ሰላማዊት አበበ
venesiak@gmail.com
ያለነው የነጻነት ሀገር፤ ግን እንቅስቃሴያችን የተገደበ፡፡ ያለነው የሰላማዊ ሀገር፤ ግን ውስጣችን ብጥብጥ እና ጦርነት! ያለነው በምንኖርበት አለም፤ በገሀድ የምንኖረው ደግሞ የማንኖርበትንና ያልተጻፈበትን የቅዠት አለም፡፡ ሀብታም ሲኖር ድሃ ሲያኗኑር መመልከት፡፡
በጣም ነው የሚገርመኝ! የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ያልተመቻቸና የሚጎረብጥ የኑሮ ዘይቤን አሜን ብሎ ከተቀበለ ውሎ አድሯል፡፡ አይናገር ነገር ከፊቱ የሚጠብቀውን የጨለማ ኑሮ ይፈራል፡፡ (ለነገሩ ከበጣም መጥፎ መጥፎ ተመርጦ ነው እንጂ ጨለማው እንኳን አልቀረልንም) ‹‹ህገ-መንግስታችን ይፈቅዳል›› ብሎ ቅሬታ እያሰማ ነገር፤ የጽሑፍ እንጂ የተግባር ሀገር ላልሆነችው ኢትዮጵያ የመደፈር ያህል ከባድ ይሆንና መጨረሻው እስር ወይም ዱላ አነስ ሲል ደግሞ ዛቻ ይቀምሳል፡፡

ስለዚህ ያለን አማራጭ ምንድን ነው? ቢሉ እንደምንም ታትሮ ፊደል ይቆጠርና በምሁራን የተቀረጸውን እውነት ሆኖ ብንመራበት ኖሮ እጅግ የሚጠቅመንን ህገ መንግስታችንን እያነበብን ሳንኖርበት መኖር ብቻ ነው፡፡ እስቲ አስቡት፣ አንድ የተራበ ሰውን ስጋ ወጥ እያሳዩ ዳቦ በሻይ እንደማብላት ማለት ነው፡፡

‹‹እሱንስ ማን አየበት?›› ትሉ ይሆናል፡፡ ‹‹አይደል?›› አዎ! በየገጠሩ እና ክፍለ ሀገሩ ወገናችን ይጫረሳል፤ በየክልሉ ህዝባችን በርሀብ ያልቃል፡፡ አዲስ አበባ መንግስታችን ባቡር ይሰራል፤ ህንፃ ይገነባል፡፡ እውነት ነው እሱንስ ማን አየበት?!

በየድንበሩ ህዝባችን ዘር እየሰነጠቀ ይፋጃል፤ የእኛ መንግስት ለአለም ሰላም ያውጃል፡፡ ‹‹እሱንስ ማን አየበት?›› በሙስና ኪሳቸው ያበጠ ባለሥልጣን የድሃ መሬት እየቀሙ በቤት ላይ ቤት ይገነባሉ፡፡፡ መንግስታችን ድሃውን ህዝብ ጫካ እንዲያለማ ይልከዋል፡፡ እውነት ነው፣ ‹‹እሱንስ ማን አየበት?!››

አሁን በቅርቡ በጋምቤላ የተገደሉ ሰዎችን ከምንም ሳይቆጥር ሙሉ ቀን ሁሉም ሬዲዮናችን እና ቴሌቭዥኖች ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ ዘፈን ሲያዘፍኑና በተለመደው የአውሮፓ እግር ኳስ ዜና ነው የአየር ሰዓቱን ሲያጣብቡ የነበረው፡፡ በጋምቤላ የተገደሉ ሰዎችን መንግስታችን እንደ ኢትዮጵያውያና ቆጥሯቸዋል ወይ? የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ሀያ አምስት አመት ሙሉ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት እያለን ጆሯችን እስኪደማ የሰማነው እና አሁን ላይ የታዘብነው እውነታ ቢኖር ዛሬም የሰብዓዊነት ክብር፣ መብትና ልዕልና የተነፈገን መሆኑም ነው፡፡ ለነገሩ፣ በስተመጨረሻ የሁለት የሀዘን ቀናት ታወጀ፡፡ በእለቱ ጨፍረን በሰልስቱ ማዘን የሚገርም ይሆናል እንጂ፡፡ እሱንስ ማን አየበት? አላችሁ፡፡ እሺ ልቀጥላ …

አዎ! የኢትዮጵያ ህዝብ ልባችን ንፁህ ነው፡፡ ሁሉን በመልካም ስለምናይ ‹‹እሱንስ ማን አየበት?!›› እንላለን፡፡ ቢያንስ ባናወራ እንኳን ዝምታችን አይነጠቅም፡፡ ባይደላንም አናጉረመርምም፡፡ ባንጮህም መጻፋችንን አንከለከልም፡፡ ስለዚህ ደግመን እንላለን፣ ‹‹እሱንስ ማን አየበት?!

አሁን መፍትሔውን ልጠቋቁም መሰል፡፡ ችግር ነቀሳ ብቻ ምን ይፈይዳል ታዲያ? እንግዲህ እላለሁ፣ ፈሪ ለእናቱ፤ ፈሪ ለልጁ ነውና የምንታገለውን እና የሚታገለንን ልንለይ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዴም እኮ ስንሞት መቃብራችን ላይ የሚነበብልንን ታሪክ ማሳጠር የለብንም፡፡ በቃ ‹‹እገሌ/እገሊት በዚህ ዓ.ም ተወለደ/ች …ከዛ ሞተ/ች፡፡›› እንዲባልንን ባናደርግ ይበጃል፡፡ ስለዚህ …

ጮክ ብሎ ማውራት ቀርቶ ማልቀስ የማይፈቀድባት ሀገር ላይ ያለው አንድና አንድ መፍትሔ ፀሎት ብቻ ነው፡፡ ሁሉም በየእምነቱ በርከክ ብሎ በድምጽ አልባ ጩኸት ጥሪ ወደ ላይ ማሰማት ብቻ፡፡ ያኔ አንድ ሐይል ይመጣል፡፡ የፈርዖንም አገዛዝ ይሰበራል፡፡ ዋናው ነገር ማመንና በፍቅር ሆኖ መፀለይ ብቻ ነው፡፡

በዘር፣ በኃይማኖትና በቀለም ሳንለያይ የሁላችንም ልብ ሳይከፋፈል፤ አንድ ሆኖ መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ህዝቤ ሆይ ተነስ! …የተኛህ ንቃ …የደከመህ በርታ እና …ተነሱ፡፡ አዎ! ተነሱ …… ለፀሎት፡፡

አበቃሁ፡፡ መልካም በዓል፡፡

ቸር እንሰንብት፡፡

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *