አቶ አምኃ መኮንን /የህግ ባለሙያ/

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ መቀመጫውን እንግሊዝ ሀገር ባደረገው ‹‹ኤሴክስ›› ዩኒቨርሲቲ በዓለም-ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል፡፡ እንደዛሬው በጥብቅና እና በሕግ አማካሪነት ከመሰማራታቸው በፊት በፍትሕ ሚኒስቴር ውስጥ ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪነትም በግል ዩኒቨርሲቲዎች አስተምረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ የተከሰሱ እና እየተከሰሱ ለሚገኙ ሰዎች ጠበቃ በመሆን ግልጋሎት በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ የባለፈው ዕትም ሌላኛው የ‹‹አዲስ ገፅ›› እንግዳ የነበሩት የሕግ ባለሙያው አቶ አምኃ መኮንን መሆናቸው ይታወሳል፡፡ ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ እና ኤልያስ ገብሩ ከጠበቃው ጋር አድርገውት የነበረው ቃለ-ምልልስ የመጨረሻው ክፍል እንዲህ ቀርቧል፡፡ መልካም ንባብ!

ሀሳብን በነጻነት ከመግለፅ መብት ጋር በተያያዘ በሕገ-መንግስቱ የተደነገገ ነገር አለ፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነታስ ምንድን ነው የሚመስለው? ሕግ በራሱ አንድ ስልጣን ላይ ያለ አካል አላማ ማስፈፀሚያ ነው ወይስ ሌላ አተያይ አለው? የሕግ አላማስ በራሱ ምንድን ነው?
‹‹ሕግ ምንድን ነው?›› ለሚለው የተለያዩ ምሁራን በተለያየ ጊዜ የተለያየ ትርጉም ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ ጥንታዊ የነበረ፣ በአንድ ወቅት ተቀባይነት የነበረው ነገር ግን በአሁን ወቅት ጭራሽ ተቀባይነት የሌለው፣ ‹‹ሕግ የገዢው መደብ ጥቅም ማስጠበቂያ›› የሚለው ነበር፡፡ ይሄ በአሁን ወቅት ተቀባይነት የለውም፡፡ የሕግ ዋነኛ ዓላማ ማኅበራዊ ፍትህን ማስፈን ነው፡፡ ሁለተኛ በመንግስትና በህዝብ መካከል፣ በገዢውና በተገዢው መካከል ያለውን ግንኙነት አስቀድሞ መወሰንና በተለይ ገዢው በተፈጥሮ ጉልበት ያለው ስለሚሆን ጉልበቱን ተጠቅሞ ህዝብን እንዳይጨቁን መጠበቂያ ነው የሕግ ትርጉም፡፡
በመሬት ላይ ያለው እውነት፣ ይሄ መብት ከሚሰጠው ጥቅምና ለዜጎች ከሚያጎናፅፈው መብት አንጻር በቂ ጥበቃ እየተደረገለት ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ በቸልተኝነትም እየታየ ነው፡፡
ሀሳቦቻቸውን በነጻነት ለመግለጽ የሞከሩ ዜጎች ሲታሠሩ፣ ሲከሰሱና ሲሳደዱ እያየን እንገኛለን፡፡ በተለይ አሁን ለተለያየ አላማ የሚወጡ ህጎችም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በዚህ መብት አተገባበር ላይ ጫና እያደረጉ ነው፡፡
በተለያዩ መብቶች ላይ ግልፅ ጫና አሳድረዋል፡፡ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች መብቶችም እንዲተዋወቁ ይሠሩ የነበሩ ሀገር በቀል ድርጅቶች ያንን መስራት የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይሄ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ አሁን ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ በመንግስት በጎ ፍቃደኝነት ስር ወድቋል፡፡ ለህዝቡ ከመንግስት ውጪ የሆነ ገለልተኛ፣የሚቆረቆርና ለሕዝቡ መብት መጠበቅ የሚሠራ ነጻ አካል በበቂ ሁኔታ አለ ብዬ አላምንም፡፡ በእርግጥ መንግስት በራሱ ያቋቋማቸው እንደሠብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ እምባ ጠባቂ ተቋማት አሉ፡፡ ተቋማቱ በሕግ የተሰጣቸው ሥልጣን ሰፊ ነው፡፡ ግን የሚጠበቅባቸውን ሥራ እየሠሩ ስለመሆኑ በግልፅ የሚታይ ነገር የለም፡፡ በፊት ከነበሩት ጋር ሲነጻጸሩ ነጻ የሆኑ ተቋማት አሁን የሉም፡፡
የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን መንግስት ለትልቅ ዓላማ እንዳወጣው ይገልጻል፡፡ እኔም በግሌ እንደዚህ አይነት አዋጅ መውጣቱ ችግር ነው ብዬ አላምንም፡፡ ‹‹የነበሩ ችግሮችን በነበሩ የወንጀል ሕጎች ሊዳኙ ይገባ ነበር››የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እኔ ግን እዚያ ድረስ መሄድ ሳያስፈልግ አዋጁን ብናየው ጥርት ያለ ነገር ይጎድለዋል፡፡ ‹‹አንድ ድርጊት ሽብር ነው የሚያስብለው የቱጋ ነው? ወሰኑ የት ድረስ ነው?›› የሚለውን በግልጽ የሚያስቀምጥ አይደለም፡፡ ይሄን ወንጀል ለመመርመር፣ ለመክሰስና ለመዳኘት ተብለው የተቀመጡ ሥነ-ስርዓቶችና የማስረጃ መርሆዎችም ብዙዎቹ ከሰብዓዊ መብት ጋር የሚጋጩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣ በማናቸውም ሁኔታ በሽብር ወንጀል የተጠረጠረ ሰው በዋስትና የመለቀቅ መብት የለውም፡፡
በዚህ አዋጅ የተጠረጠረበትን ድርጊት እንዳላደረገ የማስረዳት ጫናው /burden of proof) የወደቀውምተጠርጣሪው ላይ ነው፡፡
የማስረዳት ጫናውን ከከሳሽ ይልቅ ወደ ተከሳሽ የማዞር፣ የስሚ ስሚ ማስረጃ የመቀበል፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ተቋም የሚሰጠው መረጃ ወሳኝ ማስረጃ ሆኖ እንዲቆጠር መፍቀዱ ሁሉ ሀሳብን የመግለፅ መብት ላይ ብቻ ሳይሆን በብዙ የዜጎች መብት ላይ ትልቅ ጫና የሚፈጥር ነው፡፡ መሬት ላይ ያለው ሀቅ፣ እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎችም ሆነ እየወጡና እየተተገበሩ ካሉ ህጎች አንጻር ጥሩ ስሜት የሚፈጥሩ ናቸው ብዬ አልወስዳቸውም፡፡
እንዳሉት፣የሕግ አላማው የአምባገነኖች ወይም የጉልበተኞችን ዓላማ ማስፈጸም ሳይሆን ማኅበራዊ ፍትህ ማስፈን ነው፡፡ መንግስት ከዚያ ማዕቀፍ ወጥቶ፣ ዕለት በዕለት ተገዥዎችን ለማፈንና የእነሱን መብት ለመገደብ ሲሰራ፣ በተቃራኒ ያለው ህዝብ ወደመገፋት ሄዶ ጭቆናን ለመገርሰስ ሲል ገዥው ላይ ቢነሳ (በትጥቅ ትግልም ሆነ በሰላማዊ ወይም በሌላ)ከዚህ ረገድሕግ ምን ይላል?
በሀገራችንም በሌሎች ዓለማት ታይቷል፡፡ አምባገነን መንግስታት ሥልጣናቸውን ለማስጠበቅ ጨቋኝ ህጎችን አውጥተዋል፣ ያወጣሉም፡፡ እንዲህ ሲሆን ‹‹ዜጎች ጨቋኝ የሆነው ሕግ ሕግ ስለተባለ ብቻ ተገዝተው መኖር ወይስ ይሄን መቃወም አለባቸው?›› የሚልትልቅ የፍልስፍና ጥያቄ ይነሳል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት፣ መንግስት ለህዝቡ፣ ሕዝብም ለመንግስት ያስቀመጠለት ማዕቀፍአለ፡፡ መንግስት ከዚህ አግባብ ውጪ ውጪ ሲሄድህዝቡ መንግስትን የመቃወም፣ ተቃውሞውንም በተለያየ መንገድ የመግለጽና በሰላማዊ ሕዝባዊ አመፅ (በቅርብ ዐመታት በአረብ ዓለም እንደተከሰተው) ያንን መንግስት የማስወገድ መብትም ተፈጥሯዊ ባህሪ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሆኖም በሀይል የሌላውን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ወደጎን በማድረግ ጥቅምና መብቱን በሚጎዳ መልኩ መንካት ሊያጠያይቅ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ጉዳቱ በማይመለከተው ሕዝብ ላይ ስለሚያርፍ ነው፡፡ ‹‹ሰላማዊ አመፅ›› ወይም ‹‹ህዝባዊ እምቢተኝነት›› ተቀባይነት ያለውና የሌለው ቢባልም የሚቀር አይደለም፡፡ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ የሚሆን ነው፡፡ በግልጽም እያየነው ያለ ነገር ነው፡፡ በሕዝባዊ አመፅ ውስጥም በሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ነገሮች ከተፈጠሩ ጭቆናን ለማስወገድ ብቻ ተብሎ የሚተው አይሆንም፡፡ በዚያ ሂደት ውስጥ ተጠያቂነት አይቀርም፡፡ ጎረቤት ጎረቤቱ ላይ የተለያየ ጉዳት ቢያደርስ ‹‹ጭቆናን ለማስወገድ ነው›› ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፡፡
በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ መንግስትና ህዝብ በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ የተቀመጠማኅበራዊ ውል አላቸው፡፡ ያንን ውል መንግስት ጥሶ ከሄደ፣ ሌላው ወገን ሕግን ጥሶ ላለመሄድ ምን የሚያስገድደው ነገር አለ?
አንዳንዴ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ባለመስማማት የሚፈጠር ችግር ይኖራል፡፡ ሌላው ገዢው አካል ከሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ውጪ የራሱን ህልውና ለማስጠበቅ ብቻ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ኅብረተሰቡ እምቢ የሚልበት ሁኔታነውወሳኙ ዓላማ፡፡ ይሄንን ለመገደብ፣ ለመከላከል ብቻ እስከሆነ ድረስ በእኔ በኩል ተቀባይነት አለው፡፡ ሌላ ጥቅምን ብቻ ለማግኘት፣ መልሶ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመፍጠር፣ ጨቋኝ አምባገነን ስርዓትን አስወግዶ ሌላ ሀይል በቦታው እንዲቀመጥ ለማመቻቸት ከሆነ ተቀባይነት አለው ብዬ አላስብም፡፡ ኢ-ሕገመንግስታዊን ወደ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ለመቀየር ከሆነ ዓላማው ይሄ ትክክል ነው፡፡በዚህ ጊዜ ጨቋኝ የሚባሉ ሕጎችን መተላለፍ የሚያስወቅስ አይደለም፡፡ በዚህ ሂደትም ውስጥ የግለሰቦችና የዜጎች መብቶች መከበር መቻል አለበት፡፡ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓትን ለመመለስም ቢሆን ንፁሃን ዜጎች ዋጋ መከፈል አይጠበቅባቸውም፡፡
ጦርነት ህግጋት አለው፡፡ በአብዮት ወቅትስ ሕግ አለ?
የጦርነት ሕግ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረና በዓለም ላይ የዳበረ ሕግ ነው፡፡ ሕጉ ዓለም ዓቀፍ ጦርነቶችንና የመሳሪያ አጠቃቀማችንን የሚመለከት ነው፡፡ አብዮትን ለመምራት፣ ለመግዛት ተብሎ የወጣ ዓለም ዓቀፋዊ ሕግ መኖሩን አላውቅም፡፡ አብዮቶች ብዙ ሲተነተኑ ነው የምናውቀው፡፡ ‹‹የሕግ ድጋፍ ያላቸውና የሌላቸው አብዮቶች የትኞቹ ናቸው?››ተብለው ይተነተናሉ እንጂ የተቀመጠ ሕግ የለም፡፡ አብዮት በሂሳብ ቀመር የሚነሳ አይደለም፡፡ የብዙ ነገሮች ጥርቅም ህዝብን በአንድ ባልታሰበ ጊዜ፣ በአንድ ነጥብ ላይ እንዲግባቡ፣ ሳይነጋገሩናሳይሰባሰቡ ወደ እርምጃ የሚገፋ ሁኔታ እንጂ አስቀድሞ በሕግ የሚደነገግ ነው ብዬ አላስብም፡፡
ኢህአዴግ በተደጋጋሚሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ማረጋገጡን ከደርግ ስርዓት ጋር አነፃጽሮ ይገልፃል፡፡ ግን ንጽጽሩን ከደርግ ጋር ወይስ ከራሱ ጋር ነው ማድረግ የሚገባው? በሥልጣን ላይ 25 ዓመት ስለሞላው ለማለት ነው፡፡
ኢህአዴግ ስልጣን በያዘ በ10 ዓመታት ውስጥ የራሱን እርምጃዎች ከደርግ ሥርዓት ጋር ማወዳደሩ ጎልቶ ይታይ ነበር፡፡ ግን ይሄ ትክክል ነው ብዬ አላስብም፡፡ በሁሉም መብቶች ዙሪያ ተቀባይነት ያላቸው ዓለማቀፍ መመዘኛዎች አሉ፡፡ መንግስትም ራሱን ማየት ያለበት ከእነዚህ መመዘኛዎች ጋር አወዳድሮ፣ ምን ያህል አስፈላጊ ስራ መስራቱን ነው፡፡ የደርግ ስርዓት ሙሉ በሙሉ ወታደራዊ አምባገነን ነው፡፡ብዙ መብቶችን በግልጽ በአዋጅ የገደበ ነው፡፡ በስልጣን ላይ ለመቆየት ብዙ ግፍ ፈጽሟል፡፡ አንጻራዊነትን ለማየት ከሥርዓት ጋር ይወዳደር ቢባል ራሱ የደርግ ስርዓት ተገቢነት ያለው መለኪያ አይደለም፤ ለኢህአዴግም አይጠቅመውም፡፡ በደርግ ሥርዓት መብቶች በጣም በጣም የወረደ ሁኔታ ላይ የነበሩበት ጊዜ ስለነበረ ከዚያ ጋር ለማወዳደር ለመንግስትም ይጠቅመዋል ብዬ አላምንም፡፡ የሚጠበቅበትንም ሁኔታ እንዳይረዳ ያደርገዋል፡፡ንጽጽሩ ከደርግ ጋር ሳይሆን አሁን ዓለም ከደረሰችበት የሥልጣኔ ዘመን፣ ኅብረተሰባችን ከደረሰበት የንቃተ ህሊና ደረጃ አንጻር፣ ካለንበት የመረጃና ኮሙዩኑኬሽን ዘመን ንቃት ጋርና ከሚጠይቀው አንጻር ነው እርምጃውን ማየት ያለበት፡፡ ሁለተኛ እንደዚህ አይነት ንጽጽር ዝቅ የሚያደርግ ነው፡፡ መብቶቹን ራሳቸውን ያዋርዳቸዋል፡፡ ለዜጎችም ትክክለኛውን ክብር የሚያሳይ አይደለም፡፡ ‹‹ከደርግ ጊዜ የተሻለ መብት ስለሰጠሁህ ይበቃሃል›› ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ የሠው ልጅ በየትኛውም ቦታ ክቡር ነው፡፡ ይሄ ሁሌም መጠበቅ አለበት፡፡ ‹‹በደርግ ጊዜ ስምህን መናገርና ቀና ማለት አትችልም፡፡ ዛሬ ግን ቀና ብለህ መሄድ ችለሃል፤ ይሄ ይበቃሃል፡፡ አሁንም የተሟላ ስብዕና ባይኖርህም የተሰጠህን ተጠቀም›› ማለት ትክክለኛ ንጽጽር አይደለም፡፡
ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ባይመጣ ኖሮ፣ ደርግ ትላንት በነበረበት መንገድ መቀጠል ይችል ነበር?
በጣም እጠራጠራለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ደሴት አይደለችም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች የተለየ አይደለም፡፡ የራሱ የዕድገት ደረጃ አለው፡፡ ታሪክ፣ ባህል፣ ዕሴት … አሉት፡፡ እነኚህ በሚፈቅዱለት መልኩ ፍላጎቶቹና ንቃተ ህሊናው የሚያድግ ነው፡፡ ኢህአዴግ ባይመጣ ኖሮ ከዚህ የተሻለ ሁኔታ ላይ ልንኖር የማንችልበት ሁኔታ የለም፡፡ አሁን ያለንበት ደረጃ ኅብረተሰባችን ሊደርስበት የሚችልበት ደረጃ ነው ማለት በፍጹም ተገቢ አይደለም፡፡ እንዲያውም እኔ በተቃራኒው አስባለሁ፡፡ መብቶች በአግባቡ ቢከበሩ (በተለይ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ)፣መንግስትእንክብካቤ ቢያደርግለት፣ ሠዎች ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ ሃሳባቸውን ቢገልጹይዳብራል፡፡ ሠዎች ያለ ገደብ በሁሉም የሀገሪቷ ክልሎች ተንቀሳቅሰው መስራት ቢችሉ ብዙ የሥራ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፤ የተሻለ ሁኔታ ላይ እንገኝም ነበር፡፡
በደርግ ዘመን ህዝብ ተጎድቷል፡፡ ዛሬ ላይ ግን ያለንበት ሁኔታ የሚያስፈነጥዝ፣ ያለውን መንግስት በተለየ ሁኔታ የሚያሸልም፣ መንግስትን ክፉ ነገር ላለመናገር የማያስደፍርና ውለታ የሚያስይዝ ነገር አይደለም፡፡ መነሻችን የደርግ ስርዓት መሆን የለበትም፣ አይደለምም፡፡ መነሻችን የሠው ልጅ ክቡርነት መሆን አለበት፡፡ መነሳት ያለበት ዓለም ዐቀፍ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መመዘኛ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ያለው የማኅበረሰባችን ፍላጎት እንጂ የጭለማው ዘመን መሆን የለበትም፡፡ ማድረግ እየተቻለና እድሉ እያለ ማድረግ ያልቻለ አካል እንዲያውም ሊወቀስ ይገባል፡፡
በደርግ ጊዜ ብዙ የጦርነት ውጥረት ውስጥ ነበርን፡፡ ኢህአዴግ ከኤርትራ ጋር ከተፈጠረ ግጭትና ከህዝቡ ቅሬታ ውጪ በደርግ ጊዜ እንደነበረው በጦርነት ችግር ውስጥ አልነበረም፡፡ በተመቻቸ ሁኔታ ላይ ኖሮ ዓለም የደረሰበት ደረጃ አለመድረስ ይበልጥ የሚያስወቅስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች ለምን ይታሠራሉ? ይከሰሳሉ? ይሰደዳሉ? ይዋከባሉ?
በመንግስት በኩል ትችትን ለመቋቋም አለመቻል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
አለመቋቋሙ ከምን የመጣ ነው?
አለመቋቋሙ የሚመነጨው ህዝብን ካለማመን የተነሳ መሆኑን አስባለሁ፡፡ ‹‹ይሄ ትችት ሄዶ ሄዶ ህዝብን ከስሩ ያንሸራትተዋል፤ ሥልጣኔን ያሳጣኛል›› ከሚል ፍራቻ ይመስለኛል፡፡ በሕዝብና በመንግስት መካከል ያለ አለመተማመን ይመስለኛል፡፡
ህዝብን ያላመነ መንግስት ራሱንስ ያምናል? እምነት ከራስ ይመነጫልና…
ሌላውን ያላመነ ራሱን ማመን አይችልም፡፡
‹‹ለፕሬስ ልዩ ጥበቃ ይደረግለታል›› ተብሎ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ ለፕሬስ የተባለው ጥበቃ ተደርጓል?
ጥበቃ፣‹‹የሚያሰራናፈቃጅ ህግ ያወጣል›› ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ኢህአዴግ ‹‹የሚያኩራራ ሕገ-መንግስት አውጥቷል፣ የሚያበረታታና ያለስጋት የሚያሠራ ዘመናዊ ህጎችን አውጥቷል›› ለማለት ያስቸግራል፡፡ ካለው የሕግ ማዕቀፍ፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ፅሑፎች በሚያስከትሉት ውጤት፣ ይዘት ሊያስጠይቁናሊገድቡ አይገባም›› እያለ እንደምናየው የተለያዩ ጋዜጠኞች፣ ጦማርያንና ግለሰቦች ‹‹በኢንተርኔት፣ በኢ-ሜይል መልዕክት ተላልካችኋል›› እየተባለ ፅሑፋቸውናይዘቱ እየታየ ሲጠየቁ እያየን ነው፡፡ የሚያወራ፣ የሚያበረታታ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ካለመቻሉ የተነሳ በሀገር ውስጥ የሚፈጸም እስርና ከሀገር ውጪ የሚደረግ የጸሐፊያን ስደት መንግስትን ብዙም የሚያሳስበው አይደለምና ፕሬስ ‹‹ተገቢው ጥበቃ ተደርጎለታል››ለማለት እቸገራለሁ፡፡
የዞን 9 ጦማርያንና ጋዜጠኞች ጠበቃ ነዎት? ጉዳያቸውን ይዘው ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ይቀርባሉ፡፡ ከሕግ ባለሙያነትዎ ባሻገር እንደአንድ ኢትዮጰያዊ ዜጋ እነሱን ሲመለከቱ ምን ይሰማዎታል?
ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ እኔ የወከልኳቸው ጋዜጠኞችና ጦማርያን በአማካኝ ከ25-30 ዓመትዕድሜ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ አንብበው ካልሆነ በስተቀር የደርግን ሥርዓት ህይወት አያውቁም፡፡ የኃይለስላሴንም አያውቁም፡፡ ግን በዚህ ሀገር እንዲኖርና እንዲመጣ ከሚፈልጉት ሰላምና ዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት መከበር አንጻር በቅንነት በመነሳት ሀሳባቸውን ይገልጻሉ፡፡ይሄንን ሲያደርጉ እንዲሁ በተፈጥሮ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ለማንበብና ለማወቅ የሚፈቅዱና የሚጥሩ ናቸው፤ ይሄም አቅም ፈጥሮላቸዋል፡፡ በጎነትን ለማበረታታትና መጥፎ የሚሉትን ሳይፈሩ መጥፎ መሆኑን የሚገልጹ ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች ለዚህ ሀገር ትልቅ ዕሴቶች ናቸው፡፡ ብሩህ ተስፋ የሚያጭሩ ናቸው፡፡ ሁኔታዎች ተመቻችተው፣ እነዚህን ወጣቶች ማስደንገጥ ሳይሆን እንዴት ይሄንን ሀገር ሊጠቅሙ እንደሚችሉ ቢታሰብ ሀገራችን ትልቅ ዕድል ይገጥማታል ብዬ አስባለሁ፡፡ በበኩሌ በመታሰራቸውና ፍርድ ቤት በመመላለሳቸው በጣም አዝናለሁ፡፡ እኔ ታላቃቸው ነኝ፡፡ ካላቸው ራዕይ፣ መረጃና ቅንነት አንጻር በመንፈስ የምቀናባቸው ናቸው፡፡ ዕድል ተፈጥሮ ለዚህ ሀገር አስተዋጽኦ ማድረግ የሚቻልበት ቦታ ላይ ሆነው ባያቸው በጣም ደስ ይለኛል፡፡
በጸረ-ሽብርተኝነት አዋጅ መሠረት ጋዜጠኞችና ጦማርያን ተከሰው ይታሰራሉ፡፡ መንግስት ለዚህም ‹‹ከጋዜጠኝነት ከመጦመር ስራቸው ጋር የሚያያዝ አይደለም›› ሲል ምክንያቱን ያቀርባል፡፡ በምርመራና በክስ ወቅት የጋዜጠኝነት ስራቸው ማስረጃ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ይህንን ተቃርኖ እንዴት ያዩታል? ‹‹አንድም ጋዜጠኛ በጻፈው ፅሑፍ አልተከሰሰም፣ አልታሰረም›› ይባላል፡፡ የተመስገን ደሳለኝና የእኛ(ኤልያስ ገብሩና አምሳሉ ገ/ኪዳን) ጉዳይ ግን ከጽሑፍ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ትክክል ነው ኃላፊነቱ መንግስት ላይ ነው፡፡ ይሄ ብዙ ጊዜ ተብሏል፡፡ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙ ተብሏል፡፡ የአሁኑም ሆነ በተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች ሲነገር ይደመጣል፡፡ ‹‹አንድም ጋዜጠኛ በጻፈው ወይም በተናገረው ነገር አልታሠረም፣ አልተፈረደበትም፡፡ ጋዜጠኛ ቢሆኑም ከሽብር ጋር በተያያዘ ነው ተጠርጥረው የታሰሩት›› የሚል ነው የመንግስት ሀሳብ፡፡
እኔ የተከታተልኳቸው ጥቂት ጉዳዮችን ብናይ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የተከሰሰውና ጥፋተኛ የተባለው ዋና አዘጋጅ ሆኖ ይሰራበት በነበረው‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ ላይ በተጻፉ አምስት ፅሑፎች ነው፡፡ በሽብር ወይም በሌላ ደረቅ ወንጀል አልተከሰሰም፡፡ አሁን በቅርቡ የዞን 9 ጦማርያንና ጋዜጠኞች ከፊሎቹ በመንግስት ውሳኔ፣ ከፊሎቹ በፍርድ ቤት ውሳኔ ክሳቸው የተቋረጠላቸውና ነጻ የወጡት የተጠረጠሩት በፃፉት ፅሑፍ ነበር፡፡ በዚህ በኩል ተቃውሞ ሲቀርብ ጉዳዩ ወደሽብር የተሄደበት ነው፡፡ ክሱም ሲቀርብ የሽብር አዋጅ ተጠቅሶ ነው፡፡ በመጨረሻ ግን ፍርድ ቤቱ ‹‹የፈጸሙት ድርጊት ሀሳባቸውን በነጻነት ከመግለጽ ያለፈ አይደለም፤ መከሰስም አልነበረባቸውም›› የሚል ትርጉም በሚያሰጥ ሁኔታ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻያሰናበተበት ሁኔታ ታይቷል፡፡
መሬት ላይ ያለው እውነታ፣ ጋዜጠኞች በጻፉት ፅሑፍ እየተከሰሱና ጥፋተኛ የተባሉበትን ሁኔታ አይተናል፡፡ ከዚህ አኳያ ‹‹አንድንም ጋዜጠኛ በጻፈው ፅሑፍ አልከሰስንም›› የሚለው ኃላፊነት መንግስት ላይ ነው፡፡ መልስ መስጠት ያለበት እሱ ነው፡፡
ከወራቶች በፊት የኮሙኑኬሽን ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በጀርመን ድምፅ ሬድዮ ስለጋዜጠኞቹ እና ጦማርያኑ አፈታት ሲናገሩ ‹‹በጫና ሳይሆን በፍርድ ቤት ገለልተኝነት ነው›› ብለው ነበር፡፡ ሕግን የተማሩና ያስተማሩ ሰው ለመንግስት ውግንና ውስጥ ሲገቡ በግልዎ ምን ይሰማዎታል?
ለመንግስት መወገን በራሱ ብዙ ችግር የለውም፡፡ በተቀመጠ ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ውስጥ መሄድና ትክክለኛ የህዝብ ውክልና ያለው መንግስት እስከሆነ ድረስ ሁሉም ኅብረተሰብ መንግስትን ቢደግፍ ጤነኛ አስተሳሰብ ይሆናል፡፡ ግን በየትኛውም ሁኔታ የተማረ መሆንም አይጠይቅም፡፡ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው፣ አንድ መንግስት በጥፋት ጎዳና ላይ ሲገኝ ያንን ደግፎ መሄድ ሳይሆን በግልፅ ማውገዝ ይጠበቅበታል፡፡
የአንድ ፍርድ ቤት ገለልተኝነት የሚለካው መጨረሻ በሚሰጠው ውሳኔ ብቻ አይደለም፡፡ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ብዙ ሂደቶች አሉ፡፡ በእኛ ጉዳይ በጋዜጠኞች እና ጦማርያን የክርክር ሂደት ‹‹የችሎት ዳኛ ይነሳ›› እስከመባል የደረሰበት ደረጃ አለ፡፡ ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መጨረሻ የተሰጠው ውጤት ‹‹የፍርድ ቤቱን ገለልተኝነት ያሳያል››ቢባል በሀገሪቷ ውስጥ ያለው የፍርድ ቤት ገለልተኝነት በአንድ ፍርድ ቤት በሚሰጥ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በፍትህ ስርዓቱ ነው መታየት ያለበት፡፡
ፍርድ ቤት ነጻ አላቸው፣ ይግባኝ ተጠየቀባቸው፡፡ ይግባኝ ሰጪው ምን ውሳኔ ይሰጣል? ገና አይታወቅም፡፡ በአጠቃላይ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ያለው ሂደት ነው ‹‹ገለልተኛ ነው /አይደለም?›› የሚለው፡፡ መሀል ላይ በጎ የሚመስል ነገር ተሰርቶ ቀጥሎ ያለው ውሃ የሚደፋ አይነት ነገር የሚሰራ ከሆነ፣ በአጠቃላይ ያለው የፍትህ ሥርዓት እዚህ ደረጃ ነው ለማለት የሚቻል አይደለም፡፡ ለምሳሌ፣ በእነ ሀብታሙ አያሌው ጉዳይ ሚኒስትሩ አሉ እንደተባለው፣ ፍ/ቤቱ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ ወስኖላቸዋል፡፡ እዚህ ጋር ፍርድቤቱ ወስኖላቸዋል፡፡ እዚህ ጋር እናቁም ካልን ፍርድ ቤት ገለልተኝነቱን አሳይቷል፣ የሚያስመሰግን ስራ ሰርቷል ማለት እንችላለን፡፡ ግን በነጋታው ይግባኝ ቀርቦ በጣም ባልተለመደ ፍጥነት ይሄ ውሳኔ የታገደበትን ሁኔታ ታያለህ፡፡ እዚህ ጋር ሌላ ጥያቄ ታነሳለህ፣ አጠቃላይ የፍትህ ስርዓቱ ገለልተኛነት መታየትም መመዘንም ያለበት እዚህና እዚያች በምትፈጠር መልካም እርምጃ ሳይሆን በአጠቃላይ በፍትህ ስርዓቱ አካሄድ መሠረት መሆኑን አምናለሁ፡፡
በመጨረሻ የሚሉት …
የሰጠሁት የራሴን ዕይታ ነው፡፡ ዕይታዬ እንከን የማይወጣለት ሙሉ በሙሉ ትክክል ነው የሚባል ባይሆንም ለራሴ ትክክል ነው፡፡ ጥያቄ የማይነሳበት ግን አይደለም፡፡ በራሴ ዕይታና ድምዳሜ በመንግስት በኩል መልካም እርምጃዎች፣ እስካሁን ከመጣንበት የተለዩ አካሄዶች በተለይ ሀሳብን በነጻነት ከመግለፅ አኳያ ብዙ አዎንታዊ እርምጃዎች ቢወሰዱ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡ ይሄም እንዲሆንም እመኛለሁ፡፡ የፍትህ ሥርዓቱ አካባቢ ይበልጥ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ተደራሽ እንዲሆን ስራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ በአስተዳደር በኩል ብዙ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ግን መታገስ ያስፈልጋል፡፡ ያሉ ችግሮችን በገለልተኝነት አቅም ባለው ስርዓት ለነገ የማይባል፣ ለሕዝቡም የመጨረሻ መጠጊያ የፍትህ ስርዓቱ በመሆኑ በዚህ ረገድ በመንግስት በኩል በቀና ሊታይ የሚችል እርምጃ ቢወስድ ምኞቴ ነው፡፡
እናመሰግናለን፡፡
እኔም አመሰግናለሁ፡፡

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *