ዮሃንስ ታደሰ

ከአዲስ አበባ ማስፋፊያ ፕሮግራም ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ የተከሰተውን የተቃውሞ ድምጽ ተከትሎ የሀጎሳውያን (የትግራዊነት) ተጠቃሚነትና የቶሎሳውያን (የኦሮሞ) ከፓለቲካው እና ከኢኮኖሚው መገለላቸውን የሚያትት ሀልዮት እየተቀነቀነ እንዳለ አስተውለናል። እውን በእርግጥም የሚወራውን አይነት የማህበረ ፓለቲካና የምጣኔ ሀብት መጠናከር በአንድ አከባቢ ላይ በተወሰኑ ቡድኖች ተጠቃሎ ተይዟል? የወያኔ ዓላማ በአጠቃላይ (ትግራዊነትን) በማህበረ ፓለቲካውና በምጣኔ ሀብቱ ላይ ተዘርግቶ እናገኘዋለን?

ይሄ ጽሁፍ እየተጻፈ ባለበት ሰዓት በትግራይ ክልል በተንቤን ከተማ ላይ፣ ከአ.አ ዮንቨርስቲ የመጀመሪያ ድግሪውን በCivil and Environmental Engineering ያጠነቀቀው ገብረአረጋይ ገብረህይወት ግባዓተ መሬቱ ከተፈጸመ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።…

በትግራይ ክልል በተንቤን ከተማ የተወለደው ገብረአረጋይ ታታሪ ተማሪ ቢሆንም በዙሪያው ሊደግፈው የሚችል ቤተሰብ ስላልነበረው፤ በራሱ ጥረት እነዛን አስጨናቂ ቀናት ሲገኝ እየበላ ካጣም ጉልበቱን ታቅፎ እያደረ የአንድ ሀብታም መደብር እየጠበቀ የደካማ እናቱን ጎስቋላ ግንባር ላለማየት እየሸሸ፤ የታናሽ እህቱን የብዙ አንድምታ ጥያቄ ያዘለ ፊት እየተሳቀቀ በጥረቱ ሀገሪቱ አለኝ ወደምትለው ትልቁ ዮንቨርስቲ መጣ። በርግጥም በልቡ ታላቅ ተስፍ ሰንቋል፤ ያች ውብ እህቱ ያነጋቸውን መንጋት እያሰበች በጉጉት ተውጣለች፤ እናትም የህይወታቸው ጭለማ በልጃቸው ትጋት ወደ ጥልቁ ይወድቅ ዘንድ ምኞታቸው ነበር።

‹‹ጃዋርያውያን››፣ ‹ሀጎስያውያን የኦሮሚያን ምድር ሀብት እየዘረፉ የነቶሎሳን ጓዳ እያራቆቱ ነው’፤ ‘ቶሎሳ ምድርህ ያንተ ብቻ ነች’፤ ‘አቢሲንያውያን የተፈጥሮ ጸጋህን እየነጠቁህ ነው’፤ ‘ክንድህን አበርታ’… እያሉ ያገኙትን መገናኛ መንገድ ተጠቅመው እየሰበኩ፤ ህወሀትያውያን በሌላው ገጽ፣ ‹ትግራይ በሸዋው ማዕከላዊ ግዛት ሥር ወደቀች›፤ ‹የአማራው የመሳፍንት ቡድንና ተከታዮች የትግራይን ነጻነት ገፍፈው የህዝቧን አንድነት ያናጉት…  › ይላሉ።

ገብረአረጋይ ታላቁ ዮንቨርስቲ ውስጥ ከገባ አራት ዓመታትን ደፍ ቀና እያለ አገባዷል፤ የእረፍቱን ወራት በአንድም ወቅት ወደ ተንቤን ስለመሄድ አስቦ አያውቅም፤ ቢያስብ እንኳ የመጓጓዧ ውጪ ማን ሊሸፍንለት? እናቱንና እህቱንስ በባዶ እጁ ምን ሊያደርግላቸው ይቻለዋል? ያች የጓጓላት የምርቃቱ ቀን ደርሳ ስራ አግኝቶ ወደዛች ውብ መንደሩ እስኪገባ ድረስ፤ በአንቱታ ወደ ቀዬው እስኪነጉድ።

‹‹ጃዋርያውያ››፡- “We Oromos must capture state power by any means necessary.… In order to do this we must clandestinely organize all sectors of our society. It is the responsibility of young educated Oromos like you to disseminate this spirit of Oromo nationalism when you return to your respective communities. We can only change the deplorable condition of our people by being tolerant to one another and reestablishing Oromo unity. In this way we can build a strong organization, capture state power, and take actions that facilitate a fundamental social transformation.›› (ባሮ ቱምሳ ንግግር፣ 1963፤ ኦነግን ለመመስረት በተደረገ ምስጢራዊ ስብሰባ ላይ)። በግርድፉ ሲተረጎም እንዲህ የሚል ሀሳብን ይዟል፡- ‹‹እኛ ኦሮሞዎች የትኛውንም መንገድ ተጠቅመን የመንግስትን ሥልጣን መቆጣጠር ይኖርብናል… ይሄንን ለመፈጸም ይረዳን ዘንድ የማህበረሰባችንን ክፍል ምስጢራዊ በሆነ መልኩ ማደራጀት ይኖርብናል። የዚህ ሃላፊነት የሚወድቀው እዚህ በምትገኙት የተማራችሁ ወጣት ኦሮሞዎች ላይ ነው፤ (የኦሮሞ ብሄርተኝነት) ሀሳቡን ወደ ምትሄዱበት የኦሮሚያ አከባቢ ወስዶ በማሰራጨት፤ ይህንን የህዝባችንን አስከፊ ሁኔታ መቀየር የምንችለው አንደኛው ሌላኛውን [የኦሮሞ ክፍል] መታገስና ህብረቱን ማጠንከር ሲችል ብቻ ነው። በዚህ መንገድ ለማህበራዊ ሽግግር የሚረዳንን ብርቱ ተቋም መገንባት፣ የመንግስትን ስልጣን መያዝ፣ እንዲሁ ደግሞ ጠንካራ የሆነ እርምጃ መውሰድ እንችላለን።››

ጃዋራውያን ይቀጥላሉ፡- “With the help of European colonial powers, Ethiopians colonized Oromos during the last decades of the 19thc; killed such a large proportion of the Oromo population… ›› (አቶ አሰፍ ጃለታ 2001፣ 56) በዚሁ መጽሀፍ ላይ በገጽ 59፣ ‹‹Most Oromos were enslaved and colonized in their homeland, Oromia and tightly controlled and exploited by Ethiopians”›› መጽሀፉ ላይ እንደምናየው፣ ‹‹በአውሮፓውያን እርዳታ በ19ኛው መ/ክ/ዘ የመጨረሻዎቹ ዐሥርት ዓመታት ወቅት፣ ኢትዮጵያውያን ቁጥሩ በርከት ያለ የኦሮሞ ሕዝብን ገድለዋል፤… ኦሮሞች እትብታቸው በተቀበረባት መሬት – ኦሮሚያ – ላይ መፈናፈኛ አጥተው ቅኝ-ተገዝተዋል፤ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገባቸው በኢትዮጵያውያን ተበዝብዘዋል።››

ገብረአረጋይ የምርቃት ጣጣዎች ከፊቱ ተደቅነዋል። እንደ እድሜ አቻዎቹ ይሆን ዘንድ ህይወት አልፈቀደችም። ሌላው ሌላው ቢቀር የሚጓጓላት የምርቃቱ ቀን ከፊቱ ትጠብቀዋለች። ምን ለብሶ ቀኑን ያከብራል? እናቱ መቼም ሹርባቸውን ተሰርተውና ታናሽ እህቱን አስከትለው ወደ ሸገር መሰስ ማለታቸው አይቀርም። ለመመረቂያ የሚሆነውን ሱፍ እንግዲህ መጠየቅ ጭካኔ ነው፤ ምንም እንኳ የእናት አንጀት ቢሆን? ትኩረቱን ወደ መመረቂያ ፕሮጀክቱና ወደሚያስጠናቸው ሁለት ለግላጋ የከተማው ልጆች ላይ ማድረግ እንዳለበት አሰበ። እነሱም በፊናቸው ፈተናው እየተቃረበ ስለመጣ ጓደኞቻቸውን ቸል ብለው አትኩሮታቸውን ወደ ንባቡ አድርገዋል፤ የዛ ጎበዝ ፈላጭ ልጅ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ምርቃት ደርሷል፤ ቤት ውስጥ ጉድ ጉድ ማለት ተይዟል። የምርቃት ፕሮግራሞች እየወጡ ነው። የ2007 ዓ.ም ምርቃት ጾሙ ሊፈታ አንድ ሳምንት ይቀረዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በትክክል የተከሰተውን ነገር በመመርመር ከከተቡልን ሊሂቃን መካከል አንዱ ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847-1983 በገጽ 14 ላይ ምርምራቸውን ከአይን እማኙ እንግሊዛዊው ፕላውዲን ጋር አመሳክረው እንዲህ አስቀምጠውታል፡- ‹‹ገበሬው ለባለ ጉልቱ እህል ከመስፈር አልፎ ሁዳድ በማረስ፤ እህል በመፍጨት፤ ቤትና ጎተራ በመስራት የጉልበት ሥር እንዲያበርክት ይገደድ ነበር። ይህ የጉልበት ሥራም ካለው ጠቅላላ የስራ ጊዜ ከሶስት አንድ እጁን ይወስድበት ነበር።›› ፕላውዲን የተባለው የእንግሊዝ ተጓዥ ቆንስል የገበሬውን ጣጣ እንዲህ አድርጎ ያብራራዋል፤ ‹‹ግብሩ ሥፍር ቁጥር የለው ከቀዬም ቀዬም ይለያል፤ ገበሬው ለራስ ዓሊ ወይም ለሌላ ታላቅ ሹም እህል ይሰፍራል፤ አንዳንዴም ግብሩን በገንዘብ ይከፍላል። አልፎ ተርፎም ለመንግስት ሁዳድ የእርሻ በሬ ይሰጣል። የአከባቢው ሹም አምሾ ወይም ሌላ መጠን እህል ያሰፍረዋል፣ ወታደሩንም በገበሬው ቤት ይመራል። የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደ በሬ፣ በግ፣ ፍየል፣ ቅቤ፣ ማርና ሌላም የሚያገኘው ከገበሬው ነው።… በሰበብ አስባቡም አስተዋጽዖ እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ። ለምሳሌ ወይ ሹሙ ዘመቻ መሄዱ ይሆናል፤ ውይ መመለሱ፤ ወይ ፈረሱ ጠፍቶበት ይሆናል፤ ወይ ትዳር መስርቶ… ወይ ያለ የሌለ ሀብቱ በጦርነት ወድሞ›› (Plowden፤ 137-138)፤ በገጽ 15 ላይ በዘመኑ ኢትዮጵያን ስለጎበኘው ማንስፊልድ ፓርኪንስ ይጠቅሳሉ፡- አንድ ገበሬ ትንሽ ቅቤ ደብቆ ስለተገኘ ሲቀልባቸው የቆዮት ወታደሮች ዘነዘና ላይ ጠፍረው በቁሙ በእሳት እንደ ጠበሱት ተርኮልናል።

ትጠበቅ የነበረች እለት ቀርባለች፤ ፈተና ተጠናቋል። ፕሮጀክቱን ሰርቶ ያጠናቀቀው ተማሪ ከፕሮጀክት፣ ፈተና፣ ትምህርት እፎይ ብሏል። የመመረቂያ ጽሑፉን ጨርሷል፤ አንዳዱ የት ተቀጥሮ እንደሚሰራ ይወያያል፤ ቤተሰቦቹን ለመቀበል ሽር ጉድ የሚለውም ብዙ ነው፤ ሁሉም በየፊናቸው በደስታ ጮቤ ይረግጣሉ። የገብረህይወት ልጅ ዶርም ውስጥ ጋደም ብሏል፤ ጓደኛው የሚጠራ ስልክ በእጁ ይዞ ከደጅ ወደ ዶርም ገባ፤ እየተንደረደረ ሄዶ ስልኩን ለሳቂታው ወዳጁ ሰጠው፤ የደወለችው የሸገሯ ልጅ ነች፤ ዛሬ ሊጨፈር ነው። ከልጅቷ ጋር በጥናት ሰበብ እየተገናኙ ረጅም ሰዓት ያባክናሉ፤ ተግባብተዋል። ወሬውን ጨርሶ ስልኩን ሲመልስለት፣ ‹‹ምን አለችህ?›› አለው – ስልክ አምጪው። አሁንም በጥያቄ አይን እያየው ነው። ሊመረቁ ስለሆነ የደስ ደስ ይቀመቀማል፤ ከዛም፣ ‹‹ወዳጄ ሰው የሚሰማው መስማት የሚፈልገውን ነው፤ ለምን እንደፈለግችኝ አላውቅም፤ እንግዲህ ጠርታኝ ነው።›› ብሎት በትከሻው የወዳጃነቱን ገፋ አድርጎት ወጣ።

“A spiraling dynamic can be observed; the more public discontent, the more Tigranysation of Ethiopian politics; the more other ethnic groups become discontent.” (ዶ/ር በላቸው ገብረወልድ፣ 2009፣ 88) ዶክተሩ ፖለቲካው በትግራውያን እጅ መሆን፣ የሌሎች የብሔር ቡድኖች የመገፋት ድምጾች… ብሶታቸውን በተራው ትግራውያን ላይ እንዳይገልጽ ያስፈራቸው ይመስላል። በሀገሪቱ ውስጥ የተለያየ አመለካከት እያራመዱ ያሉ ድርጅቶች በሽብርተኝነት ሳጥን ውስጥ የሚከተቱበት መርሆ፤ የጎለበተ ሀሳብ ወደ ዜጎች ጆሮ እንዳይደርስ ተግቶ የሚሰራበት መንገድ፤ የቁጣው መጀመሪያ ከወዴት እንደ ሆነ ለመገመት የከበደ ቢያደርገውም፣ ማለዳችን ግን እየበራ ሳይሆን የበለጠ እየከሰመ ለመሄዱ አብነት መጥቀስ አያሻውም።

ገብረአረጋይ ልጅቷ ባደረገችለት ነገር ልቦናው እጅጉን ተነክቷል፤ በትምህርቷ ትበረታ ዘንድ ላደረገላት እገዛ እንዲሁም ያለበትን ስቃይ ታውቃለችና (መልካም ለማድረግ ሰው መሆን በቂ ነው እንዲል) ሙሉ ልብስ ሳትነግረው አሰፍታ አምጥታ አስደነቀችው። አሁን ይሄን ልብስ በእናቱና በእህቱ ፊት ከጓደኞቹ ጋር በኩራት ለብሶ መቆም ይችላል። ቃላት ተሰብስበው ምንም ማለት አይቻላቸውም። የሀበሻ የወንድነት ኩራቱን ድህነት አላሽቆታል። ወደ ዶርም ተንደረደረ። ገብቷታል። ተሸሽጎ ይንሰቀሰቅ ዘንድ “ወንድ ጓዳ ገብቶ ነው የሚያለቅስ”። ሁለቱን ያስጠናቸው የነበሩትን ሴት ጓደኛሞች ምን ማለት እንዳለበት አያውቅም፤ እነዛን አምስት ዓመታት ያለነሱ ለመሻገር ከባድ ነበር። በተለይም የዚህችን ቀዘባ የሸገር ልጅ።

ዶ/ር መረራ ጉዲና በአንድ የጥናት ወረቀታቸው እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹The Shewan expansion and the resultant politico-economic consequences were far profound, far brutal far devastating in the south than in the north… in the south, it was the issue of mostly bringing in new lands and new peoples into the emerging empire state on unequal terms.” ዶ/ር ላጲሶ (1982፤ 155) በበኩላቸው፡- ‹‹የኢማም አህመድ… ጦርነት ያስከተለው ውጤት የኢትዮጵያ ታላቁ የህዝቦች ፍለሳና መወራረስ ሂደትና ዘመን ተጀመረ። ባጭሩ በዚህ የማዕከላዊው የአጼ መንግስት የበላይ ሥልጣንና ቁጥጥር በወደቀበት ዘመን በአንጻሩ በሥፍራ፣ በቋንቋ፣ በሀይማኖት፣ በባህል የኢትዮጵያ የአራቱ ኩሻዊ፣ ሴማዊ፣ ኦሞአዊና፣ ናይሎቲካዊ ነባርና ተዛማጅ ህዝቦች ታላቅ ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴና መወራረስ ተካሄደ።” ይህ እንግዲህ ወደ 16ኛው መ/ክ/ አጋማሽ ላይ የተከሰተ ነው። የሁለቱን ዶክተሮች ሀተታ መመርመሩ፣ የሀጎስን እና የቶሎሳን ሀልዮት ለማስተንተን፤ የነበረውን የህዝቦች ተራክቦ ለመረዳት፤ ብሎም በየዘመናቱ ውስጥ እነዚህን ምስኪኖች እንደ ኦሪት ፍየል ኃጥያቱን ተሸክመው ወደ በረሃ/አደባባይ የሚለቀቁበትን ምስጢር ማወቅ ያስችለናል።

ገብረአረጋይ በጓደኞቹ እገዛ ያችን ትደገም የምታሰኝ ቀን አሳለፈ። እናቱን ከእህቱ ጋር ጥቂት ነገሮችን ከፈጸመ በኃላ እንደሚከተላቸው አሳምኖ ወደ ዓብይ ዓዲ፣ መንዲ የገጠር ቀበሌ ሸኘ። በሸገር አደባባዮች ላይ ጋዜጣዎችን እያገላበጠ እጣው  ወደሚጥለው ለመውደቅ ሺኅ አቻዎቹን ተቀላቀለ፤ ከተቋሙ ሲወጣ ግን ከሶስት በላይ ነጥብ አስመዝግቧል። የሸገር ወዳጆቹ የሆድ ጥያቄውን በፈቀደ ሰዓት በቤታቸው መጥቶ እንዲያሟላ ፍቃዳቸው መሆኑን አበሰሩት። ተስፍ ያደረገው ዮንቨርስቲ በክረምት ወራት መጠለያ ሆኖት የነበረው፤ አሁን ግን ለተረኞቹ እንጂ ለእሱ ግን ቦታ አልነበረውም። እጣውን ከጋዜጣዎች እና ከማስታወቂያ ቦርዶች ላይ ይፈልግ ዘንድ ለዓመታት ያስተማረውን ፍሬውን ለሸገር ጎዳና አስረከበ።

‹‹ጃዋርያውያን›› የኦሮሞን ሀብት እየበዘበዙ በትላልቅ ተቋማት ክንዳቸውን ያበረቱ ‹‹ሀጎሳውያን›› አጋለጥን አሉ። መከላከያን፣ አየር መንገድን… አመላከቱን፤ ይሁን እንጂ የሀገሪቷን ሀብት እየጋጡ ያሉትን የወሎውን ጌታ ሼኅ ዘንግተውታል፣ የሀገሪቱን ለምለም መሬት የተቀራመቱትን የውጭ ባለሀብቶች ፈጽሞ ቸል ብለዋል፣ የነቶሎሳን ቋንቋ እያወሩ መሬቱን የነጠቁትን ኮካ ቶሎሳውያን ዘንግተዋል። በጀሞና በዳለቲ መሀል ላይ ያለውን ሰፊ መሬት በስማቸው አድርገው የድንጋይ ማምረቻ ተክለው፣ መብራት የነሱ ጎጆ ብቻ የዘለቀውን ቶሎሳውያን፣ በተፊኪና በሰበታ መሀል ያለውን መሬት ሸንሽነው ለገበሬው ሀያ በግ የማይገዛ ጥሪት ነፍገው ያስለቀቁትን የነቶሎሳን ቋንቋ የሚያወሩትን ቶሎሳውያን ፈጽሞ ረስተዋል፤ ሌላ ዓላማ ከሌለን፤ በእርግጥም ፍትህ በእያንዳንዱ ጎጆ ትዘልቅ ዘንድ ከሻትን ይህችስ ለምን አትነገርም?

የገብረህይወት ልጅ የሰው ፊት እያየ መንገላታቱን አሁንም ቀጥሏል። ኑሮ በጣም ከብዷል። ሸገር ያበቀለቻቸውንም ቢሆን እያባረረች ነው፣ ወገቧ ጎብጧልና፤ አይደለም አዳዲስ ምልምሎቿን ልትቀበል። ልጅ እያለ በተደጋጋሚ ራሱን ለማጥፋት ሞክሮ ያልተሳካለት ይህ ጉብል መራቡ ከሰዓታት ወደ ቀናት ከቀናት… ረሀብ ስንት ቀን ይፈጃል? እነዛን የሸገር ቀዘባዎች መራቅ ጀመረ። ጠዋት ይወጣል። ቀኑን ሙሉ የከተማውን ሰርጥ ሁሉ ሲያስስ ውሎ ይገባል።

ጥር 26 ማለዳ ረፍድ ላይ ቀበና ድልድይ ውስጥ አንድ ወጣት ውድቆ ተገኘ። ሰዎች ተጋግዘው ወደ ምኒሊክ ሆስፒታል አደረሱት፤ ሶስት ቀናትን ቆየ፤ እጁም እግሩም ተሰብሯል። የተሰካለትን ግልኮስ ነርሶቹ ሲመለሱ ተነቅሎ ያገኙታል። በርግጥም የገብረህይወት ልጅ ህይወት ጨልማበታለችና መኖርን አይሻም። ነርሶቹ ጠባቂ አብሮት እንዲቆይ አደረጉ። ግና አልሆነም ገና በማለዳው ህይወትን የተጸየፋት ወዳጃችን በሶስተኛው ቀን ጥር 29 የሰንበት ለሊት ይህችን ዓለም ራቃት።

ገብረ አረጋይ ገብረ ህይወት የመጀመሪያ ዲግሪውን በያዘ በስድስት ወር ከሀያ አምስት ቀኑ ሊያሸንፋ እየቻለ የተረታላትን ዓለም ራቃት። እሱ እንዲህ አለ፡- ‹‹ድልድዮ ጋር ስደርስ አዞረኝ፤ ሳላውቀው ወደኩኝ፤›› እኛ እንዲህ እንላለን፡- ‹‹ምናልባትም ለቀናት ባዶ የነበረው አንጀትህ ሰውነትህን መሸከም ከብዶታል… የተስፋህ መክሰም ሞትህን አስናፍቆሀል፤ አስተምሮ ያስመረቀህ መንግስትና ዮኒቨርስቲ ግዴታቸውን ቸል ብለው አምባገነኖቹን መሪዎች ለማስተናገድ ደፍ ቀና ሲሉ ምግብና መጠጥ ሲራጩ፤ አንተ ግን በባዶ ሆድህ በየአደባባዮ ተገትረህ ነገን ተስፍ ታደርግ እንደ ነበር ከቶ አንዘነጋውም። በየደቂቃው እና በየጊዜው በተሳከረ የፓሊሲና የሀልዮት ቅኝት ትውልዱ ድምጽ አልባ ሞት ይሞት ዘንድ በነርሱ ጥበብ አልባነት የፈረዱበትን የያዳዱን ወጣት ነፍስ አንዘነጋም፣ በበረሀ ላይ የወደቁትንም ጨምሮ፤ ሁሉም የእኛው ስለሆኑ።

(የገብረአረጋይ ታሪክ እውነተኛ ነው።)

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *