ተስፋዬ አ.
ተስፋዬ አ. tes983398@gmail.com

እንደ መነሻ
ከጥቂት ቀናት በፊት የደቡብ አፍሪካ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (SABC) በዜና ሰዓቱ በርካታ ሰዎችን ያሳተፈ እጅግ አስደንጋጭ የአንድ እናት ልጆችን ድብድብ ይዞ ለህዝብ ቀረበ፡፡ ይህ የወንድማማቾች ፀብ በእግር ኳስ አሊያም በቦክስ ግጥሚያ ሜዳ ወይም በምሽት ክበብ እንዳይመስላችሁ፤ የፀቡ ምክንያትም አደንዛዥ ዕፅ ወይም መጠጥ አይደለም፤ የፀቡ ተዋንያኖችም ዞምቢዎቹ ደቡብ አፍሪካውያን ወይም ደግሞ ሰዋዊ ሞራላቸው ጥያቄ ውስጥ እየወደቀ ያሉት ምዕራባውያን አይደሉም፡፡ የፀቡ ሜዳ ቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ ከመቅደሱ ላይ ነው፣ የፀቡ ተዋንያን የሆኑት ኢትዮጵያውያኖቹ ኦርቶዶክሳዊያን ናቸው፣ የፀባቸው ምክንያት ደግሞ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር እጦት ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው የቴሌቭዥን ጣቢያ ሪፖርተር ይህን ዘገባውን የጀመረው… “ቀውስ በአምልኮ ስፍራ፤ ዛሬ መቅደሱ ከገደብ ነጻ ነው”፡፡ በሚል ርዕስ ነበር፡፡
እነዚህን ምዕመናንን ስሜታዊ አድርጎ በመቅደሱ ላይ ቦክስ እንዲሰናዘሩ ያደረጋቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቤተክርሲቲያኒቱ የቀውስ ምንጭ እየሆነ ያለው የፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ነው፡፡ ይህ ልዩ ጽ/ቤት በተደጋጋሚ ሕገ ቤተክርስቲያንን ከመጣሱ በተጨማሪ ራሱ ሕገ ቤተክርስቲያን ልዩ ጽ/ቤቱን አሁን ባለው ሥልጣን እና በሚከውነው ተግባር አያውቀውም፡፡ ሕገ ቤተክርስቲያን እኔ የምመራበት የሥልጣን መዋቅር ብሎ ያስቀመጠው የስልጣን ተዋረድ በቅደም ተከተል እንደሚከተለው ነው፡፡ “…ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ፓትርያርክ፣ ቋሚ ሲኖዶስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ የሀገረ ስብከት ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና የአጥቢያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፡፡ /ሕገ ቤተክርስቲያን ገፅ 12/ ” በዚህ የሥልጣን ተዋረድ ውስጥ የፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የሚል የለም፡፡
የልዩ ጽ/ቤቱ ታሪካዊ ዳራ
የዚህ ክፍል ታሪክ የሚጀምረው ወይም ደግሞ አሁን ያለውን መጠሪያና ሕገ-ወጥ ስልጣን የያዘው በአምስተኛው ፓትርያርክ ዘመነ ፕትርክና ነው፡፡ የአምስተኛው ፓትርያርክ ከሕግ ውጭ ነጭ ልብስ መልበስ፣ ከሲኖዶስ እውቅና ውጭ ጳጳሳትን ከሀገረ ስብከታቸው ማፈናቀል፣ ለነባር ሥርአቶችና ደንቦች አለመገዛት ብሎም አዲስ ሥርአቶችን ለመደንገግ መሞከር እና ሌሎች ፓትርያርኩ ላይ ይታዩ የነበሩ የአፈንጋጭነትና የጠቅላይነት ባሕሪ ጠንካራ ተቃውሞን አስከትሎ ነበር፡፡ ይህ ተቃውሞ የፓትርያርክን ሳይሆን የቅዱስ ሲኖዶስን የበላይነት የሚያውጀውን ሕገ ቤተክርስቲያንን አጽንቶት ቢሄድም በአንጻሩ ደግሞ ሕገ ወጥ የሆነውን ልዩ ጽ/ቤት ተክሎብን ሄዷል፡፡ የወቅቱን ፓትርያርክ ሕገ ቤተክርስቲያን ከሕግ ውጭ አላንቀሳቅስ ሲላቸው ጽ/ቤታቸውና ጸሐፊያቸው ላይ ልዩ የሚል ቅጽልን በመጨመር ልዩ ጸሐፊንና ልዩ ጽ/ቤትን ወለዱ፡፡
እዚህ ክፍል ላይ ጥያቄ የሚነሳው “ልዩ ጸሐፊ” እና “ልዩ ጽ/ቤት” ከሚለው መጠሪያ ጀምሮ ነው፡፡ መጠሪያው ላይ ያለው “ልዩ” የሚለው ቅጽል በራሱ አፈንጋጭነትን ያሳያል፡፡ ልዩ የሚለው ለምን አስፈለገ? ከምንስ ነው የሚለየው? ጽ/ቤት እና ጸሐፊ የሚለውስ ብቻውን በቂ አይደለምን?
አንዳንዶች ልዩ የሚለው ቅጽል የጽ/ቤቱን ባሕሪ ያሳያል፣ ቤተክርስቲያኒቱንም በልዩነት እየመራት እንደሆነ ይናገራል፣ ለሕግና ለቅዱስ ሲኖዶስ ተገዢ አለመሆኑን በራሱ ላይ ይመሰክራል ይላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የሥልጣን መዋቅሩ ውስጥ የፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የሚል ባይኖርም ፓትርያርክ እስካለ ድረስ የክፍሉ መኖር የግድ ነው ይላሉ፡፡ እውነት ነው፣ ፓትርያርክ እንደ ተቋም ስለሚታይ ጽ/ቤት እና የጽ/ቤት ኃላፊ ያስፈልገዋል፤ ግን ልዩ ጸሐፊ እና ልዩ ጽ/ቤት አያስፈልገውም፡፡ ርግጥ ነው ፓትርያርክ ርዕሰ መንበር እንደ መሆኑ መጠን ደጋፊና ረዳት ያስፈልገዋል፤ ግን ከቅዱስ ሲኖዶስ በላይ አድራጊና ፈጣሪ መሆን የለበትም፤ ለሕገ ቤተክርስቲያንም ሆነ ለነባር ሥርአቶችና ደንቦች ተገዢ መሆን አለበት፡፡
የልዩ ጽ/ቤቱ ተግባር
የዚህ ክፍል ተግባር ጽ/ቤቱ እና ጸሐፊው ወደ ልዩ ጸሐፊ እና ልዩ ጸ/ቤት ከመቀየራቸው በፊት ሕገ ቤተክርስቲያን ለፓትርያርኩ የሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ከማስፈፀም፣ የፓትርያርኩን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከማቀላጠፍ በምክርና በሀሳብ ከማገዝ ውጭ ሌላ ተግባር አልነበረውም፡፡ ይህም የቤት ውስጥ አገልጋዮቻቸውን ከመቆጣጠር እስከ የውጭ ጉዳዮቻቸውን ማሳለጥ ድረስ ያሉትን ማለት ብቻ ነው፡፡
አሁን ላይ እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ በቤተክርሰቲያኒቱ ውስጥ ከቅዱስ ሲኖዶስ በላይ ወሳኝ አካል ሆኗል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱን በስውር መምራት ለሚፈልጉ አካላት ጥሩ መጠቀሚያ እየሆነ ይገኛል፤ የአለመረጋጋቶች መንስኤ፣ የብልሹ አሰራሮች ምክንያት፣ የቀውሶች ሁሉ ምንጭ የዚህ ልዩ ጽ/ቤት ሕገወጥ አሰራሮች እና ውሳኔዎቹ ናቸው፡፡
ከላይ በመነሻዬ ያነሳሁት የደቡብ አፍሪካ ጉዳይ እንዳላ ሆኖ የሀዋሳና የሌሎች የበርካታ አድባራት ምዕመናን በአስተዳዳር ጉዳዮች ላይ ባነሱትና በሚያነሱት የተቃውሞ ጥያቄዎች፣ በሃይማኖት ሕጸጽ ምዕመኑ ጥያቄ ለሚያነሳባቸው ግለሰቦችና ማኅበራት የተሰጡ የእውቅናና የድጋፍ ደብዳቤዎች፣ በሙስናና በሕገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ለሚገኙ የቤተክህነቱ ሰራተኞች ሽፋን በመሆን እና በሕግ እንዳይጠየቁ ከለላ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ይህ ሕግ የማያውቀው ሕገወጥ ክፍል እጁ አለበት፡፡
ከቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከጠቅላይ ቤተክህነትና ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች እውቅና ውጭ የተደረጉ የውጭ ሀገራት ጉዞዎች፣ የስራ ዝውውሮች ወይም ሹም ሽሮች፣ የሰራተኞች ስብሰባ፣ ደብዳቤዎች፣ ፍቃዶች እና ሌሎች ተዋረዳቸውን ያልጠበቁ የሥራ ሂደቶች የዚህ ክፍል የሥራ ፍሬዎች ናቸው፡፡ በጣም የሚገርመው ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ግብረ ሰዶማዊ ነው፣ ከመቅደላዊት ማርያም ጋር ጾታዊ ግንኙነት አለው›› የሚል እና ሌሎች እጅግ አስነዋሪ ሀሳቦችን የያዘ ፊልም በኢትዮጵያ ያውም በላሊበላ ይምርሐነ ክርስቶስ፣ በአሸተን ማርያም እና በጉንዳጉንዲ ሊሰራ የነበረው በልዩ ጽ/ቤቱ ፍቃድ መሆኑ ነው፡፡
በመጨረሻም
ዛሬ በአውቶቡስ ተሰብስቦ መጥቶ ፓትርያርኩ እግር ስር ተንበርክኮ ፍትህን ፍለጋ ማንባት አስቸጋሪ ሆኗል፣ ለቡራኬም ለአቤቱታም ፓትርያርኩን ከማግኘት ጠቅላይ ሚንስትሩን ማግኘት ይቀላል፤ የፓትርያርኩ ቢሮም ጆሮም በልዩ ጽ/ቤቱ አማካኝነት ለብጹአን ጳጳሳቱም ለምዕመኑም ባልተለመደ ሁኔታ ጥርቅም ተደርጎ ተዘግቷል፡፡ ዕድሉም ቢገኝ እንኳን በዚሁ ክፍል የተነሳ መፍትሄውም የተዛባ፣ የተንሸዋረረና ሕገወጥ ይሆናል፡፡ የልዩ ጽ/ቤቱን ድብቅ አጀንዳ እና ተልእኮ የሚያውቁት በዚህ መጠን ልክ የፈጠሩት አካላትና አስፈጻሚዎቻቸው እንዲሁም ራዕዮቻቸውን የሚያስቀጥሉት ተተኪዎቻቸው ቢሆኑም ተግባራቶቹን እና ፍሬዎቹን በማየት ግን መጻኢ እድሉን መተንበይ ለማንም ቀላል ነው፡፡ አሁን ላይ በዚህ ክፍል እየተፈጸሙ ላሉ ጉዳዮች ምዕመኑ እየሰጠ ያለው ግብረ መልስ ምዕመኑንና የቤተክህነቱን መሪዎች ያስተሳሰረው መንፈሳዊነት እየላላ መሄዱን ያሳያል፡፡ የልዩ ጽ/ቤቱ ሕገወጥ አካሄድ በዚሁ ከቀጠለ ምዕመኑ በጉዳዩ ላይ እጁን መክተቱ እና ከጸሎት ሌላ ነገሮችን በራሱ እይታና መንገድ ለመፍታት መጣጣሩ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ከዚያ በፊት ግን የፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የቤተክርስቲያኒቱ የቀውስ ምንጭ ከመሆን ይታቀብ፡፡
ከጽዮን ምሕረት ለኢትዮጵያ

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *