አቶ ጌታቸው ረዳ /የመንግስት ኮሙዩኑኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር/
የመንግስት ኮሙዩኑኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የ‹‹አዲስ ገጽ›› አምስተኛ ዕትም እንግዳችን እንደነበሩና የቃለ-ምልልሳቸውም የመጀመሪያ ክፍል መስተናገዱ ይታወቃል፡፡ ሚኒስትሩ ከጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና አናንያ ሶሪ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ የመጨረሻ ክፍል እንዲህ ቀርቧል፡፡ መልካም ንባብ!
ስለ አቶ በቀለ ገርባ ሲነሳ፣ ‹‹ከሌሎች ኃይሎች ጋር ግንኙነት አላቸው›› ተብለው በመጠርጠር እንደታሰሩ ነግረውናል። እነዚያ ኃይሎች እነማን ናቸው? አቶ ጃዋር መሐመድ የሚመራው ኃይል ነው ወይስ … ? እስኪ አብራርተው ይንገሩን?
[የመገረም ሳቅ] ጃዋር የሚመራው? …ጃዋር መሐመድ የሚጽፈው ብዙ ጽሑፍ አለ – በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ። ጃዋር የሚመራው ኃይል …የበቀለ ገርባ በጣም ውስብስብ ነው። በቀለ ገርባ የጃዋር ተከታይ ነው የሚል እምነት የለኝም፤ ግን ‹‹እንቅስቃሴውን የሚያቀናጀው ከሌሎች ኃይሎች ጋር ነው›› የሚለውን ካልኩ ይበቃል።
እነዚያ ኃይሎች እነማን ናቸው?
ፖሊስ እየመረመረው ያለ ጉዳይ ነው። ፖሊስ አቶ በቀለን ‹‹ከውጭ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ የሚሠራው እንቅስቃሴ ነበር›› ብሎ ነው በጥርጣሬ የያዘው። ለአቶ በቀለ ገርባ ያለኝ አመለካከት በጥርጣሬ ታስሯል የሚል ነው።
ግን ኢሕአዴግ ዕድሜ ዘመኑን በተደጋጋሚ ሲጠቀምባቸው የምናስተውላቸው ስልቶች አሉ። የሆነ ቦታ የሆነ ነገር ሲፈጠር ወይም የሆነ ነገር ሲከሰት፣ ወዲያው ‹‹ፀረ-ሰላም ኃይሎች››፣ ‹‹ፀረ-ሕዝብ ኃይሎች›› ወዘተ. እንዲህ አደረጉ፣ እንዲህ ለማድረግ ሞከሩ፣ እንዲህ ለማድረግ ተንቀሳቀሱ …እያለ ሲያላክክ ይታወቃል። በ97 ብጥብጥ ጊዜም ተመሳሳይ ምክንያት ሲሰጥ ነበር። ይሄ ምን ያህል ያሳምናል?
የሚያሳምነው እንደ መረጃው ክብደት ነዋ!
ድጋሚ አጽንኦት ለመስጠት፤ ኢሕአዴግ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ችግር በተፈጠረ ቁጥር ሁሌም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኛች እና ሌሎች ከኢሕአዴግ ውጭ በሆነ መልኩ ሐሳባቸውን የሚያቀርቡ ሰዎች ላይ ሲያላክክ ይታወቃል። አሁንም በኦሮሚያ ተቃውሞ ጉዳይ ላይ ‹‹የታች የልዩ ዞን አመራሮች፣ የበታች ካድሬዎችም ጭምር ችግር ፈጥረዋል›› ተብሎ በኢሕአዴግ ጭምር እየተነገረ እነሱ ላይ እርምጃ ሲወስድ ግን አይታይም።
ከላይ እንደገለፅኩት ነው፤ እርምጃ የሚወስድበት ሰው ካለ እርምጃ ይወሰድበታል።
ይሄ እኮ በተግባር አልታየም፡፡ ኢሕአዴግ በራሱ ላይ እርምጃ ሲወስድ አልታየም። ‹‹እኔ ውስጥ ያሉ ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው፤ እኔ ውስጥ ያሉ ችግር ፈጣሪዎች ናቸው›› በሚላቸው ሰዎች ላይ አንድም ጊዜ እርምጃ ሲወስድ አልታየም።
አሁን ‹‹እገሌ ላይ እርምጃ ተወስዷል፣ እገሌ ላይ አልተወሰደም›› የሚለው ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ መግባት አይደለም። ጥፋት አጥፍተው ሲገኙ፣ ኢሕአዴግ የራሱ የሆኑ ግዙፍ አባላቶቹ ላይ ጭምር እርምጃ ወስዷል። አሁን በዚህ የተለየ ጉዳይ ላይ፣ የኢሕአዴግ አባላት ለእንደዚህ ዓይነት ሁከት አስተዋፅኦ አድርገው ከሆነ የሚገባቸውን ቅጣት ያገኛሉ። ኢሕአዴግ በሚመራው መንግሥት ውስጥ፣ ትልቅ ሹመት ያላቸውና ለዚህ ችግር አስተዋፅኦ አድርገው ከሆነም ይቀጣሉ፤ ምንም ጥያቄ የለውም። አሁን እናንተ አካሄድ ለማውጣት የምትሞክሩት… አስተሳሰቦቻችሁ ሆነ ተብለው የተመረጡ ስለሆኑ ነው። የምታዩት ማየት የምትፈልጉትን ነው።
እንዴት?
ለምሳሌ፣ ምሳሌውን መጠቀም በጣም እጠላለሁ፤ ቀድሞውን የማውቀው ነገር ነው። አንዲት ልጅ ነበረች፤ በሽብር ተጠርጥራ ታስራ የነበረች። ጋዜጠኛም አልነበረችም፤ አስተማሪ ነበረች። ጽሑፍ ትጽፍ ነበር፤ አምደኛ ነበረች። እኔ አምደኛ ሆኜ በምጽፈው ጽሑፍ ተጠርጥሬ ብያዝ ጋዜጠኛ ተብዬ ነው የምገለጸው?
ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ‹‹በአዲስ ፕሬስ›› ጋዜጣ ላይ አዘጋጅ ሆና ሠርታለች።
ዋናው ጥያቄ እሱ አይደለም፣ አሁን እሷ የኢትዮጵያ አርበኞ ምናምን ለሚባል ተቋም…
አርበኞች ግንቦት ሰባት ለማለት ነው?
አዎን። ለዚህ ተቋም ለጀመረችው እንቅስቃሴዎች ሥራዎች ስትሠራ ነው በቁጥጥር ሥር የዋለችው። … ለራሳችሁ ዓላማ ስትሉ ፍ/ቤት በምን እንደተከሰሰች ጠይቁ።
የፍርድ ሒደቱን ተከታትለነዋል።
‹‹ከጽሑፍ ጋር ነው ተጠርጥራ የተያዘችው›› የሚል ምንም ነገር እንዳላያችሁ ታውቃላችሁ። ከጽሑፍ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር አልነበረውም።
‹‹በቃ›› የሚል ፎቶ አንስተሻል…?
[ጥያቄያችንን አቋርጠው] በስልክ የተደረገ ልውውጥም በማስረጃ ቀርቧል። ለምን መርጣችሁ ብቻ ትናገራላችሁ?! [ትንሽ ቆጣ አሉ!]
ከ‹‹ኢትዮጵያ ሪቪው›› ድረ-ገጽ አዘጋጅ ኤልያስ ክፍሌ ጋር በስልክ የተደረገውን ልውውጥም ፍ/ቤት አድምጠነዋል።
ለማንኛውም ተጠርጥራ የተያዘችው በኃይል መንግሥትን ለመናድ በተደረገ እንቅስቃሴ ነው። አሁን ቪዛ አግኝታ አሜሪካ ስትሄድ ልክ አዲስ ነገር እንደ ተፈጠረ ‹‹ግንቦት 7ን ተቀላቅያለሁ›› አለች። ለእኔ ከእስር ቤት ወጥታ ግንቦት 7ን ተቀላቀለች የሚለው አይዋጥልኝም፤ ድንገት እስር ቤት ሆና እያለ ተለያይተው ካልሆነ በስተቀር፤ ልዩነት የለውም። [ርዕዮት በቅርቡ በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን (ኢሳት) ላይ በሰጠችው ቃለ-ምልልስ፣ አርበኞች ግንቦት 7ን ለመቃለቀል የወሰነችው እስር ቤት ውስጥ ሆና መሆኑን መግለጿ ይታወሳል፡፡]
ሆን ተብሎ በመምረጥ የምናየውን ብቻ አንይ። ኢሕአዴግ ይነስም ይብዛ፣ ተቀበሉትም አትቀበሉትም፣ ተራማጅ ድርጅት ነው። የዚህች ሀገር ብዝኃነት ከተነካ፣ የዚህች ሀገር ኅልውና አደጋ ላይ ይወድቃል። ይሄንን ሀገር ብዝኃነት የማንነካው ደግሞ ዴሞክራሲያዊ እርምጃ ነው። ስለዚህ እንደ ጀማሪ መደነቃቀፍ አለ።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ፍላጎት ያለው ተቋም ግድብ ለምን መገደብ እንዳለበት ነው የማይገባኝ። ኢትዮጵያን ለማፍረስ መንገድ ለምን ይሠራል?! የፍጥነት መንገድ (Express way) መገንባት ለምን እንዳለብን አይገባኝም? ኢትዮጵያን ለማፍረስ አንድ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሙሉ ሀገር በግማሽ ቀን ቀውጢ በሚደረግበት ዘመን፤ ሥልጣን ላይ የወጡ ሰዎች ለምን 40 ዩኒቨርሲቲዎች መቋቋም አለባቸው ብለው እንደሚያምኑ ነው የማይገባኝ። ሀገር አደንቁረህ የመግዛት ፍላጎት ካለ፣ ለምን ሁከትን ታበዛለህ? ኢሕአዴግ አድሃሪ ድርጅት ቢሆን ኖሮ ለምን ዩኒቨርሲቲዎችን ያስፋፋል? ለምንድን ነው መዳ-ወላቡ፣ ዋቸሞ፣ ስማቸውን ሰምታችኋቸው የማታውቋቸውን ተቋሞች ለምን ራስ ምታቱ እንዲሆኑ ፈቀደ? ለዴሞክራሲ ያለህ ተነሣሽነት ዩኒቨርሲቲ በማስፋፋት ካልተገለጸ – በምንም ሊገለፅ አይችልም።
እያልን ያለነው፤ እንደ ሀገር፣ [ፕሬዚዳንት] መንግሥቱ [ኃ/ማርያም] አለው ይባላል፣ እያሪኮ ነው መሠለኝ በጩኸት የፈረሰው ከተማ። ሀገር በጩኸት እንዲፈርስ እንዲፈቀድለት አይገባም። ሕዝብ ጥያቄውን መጠየቅ መቻል አለበት፡፡ ግን ከየሰፈሩ የተሰበሰበ፣ እርስ በርሱ የሚምታታ፣ የሚጋጭ አቋም ያለው… አንደኛው ‹‹ሸዋ ጠቅላይ ግዛት››፣ ሌላኛው ደግሞ ‹‹ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት መባል አለበት›› ብሎ የሚያምን፤ ሌላው ‹‹ኦሮሚያ ካልተገነጠለች… ›› ብሎ የሚያስብ፤ ይሄ ሁሉ ለአንድ አቋም ተሰልፎ፣ ግን በማን ትከሻ፣ በማን ጫንቃ፣ በማን ደም ላይ ተመሥርቶ ነው? ሕጋዊ ጥያቄ ባነሡ ተቃውሞ አሰሚ ወጣቶች ደም ላይ ተመሥርቶ የሆነ ነገር ለማድረግ ሲሞክር የሚፈጠረው ችግር እንደ ማንቂያ ደወል መቆጠር መቻል አለበት።
እገሌ ጥፋት አለበት፤ እገሌ ጥፋት የለበትም ወደሚል ነገር አይደለም እየገባን ያለነው። [የቢሮው መብራት ጠፋ] ሠላም መብራት ከመጥፋት ጋር የግድ መያያዝ የለበትም። ዋናው ነገር፣ እዚህች ሀገር ውስጥ መልካም ነገር ሊሠራ እያሰበ ግን በሚፈልገው ደረጃ መራመድ ያልቻለ ግን በእውነተኛ የሕዝብ ተጠቃሚነት ላይ ተመሥርተው የሚነሡ ጥያቄዎችን በወጉ መመለስ የሚፈልግና መመለስ የሚገባው ፓርቲ አለ፤ መንግሥት አለ። እዚያ ላይ ተመሥርተን ነው መወያየት ያለብን። ከዚያ በዘለለ በቅርቡ በተፈጠሩ ችግሮች ላይ ተመሥርተን ማን ተጠያቂ ነው? ማን ተጠያቂ አይደለም? የሚለውን ለመወሰን በጣም ረጅም ጊዜ የሚወስድ አይመስለኝም።
አንድ ቀላል ጥያቄ እናንሣ፤ ብዙ ጊዜ የተቃውሞ ካምፑን የሚመሩ ፓርቲዎች ሠላማዊ ሠልፍ ማድረግ ይፈልጋሉና በመብትና ሕግ አግባብ ለሚመለከተው አካል ወደማሳወቅ ያመራሉ። በዚህ ዙሪያ የሚመለከተው አካልም ‹‹አይቻልም››፣ ‹‹በቂ የፖሊስ ኃይል የለንም››፣ ‹‹ቀን ቀይሩ››፣ ‹‹በዚህ ቦታ ሰልፍ ማድረግ አይቻልም›› ወዘተ. የሚሉ መልሶችን በተደጋጋሚ ይገለፅላቸዋል። ግን ሰልፍም ሆነ ሕዝባዊ ስብሰባ ለኢሕአዴግ ሲሆን ሁሉም ነገሮች ምቹ ናቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞም አድማ ለወጡ ሰላማዊ ሠዎች አድማ መበተኛ አስለቃሽ ጋዝ ጭስ መጠቀም ሲቻል፤ መግደል ለምን ያስፈልጋል? በዚህ ደረጃ ፓርቲው ለምን እመርታ ሊያሳይ አልቻለም?
ፓርቲና መንግሥትን ለጊዜው እንለየው፤ እና ሕገ-መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ መከበር መቻል አለበት። የሠላማዊ ሠልፍ ማድረግ ዴሞክራሲያዊ መብት ነው። ክልከላዎች አይደረግበትም፤ ገደቦች ግን ይደረግበታል። ሕገ-መንግሥቱን በደንብ ካየነው፤ የትም ሀገር ስትሄድ፣ ጊዜ ቦታና ሁኔታ የሚባሉ ነገሮች አሉ። መስጊድ አካባቢ ሠልፍ ላድርግ ካልክ አትከለከልም። ‹‹የፖሊስ ኃይል የለንም›› የሚለውን እንደ ተጋነነ አትቁጠረው፤ የፖሊስ ኃይል ላይኖር ይችላል።
ይሄ ግን ለኢሕአዴግ አይሠራማ፤ ይሠራል?
ሠልፎች ሲደረጉ ለምንድን ነው ፖሊሶች የሚያስፈልጉት? በቅድሚያና በዋነኝነት ሰልፈኞቹ እንዳያምጹ አይደለም። ከእነሱ አቋም በተፃራሪ ያሉ ወገኖች እንዳያጠቋቸው ነው። ስለዚህ በዝርዝር የኢሕአዴግ ሰልፎች ላይ ምን ጥያቄዎች ተጠይቀው እንደ ሆነ የማውቀው ነገር የለም፤ ርዕሰ-ጉዳይ ሆኖ ስለማያውቅ ማለቴ ነው። የኢሕአዴግ ደጋፊዎች የሚያደርጓቸው ሠልፎች የታወቁ ናቸው፤ የኢሕአዴግ ጉባኤ በድል ሲጠናቀቅ፣ ለግንቦት 20፣ ለሰንደቅ ዓላማ ቀን ወዘተ. ሊሰለፍ ይችላል። እዚህ ላይ ከኢሕአዴግ ጋር ሊያያይዘው የሚችል ነገር ያለ አይመስለኝም። ሠልፍ ፍቃድ የሚጠይቅ አይደለም። ተቃውሞ ታደርጋለህ፤ ቦታው ይታወቃል። አሁን ጥያቄው ያለው፣ የተቃውሞ ሠልፍ አደርጋለሁ ስትል፤ ተቃውሞ መብት ነው። የሆነ ሐሳብን የሚያቀነቅን ኃይልን ነው የምትቃወመው። ለተቃውሞ ስትወጣ ከለላ ትፈልጋለህ። መንግሥት ሊከለክል አይችልም፤ ሕገ-መንግሥቱ ስለፈቀደ። ግን ገደብ መጣል ይችላል። የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ልስጥ፤ መድረክ ሠልፍ ጠራ። ከስድስት ኪሎ ጀምሮ፣ በአፍንጮ በር መስጊድ በኩል አድርጎ አንዋር መስጊድ ይደርስና፣ የሆነ ቦታ ዞሮ ጥቁር አንበሳ ት/ቤትን በማለፍ ድላችን ሐውልት ጋር እቆማለሁ ብሎ ነበር። አባባሉ ሆነ ብሎ ለመከልከል የፈለገ ነው የሚመስለው። ሠልፍ ማድረግ የሚፈልግ ወገን እነዚህን መመዘኛዎች ሳይጥስ ሠልፍ ቢጠይቅና ባይሳካ ‹‹ለምን?›› ብዬ በመጀመሪያ የምሟገተው እኔ ነኝ።
ተቃዋሚዎች ላለፉት ዓመታት ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ እና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ለማድረግ ብዙ ሞክረዋል። ሰማያዊ ፓርቲ፣ የቀድሞ አንድነት፣ መኢአድ፣ መድረክ ወዘተ. ከአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የሚሰጣቸው መልስ አለመፈቀዱን፣ ዓለም አቀፍ ስብሰባ መኖሩን፣ ትራፊክ መጨናነቅ መፈጠሩን ወዘተ. ነበር። ጃንሜዳ እንኳ ተፈቅዶ የተከለከለበት ሁኔታ አለ።
ቋንቋውን አትቀይረው። ‹‹ተፈቅዶ›› ሳይሆን ‹‹ታውቆ›› በለው፤ ሰልፍ ላይ ፈቃድ የለም።
በሕጉ መሠረት ለሰልፍ ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ እንደማይጠበቅ እናውቃለንይ። ግን ‹‹ተከለከሉ›› ሲባል በተደጋጋሚ እናደምጣለን። በዚህ መሠረትም የተቃውሞ ድምፅ እየተሰማ አይደለም፤ ይሄ ደግሞ ሕገ-መንግስቱን የሚፃረር ነው።
አሁን እንደምትሉት ማዘጋጃ ቤት ‹‹አይ አትችሉም፤ ከልክያችኋለሁ›› የሚል ከሆነ፤ እውነትም እገታ እየተደረገ ነው።
ተቃዋሚዎች የሰልፍ ማሳወቂያ ደብዳቤ ይዘው ሄደው እንኳ በተለያየ ሰበብ-አስባብ ይመለሳሉ። ለተቃዋሚዎች ሠልፍ ማደረግ የማይቻልሉባቸውን ምክንያቶች በደብዳቤ የሚሰጣቸው ጊዜም እንዳለ ይታወቃል። ይሄንን እኛም ስንዘግብ ነበር።
እኔ ባለኝ መረጃ ላይ ተንተርሼ ነው የምመልሰው። ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ እስካለ ድረስ የሚከለከልበት ምንም ምክንያት የለም።
ፖሊስ በሰላማዊ ተቃውሞ አሰሚዎች ላይ ከበድ ያለ ችግር ከተፈጠ፣ ከግድያ ይልቅ አስለቃሽ ጭስ የማይጠቀመው ለምንድን ነው የሚለውን አልመለሱም?
እኔ እስከማውቀው ድረስ አስለቃሽ ጋዝ መጠቀም በሚኖርበት ጊዜ ይጠቀማል። ሁከት የሚፈጥር ዝንባሌ ሲኖር ደግሞ ዝም ብሎ ማየት ያለበትን እንዲሁ ያያል።
እንደዚህ ዓይነት ግድያዎችና አደጋዎች ከሚፈጠሩ ይልቅ ያንን አማራጭ ለምን አይጠቀምም? ለምሳሌ በኦሮሚያ ጉዳይ… ‹‹ድርጊቱ መንግሥታዊ ሽብርተኝነት ነው›› የሚሉም ወገኖች አሉ። ዳርፉር ላይ እንደተደረገው ሁሉ ‹‹አንድ ዘር ላይ የተነጣጠረ የግፍ አገዳደል ስለሚፈለግ ነው›› የሚሉ ኃይሎች አሉ።
እነሱ የሚናገሩት ውሸት ነው። ምክንያቱም ሠልፈኞቹ ሕጋዊ ጥያቄ ያላቸው ናቸው። ኦሮሞ የሚል ግምባራቸው ላይ አልተለጠፈም፤ አማራ የሚል ግምባራቸው ላይ አልተለጠፈም፤ ትግራይ የሚል ደረታቸው ላይ የለም። ስለዚህ በመጨረሻው ጊዜ እነዚህ ነገሮች ሲከሰቱ ከአጠቃላይ ዝግጅት አንፃር አስለቃሽ ጭስ መጠቀም ኖሮበት ያልተጠቀመ ኃይል ካለ መጠየቅ አለበት። ሁከትና ብጥብጥ ባለበት ሁኔታ ተዋክቦ ራሱን ለመከላከል ብሎ እርምጃ የወሰደ ካለም በዚያው ልክ መታየት አለበት። በዝርዝር በምናውቃቸው ነገሮች ላይ ተመሥርተን መወያየት አለብን። አጠቃላይ ሒደቱ አድማ የሚመስል ነገር ሲኖር አስለቃሽ ጭስ መጠቀም ሊያስፈልግ ይችላል፤ ላያስፈልግም ይችላል። ቆመህ የምታይበት፣ ጊዜ ወስደህ የምትመለከትበት ሁኔታም መኖር አለበት።
እዚህ ጋር ግን…
እያሳጠርነው።
ችግሩ ከባድ በነበረበት ወቅት በጽ/ቤትዎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኦሮሞን ሕዝብ በሚያዋረድ መልኩ ገልፀዋል በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ስምዎ ሲነሣ ነበር። የነበረው ሁኔታ እንደሚባለው ነው?
[ከተቀመጡበት ተነሥተው ቆሙ] እኔ ባለኝ ባሕርይ፣ በአስተዳደጌም፣ በማምንበት ድርጅት እና በምወክለው መንግሥትም ውስጥ ሕዝብን እንደ ሕዝብ የመስደብ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ተደርጎ ሲገኝ እንኳ ምህረት የለሽ እርምጃ መወሰድ አለበት ብዬ አምናለሁ። እኔ ይህንን በሚመለከት፣ ቃለ በቃል ያልኩትን ግምት ውስጥ ለማስገባት ያልኩት… ‹‹ለምን የተለየ መግለጫ መስጠት አስፈለገ?›› የሚል ጥያቄ ተጠየኩኝ። ‹‹አይ እስከ አሁን የነበረው የሕዝብ ሕጋዊ ጥያቄ ነው። ሕዝቡ ተገቢ የሚባሉ ጥያቄዎችን እየጠየቀ ነው የነበረው። በዚያ ላይ ተመሥርተን ጥያቄዎቹን ለመመለስ ሥራዎች ስንሠራ ቆይተናል። አሁን ግን ሕጋዊ ጥያቄ ከሚጠይቀው፣ ድንጋይ ከሚወረውረውም ሕዝብ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ በውጭ ኃይሎች የሚገፋ የታጠቀ ኃይል ተፈጥሯል። ይሄ የታጠቀ ኃይል ከሕዝብ ቁጥጥር ውጭ ሆኗል። ስለዚህ ይሄንን ኃይል ማስቆም አስፈላጊ ነው›› የሚል ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ – በአማርኛና በትግርኛ አባባል የጠፋ ይመስል – የእንግሊዘኛ አባባል ነበር፡፡ እና በቋንቋው አተረጓጎም ጊዜ አንዳንድ ወገኖች ተቀይመው ሊሆን ይችላል። እንጂ ሐሳቤ እንደ ተባለው አልነበረም። … ‹‹ጋኔንን የጠራ ደብተራ በጠራው ጋኔን ላይ ቁጥጥር ስለሌለው ይሄንን ጋኔን ወደ ቦታው የሚመልሰው መንግሥትና ሕዝብ ብቻ ናቸው›› የሚል ነው መልዕክቱ። ‹‹ጋኔን›› ያልኩት ሁከቱን ነው። ይሄ አገላለፅ በእኛም የሚዲያ አቀራረብ ትንሽ ቁንፅል አድርጎ የማቅረብ ልማድ በመኖሩና ተቃዋሚውም ያንን ማራገብ ስለሚፈልግ፣ በተጋነነ መልኩ አቅርበውት ካልሆነ በስተቀር፤ ሕዝብን የመስደብ ፍላጎት የለኝም። ከምንም በላይ ሕዝብን አከብራለሁ። በተቻለኝ አቅም እነሱን ያከበረ መልስ ለመስጠት ነበር የሞከርኩት።
[በቢሮ ስልክ ሰው ሊያነጋግሩ ወደ ጠረጴዛቸው አመሩ]ትንሽ ጥያቄ ትቀረናለች።
ሌላ ጊዜ እንቀጥላ?!
ብዙ አይደለም።
ቶሎ ቶሎ ጨርሱ።
ከላይ አንስተን ያልመለሱት ጥያቄ አለ። …እርስዎ በኦሮሚያው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጉዳይ ላይ ድንጋይ ስለወረወሩ ሰዎች እንጂ በጥይት ሰው ስለገደሉ ፖሊሶች ተጠያቂነት ሁኔታ ሸፋፍነው አልፈውታል። …በፖሊስና እርምጃው የቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይም በተደጋጋሚ በ‹‹ፀረ-ሠላም ኃይሎች የተደረገና የተሞከረ… ›› የሚል ውንጀላ ሲቀርብ አድምጠናል። በግልጽ መረዳት እንደ ተቻለው፣ ጉዳዩን ወደ ሆነ አካል ላይ ጣት የመቀሰር እንጂ መንግሥታዊ ተጠያቂነት በግልፅ አልታየም። በሕግ አግባብ ወታደር ወይም ፖሊስ ጥይት ተኩሶ ሰውን መግደል እንዲችል የሚፈቀደው መቼ፣ እንዴት እና ለምን የሚለውን ያስቀምጣል። ከዚያ በመለስ ሰው ተኩሶ መግደል የሚያስጠይቅ ወንጀል አይደለም ወይ? ተኩሰው ሕፃናን፣ ሴቶችን – ነፍሰ-ጡርን ጭምር – ስለገደሉት ወገኖች ተጠያቂነት ለመመለስ መንግሥት እየሸሸ ነው። በዚህ መንግሥት ተጠያቂ አይደለም ይላሉ?
መጠየቅ ያለበት ይጠይቃል። መንግሥት መጠየቅ ያለባቸው ሰዎች መጠየቅ የለባቸውም ብሎ አያምንም። ከላይ እንደገለጽኩት በጉዳዩ ላይ መጣራት ያለበት ነገር ሲጣራ የሚወሰን ይሆናል።
መንግስት በተግባር ይሄንን እያደረገ ነው?
እርግጥ! አዎን!
ተኩሰው ዜጎችን በገደሉ የፀጥታ ኃይሎች ላይ እውነት እየተጣራ ነው?
በተሠሩ ሥራዎች ላይ አዎን። ማጣራት ለእገሌ ለእገሌ ብለህ የምትተወው አይደለም። ‹‹እገሌ ይህንን ለምን አደረገ?›› ብለህ አጠቃላይ ማጣራት ነው የምታደርገው። በዚያ ላይ ተመሥርተህ ውሳኔ ላይ ትደርሳለህ።
በኦሮሚያ በተፈጠረው ችግር የተነሣ አቶ በቀለ ገርባ፣ ዮናታን ተስፋዬና ሌሎችም ተጠርጥረው ታስረዋል። በመንግሥት በኩል ሰውን የገደሉ የፀጥታ ኃይሎች ጭምር ተጠርጥረው አልተያዙም። በዚህ ላይ ሚዛኑን የሳተ ነገር እንዳለ ያሳያል።
አጠቃላይ ሥዕሉን በሚመለከት ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎችን በሚመለከት፣ ሙሉ እይታ ካለህ፣ እነማን ናቸው የተጠረጠሩት? በምን ምክንያት? የሚለውን በተመለከተ የጠራ ዕይታ አለህ ማለት ነው።
በመንግሥት በኩል ተጠርጥሮ የተያዘና የታሰረ ሰው ቢኖር ኖሮማ በሚዲያ እንሰማው፣ እንከታተለው ነበር።
መንግሥት የሠራውን መልካም ሥራ ብዙ ጊዜ ስለማትሰሙ ብዬ ነው። ለማንኛውም መንግሥት በቂ የማጣራት ሥራ ብቻውን ሳይሆን፣ ከሌሎች ወገኖቹም ጋር አድርጎ ተጠያቂነት ያለበትን ሰው ተጠያቂ የማያደርግበት ነገር የለም።
ይሄንን ጉዳይ ለመጨረሻ ጊዜ ስንጠቀልለው፤ ተኩሶ የገደለ የፀጥታ ኃይል ለሕግ ሊቀርብ ይችላል?
አዎን ሊቀርብ ይችላል።
ወደ ፕሬስ ጥያቄዎች እንለፍ፤ በመንግሥት በኩል፣ ጠንክረው በሚሰሩ የግል ሚዲያ ጋዜጠኞች ላይ በተደጋጋሚ የሚቀርብ ውንጀላ አለ። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ይታሠራሉ፣ ይሰደዳሉ፣ የተለያዩ ጫናዎች ይደርስብናል። የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚያወጧቸው ሪፖርቶችም ጭምር በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት እጅግ በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ከጊዜ ወደ ጊዜም ደረጃው እጅግ እያሽቆለቆለ እንደሚገኝ ይገልፃሉ። የግል ፕሬስ ይጀመራል፣ ይታፈናል፣ ይዘጋል… ። በመንግሥት በኩል ደግሞ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 29 በተግባር መከበሩ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይገለፃል። በተግባር ያለው ሐቅ ግን ያንን የሚያሳይ አይደለም፤ ተቃርኖ አለ። ይህንን ጉዳይ እንዴት ያዩታል?
በሁለት ነገር ነው የማየው። ለጥገኝነት ብለው የሚሰደዱ አሉ። ይሄንን መዋሸት አልፈልግም። እናንተም ይሄንን የምትዋሹት አይመስለኝም። ለምሳሌ ጋዜጠኝነት ውስጥ ገብተው የማያውቁ ሰዎች ኬንያ ወይም ካምፓላ [የኡጋንዳ ዋና ከተማ] ሄደው ‹‹ጋዜጠኛ ነበርኩ›› የሚሉ ሰዎች አሉ።
ከተሰደዱት መካከል ብዙ ጋዜጠኞችም ነበሩ።
አሉ፤ እውነት ነው። ጋዜጠኛ የነበሩ፣ ‹‹ስጋት አለብን›› ብለው የተሰደዱ አሉ። አሁን ስጋት አለብን ብለው በሄዱት ላይ መመስረት የለብንም። ያ ማለት በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ከሠሩት ሪፖርት፣ ከዘገቡት ዘገባ ጋር በተያያዘ የሆኑ ሰዎችን ጫና አይፈጥሩባቸውም፣ ወከባ አያደርጉም ማለት አይደለም። ስለዚህ መንግሥት በተጻፈ ጽሑፍ ላይ ተመሥርቶ ጫና ያደረገን ወገን መታገስ አይፈልግም። ይሄን ስል በዚህ ደረጃ ችግር የገጠማቸው ሰዎች የሉም እያልኩህ አይደለም። በእኛ እምነት፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነ ፕሬስ መፈጠር አለበት። መንግሥት አሳካዋለሁ ብሎ የያዘው ግብ አለ። ያንን ግብ፣ ‹‹የህዝብን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የመመለስ ጉዳይ ላይ አስተዋፅኦ ማድረግ›› የሚል ፕሬስ ነፃ ሆኖ፣ ለህሊናው፣ ለህዝብ ጥቅም ጥብቅና የሚቆም ፕሬስ መኖር አለበት። ያንን ፕሬስ ከመፍጠር ረገድ ትልቅ ስራ እንሠራለን ብለን ቃል ገብተናል። ያ ማለት የእገሌ የእገሌ ሳይሆን፣ የግል፣ የመንግስት ፕሬስ ሳይባል ነው። የሆነ የመንግስት የሥራ ኃላፊን ጥያቄ ውስጥ መክተት ሲጀምሩ፣ ሲጠይቁ ጫና ማድረግ የሚፈልግ ኃላፊ ያለበት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል፤ ያጋጥማልም። ይሄንን ተባብረን ነው የምንታገለው። ቢያንስ ከፕሬስ አንፃር መንግስት ያለው አቋም፣ የህዝብን እርካታ ማረጋገጥ አለብኝ ብሎ ያምናል። ስለዚህ ያንን ለማድረግ በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ የህዝብን የአገልግሎት እርካታ አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ ህዝብን ማገልገል ሳይሆን ህዝብ እኛን ማገልገል አለበት ብለው የሚያምኑ የበላይም የበታችም ሹሞች ሊኖሩ ይችላሉ። እነሱን ለማጋለጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነ ፕሬስ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል የሚል እምነት በመንግስት በኩል አለ። ከዚህ አንፃር [ጋዜጠኞች] በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ አስፈላጊ የተባለ ድጋፍ ተደርጎላቸው በእንቅስቃሴያቸው ላይ ችግር የሚፈጥር የፖሊሲ ማነቆ ካለ እሱ ተቀርፎላቸው ሥራ የማይሠሩበት ምክንያት የለም። ያ ማለት ግን የተገኘን አጋጣሚ ሁሉ ይሄን በነፃ ሀሳብ እንዲንሸራሸር የፈጠረን ስርዓት ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት በሚደረግ እንቅስቃሴ መተካት አለበት ማለት አይደለም። እሱ ላይ ሥርዓቱ ለራሱ ህልውና ሲል እንደዚህ አይነት ስርዓቱን በሁከት፣ በግርግርና በተገኘ አጋጣሚ ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ላይ እርምጃ ቢወሰድ የሚገርም አይሆንም። ‹‹ውጭ ሄደው ተሰደዱ›› የሚባሉትን ትተን ቢያንስ ቢያንስ ግን ገጥሞናል የሚሉትን ጫና እንደ ምንም ተቋቁመው እዚህ ሀገር ላይ የሚንቀሳቀሱ የሚዲያ ተቋማት ሕግና ስርዓትን አክብረው እስከተንቀሳቀሱ ድረስ ድጋፍ የማይደረግበት ምክንያት የለም። በዚያ ላይ ብንነጋገር ይሻላል።
ብዙ የግል ሚዲያዎች ከዚህ ቀደም ተዘግተዋል። ዛሬም ድረስ በእስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞችም አሉ። መንግስት በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ያሰርኳቸው ከጋዜጠኝነት ስራቸው ጋር በሚገናኝ ምክንያት አይደለም ሲል በተደጋጋሚ ይደመጣል። በተጨማሪም ‹‹በጻፈው ጽሑፍ የተከሰሰና የታሠረ አንድም ጋዜጠኛ የለም›› በሚል በተደጋጋሚ ይገልጻል። መሬት ላይ ያለው ሐቅ ግን ከዚህ ጋር ይጣረሳል። ለምሳሌ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፍትህ ጋዜጣ ላይ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሲሰራ በጻፈውና ባስተናገደው ጽሑፎች የተነሳ ተከስሶ በፍርድ ሂደት ሶስት ዓመት ተፈረዶበት፤ በዝዋይ እስር ቤት ይገኛል። እኔና አምሳሉ ገ/ኪዳንም ‹‹ዕንቁ›› መፅሔት ላይ በተስተናገደ አንድ ፅሑፍ ሁለት ዓመት ሊሞላው ለተቃረበ ጊዜ በጥቂት እስርና በረጅም የፍርድ ሂደት እየተንገላታን እንገኛለን።
እኔ በግሌ አንተ ላይ ያለኝን አጋርነት (Solidarity) ለመግለፅ ያህል፣ እንደማስታውሰው ከጽሑፍ ጋር በተያያዙ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለህ ወዲያው እንድትለቀቅ እንደ ተደረገ አውቃለሁ። [በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ አራት ቀናት፣ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ስድስት ቀናት ታስሬ ነበር፡፡]
በጽሑፉ ላይ ተመሥርቶ ክስ የሚመሠረትብህ ከሆነ፣ እንደምወክለው መንግሥት፣ ከጻፍከው ጽሑፍ ጋር ተመሥርቶ ክስ ሊመሠረትብህ አይገባም የሚል አቋም ይዤ እከራከራለሁ። አሁን እስከሚገባኝ ድረስ፣ ከክሱ ነጻ ወጥተሃል።
አልወጣሁም። እኔና አምሳሉ ገ/ኪዳን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት 2ኛ ወንጅል ችሎት ተከላከሉ የሚል ብይን ተሰጥቶን መከላከያ ምስክሮ ለማሰማት ለየካቲት 18 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ አለን።
ለማንኛውም ዝርዝር ክስህን በሚመለከት አይተን ቢያንስ የጻፍከው ጻሑፍ የትንጀኮሳ ካልሆነ …
ጽሑፉን እኔ አልጻፍኩትም። እኔ የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ ነበርኩ። አምደኛችን አምሳሉ ገ/ኪዳን የግል ሐሳቡን ጽፎ ተስተናገደለት…
ይሄን አብረን የምናየው ነው። አብረን የምንታገለው ነው። ያለ አግባብ ተከሰህ ያለአግባብ ችግር እየገጠመህ ከሆነ አንተ ጋር ሆኜ በዚህ ጉዳይ እከራከራለሁ። ዝርዝር ጉዳዩን ለማጣራት እሞክራለሁ። በዚያ ላይ ተመስርተን፣ ከሁከት ከግርግር፣ ከስርዓት መበተን በመለስ ባለው መንግስትን መንቀፍ፣ የመንግስትን እንቅስቃሴዎች የመንግስትን የሥራ ኃላፊዎች አግባብ ባለው መልኩ መንቀፍ ላይ በምትሠራው ማንኛውም ሥራ ሁሉ ምንም አይነት ችግር ሊገጥምህ አይገባም የሚለው የመንግስት እምነት ነው። የእኔም እምነት ነው። ያለአግባብ የገጠመህ ጉዳይና ክስ ካለ በዝርዝር አይተን ከአንተ ጋር ሆኜ እከራከራለሁ ማለት ነው።
በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ መሰረት ጋዜጠኞች ሲከሰሱ፣ ‹‹ከጋዜጠኝነት ስራቸው ጋር አይደለም›› ተብለው እስር ቤት የሚገኙት እነእስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ተመስገን ደሳለኝ … በቅርቡ ደግሞ የነገረ-ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በሽብር ወንጅል ተጠርጥሮ በማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ከታሰረ ሁለት ወራት ሊሞላው ነው። ከአንድ አመት ተኩል በላይ ከታሠሩ በኋላ ክስ ተቋርጦላቸው፣ ነፃ ተብለው ከእስር የወጡ ጋዜጠኞችና ጦማርያን አሉ። ጋዜጠኛና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉም ተከላከል ተብሏል። በአቃቤ ህግ ይግባኝ የተጠየቀባቸውም ጦማሪያን አሉ። እነዚህ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በማዕከላዊ ምርመራ ሲደረግባቸው የፃፉት ፅሑፍ በኢ-ሜይልና በፌስቡክ የተለዋወጧቸው መረጃዎች ማስረጃ ሆኖ ቀርቦባቸው ነበር። ይሄ መንግስት ከሚለው ጋር አይጣረስም? በፃፉት ፅሑፍ አይደለም በሚል በአንድ በኩል እየተናገረ ፅሑፍና ሙያዊ የመረጃ ልውውጥ ማስረጃ ሆኖ ይቀርባል። በምርመራ ላይ ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተጥሶ እየተደበደቡ ፅሑፍ ማስረጃ ሆኖባቸዋል በጫና የማያምኑት ላይ እንዲፈርሙም ተደርጓል። ጉዳዩ እልባት ሳያገኝም ዛሬም ድረስ ፍ/ቤት እየተመላለሱ ይገኛሉ …
አሁን ያቀረብከው ያንተ ጉዳይ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ስለሌሎች ተጠያቂነት ደረጃና መጠን ባላወከው ልክ የሁሉንም ጉይይ በአንድ ላይ ጠቅልለህ መናገር መቻል ትንሽ ከባድ ነው የሚሆነው። እያልን ያለነው፤ ሁሉም ሰው በቀረበበት ክስ ላይ ተመሥርተን እንወስን፣ እንይ። ያለአግባብ ከግምታቸው በላይ ቦታ የተሰጣቸው ወገኖችም አሉ። አንድ ደብዳቤ ፅፎ ራሱን እንደ ጋዜጠኛ የሚቆጥር ሰው አለ። ግን ዋናው፣ መደበኛ ስራው የሚባለው ሀገር ለማተራመስ የሚያስችል እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት ከሆነ፣ በሤራ ወዘተ. ተጠይቆ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ምናልባታዊ በሆነ ጉዳይ ላይ ተመሥርተን አንነጋገር።
ለማንኛውም፣ ይሄ መንግሥት ማንኛውም ሰው በጻፈው ጽሑፍ ላይ፣ ባቀረበው ተቃውሞ ላይ ተመስርቶ ክስ መመስረት የለብኝም ብሎ ያምናል። ዐቃቤ ሕግ በምን ላይ ተመስርቶ ክስ ሊመሠረት ይችላል በሚለው ላይ ዝርዝር መረጃ ሊኖረኝ አይችልም። ግን ያለ አግባብ ክስ ተመስርቶ ያገኘሁ ሰዓት፣ ‹‹ይሄ ጋዜጠኞችን መብት መድፈቅ ነው፤ የመናገር፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ነፃነትን አደጋ ላይ መጣል ነው!›› ብዬ በይፋ መከራከር እችላለሁ። ይሄን የምለው በግሌ አይደለም፣ የመንግስት አቋምም ስለሆነ ነው። መሆን የለበትም። አመሰግናለሁ! [ከተቀመጡበት ተነሡ፡፡ እኛም ከዚህ በላይ መጠየቅ አልቻልንም፡፡]
እኛም እናመሰግናለን!
Leave a comment