በነገሠ ተፈረደኝ

 

ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋ ነበረች። ከምስራቅም ተነስተው በሄዱ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ፣ በዚያም ተቀመጡ። እርስ በርሳቸውም ‹‹ኑ ጡብ እንስራ፣ በእሳትም እንተኩሰው›› ተባባሉ፣ ጡቡም እንደ ድንጋይ ሆነላቸው፤ …  ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንስራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው›› አሉ። እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሰሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። እግዚአብሔርም አለ። ‹‹እነሆ እነርሱ አንድ ወገን ናቸው፤ ለሁሉም አንድ ቋንቋ አላቸው፤ ይህንም ለማድረግ ጀመሩ፤ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመስራት አይከለከሉም። ኑ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።›› እግዚአብሔርም ‹‹ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፣ ከተማይቱንም መስራት ተዉ›› ይላል ታላቁ መጽሐፍ።

ዛሬስ ቋንቋችን ጌጣችን፣ ውበታችን ወይስ በምድር ላይ የምንጋጭበት፣ የምንነቃቀፍበት፤ የምንጠፋፋበት፤ ከባሰም የምንበታተንበት አደገኛ መሳሪያ? ሌላስ በቋንቋ የገጠመን ችግር አለ? የፌደራሊዝምና የቋንቋ ችግሩ ተጣምረው ለኑሯችንና ለልማታችን እንቅፋት ይፈጥርብን ይሆን ወይስ በመቻቻልና በመወያየት መልስ ይኖረው ይሆን? እስቲ በዘመናችን ያሉትን ጥቂት እውነታዎች እንመርምር።

ኑ ለእኛ (ለባለሥልጣንና ለገዢዎች) ክልል (ከተማ) እና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንስራ ይላሉ። በአጭሩ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እየደረደሩ የእድገታችንም ምልክት ነው ይላሉ። በአንደኛው ገዢ ወገን፤ በሌላው ወገን ደግሞ የሰው ልጅ ሳይገነባ እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየፈረሰ /በነፃነቱና በሰብአዊነቱ ሳይከበር/፤ በክልል በመቀጠልም በዞንና በወረዳ ከተቻለም በቀበሌ በቋንቋ እየተከፋፈለ የሚኖርበት ግንብ እየተገነባ ነው ይላሉ። ለአብነትም ወልቃይትንና ጠገዴን ሌሎችንም መጥቀስ ይበቃል። በብዙ ቦታዎች ብዙ የድንጋይ ህንፃዎች እየተገነቡ የሰው አስተሳሰብና አመለካከት በመጨረሻም ሰውነት እየፈረሰ ነው፤ እነዚህ የግንባታ ቦታዎች የመልሶ ማልማት ስራው በሚጀመርበት ወቅት ቢፈርሱ እና በአፋጣኝ ወደ ስራ ቢገባ መልካም ነበር፡፡ አርቆ ማስተዋል ያደለው መሪና ካድሬ ጠፋ እንጂ። አሁን እየታየ ያለው ግን አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩትን ግንባታዎች እያፈረሱ፤ በውስጡ የነበሩትን ማፈናቀልና የቤት ችግርንና ኑሮን ማባባስ ነው። እነዚህ ቦታዎች ቅድሚያ ቦታውንና  የሽያጭ ተመኑን እንጂ ሰዎችንና ኑሯቸውን ታሳቢ አላደረጉም።

በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው እንደ ተባለው ገዢዎቻችን በምድር ላይ መበተንና መሞትን መቼ እንደሚከሰት የሚያውቁት አይመስለኝም። አላማቸው ሚሊየነር መባል፣ ባለ11-20 ፎቅ ባለቤት መባል፣ ባለሥልጣን ለዚያውም 25 አመት ቀሪው እስከ 40-45 አመት ልማት አልምተን ስማችንን እናስጠራ እያሉ ነው፡፡ ሰው የመሪውን፣ የወገኑን፣ የዘመዱን ስም አስጠራ ሲባል ምን ማለት ነው? ስምን በመጥፎም ስራ ማስጠራት ይቻላል? ሰው ተዋረደ የሚባለው ከህዝብ ተለይቶ የሚወርድበት ከፍታ ላይ፣ ስልጣን ላይ፣ ዝና ላይ፣ ሀብትና ሞገስ ላይ ሲገኝ ብቻ ነው። ፈጣሪ ብቻ ወርደው ከሚያዋርዱ ክስተቶች ይጠብቀን።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የህዝቧ ቁጥር ወደ 100 ሚሊየን መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ ቁጥር ውስጥ ከግማሽ በላይ ዕድሜው ከ25 በታች ነው። ይህም ከ50 ሚሊየን በላይ የሆነ ባለአፍላ ጉልበት የሰው ኃይል ኢህአዴግን በየአቅጣጫው እያወዛወዘው እንደ ሆነ ያረጋግጣል። ይህ ህዝብ በአግባቡ የሚያስተዳድረው ካገኘ፤ የሀገሪቱ የእድገትና ብሎም የጥንካሬ ምንጭ ሲሆን፤ በተቃራኒው ግን ችላ የሚባል ከሆነ የማኅበራዊ ቀውስ፣ የሁከትና የጦርነት መነሻ መሆኑ አይቀርም፡፡ የእያንዳንዱ ዜጋ እድገት የኢትዮጵያ ሕዝብ እድገት መሠረት ሲሆን፤ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት መሰረትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።

እነርሱ አንድ ወገን ናቸው እንደተባለው፤ እኛ ብቻ አንድ ወገን ነን፤ ሌላውን አናውቅም የሚሉ የሀጥያተኞች መንገድ የት ያደርሰናል? ሁሉም እርስ በርስ ወገን መሆኑ ቀርቶ፤ ዛሬ ወገን ማለት በአንድ ቋንቋ፣ ባህልና ወግ የተሳሰረ እየሆነ፣ የተለያየ ቋንቋ መናገር ሌላ ወገን ያሰኛል። ሁሉም ቋንቋ በፍላጎት የተፈጠረ ሳይሆን፣ በትዕቢታችንና በመጥፎ ስራችን መገኘቱን ያመነ ሰው ለምን ሌላውን ሰው በቋንቋው ሲጠቀም ይጠላዋል? ትክክል አይደለህም፣ እኔ አውቅልሀለሁ በማለት ይጠየፈዋል?  አበው ሲመርቁ፣ ‹‹ወይ መልካም ልጅ፣ ወይ መልካም ደቀ መዝሙር ይስጥህ›› ይላሉ፡፡ የሚረከብህ ማለታቸው ነው። መልካም ታሪክ ሠሪዎች ታሪካቸውን ለትውልድ የሚያስተላልፍ መሪ አጥተዋል። ገዢዎቻችን ሩጫቸው ለቋንቋ ወገናቸው እና ለግል ጥቅማቸው ሆኗል።

አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው። ቋንቋችን የተደባለቀው በጽድቅ ስራችን አይደለም። የክፋት፣ የሀጢዓት ውጤት ማለት ቋንቋ ነው፣ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማ ማድረግ ቅጣት አይደለምን? ኢትዮጵያ የበርካታ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ እምነትና ባህል ተከታዮች ሃገር እንደመሆኗኗ፤ እነዚህ ዜጎች ካለ ምንም አድልዎ ያላቸው እኩልነት ተረጋግጦና ማንነታቸው ተከብሮ በቋንቋቸው የመጠቀም፣ ባህሎቻቸውንና እምነታቸውን የማበልፀግ መብታቸው መከበር ይኖርበታል:: የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ወይም ባህልና እምነት ተከታዮች ጋር ተቀላቅለው ለሚኖሩ በቁጥር አናሳ የሆኑ ዜጎች መብቶቻቸው መከበርና ልዩ ጥበቃ በማድረግ ካልቀጠለ፤ በተወሰነ ብሄረሰብ ወይም ቡድን ላይ የኃይማኖትም ሆነ የቋንቋ እሮሮ ከበረታ፤ ቋንቋ መግባቢያ መሳሪያነቱ ይቀርና መጠፋፊያ ይሆናል።

በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው እንደተባለው፤ ዛሬም ለመበተን የሚያገለግል መንገድ አለ፤ ቋንቋ፡፡ ዛሬም ትዕቢት አለ፤ ኃጢአት አለ፤ ዜጎቻችንን መግደል አለ። ኢትዮጵያውያን በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ኑሯቸውን እየመሩ እንዳልሆነ እየታወቀ ዝምታው ምንድን ነው? ጥቅሙስ ለማን ነው? ህዝብ በረሃብ እንዳይሞት የኪነ-ጥበብ ሰዎች በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነትና ፍቅር መሠረት በማድረግ ለበጎ ተግባር ራሳቸውን ማሳለፍ በሌሎች ያደጉ አገራት የተለመደ ነው። ማኅበራዊ ኃላፊነት በኪነ-ጥበብ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው። በቀደመው ዘመን ኢትዮጵያ በረሀብ ስትመታ እነማይክል ጃክሰን፣ ቦብ ጊልዶፍ ወዘተ. ያላቸውን ተሰጥኦ ሰንቀው ለሀገራችን ችግር ቀድመው የደረሱልን ነበሩ። ዛሬ እስከ 20 ሚሊየን ሊደርስ የሚችል ህዝብ ለተፈጥሯዊው ድርቅና ለሰው ሰራሹ ረሃብ ተጋልጧል፤ በየቀኑ ሰዎች ይሞታሉ፣ ህጻናትም የዚህ ረሃብ ዋነኛ ተጠቂ ናቸው። ብዙ እንሰሳትም እያለቁ ነው። እንተባበር የሚል የጥበበኞች ድምጽ ግን የለም።

የቋንቋ አስተናባሪዎች አደገኛውን መንገድ ትተው ሰው በፈለገውና በመረጠው ቋንቋ የመጠቀም መብቱን ማስከበር አለባችሁ። ህዝባዊ ማስጠንቀቂያ በተለያየ መንገድ እየተላለፈ በመሆኑ ሰሚና አድማጭ ካለ፣ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠርና መስመራችንን መርምረን ለሀገራችን መፍትሄ ለማስቀመጥ፣ ጊዜ ሳናስረዝም ልንመካከርበት ይገባናል እላለሁ። ከሁሉም በላይ ፈጣሪንና ሕዝብን ማክበር በለመደ ማኅበረሰብ ውስጥ ለራስና ለጥቂት ወገኖች ብቻ ክብርን፣ ዝናን፣ ስልጣንንና ፍቅረ ንዋይን መሻት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአጭር ወይም በረዥም ጊዜ ቅጣትን ማስከተሉ የማይቀር ክስተት ነው። ማንኛውም ሰው በኃይማኖቱ፣ በፖለቲካ አቋሙ፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በቆዳ ቀለም …ወዘተ ምክንያት ሰብዓዊ ክብሩን መንካትና አመለካከቱን መቃወም እንዲሁም ጥቃትና መድልዎ መፈጸም በሰማይም ሆነ በምድራዊ ህጋችን ፈፅሞ የተከለከለ ነው።

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *