tigist tadele
ትዕግስት ታደለ

የሰው ልጅ ኑሮውን ለማቅለል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በርካታ ምርምሮችን ቢያደርግም በሚያደርገው ምርምር የተነሳ የሚመጡበት የጎንዮሽ ጉዳቶች በርካታ ናቸው፡፡ በተለይ ከዚሁ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ሥራው ጋር በተያያዘ በራሱ በሰው ልጅ የሚፈጠሩ በጤናችን ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የበሽታ አይነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ ይገኛል፡፡ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ ይችላሉ ተብሎ ከሚታሰቡ በሽታዎች ውስጥ ፓርኪሰን ይገኝበታል፡፡ ዘንድሮ ዓለም አቀፍ የፓርኪንሰን ቀን ባሳለፍነው ወር መግቢያ ላይ ለ20ኛ ጊዜ ተከብሮ ውሏል፡፡
ፓርኪንሰን ምንድን ነው?
እንግሊዛዊው ሀኪም ፓርኪንሰን በ18 17 ዓ.ም በሽታውን በስድስት ሰዎች ላይ ካገኘ ከ40 ዓመት በኋላ በሽታው በስሙ ፓርኪንሰን ተብሎ የተሰየመ፡፡ የፓርኪንሰን በሽታው የሚከሰተው በአንጎላችን ውስጥ የሚገኙት የሰውነታችንን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩትን ዶፓሚን የሚባለውን ንጥረ ነገር የሚያመነጩት ሴሎች 85 ፐርሰንቱ ሲሞቱ ነው፡፡ ዶፓሚን በአንጎላችን ውስጥ ትእዛዝ የሚቀበለው ክፍልና የሚያስተላልፈውን ክፍል የሚገናኙበት ፈሳሽ ንጥረ ነገር ሲሆን የዚህ ንጥረ ነገር ሴሎቹ 85 ፐርሰት ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሲሞቱ ፓርኪንሰን ህመም ይከሰታል፡፡ ፓርኪንሰን የማይድን እና ህክምና የሌለው ጠቅላላ እንቅስቃሴን የሚያውክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት የሚሄድ እጅግ ከባድ የአእምሮ ህመም ነው፡፡
ፓርኪንሰን በኢንፌክሽን የሚመጣ ህመም አይደለም፡፡ ልክ እንደ ስኳር ህመም በኬሚካል እጥረት የሚመጣ ህመም ነው፡፡ የስኳር በሽታ በኢንሱሊኒ አለመስተካከል የሚመጣ ህመም እንደሆነው ሁሉ ፓርኪንሰን ደግሞ ዶፓሚን በሚባል ኬሚካል አለመስተካከል የሚመጣ ህመም ነው፡፡ ፓርኪንሰን ከስኳር ህመም የሚለየው የአንጎል ህመም በመሆኑና ልክ እንደስኳር በላብራቶሪ ምርመራ አለመታወቁ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የፓርኪሰን በሽታ አንዴ ከተያዙ በኋላ መዳን የማይችልና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ ነው፡፡
የፓርኪሰን መንስኤ
ፓርኪንሰን እስከዛሬ ባለው የሳይንስ እውቀት በእርግጠኝነት በምን እንደሚከሰት ባይታወቅም አንዳንድ መላምቶች ግን አሉ፡፡ ይኸውም ዶፓሚን የተባሉትን ንጥረ ነገሮች የሚያመርቱት ሴሎች የሚሞቱት ከዘረመል (ጄነቲክስ) የሚመጣ ችግር፣ የዕድሜ መጨመርና በተለይም ለበሽታው መከሰት የበለጠውን ድርሻ የሚይዘው ከአካባቢ ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች የሚመጣ መሆኑ ነው፡፡ ከአካባቢ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲባል ለምሳሌ ከተለያዩ የኬሚካል ፋብሪካዎች የሚወጡ የጥርስ ሳሙና ዝቃጮች፣ ጸረ አረም መድሃኒቶች፣ የፔትሮሊየም ተረፈ ምርቶች፣ የጉድጓድ ውሃና የጭንቅላት አደጋ የመሳሰሉት ለፓርኪንሰን በሽታ መጋለጥን ያስከትላል ተብሎ ይገመታል፡፡ በተለይም ከፀረ አረም መድሃኒት ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች በይበልጥ ለበሽታው ተጋላጭ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በእርሻ ሙያ በተሰማሩ እና ኬሚካል የሚጠቀሙ ሰዎች ከሌላው ኅብረተሰብ በበለጠ በፓርኪንሰን የመጠቃት ሁኔታቸው ከፍ ይላል፡፡
የፓርኪንሰን በሽታ ምልክቶች
የፓርኪንሰን ህመም ሲጀምር በጣም በትንሽ ምልክት ሲሆን ህመም መሆኑ ስለማይታወቅ ህመምተኛው መታመሙን ላይገነዘበው ይችላል፡፡ በትንሹ እጁ መንቀጥቀጥ ሲጀምር በሥራ ብዛት ሊመስለው ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ትከሻውን ጨምደድ ሲያደርገው በድካም ምክንያት ነው ሊባል ይችላል፡፡ ቀን በሄደ ቁጥር ግን ምልክቶቹ እየከበዱ እና እየተደጋገሙ ሲሄዱ ተጠቂው ችግር እንዳለበት ማሰብ ይጀምራል፡፡
የፓርኪንሰን ምልክቶቹ መንቀጥቀጥ፣ የሰውነት መተሳሰር፣ ሚዛንን አለመጠበቅ፣ ዘገምተኛ የሰውነት እንቅስቃሴ እና ሌሎችንም ከእንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ሊያጠቃልል ይችላል፡፡ የህመሙ አጀማመር ከሰው ሰው የሚለያይ ሲሆን ህመሙ በአንድ ጎን ብቻ ጀምሮ ወደሌላ የሰውነት ክፍሎች ቀስ በቀስ ሊዛመት ይቸላል፡፡ ለምሳሌ፣ የእግራ እጅ መንቀጥቀጥ ከጀመረ ወደ ቀኝ እጅ የሚተላለፈው ዘግይቶ ነው፡፡ በሌላው ሰው ደግሞ ከምላስና አገጭ ወይም ደረትና ወገብ ሊጀምር ይችላል፡፡ ምን ጊዜም ግን ፓርኪንሰን መንቀጥቀጥ ሲጀምር በአንድ ጎን ብቻ ነው፡፡ አንዳንድ የፓርኪንሰን በሽታ ምልክቶች ከሌላ ህመም ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ የሰውነት መኮማተር ቁርጥማት፣ጨምድዶ የመያዝ በፓርኪንሰንም ሆነ በሌሎች ህመሞች ላይ ሊታይዩ የሚችሉ ምልክቶች ናቸው፡፡
በዋናነት ፓርኪንሰን እንቅስቃሴን የሚያውክ ህመም ሲሆን ይህም የሰውነት የሞተር ህመም ተብሎ ይጠራል፡፡ የእነዚህ የሞተር ችግሮች ምልክቶቻቸው በረፍት ጊዜ የሰውነት አካል መንቀጥቀጥ፣ ዘገምተኛ የሰውነት እንቅስቃሴ ወይም አለመራመድ፣ የሰውነት መተሳስር ወይም ጨምድዶ መያዝ፣ ሚዛን የመጠበቅ ችግር፣ የፓርኪሰን ሞተር የሆኑ ምልክቶች ከታዩ ሞተርም ያልሆኑ ችግሮችም በተጓዳኝ ይከሰታሉ፡፡ ሞተር ያልሆኑ የበሽታው ምልክቶች ወይም ችግሮች የሚባሉት ደግሞ የእንቅልፍ ችግር፣ የንግግር ወይም የመዋጥ ችግር፣ ዘገምተኛ አስተሳስብ እና የማስታወስ ችሎታ መቀነስ፣ የሆድ ድርቀት፣የማሽተት ችሎት መጥፋት እና ሌሎችም ብዙ ምልክቶች ሊከሰቱ ይችላል፡፡
ለፓርኪንሰን በሽታ የሚደረግ ህክምና
የፓርኪንሰን ህመምን ለመለየት የሚደረግ የምርመራ አይነት የሌለ ሲሆን በላብራቶሪም ሆነ በኤክስሬ አይታወቅም፤ አዲስም በመጡት እንደ ሲቲ ስካን ወይም ኤም አር አይን የመሳሰሉት መሣሪያዎች ፓርኪንሰንን ሊያውቁት አይችሉም፡፡ ፓርኪንሰን የሚታወቀው በልምድ ህመሙ በሚያሳያቸው ምልክቶች በኑሮሎጂስት ህክምና አይነት የፓርኪንሰን ህመም መሆኑን ሊያውቅ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ኑሮሎጂስቱ ፓርኪንሰንን የሚለዩት የፓርኪንሰን መድሃኒት በመስጠት መድሀኒቱ ለውጥ ካሳየ በሽታው ፓርኪንሰን እንደሆነ ማወቅ ይቻላል፡፡ ሌሎች ምልክታቸው ከፓርኪንሰን ጋር ተመሳሳይ የሆኑ በሽታዎች ግን የፓርኪንሰን መድሀኒት ቢሰጣቸውም ለውጥ አያሳዩም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ባለ የህክምና ጥበብ ፓርኪንሰንን የሚያድን መድሃኒት የለም፡፡ መዳን የማይችል ህመም ቢሆንም ግን በሽታውን የሚስታግሱ ጥሩ የሚባሉ መድሃኒቶች አሉት፡፡ አማራጭ የህክምናው መርህ በተቻለ መጠን በህመሙ የተጠቁ ሰዎች የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ ማስቻል ነው፡፡ አንድ ህመምተኛ ጥሩ ህክምና ሊጀምር የሚችለው በዶክተሩና በታማሚው ቤተሰብ መካከል ያለው ጥሩ ግንኙነት ከተመሰረተ ብቻ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ግንኙነት ከተመሰረተ ትክክለኛ መድሃኒት መምረጥ ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ የአኗኗር ሁኔታም ጭምር ለመምረጥ ያግዛል፡፡ ይህን አይነት መረጃም ለማድረስ ህመምተኛው ስለህመሙ በቂ የሆነ ዕውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡ ህመሙንና ምልክቶቹን ለማስታገስ መድሀኒት ብቻ መውሰድ ሳይሆን የአኗኗር ሁኔታ ለመቀየር መስማማት ያስፈልጋል፡፡
ፓርኪንሰን በማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ባሉ ሰዎች ሊከሰት የሚችል ሲሆን በአብዛኛውን ጊዜ የሚያጠቃው ከ60 ዓመት በላይ ያሉትን የእድሜ በለፀጋዎችን ቢሆንም 15% የሚሆኑ የፓርኪሰን ህሙማን ከ60 ዓመት በታች ከ20 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ያሉ ናቸው፡፡ የፓርኪንሰን በሽታ ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ላይ በአብዛኛው ጎልቶ የሚታይ ሲሆን በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር የፓርኪንሰን በበሽታ ተጠቂ ዜጎች ያሏት ሀገር አልባንያ ስትሆን ከአፍሪካ ደግሞ ግብጽ ነች፡፡ በሀገራችን በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች የሌሉ ሲሆን ከዛሬ 30ዓመት በፊት በተደረገው ጥናት ግን ከ100ሺህ ሰዎች መካከል 7ቱ የፓርኪሰን በሽታ ተጠቂዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ፓርኪሰን በሀገራችን
በሀገራችን ምን ያህል የፓርኪንሰን ህሙማኖች እንዳሉ የተደረገ ጥናት የሌለ ሲሆን በአንድ ወቅት ‹ፓርኪሰን ፔሸንትስ ስፖርት ኦርጋናይዘሽን – ኢትዮጵያ › ማኅበር ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ከጤና ጥበቃ ተወክለው የመጡ ግለሰብ መሥሪያ ቤታቸው ፓርኪሰንን በተመለከተ ብዙም መረጃው እንደሌለውና ወደ ፊት በችግሩ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልጸው ነበር፡፡ ‹ፓርኪሰን ፔሸንትስ ስፖርት ኦርጋናይዘሽን – ኢትዮጵያ › ከአምስት ዓመት በፊት የፓርኪንሰን ችግር ባጋጠማቸው በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች የተመሰረተ ድርጅት ሲሆን የማኅበሩ መስራችና ኃላፊ ወይዘሮ ክብሯ ከበደ ለዚህ ጽሁፍ አቅርቢ እንደተናገሩት ከሆነ፣ በሀገራችን በርካታ የፓርኪንሰን በሽተኞች ቢኖሩም በህክምና ተቋማትም ሆነ በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለ በሽታው ምንነት በቂ የሆነ ግንዛቤ ስለሌለ ችግሩ የገጠማቸው ሰዎች በርካታ መሰናክሎች ይገጥማቸዋል፡፡
ይህ ማኅበር የፓርኪንሰንን ህምተኞች በመደገፍ የሚገኝ ብቸኛ ማኅበር ሲሆን አጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ ከ279 ባላይ አባላትን በማቀፍ በሽታው ምን እንደሆነ ለታማሚዎችና አስታማሚዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከመስጠቱ በተጨማሪም የሚታዘዝላቸው የተለያዩ የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶች መቋረጥ ስለሌለባቸው በጣም ችግረኛ ለሆኑት አባላት የመድኃኒት መግዣ ገንዘብ ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል፡፡ በሀገራችን ያሉ አብዛኞቹ ታማሚዎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሲሆኑ እንደውም አንዳንድ የማኅበሩ ከአባላቶች በልመና ስራ የሚተዳደሩ መሆናቸውን ወ/ሮ ክብሯ ይናገራሉ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ አንድ ሰው በፓርኪንሰን በሽታ ሲጠቃ ሥራ መስራት ስለማይችል ህመምተኛው ሌላ የገቢ ምንጭ ከሌለው በስተቀር በፍጥነት ወደ ድህነት ማሽቆልቆሉ የማይቀር ስለሆነ ነው፡፡
ፓርኪንሰን እንደማንኛውም ህመም ህመም ስለሆነ ኅብረተሰቡ ይህን በመረዳት ታማሚዎቹን ማበረታታትና መደገፍ ይኖርበታል፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ደግሞ በዘርፉ የሰለጠኑ በቂ ባለሙያዎችን በማፍራትና ለታማሚዎች ድጋፍና ክትትል የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል፡፡

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *