ፍርድያውቃል ንጉሤ

(firdyawkal@gmail.com)
ያኔ ልጆች ሳለን (ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በፊት) ሀገራዊም ሆነ አለም አቀፋዊ የስፖርት ክንውኖችን የምንከታተለው በኢትዮጵያ ሬዲዮና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሚቀርቡት መደበኛ የስፖርት ፕሮግራሞች ነበር – ዘወትር ሰኞ ምሽት ከሁለት ሰዓት ዜና በኋላ። በወቅቱ ለሰላሳ ደቂቃ ብቻ በምናገኛቸው የስፖርት ፕሮግራሞች ላይ በብዛት የሚቀርቡት የሀገር ውስጥ የስፖርት ክንውኖች ሲሆኑ፣ እነርሱም እግር ኳስ ላይ ብቻ የተንጠለጠሉ ሳይሆን፤ ሁሉንም የስፖርት አይነቶች የሚዳስሱ ነበሩ። በዛሬው ፅሁፌ ትኩረቴን ያደረኩት በሬዲዮ የሚቀርቡ የስፖርት ፕሮግራሞች ላይ ነው፡፡ እናም ከአመታት በኋላ አየር ላይ የሚውሉበት ጊዜ ስለተራዘመላቸው የሀገራችን የሬዲዮ የስፖርት ፕሮግራሞችን እንመልከት።
የኢትዮጵያ ሬዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት የዛሬን አያድርገውና እንዲህ ከመዳከሙ በፊት በበሳል ጋዜጠኞች የሚዘጋጁ፤ ጥልቀት ያላቸውና ጠንካራ የሆኑ በርካታ ፕሮግራሞች ነበሩት። ከነዚህ ፕሮግራሞች መሀል ደግሞ አንዱ የስፖርት ፕሮግራም ነበር። ይህ በሳምንት አንድ ቀን (ሰኞ ምሽት) ብቻ የነበረው የጣቢያው የስፖርት ፕሮግራም በ2000 ዓ.ም መባቻ ላይ በሳምንት አምስት ቀን እንዲሆን ተደርጓል።
በሰኞና በአርብ መደበኛ ዝግጅቶቹ ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ስፖርታዊ ክንዋኔዎችን በአጫጭር ዜናዎች መልክ ይቀርቡባቸው የነበረ ሲሆን፣ ከነዚህ ፕሮግራሞች ጎን ለጎን ዘወትር ማክሰኞ፣ ረዕቡና ሐሙስ በርካታ ባለሙያዎች የሚሳተፉባቸው፤ የሀገሪቱ ህዝብም ተሳታፊ ሆኖ ጥልቀት ያለውና አንገብጋቢ መፍትሔን ያዘሉ የውይይት ፕሮግራሞች ይቀርቡ ነበር።
በእነዚህ የውይይት መድረኮች ላይ ከሩጫ እስከ እግር ኳስ፣ ከውሃ ዋና እስከ ቼዝ፣ ከመረብ ኳስ እስከ ጠረጼዛ ቴኒስና የባህል ስፖርቶች ብቻ ሁሉም አይነት የስፖርት ክንውኖች በዋናነት ይነሱ ነበር። ይህ ሂደት ደግሞ ለሀገራችን ሁለንተናዊ የስፖርት እድገት የተጫወተው ሚና ቀላል የሚባል አልነበረም። አሁንስ?
እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ። በርግጥ እንደ ስፖርት ጋዜጠኝነቴ መጠየቅ የሌለብኝ ጥያቄ ሊሆን ይችላል። ግና ነገሮች በጣም ግራ ስለገቡኝና ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እንደሚባለው ድንገት በዚህ ጥያቄዬ ዙሪያ እኔ ያልሰማሁት ሀገራዊ የአሰራር ለውጥ መመሪያ ወጥቶ ከሆነ ብዬ ነው። አዎ! ስፖርት ማለት እግር ኳስ ብቻ ነው እንዴ? እግር ኳስ ብቻ የሚወራበት ፕሮግራም መባል ያለበት የእግር ኳስ ፕሮግራም ነው ወይስ በርካታ የስፖርት ቅርንጫፎችን እንደያዘ ሁሉ የስፖርት ፕሮግራም ነው መባል ያለበት?
አሁን አሁን በሀገራችን ያሉትን ትተን በመዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ ያሉትን ዘጠኝ የኤፍኤም ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ከተመለከትን፤ ከዘጠኙ የኤፍኤም ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ ከአባይ ኤፍ. ኤም በስተቀር፣ በስምንቱ የሬዲዮ ጣቢያዎች ‹‹የስፖርት ፕሮግራም›› ስያሜን ያነገቡ በርካታ ፕሮግራሞች አሉ። ገሚሶቹ በዛው ጣቢያ ሰራተኞች፤ ገሚሶቹ ደግሞ በተባራ አዘጋጆች የሚሰናዱ በርካታ የስፖርት ፕሮግራሞች አሉ።
መብዛታቸውን ብቻ ካየን እሰየው ያስብላል። ግን ፋዳቸው ትርፍ-የለሽ ነው። ምክንያቱም እንደብዛታቸው ፋይዳ ያላቸው የስፖርት ፕሮግራሞችን ቢሰሩ ከላይ ያሉ የየፌዴሬሽኑ አመራሮችን ሊያነቁና የሀገራችንን ስፖርት አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንዲራመድ አስተዋፆኦ ያበረክቱ ነበር። ግና መጠሪያ ስማቸው ተለያየ እንጂ የሁሉም ፕሮግራሞች ይዘት ፍጹም ተመሳሳይ ነው። ሁሉም የሚያወሩት ስለ እግር ኳስ ብቻ ነው። ያውም በብዛት ስለውጭ ሀገር እግር ኳስ።
ታዲያ እውን እነዚህ ፕሮግራሞች የስፖርት ፕሮግራም የሚለው መጠሪያ ይገባቸዋል? መልሱን ለእናንተ ትቼዋለሁ። እኔ በእነዚህ በሁሉም የስፖርት ተብዬ ፕሮግራሞች ላይ ከእግር ኳሱ ውጭ፣ በወረት በውድድር ዋዜማ፣ መባቻና ማግስት ላይ አትሌቲክስን ይዘግቡ ይሆናል እንጂ፣ በፍጹም ስለሌሎች ስፖርቶች፣ ስለ እጅ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ቮሊቮል፣ ቦክስ፣ ውሃ ዋና፣ ጠረጴዛ ቴኒስ ወዘተ. ሰምቼ አላውቅም።
አንድ ጋዜጠኛ የሚሰራው ዜና በፍጹም ማጣት የለበትም። ምክንያቱም በፈለገው ርዕስ ዙሪያ የሚወራና የሚዘገብ ቢያጣ እንኳ ራሱ ዜናዎችን መፍጠር እንዳለበት ነው የሙያው ብሒል የሚያትተው። ለምሳሌ ስለቮሊቮል ለማውራት ፍላጎቱ ያለው ጋዜጠኛ ሌላው ቢቀር የቮሊቮል ፌዴሬሽን አመራሮችን በማነጋገርና አሁን ስፖርቱ በሀገር ደረጃ ያለበትን ሁኔታ በመቃኘት ዜና መስራት ይችላል። እኛ ዘንድ ግን መሰል ስራዎችን ለመስራት ከነ ፍላጎቱም የለም።
እነዚህ የራዲዮ የስፖርት ፕሮግራሞች ላይ ግን ይህ ትጋት በፍፁም አይታይም። በቃ ሁሉም ኢንተርኔትና ዲኤስ ቲቪ ላይ ተንጠልጥለው የአየር ሰዓቱን ሸፍነው ይወጣሉ። ከዛም ምርጥ ጋዜጠኞች ይባላሉ። ግን እስቲ አስቡት፤ ድንገት ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርኔት እና የሳተላይት ቴሌቪዥኖች አገልግሎታቸው ለአንድ ወር ቢቋረጥ እነዚህ ፕሮግራሞች ላይ ማን ምን ይሰራል? እነደምሴ ዳምጤ፣ ጎርፍነህ ይመር፣ ሰለሞን ተሰማና ሰለሞን ገ/እግዚአብሔር ላይ ታቹን ዳክረው የስፖርት ጋዜጠኝነትን እዚህ አደረሱት፡፡ የእነርሱ ውጤት አሁን በእጅጉ ስለመክሰሙ ይህ ሒደት ማረጋገጫ ይሰጣል።
እኛ ከእግር ኳሱ ይልቅ በአትሌቲክስ ስፖርት በአለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሆንን መሆኑ እሙን ነው። ግና በሚገርም ሁኔታ ስለ አትሌቲክስ ስፖርት እንኳ የሚዘገበው የውድድር ዋዜማ፣ መባቻና ማግስት ላይ ብቻ ነው። የጉምቱ አትሌቶቻችን የህይወት ታሪኮች ከነተሞክሮዎቻቸው፣ የወጣት አትሌቶቻችን ጥረትና ተጨባጭ ተስፋ፣ የታዳጊ አትሌቶቻችን ይዞታ፣ የአትሌቲክስ አካዳሚዎቻችን ይዞታ ወዘተ. በተመለከተ አንድም ቀን አንድም የተቀናበረ ፕሮግራም እኔ ሰምቼ አላውቅም። ግን አትሌቶቻችን በኦሎምፒክ ወይም በአለም ሻምፒዮና ውጤት ሲያጡ ‹እንዴት ተደርጎ!› ብለን ጣታችንን ሌሎች ላይ ለመቀሰር ቀዳሚ የሆንነው እኛው ጋዜጠኞች ነን።
የሚገርመው እኛ የስፖርት ምንነትና ትርጉም በእጅጉ ተዛብቶብናል። በየትኛውም ወቅት ለሀገራችን አጠቃላይ ስፖርቶች ያለን አመለካከት ራሱ ጤነኛ ያልሆነ ከመሆኑ የተነሳ አንድ ጋዜጠኛ በእነዚህ ስፖርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ቢጀምር ‹‹ያመዋል እንዴ?›› ብለን ከመጠየቅ ወደኋላ አንልም። በጣም የሚገርመው እኛ ወሬ ለመቃረምና መረጃ ለማግኘት የምንጠቀምባቸው የምዕራባውያኑ ድረ-ገፆች በፍፁም ለእግር ኳስ ብቻ ትኩረት አያደርጉም። ከቢቢሲ እስከ ዴይሊ ሜል፣ ከዴይሊ ቴሌግራፍ እስከ ዘ ጋርዲያን ሁሉም የመጀመሪያ ገፃቸው እግር ኳስ ሳይሆን ስፖርት ነው የሚለው። እነሳይክል፣ ቦክስ እና መሰል ስፖርቶችንም በሰፊው ነው የሚዳስሱት። ፉት ቦል ከሚለው አምዳቸው ስር ካልሆነ በስተቀር እግር ኳስ የስፖርት አምዳቸው አበይት ዜና ሆኖ አያውቅም። ደግሞ እንደሚታወቀው ድረ-ገፆቹ የእንግሊዝ ከሆኑ ስለእንግሊዝ፤ የጀርመን ከሆኑ ስለጀርመን በስፋትና በብዛት ከዘገቡ በኋላ ነው ወደ ቀሪው አለም ዘገባዎች የሚሸጋገሩት። እኛ ግን የእነርሱ እግር ኳስ ላይ ተንጠልጥለን ስፖርት የሚለውን የወል ስም የፕሮግራማችን መጠሪያ ላይ ለጥፈን ወደፊት ይመስለናል እንጂ እንደ እውነታው ከሆነ ወደኋላ መጓዛችንን ቀጥለናል።
በርግጥ ይህ ሁሉ ሲሆን መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እንዴት ዝም አሉ? የየጣቢያዎቹ ባለቤቶችስ ህሊናቸውን በገንዘብ ጋርደው የሀገራችን ስፖርቶች ሞቶ ሲቀበር እያዩ እስከመቼ ነው ዝምታን የሚመርጡት?…የእነዚህ ፕሮግራሞች ስር የሰደዱና ወደፊትም የሚሰዱ ተግዳራቶችስ ምንድን ናቸው? መፍትሔውስ? የሚሉትን ጉዳዮች በቀጣይ ዕትም እመለስበታለሁ።
አዎ! ፅሁፌን ለመቋጨት ግን ደግሜ እላለሁ…ስፖርት ማለት እግር ኳስ ብቻ አይደለም! ሁሉንም የስፖርት አይነቶች ሳይዳሰሱ ፕሮግራምን ‹ምናምን ስፖርት› በማለት እየሰየሙ በዚህ ባንቀላፋው ህዝብ ላይ የበለጠ ሙድ ባይያዝ መልካም ነው።

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *