ዳዊት ሰለሞን

የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሑሩ ኬንያታ በ26ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ጓደኞቻቸውን ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አገሮቻቸውን እንዲያስወጡና ህብረቱም ለዚህ የሚሆን የመውጫ ስትራቴጂ እንዲነድፍ ጠይቀዋል፣ ህብረቱም የኡሁሩን ፕሮፖዛል ያለምንም ማሻሻያ መቀበሉን አስታውቋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ አጽንኦት በመስጠትም ለሚኒስትሮች ኮሚቴ ኃላፊነት ተሰጥቶ በሄግ ከሚገኘው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አፍሪካዊያን እንዲወጡ ይደረግ ዘንድ ወትውተዋል፡፡ ዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት ‹‹ሉዓላዊነታችንን ለማጥፋት የተዘጋጀ መሳሪያ ነው›› ያሉት ኡሁሩ፣ የአፍሪካ ህብረት ለባለሥልጣናት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን ያለመከሰስ መብት እንዲያስከብርና ጉዳያቸው በፍርድ ቤቱ እየታየ የሚገኘውን የምክትል ፕሬዚዳንታቸውን ዊልያም ሩቶ ክስ እንዲቋረጥ ጫና እንዲፈጥር ጠይቀዋል፡፡
የ2007ቱን የኬንያ አገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ እጃቸው እንደሚገኝበት የተጠረጠሩት የኡሁሩ ምክትል ሶስት ክሶች ቀርበውባቸዋል፡፡ የአለም አቀፉ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ በኡሁሩ ላይ አቅርበውት ለነበረው ክስ ማስረጃና ምስክሮችን ማግኘት ባለመቻላቸው የፕሬዚዳንቱን ክስ እንዲቋረጥ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡ ከዊልያም ሩቶ ጋር የተከሰሰው የራዲዮ ጋዜጠኛው ጆሽዋ ሳንግ ጉዳዩን በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡
የሱዳኑ ፕሬዚዳንትና የተወሰኑ ባለሥልጣናቶቻቸው በምዕራብ ሱዳን በምትገኘው ዳርፉር ለተፈጸመ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ተጠያቂ በመደረጋቸው ክስ የተመሰረተባቸው ቢሆንም በአዲስ አበባ ተገኝተው አፍሪካ ከፍርድ ቤቱ አባልነት እንድትወጣ በኡሁሩ የቀረበውን ሐሳብ ደግፈዋል፡፡
በ2002 የሮም ስምምነት መጽደቁን ተከትሎ የተመሰረተው አለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በእስከአሁን ቆይታው ከ39 በላይ የአገር መሪዎችና የጦር ሹማምንት ላይ ክስ መስርቷል፡፡ በወንጀል ፍርድ ቤቱ በአብዛኛው ክስ የተመሰረተባቸው አፍሪካዊያን መሆናቸውም በአህጉሪቱ ባለሥልጣናት ፍርድ ቤቱ ጥርስ ተነክሶበት ቆይቷል፡፡
ለሮም ስምምነት ይሁንታቸውን የሰጡ 34 የአፍሪካ አገራት የፍርድ ቤቱ አባላት ናቸው፡፡ ኬንያ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ለሮም ስምምነት እውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ ብትሆንም አሁን ከአባልነት ለመውጣት ግምባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ጥሪ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
የአፍሪካ አገራት ከአለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባልነት እንዳይወጡ አጥብቀው ሲታገሉ የቆዩት ደቡብ አፍሪካዊው ቄስ ዴዝሞንድ ቱቱ ‹‹በፍጹም መውጣት የለባቸውም፣ መሪዎቹ ይህንን ለማድረግ የሚፈልጉት ያለ ተጠያቂነት ለመግደል፣ ለማሰርና ቶርቸርን ለመፈጸም ነው፣ እንደ ዘር ማጥፋት ያሉ ወንጀሎችን ከአፍሪካ ለማስወገድ ፍርድ ቤቱ መኖር ይገባዋል›› ብለዋል፡፡
የዴዝሞንድን አስተያየት የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ ኮፊ ሃናንም ይጋሩታል፡፡ ኮፊ ‹‹መሪዎቹ ፍርድ ቤቱን የሚታገሉትና ተቃርነው ድምጽ በመስጠት ጉዳያቸውን ከፍርድ ቤቱ ካስሰረዙ ለህብረቱ መሪዎችና ለአገሮቻቸው ትልቅ ሐፍረት ነው›› ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
በ2006 በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባን በአዲስ አበባ በመገኘት ተካፍለው የነበሩት የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ፊሊፕ ኪርሴች ‹‹እስከሚገባኝ ድረስ ፍርድ ቤቱ ያለአፍሪካዊያን ድጋፍ መቀጠል አይችልም›› ብለው ነበር፡፡
ኡሁሩ ኬንያታን ጨምሮ የሚበዙት የአፍሪካ መሪዎች አገሮቻቸውን ከዓለም ዓቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባልነት ለማስወጣት የሚወተውቱት ፍርድ ቤቱ በዋናነት አፍሪካዊያንን ለማጥቃት የተዘጋጀ ነው በማለት ነው፡፡ ለዚህ የሚያቀርቡት መከራከሪያም ‹‹በፍርድ ቤቱ ክስ የቀረበባቸው ተከሳሾች በሙሉ አፍሪካዊያን ናቸው›› የሚል ነው፡፡
የፍርድ ቤቱን የክስ ሂደት የሚከታተሉ ታዛቢዎች ግን ፍርድ ቤቱ ላይ የሚቀርበውን ውንጀላ ያጣጥላሉ፡፡ በፍርድ ቤቱ ክስ ከቀረበባቸው የአፍሪካ መሪዎች የሚበዙት በምስራቅ አፍሪካ እንደሚገኙ በመጥቀስ ክሱ የቀረበባቸው በአውሮፓውያን ወይም በሌሎች ሳይሆን በአፍሪካዊያን መሆኑን ያወሳሉ፡፡
በፍርድ ቤቱ ክስ ከቀረበባቸው መሪዎች መካከል ሱዳን፣ ኬንያ፣ ኮትዲቯር፣ ኡጋንዳና ሩዋንዳን የመሳሰሉ አገራት ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ አገራት ስልጣን ላይ ያሉ አካላት ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ የጅምላ ግድያ፣ አፈና፣ ቶርቸርና ሴቶችን እንደመድፈር ያሉ ወንጀሎች መፈጸማቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንዲህ አይነት በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በአውሮፓ ማግኘት የማይታሰብ በመሆኑም ‹‹አውሮፓውያን መሪዎች ሊከሰሱ አልቻሉም›› ይላሉ፡፡
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራከሪ ድርጅት አምነስቲ አፍሪካዊያኑ መሪዎች ‹‹ፍርድ ቤቱ እኛን ብቻ ዒላማ አድርጎናል›› በማለት ከሮም ስምምነት ውጪ ስለመሆን ከመጠየቅ ይልቅ አድማሱን በማስፋት ሌሎችንም ማካተት ይገባዋል በማለት ቢጠይቁ የበለጠ ተዓማኒነት ያገኙ ነበር ብሏል በመግለጫው፡፡
እንደ አምነስቲ እምነት ‹‹ፍርድ ቤቱ ሌሎችን ሳይከስ አፍሪካዊያንን ብቻ ከስሷል›› ቢባል እንኳን ክሱ ሐሰተኛ ነው ማለት አይደለም ይላል፡፡ ለዚህ የሚያቀርበው መከራከሪያም ክሶቹ የቀረቡት በራሳቸው በአፍሪካዊያን መሆናቸውን ነው፡፡ በመካከለኛ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኮትዲቯር፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ኡጋንዳና ማሊ ባለስልጣናት ላይ የቀረቡት ክሶች በአፍሪካዊያን፣ በሱዳንና በሊቢያ መሪዎች ላይ ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት መቅረቡን ይጠቅሳል፡፡
አፍሪካ በመሪዎቿ ስምምነት መሰረት ከሮም ስምምነት ውጪ ብትሆን ምን ይፈጠራል?
ደቡብ አፍሪካዊው ቄስና የጸረ አፓርታይድ ታጋይ ዴዝሞንድ ቱቱ ‹‹ከፍርድ ቤቱ መውጣት ለመሪዎች ለመግደል፣ ለማሰርና ተቃዋሚዎቻቸውን ለማሰቃየት ነጻ ፈቃድ ይሰጣቸዋል›› ይላሉ፡፡ እንደ ዴዝሞንድ እምነት አህጉሪቱ በፍርድ ቤቱ እየተዳኘች መቆየቷ መሪዎቿን ተጠያቂነት እንዳለባቸው እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡
‹‹አፍሪካ ከፍርድ ቤቱ መውጣት አለባት›› የሚሉ አካላት በበኩላቸው ‹‹አህጉሪቱ የራሷን የሆነ ፍርድ ቤት እንድታቋቁም ያደርጋታል›› ይላሉ፡፡ ብዙዎች ግን የሚበዙት የአፍሪካ መሪዎች ስለ ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያላቸውን አቋም በመመዘን በሚያቋቁሙት ፍርድ ቤት ማንን ተጠያቂ በማድረግ ሊያቆሙ እንደሚችሉ በመተንበይ በአፍሪካ እንደ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ያለ ተቋም ስለመቋቋሙ ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ፡፡
የኬንያው ተወዳጅ ጋዜጣ ዴይሊ ኔሸን በርዕሠ አንቀጹ ባቀረበው የካርቶን ምስል የአፍሪካ መሪዎች በሚያቋቁሙት ፍርድ ቤት በወንጀለኛ ሳጥን ውስጥ ጋዜጠኞች፣ የሲቪክ ማኅበራት መሪዎች፣ ተቃዋሚዎችና ከመሪዎቹ የተለየ አቋም ያላቸውን ሰዎች አቁሞ አሳይቷል፡፡
በየአገሮቻቸው ሐሳብን ለመግለጽ ነጻነት፣ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓትና ለነጻ ተቋማት መኖር ዕድል ያልፈጠሩ መሪዎች በሚያቋቁሙት ፍርድ ቤት ማንን በተከሳሽነት ሊያቆሙ እንደሚችሉ መገመት አያስቸግርም፡፡
በፍርድ ቤቱ ክስ የቀረበባቸውና በቀጣይ በፍርድ ቤቱ የተከሳሾች ሳጥን ውስጥ ራሳቸውን ሊያገኙ የሚችሉ ባለስልጣናት አፍሪካን ገፍተው ከፍርድ ቤቱ ሊያስወጧት ቢችሉም ፍርድ ቤቱ ግን የቀረበለትንና በቀጣይም የሚቀርብለትን ክስ እንደሚመለከት በመናገር ላይ ይገኛል፡፡
ዴዝሞንድ ቱቱ ‹‹የአፍሪካ መሪዎችን አደብ ለማስገዛት አፍሪካ የግድ አባል እንደሆነች መቀጠል ይኖርባታል›› ቢሉም አደብ መግዛት ያልፈለጉ የሚመስሉት መሪዎቿ በፍርድ ቤቱ ደጃፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ኅብረቱ የመሪዎቹን ደህንነት ለመጠበቅ እንጂ ለአፍሪካዊያን አለመቆሙን ለሚናገሩ ተጨማሪ ማሳያ ሆኖላቸዋል፡፡

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *