ኤርምያስ የሺጥላ
ኤርሚያስ የሺጥላ
ጆሯችን መዓት በመስማት ሠለጠነ እንጂ አሁን አሁን የሚሠማው ጉድ ድሮ ወይም በነ አጤ ምንይልክ ጊዜ የነበረ ጆሮ ቢሠማው ወይም ጨርቁን ጥሎ ያብዳል ወይ? «ምናለ ድፍን ብዬ ባረፍኩት» ብሎ ያማርራል ብዬ አስባለሁ፡፡
«ምን ሠምተህ ነው?» አላችሁ አይደል!? ይሄን እኮ ነዉ የምለው! ሲጀመር እኔ መዓት ላወራችሁ አስቤ አይደለም፡፡ እንደውም …ካሎት ሁሉን ቻይ ጆሮ ላይ ጥቂት ቀንሠው አንዳንዴ እራሶትን መሥማት እንዲችሉ ለማስታወስ ነዉ፡፡
ምክንያቴም አንዳንዶችን ጋር ሊኖር የሚገባ የደስታ ስሜት ትልቅ እንቆቅልሽ ሆኖ በየቀኑ ጥናት የሚወጣበት፣ ሚዲያዎች በብዙ ማስታወቂያ የሚያጅቡትና የብዙዎችን ጆሮ ቀንድ የሚያስመስል ጉዳይ ሆኖ «ደስታ እንዴትና ከምንናስ ይገኛል?» እየተባለ ሲፈተል ሰምቼ «…አበስገበርኩ!» ብዬ ለራሴ ጥያቄ አነሳሁኝ፡፡
‹‹ሁሉም ስሜቱን መግለጽ የሚያስችል የተራቀቀ የቋንቋ ችሎታ ላይኖረው ይችላል›› አልኩኝ፡፡ ነገር ግን ሰው ለሰከንድ ሊለየው የማይገባው የደስታ ስሜት ከምን እንዴት እንደሚገኝ እንደአዲስ በየቀኑ ሊጠይቅና ሊሰማ ለምን ይፈልጋል? …እውነት ጠፍቶት ነው! አይመስለኝም፡፡ እየረሳነው ይሆን? አሄሄ! የሆነ አልዋጥ ያለን ነገር አለ፡፡ መባል የፈለግነው ነገር አለ መሰለኝ፡፡ ምን መስማት ፈልገን ነው? ሠው አንዳንዴ መስማት የሚፈልገውን እስክትነግረው ድረስ ምንም ብትለው ላይሰማህ ይችላል እኮ፡፡ መዝረፍ ደስታ ይሠጣል እንድንባል ፈልገን ይሆን? ወይስ ሀብታም ሆኖ የተንደላቀቀ ቪላ ውስጥ በረጅም አጥር ተከቦ እንደ አሣማ በመብላትና ድሆች እውጪ እየተጉላሉ እንደሆነ ማሰብ ወይም አለማሠብ ደስተኛ ያደርጋል እንድንባል ፈልገን ይሆን? ወይስ ምቀኛ ድሀ መሆን ያስደስታል እንድንባል ፈለገን ነው?
በእርግጥ ተስፋ አለን፡፡ ጥናቶች ቀስ በቀስ ወደዛ እየሔዱ ይመስለኛል፡፡ አንድ በሚዲያ የሰማሁትን አውሮፓ ውስጥ የተሰራ ሳልፈልግ ያሳቀኝን ጥናት ልንገራችሁ፡፡ ብዙ ሰዎች ያስደስቱናል ያሏቸው አስር ነገሮች ተብሎ ነው የተቀመጠው፤ ከላይ ከአንድ እስከ ሶስት ያሉትን እስኪ እንያቸው በአንደኝነት በጣም ብዙ ሰዎች በደስታ ያስፈነጥዘናል ያሉት «ዝናብ እየጣለ እቤት መተኛት ነው» በቃ! ደስታ ለእነሱ ውጭው ሲቀዘቅዝ አልጋ ዉስጥ መሽገው፣ አድብተው የሚይዙት ከዝናብ ጋር የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ለብዙ ሰዎች አስደሳች የሆነ ጉዳይ ያሉት «በጥዋት ስራ ወይም ት/ቤት ለመሔድ ተነስቼ ለካ ቀኑ እሁድ ነው!» …ይህ እንግዲህ ድንገት ወደል (ስራ ፈት) መሆን በጣም የሚያስገርማቸው ሰዎች ደስታ ነው የሚመስለው፡፡ ሶስተኛውን ደረጃ የያዙት «ጀርባዬን በእጄ የማልደርስበት (ለማከክ የማይመች) ቦታ ላይ በልቶኝ በሆነ ረዘም ባለ ሻካረ ነገር አስገብቼ ሞዠቅ ሞዠቅ ሳደርገው በደስታ እረሰርሳለሁ» ያሉት ናቸው፡፡ የእነዚህ ደግሞ ደስታን ከቆዳ በሽታ ጋር የሚያይዙት ይመስለኛል፡፡ እንግዲህ እከክ ዋነኛ የደስታ ምንጭ ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡
ዶስቶቪስኪ «Notes from the ground» የተሰኘ መፅሐፉ ላይ እንዳለው ሰዎች ለፍላጎታችንና እምነታችንን ለመደገፍ ቋንቋን በነገር ምላጭ የመተልተልና በፍልፍስፍና ድር የመቋጠር አባዜ ያለብን፣ እዉነታውን እያወቅን ረብ የለሽ ፍላጎታችንን ለመደገፍ የማንፈነቅለው ድንጋይ የሌለን አስመሳይ ፍጡራን ነን፡፡
እኛ ሀበሾች ደግሞ ለደስታ ያለን ትርጉም በጣም የተሳሳተና የተንሸዋረረ ይመስለኛል፡፡ ብዙዎች ከእኛ ማግኘት ይልቅ በጎረቤታችን ወይም በቅርብ ጓደኛቻችን ማጣት የምንዝናና ነን፡፡ እንደውም ለዚህ ምስክር የሚሆን የጠላነውን ሰው ክፉ ስንሰማ በውስጡ አቃጥሎኝ ነበር የሚል ማስታወሻ የያዘ «አንጀቴ ቅቤ ጠጣ!» የምንለው ጉደኛ አገላለፅ አለን፡፡ ሌሎች ያስደስቱናል ብለን የምናደርጋቸው እንደ መጠጥ፣ ሀሽሽና ሌሎች አደንዛዥ እፆች ያሉ ነገሮች የደስታን ምንነት እንደማናውቅ ወይም እንደጠፉብን የሚያሳዩ ምስክሮች ናቸው፡፡ ሌላውን ትታችሁት ለዘመናት ሀገሪቷን እንደ አተት ሲያልባት እኛም እንደ ሰው ስንወቅሰው የኖርነው አመጸኛው ትልቁ ወንዛችን ሊገደብ ጉድ ጉድ እየተባለ፤ ሰዎች ስሜታቸውን ሲጠየቁ «በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ደስታዬን ለመግለፅ ቃላት ያጥሩኛል!» እያሉ ሰው የቪታሚን ብቻ ሳይሆን የቃላት እጥረትም እንደ በሽታ ሊያጠቃው እንደሚችል የሚያሳይ አገላለፅ ሲያንፀባርቁ ሰምተናል፡፡
እንደተለመደው መንግሥትም «አባይ በመገደቡ ህዝቤ ደስታውን ለመግለጽ ቃላት አጠረው» የሚል እና ማውራት ስለከበደው የአባይ ወንዝ በመገደቡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸውን ለመግለፅ አደባባይ ወጡ ብሎ ነው ያወራው፡፡ በግልፅ የተረዳሁት የእኛ ህዝብ ደስታውን የሚገልፀው በቃላት ሳይሆን ሰብሰብ ብሎ አደባባይ በመውጣት መሆኑን ነው፡፡ ብቻ ወደዳችሁም ጠላችሁም ደስታ በጭራሽ እንደ መብላት፣ መጠጣት ማጨስና መጨስ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ እንዳልሆነ እረስታችሁት ከሆነ ላስታውሳችሁ ግድ ይለኛል፡፡ የሰው ልጅ ለስጋዊ ባህሪው የሚገብራቸው ነገሮች በሙሉ አጭር የእርካታ satisfaction ስሜት እንጂ ደስታን ሊሰጡት አይችሉም፡፡
ይህ እርካታ በነጮች አፍ ‘satisfaction or utility’ የምንለው ጉዳይ በመብላትና በመጠጣት ልናገኘውና በስሌት ከፍ ልናደርገው የምንችል የኢኮኖሚክስ ሀሳብ እና የስጋ ባህሪ ነው፡፡ በአጭሩ ስጋ ሊረካ እንጂ ሊደሰት አይችልም፡፡
ደስታ (ሀሴት) በነፍስ ከባቢ አየር ላይ የሚፈጠር ብሩህ አየር ፀባይ ነው፡፡ ደስታን እንደ እርካታ አጭር፣ ድርጊቱ ሲያልቅ የሚቋጭ፣ ፀፀት አስከትሎ የሚመጣና ከህሊና የሚያጣላ ቀሽም ስሜት አይደለም፡፡ በጣም ሰላማዊ ነው፡፡ ነጥቀህ የምትወስደው ሳይሆን ሰጥተህ የምትቀበለው ደግነትና አብሮነትን የሚያጎለብት የፍቅር ብርሀን ነፀብራቅ ነው፡፡ ለዛም ይመስለኛል ተንኮል የማታውቀው ተፈጥሮ እኛ ያመረትነውን ካርቦን ዋጥ አድርጋ ደፋ ቀና ብላ ንፁህ ኦክስጅን እንካችሁ የምትለን፡፡ የሚገርመው አንዳንድ ሰዎች እፅዋትን መንከባከብ ማንም ሳያስገድዳቸው ስራዬ ብለው የወትሮው ተግባራቸው ያደርጉታል፡፡ ቀስ በቀስ እፅዋቱ በገኙት እንክብካቤ አምሮባቸው፣ ለምልመውና ህይወት ዘርተው ማየት የሚፈጥረውን የደስታ ስሜት ሱስ እንደደረገባቸው ግን ላያስተውሉት ይችላሉ፡፡
እንግዲህ ሰው እፅዋትን ተንከባክቦ ህይወትን ከሰጣቸው ተፈጥሮን ተንከባከበ ማለት ነው፡፡ እጽዋትን መንከባከብ ተፈጥሮን መንከባከብ ከሆነ ይልቁንም ሰውን መንከባከብማ ምንኛ ታላቅ ደስታ ትሆን …«ተርዤ አለለበሳችሁኝም፣ ተርቤ አላበላችሁኝም፣ ተምሜ አልጠየቃችሁኝም» እንዳለ ሰውን መንከባከብ ፈጣሪን መንከባከብ እንደሆነ አስተውሉ፡፡ …የተራበ ስታበላ ፈጣሪህን እንደመግበከው እወቀው፡፡ እነሆ አልፈኸውም ስትሔድ ፈጣሪን እንደለፍከው እወቀው፡፡ ደስታህ ከዚህ ውጭ ከሆነ ቆም ብለህ እራስህን አዳምጥ፡፡ እነሆ ደስታን በግጥም በኔ ብዕር…
ጉልበተኛ በጉልበቱ ለራሱ ነጥቆ እንዳይወስደው
ሀብታምም በገንዘቡ በጎተራ ገዝቶ እንዳይከተው
ድሀንም በድህነቱ ምክንያት አድርጎ እንዳይርቀው
ደስታን እረቂቅ አድርጎ ከሁላችን ዘንድ አኖረው
በመስጠትና በመቀበል መሀል ከአንዱ ስርቻ ደበቀው፡፡

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *