አብርሃም ፍቃደ

ከለሊቱ ስድስት ሰዓት አካባቢ ከመንገድ ማዶ የሚሰማው ድምጽ ክፍሌን ሞልቶታል። የምሰማውን ድምጽ እየታገልኩ ከሁለት ሰዓታት በኋላ ተኛሁ። ሲነጋጋ ከሁለት የተለያዩ ተቋማት የሚመጣ አስገምጋሚ ድምጽ አነቃኝ። የነዚህን ሦስት የተለያዩ የእምነት ተቋማት ጥሪ ሳስብ ማታ በሬድዮ ያዳመጥኩትን ጉዳይ ማመንዠክ ጀመርኩ።

 

ማርታ ትባላለች። እናቷ ልጅ ሳለች ነበር የሞተችባት። ያደገችውም አጎቷ ቤት ነው። የአጎቷ ሚስት ከአንድ ግለሰብ ምንዱባን በማግኘቷ በአስራ አራት ዓመቷ የአርባ ሁለት ዓመት ጎልማሳ እንድታገባ አስገደደቻት። ወደትዳር ፈተናዎችም ያለፍላጎቷ ያለ ዕድሜዋ ተጣለች። የገባችበት ተቋም የትዳር ተጋሪ ኢትዮጵያዊው ጎልማሳ ባልም በትዳር አልጋው ላይ ሌላ ሴት እያመጣ መዳራት ጀመረ። አሸማጋዮችም መፍትሔ ማግኘት አልቻሉም። ከትዳሯ ሁለት ሴት ልጆችን አፍርታለች። የባል ግፍ ሲበዛ ተፋታች። ባልም በፍርድ ቤት የመጀመሪያ ልጇን ማንነት ካደ። ሁለተኛዋ ልጅ እርሱን በመምሰሏ ምክንያት ሊክድ አልተቻለውም። ዳኛውም የቧሏን እንጂ የሷን ቃል በደንብ ለማዳመጥ ፍቃደኛ አልነበረም። ሁለት ልጆቿንም ገጠር ላከቻቸው። ሆቴል ቤት በአልጋ አንጣፊነት ተቀጠረች። የሚከፍሏት የሶስት መቶ ብር ደሞዝ ሊበቃት አልቻለም። ይህንን ጉዳይ የተረዱላት ሴተኛ አዳሪዎች እንድትቀላቀላቸው ገፋፏት። ወደሴተኛ አዳሪነትም ኑሮ ገፍቷት ገባች። በወር ለልጆቿ እና ለአባቷ ልጆች ተቆራጭ ትልካለች። ዕድሜዋ በዚህ ሰዓት ሃያ አንድ ዓመት ደርሷል። በዚህ ስራ ውስጥ ብዙ የወንድ ልጅ ፈተናዎች ተፈራርቀውባታል። በምትሰራበት ሆቴል አምስት ደቂቃ ብታረፍድ መቶ አምሳ ብር ትቀጣለች።

 

ስራውን ሰርተው ከሚያገኙት ገንዘብ በስተቀር ሁሉም ሴተኛ አዳሪዎች ደሞዝ አይታሰብላቸውም። ነገርግን አንድ ቀን ከቀሩ ሁለት መቶ ብር ቅጣት ይጣልባቸዋል። ባለታሪኳ ማርታም በወር አበባ ምክንያት ለአምስት ቀን ብትቀር አንድ ሺ ብር ተቀጥታለች። ይህንን ታሪክ የሰማሁት ከሰዓት ዕላፊ ፕሮግራም ላይ ከባለታሪኳ ማርታ ነው።

 

ማርታን በአስራ አራት ዓመቷ እንድታገባ ያስገደደቻት የአጎት ሚስት ብቻ አይደለችም። ይህ ድርጊት እውን ሲሆን ዓለም ከእነዚህ ሦስት ግለሰቦች ውጪ ምድረ በዳ አልነበረችም። ነገር ግን በማኅበረሰባችን ውስጥ የምንአገባኝ መንፈስ የተደላደለ በመሆኑ ተፈጥሮ ባህሪዋን እንድትቀይር ተገዳለች። ብዙ ሰው ይርመሰመስ ይሆናል፤ ለማርታና መሰሎቿ ግን ቦታ የለንም ወይንም ይህ ሁሉ ምድር ሰው ያልበቀለበት ጠፍ መሬት ነው። ከዚህ ይልቅ ማኅበረሰቡ የስድብና የውርደት ዱቄቱን እየፈጨ ይበትንባቸዋል። እድሜዋ ለጋብቻ ያልደረሰችን ልጅ ማግባት ወንጀል ቢሆንም በውልና ማስረጃ ወቅት ድርጊቱ በህጋዊነቱ ፍቱን የሌለው ጋብቻ እንዲሆን ይደረጋል። የሙስና እግሮች እንኳን የማርታን በደል አይደለም ሀገርን የሚያህል ግዙፍ ነገር ሲያስጨንቁ እየታዘብን ነው። ጎልማሳው ባልም ባለው ብር ተመክቶ ከህግ በላይ ሆኖ ማርታን የራሱ ካደረጋት በኋላ በቂ ነው ብሎ መቀመጥን አይሻም። የከፍታ ማማ ላይ መውጣት ይፈልጋል። ለምን? ብር አለው። ብር ካለው ከህግ በታች ሳይሆን ከህግ በላይ ነው። ማኅበረሰቡ ደግሞ አሞጋሹ ነው። ‹‹እንዴ አደገኛ ነው። አንዲት ፍሬ ልጅ አምጥቶ ነው ያገባው። ምን ጉድጓድ ገብቶ እንዳመጣት እኔጃ። ብቻ ምን አለፋህ የዘመኑ ሰው ነው። ጎበዝ ሰው ነው›› እያልን እንቀኝለታለን።

 

በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ ሃያ አምስት ላይ ስለእኩልነት መብት በተደነገገው ስር ‹‹ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው። በመካከላቸውም ማንኛውም አድልዖ ሳይደረግ በህግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል። በዚህ ረገድ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሃብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የህግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው›› ይላል። ‹‹ታዲያ ማርታን ከዚህ ህግ ጋር ምን አገናኛት?›› ብለን ልናስብ እንችላለን። ጎልማሳው ባል ፍርድ ቤት ሳለ በትዳር ውስጥ ያፈሯትን የመጀመሪያ ሴት ልጅ ‹‹የኔ አይደለችም›› ብሎ ሲክድ ‹‹አዎ ያንተ አይደለችም። ሁለተኛዋ ግን አንተን ስለምትመስል በየወሩ ተቆራጭ ቁረጥ›› ተባለ። እናም በሃብት አድሎዖ ተደረገባት። የሙስና እግሮች ድጋሚ ረገጧት።

 

ሰው በአንድም በሌላም መንገድ የግለሰቦች የክፋት መረብ ውስጥ ይወድቃል። በቀደመው ጊዜ የክፋት መረባችንን በጉያችንን ሸሽገን የክት የምንለው ቀን ሲመጣ ብቻ ነበር የምንገለገልበት። ከሚሊኒየሙ ወዲህ ግን አዘቦት የለ ሰንበት፣ የክፋት መረቡን የሚዘረጋው በርክቷል። ወይንም የክፋት ዕድገቱ ከሁለት አሃዝ በላይ ሆኗል። ‹‹ክፉ ድርጊት ብፈጽም ሰው ምን ይለኛል?›› እያልን የምንኮራበት የይሉኝታ ምሰሶ ወድቆ እንደቀረው የአክሱም ሐውልት መሬት ተከስክሷል። ከዚህ ይልቅ በርካሽ ድርጊታቸው የሚታወቁ ግለሰቦችን የፈጣንነትና የቀልጣፋነት አክሊል እንደፋላቸዋለን። ‹‹ቢዝነስ ማይንድ›› አላቸው እያልን እናዳንቃለን።

 

የአዲስ አበባው የሆቴል ከበርቴ ስለያዘው ሞዴል መኪና፣ የት እንደገዛው፣ የትኛው ካምፓኒ እንዳስመጣው፣ በኪሎ ሜትር ምን ያህል ነዳጅ እንደሚበላ፣ ቦታውን የጠቆመው ደላላ፣ ከእንደገና ስለደላላው የህይወት ታሪክ …የመሳሰሉትን ማውራት በከበበን ሰው ዘንድ ልዩ የሆነ ሙገሳ ያተርፍልናል። መንግስትም የልማታዊ ባለሃብት ካባ ይደርብለታል። ይህ ሲጨመር ደግሞ ሙቀቱ የትየለሌ ነው። ከዚህ በኋላ ማርታን በፈጣሪ ቸርነት የሰራት ዕቃው ነች። ገንዘቡ ግን ክፉ የአጎት ሚስትና ክፉ ባል ከዘፈቋት አረንቋ ለመውጣት ከምትዳክረዋ ማርታና መሰሎቿ የተዘረፈ ነው።

 

በህገመንግስቱ አንቀጽ 18/3 ላይ ማንኛውም ሰው በባርነት ወይም በግዴታ አገልጋይነት ሊያዝ አይችልም። ‹‹ለማንኛውም አላማ በሰው የመነገድ ተግባር የተከለከለ ነው …›› ቢልም ንግዱ በመላው አዲስ አበባ ቀጥሏል። ማርታም ‹‹ሰው ስራ የሚሰራው ቀን ቀን ነው። ማታ ማታ ለምንድ ነው የምትሄጂው›› የሚሏትን የእምቦቃቅላዎቿን ሞጋች ጥያቄ ተሸክማ ከመነጠቅ የተረፈ ብሯን ይዛ ትገባለች። እናም አዕምሮው ያልተበረዘ ትውልድ ለመስራት ትዳክራለች። ከአዲስ አበባ ከፍ ካሉ ድምፆች መሐል የሐይማኖት ተቋማቱ ኮታ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።

 

እባካችሁ! ቤተ-ኃይማኖቶች ድምጻችሁ ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆን ለተከታዮቻችሁ ስር የያዘ ምግባርን ስበኩ። የነማርታን ፀሐይ የቀሙትን፣ በሞራላዊነት ላይና በምግባር ላይ ጦርነት ያወጁትን እኒህ ሦስት ግለሰቦችና የበዙትን የምግባር መሰሎቻቸውን ሰብዓዊነት መሞረድ ተስኗችሁ ከዶለዶሙ ባዶነታችሁን ነውና የምትጮሁት ተጠንቀቁ! ክፋት ህመም ነው፤ መልካምነት ግን ጤንነት።

 

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *