ቴዎድሮስ ጸጋ

ያቤፅ ይባላል፤ ተወልዶ ያደገዉ ፒያሳ ደጃች ዉቤ ሰፈር ሲሆን ወላጅ እናቱ ያለአሳዳጊ አባት፤ አረቄ እየቸበቸቡ ነበር በመከራ ያሳደጉት፡፡

እቅዱ ትምህርቱን ጨርሶ እንደተመረቀ ወደ ስራዉ አለም ተቀላቅሎ እናቱን ማገዝ ነበር! ይሄዉ ዕቅዱ እንዲሰምርለትም ሊመረቅ አንድ አመት ሲቀረዉ የገዢዉ ፓርቲ አባል እንዲሆን ሲጠየቅ ሳያቅማማ ወዲያዉኑ ነበር እሽታዉን የገለፀላቸዉና አባል የሆነዉ፡፡ ፖለቲካን ባያዉቅም፤ ከስራ ገበታ ጎድሎ የመከራዉ ዘመን እንዳይራዘም፤ ፖለቲከኛ ለመሆን ወሰኖ፤ ፎቶዉና ሙሉ ስሙን በትምህርት ቤቱ ለተኮለኮሉት ካድሬዎች ሰጠ፡፡ በቅርብ ቀን ዉስጥ በኢህአዴግ አርማ ህብረ ቀለማት ያሸበረቀ መታወቂያ እጁ ላይ ደረሰ፡፡ መታወቂዉ እጁ ላይ እንደደረሰ፤ ሁሉ ነገር የሰመረለት መሰለዉ፡፡ አንድ ሸክም የቀለለት ያህል ተሰማዉ፡፡ ትምህርቱን ከጨረሰ ስራ እንደማያጣ ተማመነ፡፡ ዳሩ የተሰመረለትን ቀይ መስመር ካላለፈ፤ ኢህአዴግን ተጠግቶ ማን አፍሮ ያዉቃል?! እሱም ጠንቅቆ ያዉቃል! ሰፈር ዉስጥ አብረዉት አፈር ፈጭተዉ፤ ያደጉ ሰዎች በአንድ ለሊት የሀብት ማማ ላይ ራሳቸዉን እንዳገኙ፡፡ እንደዉም ስለነሱ ባሰበ ቁጥር አንጀቱ ያራል፤ አንድ ሰፈር ዉስጥ አብረው እንዳላደጉ፤ ለቡሄ በአል ሆያ ሆዬ፤ ለጥምቀት ጃንሜዳ ዉስጥ ምድር አልበቃ ብላቸዉ አብረዉ በአርሞኒካ በኣሉን እንዳላደመቁ፤ ቢጢኛና ኮቾሮ አብረዉ ቆርጥመዉ የልጅነት ዘመናቸዉን እንዳላሳለፉ፤ ዛሬ ቦርጫቸዉ ቢዘረገፍ እንደማያዉቁት ሆኑ፤ ብርቅ ሆኖባቸዉ የእግዜር ሰላምታን ነፈጉት፡፡ ከዚህ የተነሳ ይጠላቸዋል፡፡ ነገር ግን ህልም አለዉ! አንድ ቀን ትምህርቱን ጨርሶ እሱም እንደእኩዮቹ፤ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ፤ ልማታዊ መንግስታችን አምኖ ተጠምቆ፤ እነሱ የሚነዱትን ዉድ መኪና እንደሚነዳ፤ እነሱ የሰሩትን ቪላ ቤት እንደሚሰራ፤ እናቱን ከመሸታ ንግድ እንደሚያላቅቃት፡፡

መቼስ እንዳይደርስ የለም፤ እነሆ በያቤጽ የተናፈቀች ያቺ የተባረከች የምርቃት ቀን ደረሰች፡፡ እናቱ በመጠነኛ ድግስ ወዳጅ ዘመዶቻቸዉን ጠርተዉ ልጃቸዉን ለማስመረቅ በቁ፡፡ ያቤፅም የአመታት ልፋቱ፤ በዚያ ከሩቅ ዘመን ጀምሮ የተዘራዉ ዘር ተሰብስቦ ወደ ጎተራ የሚገባበት የመህር ወቅት የደረሰ መሰለዉ፡፡ ከጥቂት ቀናት በሁዋላ ግን ያለመዉ መልካም ህልም፤ በህይዎቱ ዙሪያ ያቀደዉ በጎ እቅድ የማይፈጸም ከንቱ፤ እዚህ ግባ የማይባል መናኛ ቅዠት መሆኑ በግልፅ ገባዉ፡፡

ስራ ፍለጋ ያላንኳካዉ የግሉም ይሁን የመንግስት መስሪያ ቤት የለም፡፡ ተማሪ ቤት እያለ ከሚጨነቀዉ በላይ አሁን መጨነቅ ጀመረ፡፡

በተለይ ሰፈር ዉስጥ ሰዎች እሱን እያዩ ስለምንም ነገር ሲያወሩ ሲስቁ በእሱ የተዘባበቱ እየመሰለዉ ክፉኛ ይናደዳል፤ ለዐይን በማይታይ ዱላ ህሊናዉ ይደበደባል፡፡ እንደ አዉሬ ከሰዉ መራቅን መረጠ፤ ያለወትሮዉ እንደ ክፉ በሬ፤ ከሰዉ ሁሉ ጋር መባላት ጀመረ፡፡ ምን ይሄ ብቻ ከራሱም ጭምር መጣላት ስራዉ ሆነ፡፡ እናትየዉ ቤታቸዉ ጠጥተዉ በሚሰክሩ ሰካራሞች፤   ሲሰደቡ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ እየሰማ ያደገ ቢሆንም አሁን አሁን ግን እናቱ ሲሰደቡ ሲመለከት፤ ዉስጡ ይቆጣ ጀመር፡፡

በጥቅሉ ሁሉ ነገር ያቤጽን ያስከፋዉ ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ አንድ አንዴ ደግሞ በልጅነቱ ሰፈር ዉስጥ ፈንጂ ሲጨፈጭፍ፤ ፍንጣሪዉ አንድ እግሩን ይዞበት ሄዶ አካለ ጎዶሎ እንዳደረገዉ ያስብና ይበሳጫል፡፡ አካለ-ስንኩልነቱ እንደልቡ ያሻዉን ስራ እንዳይሰራም እንዳገደዉ አድርጎ ያስባል፡፡ በአንዲት እርጉም ቀን፤ በህይወት ዘመኑ ለአንድም ቀን በህልሙም ሆነ በእውኑ አስቦት የማያዉቀዉ ነገር ወደ አእምሮዉ ጓዳ ሰተት ብሎ ገባ፤ ለትንሽ ደቂቃ ከራሱ ጋር ካወራ በኋላ፤ በመጣለት ሃሳብ ተስማምቶ እስኪመሽ ጠብቆ፤ ወንጀሉን ሊሰራበት ወደ አሰበዉ ቦታ ሄዶ ጨለማ ዉስጥ ጥግ ላይ ቆሞ፤ አለባበሱ ያማረለትን፤ ሰዉ መጠበቅ ያዘ፡፡ እሱ እዚያ ቦታ ከቆመ ጊዜ ጀምሮ በግምት ግማሽ ሰዓት ያለፈዉ ቢሆንም ብዙ ሰዎችም በዚያ ቦታ አልፈዉ ሄደዋል፡፡ ..በአይኑ ሲመለከታቸዉ ከእሱ የተሻለ ህይወት የሚኖሩ ግን አልመስልህ አለዉ፤ አሁንም ተስፋ የመቁረጥ ባህሪዉ ድንገት ደርሶ ብልጭ አለበት፤ ለጥቂት ደቂቃ ቆሞ መጠበቁ የተሻሉ እንደሆነ አሰበና እዛዉ ተገተረ፤ እንደ ድንገት አንድ ዉጫዊ አካሉ በጨርቅ ያማረ፤ ልጅ እግር ጎረምሳ ነገር ወደ ራስ መኮንን ከምታወጣዉ ቅያስ መንገድ ዉስጥ ለማለፍ ከላይ በጥድፊያ ሲመጣ አየና፤ የብረት መደገፊያ ክራንቹን መሬት ላይ ጣል አደረገ፤ ወጣቱ ልጅ እንደቀረበዉ የወደቀዉን ክራንች እንዲያቀብለዉ ለመነዉ፤ ምስኪኑ ወጣት ልጅ ክራንቹን ሊያነሳለት፤ ጎንበስ አለ፤ ያቤጽ በጭካኔ ሊረዳዉ ያሰበን ሰዉ፤ ተደግፎት በቆመዉ አንድ የብረት ክራንች ማጅራቱን ብሎ ደፋዉ፤ ወጣቱ ልጅ ከወደቀበት ቀና ሳይል እዛዉ ተዘርግቶ ቀረ፡፡

ያቤጽ በፍጥነት እጆቹን ወደ ኪሱ አስገብቶ የዝርፊያ ወንጀል አካሄደበት፡፡ ወደቤቱ ገብቶ ብዙም ሳይቆይ ወሬዉ፤ ቤታቸዉ በሚጠጡ ጠጪዎች መናፈስ ጀመረ፤ ልክ በቦታዉ እንዳሉ አድርገዉ ያልሆነዉን ፈጥረዉ አጣፍጦ ተቀባብሎ ሲያወሩ፤ ሳቁ መጣ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ያለጥርጥር የሌብነት ስራ እንደሚያወጣዉም ተማመነ፡፡ ጠዋት አንድ አንድ ነገሮች ለመግዛት ማልዶ ተነሳ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለዉ? ልክ ፊቱን ተጣጥቦ፤ ከቤት ሊወጣ እየተሰናዳ ሳለ ሶስት ፖሊሶች ከፊቱ እንደ ሀዉልት ተገትረዉ ቆመዉ ‹‹አንዴ ቢሮ ልናግርህ እንፈልጋለን›› ሲሉ መሃላቸዉ አስገብቶ እንደበግ እየነዱ ብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ጋር ወደአለዉ፤ ፖሊስ ጣቢያ ወስደዉ አሰሩት፡፡ በሳምንቱ አቃቤ ህግ ክስ መስርቶበት ለፍርድ ቀረበ፡፡ ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪዉ ላይ ለመፍረድ ለጠየቀዉ ማስረጃ፤ የግል ተበዳይና፤ የግል ተበዳዩን ከወደቀበት ለማንሳት ሲረዱት የነበሩ ወጣቶችን ለምስክርነት ዳኛዉ ፊት አቆማቸዉ፤ መስካሪዎችም ቃለመሃላ ከፈጸሙ በኋላ፤ በወቅቱ የግል ተበዳዩን ከወደቀበት ለማንሳት ሲሞክሩ፤ መሬት ላይ ወድቆ ያገኙትን የያቤጽን ማንነት የሚገልጽ መታወቂያ ካርድ ማግኘታቸዉን ለፍርድ ቤቱ አስረዱ፡፡ የግል ተበዳይም የደረሰበትን የዝርፊያ ወንጀል ከሀ እስከ ፐ ለፍርድ ቤቱ አስረዳ፡፡ ያቤጽ በበኩሉ ክሱን መቃወም አቅቶት እንደ እንጨት ደርቆ ቀረ፡፡ እጁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በአምስት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ወስኖ፤ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ተመለሰ፡፡

ከአራት አመት ሁለት ወር ቆይታ በኋላ ያቤፅ አሁን ከእስረ ተፈታ፡፡ ከእስር ቤት እንደተፈታ ከቀድሞዉ የባሰ ችግር ገጠመዉ፤ እንደሰካራም ራሷን ችላ መቆም አቅቷት፤ ተንጋዳ ቆማ የነበረችዉ ቤታቸዉ፤ በልማት ስም ፈርሳ እናቱ ጎዳና ላይ ወጥተዉ አገኛቸዉ፡፡

በዚህ ላይ ያቤፅን የሰፈሩ ሰዉ አገለለዉ፤ ድፍን የሰፈሩ ሰዉ በሙሉ እሱ ሲመጣ ከሩቅ አይተዉ በስሙ ከመጥራት ይልቅ ዝናቡ መጣ እያለ በቅፅል ስሙ መጥራት ጀመረ፤ በዚህ መሃል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስራ ሊፈልግ አቅራቢያዉ ወደሚገኘዉ ወደ አንዱ የመንግስት መስሪያ ቤት ጎራ አለ፤ ተሳክቶለትም ስራ መቀጠር ቻለ፡፡ የወር ደሞዙን እንደአገኘም፤ በፍጥነት ቤት ተከራየ፡፡

ስራ ከያዘ ሶስተኛ ወሩን ያስቆጠረ ቢሆንም፤ አራተኛ ወሩን ሊጀምር ሲል በስራ ቅነሳ ምክንያት ከስራዉ ተቀነሰ፡፡

አንድ ጠዋት ላይ የአዲስ አበባ አደባባዮች በያቤፅ ፎቶዎች ‹‹አፋልጉኝ›› በሚል ፅሁፎች ታጅበዉ ተሞሉ፡፡

ከአንድ አመት በኋላ ደግሞ፤ በአለማችን እጅጉን ተደማጭነትና፤ ተመልካች ካለቸዉ ሚዲያዎች መካከል፤ ኢትዮጵያዊዉ ያቤፅ በአሸባሪዉ አይ ኤስ አይ ኤስ እጅ የመታረዱ ዜና ተሰማ፡፡

ዞር ብሎ ያልአየዉ የሰፈሩ ሰዉ ሁሉ ያን እለት እሪታዉን አቀለጠ፡፡ ያን ቀን ነበር የያቤፅ እዉነተኛ የስም ትርጉም የታወቀዉ፤ ያቤፅ ማለት በእብራይስጠኛ ቋንቋ ‹‹የጭንቅ ልጅ›› ማለት ነዉ፡፡

እዉነት ነዉ ስምን መልዓክ ያወጠዋል፤ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም፤ ያቤፅ ዘመኑን በሙሉ በጭንቅ ኖሮ በጭንቅ ይቺን ክፉ አለም የተሰናበተዉ፡፡

 

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *