ፍርድያውቃል ንጉሴ

firdyawkal@gmail.com

 

መፍትሔዎቹ…

ባለፉት ሁለት እትሞች ላይ በሚዲያዎቻችን ዘንድ የሚቀርቡት የስፖርት ፕሮግራሞች ላይ ስለ እግር ኳስ ብቻ መወራቱና ሌሎች ስፖርቶች ከነጭራሹ መረሳታቸው ያለውን ተግዳሮትና አሳሳቢነቱን ለመግለፅ ሞክሬያለሁ፡፡ በቀጠሮዬ መሰረት በዚህ ሳምንት ደግሞ ይህ የተበላሸ አካሔድን ማስተካከል የሚቻልባቸውን የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚከተለው ዳስሻለሁ፡፡

የስፖርት ኮሚሽኑ ሃላፊነት

በሀገራችን ያሉ ሁሉም የስፖርት አይነቶች ያድጉና ይጎመሩ ዘንድ ትልቅ ኃላፊነት የተጣለበትና ይህንንም ሂደት የእቅዱ ዋነኛ አካል አድርጎ የያዘው የኢ.ፌ.ድ.ሪ. ስፖርት ኮሚሽን በዚህ ዘመን ባሉ የሬዲዮ ጣቢያዎቻችን የስፖርት ጋዜጠኞች በሚያቀርቧቸው ፕሮግራሞች በሙሉ ሌሎች የስፖርት አይነቶችን ረስተውና ትተው እግር ኳስ ላይ ብቻ አተኩረው ሲሰሩና ሌሎች የስፖርት አይነቶች ከነጭራሹ ሲረሱ ነገሩን ዝም ብሎ መመልከት የለበትም፡፡

እንደሚታወቀው አንድ የስፖርት አይነት በየሚዲያዎቹ በተዘገበ ቁጥር የእዛ ስፖርት አትሌቶች ይነቃቃሉ፤ ኅብረተሰቡ መረጃን ከማግኘት ባለፈ የስፖርቱ ተሳታፊ ይሆናል፤ ባለሀብቶች ወደ ስፖርቱ ሊሳቡ ይችላሉ፤ …ብቻ በአጠቃላይ ስፖርቱ የማደግ እድሉ ይጨምራል፡፡ በተቃራኒው አንድ ስፖርት በሚዲያ አውታሮች ከተረሳና ካልታገዘ ግን እድገቱ መቀጨጩና ወደኋላ ማዝገሙ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ታዲያ ከእግር ኳስና ከአትሌቲክስ ውጪ በሀገራችን ያሉ የስፖርት አይነቶች ምን አይነት ይዞታ ላይ ናቸው? ብለን ከጠየቅን የምናገኘው መልስ ‹‹ምንም›› ነው፡፡ አዎ! ሌላው ቀርቶ እነዚህ ስፖርቶች በሀገራችን ውስጥ መዘውተራቸውን ከመርሳታችን የተነሳ በአሁኑ ሰዓት እውን እየተከናወኑ ነው እንዴ? ብለን ልንጠይቅ ራሱ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ስለነዚህ ስፖርቶቻችን በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን አንድም ቀን ሲሰራና መረጃ ሲሰጥ አንሰማም፡፡

በርግጥ ለየስፖርቶቹ የጠለቀ ፍቅር ያላቸው ግለሰቦች እንደየምርጫቸው ስፖርቶቹን ይከታተሉ ይሆናል፡፡ ግና በሀገር ደረጃ እኛ ከነዚህ ስፖርቶች ጋር ያለን ትስስር ምን ያህል ነው? ካልን አሁንም መልሱ ‹‹ምንም›› ነው፡፡ እነዚህ ስፖርቶች አሁን ላይ በሀገራችን በጣም ለመዳከማቸው በየሚዲያው ስለነርሱ አለመወራቱ ዋናው ምክንያት ባይሆንም ሚዲያው ስለነርሱ አለማውራቱ ግን ለስፖርቶቹ መዳከም ራሱን የቻለ ጉልህ ምክንያት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እነዚህን ስፖርቶች ለማሳደግ ሰርክ እውተረተራለሁ የሚለው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ስፖርት ኮሚሽን ይህንን የተንሸዋረረ አካሄድ ማስተካከልና ነገሮች በተፈላጊው መልኩ እንዲጓዙ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ግዴታውም ነው፡፡

ለምሳሌ አሁን ላይ ያሉትንና ወደፊትም የሚቋቋሙትን የሚዲያ አውታሮችን የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ስለጉዳዩ አሳሳቢነት ተረድተው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ ይቻላል፡፡

ከዚህ ባሻገር የስፖርት ፕሮግራሞችን ከሚያዘጋጁ የስፖርት ጋዜጠኞች ጋር ተመሳሳይ መድረክ አዘጋጅቶ ሁሉንም የስፖርት አይነቶች መዘገብ እንዳለባቸው መምከርና ከዛም ባለፈ በተጨባጭ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊውን በጀት በመመደብ እነዚህ የስፖርት አይነቶች በሚከናወኑባቸው ስፍራዎች ላይ ጋዜጠኞች ተገኝተው እንዲዘግቡና ሽፋን እንዲሰጡ ለእነርሱ አስፈላጊ የሆኑ የአበልና የትራንስፖርት ሁኔታዎችን በመሸፈን ዛሬ ላይ የተዛነፈውን አካሔድ በፍጥነት ማስተካከል ይቻላል፡፡

ይህ አካሄድ ደግሞ የኢ.ፌ.ድ.ሪ ስፖርት ኮሚሽን ብዙም የሚከብድ ጉዳይ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ይህንን ማድረግ አንዱ ስፖርቱን የማልማት አካሔድ ነውና ለነዚህ ሒደቶች አስፈላጊውን በጀት መድቦ ቢንቀሳቀስ ውጤቱ ኪሳራ ሳይሆን ትርፍ ነው የሚሆነው፡፡

የየጣቢያዎቹም ሃላፊነት

በሀገራችን ያሉ ሁሉም የሚዲያ አውታሮችም ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በራሳቸው ጋዜጠኞችም ሆነ በተባባሪ አዘጋጆች በሚዘጋጁ የስፖርት ፕሮግራሞች ላይ ከእግር ኳስ እና ከአትሌቲክስ በተጨማሪ ሌሎች ስፖርቶቻችንንም መዘገብን እንደ አንድ መስፈርት አስቀምጠው ቢንቀሳቀሱ ተፈላጊው ለውጥ መምጣቱ አይቀርም፡፡

ለምሳሌ በየጣቢያው የሚቀርቡት የስፖርት ፕሮግራሞች የአንድ ሰዓት ርዝማኔ ያላቸው ከሆኑ ግማሽ ሰዓቱን ለሌሎች ስፖርቶቾቻችን ሰጥቶ ግማሹን ሰዓት ደግሞ እንደአዘጋጆቹ ምርጫ የፈለጉትን ፕሮግራም እንዲያቀርቡ ቢደረግ ማንም አይጎዳም፡፡ ሀገራችንና ስፖርታችን ግን በአብዛኛው ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ምክንያቱም ይህን ሂደት ሁሉም የሚዲያ አውታሮች ከተገበሩት አንዳቸው ካንዳቸው የበለጠ የሚያተርፉበት ወይም የሚከስሩበት ሂደት አይኖርም፡፡ የይህ ደግሞ ለወትሮ የነበራቸውን አድማጭ ተመልካች እንደማያጡ ማስተማመኛ የሚሆንና ምንም ዋጋ የማያስከፍላቸው ነው፡፡ ይህ ሂደት በአጠቃላይ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሂደት /Win-Win Situation/ ነው፡፡

እነርሱ ይህን ካደረጉ ለሀገራችን ሁሉም ስፖርቶች ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ተወጡ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ እነርሱን ተመስጋኝ ከማድረጉም ባሻገር ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ታሪክ እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል፡፡

የጋዜጠኞች ቀናዒነት

እኔን ጨምሮ በሀገራችን ያሉ የስፖርት ጋዜጠኞችም ሁሉንም የስፖርት አይነቶችን ለመሸፈንና ለመዘገብ ፍላጎቱና ቀናዒነቱ ሊኖረን ይገባል፡፡

ያለማንም ቀስቃሽና ጠሪ በጋራ ተገናኝተን መምከርና የተለያዩ የአካሄድና የአሰራር ዘይቤዎችን በመንደፍ በየምንሰራቸው የስፖርት ስራዎች ላይ እነዚህን የተረሱ ስፖርቶቻችንን ለመዘገብ ብንስማማና የጋራ አቋም ብንይዝ በሁላችንም ዘንድ ነገሮች እንደነበሩ ይዘልቃሉ እንጂ አንዱ አይከስርም አንዱ አያተርፍም፡፡ ሁሉም ይህን ከተገበረ አንዱ አድማጮቹን አያጣም ሌላው አድማጮቹን አያበዛም፡፡ ይህ ሂደት ደግሞ አሁንም ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሂደት /Win-Win Situation/ ነው፡፡

የስፖንሰር ጉዳይ

ሀገራችን በሁሉም ነገሯ እየዘቀጠች እንደሆነ ከሚያሳዩ እውነታዎች አንዱ የስፖንሰር ጉዳይ ነው፡፡ የዳበረ የመዋዕለ ነዋይ አቅም ያላቸው በሀገራችን ውስጥ ያሉ የተለያዩ ድርጅቶችና ፋብሪካዎች ዘወትር አንድን ፕሮግራም (የስፖርትንም ጨምሮ) ስፖንሰር ለማድረግ መስፈርታቸው ምን እንደሆነ በውል አይታወቅም፡፡ በቃ እነርሱ ስፖንሰር የሚያደርጉት ከአዘጋጆቹ ጋር እውቂያ ካላቸው አሊያም ስለሌሎች ሀገራት መረጃዎች የሚያወራ ከሆነ ነው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ስፖርት ዙሪያ በግል የሚሰሩትን በኤፍ.ኤም 96.3 ላይ የሚቀርቡትን የነዳግም ዝናቡን እና የነምስጋናው ታደሰን ማራኪ ፕሮግራሞችን መመልከት በቂ ነው፡፡

የሚገርመው ሌሎች ስለ አውሮፓ እግር ኳስ የሚያወሩ ፕሮግራሞች በስፖንሰሮች ተንበሽብሸው እነዚህ ትኩረታቸውን በሀገር ውስጥ ያደረጉ ሁለት ፕሮግራሞች ግን ለአመታት አንድ ድርጅት እንኳን ስፖንሰር አድርጓቸው አያውቅም፡፡ ታዲያ እውን ከዚህ የባሰ ዝቅጠት አለ?

አሁን ዋናው ነገር ይህንን ሂደት መኮነን ሳይሆን የሚስተካከልበትን ሂደት መጠቆም ነውና ትኩረታችንን ወደዛ እናድርግ፡፡ እንደሚታወቀው በአለም ላይ በሚዲያዎች ከሚቀርቡ መሰናዶዎች መሃል የስፖርት ፕሮግራሞች በርካታ አድማጭ ተመልካች ያላቸው ናቸው፡፡ በሀገራችንም ያለው እውነታ ይህ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር  ለወትሮ የአውሮፓ እግር ኳስን ብቻ የሚዘግቡ የነበሩ የስፖርት ፕሮግራሞቻችን ከሆነ ጊዜ በኋላ ሁሉም በፕሮግራሞቻቸው ሌሎች የሀገራችንን የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ያማከሉ ከሆኑ አንደኛ አድማጭ አያጡም፤ ሁለተኛ ስፖንሰር አድራጊዎችም እንደወትሮው ሁሉ ስፖንሰር ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ እንጂ በፍጹም የስፖንሰሩን ውል አያቋርጡም፡፡ ይልቅ እንዳውም እስከዛሬ ስፖንሰር አጥተው የነበሩት በሀገር ውስጥ ስፖርት ላይ ብቻ የሚሰሩ ፕሮግራሞች በርካታ ስፖንሰሮችን ሊያገኙ የሚችሉበት እድል ሊፈጠር ይችላል፡፡

ምክንያም ሁሉም የስፖርት ፕሮግራሞች ለሀገር ወስጥ የተለያዩ ስፖርቶች ተገቢውን ትኩረት እስከሰጡ ድረስ ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶቹ አንዱን ካንዱ ለማበላለጥ የአሰራር ለውጥ አያደርጉም፡፡ ወይም የአውሮፓ እግር ኳስን ብቻ የሚያወራ ፕሮግራምን ስፖንሰር እናድርግ ቢሉ እንኳን በዚህ ሂደት መሰረት መሰል ፕሮግራም ስለማይኖር ስፖርት ባለው ተደማጭነት ሳቢያ ያላቸው ብቸኛ አማራጭ እነዚህን ፕሮግራሞች ስፖንሰር ማድረጋቸውን መቀጠል ነው፡፡ ከአድማጭ ተመልካቾች ጋር በተያያዘ ያለው ሂደትም ተመሳሳይ ነው፡፡

በአጠቃላይ እነዚህ መፍትሔዎች ይተገበሩ ዘንድ ሁላችንም በቀናዒነት ከተንቀሳቀስን፤ ተቋማቶቻችንም በዚህ አቅጣጫ ለመንቀሳቀስ ቁርጠኛ ከሆኑ፤ እንዲሁም ሁላችንም ለዚህች ምስኪን ሀገራችን ስንል እጅ ለእጅ ከተያያዝን የማይቻል ነገር እንደማይኖር እርግጠኛ መሆን አለብን!!… አበቃሁ!!

 

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *