አብርሃም ፈቃደ

እስኪ አሁን እኛ የኢትዮጵያ ህዝብ አርነት አለን ሊባል ነውን? አርነት ያለው ህዝብ ማለት እውነተኛ ትርጉሙ ለብቻው መንግስት ያለው ህዝብ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ እራሱን የቻለ ሕዝብ ማለት ነው እንጂ ይሉናል ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ ከ92 ዓመታት በፊት በከተቡት መጽሐፍ ውስጥ፡፡

በዕድሜ ለአንቱታ ያልበቁት በእውቀት ደግሞ ለአንቱታ ክብር የተገቡት ወጣቱ ነጋድራስ ገ/ህይወት ‹‹ሰዎች መንግስት ስላላቸው በአርነት ውስጥ ነው የሚኖሩት ማለት አይቻልም›› ይሉናል፡፡ ሰዎች እራሳቸውን አልቻሉም ማለት ከአርነት ውጪ ናቸው፡፡ የአርነት ተቃራኒው ደግሞ ባርነት ነው፡፡ ዛሬ መንግስት አለን፡፡ ነገር ግን ከ92 ዓመታት በኋላም ቢሆን እራሳችንን አልቻልንም፡፡ ነጋድራስ አፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና የዛሬውን እራስን ያለመቻል ቢመለከቱ በምን መልኩ ይገልጹት ይሆን? ወደዚኛው ዘመን የተወረወረ ምናባቸውን መሸከም እጅግ ይከብዳል፡፡ ነገር ግን እራስን ያለመቻል በሽታ ደግሞ ከምናባቸው እንድዋስ ይረዳኛል፡፡ የሚተነተን ተጠቂነት ከተንታኙ ጋር ባላቸው ዝምድና በኩል መሆኑ ነው፡፡ ግምት እንዴት ያማል መሰላችሁ፡፡

የተራበውን ሕዝብ ትክክለኛ ቁጥር ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ አሞራን ሲበሉ ስሙን ጅግራ ይሉ ነውና የሁሉም አቋቋም ለየቅል ነው፡፡ ከጀገነ ለአንዱ የስልጣን መሰላል ነው፡፡ ለሌላኛው መውደቂያውን መደበቂያ ነው፡፡ ‹‹ድብቆች ነን፣ የምንሰራውን ማንም አያውቅም›› ለሚሉ ቅልጥ ያለ ንግድ ነው፡፡ በርግጥ እንዳይራቡ ያልተጠነቀቀ የተራቡትን በትክክል ይቆጥራል ማለትም ገልቱ የዋሕነት ነው፡፡ ሁሉም ይሁን ሰው መራቡን መካድ ግን አይቻልም፡፡

በሚሊየን የሚቆጠረው የተራበው ሕዝብ እራሱን ያልቻለ ሕዝብ ነው፡፡ እራሱን ያልቻለ ሕዝብ ደግሞ ይለምናል፡፡ ከአንዳንድ የዓለም አገራት ሕዝቦች የሚበልጠው የተራበው፣ እራሱን ያልቻለው ሕዝብ መንግስት አለው፡፡ መንግስት ቢኖረውም ቅሉ እራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ ጠንካራ የሆነ አስተሳሰብ የለውም፡፡ መንግስት ሲራቡ ለምኖም ሊያበላቸው ይችላል፤ ቁም ነገሩ ለምኖ ማብላቱ አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም በሚሊየን የሚቆጠረው ሕዝብ አርነት የለውም፡፡ ዓይነቱ በተለየ ባርነት ውስጥ የሚዳክር ነው፡፡ ሰንሰለቱን አርዝመው ያሰሩት ውሻ የተፈታ እየመሰለን እንምታታለን፡፡

አሮጌውን የባርነት ትርጉም የሚገልጥ ሰው ከአዲሱ የባርነት ትርጉም ጋር ይጋጫል፡፡ የሚጋጨውም አዲሱ ባርነት የሚታሰርበት ሰንሰለት ረዥም በመሆኑ ምክንያት የተፈታ መስሎት ይታለላል፡፡ በአጭሩም በረዥሙም ሰንሰለት የታሰሩ ሰዎች ግፍ ተመሳሳይ ነው፡፡ በአሮጌው የባርነት ትርጉም ውስጥ ያለፉ ሕዝቦች ታሪክ እንዳነበብነው ከሆነ ግፉ ምን ቢከፋ አራሾች ስለነበሩ ለከፋ ረሃብ አይጋለጡም ነበር፡፡ ጌቶቻቸውም ቢሆኑ በልዩ ቅጣት ሊያንገላቷቸው ካልፈለጉ በስተቀር አይጨክኑባቸውም ነበር፡፡ ለምን ቢባል በርህራሄ ሳይሆን ጉልበታቸውን ለሰፋፊ እርሻቸው ይጠቀሙበት ስለነበር ነው፡፡ አሮጌውን ባርነት ስንጠቀልለው እጅግም የማይራቡ፣ በአጭር ሰንሰለት የተጠፈሩ አርነት የሌላቸው ሕዝቦች ነበሩ፡፡

በርግጥ አሮጌው ባርነት ዘመን ተሻግሮ ዛሬም ይከናወናል፡፡ የዓለማችን አስር ሃገራት 76 በመቶ የሚሆነውን የባርያ ንግድ ተቆጣጥረውታል፡፡ ከሰላሳ አምስት ቢሊየን ዶላር በላይ ይንቀሳቀስበታል፡፡ ከእስያ ሃገራት መሐል ህንድ፣ ቻይናና ፓኪስታን ዋነኛ ተዋናይ ናቸው፡፡ ከአፍሪካ ሃገራት ናይጄሪያና ኢትዮጵያ አንቀሳቃሾቹ ናቸው፡፡ መቼም በከተማ የምንኖር ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ዓይነቱ ባርነት አይጠፋንም፡፡ ‹‹እስቲ ከገጠር ልጅ አምጡልኝ›› ማለቱን ተክነንበታል፡፡

ወደ አዲሱ የኛ ዘመን ባርነት ስመለስ አዲሱ ሰው በረዣዥም ሰንሰለት ነው የታሰረው፡፡ ሰንሰለቱ እንደ ጀምስ ቦንድ መኪና አየሩን እየሰነጠቀ ሲሽከረከር አይታይም፡፡ አጭበርባሪ በሆነ ብርሃን ከዓይናችን ይሰወራል፡፡ ከእነዚህ አጭበርባሪ ከሆኑ ረዣዥም ሰንሰለቶች መሐል እጁን ከፍ አድርጎ የሚያወጣው የመቶ ፐርሰንት ዴሞክራሲ ትልቁን ቦታ ይሸፍናል፡፡

ዲሞው ጎፈሪያም ውሻ ነው፡፡ ከጅብ ያስጥለናል ብለን ደፍረን ጨለማ ላይ የማንቆምበት፡፡ ሌቦች ግቢያችንን ሊደፍሩት አይቻላቸውም ብለን እንቅልፍ የማንተኛበት፡፡ አለ ብለን የማንዘናጋበትና ጎፈሪያምነቱን ረስተን ስንተኛ ባርነቱን ጫንቃችን እስኪሰበር የሚጭንብን ነው፡፡ በስህተት ያለ ይመስለንና ስንጠጋው ሞቱ ስቦ ያስቀረናል፡፡ ሞቱ ወደ ባርነት ቼ እያለ ይጋልበናል፡፡

ሌላኛው አዲሱ ባርነት እድገት ይባላል፡፡ የዲሞው ልጅ ነው፡፡ ባርነት ከማደግ ውስጥ እንዴት ሊፈጠር ይችላል? ብለን ልናስብ እንችላልን፡፡ የአንድ አገር እድገት አስር በመቶ እያደገ ነው ብለን እንውስድ፡፡ ይህም ያንሳል መሰለኝ፤ በቃ ኢኮኖሚው ማደግ እስከሚችልበት ጣሪያ ድረስ እያደገ ነው ብለን እንስማማ፡፡ ጉዳዩ የቀመሩ ከፍና ዝቅ ማለት አይደለም፡፡ ጥያቄው በዚህ ቀመር ውስጥ ምን ያህል ሰዎች ሊያድጉ ቻሉ ነው፡፡ አስር ሰው ያቀፈ አንደ ቤተሰብ አለ ብለን እንውስድ፡፡ ከአስሩ መሃል አንደኛው ንፍገት ያለበት ግለሰብ ሃያ በመቶ አደገ፡፡ ዘጠኙ መጀመሪያ ከነበሩበት የድህነት ገደል ወደ ባሰ አዘቅጥ ወረዱ (ምንአልባት መኖሪያቸውን ሽጦ ይሆናል)፡፡ አሁን ይህንን ቤተሰብ አድጓል ተመንድጓል ማለት እንችላለን? በአገሪቷ ላይ የተንሰራፋው የእድገት መልክም ተመሳሳይ ነው፡፡ ሩቅ አገር ለውሸት ይመቻል እንዲሉ ለዘጠኙም ወደፊት የሚባል ክታብ አንገታቸው ላይ ይጠልቃል፡፡ ነገር ግን ዘጠኙም ቤተሰቦች እናራግፍህ ሲሉት ካልተጣበቅኩ የሚል ድህነት ተጭኗቸዋል፡፡ እራሳቸውን አልቻሉም፡፡ አርነትም ርቃለች፡፡ አዘቅጡ ላይ ሆነው ባርነትን ያቦካሉ፡፡

አዲሱ ባርነት ኑሮ የሚባል ለማዳ አውሬ የነገሰበት ነው፡፡ እንደጥንቱ ባርነት ግለሰቦች እንደግመል አስረውና አሰልፈው አይነዱበትም፡፡ ነጂውም ሰንሰለቱም የተሰወሩ ናቸው፡፡ በጉልህ ይታይ የነበረው ባርነት መሻሻል ደጁ ደረሰና ተቀየረ፡፡ ርካሽ የሰው ሃይል የሚል የዳቦ ስም ወጣለት፡፡ ኢትዮጵያውያን በዚህ ሰዓት ከሰላሳ እስከ አርባ ዶላር በወር ይከፈላቸዋል፡፡ የሚሰጣቸው ደሞዝ እራሳቸውን ያቆዩበት ይሆናል፡፡ ነገር ግን የእለት ዳቦ እየበሉ ርካሽ የተባለ ጉልበታቸውን የውጭ ካምፓኒዎች ከማበረታቻ ጋር ያለከልካይ መቅኒያቸውን እንዲመጡ ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በድርጅቶቹ ውስጥ ጧትና ማታ ሲርመሰመሱ ለተመለከተ ታዛቢ የታሰሩበት ሰንሰለት ረዥም በመሆኑ ምክንያት ለዜጎች የስራ እድል የተፈጠረ ይመስለውና የማያዛልቅ ደሰታ ይጎበኘዋል፡፡ እናም መርመስመሱ ህይወት ለማቆየት የሚደረግ ተጋድሎ መሆኑን ሲገነዘብ ከእደገትና ደስታው ይኮማተራል፡፡

እነዚህ ከላይ የዳሰስናቸው ችግሮች ለዘመናት በደምስሮቻችን ጭምር ተሸክመናቸዋል፡፡ አርነት አለን ብለን እንድናውጅ ራሳችንን መቻል አለብን፡፡ አዲሱን ባርነት ለማስገወድ ሁላችንም በያገባናል መንፈስ መፍትሔ ፈጣሪ መሆን ይኖርብናል፡፡ ርሃብን ማስወገድ አለብን፡፡ የጉልበት ብዝበዛን ማጥፋት አለብን፡፡ ከሁሉም በላይ በዕውቀትና በጥበብ ሊያገለግሉን ወደአርነት የሚወስዱን የዴሞክራሲ ተቋማት መፍጠር አለብን፡፡ ልጓም አጥባቂው የመቶ ፐርሰንት አስተሳሰብ ሲከስም አርነት ይመጣል ባርነትም ይጠፋል ያኔ ሁሉም ዱቄቱን ለንፋስ ማበደር ይችላል፡፡

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *