስለወሰደው ለማሸማቀቅ ይመስለኛል።ሁለተኛው ደግሞ አንደተለመደው ሕግ እና የሕግ ሥርዓቱን የጭቆና መሣሪያነት ለማጠንከር ነው።እንጂ አሁን ያለው መንግሥት ማንንም ለመክሰስ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ሕግ አያስፈልገውም፤ ምክንያቱም ሕግ እንደ ሕግነቱ ማሟላት ያለበትን አንድም ነገር አሟልተው ሲከሱ አይታይም። ጉዳዩ ከሕግ ጋር የምር የሚያያዝ ቢሆን ኖሮ፤ መሠረታዊ የወንጀል ሕግ የሚጠይቀውንና አንድን ወንጀል ወንጀል ነው የሚያስብለውን ነገር ባለሟሟላት ብቻ ብዙዎቹ የፖለቲካ ክሶች ፍርድ ቤት ሁሉ አይደርሱም ነበር። ባልታወቁ ግርብ-አበሮች፣ ባልታወቀ ቦታ፣ ባልታወቀ ሰዓትና ሁኔታ ተብሎ የወንጀል ክስ የሚቀርብበት አገር ሆነኗል እኮ! ስለዚህ እኔ አዲስም ሆነ አሮጌ ሕግ መጣ የፍትሕሥርዓቱ ከሕግ ማርቀቅ እስከፍትሕ መስጠት ድረስ በአስፈሪ ሁኔታ እየፈራረሰ ካቴናው ከማጥበቅ ውጭ ያን ያህል ለውጥ የሚያመጣ አይመስለኝም።
በዚህ ዝቅጠት ውስጥ በሕግ ላይ ሌላ ሕግ መጨመራቸውም ብዙ አላስገረመኝም። ለእኔ የአዲሱ የኮምፒውተር ሕግ መምጣት በዋናነት ተጨማሪ ማስፈራሪያ ከመፈለግና ሕግ ያለበት አገር ከማስመሰል ጥረት ነው።ኢላማውም ተጨማሪ መሸማቀቅ በመፍጠር፣ የመናገርና አለች የምትባለውንም የፖለቲካ ውይይት ማካሄጃ የኢንተርኔት ምኅዳር ማጥበብ ነው።በአዲሱ የወንጀል ዐዋጅ ሰበብ የሚጠቃው ሰው መጨመሩ ጉዳዩን ይበልጥ አሳዛኝ ያደርገዋል።
ለአንድ ሀገር የለውጥ ዕድገት የሴቶች ሚና ወሳኝነት አጠያያቂ አይደለም። ነገር ግን በአገራችን በፖለቲካው መስክ፣ በለውጥ አራማጅነት፣ በጋዜጠኝነትና በጡመራው ዘርፍ(ጠንክር ባለ ሁኔታ) ላይ የሴቶች ቁጥር እጅግ አናሳ ነው። ምክንያቱ ምንድን ነው ብለሽ ታምኛለሽ? ይህስ ችግር እንዴት ይቀረፋል?
የሴቶች ተሳትፎ በጣም አናሳ መሆኑ ግልጽ ነው። የችግሩ መነሻ አንድ አይደለም። በጣም ዘርፈ ብዙ ነው።እንኳ ብዙ ማኅበረሰባዊ ጫና ያለብን ሴቶችን ቀርቶ፤ ወንዶችን -በሁሉም መልኩ በተሻለ ማኅበረሰባዊ ሁኔታ ላይ ያሉትንም ሳይቀር የሚያስፈራ የፖለቲካ ምኅዳር ነው ያለው። እዚያ ላይ ማኅበራዊ ጫናውን ከሴቶች የሚጠበቀውን የተለመደ (conventional) ሚና እና እሱን አለሟሟላት የሚያመጣው ጫና ብዙዎችን ያሸሻል።ብዙ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ሴት ጓደኞቼ ይህንን ማኅበረሰቡ የሚጠብቅባቸውን የተለመደ ሚና ከሟሟላት ጫናየተነሣ ወደሌላ ማኅበራዊ ኀላፊነት ተወስደው ሲቀሩ አይቻለሁ። ሙከራ ያደረግነውም ተሳታፊዎችም በየደረጃው ያስከፈለን መስዋእትነት አስከፊ ነው። የቅርብ ጓደኞቼን ማሕሌት ፋንታሁንና ኤዶም ካሳዬን ምሳሌ ማንሣት ትችላለህ። ስለዚህ ማኅበራዊ፣ ቤተሰባዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮቹን ስታያቸው የተሳትፎ ማነስ የሚገርም አይደለም።
እንደጊዜያዊ መፍትሔ በተለያዩ የሴቶች አቅም ማጎልበት ላይ የሚሠሩ ሥራዎች (ማኅበራዊ አመራር፣ ኢኮኖሚያዊም ቢሆኑ) ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብዬ አምናለሁ። ግዴታ የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ ያተኮረ መሆን የለበትም፡፡ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን መረሳት የሌለበት ነገር፤ የሴቶች አቅም በጨመረ ቁጥር፣ ጠንካራ አቅም ያላቸው ሴቶች ወደፖለቲካውም ቢሆን በሒደት ይመጣሉ።
አንዳንዴ በሴቶች መብቶች ላይ የሚናገሩና የሚሠሩ ሰዎች የፖለቲካ ተሳትፎን የሚመለከት ነገር ባለመናገራቸው ወይም እዚያ ላይ አተኩረው ባለመሥራታቸው ሲወቀሱ እሰማለሁ። እንደእኔ፤ፖለቲካዊ ንቃት እና አቅም ላይ ባይሆንም፣ ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የአቅም ግንባታ ላይ መሠራቱ ራሱ አንድ ነገር ነው።በዚያ ሒደት ውስጥ አቅማቸውን ያጠነከሩ ሴቶች በሒደት ወደፖለቲካው ተሳትፎ የሚመጡበት ዕድል አለ። እኔ በዩኒቨርሲቲ እና ከዛ በኃላ ባጋጠመኝ ዕድል የሴት ተማሪዎችንና ወጣቶችን የአመራር አቅም በሚያጠነክሩ የአቅም ግንባታ ሒደቶች ባላልፍ ኖሮ፤ አሁን ያለኝ የፓለቲካ ተሳትፎዬ ላይኖር ይችል ነበር። እና አሁንም ቢሆን ባለችው መንገድ እና ምኅዳር አቅም ግንባታው ከቀጠለ፤ በሒደት ተሳትፎ የሚያደርጉ ሴቶች ለማምጣት ይረዳል። በጣም ቀሰስተኛ ሒደት ቢሆንም፤ ምርጫ የለንም። ከዚያ ውጭ ያለው ግን ያለው አገራዊው ፖለቲካ መፍትሔ ሲያገኝ፣ ሲቪክና ፖለቲካዊ መብቶች እንደመብት የሚቆጠሩበት አገር ሲኖረን፣ የሴቶች ተሳትፎ ፍጥነትም አብሮ የሚሻሻል ይመስለኛል። እስከዛ ባለው ዕድል ማንኛውንም የሴቶች አቅም የሚያጠናክሩ ሥራዎች ማበረታታት ይገባል።
ዘንድሮ በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ችግሮች ገሀድ እየወጡ ከመንግሥት ጋር በድፍረት መታገል በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ይህ አካሄድ መጨረሻው ምን ሊሆን ይችላል?
ከባድ ጥያቄ ነው። የመመለስ አቅሙምእውቀቱም ያለኝ አይመስለኝም [ሳቅ]፡፡ የተሰማኝን ብቻ ገልጬ ልለፍ።በተለያዩ ክልሎች፣ (በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ …) አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚታዩ የአደባባይ የመብት ጥያቄዎችን ማየት መቻላችን በራሱ በጣም ሲያስገርመኝ ነበር። ከጭቆናው ብዛትና ጥንካሬነት አንጻር እንዲህ ዓይነት ሕዝባዊ አመጽን በዚህ ጊዜ ማየቴ በጣም አስገርሞኛል። በኦሮሞ ወጣቶችና በሌሎች መብታቸውን በጠየቁ ዜጎችም በጣም ኮርቻለሁ። የተከፈለው መስዋእትነትና ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ ደግሞ በጣም አሳዝኖኛል።ሐዘኑ እንዳለ ቢሆን፤ አይቻልም አይሞከርም የሚባለው ሕዝባዊ ሰላማዊ ተቃውሞ ከተሞከረ፣ የሚቻል መሆኑን ያሳየ መሆኑን አይቻለሁ። ሰላማዊ ትግል ላይ ያለኝን ተስፋ እንዳጠናክርም አድርጎኛል።
የአካሄዱን መጨረሻ መገመት ከባድ ነው። እንቅስቃሴዎቹን በቅርብ ስለማላውቃቸው አቅጣጫቸው፣ ስኬታቸውና ክፍተታቸውን ለመናገር መረጃ ይጎድለኛል። በአጠቃላይ ግን፤ አንደኛ፣ ጭቆናን እምቢ ለማለት፣ አገር ውስጥ ያለ መደራጀት በጣም ወሳኝ መሆኑን አይተናል።ሁለተኛ፣ ኢትዮጵያዊ የተቃውሞ ፓርቲፖለቲካ ሕዝባዊ እንቅስቃሴን ለመምራት የሚያስችል አመራርም ሆነ አቅም እንደሌለው በግልጽ ታይቷል።ገዥው ሕወሓትም ቢሆን በሥልጣኑ የመጡ ከመሰለው፤ የወጣት እና ሕፃናትን ሕይወት ከመቅጠፍ እንደማይመለስ አሁንም ደጋግሞ አሳይቷል።
በተጨማሪ፤ እንደአገር አጠቃላይ ያለን አብሮነት ማሳየት እና በከተሞች ላይ ያለው የመደራጀት አቅም ምን ያህል ደካማ እንደሆነ፤ በዛው መጠንም አፈናው ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ አይተናል።መሠራት ያለባቸው ክፍተቶች የቱ ጋር እንደሆኑም ለመማር ዕድል ሰጥቷል – በውድ የወጣቶች ሞት የተማርነው ሆነ እንጂ፡፡
አንድ በግልጽ የሚታወቀው ነገር፤ ነገሮች በረድ ያሉ ይምሰሉ እንጂ፣ ይሄንን ያህል ግፍ ተፈጽሞ ነገሮች እንደተለመደው ይመለሳሉ ብሎ መገመት ከባድ ነው።ጭቆና እስካለ ድረስ የመብት ጥያቄዎች መልካቸውን እየቀያየሩ መምጣታቸው አይቀርም።ስለዚህ መገመት የምችለውአካሄድመንግሥት እንደሚያስመስለው የሚቆም ነገር እንደማይኖር ብቻ ነው።
ምዕራባውያን በተለያዩ የኢትዮጵያ ችግሮች ዙሪያ ጠንካራ መግለጫዎችና ሪፖርቶችን በየጊዘው ሲያውጡ ይታያል። ነገር ግን የአሜሪካን መንግሥት ጨምሮ እንደሚያወጡት ጠንካራ መግለጫና ሪፖርት ተግባራዊ የሆነ ጠንካራ ጫና ሲፈጥሩ አናይም። ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻነት፣ ፍትሕ፣ ዕኩልነት፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበር …እውን እንዲሆን ምዕራባውያን የምር የሚረዱን ነገር አለ? ለውጥ በእነሱ ይመጣል? ከመንግሥት ጋራ እጅና ጓንት ሆነው ስለሚሠሩ ለማለት ነው ለሀገራቸው ጥቅም ሲሉ።
ያነሣኽውሐሳብ ሁሌ የሚያሳስበኝና መቀየር አለብን የምለው ነው። የምዕራብያውያንን ሚና በተመለከተ፤ የሚያወጧቸው መግለጫዎች እና ሪፖርቶች ከሚገባ በላይ ተስፋ ሲጣልባቸው አያለሁ። እኔ ከተሰደድኩ ጀምሮ በጣም ብዙ ዓለም አቀፍ የአድቮኬሲ ሥራዎች ላይ ተሳትፌአለሁ። መንግሥታት የድጋፍ አሰጣጣቸውን እንዲያጤኑት መናገሩ እና ጫና ማድረጉ ምንም ክፋት የለውም። ነገር ግን ለነጻነት የሚደረገው ትግል ለዚህ ዓይነት ሥራዎች የሚሰጠው ትኩረት ከሚገባው በላይ የተጋነነ ነው ብዬ ነው የማምነው። ምዕራባውያንን የማሳመን እና ተግባራዊ ተፅእኖ እንዲያደርጉ የማድረግ ሥራ አንዳንድ ጊዜ የልመና እና የመለማመጥ ያህል አስቸጋሪ እና ተስፋ አስቆራጭ ነው። እነሱ የሚታይ፣ ያለምንም አለመረጋጋት የነሱ ጥቅም ሳይነካ የሚቀጥልበት የሚታይ መንገድ እስካላዮ ድረስ፤ ከመግለጫና ሪፓርት በላይ እንደማይሄዱ ግልጽ ነው።
ከዚያ ይልቅ እኛ በእጃችን ላይ ያለውን የራሳችንን ዕጣ በራሳችን የመለወጥ ሥራ ላይ ማተኮር ይኖርብናል። በዚህ ዙሪያ ብዙ ጊዜ የማየው ችግር ሚና ያለመለየት ችግር ነው።የፖለቲካ ፓርቲዎች ነጮቹን ጋር አድቮከሲ በመሥራት ላይ ከሚገባው በላይ ብዙ ጊዜ ያጠፋሉ። የፓርቲ ዋና ሚና ማደራጀት፣ የራሱ ዜጎች ላይ መሥራት፣ ማንቀሳቀስ መሆኑን ይረሱታል።‹‹የእንትን ፓርቲ መሪ የአውሮፓ ኅብረት ቢሮ ሄደው ማብራሪያ ሰጡ፣ ስብሰባ አደረጉ…››ተብሎ ሁሉ ዜና ይሠራል፤ ዋና ሥራው ያ ይመስል። ይሄ ለሕዝቡም የምዕራባውያንን ሚና የሚያጋንን ሥእል ይፈጥራል፡፡ ፓርቲዎች ስለዓለም አቀፍ ግንዛቤ ያላቸውንም ችግር ያሳያል። ይህ በውጭ ያሉ ፓርቲዎችና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ በተደጋጋሚ ይታያል። አድቮኬሲውን እና አራማጅነቱን ከፖለቲካ ሥራ ጋር ቀላቅለውት ሁሉም ላይ ውጤታማነት ማጣት አስተውላለሁ። ስለዚህ የእንቅስቃሴዎችን ትኩረትና ሚና መመጠን፣ እና ዋና ለውጥ በሚያስፈልገው ሥራ ላይ ማተኮር፣ የመጀመሪያው እርምጃ መሆን አለበት። እኛ ተፎካካሪ ኀይል ሆነን ስንቀርብ፣ በዛው መጠን የምዕራባውያን ትኩረት ይመጣል። እነሱ የቤት ሥራቸውን በሚገባ ነው የሚሠሩት፤ ማንኛውንም ተፎካካሪ ኀይል የሚገባውን ቦታ ይሰጡታል።
በአጭሩ ሦስት ነገሮች ናቸው መደረግ ያለባቸው ብዬ የማስበው፤ አንደኛ፣ የተቋቋምንለትን ሚና መለየት፡፡ ፓርቲ እንደፓርቲ፣ አድቮኬሲ ድርጅት፣ሚዲያ እንደሚዲያ በሚናው ውጤታማ ከሆነ፣ የምዕራባውያንን ትኩረት ማግኘት ይቻላል፡፡ሁለተኛ፣ የተቋቋምንለት ዓላማ ከእንደዚህ ዓይነት ሥራ ጋር ሲያያዝ፣ ከሚገባው በላይ ጊዜ፣ ትኩረት እና ጉልበት አለመስጠት ያስፈልጋል። ለምዕራባውያን እንደለውጥ መንገድ ቆጥረን የምንሰጠውን ትኩረት በእጅጉን መቀነስ በጣም በጣም በጣም አስፈላጊ ነው።ለሕዝብ መረጃ ማድረስና ማንቃት ላይ ጠንክሮ መሥራትና ብዙ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የራሳችንን ድምፆች ማጠናከር ያስፈልጋል።
አገር ቤት ካሉ ወዳጆቼ ጋር፤ስለምዕራባውያንና በዚያ ዙሪያ ስለሚሠራ የአድቮኬሲ ሥራ ሁልጊዜእንደምለው፤ ውጭ ሆኖ የምዕራባውያንን ተፅእኖ ለመቀነስ ከሚሠራ ብዙ ሥራ ይልቅ፣ በንጽጽር አንድ ጦማር መጻፍ ለአገር ይበልጥ ይጠቅማል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻነት፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ ዕኩልነት፣ የሰብዓዊ መብቶ መከበር በተግባር እውን እንዲሆን ምን መደረግ አለበት? ለእነዚህ እውን መሆን ተስፋ የሚጣለው በማን ላይ ነው?
በጣም ከባድ ጥያቄ ነው። መልሱም እንዲሁ አንድና ፍጹም (absolute and singular) አይደለም። ኢትዮጵያ ነጻነት የኖረባት ፍትሕ እና ዕኩልነት የሰፈነባት አገር ሆና አታውቅም። ስለዚህ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላም ሙከራ ላይ ነን። ይህ ሒደት በተራዘመ ቁጥር ውጥንቅጥና መፍትሔውም ረጅም ጊዜ የሚፈጅ እየሆነ ይመጣል።በእኔ ዕድሜ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሙሉ ነጻነት የሰፈነባት አገር ሆና አያለሁ ብዬ አላስብም። ነገር ግን መንገዱን ለመጀመር መሠረቶች ሲጣሉ ካየን በቂ ነው። መሠረት ያለው ዴሞክራሲ ለመገንባት መሠረታዊ አገራዊ መግባባት ላይ ከተደረሰ ከዚያ በኋላ የሚፈጀው ጊዜ አያሳስበኝም። ይህ አንግዲህ አጠቃላዩን ከመንግሥት ለውጥም ባለፈ ያለውን ሒደት አስመልክቶ የማስበው ነው።
አሁን ላለን ሁኔታ ግን ተስፋ ማድረግ ያለብን በራሳችን ላይ ነው፡፡ ጥቂት ሰዎች ፓርቲ መሥርተው፣ ጽፈው፣ አውርተው፣ ታግለው፣ ታስረው…ሚሊየን ሕዝብ ለነጻነት አያበቁም።የነጻነትና ዕኩልነት ጥያቄ የብዙዎች ጥያቄ እንዲሆን ጥቂቶች ብቻ መስዋእትነት የሚከፍሉበት ጉዳይ እንዳይሆን መሥራት ይጠበቅብናል። አሁን እንደምናየው ነገሩ ልክ እንደ ተሽከርካሪ በር ነው፤ አንዱ ሲወጣ አንዱ ይገባል። አንዱ ሲፈታ ሌላው ይታሰራል። በየተወሰነ ጊዜው ሰዎች ይጠፋሉ፣ ይገደላሉ። የጭቆና ማሽኑ ግን ለተወሰነ ጊዜ ይስተጓጎለ ይመስልና እንደገና መሥራቱን ይቀጥላል። ከዚህ አዙሪት ለመውጣት የመሠረታዊ የሰው ልጅ አንደሰው የሚያስፈልገው መብትና ክብር ጥያቄን የብዙዎች በአደባባይ የሚያነሱት ጥያቄ ማድረግ ላይ መሠራት አለበት። ለዚያ ነው ሚዲያና ሐሳብን መግለጽ ከሁሉም መብቶች በላቀ ተጽእኖ ፈጣሪ የሚሆነው፤ በዛውምመጠንጫናም የሚበዛበት።
እኔ በትንንሽ በአቅማችን በሚደረጉ አስተዋፅኦዎች አምናለሁ፡፡ አሁን ኢትዮጵያ በጣም ዝግ የፖለቲካ እና የመብት ምኅዳር ያለባት፤ በነጻ መደራጀት ተአምር የሆነባት አገር ናት።ኢንተርኔት ላይ እንኳ መደራጀት አይታሰብም። ትንንሽና ግላዊ አስተዋፅኦ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ። የመብት ጥያቄና እሱን ለመመለስ የሚደረግ አስተዋፅኦ ትንሽ የለውም።ከማኅበረሰብ ሚዲያ እስከሰፈርና ቤት ድረስ መነጋገር፣ መወያየት ጥሩ ነው። መረጃን በቁም-ነገር መለዋወጥና እንደግለሰብ ማድረግ የሚቻለውን ማሰብም ቀጣይ ደረጃ መሆን ይችላል። የተለየ ኀላፊነትና ተስፋ የሚጣልበት ልዩ አካል ያለ አይመስለኝም። እንደዛ ካሰብን ነጻ አውጭ ጥበቃ መቀመጥ ይሆናል፡፡ ያ ደግሞ ይበልጥ ትክክል አይደለም፤ የጭቆናውንም ዕድሜ ያረዝመዋል፡፡
በመጨረሻም፣ሶሊያና፣የነገዋኢትዮጵያምንብትሆንከነፍሷትወዳለች?

የነገዋኢትዮጵያዴሞክራሲያዊስርዓትለመገንባትመሠረቶችንለመጣልበሁሉምመልኩየተዘጋጀችሆናብናያትእመኛለሁ፡፡መሠረቶቹንለመጣልዝግጁነትእናመግባባትካለወደተግባርመቀየሩየሚከብደንአይመስለኝም፡፡ዝግጁየሆኑአገራትበሁለትአስርትአመታትውስጥበጣምተስፋሰጪእናአንገትቀናየሚያስደርግለውጥአሳይተዋል፡፡

ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!
እኔም አመሰግናለሁ!

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *