ደረጀ መላኩ
tilahungesses@gmail.com
የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ገጽታ በድርቅና ችጋር ሊተረጎም ይችላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ያጣው መሠረታዊ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን፣ በነጻ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙትን ሰላምና ብልጽግናን ጭምር ነው። ሀገሪቱ በጦርነት፣ በጎሳ ግጭቶች፣ ስር በሰደደ የሥራ አጥ ክምችት፣ በጭቆና፣ ዛሬ ደግሞ እጅግ ከፍተኛ በሆነ የምግብ ዋጋ ንረት ፍዳዋን የምታይ ናት። በእኔ እምነት የእነዚህ ሁሉ መጠነ ሰፊ ችግሮች ምክንያት የነጻነት አለመኖር ነው። ይሁንና ዛሬ ለደረስንበት አሳፋሪ ሁኔታ ምክንያቱ የነጻነት እጦት አይደለም ብለው የሚያምኑ ሞልተዋል። ለማንኛውም ብሔራዊ ውርደት ውስጥ እንዴት ልንዶል እንደ ቻልን ዝቅ ብዬ ለማብራራት እሞክራለሁ።
ሀ/ ሀብት የማፍራት መብት
ታላቋ አሜሪካም ሆነች የምዕራቡ ዓለም እንዲሁም ሌሎች ወደ ሥልጣኔው ዓለም እየተቀላቀሉ ያሉ ሀገራት፤ የሥልጣኔያቸው ዋነኛ መሠረት የዜጎቻቸውን ሀብት የማፍራት መብት በማስከበራቸው ይመስለኛል። ኢትዮጵያውያን ግን ለዚህ አልታደልንምና የአለም የምጣኔ ሀብት ጭራ ሆነን ፍዳችንን እንቆጥራለን። በእውነቱ ያማል። የሰው ልጅ ለሚያፈሰው ሀብት ደኅንነት የሚሰጠው መንግሥት ካላገኘ ታላላቅ ፕሮጀክት እና የረጅም ጊዜ ውል ማሰብ ቀርቶ፤ በሀገሩ ምድር ላይ ለመኖር አያስብም። እዚህ ላይ በቅርቡ ከባሕር ማዶ ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ የመጣ የትምህርት ቤት ጓደኛዬ ያጫወተኝን ላካፍላችሁ፤ ሰውዬው አንድ ቤታቸው በላያቸው ላይ ሊፈርስ የደረሰ እናትን ከጎበኘ በኋላ ሁኔታው ልቡን ስለነካው፣ ቤቱን ላሳድስሎት ብሎ ጠየቃቸው። እርሳቸውም ‹‹አይ ልጄ! ኪራይ ታስጨምርብኛለህ!›› ብለው እንደ መለሱለት በኀዘን አውግቶኛል። ብዙዎች የመርካቶና ሌሎች አከባቢ ነጋዴዎች የኢኮኖሚ መብቶቻቸው ቢጠበቅላቸው ኖሮ፣ ዛሬ ሳይሆን ትላንት ነበር መርካቶን የዘመነ የገበያ ማዕከል የሚያደርጉት።
አስተውለን የምንራመድ ከሆነ ብዙ አሳዛኝ ክስተቶችን ማየት እንችላለን። በብዙ አካባቢዎች የሚገኙ የግል መኖሪያ ቤቶች (ግድግዳውና ጣራው ብቻ ነው የግል የሚባለው) ቅጥር ግቢ ውስጥ ዛፎችን ለምን እንደማይተክሉ ጠይቄ ባገኘሁት መልስ፣ የእኔነት ስሜት እንደማይስማቸው በኀዘን ገልጸውልኛል። በሌላ በኩል አብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ የዛጉ የቆርቆሮ ክዳንና ጭቃ ቤት ውስጥ የሚኖረው (ኑሮ ከተባለ) አቅም በማጣት ብቻ ሳይሆን፣ የመሬት ባለቤት የሆነው አገዛዙ በአንድ ጊዜ ተነሥቶ አካባቢውን ለልማት ብሎ ስለሚያፈርሰው ነው፡፡ (አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት፣ ሰንጋ ተራ ካዛንችስ፣ ውቤ በረሃ፣ አሜሪካን ግቢ ወዘተ. ቋሚ ምስክሮች ናቸው)።
በሀገሪቱ ላይ የኢኮኖሚ ነጻነት እውን ቢሆን ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባንና ሌሎች ከተሞችን በዘመነ ሁኔታ ለመገንባት የሚያስችላቸውን ንዋይና እውቀት ፈሰስ ባደረጉ ነበር። ያጣነው ነጻነት ነው። በዓለም ላይ እንደ ጨው ዘር የተበተነው ወገኔ በዚች ሀገር ላይ የኢኮኖሚ ነጻነት እውን ከሆነ ታምራት መሥራት ይችል ነበር። ግን አልሆነም። በእውነቱ ያማል። ከመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያና እስከ መገናኛ እንዲሁም በሌሎች አከባቢዎች የዘመኑ ሕንፃዎች ተገንብተው ሳለ ለምን ‹‹የኢኮኖሚ ነጻነት የለም፤ ዕድገት የለም›› ተብሎ ይጻፋል በማለት ቡራከረዩ የምትሉ ካላችሁ፤ መልሱ ‹‹ልማት ያለ ነጻነት የሚታሰብ አይደለም!›› የሚለው ይሆናል።
የኢኮኖሚ ነጻነት በሌለበት ሁኔታ ግለሰቦች ሀብት ማፍራትም ሆነ ለነገ የሚሆን ቀለብ ሊኖራቸው አይቻላቸውም። ጥቂቶች በቁንጣን በሚቸገሩባት አዲስ አበባ፤ ብዙኃኑ ተመጣጣኝ ምግብ በማጣቱ በሕመም እንደሚሰቃይ የታወቀ ነው። ይህ ደግሞ የሀብት አለመመጣጠን የፈጠረው አሳዛኝ ገጽታችን ነው። በ21ኛው ክ/ዘ የችጋር ተምሳሌት ሆነን የቀረነው ሀብት የማፍራት መብታችን በእኩይ አምባገነን ሥርዓት ስለተገፈፈ ነው። ገበሬው የእኔ የሚለው መሬት ቢኖረው ዛፍ ይተክላል፤ የመሬቱን ለምነት ይንከባከባል፤ በመስኖ ልማት ይጠቀማል፤ በፈለገው ዋጋ ምርቱን ለገበያ ያቀርባል፤ ወዘተ.። አለመታደል ሆኖ የኢትዮጵያ ገበሬ የመሬቱ ባለቤት ለመሆን የሚያስችለውን ነጻነቱን ስለተገፈፈ፤ ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ሆኗል። ኢትዮጵያን በመሰለ የበርካታ ወንዞች ባለቤት ሀገር ላይ ከዐሥራ ሚሊየን በላይ ሰው በችጋር መሰቃየቱ በእውነቱ እጅግ ያማል። እስራኤላያውያን በዚያ የአየር ጸባይና የመሬት አቀማመጥ ሕዝባቸውን ለመገብ ከመቻላቸውም በላይ ተርፏቸው ለዓለም ገበያ እህል ማቅረብ የቻሉት የኢኮኖሚ ነጻነታቸውን ስላወጁ ነው። ስፔንያውያን ከደቡባዊ ስፔን ወደ ሰሜናዊ ስፔን የውኃ ቧንቧ መስመር ዘርግተው ሀገራቸውን ማልማት ከጀመሩ ዓመታት አስቆጥረዋል። እኛ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለማቆም አልቻልንምና ምድሩ በውኃ ተጥለቅልቆ ውኃ ይጠማናል፤ ለግብርና ምቹ የሆነ ለም መሬት እያለን ይርበናል።
የፖለቲካ ነጻነት
እንደ ኢኮኖሚ ነጻነት ሁሉ ከገባንበት የፖለቲካ ማጥ ለመውጣት የፖለቲካ ነጻነት ያስፈልገናል። ይሁንና ዛሬም የፖለቲካ ነጻነቶቻችን ተገፍፈዋል። በባለፉት ሥርዓቶችም ሆነ ዛሬ ሥልጣን በጥቂት ቡድኖች መዳፍ ውስጥ ወድቆ ይገኛል። ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ።
በዓለም ላይ ካሉ ሀገራት ሁሉ በግንባር ቀደምነት (የስካንዲኔቪያ ሀገራትን ሳንዘነጋ) የነጻነት ተምሳሌት በሆኑት ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩ. ኤስ. አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ግዛቶች እውነተኛ የፖለቲካ ሥልጣን አላቸው ብዬ አምናለሁ። በአካባቢያቸው ጉዳይ ላይ የማዕከላዊው መንግሥት ጣልቃ ገብነት ገደብ ተበጅቶለታል፤ ሕዝባቸው ሙሉ ሥልጣን ተጎናጽፏል። ስለሆነም ሥልጣን በጥቂቶች እጅ አልወደቀም። ይህም በመሆኑ አምባገነናዊ ሥርዓት እውን እንዳይሆን አድርገዋል ማለት ነው። የፖለቲካ ነጻነታቸውን ያወጁት የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች በኅብረትም ሆነ በግል የሚፈልጉትን ይሠራሉ፤ ልጆቻቸውም የወደዱትን የትምህርት ዓይነት ያጠናሉ። በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ (የፖለቲካ ነጻነታቸውን በተገፈፉ ሕዝቦች፣ ለምሳሌ ኢትዮጵያውያን) አንድ ሰው ወይም ቡድን በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች መፃኢ ዕድል ላይ ይወስናል (ኢትዮጵያውን ስለባሕር በር ጥያቄ፤ በሱማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ስለመግባት፤ ለሱዳን ገጸ-በረከት ሊሰጥ ነው ስለተባለው የድንበር ጉዳይ፤ ስለአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳይ ወዘተ. በተመለከተ እውን ሕዝብ መክሮበታልን? መልሱን ለታሪክና ለባለኅሊና ኢትዮጵያውያን)።
ነጻ በሆኑ ሀገራት የሚኖሩ ሕዝቦች ማንኛውንም ውሳኔ በራሳቸው ይሁንታ ያደርጋሉና ጥቅሞቻቸው ምንጊዜም ይከበራል። እኛ ግን ለዚህ አልበቃንምና ዝንተ ዓለም የደም እንባ እናነባለን፤ ምንጊዜም ሥልጣን ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ተጀምሮ ወደ ላይኛው ክፍል (መንግሥት) የሚሄድ ከሆነ፤ አብዛኞቹ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሔ ሊያገኙ እንደሚያገኙ ከምዕራባውያን ሀገራት ማየት የሚቻል ይመስለኛል። የእኛ ፈርኦኖች ግን መማር አልፈለጉም። ምክንያቱ ደግሞ ከሕዝቡ ጥቅም ይልቅ ለራሳቸው እና ለሎሌዎቻቸው ጥቅም ስለቆሙ ነው።
የሃይማኖት ነጻነት
የሀገራት እውነተኛ ጥንካሬ መሠረት የኃይማኖት ነጻነት ነውና የኃይማኖት ነጻነት እጅግ ወሳኝ ነጻነት ነው። የኃይማኖት ነጻነት የሚገኘው፣ የኅሊናና የሞራል የበላይነት ያላቸው ሰዎች መንግሥት በእምነት ተቋሞቻቸው ላይ እጁን እንዳይከት መከላከል ሲችሉ ነው። የኃይማኖት ነጻነት ውድና ብዙ ጊዜ የማይታይ ነው። ምክንያቱም በዓለም ታሪክ፣ በተለይ በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ከመንግሥት ቁጥጥር የወጡበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም፤ ካለም በጣም አጭር ጊዜ ሊሆን ይችላል፤ እርሱ የሾመውን እርሱ እስኪመልሰው …እየተባለ ሲነገር ያዳመጥን ይመስለኛል። ዛሬም ቢሆን የሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱ፣ ፍትሕ ሲጓደል …ለምን ብለው የሚጠይቁ አባቶች በአደባባይ አልታዩም።
ሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የኃይማኖት ነጻነታችን ይከበር በማለት ያነሡት ጥያቄ እስካሁን ድረስ ምላሽ አልተሰጠውም። ይህ የሚያሳየን የኃይማኖት ነጻነት ጉዳይ ችግር ውስጥ እንዳለ ነው። ጥያቄያቸው መልስ አለማግኘቱ ለእኔ እንቆቅልሽ ነው። ሁላችንም መረዳት ያለብን ጉዳይ ግን የኃይማኖት ነጻነት ለአንድ ሀገር ሕዝብ የሞራል የበላይነትን የሚያስገኝ መሆኑን ነው። አንድ አሜሪካዊ ጠቢብ እንዳለው፣ የአንድ ሀገር ሕዝብ ባሕርይና መንፈስ ሀገርን ታላቅ ለማድረግ ይረዳል። የሞራል የበላይነት ሲሸረሸር ሕግና ሕገ-መንግሥት ዋጋ ያጣሉ። ሕግ ዋጋ የሚኖረው ሕግ አውጪው ራሱ የሞራል ሰው ሲሆን ነው። የሕግ አውጪው ታላቅነት መሠረት ደግሞ የኃይማኖት ነጻነት የተጎናጸፈ ኅብረተሰብ በሀገሪቱ ሲኖር ነው።
እንደ መደምደሚያ
አንድ ሀገር ወደ ታላቅ ብልጽግና እና እድገት እንድትራመድ ከተፈለገ ፍቱን መድኃኒቱ ነጻነት ነው። በማንኛውም የኑሮ ደረጃ የዓለም ጭራ ሆነን የቀረነው ነጻነታችንን ስለተገፈፍን እንደ ሆነ ማወቅ ይገባናል። ኢትዮጵያውያን ድሮም ሆነ ዘንድሮ ነጻነታችንን በአምባገነን ገዢዎቻችን ተነጥቀናል። ስለሆነም ነጻነታችንን ለማስመለስ በኅብረትና በአንድነት መነሣት ይገባናል።
Leave a comment