ፌዴሬሽኑ ፈርሷል፤ የእርቀ-ሰላም ጉባዔ ባስቸኳይ ይጣራ!

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዴ.ሪ) በታላቅ ህዝባዊ – እምቢተኝነት ሳቢያ ‹ፌዴራላዊ› የሚባለውን ስርዓት ካቆሙት ክልሎች ውስጥ በትልቅነቱ የሚጠቀሰው የ‹‹ኦሮሚያ›› ክልል በወታደራዊ አስተዳደር ውስጥ ገብቷል፡፡ የክልሉ የይስሙላ ‹አስተዳደሪ› የሆነው የኢህአዴግ አባል ግንባር ኦ.ህ.ዴ.ድም በህዝባዊው ተቃውሞ ምክንያት ህልውና በገቢር ተዳክሟል፤ አክትሟል፡፡

በሀገሪቱ ደቡባዊ እና ምዕራባዊ አካባቢዎችም ከፍተኛ የህዝብ ‹‹አልገዛም ባይነት›› መንፈስ መነሳሳት ተፈጥሯል፡፡ ማዕከላዊ ‹መንግስቱ›› በዝቅተኛ ደረጃ ያለ ስርዓትና ሰላምን እንኳ አስፍኖ፣ ህዝብን አረጋግቶ ሊመራ የሚያስችለውን የሞራል፣ የፖለቲካም፣ የጸጥታም፣ የበላይነት አጥቷል፡፡ ህዝብ በያለበት ራሱን ወደሚያስተዳድርበት አደረጃጀት ተራምዷል፡፡ ከአንድ ወር በፊት ‹‹አዲስ ገጽ›› መጽሔት ሰፊ ቃለ-ምልልስ አድርጋላቸው የነበሩት የመንግስት ኮሙዩኑኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ‹‹ሀገሪቷ በአሁን ወቅት በምን አይነት ሰላምና መረጋጋት ላይ ትገናለች? በተለይ ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ የክልል ከተሞች፣ ዞኖችና ወረዳዎች…›› ለሚለው የመጽሄቷ ጥያቄ ‹‹ሀገሩ ሠላምና ፀጥታ ላይ ነው፡፡ ግን እንደ አተያይህ ይወሰናል፡፡ …ሀገር ሠላም ነው የሚባለው፣ ወይ አያልቅብሽ ጠጅ ቤት የሚጣሉ ሠዎች ስለሌሉ አይደለም፡፡ …›› ሲል ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን ከሚኒስትሩ መልስ በተቃራኒው ሀገሪቷ ‹‹ትልቅ የአያልቅብሽ ጠጅ ቤት›› መስላ በተለያዩ ቦታዎች ተቃውሞና አለመረጋጋት በግልጽ እየታየ ይገኛል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ተገቢውን ኃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርም እነአቶ ዳባ ደበሌን ከኃላፊነታቸው ማንሳቱ ይታወቃል – ይህ ግን ‹‹ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም›› የሚለውን ሀገራዊ ብሂል የሚያረጋግጥ እንጂ አንዳች ፋይዳ ያለው መፍትሄ የማያመጣ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፡- በአገሪቱ ሰፊ ክፍል ላይ በተከሰተው አስከፊ ድርቅ/ርሃብ ሳቢያ አያሌ ዜጎች ለህልፈት እየተዳረጉም ነው፡፡ በዚህ 24 ዓመታት ውስጥ ያልታየ አስከፊ ድርቅ በተባለው የከፋ ክስተትም አገዛዙ ተፈትኖ ክፉኛ ወድቆበታል፡፡ የዚህን ችግር በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖችም እንደሚናገሩት ከሆነ ችግሩ ሥር እየሰደደ መምጣቱን ነው፡፡

ገዥው ሃይል ከዚህም ከዚያ እየተፈጠሩበት ያሉትን ችግሮች የመቋቋም አቅሙ ከጊዜ ወደጊዜ እየላሸቀ መሆኑን አስረጂ ምክንያቶች እንደአሸን ፈልተዋል፡፡ የገዥው ሀይል ችግር አፈታትም ቢሆን በሕግ አግባብ ሰላማዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ሀይልን በመጠቀም በጠብ-መንጃ ተኮሶ የንጹሃንን ህይወት መቅጠፍን እንደፈሊጥ ይዞታል፡፡

በመሆኑም ‹‹አዲስ ገጽ›› ከሀገራዊው ችግር መውጫ ትክክለኛ መፍትሄ ማበጀት እንዲቻል ሁሉን የፖለቲካ፣ የኃይማኖት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላትን በእኩልነት የሚያሳትፍ ‹‹ብሔራዊ የዕርቀ ሰላም ጉባዔ›› በአስቸኳይ መደረግ እንዳለበት ታሳስባለች፡፡

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *