ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ

 

 

ይህ ጽሑፍ ባለፈው፣ ‹‹የአፍሪካ የፍልስፍና ‹‹ዓለም›››› በሚል ርዕስ የቀረበው ጽሑፍ ቀጣይ ነው፡፡ ጸሐፊው በዚህ መጣጥፍ በአፍሪካ ፍልስፍና ላይ ትኩረት አድርገው፣ ሌሎች ነጥቦችንም ያሳዩናል፡፡

እነሆ!

 

II There is no power relation without correlative constitution of a field of knowledge, nor any knowledge that does not presuppose and constitute at the same time power relation.

(Michel Foucault)

 

ቀደም ብዬ በአጭሩ ያቀረብኩት የቅድመ-ቅኝ-ግዛት ዘመን ታሪክ ያለ ምክንያት አይደለም፤ ፍልስፍናና የሰው ልጅ ታሪክ የአንድ ድምቡሎ ሁለት ገፅታ ስለሆኑ ነው። ከሁሉ በፊት ‹‹አፊሪካ ጨለማ አህጉር ነበረች›› የሚለው አስተሳሰብ ቀጥታ የተቆራኘው ከፍልስፍና ጋር ነው። ሰይጣኑ ያለው እዘህ ነው፤ ‹‹ሥልጣኔ አልባ ሕዝብ›› የሚለው ሐረግ ‹‹የአፍሪካውያን አስተሳሰብ በምክንያት ላይ የተመሠረተ አይደለም›› የሚል አንደምታ አለው። በሌላ አገላለጽ፣ ‹‹ከምዕራባዊያኑ በተቃራን የአፈሪካውያን አእምሮ ለተጠየቃዊ ፍሰት (reasoning process) ወይም ለአመክንዮ (logic) ባዳ ከመሆኑ የተነሳ፣ ነገሮችን የመረዳት ብቃት ዝቅተኛ ነው›› የሚል ነው። አሁንም በሌላ አገላለጽ፣ ‹‹አፊሪካውያን ምክንያታዊ የእውቀት ችሎታ የላቸውም›› ማለት ነው። ምክንያቱም፣ ‹‹የአፊሪካውያን አስተሳሰብ ወይም የአእምሮ ችሎታ (mentality) በተፈጥሮ ተማልሎአዊ (mystic) ወይም ግልፅ ባልሆነ (prelogical) ነገር ላይ የተመሠረተ እንጂ፣ አመክንዮን ማዕከል ያደረገ አይደለም።›› ከአፊሪካውያን በተቃራኒ፣ ‹‹የአውሮፓዊያን የአእምሮ ችሎታ (mentality) በተፈጥሮ አመክንዮን ማዕከል ያደረገ ነው። ስለዚህ አፊሪካውያን ገና ከሕፃንነት ያልወጡና ያልሰለጠኑ ሰዎች (savages) ናቸው።›› ይህ ማለት ‹‹ጥቁሮች በረቂቁ ማሰብ ስለማይችሉ፣ የፍልስፍና ወይም የስልጣኔ ምንጭና ባለቤት ነጮች ብቻ ናቸው።›› መደምደምያ፡- (ሀ) ‹‹አውሮፓዊያን በዓይነት (qualitativily) ከአፈርካውያን የተሻሉ እና የሰለጠኑ ሕዝቦች ናቸው››፤ (ለ) ‹‹አፊሪካዊያን እንደ ምዕራቡ ዓለም ታሪክም ሆነ ባሕል ስለሌላቸው ‹አፍሪካ የዓለም አካል ልትሆን አትችልም››› (Lucien Lévy-Bruhl: 1985, 35-36, 78-79, 129-130፡ 1975 126 E. E. Evans-Pritchard: 1980 passim; Diederich Westermann: 1934, 39.  John Carothers: 1972, 93-96; T. S. Eliot: 1962, 143; G. F. W. Hegel፡ 1956, 91-99; 1975፡ 1989, 176; C. M. Neugebauer, 1991፡ 50-73; 1991፡ 247-257; Tsenay Serequeberhan፡ 1991, 7; 1997: 141-161;  Emmanuel Chukwudi Eze 1997: 103-140)

እነዚህ ፈላስፎች ትክክለኛውን የጥቁር ሕዝብ ታሪክ ሰርዘው፣ በፍልስፍና ስም የወጣለት ዘረኝነታቸውን አንፀባርቀዋል። ‹‹ምርጥ የሰው ዘር›› መሆናቸውንም ለማሳየት እንደ ጉንዳን ‹‹ከአንገት በላይ የሚወፍረው›› ነጭ ብቻ እንጂ ጥቁር እንዳልሆነ በስፋት አስነብበውናል። የዚህ ተረት ዋና ዓላማ አንድና አንድ ብቻ ነው፡- ‹‹ጥቁር በረቂቁ ማሰብ ስለማይችል፣ የፍልስፍና/የስልጣኔ ምንጭና ባለቤት ነጮች ብቻ ናቸው›› የሚል ነው። ይህ ተረት አንድ በጣም አደገኛ ሀሳብ ያንጸባርቃል፤ ‹‹የነጮች ሕልውና በዓይነት (qualitatively) ከጥቁሮች ሕልውና የተሻለ ነው›› የሚል ነው። [‹‹A pervasive bias located in modernity’s self-consciousness of itself. It is grounded at its core in the metaphysical belief or Idea (Idee) that European existence is qualitatively superior to other forms of human life.›› Tsenay Sereqebrhan 1997: 142] ‹‹የነጮች ታሪክና ባህል (ማንነት) ፍፁምና እንከን የማይወጣለት በመሆኑ፣ የ‘ሌሎች’ ሰዎች ሁሉ ባህልና አኗኗር መለክያ መሆን አለበት›› የሚል አንደምታ አለው። መደምደሚያ:- እንደ ነጭ የማያስብ ወይም የማይሰራ ወይም የማይበላ ወይም የማይጽፍ ወይም የማይናገር ወይም የማይለብስ ወይም የማይመራመር ወይም የማያመልክ ወዘተ. በአራዳ ልጆች ቋንቋ ‹‹ፋራ›› ተብሎ ይፈረጃል። በሌላ አገላለጽ ‹‹አልሰለጠነም›› ወይም ‹‹ዘመናዊ›› አይደለም! ምክንያቱም የሰው ልጅ ማንነት እና ምንነት ከነጮቹ ‹‹ህልውና›› አንፃር መለካትና መተርጎም ይኖርበታል!

አውሮፓዊያን በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ሴራዎች በመታገዝ አፍሪካውያን ‹‹ማንነታቸውን›› እንዲጠሉ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ሲሆን አሁንም ያንን እኩይ ተግባራቸውን ቀጥለውበታል። ዛሬ በብዙ አፍሪካውያን አእምሮ ውስጥ ስር ሰዶ የሰረጸው አፍርካዊ ማንነት (ባህልና ቋንቋ) ሳይሆን የምዕራቡ ‹‹ዓለም›› የአስተሳሰብ ሽርሙጥና ነው። ከሁሉ በላይ የሚገርመው፣ ምዕራባዊያን ከአፍሪካውያን በላይ አፍርካዊ በመሆን የአፍርካውያንን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች መቅረፍ የሚቻለው በምዕራባውያን ‹‹ስልጣኔ›› ብቻ ነው ብለው ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ መሆኑ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ አፍሪካውያን የራሳቸውን ቋንቋና ባህል በመተው የምዕራቡን ‹‹ስልጣኔ›› ወይም ርዮተ-ዓለም እንዳለ ኮርጀው ሲተገብሩ ብቻ መሆኑን ያክሉበታል። ምክንያቱም የአፍሪካውያን ባህልና ቋንቋ ‹‹ኋላቀር›› እና ‹‹ጊዜ ያለፈበት›› በመሆኑ፣ ‹‹በዘመናዊው›› ዓለም ውስጥ ቦታ የለውምና ነው! ‹‹ስለዚህ፣›› ይላሉ እነዚህ ‹‹የሰለጠኑ ሰዎች›› ‹‹በግድ እኛን ሁኑ!›› ያውም በኢኮኖሚያዊና (ሁልጊዜ) በወታደራዊ (አልፎ አልፎ) ማስፈራርያና ዛቻ!

የምዕራቡ ‹‹ዓለም›› ግዙፍ የመገናኛ ብዙሃንና የፊልም ኢንዱስትሪ ተቋማት፣ የአፍሪካን ማንነት ጥላሸት እየቀቡ የራሳቸውን ማንነት እያቆለጳጰሱ የሚያቀርቡበት አሰራር፣ የአፍሪካን ህዝብ አፍነው ብዝበዛቸውን ለመቀጠልና ህዝቡን በርእዮተ-ዓለም እያከፋፈሉ በማፋጀት፤ የጦር መሳርያዎቻቸውን ለመቸብቸብ ነው። ምዕራባዊያን፣ ለአፍሪካ ያላቸው ስር የሰደደ ጥላቻና ድንበር የለሽ ንቀት አይን ያወጣ ጉዳይ ስለሆነ ላያስገርም ይችላል። ይልቅ የሚያስገርመው የምዕራባውያንን ጥቅም ለማስጠበቅ ሽር-ጉድ የሚሉ አውሮ-አፍርካዊያን (Westernized Africans) ናቸው። እነዚህ አድርባዮች፣ የአፍሪካን  ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ጥቅሞችን ከማስጠበቅ ይልቅ፣ ለብዝበዛ አሳልፎ በመስጠት አፍሪካ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስር እንድትማቀቅ እያደረጉ ናቸው። ይህ ነገር ቀጣይነት እንዲኖረውም አፍሪካውያን ማንነታቸውን ችላ ብለው የምዕራቡን ‹‹ዓለም›› የአስተሳሰብ ሽርሙጥና እንዲከተሉና እንዲተገብሩ እየሠሩ ይገኛሉ።

ዞረም ቀረ አንድ በሚገባ መገንዘብ ያለብን ነጥብ ቢኖር፣ በሰዎች መካከል ያለ የባህል መወራረስ የማይቀር ጉዳይ ሆኖ ሳለ ‹‹የስልጣኔ ሁሉ ምንጭና ባለቤት አውሮፓውያን/ግሪካውያን ብቻ ነበሩ›› ብሎ መፈላሰፍ የወጣለት ዘረኝነት አልያም የወጣለት ድንቁርና መሆኑ ነው። አንድ ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ‹‹ከሌላ የተሻልኩ ነኝ›› በማለቱ ብቻ ትልቅ ሊሆን አይችልም። በተለይ ‹‹ትልቅነቱን›› የሚገልጹ ተረታ ተረቶች ተፈጥረው ወደ ፍልስፍናና ታሪክ ደረጃ ማደግ ስለሚችሉ፣ ‹‹ነፃና ገለልተኛ›› በሆነ ጥልቅ የፍልስፍና ምርምርና ትንተና ሊረጋገጥ ይገባል። የአፍሪካ ፍልስፍና ከተረትነት ወደ ፍልስፍናነት ራሳቸውን ያሳደጉትን የምዕራባውያንን ፍልስፍና ታሪክን በጥልቀት ፈትሾ የአስተሳሰብ ጋጠ-ወጥነቱን ነቅሶ በማውጣት ተገቢ የሆነ ሂስ መስጠት ይኖርበታል። ለወደፊቱ በጥልቅ ፍልስፍዊ ማብራርያ እንደማሳየው ‹‹በግድ እኛን ሁኑ!›› የሚለው የምዕራቡ ‹‹ዓለም›› አካሄድ የራሳቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስጠበቅያና የእጅ አዙር ቅኝ-አገዛዝ (neo-colonization) እንጂ፣ ፈጽሞ የአፍሪካን ማንነት እና ኢኮኖሚያዊ ነጻነት የሚያረጋግጥ አይደለም። በመሰረቱ እነርሱ ‹‹ዘመናዊ›› እያሉ የሚቀባጥሩት ነገር ባይኖርም፣ ‹‹የምዕራቡ ሥልጣኔ›› የሚባለው በራሱ የግድያና የብዝበዛ ተግባር እንጂ፣ ‹‹ስልጣኔ›› እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል።

የምዕራቡ ‹‹ዓለም›› በአፍሪካውያን ደምና አጥንት ላይ ተረማምዶ ያካበተውን ‹‹ሀብት›› በራሱ ብቃትና ችሎታ (ጉልበትና እውቀት) ብቻ እንዳስገኘ አድርጎ ማሰብ የወጣለት ቅጥፈት ነው። በአውሮፓውያን ሤራና በአፍሪካውያን ቅጥረኞቻቸው (ቡችሎቻቸው) ሸፍጥ የተገነባው የምዕራቡ ‹‹ዓለም›› ድምር ውጤት እንጂ፣ በህጋዊና ፍትሐዊ መንገድ የተገኘ ‹‹ሀብት›› እንዳልሆነ በአፅንኦት ሊሰመርበት ይገባል። ይህ ቃላት የማይገልጸው ብዝበዛና ጭፍጨፋ (Chukwudi Eze 1997፡ 13) ለመረዳት በWalter Rodney (1972፡ Passim) እና በBasil Davidson (1966፡ Passim;  1969፡ Passim) የተደረሱትን የምርምር ስራዎች ማየት በራሱ በቂ ነው። ዛሬ በ‹‹እርዳታ›› ስም ከምዕራባውያን የሚጎርፈው ገንዘብ ላለፉት 500 አመታት ከአፍሪካ አህጉር (በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ) የተዘረፈው ሀብት እንጂ የእነርሱ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። የአፍሪካውያን ሰው አክባሪነት ሆኖ እንጂ ለእንደዚህ አይነት ‹‹ልግስና›› የምስጋና ደብዳቤ መልሶ መጻፍ በገዛ ራስ ላይ እንደ መሳለቅ ይቆጠራል፡፡ (‹‹How can you thank a man for giving you what’s already yours? How then can you thank him for giving you only part of what is yours?›› — Malcom X]

የአፍሪካ ፍልስፍና ታሪክ ሲነሳ አንድ ነገር በአፅንኦት ሊሰመርበት ይገባል፤ የአፍሪካ ፍልስፍና ጥያቄ ከዲበ-ፍልስፍና (metaphilosophy) ጋር ብቻ የተሳሰረ አይደለም። ኬንያዊው ፈላስፋ ሳሙኤል ኦሉኦች ኢምቦ (Samuel Oluoch Imbo)፣ ‹‹የአፍሪካ ፍልስፍና ጥያቄ በአንድ ጊዜ ታሪካዊ፣ ምሑራዊ፣ ርእዮት-ዓለማዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጭምር በመሆኑ፣ ግልብ መልሶች የችግሩ ምንጭ ላይ መድረስ አይችሉም፡፡›› ሲል ይሞግታል። (S. O. Imbo 1998: 46) ናይጄሪያዊው ፈላስፋ ኢማኑኤል ቹሁኩንዲ ኤዜ (Emmanuel Chukwudi Eze)፣ ይህንን እውነታ እንዲህ ሲል በትክክል ያብራራዋል፡- ‹‹When Western philosophy speaks of ‹‹reason››, it is not just speaking of ‹‹science›› and ‹‹knowledge›› and ‹‹method›› and ‹‹critique›› or even ‹‹thought››. In and through these codes it is more fundamentally the question of the ‹‹anthropos›› of the human, that is at stake, for questions of knowledge and identity, logos and anthropos, always hang together. It is within this background of anthropos as logikos, the interlacing of human understanding and the understanding of the human, that Europeans originally introduced the notion of a difference in kind between themselves and Africans as a way of justifying unspeakable exploitation and denigration of Africans. (E. C. Eze 1997: 13)

የድኅረ-ቅኝ-ግዛት-አፍሪካ ሁኔታን በጥለቀት በማብራራት እና በአውሮ-አፊሪካዊያን አስተሳሰብ (reasoning) ላይ የተባ ሂስ በመሰንዘር የሚታወቀው ኤርትራዊው ፈላስፋ Tsenay Serequeberhan፣ የአፍሪካ ፍልስፍና ጥያቄ ፖሊቲካዊ መሆኑን በጥብቅ ይከራከራል። (Tsenay Serequeberhan 1994፡ passim) ለሎች ጥናቶችም ይህንን ድምዳሜ የሚደግፉ ናቸው። (ሌዊስ ጐርዶን — Lewis Gordon 1997: 241-251)፣ (ጆን ፒትማን — John Pitman 1997: 260-282)፣ (ኮርነል ወስት — Cornel West 1998: 112-118)፣  እና  ኢማኑኤል ቹሁኩንዲ ኤዜ — Emmanuel Chukwudi Eze (1998፡ 213-221)

 

ስለዚህ በአፍሪካ ፍልስፍና ላይ ጠለቅ ያለ ምርምር ያላደረጉ ግለሰቦች የሣር-መዘዛ (oversimplification) ሕፀፅ ላለመፈፀም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። በፍልስፍና ወይም በሳይንስ ስም እውነታን ለማፈለስ የሚደረግ የአስተሳሰብ ቅሬ ከዲበ-ፍልስፍና (metaphilosophy) አንፃር ተቀባይነት ስለሌለው፣ መንገዱ ሁሌ ዝግ ነው። በእርግጥ ምዕራባውያን ስለ ፍልስፍና ንጥረ-ነገር (essence) ሲነሳ ጥያቄውን አድበስብሰው ያልፋሉ። በ‹‹ፍልስፍና ታሪክ›› ላይ ብቻ አነጣጥረው የተሽከርካሪ ሕፀፅ ደጋግመው ይፈጽማሉ። ስለዚህ የእኛ ጥያቄ መሆን ያለበት፣ ‹‹የአፍሪካ ፍልስፍና ምንነት ጥያቄ ወይስ የምዕራቡ ‹ዓለም› የአስተሳሰብ ቅሬ?›› የሚለው ነው።

ጥያቄው የ‹‹ፍልስፍና›› እና ‹‹የፍልስፍና ታሪክን›› ልዩነትን የሚመለከት ነው። እስካሁን በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ ግለሰቦች ‹‹ያመነጩት›› ፍልስፍናዊ ጽንሰ-ሐሳቦችና አሚነ-መሰረቶች (ተመሳሳይነታቸውና ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ) እንጂ ከነባራዊ እውቀት (objective knowledge) ጋር አንድ የሆነ ግለሰባዊም ሆነ ማኅበራዊ ፍልስፍና የለም፤ ሊኖርም አይችልም። ስለዚህ የአንድ ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ እንደ መለኪያ የሚወሰድበት ሁኔታ አንዳችም ምክንያት የለም። ‹‹ሰው የእውነት መለኪያ ነው›› የሚል ፍልስፍናዊ ተረት ይቅርና ‹‹ሰው ምክንያታዊ እንስሳ ነው›› የሚለው ብሉይ (classical) ፍልስፍናዊ አስተምህሮ በራሱ ውሃ የሚያነሳው እስከተወሰነ ድረስ ብቻ ነው። ‹‹ሰው ማኅበራዊ እንስሳ››ም እንደ መሆኑ መጠን ‹‹አንድ ግለሰብ ከማኅበረሰቡ ተለይቶ ብቻውን ‘ሰው’ ሊሆን ይችላል?›› የሚለው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ እስካልተሰጠበት ድረስ፣ በአንድ ነጠላ ፍልስፍናዊ አመክንዮ ላይ ብቻ የተመሠረተ የሰው ‹‹ማንነት›› ወሰነ-ትርጉም የተሳሳተ የፍልስፍና ትንተና ዘዴን ስለሚከተል ተቀባይነት የለውም። (ይህ ግን ‹‹እውነት አንፃራዊ ነው›› ማለት አይደለም። በአሁኑ ዘመን ‹‹እውነት የሚባል ነገር የለም›› የሚለውን ሕፃናዊ ተረቶች እየሰማን ነው። አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ‹‹የሰው ልጅ እውነትን ማወቅ አይችልም›› የሚል ፍልስፍናዊ መደምደምያ የወጣለት ድንቁርና መሆኑ ነው።)

ከሁሉ በላይ ፍልስፍና የተጀመረው በተልስ (Thales) ጊዜ ነው የሚለው ተራ ፍልስፍናዊ ማብራሪያ የሰውን ‹‹ህልውና›› ብቻ ሳይሆን ፍልስፍና ራሱ ከሌሎች የትምህርት ዘርፎች በምን መልኩ እንደሚለይ ከቅጡ አለመረዳትን ያመለክታል። መፈላሰፍና መሰረታዊ ጥያቄዎችን መጠየቅ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከሆነ፣ ፍልስፍና ታሪካዊ አጀማመር (historical origins of philosophy) ብቻ ሳይሆን ኢ-ታሪካዊ አጀማመርም (ontological origins of philosophy) እንዳለው ነው። (Drew A. Hyland 1973, Passim) ስለዚህ ፍልስፍና በግሪክ ሀገር በተልስ ጊዜ ተጀመረ ብሎ አቋም መውሰድ፣ የ‹‹ፍልስፍና››ና ‹‹የፍልስፍና ታሪክ››ን ልዩነት ካለመገንዘብ የሚመነጭ ነው። አብዛኞቹ የምዕራባውያንና የአፍሪካውያን ፈላስፎች የፍልስፍና ታሪክን መተንተን እንጂ፣ ‹‹ፍልስፍና ምንድን ነው?›› እና ‹‹ፍልስፍና ከሌሎች የትምህርት ዘርፎች የሚለየው እንዴት ነው?›› የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ አይፈልጉም። እዚህም ሆነ እዚያ ‹‹የፍልስፍና ታሪክ›› ‹‹ፍልስፍና››ን ፈጽሞ ሊተካ አይችልም። ስለዚህ ለመፈላሰፍ የግድ በአስተሳሰብ ደረጃ የምዕራባውያን ቡችላ መሆን አያስፈልግም። ከሁሉ በላይ የሰው ልጅ ታሪካዊ ዳራ ግድ የማይላቸው ምዕራባውያን ፈላስፎችና አውሮ-አፊሪካውያን አጨብጫቢዎቻቸው፣ ራሱን የቻለ የአካዳሚ ትምህርት ዘርፍ ፍልስፍናን ከሥነ-አመክንዮ ጋር ጨፍልቀው አንድ በማድረግ አንድ ዓይነት ፍልስፍናዊ ዘዴና ትንተና እንዳለ ሊያሳምኑን ይሞክራሉ። አንድም ሥነ-አመክንዮ የፍልስፍና አንድ ክፍል እንጂ፤ ፈጽሞ ራሱን የቻለ አንድ የትምህርት ዘርፍ እንዳልሆነ እየታወቀ፤ ሁለትም ኑባሬን (being) ወይም እሳቦትን (thought) መመራመር የፍልስፍና ዋና ተልዕኮ እንጂ ቁንፅል ነገር ላይ በሚተኮረው አመክንዮ ፈጽሞ ስለማይሞከር፣ ፍልስፍናን እንደ ሌሎች የትምህርት ዘርፎች አንድ ዓይነት የምርምር ዘዴ መከተል አለበት ብሎ መደምደም የፍልስፍናን ምንነትና ተልዕኮ ከቅጡ አለመረዳትን ያመለክታል።

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *