ደረጀ መላኩ

tilahungesses@gmail.com

 

ቁጥራቸው የትዬሌሌ ኢትዮጵያውያን መተባበርን ጫና ሰጠተው ይተቻሉ። ሀሳቡ የተቀደሰ ነው። ያለ ህብረት ምን በጎ ነገር አለ? ያለ ሕብረት ብልጽግና፤ ያለ ሕብረት ድል የለም። ደርግ ስልጣን እንደ ያዘ ሰሞን ከመኢሶን እና ከአላማው ደጋፊዎቹ ጋር አንድ ላይ ለመስራት ሞክሯል፤ አሁን የኢትዮጵያ ጌቶች ለመሆን የበቁት ኢህአዴግያውያን በጫካ ሕይወታቸው አስመራ ላይ የአገዛዝ ሥርዓታቸውን ከመሠረቱት ከሻዕቢያ ጋር ተባብሯል። ባለፉት ሃያ አራት አመታት ደግሞ ከሰላማዊ ትግል አኳያ የተሰለፉ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረቶችን ወይም ሕብረቶችን መስርተው አንድ ላይ ለመስራት ሞክረዋል። መተባበሩ በራሱ ክፋት የለውም። ምን አይነት ትብብር የሚለው ግን ወሳኝ ነው።

ደርግ የስልጣን ጥመኛ ስለ ነበር ገና በጠዋቱ በደም አባላ ተደመደመ፤ አንዴ ጥምረትና ሕብረት ሌላ ጊዜ ደግሞ ቅንጅት በሚሉ ስያሜዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የህብረት ፍልስፍና ቢያራምዱም፤ ኢትዮጵያን ዲሞክራሲ የሰፈነባት ሀገር ለማድረግ የነበራቸው ጥረት ሁሉ በሰላማዊ ፖለቲካ ታጋይነት ስም በተሰገሰጉ የከንቱ ከንቱዎችና አድርባዮች የሴራ ፖለቲካ አማካኝነት መክኖ ቀርቷል። ኢህአዴግና ሻዕቢያ ሲተባበሩ ያተኮሩት በመንግስት ግልበጣ ላይ ነው። መንግስትን ገልብጦ ሌላ የራሳቸው መንግስት ማቆም የሀገሮችን ችግር ለመፍታት የሚለው ትልም የሚለው መገኛው በጥናት ወረቀት ላይ ብቻ ነው። ለሕዝብ የሚለው ሰበብ ለእርዳታ ማግኛ ሲያደርጉት አክትሟል፡፡ ሁለቱም አገዛዞች በአረብ ሀገሮችና በአውሮፓውያን ዕርዳታ  የሚፈልጉት ደረጃ ላይ ቢደርሱም፤ ዲሞክረሲያዊ ስርዓት ማቆም አልቻሉም፤ ሰብዓዊ መብቶችንም ለማስከበር ተሰኗቸዋል፡፡ ትግሉ በእርዳታ ገንዘብ ተሸጧል። እልፍ አእላፍ ታጋዮች ህይወታቸውን የሰዉለት ትግል የታለመለት ደረጃ ላይ የደረሰ አይመስለኝም። በመሰረቱ የጠራ ራዕይን ሳይዙ መጓዝ የሚያመጣው ችግር ይሀ ነው፡፡

ምክንያታቸው ሕዝብ ቢሆንም የተረዱበትን ቃል ለመፈጸም በኢንቨስትመንት ስም ባእዳን በመሬት ቅርምት ላይ እንዲሰማሩ አድርገዋል። ያም ሆኖ ግን በትብብራቸው አልዘለቁም፤ በፍቅራቸው አልጸኑም። ለስልጣን ለሀብት ክፍያ እርስ በርስ ተራኩተዋል። የጉዳዩ ባለቤቶችም ይበልጥ የሚያገለግሏቸውን ለማግኘት እድል አግኝተዋል። አንዱን ሸልመው ሌላውን በማእቀብ ቀጥተዋል። (ተወደድኩኝ ብለሽ  አትበይ ጠምበር ገተር – እኛን አንድ ሰሞን እንዲህ አርጎን ነበር) አባብሏቸዋል። ሻዕቢያ በመቀጣቱ የአዲስ አበባው አገዛዝ ተኩራርቷል። ልእለ ሀያላን ሀገራት ተጽእኖ ማሳደራቸውን ዘንግተው በራሳችን መወሰን እንችላለን ብለዋል። እናም ( ሁለት ባላ ትከል እናም አንዱ ቢሰበር በአንዱ ተንጠለጠል) በሚል ቻይናን ሁለተኛ ወዳጅ ለማድረግ ውስጥ ውስጡን እንዳሴሩ የፖለቲካ ተንታኞች በጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ አስፍረውታል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ቻይናና አሜሪካን በፈረቃ ለመጠቀም እንደ ሆነ ግልጽ ነው። (ዶሮ ገመዷን ረዘም  ሲያደርጉላት የለቀቋት ይመስላታል) እንደሚባለው ማለት ነው።

ሰዎቹ (ጥንቱን ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ) የሚለው ብሂል የደረሰባቸው ይመስለኛል። ስለዚሀም አገዛዙ ገደብ በሌለው ሁኔታ የሃገሪቱን በር ለባእዳን ክፍት አደረገ። ለአለም የውሃ ጥማተኞች እጅግ እርካሽ በሆነ ዋጋ ለም መሬት ቸበቸበ፤ ሚጢጢዋ ጂቡቲ ሳትቀር የምታቀርበው ጥያቄዎች ምላሽ ተቸራቸው፤ አገዛዙ የኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያምን አገዛዝን ከስልጣን ኮርቻ ላይ ለመጣል ባደረገው መራር ትግል ባለውለታ ለነበረችው ሱዳን እጅግ ለምና ሰፊ ቦታን የሚሸፍን የድንበር መሬት ለመስጠት ዝግጅቱ መጠናቀቁን ሱዳን ትሪቡን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት ጉዳይ ይመስለኛል። ስለ ድንበር መሬቱ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡበትም፤ የሁለቱ ሀገራት ድንበር ጉዳይ እልባት ይሰጠዋል ተብሎ የሚጠበቀው አንድ እንግሊዛዊ መኮንን (ኮሎኔል ጊዊን የሚባል) ማንንም ሳያማክርና ኢትዮጵያን ንጉስ ይሁንታ (እምዬ ምኒልክን ማለቴ ነው) ያሰመረውን መስመር እንደ መረጃ በመወሰድ እንደ ሆነ ይነገራል፡፡ ይህ መረጃ ደግሞ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ፤ መይሳው ካሳ የተወለደባትን ቋራና አጼ ዮሃንስ የተሰዉላትን መተማን የሚያሳጣ፤ አንዲሁም ትውልድ ተሻጋሪ ግጭቶችን የሚቀሰቅስ መዘዝን ሊያመጣ እንደሚችል ስመጥር የፖለቲካና ታሪክ ምሁራን ደጋግመው መክረዋል፡፡ ሆኖም ግን ሰሚ አልተገኘም። የኢትዮጵያው አገዛዝ የፖለቲካ ትርፍ እና ኪሳራውን በማስላት ብቻ ያሰበውን ገቢራዊ የሚያደረግ ከሆነ፤ ታሪካዊ ሰህተት ውስጥ እንደሚወድቅ ምሁራን ዛሬም መናገራቸውን አላቆሙም።

አገዛዙ ራሱን በቪላ፤ አፋሽ አጎንባሾቹን በኮንዶሚኒየም፤ ልጆቹን በስኮላርሺፕ አንበሸበሸ፡፡ ለድኀው ኢትዮጵያዊ ተረፍ መረፍ የደረሰው ለማስመሰል ቅንጥብጣቢ ጣለለት። የነሆለለውም በሌለ ነገር እንዲኩራራ፤ በባዶ ልቡ እንድታብጥ ተቀሰቀሰ። ግራም ነፈሰ ቀኝ በኢትዮጵያ መሬት በጥቂቶች እጅ እየወደቀ ይገኛል። የቀረበት ሕዝብ ነው። የተንገላታው ሁሉንም ያጣው ሕዝብ ነው። አገዛዙን ወገኔ በማለት እየደገፈ ያስገባው ሕዝብ ነው፡፡ እየተረገጠ ያለው በሕብረት እንዳያድም ከጎረቤቱ፤ ከኖረበት ቀዬ፤ የተባረረው ሕዝብ ነው የጨለመበት። በምትኩ ጊዜ የወለዳቸው እና ያመጣቸው ባለ ንዋዮች ናቸው በቦተው የሰፈሩበት። ከጋምቤላ፤ ከወሎ፤ ጎንደር፤ አዲስ አበባ፤ ሀዋሳ፤ አዳማ፤ መቀሌ፤ ባህርዳር ወዘተ. ከሁሉም ስፍራ ህዝብ የበይ ተመልካች እየሆነ ይገኛል። በእውነቱ አሳሳቢ ነው። ቦታው በውጭ ባእዳንም ሆነ የስልጣን አክሊል በደፉት ገዢዎቻችን እንደሚፈለግ ማወቅ ይገባናል። እናም መላሹ ማን ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደልቶኛል ብሎ ይቀበላል ወይስ በሕብረት አብሮ ይነሳል  አገዛዙ የሚያሳስት አይደለም። ድፍን ሀያ አራት አመት ሙሉ በኢትዮጵያ ህዝብ ህሊና ሲመዘን ቆይቷል። አገዛዙ የህዝብን ጥቅም አስጠብቋል ወይም በተቃራኒው ቆሟል ለሚለው ጥያቄ መልሱን መስጠት ያለበት የኢትዮጵያ ህዝብ ነው።

የሳውዲ ሀብታሞች፤ አረቦች፤ ህንዶች፤ ቱርኮች፤ ቻይናዎች ሁሉም መሬት በርካሽ ዋጋ ተቸብችቦላቸዋል። ምን ቸገረው አገዛዙ አልደማበት፤ አልቆሰለበት። ባእዳን መሬቱን አረሱ፤ ምርቱንም ሰብስበው ወደ ሀገራቸው አሳፈሩ። ማን ተው ይላቸዋል ህንድም አረብም ድርሻውን ተቀራመተ። ምስኪን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወራሪዎች ጋር ያደረገው ተጋድሎ በአገዛዙ እና ሎሌዎቹ ተነጠቀ። ወራሪዎች እና ታሪካዊ ጠላቶቻችን አንጀታቸው ራሰ። የሀገሩ ዜጋ ቤቱን መሬቱን ተቀማ ቦታ ልቀቅ ተባለ ለአንተ ሌላ ምትክ ቦታ ይሰጠሃል ተብሎ ወልዶ ከሳመበት ቀዬ ርቆ እንዲሰፍር ተደረገ። አዱኛ ብላሽ/ አዳዲስ ሀብታሞች መጥተዋል ከሜዳ፤ ሲበሉ የሚሮጡ፤ ሲጠጡ የሚራገጡ መጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ መጠኑ ይብዛ ይነስ እንጂ በኖረባቸው ዘመናት በሙሉ ከመከራ ተላቆ አያውቅም። እናም ዘውትር እራሱን ይጠይቃል ‹‹መሬት ይዤ ውስጡ አረንጓዴ – ለምን ይሆን የራበው ሆዴ›› እንዳለው ቴዲ አፍሮ። ትክክል ነው። ድርቅና ጠኔን የኢትዮጵያ መለያ ለማድረግ ሲጥሩ የኖሩት ባእዳን ለአድራጎተቸው ምክንያት ቢኖራቸውም በራሳቸው ሞክረውት ያልተሳካ በመሆኑ ዳግመኛ በዚያ መንገድ ሊሄዱበት አልፈለጉም። ይልቁንስ ለያየተውና ገነጣጥለው ማዳከምና በአለም አደባባይ እራስዋን የማትችል ተጠዋሪ ሀገር አድርጎ ማስቀመጥ የሚቻለው ሆድ አደር ዜጎች አማካይነት መሆኑን በማመን ለማስፈጸም መንደፋደፉን መርጠዋል። ለዚህም ተግባር ያሰማሯቸው የጎሳ ድርጅቶች እንዳሉ የፖለቲካ ጠበብት በጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ የስነበቡት ጉዳይ ነው።

ምንም አይነት ፍላጎተ ቢኖራቸው ተለጣፊ ገዢዎች በአፍሪካ ውስጥ ህዝብን ማስደሰት አይቻላቸውም። ምክንያቱም የተሰማሩበት ተግባር ይህን እንዲያደርጉ አይፈቅድምና። ‹‹የሰው በልቶ አይተኙም ተኝቶ›› እንዲሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሰላማዊ ትግል አኳያ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለማንበር የተነሳችሁ ሁሉ የባእዳን መጠቀሚያ ላለመሆን በርትታችሁ መታገል ይኖርባችኋል። እንዲሁም ቢያንስ ባለፉት ሃምሳ አመታት የተነሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተባብረው ለመስራት ያላስቻላቸው አንዱና ትልቁ መሰናክል የኢትዮጵያን እድገት በማይሹ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራ መሆኑ መታወቅ አለበት። ከዚህ ባሻግር የስልጣን ጥመኞች ታሪክ ይቅር የማይለውን ስህተት ሰርተዋል። ሆንም ግን ይሁንና ኢትዮጵያን ከሞት ለመታደግ እና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለማንበር ህብረት እና ትብብር ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡ ህብረት እና አንድነት ከነማን ጋር የሚለው ሁነኛ ጥያቄ በእጅጉ መጤን ይኖርበታል ባይ ነኝ። ያለ ህልማቸው የሚያልሙ፤ ያለመንገዳቸው የሚነጉዱ እንዳሉ ተስተውሏል። ለድል የጓጉ፤ የወያኔ ኢህአዲግ ግፍ ያንገፈገፋቸው፤ ህብረትን ከልብ ቢሹ ተገቢ ነው። ግን አብሮ መታየት ያለበት ‹‹ብንተባበር እስከ ምን- ባንተባበርስ›› የሚለው ነው።

አበው ሲተርቱ ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ይላሉ። ትብብራችንና አንድነታችን፤ እድገታችንና ኩራታችን ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ ነው። በባህሉና በልምዱ ተፋቅሮና ተጋግዞ መኖር እንደሚችል ያስመሰከረ ሕዝብ ነው እድሉን አንግኝ ፤ ወደ ብዙ የኢትዮጵያ ከተሞችና ገጠሮች ሄጃለሁኝ። የብዙ ቀን መንገድ በበቅሎ፣ በፈረስና በመኪና ተጉዣለሁኝ። ተራ ኢትዮጵያዊ ነኝ። የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ሃይማኖቶች አጋጥመውኛል። ግን በየደረስኩበት ሁሉ ለእንግዳ የሚሰጠው ክብር ተለይቶኝ አያውቅም። ይሄ ነው እንግዲህ እኔ የማውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋነት። ስለሆነም ይህን ታላቅና ጨዋ ሕዝብ ይዘን ለምን ተባብረን መስራት እንዳቃተን ሳስበው መልሱ እንቆቅልሽ ይሆንብኛል። ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ የህብረት ፍልስፍና እንዳንከተል ያደረገን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳተኝነት ሳይሆን በባእድ ፖለቲካና ንዋይ የሰከሩ ህዳጣን እንዲሁም የታሪካዊ ጠላቶቻችን እኩይ ሴራ መሆኑ ታውቆ ኢትዮጵያን ለመታደግ የቆምን ሰላማዊ የፖለቲካ ሀይሎች ሁሉ ዛሬን ሳይሆን ነገን በማሰብ አንድነታችን በቅን ልቦና እንዲሆን በማስታወስ ልሰናበት፡፡

የኢትዮጵያን ትንሳኤ ያሳየን!

 

 

 

 

 

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *