በፍቃዱ ኃይሉ

ጀግናው አትሌት ክቡር ዶ/ር ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ከቢቢሲ ጋዜጠኛው ቲም ፍራንክስ ጋር ባለፈው ሳምንት ያደረገው ቃለ-ምልልስ ብዙዎችን አስቆጥቷል። ኃይሌ የተናገረው ወደ አማርኛ ሲተረጎም፣ “እንደ አፍሪካዊ ዜጋ ዴሞክራሲ ቅንጦት ነው… በጣም አስፈላጊው ነገር መልካም መሪ ነው” የሚል ነው። ኃይሌ ይህንን ያለው ወደፊት (እ.ኤ.አ. በ2020) የኢትዮጵያ መሪ መሆን ይፈልግ እንደሆነ ሲጠየቅ ነው። ኃይሌ “ደስ ይለኛል” ነው ያለው። “ፕሬዚደንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ሚኒስትር መሆን ብችል ደስ ይለኛል፤ በ25 ዓመታት ውስጥ አውሮጳ፣ አሜሪካ፣ ኤዥያ… በዓለም አገራት እየዞርኩ ያየሁትን ልምድ ለአገሬ ማካፈል ብችል ደስ ይለኛል…” ነው ያለው።

ኃይሌ ኢትዮጵያ ለቢዝነስ ከማይመቹ የዓለም አገራት አንዷ መሆኗ ሲነገረውም፣ “አውቃለሁ፤ ነገር ግን እናትህ መጥፎ ባሕርይ ስላላት እናትነቷን አትክድም” በማለት ነበር ከነችግሯ በአገሩ ቢዝነስ እንደሚሠራ በዘወርዋራ መንገድ ለማስረዳት የሞከረው። እንግዲህ እነዚህን የቃለ-ምልልሱን ቁም-ነገሮች ነጥለን መመልከታችን ለምንሰጠው ትችት መሠረት ይጥላል ብለን እንገምታለን።

ኃይሌ ዴሞክራሲ ‹ለአፍሪካውያን ቅንጦት ነው› ብሎ ሲል ‹መሪዎቻችን ስለነፈጉን እንደ ቅንጦት ዕቃ ያምረናል እንጂ አናገኘውም› ማለቱ ይሁን፣ ‹ላለንበት ደረጃ አይገባንም› ማለቱ ግልጽ አይደለም። ብዙዎች በአስተያየቱ የተቆጡበትም ይሁን፣ ይሄ ጽሑፍ የተጻፈው ‹አሁን ላለንበት ደረጃ አይመጥነንም› ለማለት ፈልጎ ይሆናል በሚል እሳቤ ነው። የጽሑፉ ዓላማ ‹እውን ዴሞክራሲ ለአፍሪካውያን ቅንጦት ነው? መልካም መሪ ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ ስርዓት ውስጥ ሊበቅል (ቢበቅልስ ፀድቆ ሊቆም) ይችላልን?› ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ይሞክራል።

ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት የሚያስፈልገው ኃይሌ ገ/ሥላሴ አንድ አስተያየት ስለሰጠ ብቻ አይደለም። እርግጥ ኃይሌ ራሱን ችሎ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከመሆኑም ባሻገር ለወደፊቱ የፖለቲካ መሪ የመሆን ሕልም ስላለው ሐሳቡ ከዛሬው ተጠያቂ መሆን አለበት፤ እርሱም ይህንን እንዲረዳ ገና ከፖለቲከኝነት ትልሙ ማለዳ ላይ ሐሳቦቹን ከመናገሩ በፊት በቅጡ እንዲያጤናቸው ማስገደድ የዜግነት ኃላፊነታችን ነው። ነገር ግን ይህ ዓይነቱ አስተያየት ቋንቋውና አገላለጹ ይለይ እንጂ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከ አዛውንቱ ሮበርት ሙጋቤ ድረስ የሚንፀባረቅ አስተያየት ነው። አንዳንዴ አፍሪካውያን ለዴሞክራሲ አልተዘጋጁም ወይም ብቁ አይደሉም፣ አንዳንዴ አፍሪካውያን እንደ ምዕራባውያን ዓይነት ዴሞክራሲ አያስፈልጋቸውም የሚሉ አስተያየቶች ከዚህም ከዚያም ይፈልቃሉ። ይሄ ግን እውነት አይደለም።

በመጀመሪያ ደረጃ አፍሪካውያን እንደ ማንኛውም የሰው ዘር ሠላምና ብልጽግና የሚፈልጉ፤ ቢያገኙት የሚያምርባቸው ሕዝቦች መሆናቸው መታመን ይኖርበታል። መንግሥታቶቻቸው በእኔ አውቅልሃለሁ ፈሊጥ እርስበርስ እያባሏቸው እና በድኅነት አረንቋ ውስጥ እያዳከሯቸው ስላሉ አፍሪካውያን ከዓለም ሕዝብ ያነሰ ማዕረግ ያላቸው ንዑስ የሰው ዘር ሊሆኑ አይችሉም። በዚህ መግባቢያ ላይ ከደረስን ወደ ሌሎቹ ሐሳቦች መሻገር እንችላለን።

ዴሞክራሲ በአሁኑ ሰዐት ለአፍሪካውያን የሚያስፈልገንን ያክል፤ ለሌሎች ያስፈልጋቸው እንደሆን እጠረጥራለሁ። ነገር ግን ይህ ዓ/ነገር የኃይሌ አስተያየት ግልባጭ ሆኖ እንዲታይብኝ አልፈልግም። ለማለት የፈለግኩት፤ አፍሪካውያን ዴሞክራሲ ቢኖር፣ ሊቀረፍልን የሚችል ከየትኛውም አህጉር የበዙ ችግሮችን አዝለን የምንኖር ሕዝቦች ነን ነው። በዛሬ ጊዜ በሰብኣዊ ክብርና ፍትሕ እንዲሁም የግል ነጻነቶች እጦት የአፍሪካውያንን ያክል የሚማቅቅ ሕዝብ የለም። የአፍሪካ እስር ቤቶች በፖለቲካ እስረኞች የታጨቁ ናቸው፤ የአፍሪካ ባለሀብቶች ከብዙኃኑ ጉሮሮ በሕገ-ወጥ መንገድ ተዘርፎ በተከማቸ ገንዘብ ነው ቦርጫቸውን የሚያሳብጡት፤ ወዘተርፈ። ለአፍሪካውያን ዴሞክራሲ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የጊዜ ቀጠሮ ሳይያዝለት ሊዘረጋ የሚገባው ስርዓት የሚሆነው ለዚያ ነው። ዴሞክራሲ በዘገየ ቁጥር ብዙ የሚያብቡ ነፍሶችን በየእስር ቤቱ እናጣለን። ዴሞክራሲ በዘገየ ቁጥር የድኅነት አረንቋችን ውስጥ እየላቆጥን እንከርማለን። ያለዴሞክራሲ፣ ለሚጠፋው ጥፋት ተጠያቂ በሌለበት ስርዓት ውስጥ፣ እያንዳንዷ ቀን ለብዙ ግለሰቦችና ቤተሰቦች የመከራ ጊዜ ነች።

በአሁኑ ጊዜ፣ በአገራችን በፖለቲካዊ ጉዳዮች ብቻ (“ሽብር”፣ “አመፅ [ማነሳሳት]” እና “ጉባኤ ማወክ” በሚሉ ክሶች) ከሦስት መቶ በላይ ሰዎች ክስ ተመስርቶባቸው እና ተፈርዶባቸው፤ እንዲሁም ከዚያ በላይ የሆኑ ዜጎች ክስ ሳይመሰረትባቸው (በምርመራ ቀጠሮ ተይዘው) በየእስር ቤቱ እየማቀቁ ይገኛሉ። እነዚህ ዜጎች አምራች ዜጎች ናቸው። እነዚህ ዜጎች የሚያስተዳድሩት ቤተሰብ፣ የሚያሳድጉት ልጅ ያላቸው ናቸው። እነርሱ ላይ የሚደርሰውን የዕለት ተዕለት የሰብኣዊ መብት ጥሰት ማስቆም የሚችለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ነው። ለነዚህ ሰዎች ፍትሕ ማስገኘት የሚችለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ነው። ደርግ መጣ – ብዙ ነፍስ አስከፍሎ ሄደ፤ ኢሕአዴግም መጣ – ይሄዳል። እስከሚሄድ ግን ብዙ ነፍሶችን እያስከፈለ ነው። በ25 ዓመት ውስጥ ዓለም የዘገበውን የነፍስ ኪሳራ መመልከት ይቻላል። ነገር ግን ከዚያም በላይ እንደየትኛውም አምባገነን ያለበት የአፍሪካ አገር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖርም ከመሞት የከበደበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ዴሞክራሲ በሌለባት ኢትዮጵያ መኖር ጭራሹኑ ካለመኖር ይከብዳል። ለዚያ ነው ዛሬ ሕዝቡ ሁሉ ክንፍ ያወጣ የስደት ምኞት ያማለለው ሆኖ የምናየው። ይህንን ሐቅ መረዳት ብቻ ዴሞክራሲ ለእኛ አፍሪካውያን ቅንጦት እንዳልሆነ ይነግረናል።

ኃይሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ መሥራት አስቸጋሪ እንደሆነ ሲጠየቅ ትክክል መሆኑን ተስማምቷል። ብዙዎች ችግር ያለው በተሰማሩበት ዘርፍ ብቻ ይመስላቸዋል። ጠበቆች ሲጠየቁ ‹ትንሽ የፍትሕ ስርዓቱ ቢስተካከል ሌላው እኮ ጥሩ ነው› ይላሉ። መምህራን ሲጠየቁ ‹አብዛኛው ችግር እኮ ያለው የትምህርት ስርዓቱ ላይ ነው፤ ሌላው ቀስ በቀስ መስተካከል የሚችል ነው› ይላሉ። አንዳቸውም እነርሱ የተሰማሩበት ዘርፍ ላይ ያለው ችግር ሌላውም ላይ ይንፀባረቅ እንደሆን አይጠይቁም። ኃይሌ ገ/ሥላሴም እንደነዚሁ ነው። ብዙ ጊዜ ለጥያቄዎች በሚሰጠው መልስ ነገሮችን አቃልሎ የመመልከት ዝንባሌ አለበት። “በጣም አስፈላጊው ነገር መልካም መሪ ነው” ብሎ ሲል የዴሞክራሲ አለመኖር ለመልካም መሪ አለመኖር መንስኤ ሊሆን እንደሚችል የጠረጠረ አልመሰለኝም።

አንድ መሪ የቱንም ያክል መልካም ቢሆን፣ ብቻውን አገር መለወጥ አይችልም። በዚያ ላይ በዓለም ታሪክ እንደምንረዳው፣ መሪዎች ሁሉ ሲመጡ መልካም ዓላማ ይዘው እንደሆነ ነው፤ ቢያንስ እነርሱ የሚያስቡት እንደዚያ ነው። የሚለውጣቸው ወንበሩ ነው። ተጠያቂነት የሌለበት ስርዓት ነው የሚለውጣቸው። ብዙዎቹ የአፍሪካ አምባገነኖች መጀመሪያ ላይ የነጻነት ታጋዮች ነበሩ። የሊቢያው የቀድሞ አምባገነን መሪ ሙአመር ቃዳፊ ወደ ሥልጣን ሲወጡ ‹እያንዳንዱ ዜጋዬ የቤት ባለቤት ሳይሆን እኔ ከድንኳን ወጥቼ ቤተ-መንግሥት አልገባም› ያሉ የሕዝብ ወገን ነበሩ። መልካም መሪ የሚፈልቀው ከመልካም ስርዓት ነው። በዓለማችን ተፈትኖ ያለፈው መልካም ስርዓት ደግሞ ዴሞክራሲ ብቻ ነው።

ኃይሌ ገ/ሥላሴ ሰይፉ ፋንታሁን ሕዝባዊ ቁጣውን አስመልክቶ ላቀረበለት ጥያቄ በሬዲዮ ሲመልስ ‹በመልካም አስተዳደር እንደ ቻይና መሆን ይቻላል ባይ ነኝ› ብሏል። እንደ እውነቱ ከሆነ ቻይና ዓለምን የሚያስቀና የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ነው። ነገር ግን ቻይና በመልካም አስተዳደር አመርቂ ደረጃ ላይ ደርሳለች የሚል ድምዳሜ እውነታውን በቅጡ ያላገናዘበ ነው። ቻይና ዋነኛ ፈተናዋ ለምሳሌ ሙስና ነው። ሌላ የቻይናን ገመና የሚያሳይ ምሳሌ እንውሰድ። በቻይና በየቀኑ፣ በአማካይ 500 ‹ሕዝባዊ ተቃውሞዎቸ› ይካሄዳሉ። ተቃውሞዎቹ በታችኛው የአስተዳደር እርከን ውስጥ ባሉ የመንግሥት ተቋማት ባለመርካት የሚመነጩ ናቸው። ቻይና ተፈጥሯዊውን ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት በአፋኝነቷ የሚወዳደራት የለም። ሰዎች በፖለቲካ አስተሳሰባቸው እስር ቤት ከሚታገሩባቸው አገራት በግምባር ቀደምትነት የምትሰለፍ ነች። መሪዎቿም ሀጢያታቸውን ‹ይህንን ሁሉ የምናደርገው ራሳችንን ከምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት ለመጠበቅ እንዲሁም ባሕሎች እና ወጎቻችን በምዕራባውያን እንዳይበረዙ ነው› ይላሉ። እርግጥ የቻይናን ገመና የኢኮኖሚ ዕድገቷ ሸፍኖላታል እንጂ፣ የሕዝቦቿን አንጀት አርሶላታል የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ የሚያስችል ምንም እውነታ መሬት ላይ የለም።

ስለዚህም እላለሁ፤ በአትሌቲክስ የተከበርክ አትሌታችን ኃይሌ ሆይ፣ በፖለቲካዊ አስተያየቶችም እንድናከበርህ፣ እንዲሁም ድምፃችንን በምትፈልግ ጊዜ እንድንሰጥህ ‹የሚበጃችሁን አውቅላችኋለሁ› የሚሉትን የአፍሪካ መሪዎች አባባል አትከተል። በዚያ መንገድ እስከ ዛሬ መጥተን የትም አልደረስንም። ዴሞክራሲ የሕልውናችን መሠረት ነው፤ የቅንጦት አምሮታችን አይደለም።

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *