ተጠያቂዎቹ…!

ፍርድያውቃል ንጉሴ

firdyawkal@gmail.co

 

እንደ መንደርደሪያ

ባለፈው እትም ፅሁፌ በራዲዮን ጣቢያዎቻችን የሚተላለፉት የ‹ስፖርት› ፕሮግራሞች እግር ኳስ ላይ ብቻ ማተኮራቸውንና ሁሉም የዚህ ስፖርት ብቻ አቀንቃኝ መሆናቸውን ዳስሼ ነበር። በቀጣይነትም መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እንዴት ዝም አሉ?… የየጣቢያዎቹ ባለቤቶችስ ህሊናቸውን በገንዘብ ጋርደው የሀገራችን ስፖርቶች ሞቶ ሲቀበር እያዩ እስከ መቼ ነው ዝምታን የሚመርጡት?… የእነዚህ ፕሮግራሞች ስር የሰደዱና ወደፊትም የሚሰዱ ተግዳራቶችስ ምንድን ናቸው? መፍትሔውስ? የሚሉትን ጉዳዮች እንደምመለስባቸው ቀጠሮ ይዤ ነበር። በቀጠሮአችን መሰረትም ዛሬ እነዚህን አጀንዳዎች እመለከታለሁ።

ዝምታው እስከመቼ!?

በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ የሚዲያ አውታሮች የሚያዘጋጇቸው ፕሮግራሞች ለሀገር የሚበጁ፣ ሁሉኑም ሰው ያማከሉና ተፈላጊውን አስተዋጾ የሚያበረክቱ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ይህ ካልሆነ ደግሞ በየሙያውና በየዘርፉ የተሰማሩ ጉምቱ ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በጉዳዩ ዙሪያ ሂደቱን በአምባገነንነት ማስቆም፣ አሊያም በርካቶችን በማያሳምን መልኩ አጓጉል ተግባራትን ከመፈፀም ይልቅ ጥልቀት ያላቸው የጋራ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ሚዲያዎች እውነተኛውን፣ ትክክለኛውንና ተፈላጊውን ስራ እንዲሰሩ መስመር ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል።

ወደ ርዕሴ ስመለስ፤ በሀገራችን ሚዲያ ላይ ያሉ የስፖርት ፕሮግራሞች ይህ ሰፊ የጋራ መድረክ ከሚያስፈልጋቸውና መስመር ማበጀት ካለባቸው ፕሮግራሞች መሃል አንዱ ነው።… እንዴ!? መንግስት እኮ ‹‹ልማት… ልማት›› ብቻ ከለማት ውጭ ነገሮችን መቃኘትና አሁን ላይ ያሉ ተጨባጭ ሒደቶች ምን እንደሚመስሉ ወረድ ብሎ ማየት አለበት! ምክንያቱም በስፖርቱ ረገድም ሀገሪቷን ማልማት አንዱ የመንግስት ግዴታ ነው።

ከዚህ እውነታ አንፃር በዚህ ጉዳይ ዙሪያ መንግስት በቸልተኝነትና በዝምታ ነገሮችን መመልከቱ የተጠያቂነትና የአመራር ብቃቱን ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከት ነው። ክልሎች ስታዲየሞችን እንዲገነቡ፣ የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች እንዲከናወኑ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል እንዲያደርጉ ማድረግ ብቻውን በቂ አይደለም።

ሁሉም ሚዲያዎች ስለእግር ኳስ ብቻ በሚለፍፉበት በዚህ ዘመን፣ እነዚህ አሁን እተከናወኑ ያሉ፣ ሁሉንም የስፖርት አይነቶች ያማከሉ እንቅስቃሴዎች በዚህ መልኩ መከናወናቸው፤ በብሔራዊ ጣቢያ ከመዘገብ የዘለለ ፋይዳም አይኖራቸውም። ምክንያቱም ህብረተሰቡ ስለእነዚህ የስፖርት እንቅስቃሴዎች በተገቢው መልኩ መረጃን አያገኝም።

ከእግር ኳስ ውጭ ምንም ነገር በሚዲያዎቿ በማይወሩባት በሀገራችን ላይ የሚደረገው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች እውን ተጨባጭ ትርጉምና ፋይዳ ይኖረዋል? በዩንቨርስቲዎች መካከል የሚደረገው የስፖርት ፉክክርስ ቢሆን፤ ለሚዲያ ፍጆታነት ካልበቃና ህብረተሰቡ ዘንድ ካልደረሰ ሀገራዊ ትርጉምና ፋይዳው ምንድን ነው? በዚህ ሁኔታስ ነገ ከነገ ወዲያ በየስፖርቱ ተተኪ መሆን የሚችሉ ሁነኛ ስፖርተኞችን ማፍራት ይቻላል?

ዋነኛው ተጠያቂ…

ርግጥ እኔ መንግስት በየትኛውም የስፖርት ዘርፍ ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ የማልፈልግ ሰው ነኝ። ግና ነገሮች መስመር ሲስቱ ደግሞ ቆም ብሎ ነገሮችን ማስተካከልና መስመር ማስያዝ ያለበት ሀገሪቷን የበላይ ሆኖ የሚያስተዳድረው መንግስት የሚባለው አካልና በስሩ በየዘርፉ ያዋቀራቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንደሆኑ አምናለሁ። የሚገርመው እኛ ኢትዮጵያውያን ተዝቆና ተሰፍሮ የማያልቅ እምቅ የሰው ሃይል ሀብት፣ በበርካታ የስፖርት አይነቶች ውጤታማ መሆን የሚያስችል የአየር ንብረት ያለን ነን። በየስፖርቶቹ ውጤታማ የሆኑ ስፖርተኞችን ማፍራት ደግሞ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ስፖርት ኮሚሽን እቅድና ኣላማዎች መሃል አንዱ ነው።

ግና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ስፖርት ኮሚሽን ከሌሎቹ እቅዶቹ ጋር ይህንንም በወረቀት ላይ አብሮ አካቶታል እንጂ ለእቅዱ ገቢራዊ መሆን የአንድ እርምጃ ታህል እንኳ ተንቀሳቅሶ አያውቅም። ለምሳሌ በሀገሪቷ ውስጥ በየሰፈሩ የነበሩ የመጫወቻ ሜዳዎች ለተለያዩ መሰረተ ልማቶች ሲውሉ፤ ‹‹ሰዎች በሚኖሩበት፣ በሚማሩበት እና በሚሰሩበት ቦታዎች ስፖርትን እንዲያዘወትሩ ማድረግ›› የሚልን አላማ ያነገበው ይህ ተቋም፤ በጉዳዩ ዙሪያ ግንባታዎች ሲከናወኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቶ ነገሮች እንዲመቻቹና ልጆች መጫወቻ እንዲያገኙ ያደረገው ጥረት ምንም ነው። ከሚዲያው አንፃር ያለውም ሒደት ተመሳሳይ ነው።

በየአምስት አመቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የሚመሩ ግለሰቦችን እየቀያየሩ መሾምና ተሻሚዎቹም የሆነ ክስት ላይ በየጣቢያዎቹ እየቀረቡ መግለጫ መስጠታቸው ምን ትርጉምና ፋይዳ አለው? ይሄ ጉዳይ በዋናነት የሚመለከተው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ስፖርት ኮሚሽን ዝምታን ከመረጠ፣ ከወዴትስ ነው መፍትሄ የሚገኘው? በሀገሪቷ ውስጥ ያሉት የስፖርት ፕሮግራሞች በሙሉ ስለ እግር ኳስ ብቻ እያወሩ ያለበት ሒደት፤ አንደኛ ሌሎች ስፖርቶችን ከማስረሳቱና ሌሎች ስፖርቶቻችንን ከማቀጨጩ አንጻር፤ ነገሮች ይስተካከሉ ዘንድ መንግስት በሀገሪቷ ካሉ የስፖርት ባለሙያዎች፣ የስፖርት ጋዜጠኞች እና የራዲዮ ጣቢያ አመራሮች ጋር በመምከር የበኩሉን ሃላፊነት መወጣት ይጠበቅበታል።

ራሱን መገምገም ያለበት ማህበር

ሌላው ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተውና ዛሬ ነገ ሳይል አፋጣኝ መፍትሔ መሻት ያለበት ተቋም የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ነው። በዚህ ማህበር ውስጥ በጣም የካበተ ልምድና የጠለቀ እውቀት ያላቸው የስፖርት ጋዜጠኞች ይገኛሉ። እኔም የዚህ የማህበሩ አባል ነኝ።

ግን ከስሙ ብንጀምር የማህበራችን ስያሜ ‹የስፖርት ጋዜጠኞች› ማህበር ቢሆንም ስንታችን የስፖርት ጋዜጠኞች… ስንቶቻችን ደግሞ የእግር ኳስ ጋዜጠኞች እንደሆንን በውል አይታወቅም። ምክንያቱም እኔንም ጨምሮ በግል ሚዲያው ላይ ሁላችንም የምንዘግበውና የምንሰራው እግር ኳስን ብቻ ነውና። በፕሮግራሞቻችን ዘወትር እግር ኳስን ብቻ የምንሰራ ከሆነ እውን እኛ የስፖርት ጋዜጠኞች ነን ወይስ የእግር ኳስ ጋዜጠኞች?

ይህ ማህበር እስካሁን መልካም የሚባሉ ተግባራትን እየፈጸመ ሲሆን ለሀገራችን ሁለንተናዊ የስፖርት መጎልበት ጉልህ የሆነ አስተዋጾን ማበርከት የሚችል አቅምንም የታጠቀ ነው። ከዚህ አንፃር በተለይ የአውሮፓን እግር ኳስ ሳይሆን የሀገራችንን ስፖርቶች በተጨባጭ አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲራመድ የበኩሉን አስተዋጾ መወጣት ውዴታው ሳይሆን ግዴታው መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ።

እኛ የሀገሪቷ የስፖርት ጋዜጠኞች ከእግር ኳስ ውጪ ያለውን የሀገራችንን የስፖርቱን እንቅስቃሴ ካልቃኘን፣ ካልዘገብንና ስፖርተኞቻችንን በሚያነቃቃ መልኩ መድረኮችን ካላዘጋጀን ማን ሊዘግብልንና ሊያዘጋጅልን ይችላል? ከዚህ አንፃር ማህበሩ ራሱን በሚገባ መገምገም አለበት ብዬ አምናለሁ። ነገሮች ከተበላሹ፤ በየስፖርቱ መጥፎ ውጤቶች ከተመዘገቡ በኋላ ጣትን ሌላው አካል ላይ እየቀሰሩ ሉሎችን ከመኮነንና እዬዬ ከማለት በፊት ወደራስ መመልከትና በእውነት፣ በትክክል ለሀገራችን የሚበጀውን ነገር መስራት ለነገ ማደር የሌለበት የኛ የጋዜጠኞች ሃላፊነት ነው ብዬ አምናለሁ። በዚህ አጠቃላይ ችግራችን ዙሪያ መፍትሔው ምንድን ነው የሚለውን በቀጣይ ዕትም እመለስበታለሁ።

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *