ተማም አባቡልጉ
ተማም አባቡልጉ

እንኳን አደረሳችሁ! የዘንድሮውን የድል በዓል ልዩ የሚያደርገው አርበኞች አባቶቼን በጦር፣ በጎራዴ …ወዘተ የኢጣሊያንን ፋሽስት ቅኝ ገዢ መንግስት ለአምስት አመታት በዱር በገደሉ ተዋድቀው ድል በመምታት ለሁለተኛ ጊዜ አሳፍረው ከሀገር በመባረር ያስረከቡን ነፃነት እኛ ልጆቻቸው በ21ኛው ክፍለዘመን ዳር ድንበራችንን መጠበቅ አቅቶን ውድቅዳቂ መሣሪያ የታጠቁ የደቡብ ሱዳን ጎሳዎች ድንበራችንን ዘልቀው ገብተው ያሻቸውን መጠን ዜጎቻችን ገድለው፣ አቁስለውና የቻሉትን ያህል ልጆችና ከብቶች ዘርፈው ሲሄዱ በአቅመቢስነት ቁጭ ብለን ያየንበት መሆኑ ነው፡፡በአጭሩ የእሳት ልጅ አመድነታችንን በተግባር መረጋገጡ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ሰሞኑን ‹‹ኢሕአዴግ ስለጦር ችሎታውና ጀግንነቱ እንደሚደነፋው ሳይሆን የማይዋጋውና የሚያረሳሳው ሙርሌን እንኳ የማይወጋው እንደሚባለውና እንደሚለን ሳይሆን ጠንከር ያለ ነገር ከገጠመው ውጊያም ስለማይችል ነው›› በሚል ከአንድ ወዳጄ ጋር አወጋን፡፡ የእኛ ካለመሆኑና ለእኛ ካለመቆሙም በተጨማሪ ለማስመሰል እንኳ ያንን ያልሞከረው በዚህ ሊሆን ይችል ይሆን?
አንድ የኦሮሞ ተረት አለ ‹‹የምትችለውን ምታ ሲሉት ሞኝ ገብቶ ሚስቱን ደበደበ›› የምትል ናት፡፡ ኢሕአዴግ ‹‹ለምን የውጭ ወራሪዎችንና ጥጋበኞችን አትከላከልልንም?›› ስንለው ‹‹እነሱን ሳይሆን በእርግጠኝነት የምችለው እናንተን መደብደብ ነው›› በሚል ወደኛ ዞሮ ምንም መሣሪያ ባልያዝን እና ባዶ እጃችንን መብታችን በጠየቅነው ዜጎች ላይ የሚፎክረውና የሚተኩሰው እንደሚጮኸው ሳይሆን የሚኩራራበትን ጦርነትም ባይችል ነው የሚል እምነት እየያዝኩ መጥቻለሁ፡፡
በእነኦባማም አፍ ያንን ማስነገሩ፣ በተግባር ያላየነው ስለሌለው ቢሆን ነው እያልኩምነው፡፡ ቢያንስ ጀግና አይደለም፣ በሱማሌም ያደረገው ጦርነትና ከኤርትራ ጋር በእኛ ድጋፍ ያደረገውም የሚያሳየው ብዙ ሰዎች አስገድሎ በማይመጣን አቅም የተደረጉ ስለሆነ ብቃቱን አያሳዩም፣ ከደርግ ጋር የተደረገውም ቢሆን የህዝብ እምቢተኛነትን(ፅናትን) እንጂ ብቃትን የእርሱን የጦር ችሎታ አያሳይም፡፡ ፅናቱ በብቃት ካልተተካ በሀገር ደረጃ ሳይንሳዊ ለሆነ ሙያ ደግሞ አያስተማምንም፡፡ ያ ደግሞ አልሆነም፡፡ የሠለጠኑ አመራሮች ጦሩን በመሪነት አልያዙትም፡፡
ስለዚህ ኢህአዴግ እኛን ለመከልከል የሙርሌ ጎሳዎችን ሊፈራረም ይችላል፣ ምክንያቱም እነዚህ በእሱ ቁጥጥር ስር ያልሆኑና እሱ ፈጥሮ የላካቸው ካልሆኑ በግንባር ገጥመውት ሊያመጡበት የሚችለውን እርግጠኛ ስላልሆነና ይህም በራስ ካለመተማመን ስለሚመጣ ነው፡፡ በማኪያቬሊ አባባልም መሠረት ‹‹ስለችሎታቸው የአፍ ፕሮፓጋንዳ በዝቶ በተግባር ምንም የሌለው፣ እውነቱ የተግባሩ ሆኖ አብዛኛው ሕዝብ የሚባለውን እንጂ የሚሆነውን አያይም›› ከሚል በአፍ አሳምኖ በማስቦካት ተፈሪ አድርጎ ለማስቀጠል የተደረገ ሙከራ ሊሆን ይችላልና ነው በሚል እኔም አምኜዋለሁ፡፡ ሊሆን ይችላል ብያለሁ፡፡
የዘንድሮውን የፕሬስ ቀንም ልዩ የሚያደርገው የሀገራችንን ነፃ ፕሬስ ፋና ወጊዎችንና ፊታውራሪዎችን ማለትም ዋና አባቱን እስክንድር ነጋንና ተከታዩን ተመስገን ደሳለኝን እስር ቤት በመክተት የነፃና ነፃነትን ትርጉም በምናሰላስልበት ወቅት መከበሩ ነው፡፡ መከበር ራሱ ምንድን ነው? ኒኮሎማኪያቬሊ ‹‹በአብዛኛው ሰው(ዜጋ) የምትናረውን ወይም የምትለውን እንጂ የምታደርገውን ስለማያይብህ የማታደርገውን በል፡፡›› እንዲል የፕሬስ ነፃነት የማይከበርባቸው ሀገራት የፕሬስ ቀንን በደማቅ ሁኔታ ያከብራሉ፡፡ የኢትዮጵያም ሁኔታ ከዚህ ውስጥ የሚደመር ይመስለኛል፡፡
ዩሱፍ ጌታቸውና ውብሸት ታዬም ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ያሉት እሥር ቤት ነው፡፡ ማኪያቬሊ ‹‹የአምባገነኖቹን ውሸት የሚያውቁትንና የሚረዱትን ጥቂቶችን ደግሞ እብዶች ናቸው›› በሏቸው ብሎም መክሯል አሉ፡፡ በብዙዎች ዘንድ በብዛት ያለቦታውና አግባቡ (out of context) እንዲሁም ያለትርጉሙ ትርጉም እየተሰጠው የሚጠቀሰውና ግንዛቤ የተወሰደበትን ይህን የፖለቲካ አዋቂ ወይም የሴራ መምህር እንድታነሱትና እንድታረጋግጡ በማለት ነው “አሉ” የሚለውን የተጠቀምኩት፡፡
ወደጉዳዬ ስመለስ፣ ሰሞኑን በሽብር ከተከሰሱት ውስጥ ዮናታን ተስፋዬ ይገኝበታል፡፡ ይህ ወጣት ፖለቲካኛ የሠማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ እናውቀዋለን፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ኦነግ ነው ተባልን፡፡ ለመሆኑ ኦነግነት ራሱ ምንድን ነው? በምንስ ይረጋገጣል? ወይስ ኦሮሞ መሆን በራሱ እና/ሲደምር መብትን መጠየቅ የኦነግነትን ግምት ያስወስዳል? ሃሳብን የመግለፅ መብት ዳር ድንበሩ የትነው? ይህ የሚያበቃበት ነጥብና የማነሳሳት ወንጀል የሚጀምርበት ነጥብ የቱጋ ነው? ሽብር ምንድን ነው? ሽብርተኛስ ማን ነው? አሸባሪው እና የሚሸበረውስ ማን ነው? ሽብር ስለምን በማን ማን ላይ የሚፈፀም ወንጀል ነው? በሽብርና በሌሎች ወንጀሎች መካከል ያለው ልዩነትና አንድነት ምንድን ነው? በጽሑፍና በቃል የሚፈፀም የሽብር ወንጀል የቱ ነው? በኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ሰዎችን በውሸት የሽብር ወንጀል መክሰስና ማስከሰስን እራሱ የሽብር ወንጀል ስለሚያደርግ ከዚህ አንፃር በውሸት በሽብርተኝነት ተከስሰው ነፃ የተባሉ የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ አባላትና ሌሎች በብዛት ስላሉ እነዚህን በውሸት በመክሰስ እሥር ቤት ያከረሙ አካላት (የኢሕአዴግ መንግስት መሪዎች) መቼ ነው በሽብር ወንጀል የሚከሰሱት? የግል አቤቱታ ሳይቀርብ ነው መከሰስ ያለባቸውና እስካሁን ለምን አልተከሰሱም? ወይስ ሕግ የገዢው መደብ የመግዣ መሣሪያ ስለሆነ በነሱ ላይ አይሠራም? እነሱ ላይ ካልሠራ ለምን እኛስ ሕግ ነው ብለን እናክብረው? ሕገ-መንግስት ጥሰት ብቻ ሳይሆን ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን መናድ ስለሆነ ራሱ የናደውን ሥርዓት ‹‹ልትንዱ ነበር›› በሚል ሰውን መክሰስስ ለምን ሊፈፀም የማይቻል ወንጀል (coupde grace) አይሆንም? ወዘተ እያሉ መቀጠል ይቻላል፡፡
እርግጥ ነው፣ ለእነዚህ ሁሉ መልስ መስጠት ያለበት ኢሕአዴግ ነው፡፡ ራሱን መክሰስ ያለበትም ራሱ ነበር፡፡ ሐጢያቱ የሚሠረይለት ይህንን ቢያደርግ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ‹‹ኃጢያተኛ አይደለሁም›› ካለ ደግሞ በርግጥም ‹‹ኃጢያት የለም›› ማለት ብቻ ነውና ሊሆን የሚችለው፡፡ ይህ መዳኘት አይደለም እውነት መናገር ነው፡ ፖለቲካና ሃይማኖትን በማገናኘት ባንዱ ሌላኛውን እየዳኘሁና እያስረዳሁ አይደለም፣ ፖለቲካ በሌለበት (ፖለቲካ ውሸትና ጉልበት ብቻ ነው ካልተባለ በቀር እዚህ የለምና) ሀገርን ማመስ ሕዝብን ማሰቃየት አባትን ከልጅና ከሚስት እየነጠሉ ማሠር፣ በውሸት የሠውን ስም ማጥፋት በአደባባይ ሕፃናትን፣ አዛውንትንና ሰብዓዊ ፍጡር መረሸን ወንጀል፣ ኃጢያትና እብደት ካልሆነ ምን ሊባል ነው? አረመኔነት ጨካኝነትና ነውረኛነት የተሞላባቸው እነዚህ ድርጊቶችስ ለአድራጊው ባህሪና የጤንነት ሁኔታስ የሚነግሩን ምንድን ነው? ይህንን ድርጊት የሚያዙትና የሚፈፅሙትን ሁሉ እብዶ ወይም ስልጣን ሀብት ወይም ትዕቢት ወይም ሌላ የሰከራቸው ከማለት ውጪስ በምልንጠራቸው እንችላለን? እነዚህን ፖለቲከኞች ብሎ የሚጠራ ካለ የፖለቲካ አምላክ እንዲሁ የሚተዋቸው አይመስለኝም፡፡ እነዚህ ጤነኞች የሚባሉት ግን ይህንን የሚፈጽሙት የሚፈልጉትን በስልጣን ላይ እንዲሁ ዝም ብለው የመቆየት ፍላጎታቸውን ስለሚያሳካላቸው ነው የሚሉ ቢኖሩም የስልጣን ትክክለኛ ዓላማ ያ ባለመሆኑ ብቻ ሳይሆን እንዲሁ አንድ ቦታ ላይ እንደሆኑት ሆነው ሳይለወጡ መክረም የተፈጥሮ ሕግ ከሆነው የለውጥ ሕግ ጋር የሚጋጭ ስለሆነ የሚሆን አይሆንም፣ በርግጥ ይህን የማስቀረት ግዴታ ያለው በዚህ ድርጊት በሚጎዳውና የሀገሩ ባለቤት በሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ነው፡፡
አሁንም ወደጉዳዬ ልመለስ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ያለው ኢትዮጵያዊ ሕዝብ መብቱን ጠየቀ፡፡ ኢሕአዴግም በሕዝቡ ላይ እየተኮሰና እየገደለም የሕዝቡ ጥያቄ ሕጋዊ ነው አለ፡፡ በአፉ መልሻለሁ አለ፡፡ እነበቀለ ገርባንና ዮናታን ረጋሳን በማነሳሳት ወንጀል ብቻ ሳይሆን የሽብርን ድርጊት በማነሳሳት ደግሞ ከሰሳቸው፡፡ አነሳሱት የሚለው ደግሞ ኢሕአዴግ ራሱ የመብት ጥያቄና ሕጋዊ ነው ያለውን በኦሮሚያ ክልል ሕዝቡ መብቱን የጠየቀበትን ድርጊት ነው፡፡ ሕጋዊ መብትን መጠየቅ ማነሳሳት እንዴት ለምንና በምን ሕግ ወንጀል ይሆናል? ይህን ሰምተን በሳቅ ያልሞትን ኢትዮጵያውያን የሕግ ባለሙያዎች በእርግጥ ምን ማድረግ እንዳለብን አላውቅም፡፡
በኦሮሚያ ውስጥ ለፍርድ መቅረብ ያለባቸው ብቸኞቹ የወንጀል ድርጊት ፈፃሚዎች የኢሕአዴግ የጦርና የሲቪል ባለሥልጣናት ብቻ ሲሆኑ እነሱም ሕዝቡን በመረሸን ያለፍርድ በመግደል (Summery execution) እስረኛን በመደብደብ …ወዘተ በሰብዓዊነት ላይ በፈፀሙት ወንጀል መሆን ይኖርበታል፡፡ (በ1987 ኢህአዴግ ያወጣውን ሕገ-መንግስት አንቀፅ 28 ይመልከቱ፡፡) ራሱ የማያከብረውን ሕግ ሌላውን አክብር ማለት ንጉስ ነኝ ማለት ካልሆነ እብደት ይሆናል፡፡ ኢሕአዴግ ለሕዝብ ክብር አለኝ የሚለው ውሸቱን ነው፡፡ እነበቀለ ገርባን በሽብር ሲከስ የኦሮሚያ ክልልን መብት ጠያቂ ኢትዮጵያዊ ድርጊትን የሽብር ድርጊት ነው እያለ በመሆኑ የሕዝብን መብት ማክበር ይቅርና፣ ሕዝብን ያውቃል ወሳኝነት አለው ብሎ መቀበል ይቅርና በድርጊት አሸባሪ ነህ ወይም የሽብርን ድርጊት የሚፈፅም አካል ነው በማለት ሕዝቡን መፈረጁ ለሕዝቡ ያለውን ንቀት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይም ስለሆነ ነው፡፡
የፀረ ሽብርተኝነት ዓላማ በሕዝብ ላይ የሚፈፀምን ወንጀልና የጦርነት ድርጊት ያልሆነን ጥቃት መከላከል ነበር፡፡ መንግስት ከሕዝቡ የሚቀርብለትን የመብት ጥያቄ ላለመመለስ የሚከላከልበት ጋሻ አልነበረም፣ በኢትዮጵያ የሆነውና እየሆነ ያለው ግን ይህ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ከዚህ ቀደም በዝርዝር በኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣና በሌሎች ላይ አቅርቤያለሁ፡፡ ሀበሻ የፀረ-ሽብር አዋጅን ያህል ነገር አስቀምጦ ገብቶ መተኛቱ የጤና አለመሆኑን በሕግ ቋንቋና በማስረጃ በማስደገፍ አስረድቻለሁ፡፡ ስለመንግስታዊ አሸባሪነትም ገልጫለሁ፡፡ እነአቡበከር አህመድ የሕዝበ-ሙስሊሙ ወኪል በመሆን ኢህአዴግ ሕጋዊ ነው ያለውንና ኋላ ላይ መለስኩ ያለውን የኢትዮጵያ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ የመብት ጥያቄዎችን በመያዝ ከሱ ጋር ሲደራደሩ ነበር፡፡
በአፉ ይህንን የሙስሊሙን የመብት ጥያቄ ‹‹ሕጋዊ ነው›› እያለ በተግባር ግን ይህንን ጥያቄ በውክልና ያመጡለትንና እሱም ተቀብሎ ሲደራደራቸው የነበሩትን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አካላትን የፀረ-ሽብር አዋጁን ጠቅሶባቸው ክስ አቅርቦባቸው የእሥራት ውሳኔ አስተላለፈባቸው፡፡ በዚህም የሙስሊሙን ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ በተግባር የፈፀምከው የሽብር ድርጊት እንጂ የመብት ጥያቄ የማቅረብ ሁኔታ(ድርጊት) አልነበረም በማለት ፈረጀው፡፡
የኦሮሚያ ክልል ኢትዮጵያዊ ሕዝብም ሆነ የሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ የመብት ጥያቄ ማቅረብና አቀራረብ የሽብር ድርጊት ካልሆነና ካልተባለ በቀር እነአቡበከር አህመድ፣ እነበቀለ ገርባና ዮናታ ረጋሳ የሽብር ድርጊት አነሳሳችሁ ተብለው ሊከሰሱና ሊፈረድባቸው ወይም ሊከሰሱ አይችሉም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ኢሕአዴግ፡-
(ሀ) የኦሮሚያ ክልን ወይም ሙስሊም ኢትዮጵያዊውን ሕዝብ በጅምላ ሽብርተኛ አድርጎ ፈርጇል ወይም በዚህም
(ለ) ለእሱ የሽብር ድርጊት ማለት የመብት ጥያቄ ማቅረብ ነው ወይም
(ሐ) የሕዝብን የመብት ጥያቄ መመለስ ሳይሆን ይህንን ጥያቄ በውክልና ያቀረቡትን በማሰር ለሕዝብና ለሕዝብ የመብት ጥያቄ ያለውን ንቀትና ጥላቻ አሳይቷል(ያሳያል) ማለት …ወዘተ ይሆናል፡፡ ለኢሕአዴግ አሸባሪ መብት ጠያቂ ሕዝብና ወኪሎ ናቸው ማለት ይሆናል፡፡
ካልሆነና በርግጥም ኢህአዴግ የሕዝብን ሕፃን ያለመሆንና የራሱን መብት አውቆ መጠየቅ መቻልን የሚቀበልና ለሕዝብ የመብት ጥያቄ መልስ ለመስጠት የቆመ መሆን ይቅርና ሕዝብ ራሱን የሚያውቅና መብት ያለው መሆኑን በአፉ እንደሚለው ከተቀበለ እነአቡበከር አህመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ዮናታን ተስፋዬና ሌሎችም የታሰሩት ምንም ወንጀል ሳይፈፅሙ ነው ማለት ይሆናል፡፡
ስለሆነም ኢህአዴግ እነዚህን የሕሊና እስረኞች ዛሬውኑ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ይቅርታ ጠይቆ ከእሥር ቤት መልቀቅ አለበት፡፡ ካልሆነ ግን በኦሮሚያ ክልል ያለውን እና ሙስሊሙን ኢትዮጵያዊ መብት ጠያቂ ሕዝብ እንዳለ ሽብርተኞች ናቸው እያለ መፈረጁ መሆኑ ይሆናል፡፡
አብዛኛው ሰው የሚባለውን እንጂ የሚደረገውን ላይመለከት ይችላል፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ በዚህ ላይ ትልቅ ምላስ አውጥቶ ከፍ ያለ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ሰርቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ግን እውነቱን አይለውጠውም፡፡ እውነቱ ደግሞ ከላይ የተባለው ነው፡፡ ማኪያቬሊ ይሙት፣ እውነቱ በአፍ የምትሉት ሳይሆን በተግባር የምትሉት ነው፡፡
ያ ደግሞ በሕዝብ ላይ ምላስ በማውጣት የሚመስል ፀያፍ ተግባር ነው፡፡ እነ አቡበከር አህመድ፣ እነ በቀለ ገርባ፣ ዮናታን ተስፋዬ የመሳሰሉት መብት ጠያቂዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞችና ሌሎችም የሕሊና እስረኞች (የሕሊና እስረኞች ባደረጉት ሳይሆን ባሰቡት ምክንያት የታሰሩና ከታሰሩ በኋላም ዶክሜንተሪ የሚሰራባቸውና ሃሳባቸው ከሕዝብ ውስጥ እንዲወጣ በስብሰባ …ወዘተ ፕሮፖጋንዳ የሚሰራባቸው ናቸው) ተፈትተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እስካልተቀላቀሉ ድረስ ሁሉ ኢሕአዴግ በእኛ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ምላሱን እንዳወጣ ይሆናል፡፡ በጅምላ እናንተ ሽብርተኞች እያለን እንደፈረጀንና እንደሰደበን መቀጠሉ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዳለ ፈርጆ ሽብርተኛ የሚል ጤነኛ የኢትዮጵያ የሚባል መንግስት ሊኖር አይችልም፡፡ ኢሕአዴግ ግን እያደረገ ያለው ይህንን ነው፡፡ ተግባሩ የሚናገረው እንደዚህ ነው፡፡ ተግባራዊ ንግግሩን በተግባር ለመለወጥ ዛሬውኑ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ መብታቸውን ስለጠየቁና የሕዝብ ወኪል ስለሆኑ ያሠራቸውን የሕዝብ ወኪሎች፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች ወይም ሁሉንም የሕሊና እስረኞ ከእሥር መፍታት ይኖርበታል፡፡ ለገደላቸው ካሳ መክፈል፣ ገዳኞችን ለፍርድ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ወደደም ጠላም ይህ ሀገር የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ነው፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በሀገር ውስጥ ያለም የሌለም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሀገሩ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢህአዴግ የሚጎረብጠው የፖለቲካ ወይም የሌላም እምነትና ሃሳብ ያላቸው ሁሉ ይህቺ ሀገር ሀገራቸው ናት፡፡
ይህ ሀገር የእነአቡበከር አህመድም ነው፣ የእነበቀለ ገርባም ነው፣ የእነ ዮናታን ተስፋዬም ነው፣ የእነ አብርሃ ደስታም ነው፣ የእነ ተመስገን ደሣለኝ፣ የነእስክንድር ነጋና የእነ ውብሸት ታዬም ነው፡፡ ሽብርተኛ በማለት ኢህአዴግ የፈረጃቸው የፖለቲካ ድርጅት አባላት የሆኑት ኢትዮጵያውያንም ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ኢትዮጵያዊ በየትኛውም አቋሙ ልዩነት ካልተደረገበትና እኩል ካልተደረገ ኢትዮጵያዊነት የሚለው ፅንሠ-ሃሳብ ራሱ ይጠፋል፣ ይህ ስለመሆኑ የኢሕአዴግ የሕገ-መንግስቱን አንቀፅ 25 እና 93 ድምር ንባብ አይቶ ይረዳዋል፡፡
ለዚህም ነው የፀረ-ሽብር አዋጁ አንቀፅ 2(5) እና 25 ፀረ-ኢትዮጵያዊነት የሚሆኑት ሕገ-መንግስቱን መጣስ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የኢሕአዴግ ፍላጎትና መሻት በማድረግ ሁላችንንም ሀገር አልባ ከሚያደርጉንና ካደረጉን ውስጥ የፀረ-ሽብር አዋጁ በተለይም ከላይ ከተጠቀሱት አንቀፆች በተጨማሪ አንቀፅ አንቀፅ 3፣ 4፣ 5፣ 6፣ 7፣ 8 እና ሌሎም ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያውያንንና የኢትዮጵያን በሙሉ(ሀብትና ዕድል) ለኢሕአዴግ የሰጡ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ(ግዴታ) ይመስለኛል፡፡ ኢሕአዴግ ይህን አዋጅ ጨምሮ አብዛኛዎቹን ሕጎቹን መሻር ወይም ማሻሻል ያለበት ለራሱ ብሎም መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ ያ ሳይሆን አሁን ባሉት በእነዚህ አዋጆች በቡድንና በግል የሚከሰሱበት ሁኔታ ከተፈጠረ አንድም የኢህአዴግ አባልና ኢህአዴግ ጥፋተኛ ሳይሆኑ ስለማይቀሩ ነው ይህን የሕግ ምክር ያለክፍያ የሰጠሁት፡፡ ከረፈደና ባልኩት መሠረት ሳትፈፅሙ ያልኩት ወቅት ከደረሰ እኔም ባልሆን ብዙ ኢትዮጵያዊ “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ” ተብሎ አልነበረምን ብሎ መተረቱ አይቀርም፡፡ የፀረ-ሽብር አዋጁ ሁሉንም ለኢሕአዴግ እንደሰጠው ሁሉ ያንን በኢህአዴግ ላይም የኢህአዴግን ቦታ ለያዙት ሊሰጥ ይችላል፡፡
ሀገሩ የሕዝቡ ከሆነ (ነው ተብሎ የሚታመን ከሆነ) ያ እንዲሆን ዋናው ጋሬጣ የሆነው አገዛዝ (ጭቆናና) በተለይም የፀረ-ሽብርተኝነት የሊዝና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አዋጅ ወዘተ …ዓይነቶቹ ጋሬጦች መነሳት ይኖባቸዋል፡፡
ይህና እነዚህ እያሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገሩ(የመንግስቱና የሌሎም ዕድሎቹ ግንኙነቶቹና ሀብቶቹ) ባለቤት ነው ወይም መሆን ይችላል ማለት ውሸት ነው፡፡ ሀገር የታሠረው በእነዚህ ሕጎች ይህን በሚያወጣው አካል (ፓርላማ)፣ በጦር ሠራዊት፣ ፖሊስ፣ ደህንነት ወይም ሌሎች የፍትሕና የገቢ ተቋማት በሚባሉት መሆኑን የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ እኔ እንደዚህ የሚሉትን አካላት ጤነኞች እንጂ እብዶች አልላቸውም፣ እብደት የታሰሩበት ሰንሰለት ያለመረዳትና ያለማወቅ ነውና፡፡
የሚቀጥለውን የድል ዓመት ሁላችንም ተፈትተን፣ ድነንና ጤነኞ ሆነን ለማክበር ያብቃን አሜን! እስከዚያው ግን ‹‹ጅራፍ ሁሉ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል››እንደሚባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱ እውነተኛ ልጆቹ፣ ወኪሎቹ፣ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እራሳቸውን በሚያሸብር አካል ሽብርተኞች እየተባሉ ሲቀለድባቸው መክረሙ አይቀርም፡፡
አመሠግናለሁ!

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *