ደርበው ችሮታው

ከሰሞኑ ወደ አዲስ አበባው ‹‹አትክልት ተራ›› ጎራ ብዬ ነበር። ጎራ አባባሌ፣ እንደ ሌሎች ጊዜያት ያልዋለ ያላደረ አትክልት አግኝቼ፣ አልወጣልኽ ያለኝን አምሮቴን የሚያወጣ ነገር ልሸምት በሚል ነበር። እና የምፈልጋቸውን በጠቅላላ ገዛዝቼ፣ አንድ ያልገዛሁት ነገር ኖሮ፣ ነጋዴውን እንዲያቃብለኝ ጠየቅኩት። ነጋዴው የሰጠኝ መልስ፣ ‹‹አልበሰለም!›› የሚል ነበር። መግዛት የፈለኩት አቮካዶ ነው። እናም ሌላ ቦታ ገዛዋለሁ ብዬ ከተራው ወጣሁ። ነገር ግን ከትልቁ የአትክልት ተራ እስከ ትንሹ ጭማቂ ቤት ድረስ ባስስ-ባስስ የሁሉም መልስ ተመሳሳይ ሆነብኝ – ‹‹አልበሰለም!›› መጨረሻ ላይ አንዱን ሻጭ፣ እንደ መበሳጨት እያደረገኝ፣ ‹‹ባይበስል ምን ችግር አለው!? ዝም ብለኽ ሽጥልኝ!›› አልኩት። ‹‹ይቅርታ፣›› አለኝ ነጋዴው ኮስተር ብሎ። ‹‹ይቅርታ! ካልበሰለ አይሸጥም!›› እኔም የነጋዴው አመላለስ እያስገረመኝ፣ እንዲሁ የእርሱን ‹‹ካልበሰለ አይሸጥም!›› ምላሽ ሸምቼ ወደ ቤቴ ተመለስኩ።

ወደ ቤቴ እየተጓዝኩ ‹‹ካልበሰለ አይሸጥም!›› የሚለውን ደጋግሜ አሰብኩት። እውነቱን ነው፤ ያልበሰለ ጤና አይሰጥም፤ ይጎረብጣል፤ ያማል፤ ጤና ያውካል፤ … እያልኩ ደጉን ትርጓሜ ወሰድኩት። ነገር ግን ‹‹አልበሰለም!›› የሚለው ቃል ረፍት ሊሰጠኝ አልቻለም። ‹‹አልበሰለም››ን ከሐሳብ፣ መመሪያ፣ ደንብ፣ ዐዋጅ … ጋር አያያዝኩና ትንሽ ቆዘምኩ። ስንት የኤፍ.ኤም.ሬዲዮ ፕሮግራም ያልበሰለ ሐሳብ አቅርቦ ራሳችንን አሳመመን? ስንቱን ሸውራራ ሐሳብ ሊያስይዘን ሞከረ? ስንቱ የቀበሌ ካድሬ ያልበሰለ ሐሳብ አምጥቶ፣ ‹አሠራር ነው! እንደ ወረዳ፣ እንደ ቀበሌ መያዝ ያለበት! ሁላችንንም ይመለከተናል፤ እንደ አሠራር… › እያለ ስንቶቻችንን አናወዘን? ስንቱ የወረዳ ካቢኔ፣ የክ/ከተማ፣ የከተማ፣ የክልልና የፌዴራል ም/ቤት ያልበሰለ መመሪያ፣ ደንብ፣ ዐዋጅ አጽድቆ – ምን ያህሉን ኢትዮጵያዊ በሽተኛ አደረገ? ስንቱን ኢትዮጵያዊ ዘብጥያ አስወረወረ? የስንቱን ኢትዮጵያዊ የሰብዓዊ መብቶች አስነፈገ? ስንቱን ኢትዮጵያዊ በአገሩ ባይተዋር አደረገ? ስንቱን ኢትዮጵያዊ በጦርነት ማገደ? የሳት ራት አደረገ?

እንዲያ ያስቆዘመኝ እኔም ያልበሰለ ሐሳብ አራማጅ ሆኜ አይደለም። እልቁንስ ሀገሬ እንደ በርበሬ ጆንያ ባልበሰለ ሐሳብ እየተጠቀጠቀች መሆኗ ታስቦኝ – አሳስቦኝ እንጂ! ለምን? ካላችሁኝ፣ የምታውቋቸውን  መመሪያዎች፣ ደንብቦችና ዐዋጆች አስቧቸው፤ ለምሳሌ በ2006 ዓ.ም የወጣውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋት ዐዋጅ ውሰዱት (የዐዋጅ ቁጥሩን ማስታወስ ባለመቻሌ ይቅርታ)። ይህ ዐዋጅ በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ ሰው የፈለገውን ትምህርት መርጦ መማር ሲችል፣ በግብርና ትምህርት መስክ ላይ ያሉ የብቃት ምዘና ፈተና ወስደው መቀየር ሲችሉ፣ በትምህርት ዘርፍ ላይ ያሉ ግን ከሙያቸው ውጭ ቀይረው መማር የማይችሉ መሆኑን ይደነግጋል፤ የግልም የመንግሥትም የከ/ት ተቋማት ተፈጻሚ እንዲያደርጉትም ያውጃ። ይህን ያላደረገ የትኛውም ተቋም ሕጋዊ እርምጃ ይወሰድበታልም ይላል።

ወዳጆቼ! ከዚህ በላይ ምን ያልበሰለ ዐዋጅ አለ!? የፈለጉትን መማር የእያዳንዱ ዜጋ ምርጫ ነው።  ይሄ ያልበሰለ ዐዋጅ ባንድ ጀምበር የትምህርት ምርጫን  ወደ መከልከልና ወደ መንግሥት ስጦታነት ቀይሮት ነው ያረፈው! ይህ ያልበሰለ ዐዋጅ ማንን አሳመመ? ማንን ጎረበጠ? የማንን ጤና አሳጣ? … ከተባለ – መልሱ ግልጽ ነው። አሁን አንድ መምህር በዚህ ያልበሰለ  ዐዋጅ መሠረት ግዞተኛ ነው ማለት ነው። ተማሪውም የፈለገውን ሳይሆን፣ ‹‹ይህን ተማር!›› የተባለውን ብቻ ይማራል። ልእልናውን ማሳደግ ላይ ሳይሆን፣ ዐዋጁን ማስፈጸም ላይ ተሰማርቷል በሉት።

የሆነው ሆነና፤ አሁን ድረስ ይህን ዐዋጅ ደፍረው አንቀበለም ያሉ የሚመስሉ አስመሳይ የከ/ት/ተቋማት፣ ዐዋጁን ብር መሰብሰቢያ አድርገውታል። ስም መጥቀስ ካስፈለገ፣ በ2008 ዓ.ም የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በከተማ ሥራ አመራር፣ ትራንስፖርት፣ አስተዳደር ወዘተ. ብዙዎችን መዝግቦ ነበር። ከተመዘገቡት ውስጥም አብዛኛዎቹ መምህራን ነበሩ። ግን በ28/01/2008 ዓ.ም ላይ፣ ‹መምህራን የሆናችሁ፤ ከትምህርት ሚኒስቴር አዲስ መመሪያ መጥቷልና በሙያችሁ ብቻ መቀጠል ትችላላችሁ፤›› ብሎ ለመመዝገቢያ የሰበሰበውን ገንዘብ ወደ ካዝናው ከትቷል፤ ከዚያም፣ ‹በትምህርት ዘርፋችሁ ከተማራችሁ ተማሩ፤ ካልሆነ የተቋን ግቢ ለቅቃችሁ ውጡ!›› በማለት ተመዝጋቢዎችን አባርሯል። ይሄ ምን ያሳየናል? መልሱት።

ያልበሰለ ዐዋጅ፣ መመሪያ፣ ደንብ ወዘተ. የመኖር ሕልውናን ይገፍና ሌላው ቀርቶ የሞት መንገድን ያከብዳ!ል! ኅሊና ያቆስላል። እየተበደልኩ ከምኖር ትልና፣ ወደማታውቀው ሀገር እንድትሰደድ ያስገድድኻል። ወገኔ ከሚበድለኝ – ባዳ ይበድለኝ ትላለኽ፤ ሕመሙ አጥንትህ ድረስ ዘልቆ ይሰማኽና፣ ያልበሰለ ሐሳብ፣ ሕግ… አላኖር ይልኽና፣ እትብትህ የተቀበረባትን አገር ጥለኽ ትሄዳለኽ። ያልበሰለ ሐሳብ፣ መመሪያ፣ ደንብ … ማራመድ ለእኛ ቀላል ነው። ለዚህ አባባሌ ምስክር ፍለጋ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም። የቅርብ ጊዜው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች እቅድ ያስከተለው የሰው ሕይወት መጥፋት እና የንብረት ውድመት ማስታወስ ይበቃል። የዚያ ሁሉ ክስረት መከሰት አንዱ መነሻ ምክንያት የእቅዱ (የሐሳቡ) ቀድሞም ያልበሰለ መሆን ነው። ራሳቸው የሐሳቡ ጠንሳሾች በቴሌቪዝን መስኮት ቀርበው፣ ‹‹በጉዳዩ ላይ ከሚመለከተው ሕዝብ ጋር አልተወያየንም። ሐሳቡ በሕዝቡ ዘንድ በደንብ አልተብላላም። … ››  እያሉ ሲቀበጣጥሩ ነበር። ይህ የሚያሳየን፤ ያልበሰለ ሐሳብ ጉዳትን እንጂ፤ ያለውን ጥቅም አይደለም።

እስቲ ያልበሰሉ መመሪያዎች ሐሳቦች፣ ዐዋጆች… ይብቁ። ለኛ የሚያበረክቱት አንዳችም ጥቅም እንደሌላቸው ከእኛ በላይ ማን ያውቀዋል? ማንም አያውቀውም! ይብቁን።  መምህሩን የመማር መብቱን ስንነፍገው፣ መንገድ ቀይሮ የቀን ሠራተኛ፣  ሾፌር፣ ዲግሪ እያለው የሰርተፍኬት ትምህርት እንዲማር አናድርገው! ሕይወቱን አናጠልሽበት! ኑሮውን ሞት አናድርግበት! አለበለዚያ ውድ ዋጋ ያስከፍለናል። በከፍተኛ ወጪ አገሪቷ ያስተማረቻቸውን ዜጎች፣ በአንድ ያልበሰለ ሐሳብ ውጤት ዐዋጅ እንድታጣቸው አንፍቀድ። እውቀታቸውን፣ ብስለታቸውን እንጠቀም!  መምህር የሌለባት ሀገር – ሀገር አትሆንም። አለበለዚያ መጨረሻዋ መካን፣ የማታመርት ሀገር መሆን ነው።

ስለተባለምሐሳቦቻችን፣ መመሪያዎቻችን፣ ደንቦቻችን…  ቀድመው ይብሰሉ። እንዲበስሉ እንወያይ፤ የሐሳብ ልዩነትን ማድመጥ ይዳብር፤ የሕይወት፣ የአገር ሚዛናችን ከኪስ፣ ከግለሰብ ወይም ከሆድ አንጻር ብቻ ሳይሆን፤ ከዜጋ፣ ሀገር… አንጸር ጭምር ይሁን። መመሪያዎቻችን፣ ደንቦቻችን፣ ዐዋጆቻችን…  እንደወረዱ ‹‹በሙሉ ድምጽ›› ያለአንድ የተቃውሞ ድምጽ አይጽደቁ፣ ተግባራዊ አይደረጉ። በጭብጨባ እና እልልታ ብቻ አይታጀቡ። በበሰለ ሐሳብ ጭምር አምረው ይታጀቡ! ጥቂቱን መሪ ሳይሆን፣ ብዙውን ተመሪ ይጥቀሙ። እንደ ጉሽ ጠላ የይድረስ የይድረስ ሳይሆን፤ ታቅደው እና ተብላልተው ይጽደቁ። ተወካዮችን ብቻ የሚጠቅሙ ሳይሆን፤ ወካዮችንም፣ ያልተወከሉትንም ጭምር የሚጠቅሙ ይሁኑ።ሐሳባችን ያልበሰለ ከሆነ፣ እኛም እንደኔው ነጋዴ በቅንነት ‹‹አልበሰለም!›› እንበል።የበሰለ ዴሞክራሲ የምናይበት ዘመን አይራቅ።

አበቃሁ። ሰላም!

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *