ኢቴቪ፣ ‹‹ኢብኮ›› ለባለቤቱ ይመለስ!

ላለፉት 50 ዓመታት አገልግሎቱን ሲሰጥ የቆየውን የቀድሞ ‹‹የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን››፣ የአሁኑ ‹‹የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን›› የተቋቋመበትን ዓላማ ለማስፈጸም መመሥረቱ ይታወቃል። ባሳለፍናቸው ዓመታትም በኢትዮጵያ ሕዝብ ሥነ- ልቦና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳረፉ ሁነቶችን በመዘገብ፣ በማሳወቅ፣ በማዝናናት እና መረጃ በማቀበል ሚናውን ለመወጣት ሞክሯል።
ይሁንና ገና ከምሥረታው ጀምሮ ከሕዝብ ይልቅ ዘውዳዊ አገዛዝን በማሞካሸት እና በማንቆለጳጰስ ሥራውን የጀመረው ይህ የዕድሜ አንጋፋ ተቋም፤ እውነተኛ የሕዝብ ድምጽ ሆኖ ለሰፊው የኅብረተሰብ ክፍል ይደርስ ዘንድ ተዓማኒነትን እና ተቀባይነትን ከማትረፍ ይልቅ፤ በየዘመኑ ለተፈራረቁ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነኖች አፈ-ቀላጤ በመሆን በዝንብ ቁስል ላይ እንጨት ሲሰድ መኖሩ ይታወቃል።
እንደ አንድ ‹‹ብሔራዊ›› የመገናኛ ብዙኃን ተቋምም የሚጠበቅበት ደረጃ እጅግ የወረደ ‹‹ሥራ›› በመሥራት ከኩራትነት ይልቅ የችግራችን አንዱና ዋነኛ ምንጭ ሆኗል። ሕዝብ እየተሰቃየ፣ በኑሮ ውድነት እየተማረረ፣ በሥራ አጥነት እየተንገላታ፣ በባሕር ማዶ ስደት እየተቀጣ፣ በድርቅና ረሃብ እየተጎሳቆለ፣ በአንባገነኖች ክፉ በትር እየተቀጠቀጠ ባለበት ወቅትም፣ በተቃራኒው ‹‹በሬ ወለደ›› ነጭ ውሸቱን ሊምገን ሲሞክር የኖረ፤ የግፈኞች መሣሪያ እንደ ሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው።
ባለፉት ዐሥርት ዓመታት እንኳ ምን ያህል ሲዋሸንና ፍጹም ከጋዜጠኝነት ሥነ- ምግባር የራቁ አሳፋሪ ድርጊቶችን ሲሠራ እንደኖረ ሁላችንም የምናውቀው ነው። በንጹኃን ዜጎች ላይ የፈጠራ ዘገቢ-ፊልሞችን በማቅረብ፣ የፍርድ ቤት ሥራ ላይ ተጠምዶ በግላጭ ጣልቃ ሲገባም አይተናል። ለዜጎች የሰብዓዊ መብቶች መጣስ ምንም ግድ ሳይኖረው፤ አይቶ እንዳላየ ሲያልፍም ታዝበናል።
የሕዝብ አጀንዳ ከመቅረጽና ከማስተዋወቅ ይልቅም፤ የአምባገነኖችን ቀጫጭን ትዕዛዞች ተቀብሎ በማስተላለፍና እንደ ገደል ማሚቶ በማስተጋባት ኅሊናችንን ሲያደማ ኖሯል፤ አሁንም በዚሁ ድርጊት እንደገፋበት አለ።
ተቋሙ ዘመን ከመቁጠር ባለፈ ለሕዝብ ፋይዳ ያለው ሥራ መሥራት ይኖርበታል! መሥራት ካለበትም ከተጠናወተው ፍጹም የአሽከርነት ‹‹ሥራ›› ወጥቶ የራሱን የኤዲቶሪያል ነጻነት በተግባር ማረጋገጥ ይኖርበታል። አረጋግጦም ከደኅንነት መሥሪያ ቤትና ካልታወቀ የዋልታም ሆነ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢ.ዜ.አ.) ምንጮች የሚላኩ አፍራሽ ዘገባዎችን ባለመቀበል፣ የራሱን ኅልውና ሊያስጠብቅ ግድ ይለዋል። በዚህም፣ ኢቴቪ፣ ‹‹ኢብኮ›› ለእውነተኛ ባለቤቱ ‹‹ለኢትዮጵያ ሕዝብ›› ጥቅም በመሥራት የማን አጋር እንደ ሆነ በተግባር ያሳይ! አሊያ ግን፡- ‹‹ጨፍኑ ላሞኛችሁ›› ቢለን – መስሚያችን ድፍን ይሆንበታል!

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *