ፍርድያውቃል
ፍርድያውቃል ንጉሴ
firdyawkal@gmail.com

እውን የሚጠቅመን የቱ ነው?
GK፤ ANTI-GK፤ ወይስ…?

እንደመንደርደሪያ
የዛሬ አምስት ዓመት ግድም ነው፡፡ የአበበ ቢቂላ መታሰቢያ የማራቶን ውድድር በመስቀል አደባባይ ሊጀመር ጥቂት ደቂቃዎች ቀርተውታል፡፡ እኔና የሙያ አጋሬም ውድድሩ እስኪጀምር ሻይ ቡና ለማለት በአቅራቢያው በሚገኝ ካፌ ውስጥ ቁጭ አልን፡፡ ከዛም ስለ ሀገራችን እግር ኳስ አነሳንና የየራሳችንን እምነት እየገለፅን ሳለ ድንገት በጨዋታችን መሃል ‹‹ጂኬ›› ስለተባለው የአሰለጣጠን ሁኔታ ሲነሳ አብሮኝ የነበረው የሙያ አጋሬ ድንገት እንደመበሳጨት ብሎ ‹‹ባክህ እነርሱን ተዋቸው፡፡ በተለይ እከሌ የተባለው የእናንተ ቢሮ ጋዜጠኛ በጣም ያናደኛል፡፡ እሱ ኮ የገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ደቀ-መዝሙር ነው፡፡›› በማለት ተናገረ፡፡ እኔም በሁኔታው ተገረምኩ፡፡ በተለይ ደግሞ ያ ስሙን ያነሳው ጋዜጠኛ በጂኬ ፍልስፍና የሚያምን ቢሆንም ይህ የግል እምነቱ ከገነነ ደቀ-መዝሙርነት ጋር መያያዙ አግባብ አለመሆኑን ስለማውቅ ‹‹ተው እንጂ! እርሱ በግሉ በጂኬ ፍልስፍና ማመን አይችልም እንዴ? ሌላው ቀርቶ ለስፖርቱ ቅርብ የሆነ፤ ስፖርቱን ጠንቅቆ የሚያውቅ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ጂኬንስ የደገፈ በሙሉ ግለሰባዊ መብቶ ተገፎ የገነነ ደቀ-መዝሙር የሚል ታፔላ ነው የሚለጠፍበት?›› በማለት ጥያቄ አዘል ተግሳፄን አቀረብኩ፡፡
በርግጥም እኔ እስከዛሬ በሰራሁባቸው የኤሌክትሮኒክስና የህትመት ሚዲያዎች ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች በተለይ ለሀገራችን እግር ኳስ መጎልበት ይበጃል ያሉትን የአጨዋወት ፍልስፍና ፕሮግራሞቻቸው ያንፀባርቃሉ፡፡ (አልፎ ተርፎም ሙያው ከሚፈቅደው ሥነ-ምግባር ውጪ በመሆን በአሰልጣኞች ቅጥር ላይ ጣልቃ እስከመግባት የሚደርሱም አይጠፉም፡፡) እነዚህን ትተን ወደ ርዕሳችን ስንመለስ ሁላችንም የስፖርት ጋዜጠኞች ለሀገራችን እግር ኳስ የሚበጅ ነው ብለን የምናምንበት የየራሳችን የሆነ አስተሳሰብ እና እምነት ይኖረናል፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ ደግሞ የሌሎች ሰዎች አመለካከት ላይ ተፅዕኖ የማሳደር እድሉ ሰፊ ነውና እኛን የሚያደምጡ፤ እኛ የፃፍነውን የሚያነቡ ሰዎችም በየፊናቸው የየራሳቸውን አመለካከት አዳብረው ‹‹ለሀገራችን እግር ኳስ የሚበጀው ይህ ነው፤ ይህ አይደለም›› እያሉ ሲናገሩና ሲሟገቱ ይደመጣሉ፡፡
የሰሞኑን ትኩሳት
በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደአልጀሪያ ተጉዞ በአልጀሪያ አቻው 7 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት መረታቱን ተከትሎ፤ እንዲሁም ደግሞ ክለቦቻችን ከአህጉራዊ ውድድሮች በጊዜ ከተሰናበቱ በኋላ ይሄ ቀዝቀዝ ብሎ የነበረው ሁለት ጎራን ለይቶ የመናቆርና የመነታረክ ነገር አሁን በአዲስ መልኩ ተጧጡፏል፡፡
በርግጥ ከንግግር ነፃነት አንፃር ሁሉም ያመነበትን ነገር ይበጃል ብሎ መናገሩ ብዙም ክፋት የለውም፡፡ ግና ካለን አስቀያሚው የአስተሳሰብና የምግባር ዝቅተኛ ደረጃ አንፃር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሲያመዝን እያስተዋልን ነው፡፡
እንደሚታወቀው አንድ ነገር የግድ ሁሉንም ሰው ማስማማት ላይጠበቅበት ይችላል፡፡ ሁሉም ሰዎችም የግድ አንድ አይነት አስተሳሰብን ማንገብ አይጠበቅባቸውም፡፡ ይሔ ማለት ግን ሰዎች የራሳቸውን ግላዊ እምነትና አመለካከት ሲይዙና ያንን እምነታቸውን ሲያንፀባርቁ ግን መኮነን፣ መዝለፍና ማንቋሸሽ አለባቸው ማለት አይደለም፡፡
ሁሉም ሰው እንደየምርጫውና እንደየፍላጎቱ የራሴ የሚለውን አቋም መያዝ የማይናድና መቼም የማይሻር መብቱ ነው፡፡ ግና ይህ ሰው የእኔ ያለውን የግል እሳቤዎቹን በሚናገርበት፣ በሚገልፅበትና በሚያንፀባርቅበት ሰዓት የራሱን የዳበረ እሳቤ በዳበረ መልኩ ቢያቀርብ ይሻላል እንጂ ከእርሱ ተቃራኒ የሆነ እሳቤ የያዘን ሰው በመዝለፍና በማጣጣል ላይ የተመሰረተ አካሔድን ከተጠቀመ ትርፉ ትርፍ የለሽ ነው፡፡ ከዛ ይልቅ ጊዜውንና ቃላቱን ቆጥቦ የራሱን እሳቤ በምሳሌና በጥናት አስደግፎ ቢናገርና ቢፅፍ ነው ውጤታማ ሊሆን የሚችለው፡፡ ምክንያቱም ሌላው ቢቀር ያነሳው ሃሳብ ሌሎችን የማሳመን አቅሙ ይጨምራልና፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ይህንን የአንዱን ግለሰብ አስተሳሰብ የሰማን ወይም ያነበብን ሰዎች ተቃውሞ አሊያም ድጋፋቸውን መስጠት ያለባቸው ተገቢና አስተማሪ በሆነ መልኩ መሆን አለበት፡፡ እኛ ዘንድ ግን ይህ እሴት የሩቅ ሀገር ተረት ሆኗል፡፡
ጉንጭ አልፋ ሰጣ ገባው
አዎ! ሰሞኑን ከዚሁ ከብሔራዊ ቡድናችንና ከክለቦቻችን አጨዋወት ጋር በተያያዘ በተለያዩ የማኅበረሰብ ድረ ገፆች ላይ (በተለይ በፌስ ቡክ ላይ) እየተሰጡ ያሉት አስተያየቶች ባግባቡ ግላዊ ምልከታዎችን ተንትኖ ከማቅረብ ይልቅ የበለጠ ትኩረታቸውን ያደረጉትና ያዘነበሉት በመነቃቀፉ፣ በመዘላለፉና ‹ከእኔ በላይ ላሳር› የሚል አጉል ትምክህት የተጫናቸው አስተያየቶችን በመስጠቱ ላይ ነው፡፡
ይሔ ደግሞ ሌላው ቀርቶ ከሁለቱም ገለልተኛ የሆነውን አንባቢ ስለ ጂኬም ሆነ ከጂኬ ተቃራኒ ሆኖ ስለቆመው የአጨዋወት ዘይቤ ምንም አይኔ ግንዛቤ እንዳይኖረው መንገዱን የሚዘጋና በርግጥም የሚበጀን የትኛው እንደሆነ እንዳንረዳ ጋሬጣ የሚሆንብን የተራ ማንነት ውጤት የሆነ ተራ ተግባር ነው፡፡
ከዚህ እውነታ አንፃር አንድ ነገር ልብ ልንል ይገባል፡፡ አዎ! ለሀገራችን እግር ኳስ የሚበጀው የቱ ነው በሚል ጎራ ለይቶ መወያቱና ሃሳብን ማንሸራሸሩ የሚጠቅም ጉዳይ ቢሆንም ይህንን ሒደት ባግባቡ እየተገበሩ ከመወያት ይልቅ ሰርክ ስድብና ዘለፋ ላይ ተንጠልጥለን ራሳችንን ለመግለፅ የምንሞክር ከሆነ አንድም ጊዜን ከማባከን ውጪ ምንም ፋይዳ አይኖረውም፡፡ አንድም ደግሞ ‹‹ትሻልን ሸኝቼ ትብስን አመጣሁ›› እንደሚባለው በፍጥነት ወደኋላ እየተጓዘ ያለውን እግር ኳሳችንን የበለጠ የሚያቀጭጭና ሙያተኞቻችንም በጭፍን ጥላቻና ፍረጃ ተጋርደው ለሀገራችን የእግር ኳስ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጾ እንዳያበረክቱ እንቅፋት የሚሆን ሒደት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ይህ አባዜያችን ቢታረም መልካም ነው፡፡
መፍትሔው
ይህ አሁን በተጧጧፈ መልኩ እየተከናወነ ያለው የእነዚህ ሁለት ጎራዎች ጭቅጭቅ ላይ ተሳታፊ የሆኑት አካላት ጋዜጠኞች፣ አሰልጣኞችና ለስፖርቱ የጠለቀ ፍቅር ያላቸው ግለሰቦች ናቸው፡፡ ታዲያ በዚህ መልኩ በተናጠል ሆነው የሚታኮሷቸው የቃላት ጥይቶች ምንም ፋይዳ እንደሌላቸው በመረዳት የጋራ መድረክ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡
አዎ! በዚህ አታካራ ላይ ተሳታፊ የሆኑ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት ያሉ የስፖርት ጋዜጠኞቻችን፣ አሰልጣኞቻችን፣ የስፖርቱ ባለሙያዎችና የተመረጡ የስፖርቱ አፍቃሪዎች በጠቅላላ በጋራ የሚሰባሰቡበትና እነዚህን ተናጠላዊ አስተሳሰቦቻቸውን በጋራ መክረው ወደ አንድ የመፍትሔ ሃሳብ የሚያመጡበት መድረክ ቢያዘጋጁ መልካም ነው፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች እነርሱ ይህን መድረክ ማዘጋጀት ባይችሉ እንኳን የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነውና የገዘፈ ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዝም ብሎ በጨዋታ ማግስት የአሰልጣኞችን ሹም ሽር ከማድረግ በዘለለ መልኩ ለእነዚህ አካላት በጋራ የሚመክሩበት አንድ የጋራ መድረክ አዘጋጅቶ በርግጥም ከእኛነታችን፣ ከተጨባጭ የኢትዮጵያዊነት ሁኔታዎቻችን አንጻር ለእግር ኳሳችን የሚበጀው መንገድ የቱ እንደሆነ ቢታይና ቢሞከር በአብዝኻው ተጠቃሚ እንሆናለን ብዬ አምናለሁ፡፡
ምን አልባትም በሀገራችን ፖለቲካ ላይ ጎራ ለይቶ መባላቱ ምንም ፋይዳ ለሀገራችን እንዳላመጣ በማስተዋል በእግር ኳሱ ይህን መድረክ ማዘጋጀት ለእግር ኳሳችን ማደግ ከፍተኛ አስተዋጾ ከማበርከትም ባለፈ ለሀገራችን ፖለቲካ አስተማሪ ሆኖ ያልፋል፡፡ ስለዚህ እንደኔ እንደኔ ለሀገራችን እግር ኳስ የሚበጀው አጣዳፊውና ዘላለማዊው መፍትሔ የጂኬ ፍልስፍና ወይም የጸረ ጂኬ ፍልስፍና ሳይሆን ከእኛነታችን አንጻር የተቃኘ፣ በሁለቱ ፍልስፍናዎች መሃል ያለውን ልዩነት በጋራ አጢኖ፤ ለሀገራችን እግር ኳስ የሚበጀውን ፍልስፍና በጋራ ማበልጸግና ሁላችንም እንደየእውቀታችን ለዚህ እሴት መሳካት የየበኩላችንን አስተዋጾ ማበርከት ይጠበቅብናል፡፡
እንጂ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ የሚሔደው እግር ኳሳችን ላይ የባሰ እኛ ጎራ ለይተን ሰርክ የምንነታረክ ከሆነ የእግር ኳሳችን ቅስል ላይ እንጨት መስደድ ነው የሚሆነው፡፡

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *