ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ሰኞ የመከላከለያ ማስረጃውን ያቀርባል
-አራቱ ጦማሪያን ትናንት በጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ ቀጠሮ ነበራቸው

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ታስረው፤ በፍትሕ ሚኒስቴር ክሳቸው ተቋርጦ በነጻ ተሰናብተው ከእስር ከተለቀቁት የዞን 9 ጦማሪያንና ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ፣ የሰውና የሰነድ መከላከለያ መስረጃውን የፊታችን ሰኞ ጥር 30 ቀን 2008 ዓ.ም ያቀርባል፡፡
በጥቅምት 10 ቀን 2008 ዓ.ም ላይ፤ የቀድሞ የ‹‹ዕንቁ›› መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተር፣ ጋዜጠኛ እና ጦማሪ የሆነው በፍቃዱ ኃይሉ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 257 /ሀ/ መሠረት ‹‹ተከላከል›› የሚል ብይን እንደ ተሰጠው ይታወሳል፡፡
ጋዜጠኛና ጦማሪ በፍቃዱ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ‹‹ተከላከል›› የሚል ብይን የተሰጠው፣ በዚሁ ፍርድ ቤት የዋስትና መብቱ ተጠብቆለት ከእስር በተፈታበት ጥቅምት 10 ቀን 2008 ነበር፡፡
ጋዜጠኛና ጦማሪ በፍቃዱ፣ ከጦማርያን አቤል ዋበላ፣ አጥናፍ ብርሃኔ እና ናትናኤል ፈለቀ ጋር ይግባኝ በተጠየቀበት መሠረት፣ ታኅሣሥ 20 ቀን 2008 ዓ.ም ከፌዴራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ መጥሪያ ወስዶ፣ በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኙን ለመከታታል ቀጠሮ ነበረው፡፡
በተያያዘ ዜና፤ ከላይ በተጠቀሰው ፍርድ ቤት፣ ጥቅምት 5 ቀን 2008 ዓ.ም ‹‹መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰነበቱ›› የሚል ውሳኔ ተሰጥቷቸው፣ በነጋታው ከእስር ተለቅቀው የነበሩት ጦማርያን አቤል ዋበላ፣ አጥናፍ ብርሃኔና ናትናኤል ፈለቀ፣ ወዲያው ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ በጠየቀባቸው መሠረት፣ ይግባኙን ለመስማት ለትናንት ጥር 28 ቀን 2008 ዓ.ም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀጠሮ ነበራቸው፡፡ ‹‹አዲስ ገጽ›› ከዚህ የፍርድ ቤት ቀጠሮ በፊት ማተሚያ ቤት በመግባቷ፣ የፍርድ ሒደቱን መዘገብ አልቻለችም፡፡

አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር፣ ዳንኤል ሺበሺ እና ሦስት ሙስሊሞች ጨለማ ቤት ታሰሩ

ሰኔ 12 ቀን 2003 ዓ.ም በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በፍርድ ሒደት 18 ዓመት የተፈረደባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ዘሪሁን ገ/አግዚአብሔር፣ ሐምሌ 01 ቀን 2006 ዓ.ም በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ተከስሰው በፍርድ ሒደት ነጻ ቢባሉም፣ ይግባኝ ተጠይቆባቸው የፍርድ ሒደቱን በመከታተል ላይ የሚገኘው የቀድሞ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራር የነበረው አቶ ዳንኤል ሺበሺና ‹‹አዲስ ገጽ›› ማንነታቸውን በግልጽ ልትለይ ያልቻለቻቸው ሶስት ሙስሊሞች የባለፈው ሳምንት ረቡዕና ሐሙስ ዕለት በታሰሩበት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ዞን 2 በእስረኞችና በፖሊሶች መካከል በተፈጠረ ግጭት ‹‹ግጭቱን ከጀርባ ሆናችሁ ያነሳሳችሁት እናንተ ናችሁ›› በሚል ከአርብ ጥር 20 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ቀዝቃዛ ጨለማ ክፍል በሆነ ኮንቴይነር ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ምንጮች ገለጹ፡፡
ለግጭቱ መነሳት እንደ ምክንያት የተነሳው፣ እስረኞች የጠየቁት ጥያቄ በማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በኩል ተገቢውን ምላሽ ባለማግኘቱ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡
‹‹ወላጅ አባቴን ሰኞ ዕለት ቃሊቲ ሄጂ ጠይቄው ነበር፡፡ ከዋናው ፍተሻ ባሻገር ውስጥ ጥብቅ ፍተሻ ነበር፡፡ ተፈጠረ ስለተባለው ጉዳይ አባቴን ጠይቄውም ነበር፡፡ በእስረኞች እና በፖሊሶች መካከል ለሁለት ቀናት ግጭት መፈጠሩንና ‹ከግጭቱ ጀርባ እናንተ ፖለቲከኞች አላችሁበት› ተብለን በዚህ ቀዝቃዛ የኮንቴይነር ጨለማ ክፍል ውስጥ ታስረናል፡፡ በጉዳዩ ላይ እጃችን የለበትም፡፡›› ብሎኛል የምትለው ወ/ት ሊዲያ ዘሪሁን፣ የአባቷ እጆች መጥቆራቸውን ለ‹‹አዲስ ገጽ›› ተናግራለች፡፡
ወ/ት ሊዲያ አያይዛም፣ አባቷ ከአራት ወራት በፊት ታስሮ ከነበረበት ዝዋይ ለህክምና ቃሊቲ መመለሱን ጠቅሳ፣ ማዕከላዊ ታስረው በነበረበት ወቅት በደረሰበት አውጫጪኝ ግርፍ የእጁ አጥንት መሰበሩን፣ የኩላሊትና የጆሮ ህመም እንደ ጀመረው ገልጻለች፡፡ አቶ ዘሪሁን ቃሊቲ ከተዘዋወሩ በኋላ ፖሊስ ሆስፒታል ህክምና አድርገው የቀዶ ጥገና ለማድረግ ሌላ ቀጠሮ ተሰጥጧቸው እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የፌዴራል የማረሚያ ቤቶች አስተዳደርን አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ከጠበቃው ጋር መገናኘት አልቻሉ ተገለጸ
– ‹‹የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ሕግንና የፍርድ ቤት ትዕዛዝን እያከበረ አይደለም››
አቶ አምሃ መኮንን
(የጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የሕግ አማካሪ)

በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ ታህሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ በፌዴራል ወንጀል ምርመራ ታስሮ የሚገኘውን የነገረ-ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ጠበቃ የሆኑት አቶ አምሐ መኮንን ባሳለፍነው ረቡዕ ጥር 25 ቀን 2008 ዓ.ም ለሰባተኛ ጊዜ ሊያገኙት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ ‹‹ማግኘት አይቻልም›› የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ለ‹‹አድስ ገጽ›› ገለጹ፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ጥር 14 ቀን 2008 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ከጠበቃው ጋር መገናኘት አለመቻሉን ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው እንደ ነበረ የሚገልጹት ጠበቃ አምሐ፣ ‹‹አቤቱታው የጊዜ ቀጠሮ ላይ እንዲመዘገብ አድርጌያለሁ፡፡ ከደምበኛዬ ጋር ሊያገናኙኝ አለመቻላቸውን ተናግሬ ፍርድ በመዝገቡ ላይ አያይዞ ነበር፡፡ ችሎቱም ይህ ሕገ-መንግስቱን የሚጻረር መሆኑን ጠቅሶ በወቅቱ የነበረውን መርማሪ ለአለቆቹ አስረድቶ ተከሳሹን ከጠበቃ ጋር ማገናኘት እንዳለባቸው ተነግሮት ነበር፡፡ ግን ይህ በተግባር መሆን አልቻለም›› ብለዋል፡፡
‹‹አሁን ማዕከላዊ ስሄድ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ አይቻልም›› የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ጠበቃው ይናገራሉ፡፡ ‹‹የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ሕግንና የፍርድ ቤት ትዕዛዝን እያከበረ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም ማዕከላዊ ደንበኛዬን ላገኘው ሄጄ ጥበቃው ካህሳይ ከሚባል ሰው ጋር በሬዲዮ መገናኛ ከተነጋገረ በኋላ፣ ክህሳይ የተባለው ሰው ከዚህ በኋላ እንደዚህ አይነት ነገር [ተጠርጣሪን ከጠበቃ ባር ማገናኘት] ተከልክሏል ሲል ሰምቸዋለሁ፤›› የሚሉት ጠበቃ አምሐ፣ ‹‹የዚህ መ/ቤት የበላይ የሆነው ፍትሕ ሚኒስቴር የዜጎች ሕገ-መንግስታዊ መብት መጣሱን አውቆ ተገቢውን አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድ›› ሲሉ አጽንኦት በመስጠት አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ወንጀል ምርመራ መ/ቤት ከዚህ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ተጠርጥረው የሚታሰሩ ዜጎችን ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የማያገናኙ ከሆነ፣ በእስር ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችም ሆኑ ከዚህ በኋላም በማናቸውም ምክንያት የሚገቡ ወይም የሚታሰሩ ዜጎች የሕግ አማካሪ ፈልገው ማግኘት ከተከለከሉ፣ ቃላቸውን ለፖሊስ እንዳይሰጡ እንደሚመክሩ ያስረዳሉ – አቶ አምሐ፡፡
‹‹ይህ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ሊያምኑ የሚፈልጉ ዜጎች እንዳያምኑ ያደርጋል፡፡ ይህ የሚጎዳው መርማሪውን አካል ነው፡፡ የፖሊስን ሥራ ከባድ ያደርገዋል፡፡ በእኛ በኩል ወንጀል አይውጣ አንልም፡፡ እኛ ጠበቆች ምርመራ እንደምናደናቅፍና ወንጀል እንዳይወጣ የምንተባበር ተደርጎ መገመት የለብንም፡፡›› የሚሉት ጠበቃ አምሐ፣ ደንበኛቸው የሆነውን ጋዜጠኛ ጌታቸውን ከዚህ በኋላ የሚገኙት ለሦስተኛ ጊዜ የካቲት 11 ቀን 2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት ለቀጠሮ ሲቀርብ መሆኑን ለ‹‹አዲስ ገጽ›› ተናግረዋል፡፡
በሌላ ተያያዥ ዜና፤ የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ጠበቃ አቶ ሽብሩ በለጠ፣ ደንበኛቸውን ማግኘት አለመቻላቸውን ‹‹አዲስ ገጽ›› ለማወቅ ችላለች፡፡ አቶ ዮናታን ተስፋዬ የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሏል፡፡

About the author

3 Comments

  1. admin

    Dear anjonesgamo, please read the directions on the breaking news part or in the blog. It should be working if you properly follow the steps.

  2. anjonesgamo

    Please Log In to read the rest of this content. If you are a new user, click Here to create new user name and password. this link is not working please and the pdf format is difficult to download cant you make it best to read and download please?? we dont have option the hard copy her in Hamer Jinka SNNPR
    Regards

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *