ኤልያስ ገብሩ

ለአንዲት ሉዓላዊት ሀገር እጅግ ወሳኝ ከሆኑ ምሰሶዎች መካከል አንዱ ‹ዴሞክራሲ› ነው። ዴሞክራሲ በሒደት (በረዥም፣ መካከለኛ እና አጭር ጊዜ ውስጥ) የሰፈነባቸው ሀገራት እንዳሉ ሁሉ፤ ይሄው ‹ዴሞክራሲ› ጮራውን ፈንጥቆባቸው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የከሰመባቸውም፤ የፈነጠቀው የ‹ዴሞክራሲ› ብርሃን ወዲያው ከስሞ በድቅድቅ ጭልማ የተዋጡ ሀገራም አሉ። የዴሞክራሲ ብርሃንን ጨርሶ በዘመናቸው ያላዩም ሞልተዋል – በተለይ በእኛዋ አፍሪካ።

ከሰሞኑ፣ በረዥም ርቀት ሩጫ፣ የእኛና የተቀረውም ዓለም ጭምር ፈርጥ የሆነው፣ እጅግ በርካታ ውድድሮችን በአንደኝነት ከማሸነፍም በላይ፣ በተደጋጋሚ የረዥም ርቀት ክብረ-ወሰኖችን በመሰባበር መላውን ዓለም ያስደመመው የሀገራችን ወርቅ – ሻለቃ ኀይሌ ገ/ሥላሴ – በቢቢሲ ዓለም ዓቀፍ አገልግሎት (የራዲዮ) ፕሮግራም ላይ ቀርቦ፣ በእርሱ እይታ፣ ዴሞክራሲ ለአፍሪካ ቅንጦት እንደ ሆነ ተናግሮ ነበር። ይህም የኀይሌ ንግግር፣ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ከፍተኛ ትኩረት ስቦ፣ ትልቅ የመነጋጋሪያ አጀንዳም ሆኖ ነበር። አትሌቱም በርካታ ቁጥር ባላቸው ኢትዮጵያውያን ጠንካራ ነቀፋና ትችት ተሰንዝሮበታል። የተወሰኑትም ‹ኀይሌ እንዲህ እንዲያ ለማለት ፈልጎ ነው› እያሉ፣ ንግግሩን ለማለሳለስ፣ አንዳንዴም ለመደገፍ ዳድተው ታይተዋል። ንግግሩንም ጭራሽ እንደ እግዜር ቃል የቆጠሩም ነበሩ! ‹ኀይሌን አትንኩት!›፣ ‹ኀይሌ መነካት የለበትም!›፣ ‹ኀይሌ… › እያሉ፣ እንደ መፈክርም የቃጣቸውን ቃላት የሰነዘሩ ብዙ ነበሩ።

በኀይሌ አገላለጽ መበሳጨቴ አልቀረም፤ የበመሳጨትም፣ ያለመበሳጨትም ‹ምርጫ› የእኔ ጉዳይ ነው (ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኀይሉ፣ ‹ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እስከ ማበሳጨት› እንደሚሄድ፣ በዚህች መጽሔት ቅጽ … ቁጥር 04 ላይ ማውሳቱን ልብ ይሏል)። እኔም ሐሳብን በሐሳብ ልሞግት በሚል እሳቤ ተነሳስቼ፣ ይህቺን ጽሑፍ ወደ ማጠናቀሩ አመራሁ።

ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ ዴሞክራሲያዊና ሕገ-መንግሥታዊ መብት አኳያ፣ አትሌት ኀይሌ ‹የቀባጠረውን›› መቀባጠር ይችላል። እርሱ ያለውንም ነገር አብጠልጥሎም፣ ደግፎም ማውሳት፣ በዚሁ መብት ውስጥ የሚታቀፍ ይሆናል። የኀይሌን አስተያየት ሰዎች በፈለጉትና ባሻቸው መንገድ የመረዳት እና የመተንተን ነጻነቱ አላቸው፤ እኔም፣ ‹‹እውነት ዴሞክራሲ ለአህጉረ-አፍሪካ እና አፍሪካውያን ቅንጦት ነው?›› ብዬ እጠይቃለሁ – ወደ ጉዳዬ ከመግባቴ በፊት።

ለጥያቄውም፣ ‹‹በፍጹም አይደለም!›› ነው መልሴ። ኢትዮጵያውያን (እና በርካታ የአፍሪካ ሀገራት)፣ በአምባገነናዊ አገዛዞች ከባድ ጭቆና ሥር ተረግጠን እየተሰቃና ያሳለፍነውና አሁንም እየተሰቃየን ያለንበት ዋነኛ ምክንያቶች፤ የእውነተኛ ነጻነት፣ የእውነተኛ ፍትሕ ዕጦት፣ የአያሌ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻቶች አለመኖራው ነው። አንድም የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጨፍለቅ፣ መናድና መነፈግ ነው ለረዥም ዓመታት በችግር አረንቋ ውስጥ እንድንዳክር ያስገደደን። በሰዋዊም ሆነ በቁሳዊ ሀብት የዓለም ጭራ የሆንነውም እውነተኛውንና የዴሞክራሲ ጮራ ብርሃን በወጉ ማየት ስላልተቻለን ነው።

የሀገራችንን ነጥለን ብንመለከት፤ የዛሬ ገዥዎቻችንም ቢሆኑ እውነተኛ ዴሞክራሲን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢቀምሰም፤ በመንበረ-ሥልጣናቸው ላይ አንድ ቀን እንደማይገኙ ጠንቅቀው ስለሚውቁ፤ ‹ዴሞክራሲ ሒደት ነው። ዴሞክራሲ የሰፈነባት አሜሪካ እንኳ በረዥም ዓመታት ነው የተሳካላት። እኛም ዴሞክራሲን በሒደት እያጎለበትን እንሄዳለን… › የሚሉ የክፋት ጭንብል የለበሱ ቃላትን እንደ በቀቀን መለፍለፍ ምርጫቸው አድርገዋል። አምባገነን አገዛዞች እንዲህ አስመሳይ አገላለጾችን ከመናገር ውጭስ ሌላ ምን ሊሉ ይችላለ?! ምንስ አማራጭ አላቸው?!

ኢትዮጵያውያ ለዓመታት በዴሞክራሲ እጦት መኖራችን ለአስከፊ ርሃብ፣ ሞት፣ ለግፍ እስር፣ እርዛት፣ ስደት፣ ጉስቁልና … ዳርጎናል። አያሌ ችግሮች አድማሳቸውን አስፍተው እንደ ጥገኛ ተውሳክ አብረውን እየኖሩ ነው። ለውጥ ከሌለም አብሮ ኗሪነታቸው ይቀጥላል። ይሄው ነጥቤ ነው የአትሌት ኀይሌ የዴሞክራሲ ቅንጦት ነው አባባል – ያበሳጨኝ፣ ከልብም እንዳዝን ያደረገኝ።

ለአፍሪካውያን ችግሮች ዋነኛ ምንጭ የሆነው የዴሞክራሲ ዕጦት፣ ቅንጦታችን ሳይሆን አስፈላጊያችን ነው። እውነተኛ ዴሞክራሲ በአፍሪካ አህጉር በተግባር ሲሰፍን ድህነት፣ ረሃብ፣ አላስፈላጊ ሞት፣ የግፍ እስር፣ እርዛት፣ ስደት፣ ውርደት… መቀረፍ እና መክሰም ይጀምራሉ። በሀገራችንም እንደ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ እንደ ፖለቲከኞቹ አንዷለም አራጌና በቀለ ገርባ ያሉ ኢትዮጵያውያ ለእስር የተዳረጉት፣ በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑ ነው፤ በሀገሪቱም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ሆኖ ማየት ታላቁ መሻታቸው ስለሆነም፣ ባመኑበት መስመር በድፍረት ስለተጓጓም ነው። ሦስቱን ብቻ ጠቀስኳቸው እንጂ፤ ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ ሲሉ ዋጋ ከፍለዋል፤ በግፍ ታስረዋል። የሞቱም በርካቶች ናቸው፤ እውነተኛ ዴሞክራሲ ዋጋ ሳይከፈልበት፣ በቀላሉ ዕውን የሚሆን አይደለምና።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስትም ቢሆን ስለዴሞክራሲዊ መብቶች ይዘረዘራል። ከእነዚህ መብቶች መካከል በአንቀጽ 29 የአመለካከትና ሀሳብን በነጻነት የመያዝና የመግለጽ መብት፤ በአንቀጽ 30 የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት፤ በአንቀጽ 31 የመደራጃት መብት፤ በአንቀጽ 32 የመዘዋወር ነጻነት መብት… በዝርዝር ተጠቅሰው ይገኛሉ። ነገር ግን መሬት ላይ ባለው እውነታ እነዚህ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በአገዛዙ ተደፍጥጠዋል። እንግዲህ እነዚህን ነው ሻለቃ ኀይሌ ‹‹ቅንጦት›› ብሎ ያላቸው።

ዴሞክራሲ ወይም ዴሞክራሲያዊ መንግሥት፤ የመንግሥት መዋቅር ዓይነት ነው። በሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ (ቀጥተኛ ዴሞክራሲ) ወይም በሕዝብ በተመረጡ አካላት (ቀጥተኛ ያልሆነ ዴሞክራሲ) ሊመራ ይችላል። በአሁኑ ሰአት አብዛኛዎቹ የአለም ሀገራት የሚጠቀሙበት የመንግስት መዋቅርም ነው። እንግዲህ፤ ዴሞክራሲ ማለት ህዝብ የሚያስተዳድረውን አካል ያለምንም ተፅዕኖ ከመካከሉ መርጦ ሥልጣን የሚሰጥበት ሥርዓት ነው ማለት ነው። ይህም ማለት ሕዝቡ ተወካዮቹን (የፓርላማ ዓባላትን) ይመርጣል፤ ተመራጮችም መንግሥትን ይመሠርታሉ። በዚህ ሥርዓት ብዙኃኑ መንግሥት የማዋቀር መብት አለው። ቢሆንም የጥቂቶች ሙሉ መብት በሕግ የተጠበቀ ነው። የሰው ልጆች መብቶች፣ ነጻነች፣ እኩልነት፣ የሕግ የበላይነት፣ ሐሳን የመግለጽ ነጻት፣ ፍትህን ማግኘትና ሌሎችም መብቶችና ነጻቶች የሚሰፍኑበት – ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው።

ከላይ በአጭሩ የሰፈረውን ሐሳብ መሠረት በማድረግ፣ ዴሞክራሲ በአፍሪካ ውስጥ በተግባር ተተርጉሟል? ብሎ ማየት፣ መጠየቅ ጠቃሚ ነው። ኀይሌም ይሄንኑ ነጥብ ያስተውለው – እላለሁ። አስተውሎም ራሱን ብቻ ሳይሆን – ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይይበት። መልሶም – ራሱን ይመርምር። በመጨረሻም፣ ኀይሌን ልጠይቀው፡- ኀይሌ፣ አንተ ‹ቅንጦት› ያልካት ዴሞክራሲ የት ነው ያለችው?

በ1997 ዓ.ም ሰፊ ሕዝባዊ ቅቡልነት አግኝቶ ትልቅ የፖለቲካ መነቃቃትን መፍጠር የቻለው ‹‹ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ›› የፖለቲካ ድርጅት፣ በማኒፌስቶው ላይ ያሰፈረውን፣ የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን አስመልክቶ በገጽ 67 ላይ ያሰፈረውን ከሥር አስፍሬ – የዛሬ ጽሑፌን እቋጫለሁ።

‹ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ በታወቁት ዓለም አቀፍ የልማትና የዕድገት መመዘኛዎች ሲታይ እጅግ አሳፋሪ ነው። ለምሳሌ፣ ስለአፍሪካ መልካም አስተዳደር ሁኔታ ለመለካትና ለመገምገም በ1996 ዓ.ም የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በ28 አፍሪካ አገሮች ላይ ባደረገው ጥናት በፖለቲካዊ ውክልና፣ ሙስናን መቆጣጠር፣ በኢኮኖሚ አመራር፣ በሚዲያና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ነጻነት፣ በዴሞክራሲ ተቋሞች ምስረታና ብቃት፣ በአፈጻጸም ውጤታማነት ወዘተ …ኢትዮጵያ የምትገኝበት ደረጃ ከመጨረሻዎቹ 2ኛና 3ኛ መሆኑን አረጋግጧል። ሀገሪቱ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ እንኳ ከጭቆና አገዛዝ ለመገላገል አልቻለችም። በሀገሪቱ የረዥም ዘመን የመንግስት ታሪክ ውስጥ አንደኛው የጭቆና አገዛዝ በሌላኛው እየተተካ ከመኖሩ በስተቀር የዴሞክራሲ ሥርዓት አልተፈጠረም። ህዝቡም ከድህነት ወደ ድህነት ከመሸጋገር የተለየ ዕድል አላገኘም። ለእድገትና ለልማት የተመቸ የተፈጥሮ ፀጋ ቢኖርም ይኸንን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚረዳ መልካም አድተዳደር ባለመመስረቱ ኢትዮጵያ ሳታጣ ያጣች ለመሆን ተገዳለች።››

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *