ተማም አባቡልጉ

ኢህአዴግ በኦሮሚያ ክልል ለተፈፀመው የጦር ወንጀል (ቶርቸርና በአደባባይ ሰውን መረሸን ተጠያቂ የሚሆኑ የጦርና የሲቪል ባልሥልጣናቱን ለፍርድ የማቅረብ ፍላጎትና ፍቃደኝነት የሌለውና የወንድሞቻችን፣ የእህቶቻችን፣ የልጆቻችን፣ የእናቶቻችንና የአባቶቻችን ደም እንደውሻ ደም እንዲሁ በአደባባይ ፈስሶ ሊቀር ለመሆኑ ማረጋገጫ ባለሥልጣናቱ ሰሞኑን ስለዚሁ ጉዳይ በሚሰጡት ቃል የማጣራቱን ሂደት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እየፈፀመ ነው ማለታቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ የቱንም የወንጀል ድርጊት የማጣራት ስልጣን ለሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ያልተሰጠ በመሆኑ ስለዚሁ ጉዳይ ምንም ዓይነት ማጣራት እየተደረገ ያለመሆኑንና ባለሥልጣናቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ እያታለሉና እንደለመዱት ጊዜ በመግዛት አረሳስተው የሕዝቡን ሃሣብ በጊዜ ብዛት ወደሌላ ነገር ለመለወጥ እየሠሩ መሆኑን እንረዳለን፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሠ አታምጣ እያለ ቀይ ሽብርንም ስለተቀበለ በ1997 ዓ.ም. ምርጫና ከዚያም በኋላ በአደባባይ የተፈፀሙትን ርሸናዎች፣ ድብደባዎች፣ ውርደቶች፣ ሕገ-ወጥ እሥራቶች በመታገስም እነዚህ ጥሩና ተገቢ የሥልጣን ማስጠበቂያ ዘዴዎች መሆናቸውን ኢህአዴግ በማየት (through trial and error) እንዲያረጋግጥ ያገዘው በመሆኑ አሁንም ከማረሳሳት የተሻለ መንገድ ለመከተል አልተጨነቁም፡፡ ነገር ግን አሁን እንዳለፈው ጊዜ ሳይሆን ሕዝቡ ‹‹የልጆቼን ደም አፍስሰህማ ምንም ያልሆነ ይመስል እኔን እየገዛህ አትቀጥልም›› ማለቱ የማይቀር መሆኑን ለመረዳት እጅግ ቀላል ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ሁላችንም ምንም ኑሮና ፍርሃት (ፕሮፓጋንዳዎችን ጨምሮ) ቢያደነዝዘንም የሰንጋ ፈረሰኞቹ የእነ ኦርዶፋ ጨንገሬ ልጆችና የልጅ ልጆች መሆናችንን ማስታወስ ይበቃል፡፡ በዚህም ሞትን ፊት ለፊት ዓይኑ ውስጥ እያዩ መኖር የሚችሉ ብቻ ሳይሆኑ ሞተው ዘላለማዊ ሕይወትን የተቀናጁ ጀግኖች አባቶችና እናቶች ደምም በደም ሥራቸው ያለና እንደ እሳት የሚንቀለቀል ስሜት ያለባቸው ጀግኖቻችንን ሁሌም ወቅቱ ያንን በፈለገ ጊዜ ሁሉ ያንን መድገማቸው የማይቀር እንደሆነ ስለምናውቅ ነው፡፡ እንኳን ባዶ እጁን በወጣ ሕዝብ ላይ ለሚተኩስ ፈሪ ቀርቶ አባቶቻችን ለፋሽስት ኢጣሊያ የመርዝ ጢስ አልተገዙም፣ እንኳን አዛውንት ሴት ሕፃንና የታሠረ ለሚደበድብ ቡክኔ ይቅርና እነ አብዲሳ አጋ (በሮም) እነ ዘርዓይ ደረስ በአዲስ አበባ ለግራዚያኒና ፋሽስት ኢጣሊያንን የሽንፈት ፅዋውን እንዲጎነጭ በሕይወታቸውና በሞታቸው ከማድረግ አልተመለሱም፡፡ ይህ ያለፈ ታሪክ ሳይሆን የምንኖረው ሕይወት መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያውቀዋል፣ ሌላውም የሚያውቅበት ጊዜ ሩቅ አይመስለኝም፡፡

በየትኛውም ወቅት፣ በየትኛውም ሀገር የሠው ልጅ በዘመናዊ ሕግ መተዳደር ከጀመረበት የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ መሣሪያ የታጠቁ ወታደሮች የሠው አጥር ዘለው ገብተው የሚያጠኑ ተማሪዎችን መረሸናቸው ሕጋዊና የመንግስት ሥራ ሆኖ አያውቅም፡፡ እነዚህን ወታደሮች በተመጣጣኝ ጉልበትና መንገድ ከራስ ላይ መከላከልም ወንጀል ሊሆን የሚችልበትም መንገድ አይኖርም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ወንጀል ተፈፅሞም እያለ ዝም የሚል ወይም ይህንን ያዘዘና ያስፈፀመ አካል ሽፍታ ወንበዴ ወይም የተደራጀ ዘራፊ ወይም ሌላ ልትሉት ትችላላችሁ፤ በፍፁም ግን መንግስት ሊባል (ሊሆን) ወይም ተብሎ ሊጠራ አይችልም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሁሉ ከመንግስት ትርጉም ውስጥ የሉበትምና ነው፡፡ ይህ ሁሉ አሁን በሀገራቸው ያለ እውነት የሚሆነው የማጣራቱ ሥራ ባለመሠራቱና በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠቂ (Victim) የሆኑትን እነበቀለ ገርባ፣ ደስታ ዲንቃና ሌሎችም ስማቸውን የማንለያቸው ሺህዎች (ወንድሞቻችንና እህቶቻችን) ራሳቸውን ስለተከላከሉና አትምቱን ስላሉ ብቻ በአሁኑ ወቅት ታስረው እየተሰቃዩ በመሆኑ ነው፡፡ አሁን በኦሮሚያ ክልል ያሉ ወገኖቼ ያሉበትን ሁኔታ እኔ ኢትዮጵያ በፋሽሽት ኢጣሊያ ሥር ከነበረችበት የአምስት ዓመት ጊዜ እና በደርግ ጊዜ ከነበረው የቀይ ሽብር ጊዜ ለይቼ አላየውም፡፡ እንደዚህ የማይመለከት ኢትዮጵያዊም ካለ በናዚ እሥር ቤት ወገኖቹን ወደሚቃጠሉበት ቦታ እንዲመራ ከተመረጠ እና እሱም ኋላ ላይ ከሚጋደል አይሁድ ለይቼ አላየውም፡፡

የወንጀል ድርጊትን የማጣራት ስራ ሁሌም የፖሊስ ኃላፊነት ስለሆነ በኦሮሚያ ሠው የገደሉትን ሠዎች ጉዳይ ‹‹የሰብዓዊ መብት ጉባኤ እያጣራው ነው›› ማለት ፍፁም ስህተት ነው፡፡ ይህ ምርመራ ሳይጣራ ደግሞ ሠላማዊ ሠልፍ አደረጉ የተባሉትን ፖሊስ አፍሶ እያሰረ ወንጀል ያልሰሩትን አጣርተን እንለቃለን ይላሉ፡፡ ለነገሩ ሰዎች በደፈናው በዘፈቀደ ታፍሰው ታስረው ወንጀል ያልሰሩት እየተጣሩ የሚወጡበት አሠራር የዘፈቀደ እሥራት ተብሎ ይታወቃል፡፡

ሠልፍ አደረጉ የሚባሉት እየታፈሱ (ሣይጣራ እየታሰሩ) ሰውን ተኩሰው የገደሉትን ግን ለማሠር ‹‹ገና ማጣራት ላይ ነን›› ማለት ‹‹ሠውን ከመግደል ሠልፍ ማድረግ ይበልጣል›› ማለት ካልሆነ አድልኦ ነው፡፡

በሕግ ተቀባይነት ያለው አሠራር ማንም ወንጀል ያልሠራ ሰው ሳይነካ ወንጀል የሰሩት ብቻ ተነጥለው የሚታሠሩበት ሁኔታ ነው፡፡ በወንጀል ሕግ መርህ አንድ ንፁሕ ሠው ያላግባብ ከሚታሠር 10,000 ወንጀለኞቸ ቢያመልጡ ይሻላል የሚል ነው፡፡

ኢህአዴግ በሠልፍ ምክንያት የሚለው እውነት ከሆነና ተሳስቶ ማጣራቱ የፖሊስ ሳይሆን የኮሚሽኑ ከመሰለው በሠልፉ ምክንያት ያሠራቸውን ሁሉ ፈትቶ የማጣራቱን ሥራ ከጨረሰ በኋላ ካላሠራቸው እና ወይም ሰው የገደሉትን ዛሬ ላይ አሥሮ ምርመራውን ማድረግ ካልጀመረ ድርጊቱ ሠው የገደሉትን ለፍርድ አላቀርብም ከማለት አይለይም፡፡

በኢትዮጵያ ሠሞኑን እየተካሄደ ያለው (በኦሮሚያ፣ በጎንደር፣ ወይም በአዲስ አበባ ታክሲ አድማ) ሁኔታ፡-

  1. ‹‹የኢህአዴግ መንግስት የእኔ ነው ወይም እኔ መርጬ የሾምኩት ነው፡፡ በዚህም እኔን (የእኔን ጥቅም) ይወክላል ወይም ያስጠብቃል›› ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለማያምንና እንደዚያ ብሎ ከልቡ ስለማይቀበል፣
  2. ኢህአዴግም በውስጡ ይህንኑ የሕዝቡን አመኔታ ስለሚጋራና ስለሚያምን ‹‹ለሕዝቡ የቆምኩ ወይም የሕዝቡ ነኝ›› ብሎ ሳይሆን ‹‹እኔ እኔ ነኝ፤ ሕዝቡም ሕዝቡ ነው፡፡ ጥቅማችንም ይጋጫል፡፡ የሕዝቡ መብት ከተከበረ የኢህአዴግ ጥቅምና የበላይነት ይቀራል›› ብሎ ስለሚያምን ነው፣
  3. ከዚህም የተነሳ በባህሪው የሆነውንና ነኝ ብሎ በውስጡ የሚያምነውን እንጂ ነኝ ብሎ የሚሰብከውን ስለማያደርግ ስለየትኛውም ጉዳይ ሕዝቡን ባለድርሻ አካላቱን ወይም ጉዳዩ የሚመለከተውን ዜጋ አማክሮ ሳይሆን የመሰለውን ከላይ ወደታች በሕግነት በሕዝቡ ላይ ስለሚጭንና አዋጁ የድርጅቱን ጥቅም ከማስጠበቁ አንፃር ብቻ ታይቶ ወጥቶ ስለሚተገበርና ከሕዝቡ በሕዝቡ ለሕዝቡ (የሕዝቡ) ባለመሆኑ፣
  4. ይህንን ሁሉም ስላወቀ የተፈጠረ ነው፡፡ ሕዝቡ ‹‹ጠላቴ ኢህአዴግ ነው፣ ኢህአዴግ ደግሞ ጠላቴ ሕዝቡ ነው›› በሚል በውስጣቸው የያዙትን እምነት ሁለቱም ስለተነቃቁ የተፈጠረ ነው፡፡ ኢህአዴግ ዋናው ጠላቱ የነቃና መብቱን የሚጠይቅ ዜጋ ሁሉ ነው፡፡ ኢህአዴግ የማንንም ዜጋ የትኛውንም መብት ማክበር (የየቱም ዜጋ የትኛውም መብት መከበር) ጥቅሜን ይነካል ብሎ ያምናል፡፡ ሕዝቡ ያገሩ (የሀገሩ ሀብትና ዕድል) ባለቤት ነው ብሎ ከልቡ ስለማያምን ስለየትኛውም ሀገራዊ ጉዳይ (ሕዝበ-ውሳኔ የሚሹትን እንደ አባይ ግድብ ያሉትን ጨምሮ) በሚመለከት የመሰለውን ወስኖ ሕዝቡ በግድ እንዲቀበለው ይጥራል እንጂ ሕዝቡን አማክሮ አውጥቶ ወይም ባያማክርም ሕዝቡ እምቢ እያለም በግድ ለማስፈፀም ይጥራል እንጂ ለሕዝቡ ካልሆነና ሕዝቡ እምቢ ካለ ይቅር ብሎ አይተወውም፡፡ ይህም የተባለው ሕግ በውስጡ (በልቡ ወይም በደመ ነፍሱ ለራሱ ለኢህአዴግ እንጂ ለሕዝቡ ይጠቅማል ብሎ ስለማያምንና በአብዛኛውም ሕዝቡን እንደሚጎዳው ስለሚያውቅ ሕዝቡ ፈርቶ ተታሎ ወይም ተገዶ ካልሆነ ፈልጎ ይቀበለዋል ብሎ ስለማያምን ነው፡፡ ይህንን ኢሕአዴግ ከድሮ (1983 ዓ.ም) ጀምሮ ያውቀዋል፡፡

አሁን አዲስ የተፈጠረው ነገር ምንድን ነው? ቢባል ይህ መሆኑን ሕዝቡ አሁን ከልቡ (ከውስጡ) አውቆ ተረድቶ ተቀብሎ የሚኖርበት እምነቱ በማድረጉ መብቱን ራሱ ሕዝቡ እንጂ ኢህአዴግ ያስከብርልኛል የሚለውን ቅዠት በመተው ነው፡፡

ኢሕአዴግ ሀገሩን ለሕዝቡ መልሶ አስረክቦ ሕዝቡ በሀገሩ ላይ ወሳኝነቱን በሕግም በተግባርም ካረጋገጠና የራሱን ወኪል በእውነትም መምረጥ ከቻለ በኋላ ኢህአዴግም ከሁሉም ጋር በእኩልነት እንዲወዳደር ማድረግ (ካልሆነና ይህንን አሻፈረኝ ካለ እሱ የሌለበትን ምርጫ አስደርጎ ሀገሩን ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለመመለስ እንዲቻል መድረኩን ለሌሎች (ይህንን ለሚቀበሉት) እንዲለቅ ሕጋዊ የሆኑትን የማስገደድ ዘዴዎች በሙሉ መጠቀም መፍትሔው መሆኑን ሕዝቡ የተረዳ መሆኑን ያልተረዳው ኢህአዴግ ብቻ በመሆኑ ‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ›› የሚለውን መተረት ነው የሚሉ አሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ ግን ‹‹የኢሕአዴግ መንግስት የእኔ መንግስት ነው›› ብሎ ሕዝቡ ከልቡ ቢያምን ኖሮ ‹‹የቆመውና የሚሠራው ለእኔ ጥቅም ነው›› ብሎ ስለሚያምን ሕግ አውጥቶ በሥራ ላይ በተግባር ሲተረጉም ‹‹እኔን ሳታማክር አወጣህና ተረጎምከው›› በሚል መነሻ ሕዝቡ ተቃውሞ አያቀርብም ነበር፡፡ ኢህአዴግን መንግስት አድርጎ በተቀበለባቸው ጊዜያት ይህንን ምክንያት ለተቃውሞው ምክንያት አያደርግም እንደነበረው ማለት ነው፡፡ መንግስትነቱን (ሕጋዊነቱን) መቀበል ሲተው አላማከርከኝም የሚል ምክንያት በሕጋዊ (Legitimate) ምክንያትነት ማስቀመጥና ማቅረብ ጀመረ የሚሉም አልጠፉም፡፡ ይህ አቀራረብ አሳማኝ ነው፡፡ በሕግ ያለመስራት ሕጋዊነትን ያሳጣልና ነው፡፡

ስለሆነም አሁን በኦሮሚያ፣ በአማራ (ምንጃርና) በአዲስ አበባ ታክሲዎች የተነሳው “እኛን ሳታማክር ሕግ አወጣህ” የሚል የተቃውሞ ምክንያት ሕዝቡ በኢሕአዴግ መንግስት ሕጋዊነት (Legitimacy) ላይ እምነት የሌለው ከመሆኑ ወይም ሕዝቡ ‹‹የኢሕአዴግ መንግስት ሕጋዊ (Legitimate) አይደለም ወይም የቆመው ለእኛ ጥቅም አይደለም፤ በተቃራኒው እኛን ጎድቶ የራሱን ጥቅም ከማስከበር አይመለስም›› ብሎ ከማመኑ የመነጨ ነው ብለን መደምደም እንችላለን ማለት ነው፡፡ የየቱም መንግስት የሕጋዊነት ምንጩ በሕዝቡ መመረጥ ብቻ ሳይሆን የአስመራጭ አካላቱ ጉለልተኝነትና ነፃነትም መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህም መዋቅሮቹ (ምርጫ ቦርድ፣ ፍ/ቤት፣ አመራሮቹና ዳኞቹ) በሕግና በሕግ (በህሊናቸው) መሰረት ብቻ መስራታቸውን ይመለከታል፡፡

ይህም ሁኔታ የኢትዮጵያን ሕዝብ የንቃተ ሕሊና እድገት ትልቅ ደረጃ መድረሱን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህንን ሁኔታ ያለመገንዘቡን ችግሮችን በተለመደው መንገድና ዘዴ ለመፍታት ከመሞከሩ መረዳት ይቻላል፡፡

የሕዝቡ ስለኢሕአዴግ (ባህሪና ማንነት)ና ስለሀገሩ (መብቱና ነፃነቱ) ያለው የነበረው ግንዛቤ እድገትና መለወጥ በሁለቱ መካከል የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ የለወጠ መሆኑን ለመረዳት በኦሮሚያ የተፈጠረው ችግር (ጥያቄ) ፍፁም ተለዋዋጭ (ያልተቸነከረ)ና ሕዝባዊ (አጠቃላይ የመብትና የነፃነት ጥበቃን ጥያቄ እያለዋወጠ ማቅረቡና ማደጉ) መሆኑ ሲሆን ኢህአዴግ ችግሩን በውጪ ኃይሎች ላይ በማላከክ ከሀገር ውስጥ እነበቀለ ገርባን (ወዳጄ ደስታ ዲንቃን) በማሠር እና ከራሱም እነዳባ ደበሌን ከስልጣናቸው በማባረር ለማረጋጋት መሞከሩን ስንመለከት ለውጡን ያለመረዳቱን እንረዳለን፡፡ እነዳባ ከሁለቱም ያጡና ማንም እንዳያዝንላቸው የተደረጉት ድሮ ቢሆንም የተባረሩት በውስጥ ተነጋግረው በመስማማት አስመስለው ሕዝቡን ለመሸወድ ከሆነም ውጤት አይኖረውም፡፡ በተቃራኒው ውጤቱ የበለጠ ሕዝቡን የሚያናድድ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዳባ ደበሌ የተባረሩት ‹‹የሕዝቡን መብትና ነፃነት ጣሳችሁ ወይም አላስከበራችሁም›› በሚል ሳይሆን ኢሕአዴግ ራሱ ‹‹የእኔ መልካም አስተዳደር ያለማስፈን የፈጠረው ሕጋዊ የመብትና የነፃነት ጥያቄ ነው›› በማለት አምኖ የተቀበለውን ጥያቄ ባቀረበው ሕዝብ ላይ በጊዜው ከፍ ያለ እርምጃ በመውሰድ ማስቆም አልቻላችሁም በሚል በመሆኑ ነው፡፡

ሕዝቡን (ተቃውሞው በደንብ ወዲያውኑ ሳይስፋፋና ሳያድግ) ‹‹በሚገባ አልመታችሁም›› በሚል የተባረሩ መሆኑ (የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ በ23/06/2008 ዓ.ም. ምሽት በሪፖርተር ጋዜጣ አገኘሁ በማለት እንዳቀረበ) ነው፡፡ ኢሕአዴግ አባላቱን ራሱ ትክክል ነው ያለውን የሕዝብን መብቴ ይከበርን ጥያቄ በደንብ አልመታህም በሚል ማባረሩ ከላይ ያልነውን ኢሕአዴግ የሕዝቡ መብት መከበር በራሱ የኢህአዴግን ጥቅም ይጎዳል የሚል እምነት ያለው መሆኑን የሚያጠናክርልን (ተጨማሪ ማሳያ) ይሆናል፡፡ እነዳባ ደበሌ ሕዝቡን በሚገባ በተገቢ ጊዜ ውስጥ ባለመምታት ወደሕዝቡ ወገናችሁ ለሕዝቡ አደላችሁ ወይም ለሕዝቡ ፍፁም በሆነ ሁኔታ ምንም ዓይነት ርህራሄ ማሳየትና መዘናጋት የሌለባችሁ የመሆኑን ሁኔታና ባህሪ አላሳያችሁም በሚል አንድምታ ምክንያትነት የተባረሩ መሆኑ እነሱን (ተባራሪዎቹን) የሕዝብ ወገን አደረጋቸው አላደረጋቸው ለሕዝቡ በግልፅ የሚያስተላልፈው መልዕክት ኢሕአዴግ ሕጋዊ ጥያቄን ያቀረበን ሕዝብ ጭምር እንዲመቱ ለባለሥልጣናቱ መመሪያ የሚሰጥና ያንንም ውጤት ከእነሱ የሚጠብቅ መሆኑን ነው፡፡ ኢህአዴግ በአፉ እንደሚለው ሳይሆን (አሁን ለአፉም አልቻለም) ማንም የቱንም የመብት ጥያቄ የሚያቀርብ ዜጋ ‹‹ጠላቴ ነው፣ መመታት አለበት›› ብሎ አምኖ የሚሰራ እንደሆነ ይህ ሁኔታ ተጨማሪ አስረጂ ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ እየሰጠ ካለው መልስ ተነስተን ማለት የምንችለው ሕዝቡ ይህንን ሁኔታ መረዳቱን አልተረዳም፡፡ ሕዝቡ ‹‹ችግሬና የችግሬ ምንጭ አንተ ነህ›› እያለው መሆኑን እንኳ አላወቀም፣ ወይም አውቆ እንዳላወቀ ይሆናል፡፡ የሚለውን ነው፡፡

 

‹‹እኔን አላወያየህም›› በሚል የአንድን መንግስት ሕግ አልቀበልም ያለ ሕዝብ ‹‹ሕጉም መንግስቱም የእኔ አይደሉም›› ማለቱ እንደሆነ ለመረዳት ሕዝብ መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ሕዝብ ከመንግስት ጋር ሌላ ውል የመግባት (የሕገ-መንግስትና የሥርዓት ለውጥ) ጥያቄ እያቀረበ መሆኑን ለመረዳት ትንሽ ማሠላሠል ብቻ የሚፈልግ መሆኑም እየቀረ ይመጣል፡፡ ምክንያቱም ከትንሽ ጊዜ በኋላ ሕዝቡ የውክልና ጥያቄውን (መንግስቱ አይወክለኝም የሚለውን) ግልፅ እያደረገው ስለሚመጣ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ግን የነጋበት ጅብ ማለት ሳይሆን መሆን ሊመጣ ይችላል፡፡

 

እኔ እራሴን የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ እራሴን አውቃለሁ ብዬ መናገር ከቻልኩ (ሰው ራሴን አውቃለሁ ብሎ መናገር መቻሉ የሚችል ከሆነ) የኢትዮጵያ ሕዝብ እየሞተ፣ እየታሠረና እየተደበደበ ጥያቄውን ያለመጣሉ ብቻ ሳይሆን አላማከርከኝም የሚልን ምክንያት ለተቃውሞው መነሻ ማድረጉን በማየት የሆነን አካል የነጋበት ጅብ እያለ (በነጋበት ጅብነት እየከሠሠ) መሆኑን ለመረዳት አያቅተኝም (አያቅተንም)፡፡

 

ሕዝቡ ኢህአዴግን ‹‹ወርቄን ማፈስ ትተህ ወርቅ ብታፈስልኝ እንኳ አልፈልግህምና (ገለል በልልኝ)›› እያለው መሆኑን ግን ኢህአዴግ ያለመረዳቱ  የሚያስረዳን ነገር የነጋበት ጅብ በርግጥ ከእሱ ውጪ ያለመኖሩን ነው ለማለት ለምን አያስችለንም?

 

አንድ የሕግ ባለሙያ በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የትግርኛ ፕሮግራም ላይ በ24/06/2008 ዓ.ም. ምሽት ቀርበው በኦሮሚያ የተፈጠረውን ሁኔታ አስመልክቶ ‹‹ችግሩ ኦሮሞን ለኦሮሞዎች የሚሉ አካላት ናቸው›› ማለታቸውን ስሰማ፣ ጋዜጠኛው ‹‹የአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሞዎች ከመሬታቸው መነሳትስ አይደለምን?›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርብላቸው እንኳ ይህንን ኢሕአዴግ የችግሩ ዋና ምክንያት አድርጎ የተቀበለን ጉዳይ ወደ ሁለተኛ (ዝቅተኛና የጎን) ምክንያትነት መግፋታቸውን ሳዳምጥ ‹‹ለካስ በየቋንቋችን ተናገሩ የተባልነው በየቋንቋችን ለያይተው ሊዋሹንና አንዳችንን ለሌላኛችን ችግር ምክንያት እያደረጉ ሊይዙን ነው›› የሚል ስሜት ብቻ ሳይሆን ባለፈው ሁለት ሳምንት ቀይ መስመር አላፊ የሕግ ባለሙያዎችን አስመልክቶ ያቀረብኩትን ሐተታ ትክክለኝነት አሳይቶኛል፡፡

 

በነገራችን ላይ እየሆነ አይደለም እንጂ ብለዋልን የኦሮሞ ወይም የወልቃይት ሕዝብ የራሱን ባህል ቋንቋና ማንነት ሌላው በፈለገበት መልክ ሳይሆን ራሱ እንደፈለገው ማሳደግ ቢችል የሁላችንም ባህል፣ ቋንቋና ማንነት አደገ ማለት አይደለምን? እኔና እናንተ (ሁላችንም ኢትዮጵያውያን) እያንዳንዳችን ቢደላን መብቶችና ነፃነቶቻችን ተባብረው በሀገራችን ላይ አድገን ላሰብነው ብንበቃ ሀገራችንስ አደገች ማለት አልነበረምን? እርግጥ ነው ቀይ መስመር ላለማለፍም ሆነ ይህንን ለማሰላሰልና ለመረዳት ሕሊና ያስፈልጋል፡፡

 

ከዚያ በፊት ግን ‹‹ቋንቋ አይሰሙም›› በሚል የቀረበው የዚህ ባለሙያ ሁኔታ ከዛሬ ወር በፊት ከዚህ መፅሔት ላይ “ለኢትዮጵያ ኦሮሞም ትግሬ ነው፡፡” በሚል ርዕስ ስር ያቀረብኩትን ፅሑፍ ሳጠቃልል ኦሮሞን መትቶ በትግራይ ሕዝብ ጉያ ስር ለመደበቅ መፈለግ ልጇን ገድሎ በእናት ቤት መጠለል ነውና ‹‹አቶ አባይን የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም የትግራይ እናቶችና አባቶች ይፍረዱን›› በማለት ያቀረብኩትን (በቦታ እጥረት ምክንያት ተቆርጦ የቀረን) ካለመስማትና አንድነታችን ከልብ መሆኑን ካለመረዳት የመጣ “መሣሣት” ይሁን ማሣሣት ሕሊና ለሕሊና ታማኝነት ካለማጥራት ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡

 

ለዚህም የዛሬ ፅሑፌን ባለፈው እትም ላይ ‹‹የሕግ ባለሙያ ባህሪና ቀይ መስመሮቹ›› በሚል ርዕስ ሥር ካቀረብኩት ፅሑፍ መደምደሚያና የርዕሰ አንቀፅ ሃሳብ ሆኖ እንዲያገለግል ሁለቱም ላይ እንዲወጣ ተብሎ ግን በስህተት በፅሑፌ ማጠቃለያ ላይ ሳይወጣ በቀረው አባባል (ሃሣብ) አጠቃልላለሁ፡፡

ኅሊና ያለው ሰው ፈርቶ መኖርን አይተውም። ሌላውም ፈርቶት ኑሮውን እንዲተው አያደርግም። ባዶ እግሩን ሲሄድም ክንፍ አውጥቶ ሲበርም – ሰው ነውና ሁሌም የሆነውን ሆና እንጂ – ለአንዱ ሌላኛውን ‹‹አይገድልም››። ለራሱ ድሎት፣ ከሌለው ሥር ምድር እንደ ምንጣፍ ተጠቅልላ እንድትነሣ አያሤርም፣ አይሠራም።

ኅሊና ያለው ሰው – ሕግና ማስፈጸሚያ ስላለው እሺታውም እምቢታውም፣ ፍቅሩም ጥሉም፣ ጥላቻውም ስምምነቱም፣ ጦርነቱም መልክ አለው – ያምራል። ቢያንስ ይታያልና – ይታወቃል። ኅሊና ያለውን ሰው ሕልውና ማንም መካድ አይችልም። እሱም የማንንም ህውልና ሰው ህልውና ማንም መካድ አይችልም፤ እንቢ ማለት መቻሉም ይህንኑ ያሳያል፡፡ ከዚህም ነው አንዳንዶቹ በሕይወት እያሉ ብቻ ሳይሆን ሞተውም የሚኖሩት፡፡

እስስት አድርባይ ናት፡፡ እስስትነት አድርባይነት ነው፡፡ እስስት መልክም፣ ቦታም፣ ሚናም፣ ግብም ሆነ ማንነት ሳይኖራት ወይም ኖራ ሳትኖር፣ እያለች ተክዳ እሷም ራሷን ክዳ መኖሯ ሳይታወቅ፤ በራሷ ቆማ እንደሆነችው ሆና ሳትሆን (መሆኗ መምሰል ነው ካልተባለ በቀር) ሌላን እንደመሰለች በእሷ ውስጥ (በእሷ ፊት ገላ ወይም መልክ ውስጥ) ሌላ እየታየና እንደታየ ወዳለመኖር ተለውጣ ትቢያ ትለብሳለች፡፡ ሚዛንም የሚመዘንም ሳይኖራት ህልውናዋ በራሷ ፍቃድ በሁሉም ተክዶ (ያለመሆንና ያለመኖር ምሳሌ እንደሆነች) ሳትኖር ትሞትና ትቢያ መሰል ትቢያ ይባልላታል፡፡

የሕግ ባለሙያነት በልምምድ የሆነን ሥራ መሥራት መቻል ብቻ አይደለም። የሕግ ባለሙያነት ባሕርይና ስብዕና መፍጠር ነው። በዚህ ባሕርይ ለዚህ ባሕርይ መሆኛ የሚመች አካባቢ ለመፍጠር መሥራትና መኖር ማለት ነው። ስለሆነም፣ የሕግ ባለሙያው ያንን ለማጥፋት በመተባበር፣ የራሱን ስብዕና አያጠፋም። የፍርድ ቤትን ነፃነት እና ገለልተኝነት፣ የሕግ የበላይነትን እና የዜጎችን መብትና ነጻነት እንዳይከበር መሥራት እና ለዚያ ከሚሠራ አካል ጋር መተባበር፣ ያንን ለማጥፋት መሥራትና ከሚያጠፋው ጋር መተባበር ነውና። ከዚህ እና ቃል የቆመው በሕግ ከመሆን በመነሳት ስንመለከተው ለሕዝብ መብት፣ ነጻነት እና እኩልነት መከበር መቆምን በባለሙያው ላይ በግዴታነት ያላስቀመጠ፣ ስብዕናውን ያልፈጠረበት፣ ለሕግ የበላይነት ያልቆመ የሕግ ባለሙያነት የቃልን መሰረት ንዶ መቅበርን የፈቀደና የሚፈቅድ (ለዚህ መተባበርን መፍቀድ ጨምሮ) ከመሆን አይለይም፡፡ ይህ ቃል ይሞታል (ሊሞት ይችላል) ብሎ ከመጠበቅ (ከማመን) የመነጨ ክህደት የክህደቶች ሁሉ ቁንጮ የሆነው (የሚሆነው) ወይም ተደርጎ የሚወሰደው በሆነው ሁሉ ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ሲሆን ውጤቱም ሞት ነውና እባካችሁ እንንቃ!

 

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *