ተማም አባቡልጉ

 

የ1949ኙን የወንጀለኛ መቅጫ እና የ1952ቱን የፍትሐ-ብሔር ሕጎችን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ሕጎች የተቀዱት ወይም ሕጎቹን የማርቀቅ(legal drafting) ሥራም የተሠራው ከፈረንሳይ ወይም በፈረንሳዮች ነው። የፈረንሳይ የሕግ ምሑራንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ያስተምሩ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት እንደፈረንሳይ ሁሉ ኮንቲኔንታል ሎው የሚባለው የተፃፈ ሕግን የሚከተለውና ከአሜሪካ እና ከእንግሊዙ ኮመን ሎው ከሚባለው የተለየ ነው። የዛሬ አነሳሴ ስለዚህ ጉዳይ ለመፃፍ ሳይሆን፣ የፈረንሳይ የፍትሕ ሚኒስትር የነበሩት ወይዘሮ ስልጣን ከመልቀቃቸው ጋር በተያያዘ አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት ፈልጌ ነው በዚህ የተንደረደርኩት።

ሚኒስትሯ ለምን ስልጣናቸውን ለቀቁ? ሥልጣን ለቀው ለአዲሱ ተሿሚ አስረክበው ወደተራ ዜጋነት ሲቀየሩ ወደቤታቸው በብስክሌት የሄዱበት ሁኔታ ያሳደረብኝን ስሜት ለመግለፅ ብቻ ሳይሆን፤ መነሻውንና አንድምታውን ለማመልከት ነው።

ሥልጣን ምንድን ነው? ዜግነት፣ መርህ፣ ሕግና ሕሊናስ ምንድን ናቸው? ለምን ያስፈልጋሉ? እነዚህ ሁሉ የሕግ ፅንሠ-ሃሣቦች ናቸው፤ ወይም በሕግ የራሳቸው ትርጉም ያላቸው ሲሆኑ ስልጣን(Power) ማለት ስለሌላው ለመስራት አቅም ማግኘት (Empower መሆን) ማለት ሲሆን፤ ስልጣን (ወይም ስልጣንን ማግኘትና መጠቀም መቻል) ራስን በግል የመጥቀሚያና ራስንና የራሴ የሚሉትን (ቤተሰብ፣ ዘር ወይም አካባቢ) ብቻ ከሁሉም ነጥለው በተለይ የማበልፀጊያ መንገድና መሣሪያ አይደለም። ዜግነት በአንድ ሀገር ውስጥ ያለ ሕዝብ በአጠቃላይ (በእኩልነት) ከሀገሩና ከመንግስቱ ጋር ባለው ግንኙነት ያለው ቦታን ይመለከታል። መርህና ሕግ ደግሞ ስለሆነ ጉዳይ አሠራር ድርጊት ወይም ሁኔታ በዚያን ወቅት የተያዘን (የተደረሰበትን) አሠሪ ድምዳሜዎችን ይወክላሉ። ሕሊና ደግሞ ባለሙያው ስለራሱ ስለሠው ስለዓለምና ስለሙያው ምንነትና የርስበርስ ግንኙነት አንድምታ በሚመለከት በተግባር ካሳየው ድርጊት ሁኔታ(አኗኗር) አባባል(ውሳኔ) በመነሳት(በማየት) የሚታወቅ(ሊታወቅ የሚችልና የሚገባ) ምልከታ ሚዛን ምዘና አመዛዘንና መመዘን ነው። ምን ልክ መሆን(ያለመሆኑን) የሠው ልጅ የሚለይበትን በውስጡ የተቀመጠ መለኪያ አድርገው የሚቀበሉበትም አሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ሕሊና በውጭ የምናሳየውን ሃሣብ እና ድርጊት የሚመራና የሚቆጣጠር መሣሪያ(ነገር) ነው። እነዚህን በማየት ብቻ ነው የአድራጊውን ሕሊና-ቢስነት ወይም ባለሕሊናነት የምንወስነው።

የሠው ልጅ በሕይወቱ፣ በልጅነቱ ወይም ራሱን ማወቅን ከቻለበትአንስቶ በሌሎች አካላት፣ ቤተሰብ፣ አካባቢ ወዘተ. በሚደርስበት ጥቃት፣ መገለል፣ መጣል፣ ወዘተ. ምክንያት ለራሱና ለሌላው(ለዓለምና ለሌላው ሰው) ያለው ምልከታ እምነት ሊጣመም፣ ሊበላሽ ወይም ሁሉንም እንደሆነው በመቀበል መሠረት መሥራት እንዳይችል(የማይችል) ሊሆን ይችላል።የሰው ልጅ አብሮ የሚኖር በመሆኑ፣ ግንኙነቱን ከሚገዙ ሕጎች፣ ነገሮች፣ ወዘተ. መካከል ስለሆነ ሁሉም የተቀበለውንና የሚኖርበትን ባህል፣ ሃይማኖት፣ ሕግ፣ እምነት፣ አመለካከት በአዲሱ ሕፃን ውስጥ በማስገባት(በተግባር በማሳየት፣ በመንገር ወዘተ.)፣ ስለዚህና ስለራሱ የራሱን ሚዛን እንዲያበጅ የሚያደርግበቱ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዝ ሲሆን፤ ይህ ትክክል እንዲሆን የሚከለክል ሁኔታ ከተፈጠረ በማህበረሰቡና በሕፃኑ መካከል ግንኙነት ካልነበረ ወይም ግንኙነቱ የፍቅር ካልሆነና የፍቅር ሆኖ ካልቀጠለ ይህንን መሠረት ያደረገ የተዛባ ምልከታና ምዘና በልጁ ውስጥ ይፈጠራል። ይህ ሕሊና የሚባለው ራስንም በዚህም ሁሉንም ሚናና ቦታ ደልዳይ የሆነ አንዱ ራሱንና አጠቃላዩን ፈርጆ ዳኝቶ የሚያስፈፅምበት ፍርድቤት አድርገን ልንወስደው እንችላለን። የራሱንና የአጠቃላዩን ግንኙነት በሚጠቅሱ(በሚመለከቱ) ጉዳዮች ላይ በተለይም በአጠቃላይ የጋራ ጉዳይ ላይለራስ ሲቆርስ ለሌላው ከሚቆርሰው የተለየ(የበለጠ) እንዳያደርግ ለማስቻል አስተዳደግና ትምህርት (ሃይማኖት ባህል ወዘተ.) ወሳኙን ሚና(ድርሻ) ይኖራቸዋል።

በፍትሐዊ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብና አካባቢ ውስጥ ያላደገና አኗኗሩ ፍርሃትና ስጋትን የጫኑት ዜጋ ሌላውን አካባቢውን፣ ሰውን(ውጭውን) ለማየት፤ ውስጡና መነፅሩ የጠየሙ ከመሆኑ የተነሳ አጋድሎ ሊመለከት ይችላል። “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ”፣ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” በሚል መርህና አካሄድም ተጠቅሞ ያሻውን ማሳካት ስኬት አድርጎ ሊቀበል ይችላል። የእንዲህ ዓይነቱን ግለሰብ ባህርይና ስብዕና ማህበረሰቡ የመሞረድና ለሁሉም እንዲበቃ የማስቻል ዕድል በልጅነት ወቅት ቢያመልጠውም፤ መደበኛ ትምህርት ያንን የማስተካከል ሥራ ይከውናል የሚል ግምት በመኖሩ፤ እንደ ዳግማዊ ዕድልም ይወስዳል። ይህ ማህበረሰቡን ሸውዶ ያለፈ ባህርይ ትምህርቱንም ለመሸወድ የሚያስችለውን ያህል ሄዶ ከደነደነ፣ ግለሰቡን በትምህርት ቤት ውስጥ በማሳለፍ ትምህርትበሱ ውስጥ አልፎ የባህርይ ለውጥ ሳያስከትልበት፤ ሁሉንም ሸረካክቶ በግርድፍ እንዳይሆኑ አድርጎ በማበላሸት ለማስተካከል ይቅርና ችግሩን መለየት እንዳይቻል ሊያደርግ ይችላል። ለህብረተሰቡ ፍላጎትና ጥቅም ደንታ የሌለው ሆኖ ግን ያለው በማስመሰል ያለፈው ይህ አይነቱ ግለሰብ፣ በትምህርቱም የተባለውን መድገም በመቻሉ ከስሙ ጋር ተመሳስሎ ማደር ይጀምራል፤ አንዳርጋቸው ጽጌ ይህን ሁኔታ የደብተራ ትምህርት፣ ግለሰቡን የደብተራ ባሕርይ ያለው ብሎ ይገልጸዋል። ይህ የሁሉንም ለሁሉም መስጠት የማይቻለው ሰው ሲችል እያስፈራራና እያታለለ ካልሆነም እየፈራ (በአደርባይነት) የሁሉም ለሱ ብቻ እንዲሆን መስራትንና በዚያ መሠረት መኖርን ተገቢ መርህና የአኗኗር መንገድ አድርጎት ሊገኝ ይችላል። ቀጥሎም “ይዞ መገኘት” እያለ በመፎከር ፉገራን(ማታለልን፣ መስረቅን፣ ይሉኝታንና የጥፋተኝነት ስሜትን ማጫርን ወዘተ.) ከሁሉም ጋር ያለውን ግንኙነት የሚገዛ(ገዢ) ሕግ ሊያደርግም ይችላል።

ሕሊና ሚዛን ነው። ፍትሐዊነት የጠራ ሚዛን መኖርን (ሚዛንን፣ ማጥራትን እና በእኩልነት እንዲመዝን ማድረግን) (በዚህም) ለሁሉም የሚገባውን መስጠትን የሚመለከት፤ የአመዛዘን መርህ (የሚዛንአፈጣጠር ዘዴ) ወይም የአብሮነት ቋሚ መሠረት(መርህ) ነው። እንደ ሰው ታይቶ ያላደገ ወይም እሱም ያው ሰው መሆኑን በተግባር ያላወቀ ወይም ኃላ ላይም ያልተረዳ፤ ለሱ የሚገባውን ለመጠየቅም ያዳግተዋል። በቻለ ወይም የሁሉም የሆነ በእጁ ከገባ ደግሞ ለራሱ ብቻ ጠቅልሎ ከመጠቀም መታቀብ አይቻለውም፤ ራሱን መግዛት አይችልምና። ይህም የሚዛኑ መዛባት የፈጠረበት ጉድለት ሲሆን፤ ይህንን አኗኗር የጫነበትን ሸክም ትምህርትና ልምድም እንዳያስተካክለው ከልቡ ለመቀበል(ለማመን) ስለማይችል፤ጠጥሮ ሳይሆነው ይቀራል። ትምህርቷም የጭነት ማራገፊያ ሳይሆን፣ ራሱ ተጨማሪ ጭነት ይሆነዋል(ይሆንበታል።) ይህ ዓይነቱ ችግር ፈቺ ሳይሆን(ላይሆን) ራሱ ሌላ ችግር ወይም ችግር አወሳሳቢ መፍትሔ አፈላለጉን የሚዘበራርቅና መፍትሔውን የሚያርቅ ሆኖ ይወለዳል። ይህንን ዓይነቱን ሰው በችግር ፈቺነት ስንሾመው (ችግር ፈቺ ስናቸርገው) ችግሩ በይበልጥ ውስብስብ እየሆነ የሚመጣው ለዚህ ነው። ሀበሻ “በድንጋይ ላይ ውሃ ማፍሰስ” የሚለው ይህንን ዓይነቱን ትምህርትና ተሞክሮ ሲሆን፤ ግለሰቡን ደግሞ “አድሮ ቃሪያ”፣ “ከርሞ ጥጃ”፣ “ታጥቦ ጭቃ” በሚሉት እና በመሳሰሉት አባባሎች(ምሣሌዎች) ይገልፀዋል።

ከዚህ ውጭ (ተቃራኒ) የሆነና ከራሱና ከኅብረተሰቡ ጋር ተስማምቶ እና ሆኖ ያደገ፣ የታረቀ ግለሰብ ደግሞ ኀሊና ስለሚኖረው፤ ለራሱ የሚገባውን ይጠይቃል፣ ለሁሉም የሚገባውን፣ የሁሉም የሆነን፣ ለሁሉም ይሰጣል፤ ለብቻው (ለተወሰኑ ወገኖች የተለየ ጥቅም እና ዓላማ ለማዋል በሚል) ጠቅልሎ አይይዝም፤ አይወስድም፤ ያምናል፣ ይታመናል፤ ከተጠራጠረም አጣርቶ ይረዳል፣ ሀቁን(እውነቱን) ይደርስበታል፤ ያውቃል፣ ይገነዘባል። ለራሱም፣ ለሀገሩም፣ ለሕዝቡም፣ ለሰውም፣ ለሚያምነውም (ፈጣሪን ጨምሮ) ሁሉ ይታመናል። በተለይ በድርጊት የሚገለፀው ማንነቱ(ስብዕናው) ከዚህ ውጭ አይሆንም። ያመነውን(ያመነበትን)፣ ያደርጋል። ያላመነበትን፣ አላደርግም በማለት(ባለማድረግ) ያመነውን ብቻ ማድረግ መቻሉን (የሚያደርግ መሆኑን) ያፀናል፣ ያሳያል። ይህ ከራሱ፣ ከፈጣሪው፣ ከሰው፣ ከፍጡሩና ከዓለም ጋር የታረቀ ሰው ከሙያው(መርህዎች) ጋርም የታረቀና ለነሱም የታመነ ስለሚሆን፤ እነዚህን መርምሮና አረጋግጦ ለመያዝም ሆነ ከያዛቸው በኋላ ግን እንዲሆኑት በሥራ ላይ ከማዋል፤ ካልሆነም እንዲውሉ ከመጣር፤ ሲጣሱም ከመቃወም በስተቀር ከነዚያ ጣሺዎች ጋር ካለመተባበርና ጥሰቱን ለማስቆም ከመሥራት ውጭ በተቃራኒው ሥራ(ተግባር) ላይ ሊገኝ አይችልም።

በፈረንሳይ በሥልጣን ላይ ያለው ሶሻሊስት ፓርቲ በሽብርተኝነት ተከሰው የተፈረደባቸውን ዜጎች ዜግነት መግፈፍ የሚያስችልን ሕግ አዘጋጅቶ(አውጥቶ) ሥራ ላይ ማዋል ስለሚሻ፤ ያንን ለማዘጋጀት ይፈልጋል፣ ዜግነት በመግፈፍ ዜግነት የሌለው ማድረግ የተለመደ ባለመሆኑ፤ ዜግነታቸው የሚገፈፈው የፈረንሳይና የሌላ ሀገር ጥምር ዜግነትን የያዙ ሰዎች ናቸው፡፡ ይህ ነገር በሌሎች(ነጭ?) ፈረንሳዮች ላይ ተግባራዊ አይደረግም የሚል ጭምጭምታ አለ። “ሽብርተኛ በመሆን አጥፍተው ለመጥፋት ጭምር የቆረጡ ሠዎች ስለ ፈረንሳይ ዜግነታቸው መገፈፍ እምብዛም ደንታ ሊኖራቸው ስለማይችል፣ ይህ ሁኔታ የቀኝ አክራሪዎችን ስሜትና ትኩረት ለመሳብ የተደረገ የአጀንዳ ነጠቃ ነው” ያሉም አልጠፉም።

ያም ሆነ ይህ ግን ይህንን ሕግ የማርቀቅ ኃላፊነት ያለባቸው የፈረንሳይ የፍትሕ ሚኒስትር የሆኑት ሰው ይህንን ሕግ እንዲሆን የተፈለገውን የፓርቲያቸውን ፖሊሲ አላምንበትም፣ ሕገ-መንግስቱን(መርህን) እና እምነቴን፣ አስተሳሰቤን እና ኅሊናዬ የሚያምንበትን ይቃረናልና(ይጥሳልና) ለነዚህ ሁሉ መታመን ደግሞ ግዴታዬ ነው አሉ። የምቀረው ከራሴ ጋር ነው በሚል የደረቡትን ሥልጣን ትተው አውልቀው፣ ለሌላ በመስጠት ካፖርታቸውን ደርበው በብስክሌት ወደቤታቸው ሄዱ። እኚህ አንድ የምናውቃቸው ኢትዮጵያዊ እናት የሚመስሉ ትልቅ ሴት በርግጥም ሰው፣ እናት፣ ባለሙያ መሆናቸውን ለሁሉም ያረጋገጡ ኅሊና ያለው ሰው(ስብዕና) ምሣሌ ሊሆኑ(ሊደረጉም) የሚችሉ ናቸው። አምነው ያመኑበትን በመሆንና በማድረግ ነገን መፍጠር መሆኑን አሳይተውናል።

ከዚህ ውጭ ያለው ሁሉ ሞት መሆኑን ደግሞ ከኛ በላይ ማን ያውቃል? ሰው ሥልጣን፣ ሥልጣንም ማንነት አይደለም። የሁለቱ ምንነት እንደዱባና ቅል አበቃቀል ለየቅል ናቸው። ስልጣንኃላፊነትና ስለሌላው ጥቅም የምንሸከመው ዕዳ ነው። ይህንን ያውቃሉ፤ ከዚህ በላይ ስልጣን ከየት ይመጣል? ከዚህ በላይ ራስን ማሸነፍን የሚያሳይ ድርጊትና ራስን ከማሸነፍ የሚልቅ ችሎታስ ምንድን ነው? (ከወዴትስ ይገኛል?) ሰውን(ሀገርን) ከመውደድና ለመርህ ከመታመን የሚበልጥስ ጥበብ ይኖር ይሆን? ከሚኒስትርነት ወርደው በብስክሌት ወደቤት ከመሄድ በላይ ባላገርነትን(የሀገር ባለቤትነትን) ሊያሳይ የሚችል ምንም ነገር(ማሳያና ማረጋገጫ) የለም።“ሰውነትንም(የሆነውን እንዳለ ወስዶ(ተቀብሎ) መገኘትን) ከዚህ በተሻለ ነጋሪ አይኖርም።‹‹ማሸነፍ ሆድን ነው ብሏል ትጉህ አሣማ›› ይላሉጸጋዬ ገብረመድኅን።

የሁሉንም ትክክለኛ ትርጉም(ጥቅምና ግልጋሎት) የተረዱና ሥልጣን ለሌላ(ለአጠቃላዩ) ማገልገል(ለሁሉም ጥቅም ማሳኪያነት የሚገለገሉበት መሣሪያ) እንጂ፤ ለራስ ስብዕና ማዳበሪያነት የሚደርቡት ጋቢ የሚከናነቡት ማንነት ፈጣሪ ያለመሆኑን የተገነዘቡት እኚህ ሴት፣ ለተገቢው ዓላማ በተገቢው ሁኔታ ላውለው አልችልም ብለው ባመኑ ጊዜ ያለምንም ማንገራገር በሙሉ ፍቃዳቸው ውልቅ አድርገው ለሌላ አስረክበው ወደቤታቸው ሳይሸማቀቁ የሄዱት፤ ሥልጣን እኔን ነው ብለው ባለማመናቸው ነው። የእነ ሞንቴሲኩ፣ ሩስ፣ ቮልቴር፣ አልበርት ካሙ፣ ቪክቶሪ ሁጎ፣ዣንፓል ሳትሬ(Sartre) ሀገር በብዙ መልኩ በሁሉም የዕውቀትና የጥበብ ዘርፍ ከሁሉም የላቁ የአፍሪካ ምድር ዝርያ ያላቸው አዋቂዎች፣ ባለሙያዎችና ጠቢቦች እንዳሏት እንሰማ ነበር።

የፈረንሳይን ሕገ-መንግስትና ሕግ አስመልክቶ ደግሞ የፍትህ ሚኒስትሯ ይህንን ሲባል እንሠማ የነበረውን እውነት በዓይናችን አሳዩን። “ሽብርን ጨምሮ ለየትኛውም የወንጀል ወይም የሌላ ችግር በመርህ በመመራት እንጂ፤ መርህን በመጣስ መፍትሔ ማምጣት አይቻልም። ዜግነት እኩልነት ነውና ሕግን የጣሰ(ዜጋ) በሕግ ይቀጣል እንጂ፤ እኩልነቱ(ዜግነቱ) አይገፈፍም፤ የፈረንሳይ መሠረቷ እኩልነት፣ ነፃነትና ወንድማማችነት ስለሆነ፣ ከነዚህ መሠረቶቿ አንዱ የሆነውን የእኩልነትን የመሠረት ድንጋይ በማንሳት(በመቀነስ) ሀገሪቷ እድትንጋደድ(እንድታንጋድድ) ለሚደረገው ተግባር በፍፁም አልተባበርም” ብለዋል። ይህንን ያሉት በተግባር ነው። የፓርቲዬ ጥቅምና ፍላጎት ከሙያዬ መርህ እና ከራሴ ኅሊና አይበልጥም ብለው አልተቀበሉትም እንጂ፤ ለየቱም ምክንያት ሲሉ አልተቀበሉትም። እንደኛ ሀገር የሕግ ባለሙያ ተብዬዎች፣ የፓርቲን አሠራር ለክሽፈታቸው ምክንያት በማድረግ አልተጠቀሙም።

የኚህ ትልቅ ሰው ተግባር የሕግን ትምህርት ለብዙ ዓመታት ከማጥናት የላቀ ሞራላዊ ፋይዳ አለው። ሕጎቻችንን ከፈረንሳይ ቀድተን(ያንኑ) ተምረንና በዚያ የሠለጠነ ባለሙያ ሆነን የሠውን(የዜጋን) መብት፣ ነፃነትና እኩልነት ካድሬዎች ሊጥሱ ስለሚችሉባቸው ሕግ የምናማክር፤ ይህንንና ዋስትና መከልከል የሚያስችሉ አዋጆችን፣ ውልንና ይርጋ የሚያስቀሩ ደንቦንችንረቂቅ የምናዘጋጅ ሰዎች፤ ይህንን ሁኔታ(ድርጊት) ስናይ ምን ተሰምቶን ይሆን? በፈረንሳይና በኛ መካከል ያለውን ልዩነት አትገነዘብም እንዴ!?” ትሉኝ ይሆናል። መልሴ፣ ‹አዎ፣ አልገነዘብም› የሚል ነው። ከላይ እንዳልኩት፣ የሙያችን(የትምህርቱ) መመሳሰል ስላለ ብቻ ሳይሆን፣ የናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ በቂ ምክንያት አይሆንምና ብቻ ሳይሆን፤ እኚህ ጥቁር ፈረንሳዊት የሕግ ባለሙያ ሚኒስትር ስልጣንና ስልጣኑ የሰጣቸውን ሁሉ መልሰው የግላቸው ንብረት በሆነች ብስክሌት ከኅሊናቸውና ሙያቸው ክብር ጋር ወደቤታቸው የገቡበትን መንገድ(ሁኔታ) ያየ የሕግ ባለሙያ ሁሉ፣ አካፋን አካፋ ብሎ ጠርቶ በመጥራት(ለመጥራት) አንገቱን ቀና አድርጎ አደባባይ ይወጣ እንጂ፣ ‹‹ቢሆንም›› ብሎ ጭንቅላቱን አሸዋ ውስጥ ለመቅበር ይሠራል ብዬ አልጠብቅምና ነው። ቴዎድሮስ ካሣሁን “አንገት ከሚሰበር ባይበላስ ቢቀር” ብሎ የለ!?

የፍርድ ቤት የዕግድ ትዕዛዝ እንዲጣሱ የሚፈቅዱ(ለምሣሌ ጅሃዳዊ ሀረካት የተባለ ፊልም በኢቲቪ የተላለፈው በዚህ መልኩ ነው)።የሁከት ይወገድልኝ ክስን ፍርድቤቶች እንዳያዩ የሚፈቅድ ደንብ አርቅቃችሁ በማቀረብ፣ የአ.አ. ከተማና የኦሮሚያ ነገር ነዋሪው ለውጭ ወራሪ መሬቱን በቀላሉ እንዲያስረክብ እጅ ወደላይ ብሎ በቀላሉ እንዲነጠቅ ያደረጋችሁ የሕግ ባለሙያ ተብዬዎች) ይህ ክቡር ሙያ ከቁስ ሰቀቀን ለመላቀቅ ወይም የከባድ ዘረኝነትን ሐራራ ከመወጣት ለላቀ ፋይዳ ሊውል መቻሉን ከኚህ ፈረንሳያዊ ልትረዱ ይገባል።

መቼም ኅሊናን አይዋሱትም፤ ከጫካ የመጣ ሰው ኅሊናው የታወረ ቢሆን፣ እምብዛም አይገርምም፡፡ እዚሁ ከኛ(ከሕዝቡ) መሀል ወጥተው ሸውራራ ኅሊና የያዙትን ወገኖ መመልከት ግን ግራ ያጋባል።ስለሆነም በተለያዩ ቁሳዊ፣ ስነ-ልቡናዊ፣ ስሜታዊ ምክንያቶች በመገፋት፤ ሳይማር ያስተማራችሁን ክቡሩን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕግ ከለላ በማሳጣት ወደማስጠቃት የፀረ-ሕዝብነት ደረጃ ዝቅ ያላችሁ የሕግ ባለሙያ ተብዬ ጓዶቻችንና ጓደኞቻችን፣ ከዚህች ደቂቃ ጀምሮ የበደላችሁትን ሕዝብ በምንና እንዴት እንደምትክሱት ማሰላሰል፣ ያንን መፈፀም መጀመር ይኖርባችኋል።

የኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒቴር ግን የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ የሎሚ መፅሔት ሕግ አማካሪ በመሆኑና በሕግ ባለሙያነቱ ከአንባቢ ለቀረበለት የሕግ ጥያቄዎች በሰጠው መልስ፤ የሀገሪቷን ሕገ-መንግስት ጥሶ ስለወጣው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 በሰጠው ትንተና፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግስት ያወጣውን(ኢ-ሕገ-መንግስታዊ የሆነን) ሕግ እንዳይቀበል አድርጓል የሚል የዲሲፕሊን ክስ አቅርቦበታል። ለዚህ ክስ በሰጠው መልስ፣ ‹‹ሕገ-መንግስቱን የሚጥሱ ሕጎችን ለይታችሁ ማሻር የናንተ(የፍትሕ ሚኒስቴር) ሥራና ኃላፊነት ነበር። እኔ ያለክፍያ የሠራሁት የናንተን ሥራ በመሆኑለዚህ ልትሸልሙኝ ሲገባ እንዴት ትከሱኛላችሁ? ነገር ግን የክሱ እንደምታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢትዮጵያ መንግስት ይልቅ ኢትዮጵያዊውን ተማም አባቡልጉ ይሠማል፣ የሚለውን ያምናልበሚል የመንግስት አካል ነኝ በሚል አካል የተሰጠ ማረጋገጫ ስለሆነ እንደክስ ሳይሆን እንደሽልማት እወስደዋለሁ›› የሚሉ ይገኙበታል።

ዋናው ነገር ግን የፈረንሳይ የፍትሕ ሚኒስትር በፓሪስ ላይ የሽብር አደጋ ደርሶ ከ140 በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተው እያለ ጭምር ይህንን በመከላከል ስም የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብት የሚነካ አዋጅ አላረቅም በሚል ስልጣን ይለቃሉ። የኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር ሕገ-መንግስቱን በመጣስ በሀገሪቷ ላይ የደረሰ የሽብር አደጋ ሳይኖር (በሚቀጥለው የምርጫ ዓመት ስለነበረ የወጣ ነው) ስለወጣ አዋጅ ኢ-ሕገ-መንግስታዊ ማብራሪያ የሰጠ አንድ ምስኪን ጠበቃ በዲሲፕሊን ይከሰሳል፤ በዚህም ምስኪኑ ራሱ መሆኑን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያረጋግጣል። ለተወሰኑ ወገኖች ልዩ ጥቅም መጠበቅ እንጂ፤ ለሕዝብ ጥቅም ላልቆመ አካል መሸለም ውርደት ሲሆን፣ መከሰስ ደግሞ ክብር ነው ብዬ አምናለሁ።

ስለሆነው ሁሉ የፈረንሳይ የፍትሕ ሚኒስትር የነበሩትን ክብርትክርስቲያን ቶቤራን እናመሰግናለን!

 

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *