ዩሐንስ ሞላ
ዩሐንስ ሞላ

የሶስት አገራት ወግ
“በታንዛኒያ፣ በኬንያ እና በኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶች የኢንተርኔትና ስልክ አጠቃቀማቸው ምን ይመስላል? በየሚኖሩበት አካባቢ የሚያገኙት አገልግሎትስ?” በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ በቪኦኤዋ ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ አስተባባሪነት በስልክ ተወያይተን ነበር። (ውይይቱ እሁድ መጋቢት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. የተላለፈ ሲሆን፥ ድምጹ ድረ ገጻቸው ላይ ይገኛል።) እገምት እንደነበረውና ከውይይቱ እንተገነዘብኩት፥ በኬንያ እና ታንዛንያ በዛ ያሉ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ሲኖሩ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ክፍያቸውም ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር በጣም ርካሽ ነው። የኢትዮጵያው የግንኙነት ዋጋ (cost of communication) ከአጠቃላይ የኑሮ ዋጋ (cost of life) ከፍ ያለውን እንደሚሸፍን ተሰምቶኛል። – ምናልባትም ከቤት ኪራይ ጋር እየተፎካከረ!
የታንዛኒያዋ ወጣት፥ ያልተገደበ የኢንተርኔት አገልግሎት (unlimitted service) ለማግኘት በኢትዮጵያ ሁለት መቶ ሃምሳ (250) ብር ገደማ እንደምትከፍል ነግራናለች። የኬኒያው ተወያይም፥ ላልተገደበ የኢንተርኔት አገልግሎት በኢትዮጵያ ሰባት መቶ (700) ብር ገደማ ለኢንተርኔት እንደሚከፍል ነግሮናል። እኔ ደግሞ፥ ለ4 ጊጋ ባይት (4GB) መጠን ያለው የተገደበ ኢንተርኔት ለማግኘት አንድ ሺህ (1000) ብር እከፍላለሁ። እንዳጠቃቀም ሁኔታ፥ የእኔ 4 GB ኢንተርኔት በአንድ ቀንም የማለቅ አቅም አለው። እንግዲህ ልዩነቱን መረዳት፥ ተንታኝ የሚሻው አይደለም። ግልጽ ነው።
ወጋችንን ዓለማቀፍ ስናደርገው NUMBEO የተባለ ድረ ገጽ እናገኛለን። እዚያ “Prices by Country of Internet (10 Mbps, Unlimited Data, Cable/ADSL) (Utilities (Monthly))” በሚል ዘርፍ የኑሮ ዋጋን (Cost of life) ሲያሰላ፥ ኢትዮጵያን በ182.14 የአሜሪካ ዶላር ክፍያ በመጠየቅ ከ120 አገራት መካከል 1ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች “ውድ” አገር ይላታል። በመጨረሻ የተቀመጠችው፥ ለዚህ አገልግሎት 3.53 የአሜሪካ ዶላር የምታስከፍለው አገር ዩክሬይን ናት። (ከwww.numbeo.com ድረ ገጽ ሚያዝያ 3 የታየ) ሆኖም ግን፥ በኢትዮ ቴሌ ድረ ገጽ ላይ እንደሚታየው፥ ዋጋው ኑምቤኦ ላይ ከተጠቀሰው በጣም ይወደዳል። የ4Mbps, Unlimited Data, Cable/ADSL ዋጋ በወር 5,550 ብር (262 የአሜሪካ ዶላር ገደማ) ነው። ለዚያውም፥ የፍጥነቱ ጣሪያ 10 Mbps ሳይሆን 4 Mbps ነው።

What’s up ቴሌ!?
ስልክን እንደሰይጣን ሰራሽ ከመቁጠር አንስቶ ስለስልክ እስከመዝፈንና እስከመቀኘት የደረሰ ታሪክ አለው፥ ይህ ህዝብ። በስልክ አገልግሎት ግራ የመጋባቱን ያህል ቆይቶ ግንኙነቱን ማቀላጠፊያ እንደሆነ ሲገነዘብ ተደስቶበታል። ደግሞ “ተደሰትኩ፤ ግንኙነቴ ተቀላጠፈ” ሲል፥ በዚሁ በስልክ ምክንያት የደረሰበት መጉላላት ብዙ ነው። ከኔትዎርክ መቆራረጥ አንስቶ፣ ብሩ ካለታሪፍ ተቆርጦ እስከማለቅ፤ ከድምጾች መደበላለቅ አንስቶ የተላከን የጽሁፍ መልዕክት አዘግይቶ እስከማድረስ የደረሱ ትውስታዎች አሉን። በቴሌ ምክንያት ብዙ ሰው ተጋጭቷል። የጨጓራ ህመሞች ትክክለኛ መንስሄ መጠናት ቢችል፥ በቴሌ ምክንያት የሆነው ቁጥር ቀላል ሊባል እንደማይችል አስባለሁ።
“በስልክ አነጋግሪኝ በቀጭኑ ሽቦ
ትዝታ እንዲመጣ ደርቦ ደራርቦ።” የሚለው ዘፈን እንደ “ለምለሚቷ አገሬ” እያደር ስላቅ ለመሆን ምንም አልቀረውም ነበር። ቢሆንም ግን ሕዝቡ የሚሄድበት ሌላ አማራጭ፣ ድርጅቱም የሚወዳደረውና የሚፎካከረው ሌላ ስለሌለ፥ “ሃሎ ሃሎ…” ሲል ይውላል። “ሃሎ ሃሎ…” የሚሉ ዘፈኖችም በዙ። የሚኮረፍበትና አፍንጫ የሚነፋበት አማራጭ የግንኙነት አሳላጭ ድርጅት የለምና በታማኝነት የምንገለገልበት ድርጅታችን ነው፥ ኢትዮ ቴሌኮም! አንዳንዴ ማስታወቂያ በማስነገር ሲባዝኑና ማራኪ መሪ ቃሎችን (mottos) ለመናገር ሲባክኑ፥ “ምን ነክቷቸው ነው?” እላለሁ።
እንደዋዛ፥ በምናብ ወደ ዘ-ፍጥረት መቼት ገስግሼ፥ “አዳም ባንዲቱ ሴት በሄዋን ቀንቶ ያዙኝ ልቀቁኝ ብሎ ያውቅ ነበር ይሆን? ወይስ እርሱ ከወንዶች ሁሉ የተሻለ መሆኑን እንድታውቅ ይደሰኩርላት ነበር?” እላለሁ። ስለገቢና ትርፍ መጨመር ሲወራ ግን ወጪን መቀነስም አንዱ መንገድ ነውና፥ ኢትዮ ቴሌኮም በዚህ ረገድ ሊያስብባቸው የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ። ካላስፈላጊ ማስታወቂያዎችን ማቆም አንስቶ፣ ስብሰባዎችን እና የይስሙላ ጥናቶችን እስካለማከናወን! ሰሙንም አልሰሙንም፥ ቴሌ በሕዝብ የቆመ (“ለሕዝብ” አላልኩም) መስሪያ ቤት ነውና እንናገራለን!
አሁን ‘Connecting Ethiopia to the Future’ ነው የሚሉት። እንግዲህ “ለእነ ዋትስአፕ እና ቫይበር አስከፍላለሁ” እያለ ነው ኢትዮጵያን ከነገ ጋር ለማገናኘት የሚተልመው? በነጻ የጽሁፍ መልዕክት ማሰልቸቱን ትቶ፥ ከዛሬም ጋር እንድንገናኝ በተወን!
“ፖሊሲ ቻርጅ ኤንድ ኮንትሮል ሲስተም”
በኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎች ዘንድ በስፋት የሚታወቁትን ቫይበርና ዋትስአፕ የመሳሰሉትን አፕሊኬሽኖች ለመቆጣጠር፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሜ አቶ አንዱአለም አድማሴ “አለን” ያሉት ቴክኖሎጂ ነው። ለአፕሊኬሽኖቹ በኢትዮ ቴሌኮም ክፍያ ሊቆረጥ መሆኑ በካፒታል ጋዜጣ ላይ (በእንግሊዘኛ የሚታተም) ከተወራ በኋላ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ እዚህም እዚያም ተቃውሞዎች መነሳታቸውን ተከትሎ በመጋቢት 27 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮ ቴሌኮም የፌስቡክ ገጽ ላይ፥
“ክቡራን ደንበኞቻችን: በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ኢትዮ ቴሌኮም በቮይስ ኦቨር አይፒ (ማለትም ቫይበር፣ ዋትስ አፕ እና የመሳሰሉት አፕሊኬሽኖች) የተለየ ክፍያ ማስከፈል ሊጀምር ነው በሚል የተሳሳተ ዘገባ በዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዱአለም አድማሴ ስም ያወጡ ሲሆን ይህ መረጃ የተሳሳተ እንደሆነና የሚዲያ ተቋሙ እርምት የሚያደርግበት መሆኑን እየገለጽን፤ ክቡራን ደንበኞቻችንን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ እናመሰግናለን!” ብለው ለጥፈው ነበር።
በማግስቱ መጋቢት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ደግሞ፥ ሪፖርተር ጋዜጣ የድርጅቱ ዋና ኃላፊ ንግግር ይዞ ወጥቷል። (ሪፖርተር ላይም ስለተደገመ “ስህተት” የተባለውና ማስተባበያው አልገባኝም።) “ከአፕሊኬሽን ባለቤቶች ጋር መደራደር ሌላኛው አማራጭ ነው” ብለዋል። ሰዎች ግንኙነትን የሚያቀላጥፉበትን ቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅት፥ “ከምታገኘው የማስታወቂያና ሌሎች ገቢዎች ተቆራጭ እንድታደርግልን” ተብሎ ሲጠየቅ ምን እንደሚል ማሰብ ነው እንግዲህ። ራሳቸው አፕሊኬሽኖቹ ጥርስ አውጥተው እንዳይስቁ እንጂ ሌላው ቀላል ነው።
“በኢንተርኔት አማካይነት የድምፅና የምሥል ጥሪዎችና መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ አፕሊኬሽኖች፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከውጭ ጥሪዎች ማግኘት የሚችለውን ከፍተኛ ገቢ እንዳስቀሩበት ተገልጿል፡፡” ይሄ ነገር በደፈናው ሲታይ ስሜት የሚሰጥ ቢመስልም፥ አተኩረው ሲመለከቱት በሂሳብ ቀመር የተቀናበረ አይመስልም። ከዚህም ባሻገር፥ አፕሊኬሽኖቹን የሚጠቀም ሰው ቀላል የማይባል የኢንተርኔት ክፍያ ስለሚቆረጥበት፥ ገቢው ከውጭ አገር ጥሪዎች ያገኙ የነበሩትን የሚያካክስ/የሚበልጥም ሊሆን ይችላል።
በዚያም ላይ፥ ያን ያህል የሚያኮራ የኢንተርኔት ፍጥነት ስለሌለና፣ “እንዳይቆጥርብን” በሚል ፍርሃት የስልክ ኢንተርኔታችንን አጥፍተን ስለምንቆይ፣ ሰዎች አሁንም ቢሆን ለአስቸኳይ እና ቁም ነገር መልዕክቶች መደበኛውን ስልክ ነው የሚጠቀሙት። እነ ቫይበር እና ዋትስአፕ፥ ድሮ ቢሆን ትዝ ሳይባባሉ የሚታለፉ ጊዜያትን በመሸፈን፣ የተሻሉ መቀራረቦችንና መግባባቶችን ነው የፈጠሩት። ከአንድ የውጭ አገር ጥሪ የሚያገኙትን የተጣራ ገንዘብ ገልጸው ቢሆን ኖሮ ግን፥ መለስተኛ ስሌት በማድረግ የማወዳደርና ነገሩን የመመርመር ስራ ለመስራት ቀላል ይሆን ነበር። እሱም ነገሩን በገራገርነት ከገቢ ማሳነስ ጋር ከተመለከትነው ነው።
“አጭበርባሪዎቹ”
የዛሬ 2 ዓመት ገደማ “ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ወይም ኩባንያዎች ድብቅ መሳሪያ ተክለው ከውጪ አገር የሚደውሉ የስልክ ጥሪዎችን በራሳቸው መሣሪያዎች በመቀበልና ለደንበኞች በማስተላለፍ በሕግ የተከለከለ የስልክ አገልግሎት እየሰጡ ነው ሲል ኢትዮ ቴሌኮም አረጋገጠ።” የሚል ዜና በድረ ገጾች አማካኝነት ሲሰራጭ ተመልክተን ነበር። የኢሳት ዜና ዝርዝር፥ 9 ዓመታትን ወደኋላ ሄዶ ሲያወሳም “በ1995 ዓመተ ምህረት ሟቹ ኢያሱ በርሄ እና ሌሎች ግለሰቦች በህገ-ወጥ መንገድ ባስገቧቸው የቪሳት መሳሪያዎች ተመሳሳይ አገልግሎት ሢሰጡ ተይዘው ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል።” ይላል። በነጻ መሰናበታቸውንም ያስታውሳል። “ለተከሳሾቹ በነፃ መሰናበት በፍርድ ቤት በኩል የተጠቀሰው ምክንያትም፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የደረሰበትን ኪሳራ በሚገባ ለፍርድ ቤቱ ማቅረብ አልቻለም የሚል እንደሆነም አይዘነጋም።” ብሎም ነበር። (ኢሳት ዜና: ግንቦት 1 ቀን 2004 ዓ.ም.፤ በሚያዝያ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረ ገጹ ላይ የታየ)
የአጭበርባሪ ግለሰቦቹ ጉዳይ በተለያዩ የኢትዮ ቴሌኮም ዜና መግለጫዎች ላይ የሚጠቀስ እንደሆነ ይታወቃል። አቶ አንዷለምም፥ ለሪፖርተር “በአሁኑ ወቅት ክፍያ ለማስከፈልም ሆነ በማጭበርበር ተግባር ላይ የተሰማሩትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ባለቤት ነን። ነገር ግን ክፍያ ለመጣል አልወሰንም፤” ብለዋል። ሌላ ሌላውን ትተን የቴክኖሎጂው አዎንታዊ ፋይዳው ላይ ካተኮርን፥ ከዚህ ቀደም ክሱን እስከማቋረጥ ያደረሳቸውን ነገር በመተንተን፣ ቀድመው አጭበርባሪዎቹን በመቆጣጠር ስለመጀመር ቢናገሩ፥ ለሰሚ ጆሮ የተሻለ ስሜት የሚሰጥ ይሆን ነበር። “በማጭበርበር ተግባር ላይ የተሰማሩትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ባለቤት ነን” ብሎ፥ ለአንድም ቀን በትዕግስት ማሳለፍ ግን በህገ ልቡናም በህገ ወንጌልም ያስወቅሳል!
ዲያስፖራና የሚልከው ገንዘብ (Remittance)
“ኢትዮጵያና ኬንያ በውጭ ከሚኖሩ ዜጎቻቸውና ተወላጆቻቸው የሚላከው ገንዘብ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት አንፃር የተሻለ እድገት ማሳየቱን የአለም ባንክ አስታወቀ።” የሚል ዜና ያወራልን፥ ኢብኮ ዴይሊኔሽንን ጠቅሶ ነበር። ሲዘረዝር፥ የአገራቱ ብሄራዊ ባንኮች ባወጡት መረጃ የቀደሙት አመታት ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ የተላከው ገንዘብ በኢትዮጵያ 88 በመቶ ማደጉን አውስቶ፥ “የዘርፉን ፍሰት ብቻ በ50 በመቶ እንዲጨምር አድርጎታል።” ብሎናል። (EBC ዜና: ጥቅምት 23፣ 2008፤ በሚያዝያ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረ ገጹ ላይ የታየ)
በዚሁ ዓመት ታህሳስ ወር፥ “የዲያስፖራ የታመቀ አቅም ለእድገትና መዋቅራዊ ለውጥ” በሚል መሪ ቃል፥ ለ2 ቀናት የቆየውና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ በተካሄደበት ወቅት የሰማነው የኢብኮ ዜና ደግሞ “ኢትዮጵያ ከዲያስፖራ የምታገኘው የገንዘብ ፈሰስ ከውጭ የቀጥታ ኢንቨስትመንትና የልማት እርዳታ ከምታገኘው በ200% የበለጠ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የንግድና ልማት ጉባኤ /UNCTAD/ አስታወቀ።” ብሎን ነበር። ለሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተስፋ መጣሉም ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም “ኢትዮጵያ ከዲያስፖራ የምታገኘው ፈሰስ ገቢ በቀጥታ ኢንቨስትመንትና በብድር ከምታገኘው የበለጠ ሲሆን አገሪቱ ከንግድ የምታገኘውን 90 በመቶ የሚሸፍን ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑን በጉባኤው ተመልክቷል።” ተብሏል። የዲያስፖራውን አቅም አሟጦ ለመጠቀም መሻሻል ስለሚገባቸው የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታዎችም በመድረኩ ላይ ተንፀባርቀዋል። (ኢብኮ ዜና: ታህሳስ 13 ቀን 2008 ዓ.ም.፤ በሚያዝያ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ከድረ ገጹ ላይ የታየ)
እንግዲህ ይሄ ተብሎ ነው ስለ ኮሙኒኬሽን ወጪዎች ጭማሪ የተወራው። የኮሙኒኬሽን ወጪዎች ጭማሪውም በዋናነት፥ የአገር ቤት ነዋሪ ውጭ ካለ ዘመዶቹ ጋር ሊገናኝ በሚችልበት ላይ ነው። በርግጥ የዲያስፖራ ገንዘብ መጨመር/መቀነስ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ምክንያቶች ብዙ ናቸው። የስደት መብዛት/ማነስ፣ ስደተኞቹ የሚኖሩባቸው አገራት ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ የነዳጅ ዋጋ ሁኔታ፣ ሌላም ሌላም ሊጠቀሱ ይችላሉ። የግንኙነት ወጪ ከፍ ማለትም አብሮ መነሳት ይችላል። እነ ቫይበር በመኖራቸው ምክንያት፥ ዲያስፖራው ማትረፍ የሚችለውን ብር፣ ለቤተሰቦቹ የሚልከውን ገንዘብ እንዲያሳድግ አቅሙን ያበዙለት ይሆናል። ከቤተሰቦቹ ጋርም በስልክ ርቀት ስለሚሆን (a phone call away) ልቡ በዚህ ይኖራል። “አንገናኝም” ያሉ ሰዎች በእነዚሁ አፕሊኬሽኖች አማካኝነት ተገናኝተው ትልልቅ ስራዎችን ሰርተዋል። ስለሆነም፥ “ገቢዬ ቀነሰ” ሲባል እንዲሁ በአረፍተ ነገር ቅመራ ፍጥነት ሳይሆን፣ በስሌት እና በጥናት መሆን ይኖርበታል።
“በኢንተርኔት አማካይነት የድምፅና የምሥል ጥሪዎችና መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ አፕሊኬሽኖች፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከውጭ ጥሪዎች ማግኘት የሚችለውን ከፍተኛ ገቢ እንዳስቀሩበት ተገልጿል።” የሚለው ውሀ የሚያነሳ ንግግር አይደለም። ተቋሙ ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር እንጂ፥ “እንዲህ ባይሆን ይሄን ያህል አገኝ ነበር” የሚል ‘opportunity cost’ ማስላት የለበትም። ካልሆነም፥ ምስሉን ለጠጥ አድርጎ በዋናነት የአገርን እና የሕዝብን ጥቅም ማስከበር ላይ ማተኮር ነበረበት። ይሄ እኮ፥ “የዓለም የቴሌኮም አገልግሎት በእኛ ስር ቢሆን ኖሮ፥ ከዓለም አንደኛ ሀብታሞች እንሆን ነበር።” ከማለት የሚተናነስ ሀሳብ አይደለም።
“አሜሪካዊ ብንሆን ኖሮ እኮ ይህን ያህል ሰው አይራብም ነበር!” “አውሮፓውያን ብንሆን ኖሮ እኮ ሀሳባችንን በነጻነት እንገልጽ ነበር!” እንደነዚህ እና እንደሌሎች ብዙ ገራም ድምዳሜዎች!
“አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል!”
የቴሌኮሙኒኬሽንን ጽንሰ ሀሳብ ጊዜና ባለአዕምሮ እንዳመጣቸው ሁሉ፥ የአፕሊኬሽኖቹንም ነገር እንደዚያ ነው። ስለዚህ ጊዜ ባመጣቸው ትሩፋቶች “ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የወጣበትን የቴሌኮም መሠረተ ልማት ያለባለቤቱ ዕውቅናና ተጠቃሚነት የሚገለገሉና ከፍተኛ ትርፍ ለራሳቸው የሚያካብቱ ናቸው፤” ማለት እንዴት ጤናማ እንደሚሆን አላውቅም።
የቴሌኮሙኒኬሽን ጽንሰ ሀሳብ ባለቤት የኢትዮጵያ አይደለችም! ኢንቨስትመንቱም ከዘ-ፍጥረቱ አንስቶ ከሕዝብ ተሰብስቦ እንጂ፥ ከሌላ አይደለም። ቴሌ፥ መንግስት ሌላ ሌላ ስራ ሰርቶ አተራርፎ ያቀናው ድርጅት አይደለም። እቁብ ገብቶ፣ አልያም ዳቦ በሻይ እየበላ ቆጥቦ የከፈተው ካምፓኒ አይደለም። ከነኋላ ቀርነቱ በጊዜ ወደ አገር ገብቶ፥ በጊዜ የሚሻሻል መሰረተ ልማት ነው። በአሁኑም ሰዓት፥ ከፍተኛ ትርፉን የሚያገኘውና ለራሱ የሚያካብተውም “የሚታለበው ላም” ቴሌ ነው።
ማንሳት ካስፈለገ፥ እናነሳለን። የቴሌኮም አገልግሎቱ አልበቃ ብሎት ስልክ ወደ መቸርቸር የገባው ቴሌ ነው። አዳዲስ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በመቀየር ሰበብ ሕብረተሰቡን ተጨማሪ የapparatus ወጪ የሚያስወጣው (ለምሳሌ ከEVDO ወደ 3G ሲያሻግሩን) ቴሌ ነው። የሞላነውን ካርድ መቆጣጠር በማንችልበት ግልጽ ያልሆነ አሰራር የሚገዛን ቴሌ ነው። ከሸፍጠኛ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በጥያቄና መልስ እና በስነ-ልቡና ምክር ስም በሚመጡ የጽሁፍ መልእክቶች የሚጫወተው ቴሌ ነው።
የዚህን ምስኪን ነዋሪ ኑሮን በግንኙነት ወጪዎች (communication cost) መደጎም ማሰብ ቢቀር፥ ከፍተኛውን ወጪ ለግንኙነት እያወጣን ባለበት ሁኔታ እንዲህ ያለ ነገር ግፍ ይሆናል። ደግሞ ግንኙነት ሲቀላጠፍ እና ሕዝብ የግንኙነት ወጪ ሲቀንስ፥ ገንዘቡን ቀቅሎ አይበላው ነገር፤ …ስራ በተሻለ መልኩ ተሰርቶ ኢኮኖሚው ያድጋል እንጂ?!
በmacro economics ጽንሰ ሀሳብ ብናየው፥ ዓለማቀፍ የግንኙነት ወጪዎችን መቀነስ ማለት፥ ዓለምን አጥብቦ ስራዎችን ከማቀላጠፍ ባሻገር፣ የዲያስፖራውን ወጪ በመቀነስ፥ ወደ አገር የስራ ሀሳቦችን ይዞ እንዲመጣ ማነቃቃት፣ አገር ውስጥ የሚላከውን ገንዘብ (remittance) ማሳደግና የአገር ውስጥ እንቅስቃሴን መደገፍ ማለት አይደለምን? ታዲያ ይሄ ብዙ የተወራለት፣ የተጓጓለት እና ዘወትር የሚንቆላጰሰው ከዲያስፖራ የሚገኝ ሀብት ማሳደግ እንጂ ሌላ ምን ነገር አለው? ደግሞ ምን ያህሉ የስልክ ተጠቃሚ ኢንተርኔት ይጠቀማል?
“ለየት የሚያደርገው. . .”
“የዘንድሮን ሚሊኒየም ለየት የሚያደርገው ከእንቁጣጣሽ ጋር አብሮ በመዋሉ ነው።” እንዳሏት ገዳይ ንግግር አይነት፥ “ለየት የሚያደርገው”! የቴሌ ለአፕሊኬሽኖች የማስከፈልን ሀሳብ ለየት የሚያደርገው፥ “እኔና ሌሎች ሁለት አፍሪካ አገራት ውስጥ የምንኖር ወጣቶች በኢንተርኔት ዙሪያ ቪኦኤ ላይ በተወያየን ማግስት መወራቱ ነው።” አልልም። “ሀሳቡን ለየት የሚያደርገው” በመደዳ “ተሸለምኩ” እያለን፥ እኛም “መሸለም ያዳብር” እያልን፥ ካንገት በላይ እየተመራረቅን ባለንበት ሰዓት መሆኑ ነው።
“ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. በፓሪስ ከተማ በተካሄደውና የዓለም አቀፉ የንግድ መሪዎች ክበብ ባዘጋጀው የሽልማት ፕሮግራም ላይ ኩባንያው፥ ላስመዘገበው የቢዝነስ ሥራ አመራር ጥራት ቁርጠኝነት “የ2015 ኢንተርናሽናል የአውሮፓ ጥራት” ተሸላሚ ሆኗል።”፣ “ህዳር 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በሞሪሺየስ በተካሄደው የ2015 የአፍሪካ ቴሌኮም ሊደርሺፕ ሽልማት ላይ በአራት ዘርፎች ማለትም የዓመቱ ምርጥ የቴሌኮም ኦፕሬተር፣ የዓመቱ ምርጥ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ምርጥ የሰው ሃይል ተኮር ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም ግሎባል ሰስቴይነብሊቲ አመራር ሽልማት በሚሉት ዘርፎች ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት አቻ ተቋማት ጋር በመወዳደር አሸናፊ በመሆን ተሸላሚ ሆኗል፡፡” እንዲሁም “መጋቢት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በእንግሊዝ አገር በተጋሄደው የአውሮፓ ቢዝነስ ጉባኤ ላይ “የዩናይትድ ዩሮፕ ሽልማት” እና “ዓለም አቀፍ የሶቅራጥስ ሽልማት” አሸናፊ በመሆን በሁለት ዘርፎች ተሸላሚ ሆኗል።” የሚሉትን ዜናዎች በዚሁ ዓመት ከኢትዮ ቴሌኮም የሰማናቸው ናቸው።
“የሽልማቶቹ መስፈርቶችና ሀቀኝነት ይመርመሩልን አንልም”፤ ፈጣሪ ኢትዮቴሌኮምን በካድሬዎች ወይም በሸላሚዎቹ ድርጅቶች ዐይን ያሳየን ዘንድ እንመኛለን እንጂ!
“እምቧ በይ ላሚቱ. . .”
በመጋቢት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ደግሞ “ኢትዮ ቴሌኮም በ2008 በጀት ዓመት የመጀመሪያው መንፈቅ አበረታች ውጤት አስመዘገበ” ብሎናል። ልብ አድርጉ፥ “የቴሌኮም አገልግሎትን በሃገራችን ከማስፋፋት፣ የቴሌኮም ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከማሳደግ እና ደንበኞች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር አበረታች ውጤት አስመዘገበ።” ነው የተባለው። ታዲያ ይህ በተባለበት ሁኔታ ነው፥ የደንበኞችን አጠቃቀም ሊጎዳ እና ተገልጋዮችን ሊቀንስ የሚችል ውጤት ለማስመዝገብ ደፋ ቀና የሚለው።
የሞባይል ስልክ የደንበኞች ቁጥር አፈጻጸም (በመቶኛ) 92፣ የዳታ እና ኢንተርኔት 103፣ የብሮድባንድ 122፣ ናሮውባንድ፣ 216፣ የሞባይል ኢንተርኔት 98፣ የመደበኛ ስልክ 46 በመቶ መሆናቸው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ ሰኔ 2007 ላይ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ሁሉም ዘርፎች ላይ ያሉት የደንበኞች ቁጥር በሺዎች እድገት አሳይተዋል። በ2008 ግማሽ በጀት ዓመት የገቢ አፈጻጸምን በተመለከተ ከሁሉም የአገልግሎት ዓይነቶች 13.4 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ያልተጣራ ትርፍ መጠን 10.09 ቢሊየን ብር ሲሆን ይህም የእቅዱን 111 በመቶ አፈጻጸም የሚያመላክት ሲሆን፣ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ33 በመቶ እድገት አሳይቷል። (ከኢትዮ ቴሌኮም ድረ ገጽ የተገኘ መረጃ)
ታዲያ ከየትኛው ያልተጣራ ትርፍ መጠን እቅድ ነው ገቢው የጎደለው?
“አታባረው፣ እንዲሄድ አርገው።”
“በሌላ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም ‹‹ኢኪዩፕመንት አይደንቲቲ ሬጂስተር›› ማለትም ያልተቀረጡ የሞባይል ስልኮች ወይም የተሰረቁ የሞባይል ስልኮችን ከአገልግሎት ውጪ ማድረግ የሚያስችለው ቴክኖሎጂ ባለቤት መሆኑንም ተናግረዋል።” ሴንሰርሺፕ እና ስግብግብነት ሲቀሸሩ ካልሆነ በቀር፥ ዓላማው ከኢትዮ ቴሌ ይልቅ ለገቢዎች የሚቀርብ ነው። በነገራችን ላይ፥ የአፕሊኬሽኖቹ ክፍያ ወሬም በቀጥታም በተዘዋዋሪም ሳንሱር የማድረግና የሀሳብ ነጻነትን የማቀጨጭ ተጽዕኖ አለው። በቀጥታ፥ በክትትል እና ንግግሮችን ሳንሱር በማድረግ። በተዘዋዋሪ ደግሞ፥ ሰዎች የግንኙነት ዋጋ ሲንር ሀሳባቸውን ይሰበስቡ ዘንድ ይገደዳሉ ተብሎ ስለሚታሰብ።
ኢትዮ ቴሌኮም ስለግለሰቦች መሰረቅ ያን ያህል ግድ ቢሰጠው ኖሮ፥ በተለያዩ ጊዜያት በስህተት ስለተቆረጡብን ካርዶች ግድ ሰጥቶት መመለሱ ቢቀር ማስተባበያውን ያደርስ ነበር። ለተሰረቁ ስልኮች ግድ ከሰጠው፥ በውድ እየገዛን የምንጠቀመውን ኢንተርኔትና ስልክ “ከምስራቅ አፍሪካ ርካሽ ታሪፍ” በማለት አይቀልድብንም ነበር። “ሲም ካርድ ግዙ” ብሎ ሲም ካርድ ያለው ግለሰብ ጋር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ የሚያሰለቸን ቴሌ፥ ቀፎን ከሲም ካርድ ጋር ማቆራኘትን ጠቀሜታ ሲነግረን ያሳፍራል።
“አታምጣው ስለው. . .”
እንዳለው፥ ዳንኤል ብርሀኔ (የሆርን አፌይርስ ጦማሪ እና ወዘተረፈ) “ቀጥሎ ደግሞ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ይመጣና፣ “ሰዎች ኢሜይል በመጠቀማቸው ብዙ ገቢ እያጣሁ ነው፤ ስለዚህ ኢሜይል በላካችሁ ቁጥር ክፈሉኝ” ይበል። ለቁጥጥር እንዲያመች የሁላችንም ኮምፒውተር ቢመዘገብም ይቻላል።
መብራት ሀይልም “ሰዎች በፀሐይ ብርሀን እየተጠቀሙ ገቢዬ ቀነሰ” ይበል።
በቅሎኞችም፥ “መልእክት ይዘን ከአገር አገር እንዳንንቀሳቀስ ትራንስፖርት መሻሻሉ ጎዳን” ይበሉ። በዚህ አያያዙ፥ “አይሉም” አይባልም።
የሰው ልጅ አዕምሮ “አይፈጥርም” የሚባለው ነገር የለምና፥ ከችግራችን በላይ ሆነን ከክፋታቸው በታች እናውላቸው ዘንድ ተስፋ እናደርጋለን! “ችግር በቅቤ ያስበላል”ና!
ሰላም!

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *