ሲራክ ተመስገን

 

 

ወደጆቹ ኤንዲ እያሉ የሚጠሩት የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር የነበረው አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በየመን የጸጥታ ኀይሎች ሰንዐ ላይ ተይዞ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ ከተሰጠ ድፍን አንድ አመት አለፈው። ዩ.ኤስ አሜሪካ የምትታተመው 7ኪሎ መጽሔት፣ «ኤንዲ ያቺን ሰዐት» በሚል ርዕስ ስለ አንዳርጋቸው ጽጌ አያያዝ እና ማንነት በሰፊው ጽፋ ነበር። እሷ ስለሰነዐው የአንዳርጋቸው አያያዝ ከጻችው ውስጥ አንዱን አንቀጽ እዚህ ላመጣው ወደድሁ፤ ጥሩ ምስል ከሳች ነች፤

 

‹‹አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን የጸጥታ ኀይሎች አስገዳጅነት የመንገደኞች ማመላሻ አውቶቡስ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገው ሰንዐ አየር ማረፊያ ወደሚገኘው የጦር አውሮፕላን ማረፊያ ተወሰዱ። ብዙም ሳይቆይ በአነስተኛ አውሮፕላን እንዲሳፈሩ ተገደው፤ ከአንድ ሰዓት ከኀምሣ ሦስት ደቂቃ በረራ በኋላ ደብረ ዘይት አረፉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ዋነኛ ተፈላጊ፣ ፍርድ-አምላጭ እና ነፍጥ ያነሳ የተቃዋሚ ቡድን መሪ በአገሪቱ የጸጥታ ኀይሎች እጅ ወደቁ። የስድስት ዓመት ክትትል ባልታሰበ ጊዜ በድንገት አበቃ።»

 

ከዚህ ድራማዊ ከሚመስለው ድርጊት በኋላ አንዳርጋቸው በፖሊስ ፕሮግራም ላይ ከታየ በኋላ የት እንዳለ በይፋ አይታወቅም። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት በጥበቃ ሥር ላሉና በፍርድ ለታሠሩ እስረኛ የሚሰጠው መብታቸው ተነፍጓል፤ ሕገ-መንግሥቱ በአንቀፅ 21 (ንኡስ አንቀፅ 1 እና ኹለት፣ በተከታታይ) እንዲህ ይላሉ፡- «በጥበቃ ስር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብአዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው።»፤ «ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘት እና እንዲጎበኟቸውም ዕድል የማግኘት መብት አላቸው።»

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት እንዲህ ደንግጎ ለተያዙ ሰዎች መብት ቢሰጥም፤ ሕገ-መንግሥቱን ባለማክበር የሚታወቀው የኢሕአዴግ መንግሥት ለአንዳርጋቸውም አልራራለትም። የራሳቸውን ሕገ-መንግሥት እንኳ የመተግበር አቅሙም ፍላጎቱም የላቸውም። አንዳርጋቸው የእንግሊዝ ዜግነት እንዳለው የታወቀ ነው። የእንግሊዝ ዜግነት ያለው ሰው መሰወሩ ያሳሰባቸው የመብቶች መጠበቅና መከበር ተሟጋቾች እና ፖለቲከኞች ለእንግሊዝ መንግሥት በተደጋጋሚ ለሚያሰሙት የአንዳርጋቸው የት ነው ያለው ጥያቄ፤ ከእንግሊዝ ኢምባሲ አካባቢ፣ «ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ነው ያለው፤» የሚል ምላሽ ይሰማል።

በቅርቡ ቲውተር ላይ አንድ ተጠቃሚ ለእንግሊዙ አምባሳደር፣ «አንዳርጋቸው የታሰረበት አይታወቅም?» ብሎ ላነሳባቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ፣ አንዳርጋቸው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ነው ያለው የሚለውን የመንግሥታቸውን ሐሳብ ያጎላዋል። መልሳቸው፣ «It’s called Kality Prison. At least that’s where I have been meeting him recently» የሚል ነበር።

የእንግሊዙን አምባሳደር እንዳናምናቸው የሚያደርገን ሌላ ክስተት አለ። አንዳርጋቸው የመጎብኘት መብቱ ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎች ለመመስከርም ነው ያልቻለው። «የግንቦት 7 አባል ናችሁ፤ ከአንዳርጋቸው ጋር ትገናኙ ነበር። … » ተብለው ተከሰው እስር ላይ የሚገኙ ግለሰቦች፤ በተደጋጋሚ፣ «የግንቦት 7 አባል እንዳልሆንን የግንቦት 7ቱ ከፍተኛ አመራር አንዳርጋቸው ጽጌ ለፍርድ ቤቱ ቀርቦ ይመስክርልን፤» ቢሉም፤ ፍርድ ቤቱም፣ «አንዳርጋቸው ይቅረብ» ብሎ ቢያዝም፤ ማረሚያ ቤቱ ሊያቀርበው ፍቃደኛ አልሆነም።

ነገሩ ማረሚያ ቤት ከፍርድ ቤት በላይ የሆነ ነው የሚያስመስለው። የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አንዳርጋቸውን ፍርድ ቤት የማያቀርበው ለምንድን ነው? በማረሚያ ቤቱ ስለሌለ? ነው ወይስ የእንግሊዙ አምባሳደር እየዋሹን ነው?

እንግዲህ፤ ለመንግሥት አስጨናቂ ነበረ የተባለው አማፂ ቡድን መሪ፣ የመን ሰንዐ ላይ ከተያዘ ወዲህ በግልፅ የት እንዳለ አይታወቅም። ሕገ-መንግሥታዊ መብቱ ተነፎጎ፤ ከተሰወረ ድፍን አንድ ዓመት አለገፈው። እኔም፣ ‹‹ኤንዲ የት ነው ያለው?›› ብዬ ጠየቅኩ።

ሰላም!

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *