‹‹ዙጥ-15›› መንግሥታት
ዳንኤል ቢ.
በአፍሪካ አሕጉር ውስጥ ‹‹መሪው ሥልጣን አለቅም አሉ››፣ ‹‹መሪው በሥልጣን ለመቆየት የአገራቸውን ሕገ-መንግሥት አሻሽለው በሀገሪቱ ብጥብጥ ተከሰተ››፣ ‹‹መሪው በሕዝብ ተማጽኖ የሥልጣን ዘመናቸውን አራዘሙ›› ወዘተ. የሚሉ ዜናዎችን መስማት ማንንም አያስደንቅ ይሆናል። በርግጥኝነትም አያስደንቅም። እንደ ዮሪ ሙሴቬኒ፣ ብሌዝ ኮምፓዎሬ፣ ኤድዋርዶ ዶ ሳንቶስ፣ ሮበርት ሙጋቤ፣ ፕሬሪ ንኩሩንዚዛ፣ ፖል ካጋሜ፣ ሳሱ ኑጌሶ ያሉ እፍርታም መሪዎች ባሉባት አህጉር፣ እንዲህ ዓይነቱን ዜና መስማት ብርቅ አይደለም። ነገር ግን የሆነ የአፍሪካ አገር ፕሬዚዳንት በሥልጣን የመቆያ ጊዜውን ከሰባት ዓመት ወደ አምስት ዓመት በገዛ ፈቃዱ (እደግመዋለሁ – በገዛ ፈቃዱ!) እንዲቀነስ አደረገ የሚል ዜና ብትሰሙ ምን ይሰማችኋል? መጀመሪያ ሰውየው በርግጥም አፍሪካዊ መሆኑን፣ ከዛም ዜናው የወጣበት ቀን አፕሪል ዘፉል አለመሆኑን፣ ከዛም እራሱ ሰውየው ‹‹ፉል›› አለመሆኑንና ሌላም ብዙ ብዙ ነገር ከግራም ከቀኝም የምታጣሩ ይመስለኛል።
ተሰፍሮ የተሰጣቸውን የሥልጣን ዘመን መቀነስ ይቅርና፣ ሰላሳና አርባ ዓመት እንደ ብረት ቀጥቅጠውና እንደ ሰም አቅልጠው የገዙትን ሕዝብ መሰናበት እንደ ሞት እየከበዳቸው፤ ማቄን ጨርቄን የሚሉ መሪዎች በሚርመሰመሱባት አፍሪካ፤ እንዲህ ዓይነቱን ዜና ማን በቀላሉ ያምናል!? ከላይ የነገርኳችሁ ዜና ግን ብታምኑም ባታምኑም እውነት ነው። ነገሩ ወዲህ ነው፤ ሰውየው ማኪ ሳል ይባላሉ። የ55 ዓመት ሴኔጋላዊ ጎልማሳ ናቸው። በአ.አ ከ2012 ጀምሮ ሴኔጋልን በፕሬዚዳንትነት እየመሩም ይገኛሉ።
ማኪ ሳል ከአራት ዓመት በፊት ለሀገራቸው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲወዳደሩ፤ ከተመረጡ አደርጋቸዋለሁ ብለው ለሕዝባቸው ቃል ከገቡላቸው ነገሮች መካከል አንዱ፤ የሀገሪቱን የፕሬዚዳንትነት የሥልጣን ዘመን ቆይታ ከሰባት ዓመት ወደ አምስት ዓመት መቀነስ ነበር። እርግጥ እንዲህ ዓይነቱ የምረጡኝ ማግባቢያ ለሴኔጋላውያንም ሆነ ለተቀሩት አፍሪካውያን አዲስ አይደለም። ብቻ፣ ከእርሳቸው በፊት ሀገሪቱን ለዐሥራ ኹለት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ያስተዳደሩት አብዱላየ ዋዴ ነበሩ። እና እርሳቸውም ቢሆኑ በአ.አ 2000 ላይ ለፕሬዚዳንትነት በትረ-ሥልጣን-ጭበጣ ሲፎካከሩ፣ ይሄንኑ የሥልጣን ዘመን ቆይታ ከሰባት ወደ አምስት ዓመት አወርደዋለሁ ብለው ቃል ገብተው ነበር። እና ልክ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ከተጠናቀቀ በኃላ ተፈጻሚ የሚሆን አዲስ ሕገ-መንግሥት በአ.አ 2001 ላይ አስጸደቁ።
በአ.አ 2007 ላይ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ሲቋጭ፣ በአዲሱ ሕገ-መንግሥት መሠረት ለአምስት ዓመት በድጋሚ ተመረጡ። ከተመረጡ በኋላ ‹‹ማምሻም ዕድሜ›› መሆኑ ገባቸው። እና እንደገና በአ.አ 2008 ላይ የሀገሪቱን ሕገ-መንግሥት በድጋሚ እንዲሻሻል አስደረጉ። የተሸሻለውም አምስት ዓመት፣ ከእንደገና ሰባት ተደርጎ ተሻሻለ። ለሕዝባቸውም ሰጥተው የነበረውን ተስፋ በእንጭጩ ቀጩት። ያም ሆኖ ግን ከውጭም ከውስጥም ከፍተኛ የሆነ ግፊትና ተቃውሞ ስለተነሳባቸው፣ ከአምስት ዓመት በኋላ በአ.አ 2012 ላይ ምርጫ ለማካሄድ ተገደዱ። በዚያ ዓመት ላይ ነበር የቀድሞው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማኪ ሳል ተቀናቃኛቸውን ፕሬዚዳንት አብዱላየ ዋዴን በዝረራ አሸንፈው የፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን የያዙት።
አንዴ ጓደኛዬ፣ ‹‹ለሕዝባቸው የገቡትን ቃል የልባቸውን ካደረሱ በኋላ የሚያጥፉ መንግሥታት ‹ዙጥ-15› ይባላሉ›› ሲል ነበር ያጫወተኝ። ታሪኩ እንዲህ ነው፡- አንዴ የሆኑ መምህር በመማሪያ ክፍል ውስጥ ተማሪዎቻቸውን እያስተማሩ ሳለ ድንገት ‹አምልጦ› ያመልጣቸዋል። በነገሩ የተደናገጡት መምህር በፍጥነት አንድ ውሳኔ ወሰኑ፤ ተማሪዎቻቸው ይኸን ‹ጉድ› ለማንም ትንፍሽ ካላሉ ለእያንዳንዳቸው ዐሥራ አምስት ዐሥራ አምስት ነጥብ እንደሚሰጧቸው ተናግረው የሰላም ስምምነት ሐሳብ አቀረቡ። ተማሪዎቹም በሙሉ ድምጽ በሐሳቡ መስማማታቸውን፣ ለማንም ትንፍሽ እንደማይሉ በመግለጽ፣ ነጻውን ዐሥራ አምስት ነጥብ ለመውሰድ ፈቀዱ።
ቆይቶ አስተማሪው ያቀረቡት ሐሳብ እንደማይሠራ፣ የሠሩት ሥራ አግባብ እንዳይደለ ተረድተው ኖሮ፤ ቃል የገቡትን ዐሥራ አምስት ነጥብ በጭራሽ አላልኩም ብለው በመሸምጠጥ ተማሪዎቻቸውን ‹ካዱ›። በእሳቸው ቃል-አባይነት ተማሪዎቻቸው እርር ድብን ብለው ተቃጠሉ። ‹‹ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን›› ሆኖ ይቀራል።
ከጊዜም በኋላ እኒህ ምስኪን መምህር የሚሰሙትን ከቶም ማመን አልቻሉም። ተማሪዎቻቸው እንዲህ አደረጓቸው፡- የመጀመሪያ ጥፋታቸውን (መፍሳት ጥፋት ከሆነ) ለመዘከር ‹‹ዙጥ›› ብለው ሰየሙት፤ ዐሥራ አምስቷን ነጥብ አልረሱም፤ እሷንም ለማስታወስ ‹‹ዙጥ››ን በአኃዝ ‹‹15›› አያያዙት – ‹‹ዙጥ-15››። እንግዲህ ይህ ዓይነት ስሕተት፣ ከብዙ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ‹‹ስሕተት›› ጋር ይመሳሰላል ብሎ ነው ወዳጄ ‹‹ዙጥ-15›› መሪዎች የሚላቸው። እውነቱን ነው፤ አፍሪካ የ‹‹ዙጥ-15›› መሪዎች ሀብታም ነች። ከሴኔጋል የተሰማውና ከላይ በመግቢያዬ የነገርኳችሁ ዜና ግን የተለመደውን የአፍሪካ መሪዎች የሥልጣን ዘመን የማራዘም ጥማት የሰበረና፣ የ‹‹ዙጥ-15›› መሪዎችን ቁጥር በአንድ የቀነሰ ነበር።
ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ወደ ሥልጣን ሲመጡ ለሕዝባቸው ቃል በገቡት መሠረት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት የሥልጣን ዘመን ቆይታ ከሰባት ወደ አምስት ዓመት እንዲወርድ ማድረጋቸውን ይፋ አድርገዋል። ይህም በቀጥታ ተፈጻሚ የሚሆን በመሆኑም፣ በአ.አ 2019 ላይ መጠናቀቅ የነበረበት የሥልጣና ጊዜያቸው፣ በኹለት ዓመት ተቀንሶ ከዓመት በኋላ – በአ.አ 2017 – ምርጫ ይካሄዳል። እርሳቸውም ለፕሬዚዳንትነት ለኹለተኛ ጊዜ ይወዳደራሉ።
ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ‹‹በአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ነገር መሥራት እንደምንችልና ሥልጣን የሁሉም ነገር ፍጻሜ እንዳልሆነ መረዳት አለብን›› እንዳሉት፤ አፍሪካ ቃላቸው ሌላ ተግባራቸው ሌላ የሆኑ መሪዎች መናኽሪያ ብቻ ሳትሆን፤ ቃላቸውን የሚያከብሩ መሪዎች ያሏት እንደ ሆነች በተግባር አሳይተዋል።
የላይቤሪያዋ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፊም ስድስት ዓመት የነበረውን የሀገራቸውን የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ዘመን ቆይታ ወደ አራት ዓመት ዝቅ ለማድረግ እየሠሩ እንደ ሆነ ተናግረዋል ተብሏል። እንዲህ ያለው ዜና የተስፋ ብርሃን የሚፈነጥቅ ነው።

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *