የትነበርክ ታደለ

 

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ (የቦሌ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት) የ‹‹ጊብሰን ዩዝ አካዳሚ››ን ማገዱን በቅርቡ ተዘግቦ ሰምተናል። እንደ ዘገባው ከሆነ ትምህርት ቤቱ የታገደው ህገ ወጥ ገንዘብ በመሰብሰብና ከመምህርነት ሙያ ውጪ ያሉ ሰዎችን ቀጥሮ በማሰራቱ ነው።

በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ ከአራት ዓመታት በላይ በመምህርነት እና በአስተዳዳሪነት እንደመስራቴም፤ የትምህርት ቢሮው ምክንያት ብሎ ላቀረባቸው ክሶች የራሴን ጥያቄዎች የማቅረብ ሙያዊ ኃላፊነት እንዳለብኝ ተሰምቶኛል። በየትኛውም የሙያ ዘርፍ ህገ ወጥ ገንዘብ መሰብሰብ ወንጀል ሲሆን ከሙያ አግባብ ውጪ ያለ ባለሙያ ቀጥሮ ኅብረተሰብን ለተሰናከለ አገልግሎት ማዋልም እንዲሁ ከሥነ-ምግባር ውጪ ነው።

ነገር ግን የትምህርት ቢሮው ለዚህ አይነት ጉዳይ አዲስ ነው እንዴ? መላ ከተማዋን ከራስ ጠጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ የወረሯት ‹‹ትምህርት ቤት›› ተብዬዎች እውነት በሰለጠኑ መምህራን ነው ወይ የተሞሉት?

እኔ ራሴ እንደታዘብኩት፣ በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ ከሚገኙ መምህራን መካከል በሙያው የሰለጠኑት አንድ ሶስተኛ እንኳ የሚሞሉ አይደሉም። አብዛኞቹ በሰለጠኑበት ሙያ ስራ ማግኘት ተስኗቸው ‹‹ልጆች ማስተማርማ አይከብድም›› ተብለው ያለምንም የኋላ ታሪክ ዘው ብለው ለገንዘብ ሲሉ የገቡበት ናቸው።

ከዚህ እጅግ የሚከፋው ደግሞ የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች በስጋና በአበልጅነት ዝምድና የሚሰበስቧቸው ሰዎች ናቸው። እነዚህ እንኳንስና የማስተማር ሙያ ሊኖራቸው ይቅርና ለራሳቸውም መሠረታዊ የተባለውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በአግባቡ ያልተወጡ ናቸው። ሀገሪቱ ከእነዚህ የምታተርፈውን ፍዳ መቼም ትውልድ ነው የሚቆጥረው።

ለዚህ ሁሉ ሰበቡ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚቆጠረው የመምህራን ፍልሰት ነው ሊባል ይችላል። በሙያውም በቂ የሚባል የተማረ የሰው ሀይል ማፍራት አለመቻሉም ወደ ኋላ ሊገፋ የማይችል ነገር ነው። ይህ ሁሉ ታሳቢ ሆኖ ግን የ‹‹ጊብሰን ዩዝ አካዳሚ››ን ክስ እዚህ ጋር ስናመጣው ጉዳዩ ትንሽ ለየት ይላል። ይህ ትምህርት ቤት ብዙ መምህራን፣ ትምህርት ቤቶች እና የትምህርት ቢሮው ከሚመሰክሩለት ጥንካሬው አንዱ መምህራንን በተከታታይ የማሰልጠን አቅሙና ተነሳሽነት ነው።

ከላይ በተጠቀሰውም ሆነ በሌላ ምክንያት፤ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሚቀጠሩ ሰዎች ለማስተማር ወደ ክፍል ከመግባታቸው በፊት ቢያንስ የ40 ቀናት ቀጥተኛና ተከታታይ ስልጠናዎች ይሰጣቸዋል። ስልጠናው የማስተማር ዘዴ (pedagogy) እና ሥነ-ልቦና (psychology) በዝርዝር እና በተግባር ሲሆን ይህም በጋራና በተናጠል የሚሰጥ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም በትምህርት ቤቱ ውስጥ የቆየ መምህርም ቢሆን በየሶስት ወሩ የትምህርት ማጠቃለያ በኋላ የክለሳ ስልጠናዎችን የመውሰድ ግዴታ አለበት። ዝርዝር የክፍል ውስጥ ግምገማና ክትትል የተሻለ ውጤት ማምጣት ደግሞ በትምህርት ቤት ውስጥ ለመቆየት ዋነኛው መመዘኛ ነው። የመምህራን ማንዋል (Teacher’s Hand book) በየጊዜው ማንበብና እዚያ ውስጥ የተጠቀሱ መልመጃዎችንም እንዲሁ መምህሩ እንዲሰራ ይገደዳል።

በዚህ መንገድ የሰለጠኑት መምህራን ዛሬ ለብዙ አዳዲስ የግል ትምህርት ቤቶች ዳይሬክተሮችና ዩኒት ሊደሮች ናቸው። እነዚህ መምህራን ናቸው ለብዙዎች አማካሪና ምርጥ መምህራን ተብለው እንደምሳሌ የሚጠቀሱት። [ይህንን የትምህርት ቢሮው አሳምሮ ያውቀዋል]

በነገራችን ላይ፣ እዚህ ትምህርት ቤት በቆየሁባቸው ዓመታት አንድም ቀን ከቢሮው ለግምገማ የመጣ ባለ ሙያ አይቼ አላውቅም። ምንም እንኳ ትምህርት ቤቱ በተማሪ ተኮር ትምህርት አሰጣጡ የሚወደስ ቢሆንም መምህራን የሚያነሷቸው በርካታ ጥያቄዎች ነበሩ – ከሙያም ከህግም አንጻር ሊደመጡ የሚገባቸው። ግን ምን ያደርጋል፣ የአንድ ሰሞን ሮሮ ሆነው ከማለፍ በስተቀር አንድም ቀን መፍትሄ ተበጅቶላቸው አያውቅም። ምክንያቱም ይህ የመንግስት ባለሥልጣናት ልጆቻቸውን ተሽቀዳድመው የሚያስመዘግቡበት ትምህርት ቤት አንድም ቀን የትምህርት ቢሮ ባለሥልጣናት ድርሽ ብለውበት አያውቁም።

እና ዛሬ ምን ሆድ አስባሳቸው? ዛሬ ምን ታያቸው? ‹‹ህገ ወጥ ገንዘብ መሰብሰብ›› የሚለው ክስ በደምብ ግልጽ ስላልሆነልኝ ብዙም ልዳስሰው አልችልም። ምናልባት ወላጆችን ከመጠን በላይ ዋጋ መጠየቅ የሚል ከሆነ ግን የምለው አለኝ።

አዲስ አበባ ውስጥ አንድ የተለመደ ነገር አለ። ይሄውም ‹‹ምናምን ኢንተርናሽናል›› የሚል ዘይቤ። ትምህርት ቤቶቹም ‹‹ኢንተርናሽናል›› ስለተባሉ ብቻ ሁለነገራቸውን ዓለማቀፍ ማድረግ ያምራቸዋል። ትምህርቱማ ሁሉም ያው ነው፡፡ ከአሜሪካ እና ከእንግሊዝ ያረጀ ካሪኩለም ፎቶ ኮፒ እያደረጉ በዚያ ይጫወታሉ። ወደ ፊት ሀገር በዚህ ማዘኗ አይቀርም!

ከዚያ ባስ የሚለው ደግሞ የክፍያው ነገር ነው። የወፍ ጎጆ የምታክል ትምህርት ቤት ከፍተው ‹‹ …ኢንተርናሽናል›› የሚል ትልቅ ታፔላ ይለጥፉና ክፍያው ሰማይ ጠቀስ ነው። ይግረማችሁና እነዚህ ትምህርት ቤቶች መምህራኑ በሙሉ ሀበሾች ሲሆኑ አብዛኞቹ ደግሞ ከ‹‹ጊብሰን ዩዝ አካዳሚ›› በጭማሪ ክፍያ የተዘዋወሩ ናቸው። እኔ በወቅቱ በነበረኝ መረጃ የ‹‹ጊብሰን ዩዝ አካዳሚ›› የአንድ ዓመት የትምህርት ክፍያ በብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች የግማሽ አመት ክፍያ ያህል ነው።

ለመሆኑ የትምህርት ቢሮው ዘንድሮ በጊብሰን ላይ ምን አየበት? ቢሮው ያቀረበው ክስ አሁን ባለው ነባራዊ የግል ትምሀርት ቤቶች ሁኔታ አሳማኝ አይመስልም። የተጠቀሱት ችግሮች ሁሉንም የሚያካትት ከሆነ እመኑኝ አዲስ አበባ ውስጥ አንድም ትምህርት ቤት የለም! ሁሉም ሊታገድ የሚገባው ነው። ይህ ክስ ደረጃ በደረጃ ይቅረብ ከተባለም ደግሞ ‹‹ጊብሰብ ዩዝ አካዳሚ››ን መጨረሻ ላይ እንጂ መጀመርያ ላይ ሊነካው አይችልም ነበር።

ጠቅለል ለማድረግ ያክል፣ ትምህርት ቢሮው በዚህ ትምህርት ቤት ላይ የጠቀሰውን ችግሮችና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለውሳኔ ያንደረደረውን ምክንያቶች ወደ ሌሎችም ቢያደርጋቸው ዜጎች ከዚህ ይጠቀማሉ። ነገሩ እንዲሁ የአንድ ሰሞን እሳት ማጥፊያ ብቻ ቢሆን ግን እንደለመድነው ታዝቦ ከማለፍ በዘለለ ምን ልናደርግ እንችላለን?!

አበቃሁ!

 

 

 

 

 

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *