‹‹ዴሞክራሲ ወታደር የለውም››
አብርሃም ፍቃዱ

‹‹እመጓ››ን እያነበብኩ መንዝ የተከሰተው ታሪክ ቀልቤን ሳበው። በጓሳ መገራ ፓርክ አቅራቢያ የሚኖሩ ገበሬዎች ማሣቸው መሀል እየገባ ሰብላቸውን ባዶ የሚያስቀር አይጥ አስቸገራቸው። ጎተራቸው እንዳይሞላ የሚያግዳቸውን ጠላት ለመከላከል መርዝ አስቀመጡ። አይጥም እንደልማዷ ወደ ማሣው ስትገሰግስ አዲስ ነገር ታያለች። ያየችውንም ልሳ ጉድጓዷ ሳትደርስ ሜዳ ላይ ትወድቃለች። አሞራ ደግሞ በተራዋ አይጧን ይዛ እብስ ትላለች። እርሷም ተራዋ ይደርሳል፤ እናም ክንፍ ሆዬ አልታዘዝ ይላታል። ይህን ጊዜ ሌላ ጉድ ይመጣል። አሞራም፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬና ድንቅዬ ቀይ ቀበሮዎች መሀል፣ የአይጧን መርዝ ይዛ ዱብ ትላለች። አንዲት ትንሽ መርዝ ግዘፍ ነሥታ አይጥን ሆና አሞራን አክላ በመመናመን ላይ የሚገኙትን ቀይ ቀበሮዎች ትገድላለች።
ርዕሱ፣ ‹‹ዴሞክራሲ ወታደር የለውም›› አይደል የሚለው? እናም የሚገድለን የለምና ጓሳ መገራ የተከሰተውን ታሪክ በሚመቸን መልኩ ገልብጠን ከምንኖርበት እውነት ጋር እያዛመድን ስለመርዟ አንድ ሁለት እንበል። በዘጠኝ ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረችው ኢትዮጵያ፣ በድን እየሆኑ በድኑን እየበሉ ወደ ኃላ የጎተቷትን ልምዶች እናንሣ።
ከመቶ አርባ በላይ ኢትዮጵያውያን ያለቁበት፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የቆሰሉበትና እስር ቤት የሚንገላቱለት ዋነኛው ምክንያት የመልካም አስተዳደር እጦት ነው። ማስተር ፕላኑ መጥፎ ጎኑ እንዲያሸበርቅ የመጣ የሃያ አምስት ዓመቱ ባህላዊ ልብሱ ነው። መልካም አስተዳደር በባሕርይው – ከስሙ መረዳት እንደምንችለው – የሕዝቦችን መሻት በመልካምነት፣ በቀናነት፣ በውይይት እና ለፍትሕ በቀረቡ ሕጎች አማካኝነት ሟሟላት ነው። ፖሊሲ ቀርጾ የከተማ ፕላን ነድፎ፣ ሕዝብ ተጠቃሚ ይሆንበታል የተባለውን ጉዳይ ‹‹መረጠ›› ለተባለው ሕዝብ – ጥቅሙንና ጉዳቱን ሳያስረዱትና ሳይረዳው – እንዲሁ እንደ ዱብ ዕዳ ከላይ ወደ ታች ማውረድ የመልካም አስተዳደሩን ገመምተኝነት ሜዳ ላይ እንደ በቀለ ተራራ በጉልህ እንዲታይ ያደርገዋል።
መንግሥት በሪፖርቱ (በባለ 800 ገጹ ሪፖርት) እንዳተተው፤ የመልካም አስተዳደር መላሸቅ አገሪቷ ላይ እንዳንዣበበ፣ ሙስና እና ሙሰኛ እንደ ከበረ፣ በፍርድ ቤቶች ውስጥ ፍርድ ማጓደል እንደ ሰፈነ፣ በተለያዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀም እንደ ደረጀ ገልጧል። ጓሳ መገራ ፓርክ ውስጥ የሚኖሩ ገበሬዎች ለአይጦቹ መርዙን የሚያስቀምጡት ማሳቸው አካባቢ ነው። እዚህ እኛን የሚያኖረን መልካም አስተዳደር በተቃራኒው መርዙን ፍለጋ ገበሬዎች ጓዳ ድረስ ይዘልቃል።
ልማታዊ መንግሥት (developmental state/hard state) የሚለውን ቃል ፕ/ር ጆንሰን የደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገሮችን (ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን፣ ሲንጋፖር፣ ሆንግ ኮንግ ወዘተ.) የኢኮኖሚ ግስጋሴ ለመግለጽ የተጠቀሙበት ነው። የኢትዮጵያ ዕድገት በልማታዊ መንግሥት እሳቤ እንደ አሞራ እየበረረ እንደሚገኝ የሚገልጸው ገዢው ፓርቲ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተደቅነውበታል። የልማታዊ መንግሥት ዋነኛ እሳቤ የፖለቲካውንም የኢኮኖሚውንም ክንፍ በአንድ ፓርቲ የበላይነት አቅፎ ለረዥም ዓመታት በአየሩ ላይ ብቻውን መቅዘፍ ነው። የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን ያበረታታል። ከግል ዘርፉ ይልቅ የመንግሥት የኢኮኖሚ ጡንቻ መፈርጠም አለበት ይላል። እና የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት ድርጅቶች ጋር ተፎካክሮ ለመሥራት ያዳግተዋል። ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ‹‹በሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ውስጥ እንሰለፋለን›› ለሚለው ገዢው ፓርቲም የግል ዘርፉን ፖሊሲ ካላሻሻለ እንደማይሳካ ይገልጻሉ።
የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ጋባዥነት (አ.አ 2007) ንግግር ባደረጉበት ወቅት ኒዮ-ሊበራሊዝም በአፍሪካ ያለው ቆይታ እንዳበቃለትና አዲስ የልማታዊ መንግሥት እሳቤ አፍሪካን ከድህነት እንደሚያላቅቃት ገልፀው ነበር። በልማታዊ መንግሥት የምትመራ አገር ዕድገት ሊሳካ የሚችለው የፖለቲካ ስትራቴጂው ከኢኮኖሚው ጋር መዋሀድ ሲችል ነው ይላሉ። በሌላ መልኩ የዘርፉ ባለሙያዎች አንድ ልማታዊ መንግሥት ለሙስናና ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ መሆኑን ይመሰክራሉ።
በኮምኒስት ፓርቲ የምትመራው ቻይና በሰላሳ ዓመታት ውስጥ ስድስት መቶ ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎቿን በልማታዊ መንግሥት እሳቤ ከድህነት አላቅቃለች። በተቃራኒው የግራና የቀኝ ፖለቲካ እሳቤ ያደባለቀው አብዮታዊ ዴሞክራሲ 20 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎቹ አርሰው መመገብ አልቻሉም። በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከሚማቅቁት ሶሪያውያን እኩል እርዳታን ይሻሉ። ባለአሞራው ኢኮኖሚ በድን የሆኑ አይጦችን እየተመገበ ክንፎቹ ረግፈዋል።
ዴሞክራሲና ልማታዊ መንግሥት የማይነጣጠሉ አስተሳሰቦች ናቸው በማለት በተደጋጋሚ ገዢው ፓርቲ አቋሙን ያንጸባርቃል። በርግጥ በምሳሌ አስደግፎ መተንተን እና እሳቤውን ወደ ተግባር መለወጥ ለየቅል ቢሆኑም፤ ከልማታዊ መንግሥት አገሮች መሀል ጃፓንን በመጥቀስ በአንድ ፓርቲ አገዛዝ ሥር ኢኮኖሚዋ ሳይደናቀፍ ለሃምሳ ዓመታት እንደ ተጓዘች ያነሣሉ።
ሕገ-መንግሥቱ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ቢፈቅድም፤ ከ97 ምርጫ በኋላ የመጣው የልማታዊ መንግሥት እሳቤ በበኩሉ የአውራ ፓርቲ ሥርዓት ለአንድ አገር ቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገት የግድና አስፈላጊ ነው ይላል። ሁለቱም ‹‹ልማትን እናስፈጽማለን›› የሚሉበት መንገድ የተለያየ ነው። የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ልማታዊ መንግሥት ባለበት ቦታ የበይ ተመልካች ነው ወይም የመኪናውን መሪ ይዞ አደባባዩን የሚዞረው ልማታዊ መንግሥት ብቻ ነው። የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እግር ጥሎት ወደ አደባባዩ ለመግባት ቢሞክር፣ ልማታዊ መንግሥት በበኩሉ ኢኮኖሚው ባፈረጠመለት ትልልቅ ጎማዎች ተጠቅሞ ይደፈጥጠዋል።
ከልማታዊ መንግሥታት ትልልቅ ችግሮች መሀል ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትንና የፕሬስ ነጻነትን መጋፋቱ ነው። በጥቅሉ እነዚህ ሁለት መብቶች እንዲከበሩ ወታደር አያሰልፍም። በተቃራኒው እነዚህና ሌሎች መብቶች (የጠየቋቸው መብቶች ትክክል መሆናቸው ቢረጋገጥ’ኳ) የልማታዊ መንግሥት ሥልጣን አደጋ ከሆኑ የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል።
‹‹መፍትሔ የለህም’ዴ? መፍትሔህን አስፍር እንጂ!›› ለምትሉኝ ወዳጆቼ፤ ዴሞክራሲ ወታደር አልባ ሆኖ ብርድ አንዘፍዝፎ ገድሎታል። ሥልጣን በበኩሉ የወታደሮችን ትንፋሽ እየሞቀ ወደ ፊት እየገሰገሰ ነው። ለአንዳንዶች መፍትሔው የሞተውን ነፍስ ይማር ብሎ ሙቀቱን መጋራት ሊሆን ይችላል። ለሌሎች አንጎሉ ይሠራል፤ ልቡ ነው የሞተው እያሉ በተጋድሎ ወደ ሕያውነት መመለስና ሙቀቱን በሰላማዊ መንገድ መንጠቅ ይሆናል። ለሁሉም ጉዳይ ችግሩን ቆመን የምናይበት ቦታ ነው፤ መፍትሔውን ይፈጥረዋልና።
ቸር እንሁንማ!
ማስታወሻ፡- (ለዚህ ጽሑፍ ርዕስ ያደረግኩትን ንግግር የተናገሩት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ናቸው።)

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *