ከተስፋዬ አ.

(tes983398@gmail.com)

 

እንደ መግቢያ

እነሆ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ልጆች መመራት ከጀመረች 57 ዓመት ሊሞላት ጥቂት ወራት ቀራት። በእነዚያ 57 ዓመታት ውስጥ አሁን በመንበሩ ላይ ያሉትን ሳይጨምር 5 ፓትርያርኮችን አስተናግዳለች። እነዚህ አባቶች በዘመናቸው በቤተክርስቲያንና በምድሪቱ ላይ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈው አልፈዋል።

አቡነ ማትያስ ስድስተኛው የቤተክርስቲያናችን ፓትርያርክሲሆኑ፤ ከቀናት በኋላም ሦስተኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸውን ያከብራሉ። እኔም ‹‹መቼም ክፉም ይሁን ደግ ታሪክ ነውና መጻፍ አለበት›› የሚለውን የአባታችንን ቃል መነሻ በማድረግ ለበዓለ ሢመታቸው መታሰቢያ ይህን መጣጥፍ አዘጋጀሁ።(በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ያለው ቃል፣ አቡነ ማትያስ ራሳቸው በኢትኦጵ መጽሔት ላይ ስለ አቡነ ጳውሎስ ጉዳይ ሲጽፉ የተጠቀሙት ነው፡፡) መቼም የቤተክህነቱ ሹማምንት የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና እና የሐሳብን ልዕልና አጥበቀው ቢጋፉም፤ አንጻራዊ ነፃነቴን ማለትም ቢያንስ የቤተክህነቱ ሠራተኛና የየትኛውም ማኅበር አባል አለመሆኔንተጠቅሜ፣ ጥቂት ልተንፍስ። ከዚያ በፊትይህቺን፡- … በአንድ አባት ዘመነ ፕትርክና ነው አሉ። በቤተክህነቱ ብልሹ አሠራር ክፉኛ የተማረሩ ምእመን ፓትርያርኩ ባሉበት ስብሰባ ላይ ስለሙስናውም፣ስለዘረኝነቱም፣ስለኑፋቄውም እውነት እውነቱን በድፍረት ሲያወሩ የተደናገጡት ፓትርያርክ አጠገባቸው ወዳሉት አማካርያቸው ዞር ብለው፣ ‹‹[ብሔራቸውን መሰለኝ] ይህ ሰው ከየት ነው? የትስ ነው የሚሠራው?›› ብለው ጠየቁ። አማካሪያቸውም፣ ‹‹ከእኛ ነው።ግን የቤተክህነት ሠራተኛ አይደለም፡፡›› ብለው መለሱላቸው።›› እሳቸውም፣ ‹‹…እህ! ለዚህ ነዋ…በል ቀጥል የልብህን ተናገር።›› አሉ ይባላል። ወደ ነገሬ…

አቡነ ማትያስ – ቅድመ ፕትርክና

በአብዮቱ ዋዜማ የአሁኑ ፓትርያርክ የቀድሞው አባ ተክለማርያም አስራት ከሚለው ስማቸው ጋር ነበር ወደ ሀገሪቷ መዲና የመጡት።ሲመጡም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቀዳሽነት አገልግለዋል። ከሦስት ዓመት ቆይታ በኋላ የመናኙ የአቡነ ተክለሃይማኖትን ወደ መንበረ ፕትርክናመምጣት ተከትለው በ1968 ዓ.ም የፓትርያርኩ አቡነ ቀሲስና ምክትል ልዩ ጸሐፊ ሆነው ተሹመዋል። ለዚህ ሹመት ያበቃቸው ወታደራዊው ደርግ በወቅቱ ይከተለው የነበረው ርዕዮተ ዓለም እና የአባ ተክለማርያም ተክለ ቁመናና የፊት ገጽታ ነው።

አቡነ ቴዎፍሎስን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን በግፍ የገደለው የደርግአገዛዝ ለንጉሣውያኑ ከነበረው ጥላቻ በመነሣት ከነገሥታቱ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ጳጳሳት በሞት፣በእስር፣በጡረታና በስደት ከቤተክህነቱ ሲያስወግድ፤ በምትኩ ከነገሥታቱ ጋር ፈጽሞ ግንኙነት የላቸውም ብሎ ያመነባቸውን መናኙን አባት አቡነ ተክለሃይማኖትን ወደ ፕትርክናው አምጥቷል።በወጀብ እና በአውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ ያለው እግዚአብሔር በዚህ የደርግ የከፋ ሂደት እኒያን የመሰሉ ቅዱስ አባትን ለምድራችን አበርክቶልናል።

የአቡነ ተክለሃይማኖት ፍጹም መናኝነት ለደርግ ምቾት አልሰጠውም፣በባዶ እግራቸው መሄድ፣የላመ የጣመ አለመብላት፣በወርቅ የተንቆጠቆጠ ልብስ አለመልበስና ባጠቃላይ ወቅቱ ለሚፈቅደው መንግሥታዊ ሥነ ሥርዐት (ፕሮቶኮል) አለመገዛት፣ የአብዮቱን ልጆች ረፍት ነሳቸው፤ ለዚህም መፍትሄ ያደረጉት ባለግርማ ሞገስ የሆኑ አባትን በረዳትነት መመደብ ነበር። በዘመናዊ ትምህርት እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል የሚባሉትየአሁኑ ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ በተክለ ቁመናቸው ማራኪነትና እና በጺማቸው ውበት ለዚህ ተመራጭ ሆነው መቅረባቸው ይነገራል።

በደርግ መንግሥት መወደድን ያገኙት አባ ተክለማርያም አስራት፣ በ1969 ዓ.ም ከሌሎች መልእክተኞች ጋር በመሆን ወደ ጎንደር ተጉዘው ለኢዲዩ ድጋፍ እየሰጠ የነበረውን የቤጌምድር ደገኛ አርፎ እንዲቀመጥና ለደርግ እንዲገዛ ሊያስጠነቅቁ ተልከው ነበር፤ ስለጉዞው ዓላማ ብርሀኑ አስረስ፣ ‹‹ማን ይናገር የነበረ…የታኅሣሡ ግርግርና መዘዙ›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ፡-‹‹…ጉዳዩ ኢዲዩ /EDU/ የተባለ መንግሥትን የሚቃወም ኃይል በቤጌምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት ተነስቶ ቆላውን ይዟል። ወደ ደጋውም እየወጣ ነው። ደገኛው ከቆለኛው ጋር እንዳይተባበር መምከርና ማቆም አለባችሁ። ይህ ባይሆን ግን ደገኛው ከቆለኛው ጋር ከተባበረ መንግሥት ሥላጣኑን በዋዛ አይለቅም። ያለ የሌለ ጉልበቱን ተጠቅሞ መንግሥቱን ለማቆየት ይሞክራል።… ከደርግ አባላት ጋር ሄዳችሁ መክራችሁ ነገሩን እንድታቀኑ ነው የተፈለጋችሁት… ›› (ገጽ 401)››

ይህ በሆነ በሁለተኛ ዓመቱ በ1971 ከዶ/ር ክነፈ ርግብጋር ጥብቅ የሆነ ግንኙነት የነበራቸውአባ ተክለማርያም አስራት አቡነ ማትያስ በመባል የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ በመሆን ተሹመው፣ እስከ 1974 ዓ/ም ድረስ ለሦስት ዓመታት አገልግለዋል። (ክነፈ ርግብ በኮሎኔል አጥናፉ አባተ ተቋቁሞ የነበረውን ‹‹የጠቅላይ ቤተክህነት ጊዜያዊ የሽግግር ጉባኤ›› በሊቀ-መንበርነት የመሩ ናቸው፤ ጉባኤው በድኅረ አብዮት ቤተ ክህነት ላይ በርካታ ውሳኔዎችን ወስኗል፡፡)

የአቡነ ማትያስ የኢየሩሳሌም ቆይታ በመወገዝ ነበር የተፈፀመው። በአቡነ ተክለሃይማኖት የሚመራው የወቅቱ ሲኖዶስ አቡነ ማትያስ ላይ በተደጋጋሚ የቀረበን አቤቱታ ለማጣራት ጥሪ ቢያደርግላቸውም፣ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ስላልፈቀዱ፣ ቤተክርስቲያኒቱ በታሪኳ (ከኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ነፃ ከወጣች በኋላ) የመጀመሪያውን ውግዘት በአቡነ ማትያስ ላይ አካሄደች (Widu፡ ገጽ 366)፡፡በስማቸውም ሌላ ጳጳስ ሾመች፤ አሁንም በቤተክርስቲያኒቱ ሁለት አቡነ ማትያሶች ይገኛሉ።የተወገዙት የአሁኑ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስም ጓዛቸውን ሸክፈው ወደ ሰሜን አሜሪካ ተጓዙ።

የአቡነ ማትያስ መወገዝ በሲኖዶስ ይነሣ አይነሣ የሚለውን ለማረጋገጥ የጽሑፍም ሆነ የሰው ማስረጃ ባላገኝም፤ ለበዓለ ሢመታቸው የታተመ ‹‹የብፁዕ አቡነ ማትያስ አጭር የሕይወት ታሪክ›› የሚል መጽሐፍ ግን እንዲህ ይላል፡-  ‹‹ከ 3 ዓመታት የኢየሩሳሌም ቆይታ በኋላ በነበረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት በ1974 ዓ.ም በስደት መልክ ወደ አሜሪካን ሀገር ተሻግረው ለ10 ዓመታት ያህል ለስደተኞች ኢትዮጵያውያን መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡ ከቆዩ በኋላ እርቀ ሰላም ወርዶ በ1984 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ጠርቶ ወደ አዲስ አበባ በማስመጣት የአሜሪካንን ሀገረ ስብከት አጽድቆላቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በአሜሪካን አህጉረ ስብከት እየተዘዋወሩ ለ15 ዓመታት ያህል ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ሲያበረክቱ ቆዩ።››(ገጽ. 9)

የ15 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታቸው መንገራገጮች የበዙበት፣ ከአምስተኛው ፓትርያርክጋር ስምም እንዳልነበሩ፤ አብዝተውም በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ይሞግቷቸው እንደነበረ የተለያዩ መረጃዎች ይናገራሉ።አቡነ ማትያስ በአንድ ወቅት ለ‹‹ኢትኦጵ›› መጽሔት በላኩት ጽሑፍ ላይአምስተኛው ፓትርያርክ ለሲኖዶሱ ‹‹ክብር የሌላቸው››፣‹‹ለሲኖዶሱ የማይታዘዙ››፣‹‹በሲኖዶሱ ስም የሚያጭበረብሩ››፣‹‹የሰው ሀሳብ የማይቀበሉ››፣‹‹ተርእዮ (እዩኝ እዩኝ) ያለባቸው›› በሚሉጉዳዮች ከስሰዋቸው የነበር ሲሆን፤ ከአቡነ ተክለሃይማኖት ያላነሰ መወገዝም አድርሰውብኛል ብለው ሀሳባቸውን እንዲህ አስፍረዋል፡- ‹‹…የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀኖና፣ አንድ ጳጳስ በሕይወት እያለ ሌላ ጳጳስ በስሙ አይጠራበትም ነበር። ሟቹ ፓትርያርክ አቡነ ተክለሃይማኖት አረመኔውን ደርግን ለምን አወገዝህ ብለው በሕይወት እያለሁ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የእኔውን ስም ሌላ ሰው ሰየሙበት። አሁን ደግሞ ፓትርያርክ ጳውሎስ አቡነ ተክለሃይማት ከፈጸሙት ድርጊት ባላነሰ ሁኔታ ማትያስ ወዳለበት አካባቢ ሌላ ማትያስ መላካቸው ሆነ ብለው ለማደናገር የፈጸሙት ተግባር መሆኑን ለማንም ምስጢር አይሆንም…።›› (ገጽ 24) መጽሔቱ ለጽሑፋቸው ‹‹አትምጡ ስንላቸው መጥተው እኛንም በገማ እንቁላል አስደበደቡን›› የሚል ርዕስ ሰጥቶት ነበር።አቡነ ማትያስ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ፓትርያርክ እስከሆኑበት ዓመት ድረስ ለስድስት ዓመታት በውግዘት ወደ ተሰናበቷት ኢየሩሳሌም በመሄድ ሊቀጳጳስ ሆነው አገልግለዋል።

 

አቡነ ማትያስ- ድህረ ፕትርክና

ገና ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ ‹‹ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ አሜሪካዊ ነዎት››በሚል ዜግነታዊ ጉዳይ ከአንዳንድ አባቶች ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡት አቡነ ማትያስ፤ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ስድስተኛው ፓትርያርክ ሆነው በጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ ተመረጡ። በጊዜው መንበሩን ይረከባሉ ተብለው በብዙዎች ቅድመ ግምት የተሰጣቸው በበርካታ ምዕመናን ዘንድ ተወዳጅ የሆኑት ሌላ አባት ነበሩ።በተቃራኒው ግን ምክንያቱ ብዙም ግልጽ ባልሆነና ይፋ ባልወጣ ጉዳይ እኚህ አባት እጩ ሆነው ሳይቀርቡ ቀሩ። የእኚህ አባት እጩ ሆኖ ያለመቅረብና የአቡነ ማትያስ የዜግነት ጉዳይ በምርጫው ሂደት ላይ የራሱን አሉታዊ ጥላ ከማሳረፉ በላይ፣ የምርጫውን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ከቶት ነበር።ቢሆንምግን ድምፅ ከሰጠው 806 ሰው፣ 500 ድምፅ ‹‹አግኝተው›› አዲስ አጀንዳን ይዘው በአዋጅ ወደ መንበሩ መጡ።

ወቅቱ ቤተክህነቱ በክፉ ዘረኝነት፣በሙስና፣በኑፋቄና እና በአጠቃላይ በብዙ ችግሮች የተዘፈቀበት ስለሆነ፣ ምዕመኑ ይህን ችግር የሚቀርፍ ጠንካራ መንፈሳዊ አባት አጥብቆ ይሻ ነበር። ይህን ዘርፈ ብዙ ችግር ያወቁ የመሰሉት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ገና ከመነሻቸው ሙስናና ሙሰኞች ላይ ጠንከርያለ ማስፈራሪያ በመሰንዘር ወደ ህዝበ-ክርስቲያኑ ልብ ውስጥ ገቡ። በተገኘው መድረክ ሁሉ በሙሰኞች እና በመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ የእርዱኝ ጥያቄን አቀረቡ፡፡ ብዙዎች የሀሳባቸው ደጋፊ በመሆን ሊረዷቸው ቃል ገቡ።

ለዚሁ እንቅስቃሴ ይረዷቸው ዘንድ በራሳቸው በፓትርያርኩ አቅራቢነት የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስን ወደ መዲናዋ በማምጣትና የአዲስ አበባን ሀገረ ስብከት እንደ መነሻ በማድረግ የአስተዳደሩን እና የሙስናውን ችግር ይፈታል ያሉትን መዋቅራዊ ጥናት እንዲጠና አስወሰኑ። ጥናቱም ሀገሪቷ ወስጥ አሉ በሚባሉ ኦርቶዶክሳውያ ልሂቃን ቀንና ሌሊት ተሠርቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውይይት ቀረበ።የቀረበው ጥናት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያስቀመጠና ለተግባራዊነት የተዘጋጀ ከመሆኑ በላይ፣ ፓትርያርኩን ጨምሮ በከፍተኛ የመንግሥት አካላት ሳይቀር የተደነቀና የተወደሰ ነበር።ግን በጥናቱ ተጎጂ በሚሆኑ በኃላፊነት ላይ ባሉ ሙሰኛ ሹማምንት፣ የቤተክርሲቲያኒቱን ውድቀት በሚሹ ዘረኞችና በተሐድሶ መናፍቃንበተቀነባበረ ዘዴ ከሽፎ ቀረ። አጥኚዎቹም ሞራላቸው ክፉኛ ተነካ፤ የጥናት ቡድኑንበኃላፊነት ሲመሩ የነበሩት አቡነ እስጢፋኖስም በይፋ ከፓትርያርኩ ጋር መሥራት እንደማይችሉ ተናግረው ወደ ጅማ ሀገረ ስብከት ተመለሱ፤ከፊሎቹየጥናት ቡድኑ አባላት ደግሞ፣ በስድስተኛው ፓትርያርክ ዘመን የቤተክህነቱን ግቢጨርሶ እንደማይረግጡት ምለው ወደየሥራቸው ሄዱ። ፓትርያርኩ ጥናቱን ያከሸፉበት ምክንያት በጥናት ቡድኑ ውስጥ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት መኖራቸው እንደሆነ በተለያዩ ሚዲያዎች ተነገረ።

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በሁለተኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸው ማግስት ከሙስና እና ከመልካም አስተዳደር በመቀጠል ሁለተኛውን የዛቻ ምዕራፍ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ከፈቱ።ባይሳካላቸውም እንኳሙስና እና ብልሹ አሠራርን ላጥፋ አግዙኝ ያሉት አባት፤ አሁንም ማኅበረ ቅዱሳንን ላጥፋ እባካችሁ እርዱኝ ማለት ጀመሩ።ኅብረታቸውንም በፊት አጠፋዋለሁ ብለው ከዛቱበት ክፉ ተግባር አራማጆች (ከሙሰኞቹ እና ከተሐድሶዎች) ጋር በማድረግ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ማኅበረ ቅዱሳንን እዋጋለሁ፣ አጠፋለሁ ብለዋል ሲል ሐራ-ተዋሕዶ የተሰኘው ድረ-ገጽ ዘግቦት ነበር።

አቡነ ማትያስ በዚህ ብቻ አላበቁም፤ በቤተክርስቲያኒቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ፤ ለመንበሩም የማይመጥን ከፍተኛ የኾነ የሕግ ጥሰትና የተዋረድ ችግር ያለበት፤ ማኅበሩን ለክፉ አሳልፎ የሚሰጥ ደብዳቤን በምድሪቱ ላይ በተኑ (ይህንደብዳቤ ሳይ የንጉሥ አርጤክስስንና የእስራኤላዊቷ አስቴርንየሰመረ ግንኙነት ያላወቀው ሐማ፣ በእስራኤላውያን ላይ የበተነውን የሞት ደብዳቤ አስታወሰኝ። ሙሉ ታሪኩን እዚህ መጥቀሱ ጊዜ ቢወስድም፣ የደብዳቤው መጨረሻ ግን ሐማ በጠላቶቹ ላይ የደገሰው ሞት ለእሱ ፍፃሜ እንደሆነው ነው)።

ፓትርያርኩ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የያዙት የአጠፋሃለሁ ማስፈራሪያ እና ዛቻ የማኅበሩን ወቅታዊ ሁኔታ ካለማወቅ የመነጨ ይመስለኛል።ማኅበረ ቅዱሳን መንፈስ ነው፤የእነዚያ የቅዱሳን አባቶች መንፈስ። እሳቸው በውስጤ የለም ብለው ካልካዱ በቀር፣ አባል በሆኑትም ሆነ ባልሆኑት ውስጥ ያለ የአባቶቻችን መንፈስና እውነተኛ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ መንገድ ነው። ምናልባት ጊዜው ፈቅዶ ዕውቅናውን መቀማት ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን እሳቸውን ጨምሮ፣ ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል፣ ውስጣችን ያለውን ማኅበረ ቅዱሳንንማጥፋት አይችልም።

 

ማኅበረ ቅዱሳንን ለምን?

የዛሬን አያድርገውና አቡነ ማትያስ ወደ መንበረ ፕትርክናው ከመምጣታቸው በፊት፤ ቀና የሆነ አመለካከትና የዓላማው ደጋፊ ነበሩ፤ ከዚያም በላይ በአደባባይ የማኅበረ ቅዱሳን ምስክር ሆነው ይቀርቡ ነበር።አቡነ ማትያስ በሙስና አይታሙም ይባላል እንጂ፤ ዛሬ ላይ የአማሳኞቹ ቡድን ምርኮኛ ሆነዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ፓትርያርኩ በኑፋቄ አይጠረጠሩም፤ ነገር ግን ለተሐድሶዎችከለላ የሆኑ ይመስለኛል ብዬ አስባለሁ። ርግጥ ነው ማኅበረ ቅዱሳን ይዞት ከተነሣው ዓላማ አንጻር መናፍቃን እንደሚፈታተኑት፤ እውነት ነው ማኅበሩ የቤተክርስቲያኒቱን ውድቀት ለሚመኙ ሰዎች የጎን ውጋት እንደሆነ፤ የማኅበሩ ህልውና የእነርሱን ሞት እንደሚያፋጥነው ሙሰኞቹ እና መናፍቃኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ግን ፓትርያርኩን ምን አደረጋቸው? ለምንስ ፊታቸውን አዞሩበት? ለምንስ ለጠላት አሳልፈው ሊሰጡት ወደዱ?

ይህን ጽሑፍ ስጽፍ ካነጋገርኳቸው ሰዎች ከፊሎቹ ለዚህ ጥያቄ የፓትርያርኩን ከሦስት አስርት ዓመታት በላይከኢትዮጵያ ርቆ መቆየትና ለቤተክህነቱ ፖለቲካ ባዕድ መሆንን እንደ ምክንያት ሲያቀርቡ፤ ባለፉት ዓመታት ፓትርያርኩ ከአቡነ ተክለሃይማኖት ጋር የነበራቸው ግንኙነትንና በኋላ የተፈጠረው ልዩነትን፣ ከደርግ መንግሥት ጋር የነበራቸው ፍቅርን እና ዘግይቶ የተከሰተው ፀብ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ይመለከቱበት የነበረው የስስት ዓይን መቀየሩን ወዘተ. በመጥቀስ የአቡነ ማትያስን ምንታዌ ባሕርያት እንደምክንያት ያቀርባሉ፡፡ ጥቂቶችም የመናኙ አባት የአቡነ ተክለሃይማኖት ውግዘት እርሳቸው አሁን ላሉበት ያለመረጋጋት ሁኔታ ዳርጓቿል ይላሉ። እኔም ከዚህ በተለየ ሁለትጉዳዮችን ምክንያት አደርጋለሁ።

የመጀመሪያው ጥሩ ያሆነ ስሜታቸው ምክንያት በቤተክርስቲያንና በማኅበረ ቅዱሳን ታሪካዊ ጠላቶች እየተቀነባበረ የሚቀርብላቸው ማኅበሩ ባልነበረበት ዘመንእንኳ ከዚህ ዓለም ላለፉአባቶችየሞት ምክንያት በማድረግማኅበሩን እንደ ደም አፍሳሽ አድርጎ በማስፈራሪያነት የመጠቀም ሂደት ነው። ይህ ፓትርያርኩን የማሸማቀቂያ ክስ ግዘፍ የሚነሳው ከዚህ ቀደም የሞቱት አባቶች ለሞታቸው ምክንያት ማኅበሩን መንካታቸው ነውበሚልወሬና ወሬውንም በተደጋጋሚ ፓትርያርኩ ጆሮ በማድረስ ነው። ይህ ወሬ ማኅበሩና ፓትርያርኩ በዓይነ-ሥጋ እየተያዩ እንዳይነጋገሩ ከማድረጉ በላይ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ክፉኛ እንዲፈሩና አጥብቀው እንዲጠሉ አድርጓል።

ሌላኛው፤ ፓትርያርኩ ሙሉ ጊዜያቸውን ማኅበሩን ለማጥፋት እንዲሰሩ ያደረጋቸው ምክንያት፣ ለማኅበረ ቅዱሳን መጠንሰስቀዳሚ ተጠቃሽ ለሆኑት ለቅዱሱ አባት ለአቡነ ጎርጎርዮስ ካልእሊቀ ጳጳስ ዘሸዋ ያላቸው ለዘመናት ተዳፍኖ የቆየ አሉታዊ አመለካከት ነው።አቡነ ጎርጎርዮስ እና አቡነ ማትያስ ዘመነኞች ናቸው፤ ሁለቱም በ1971 ዓ.ም ነበር የጰጰሱት። ለዚህ ጽሑፍ ይረዳኝ ዘንድ ያነጋገርኳቸው አንድ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ለመመሥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የዝዋይ ገዳም አባትእንዳጫወቱኝ፣ አቡነ ጎርጎርዮስ በአቡነ ማትያስ ደስተኛ አልነበሩም፤ በወቅቱ አቡነ ማትያስ ከፖለቲካውና ከፖለቲከኞቹ ጋር የነበራቸው ፖለቲካዊ ቅርበት እንደነበርና አቡነ ጎርጎርዮስ  በአቡነ ማትያስ መወገዝ  ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን አውግተውኛል።

በአቡነ ጎርጎርዮስ የተጻፈውና በቤተክርስቲያኒቱ የጥናት መስክ ላይ ተጠቃሽ የሆነውአሁንም በተደጋጋሚ እየታተመ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ››የተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 84 ላይም በእነአቡነ ማትያስ ዘመን የነበሩትን 22 ጳጳሳት ከእነ ኃላፊነታቸው ሲጠቅስ፤ አቡነ ማትያስን ግን በመወገዛቸው ምክንያት አልጠቀሳቸውም። ይህም አቡነ ማትያስ ጮኽ ብለው የማያወሩትን የውግዘታቸውን ጉዳይ ዘላለም እንዲታወስ ያደርገዋል። ሌላው ማኅበሩ የትምህርት ተቋማቱን በአቡነ ጎርጎርዮስ ስም መሰየሙ፣ በተለያዩ ቦታዎች እና በኅትመት ውጤቶቹ ላይ ለቤተክርስቲያን ካደረጉት አስተዋፅኦ አንጻር ደጉን አባት መዘከሩበፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ዘንድ ካለመወደዱም በላይ፣ ታሕታይ ምስቅልቅ የፈጠረባቸው ይመስላል።

 

ስደመድመው

ቤተክርስቲያኒቱበ57 ዓመታት ታሪኳ ውስጥ እንደዚህ ጊዜ በብዙ የቤት ሥራዎች የተወጠረችበት ወቅት የለም። በአንጻሩም እንደዚህ በከንቱ የባከኑ ሦስት ዓመታትም አጋጥሟት አያውቅም።

ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ በሦስት ዓመታት የፕትርክና ጊዜ ውስጥ የስብከተ ወንጌል ድርጅት አቋቁመዋል፣ 17 ሊቃነ ጳጳሳትን ሾመዋል።ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ የልማት ኮምሽንን መስርተዋል፣ ሰበካ ጉባኤን አቋቁመዋል፣ 7 ሊቃነ ጳጳሳትን ሾመዋል። መናኙ አባት ፓትርያርክ አቡነ ተክለሃይማኖት 28 ጳጳሳትን ሾመዋል፣ ተዘግቶ የነበረውን ስዋሰወ ብርሃን ኮሌጅ አስከፍተዋል፣ ለአብነት መምህራን ደሞዝ እንዲከፈላቸው አድርገዋል። በአስቸጋሪ ወቅት የነበሩት ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ (አባ ዘሊባኖስ) ቢያንስ 6 ጳጳሳትን ሾመዋል።  በበርካታ አወዛጋቢ ጉዳዮች የሚታወቁት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እንኳ በሦስት አመት ውስጥ በርካታ ጳጳሳትን በመሾም አህጉረ ስብከቶችን አስፋፍተዋል፣ አገልግሎት አቁሞ የነበረውን ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን አስከፍተዋል፤ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ፣ ሲኖዶሳዊ  የሕግ ማእቀፍ በማበጀት ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል።የቀደሙት ፓትርያርኮች ይህን እና ሌሎች መልካም ተግባራትን በተሾሙ በሦስት ዓመታት ውስጥ ሲፈጽሙ፣ ስድስተኛው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ግን ከወረቀት ያለፈ ይህ ነው የሚባል ተግባር የፈጸሙ አይመስለኝም።

የፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የሦስት ዓመታት የሥራ ፍሬዎች ከብፁአን አባቶች ጋር በስምምነት አለመስራት፣ ያለምንም መንፈሳዊ ፋይዳ አሜሪካ መመላለስ (በሦስት ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ሄደዋል)፤ የማኅበረ ቅዱሳንን ጉባኤያት፣ የውይይት መድረኮችና የቴሌቭዥን ፕሮግራምን ማገድ፣ማኅበሩንማእከል ያደረጉደንቦችና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ከአገልግሎት ማደናቀፍ ወዘተ. ናቸው የሚል ግምት አለኝ።

ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ከመሆናቸው በፊት፣ ፓትርያርኩ ያሳለፏቸውን ሦስት ዓመታት በማስተዋል መገምገም እና መጪውንየመንፈሳዊ የአገልግሎት ዘመናቸውን ቢያጤኑት እላለሁ፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አምላክም ይርዳቸው።

 

ከጽዮን ምሕረት ለኢትዮጵያ

ምንጭ፡-

ጎርጎርዮስ (ሊቀ ጳጳስ ዘሸዋ) 1974፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ

መርሻ አለኸኝ (ዲ/ን) ፣1996፤ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን

የብፁዕ አቡነ ማትያስ አጭር የሕይወት ታሪክ፣ 2005

ብርሀኑ አስረስ፣ 2005፣ የታኅሣሥ ግርግር እና መዘዙ

ጌታቸው ኃይሌ፣ 2006፣ አንድአፍታ ላውጋችሁ፤

Widu Tafete ( Diss) , 2006, The Ethiopian orthodox Curch , the Ethiopian State and the Alexanderian See : Indigenizing the Episcopacy and Forging National Identity, 1926-1991

አቡነ ማትያስ ፤ 1992 ፤ አትምጡ ስንላቸው መጥተው አስደበደቡን ፤ (ኢትኦጵ) ቅጽ 1፣ቁ 6

 

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *