እነ ሀብታሙ አያሌው ለየካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም ተቀጠሩ

በጸረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ‹‹መከላከል ሳያስፈልጋችሁ በነጻ እንዲሰናበቱ›› የሚል ብይን ሰጥቷቸው የነበሩትና አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆባቸው ጉዳቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤት እየተከታተሉ የሚገኙት ፖለቲከኞቹ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሺ እንዲሁም መምህር አብርሃም ሰለሞን ባሳላፍነው ረቡዕ የካቲት 09 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት አቃቤ ሕግ ባቀረበው የሰነድ ማስረጃ ላይ መልስ እንዲሰጡ ለየካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም ተቀጠሩ፡፡

አቃቤ ሕግ በእስር ፍርድ ቤት ከብሔራዊ የደህንነትና የመረጃ መ/ቤት በእያንዳንዳቸው ላይ ያቀረበውን ማስረጃ በአግባቡ አልተመዘነልኝም በሚል ይግባኙን አቅርቦ ነበር፡፡ ጠ/ፍርድ ቤትም የመረጃውን ዝርዝር ካየ በኋላ የብሔራዊ የደህንነትና የመረጃ መ/ቤት በራሱ መንገድ ትንተና አድርጎበታል በሚል የስልክም ሆነ የኢ-ሜይል መረጃዎቹ በይዘታቸው ቃል በቃል ይድረሰኝ የሚል ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ አቃቤ ሕግም ቀን እንዲጨመርለት በደብዳቤ ካሳወቀ  በኋላ ከላይ በተጠቀሰው ቀን 367 ገጽ ሰነድ (ወደጽሑፍ የተቀየረ) በአቃቤ ሕግ ቀርቦ ለሀብታሙ፣ ለየሺዋስ፣ ለዳንኤልና ለአብርሃ በጠበቃቸው አቶ አምኃ መኮንን በኩል መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ በዐ/ሕግ የቀረበው መረጃ መምህር አብርሃም ሰለሞንን አይመለከተውም፡፡ ነገር ግን፣ በቃቤ ሕግ ላቀረበበት የሰው ምስክር በጠበቃው በኩል መልስ ይሰጣል ተብሎ ይገመታል፡፡

አምስቱም ግለሰቦች የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነጻ ባላቸው ጊዜ ከእስር እንዳይወጡ አቃቤ ሕግ ዕግድ አስወጥቶባቸው ወደክርክር ከተገባ በኋላ በቅርቡ የሰበር ሰሚ ችሎት ዕግዱን በመቃወም ከእስር እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ሆኖም የቃሊቲ እና የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ትዕዛዙን ተፈጻሚ ሳያደርጉ በመቅረታቸው የተነሳ ባሳለለፍነው ሰኞ 07 ቀን የካቲት 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት ዳኞ ዳኜ መላኩ ማረሚያ ቤት የፍርድ ቤት ትዕዛዝንና ሕገ-መንግስቱን አለማክበሩን አሳስበው ግለሰቦቹ ከእስር እንዲወጡ በድጋሚ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሰረት በሳላፍነው ማክሰኞ አቶ ሀብታሙ አያሌውና መምህር አብርሃም ሰለሞን ከእስር ሊወጡ ችለዋል፡፡ የተቀሩት አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋና ዳንኤል ሺበሺ በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ሁለት ጊዜ ያህል ‹‹ችሎት ደፍረዋል›› በሚል አብርሃ የ16 ወራት፤ የሺዋስና ዳንኤል ደግሞ የአስራ አራት አስራ አራት ወራት ቅጣት ተጥሎባቸው ተከትሎ የእስር ጊዜያቸውን ስላላጠናቀቁ በሚል ከእስር አለመውጣታቸው ታውቋል፡፡

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *