በያላችሁበት የፈጣሪ ፀጋና ሰላም ይብዛላችሁ!
አንዷለም አራጌ /ከቃሊቲ እስር ቤት/

ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ልጽፍላችሁ ሳስብ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ጉዳዮችን በተለይም ፖለቲከኛ ሆኖ ለኃይማኖት አባቶች ደብዳቤ መጻፍ የተለያዩ ወገኖች በተለያዩ መላ ምቶች እንዲጠመዱ ብሎም እንዲሳሳቱ እድሉን ይከፍታል የሚሉ ሃሳቦችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለዓመታት በይደር አቆይቸዋለሁ፡፡ ደብዳቤውን እንድጽፍ ሀሳብ ያጫሩብኝ ጉዳዮች ግን ከጊዜ ወደጊዜ እየከፋና እየሰፋ በመሄዳቸው ከዚህ በላይ ማሳደሩ ተገቢ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ለማንኛውም በጊዜው ከእናንተ ጋር እንድገናኝ የፈጣሪ ፈቃድ ስለሆነ ምስጋና ይግባው!
ምንአልባት ጥቂቶቻችሁ ስለእኔ ማንነት በጨረፍታ እንደምታውቁኝ ብገምትም አያሌዎቻችሁ ግን ‹‹ለመሆኑ አንተ ማን ነኝ አልክ?›› እንዳትሉኝ እሰጋለሁ፡፡ እንደ እናንተ ሰርክ በበርካታ መንፈሳዊና ስጋዊ አገልግሎቶች የተጠመደ አባት ስለእንደኔ አይነቱ ሰው ሁኔታ ለመረዳት ሁኔታዎች እድል እንደሚነፍጉትም እገምታለሁ፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ፣ ወደዋናው የደብዳቤዬ ጭብጥ ዘልቄ ከመግባቴ በፊት በጥቂቱ ስለራሴና ቃሊቲ እንድወርድ ስላደረጉኝ ሁኔታዎች እንድገልጽ ፈቃዳችሁ ይሆን ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ ‹‹ልጁ ምን ፍሬ አለው?›› ሳትሉ ነገሬን እስከመጨረሻው በጥሞና እንደምትከታተሉም ተስፋዬ ከፍ ያለ ነው፡፡
አንዱአለም አራጌ እባላለሁ፡፡ ከድሀ የገበሬ ቤተሰብ የተገኘሁ ኢትዮጵያዊ ነኝ! ከልጅነቴ ጊዜ ጀምሮ ‹‹እራሴንና ቤተሰቤን ከምንገኝበት የኑሮ አዘቅት ስለማውጣት ወይንስ የሀገርን አጠቃላይ ሁኔታ ከመሠረቱ የሚቀይሩ ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት?›› በሚሉ ሁለት ጥያቄዎች ስላጋ ቆይቻለሁ፡፡ በሂደትም ቤተሰቤን በመቀየር ሀገርን ለመቀየር የሚደረገው ጉዞ እረጅም ሆኖ አገኘሁት፡፡ ቅድሚያ ለሀገር በመስጠት ብሰራ ግን ሀገር ሲለወጥ የቤተሰብ መለወጥ አስተማማኝ እንደሚሆን ጊዜውም በአንጻራዊነት ሊያጥር እንደሚችል ግምቴን ወሰድኩ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ህልሜ እውን ቢሆን እንኳን ባልተለወጠ፣ በተጨቆነና በተራበ ህዝብ መካከል የአንድ ቤተሰብ መለወጥ ትርጉም ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በመሆኑም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዋና ትኩረቴን አድርጌ መንቀሳቀስ እንደሚገባኝ ወሰንኩ፡፡ የሀገራዊ ጉዳዮች እምብርት ደግሞ ፖለቲካው ስለመሆኑ ለመረዳት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ የፖለቲካል ክርታስ ሲዘረጋ ሌሎችም ጉዳዮች ብርሃን ያገኛሉ፤ ትቢያቸውም ይራገፋል፡፡
በመሆኑም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ጀምሮ አቅም በፈቀደ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ ነገር ግን እምነቴ እውን ይሆን ዘንድ በኢትዮጵያ ሰላማዊ የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ 15 ዓመታትን ያህል ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡ ለአብነት ያህል የቀድሞ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ አመራር አባል የነበርኩ ሲሆን ከእርሱም ውስጥ ወህኒ ወርዶ ከነበረውና ከ18 ወራት ቆይታ በኋላ ከተፈታው “ነውጠኛው” አመራር ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም የቀድሞውን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)ን በዋና ፀሐፊነትና በመጨረሻም በምክትል ሊቀመንበርነትና በህዝብ ግንኙነት ኃላፊነት አገልግያለሁ፡፡ ከእስር ከተፈታሁ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትዳር መስርቼ ሁለት ወንድ ልጆችን ወደዚህ ዓለም በማምጣት የአባትነትን ፀጋ ለመጎናጸፍ ችያለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ትልቁ የሦስት ዓመት ተኩል ትንሹ ደግሞ የ10 ወር ባሉበት ዳግም ወደ ወህኒ የመውረድ እዳ ወደቀብኝ፡፡ በዶፍ ዝናብ መሃል እንደምትወጣ ፀሐይ የአባትነት ደስታዬ በድንገት በግፍ ተገፈፈ፡፡ ይህ ታሪክ የእኔ ብቻ ሳይሆን የእነ እስክንድር ነጋ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ሀብታሙ አያሌው፣ የሽዋስ አሰፋና የሌሎችም በእስር ላይ የሚማቅቁ እናቶችና አባቶች ታሪክም ነው፡፡
ስለግል ታሪኬ ይህንን ያህል ካወሳሁ፣ ስለአጠቃላይ ሁኔታዎች ለውይይታችን የሚረዱ ሀሳቦችን ባነሳ ጥሩ መንደርደሪያ እንደሚሆነን እገምታለሁ፡፡ መቼም መንፈሳውያንን በዓለም ጉዳይ ላይ ጊዜያቸውን መሻማት ምቾት አይሰጥም፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊ ግዳጃችሁንም የምትወጡት በአለም ነውና ይህንንም የእርሱ አካል አድርጋችሁ ቁጠሩልኝ፡፡ ደግሞስ በፖለቲካና ኃይማኖት መካከል ያለውን ደረቅ መሬት የመፈለግ ያህል የሚከብድ ስንት ነገር ቢኖር ነው? እናም ጥቂት ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ነገሮች ባነሳም ይቅርታችሁ እንደማይለየኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በቅጡ እንደምትረዱት፣ ለዘመናት የተቆራኘንን ገዥዎችን በአፈ-ሙዝ የመቀያየር ባህል በሰለጠነና የህዝብን ልዕልና መሠረት ባደረገ ሰላማዊ መንገድ እንዲተካ ማድረግ የኢትዮጵያን የመገዳደል ባህል ለመቀየር ትልቅ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለተወለዱትና ላልተወለዱ ልጆቻችንም ጭምር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዋስትና የምትሰጥን ሀገር ለመፍጠር ወሳኝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እስከ አሁን ድረስ የተተከለው የአገዛዝ ባህል ይህንን የትውልድ ስስት እውን እንዳይሆን ደንቃራ ሆኖበታል፡፡
አሁን ስልጣን ላይ የሚገኘው አገዛዝም በዚሁ የመገዳደል ባህል ተጀቡኖ ወንድማማቾች የተራረዱበትን ጦርነት ተከትሎ መንበረ ስልጣኑን የተቆናጠጠ በመሆኑ ሰላማዊ ትግልንና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን እንዲፈጽም የማይለመድ እንግዳ ነገር ከማየቱም በላይ ይህንን መንገድ የሚያቀነቅኑ ወገኖችን ግንባር ቀደም የስርዓቱ አደጋ አድርጎ ይወስዳል፡፡ ያም ሆኖ ከጊዜ ጊዜ እየጠበበች በመጣችው ዓለም ውስጥ የሚያግባባ ቋንቋን መፈለጉ አልቀረም፡፡ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርንና ሰላማዊ ትግልን ፈቅጀ በስልጣኔ ጎዳና እየነጎድኩ ነው ይላል፡፡ በራሱ ላይ የደረበው ካባና በተግባር የሚገለጠጸው ግን ፈፅሞ የመቀራረብ አዝማሚያ እንኳን ሊያሳዩ አልቻሉም፡፡
ከብዙ በጥቂቱ በተለይም ከ1993 ዓ.ም. የኢህአዴግ ጉባኤ በኋላ የሚባለው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርና ሰላማዊ ትግል ከማደናገሪያነት ባለፈ ቦታ እንዲኖራቸው የተፈለገ አይመስልም፡፡ አሁን ድረስ በህይወት የሚገኙ የተከበሩ አቶ ስብሀት ነጋ ‹‹የኢትዮጵያን ህዝብ እንደራሽያ ረግጠን መግዛት ካልቻልን ወደፊት መራመድ አንችልም፡፡›› በማለት የሰነዘሩት ሀሳብ ከጊዜ ወደጊዜ ፍሬውን እያጨድን ነው፡፡ የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ተከትሎም ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያሸጋግር ውሳኔ አሳለፈ፡፡ አሁንም በህይወት ያሉ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚዎች ቢያንስ ለህሊናቸው የእውነት ምስክርነቱን መስጠት ይችላሉ፡፡ እናም ተሰብስበው ‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች እግር እስኪያወጡ እንጠብቃለን፤ እግር ሲያወጡ ግን እንቆርጣለን፡፡›› የሚል ሰላማዊ ትግልን በስልት የማዳፈን ዘመቻ እቅድ ነደፉ፡፡ በተግባር እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ስለ ሰላም አስፈላጊነት፣ ስለሰላማዊ ትግል በሰፊው ስለተከፈተው በታሪክ ተወዳዳሪ የሌለው በርና በህገ-መንግስት ስለተረጋገጠው የህዝብ ልዕልና የሚዘመረው መዝሙር ተቋርጦ አያውቅም፡፡
ይህንን በሚመስለው ሸፍጥ የተሞላ ሰርጥ የኢትዮጵያን ህግጋት በሚፈቅዱት መሠረት የሰላማዊ ትግልና የህዝብን ሉዓላዊነት መሠረት የሚያሰፉ ትግሎችን ከማድረግ ውጪ ሌላው አማራጭ የአፈናውን አዙሪት የሚያስቀጥል መሆኑን የምናምን ዜጎች በትግሉ መቀበላችን የሚጠበቅ ነበር፡፡ ይህንን የመሰለ በሸፍጥና በሀኬት የተሞላ አገዛዝን መታገል ደግሞ ውሎ አድሮ መዘዙ ከማንም የሚሰወር አልነበረም፡፡ በተለይም የቀድሞው የቅንጅት አመራር ለነበረና እድሜ ልክ እስር ተፈርዶበት በይቅርታ የተፈታ ሰው በየምክንያቱ የኦሪት ፍየል እንደሚሆን ነጋሪ አያሻውም፡፡ ነገር ግን ምንም ያህል የከፋ ቢሆንም የቀደሙ አባቶች ከውጪ ወራሪዎች ህይወታቸውን በመክፈል የድንበር ሉዓላዊነቷን ላስከበሩት ሀገር በዚህ ዘመን የህዝብ ሉዓላዊነት እንዲከበር መታገል ምንም አይነት ዋጋ አይበዛበትም፡፡ ደግሞስ ኢ-ፍትሃዊነት በተንሰራፋበት በዚያ በቦታው ላይ መታገል ትልቅ ነገር አይደለም ትላላችሁን?
እናም በሌላ ወገን በህግ የተፃፈውንና በአንደበት የሚያነበንቡትን በተግባር ይጠሉታል፡፡ ይወጉታል፣ ይገድሉታል፡፡ መሞት፣ መታሰር፣ ሀገር ለቆ መሰደድና በፖለቲካ ተስፋ ቆርጦ መቀመጥ ብቻ እንደ አማራጭ ቀርበውልናል፡፡ የተለየ ሀሳብ ያለውን ሁሉ አንገቱን ለመስበር የህዝብ ንብረት ያለገደብ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ በህገ-መንግስቱ የተቀመጡ የመደራጀት፣ የመሰብሰብና ሀሳብን የመግለጽ መብቶች በአገዛዙ በማንአለብኝነት ይጣሳሉ፡፡ የተወሰኑ ነገሮች ላንሣ፡፡ የመደራጀት መብት በህገ-መንግስቱ መፈቀዱ በራሱ እንዳይጣስ ዋስትና አልሆነውም፡፡ ይህንን ስል አንዳንድ ወገኖች ‹‹‹በየዕለቱ ፓርቲ እየፈለፈላችሁ ተበጣጥሳችሁ በመጣችሁ ቁጥር ሰርተፊኬት እየተቸገራችሁ እንዴት እንዲህ ያልተገባ ነገር ትናገራለህ?›› ትሉኝ ይሆናል፡፡ እውነት ነው፣ መደራጀት ማለት የፓርቲ ሰርተፊኬት ይዞ በአገዛዙ ፈቃድና መዳፍ ውስጥ መንከላወስ ብቻ ከሆነ ትክክል ነው፡፡ መደራጀት ከስምና ከምስክር ወረቀት ባለፈ ህዝብን አደራጅቶ፣ አስተባብሮና መርቶ የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት ማድረግ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የህልም ያህል የማይጨበጥ ነው፡፡ በሌሎች ሀገሮች በተለያዩ ዘመናት የተፈፀሙትን የሰላማዊ ትግል ስልቶች አንዱን እንኳን ተግባራዊ ለማድረግ ይቅርና በየክፍለ-ሀገሩ አባሎች ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ መታደግ አንችልም፡፡ አገዛዙ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ፅ/ቤቶችን እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ቢኖርበትም እግራቸው መቆረጥ አለበት ያላቸውን ፓርቲዎች በተለያዩ የአፈና ስልቶች ይቀይዳቸዋል፡፡ በጭንቅ የሚገኙ ሳንቲሞች አሟጠን ቢሮዎችን ለመከራየት ስንሞክር ሰማይን የመንካት ያህል ከባድ ነው፡፡ በአባላቶች ላይ የሚደርሰው ጫና ጥግ የለውም፡፡ በተለይ ከከተማ ወደገጠር በለቀቅን ቁጥር አፈናው በዚያው መጠን ይከፋል፡፡ ‹አንፃራዊ ነፃነት አለው› በሚባለው በአዲስ አበባ እንኳን ቢሮ መከራየት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ቢሮ ለመከራየት በምንሄድበት ሁሉ የደህንነት መኪናዎች ጢም ብለው ይከተሉናል፡፡ ከእኛ ጋር ውል ሊፈርሙ የሚችሉ አከራዮች ስጋት ላይ ይወድቃሉ፤ የቋጨናቸው ውሎች ይጨናገፋሉ፡፡
ፍርሃትን አሸንፈው ወደቢሯችን በአባልነት ለመታቀፍ የሚመጡ ዜጎች በዙሪያችን በሚሰማሩ “የደህንነት” አባላት እስከመኖሪያ አካባቢያቸው ድረስ ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ ለክፍለ ከተማው ደህንነትም ያቀብሏቸዋል፡፡ በየክፍለ ከተማውም እየተጠሩ በልጆቻቸው በባለቤታቸውና በራሳቸውም ህይወት መመዘዝ ሳይመጣ ከተቃውሞ እንቅስቃሴ እንዲወጡ በምትኩም ከደህንነት አባላት ጋር እንዲሰሩ ይነገራቸዋል፡፡ ትንሽ ጠንከር ካሉ ጉዳዩ ወደሚሰሩበትም መስሪያ ቤት አምርቶ ጉሮሯቸው ሊታነቅ ይችላል፡፡ በሁኔታው ህፃናት፣ የትዳር አጋሮችና ዘመድ አዝማድ ጭንቅ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ዜጎች በነፃ እምነታቸውን እንዳያራምዱ ስጋን ብቻ ሳይሆን ነፍስን የሚያጎብጥ መከራ ይወድቅባቸዋል፡፡ ስለህዝብ ከግፍ አገዛዝ ነፃ መውጣት የሚዘመረው መዝሙር ግን አይቋረጥም፡፡ የመደራጀት፣ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ፣ የመሰለፍና የመሰለፍ መብቶች ሳይሸራረፉ ተከብረዋል ይባላል፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ይረዳሉ ተብለው የተጠረጠሩ ባለሀብቶች በባለስልጣናት ቢሮ እየተጠሩ ማስፈራሪያ ይደርስባቸዋል፡፡ የንግድ ተቋሞቻቸው ስልታዊ በሆነ መንገድ ይመታሉ፡፡ አገዛዙን የሚደግፉ ደግሞ ሁሉም አልጋ በአልጋ እንዲሆንላቸው ይደረጋል፡፡ ተቧድነው አሊያም በተናጠል ኢህአዴግን በመቶ ሚሊየኖች እንዲረዱ ይደረጋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ የኢትዮጵያ ህግጋት ፓርቲዎች መነገድ እንደማይችሉ ይደነግጋሉ፡፡ ነገር ግን የገዢው ፓርቲ ለቁጥር የሚያታክቱ ካምፓኒዎች በቢሊየን በሚቆጠሩ ዶላሮች ይነግዳሉ፡፡ በአንድ እጃቸው የሀገር በሌላኛው ደግሞ የንግድ ተቋሞቻቸውን መሪ ጨብጠው ባቡሩን ይነዳሉ፡፡ የዚህ ውጤት ግልፅ ነው፡፡ የንግድ ተቋማቱን እዚህ ላይ መጥቀስም ጊዜያችሁን ያለ አግባብ ማባከን ይሆንብኛል፡፡ ደግሞስ ምን የማታውቁት ነገር እጨምርላችኋለሁና?!
በተዳከመ አቅማቸውና በታሰረ እጃቸውም ቢሆን ህዝብ ማንቃት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ እንደምታውቁት በሰላማዊ ትግል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቁ ኃላፊነት ህዝቡን ማስተማር ሲሆን በመጨረሻም ለውጡን የሚያመጣውም ሆነ ባለቤቱ ግን ህዝብ ነው፡፡ አሁንም በህግ ደረጃ ፓርቲዎች ህዝቡን እንዲያደራጁና እንዲያነቁ እድሉን የሚሰጡ አንቀፆች ችግር የለም፡፡ በተግባር ግን ‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከህዝቡ ጋር ይገናኙባቸዋል›› የሚባሉ በጥቂት ሰዎች ቅጅ የሚሰራጩ የግል ጋዜጦች በጥቂት የአገዛዙ ቁንጮዎች በሚቀመር ስልት ወደ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት እንዲጣሉ ይደረጋል፡፡ ጋዜጠኞች በግፍ ይሰደዳሉ፣ በግፍ ለእንግልትና ለእስር ይዳረጋሉ፣ በግፍ ይሰደዳሉ፣ ቀሪ ዘመናቸውን በባዕድ ሀገር ታዛ ተጠልለው እንዲያሳልፉ ግድ ይሆንባቸዋል፡፡ ልክ አገዛዙን እንደሚደግፉ ባለሃብቶች አገዛዙን የሚወግኑ ደግሞ እሾህ እንዳይወጋቸው እንቅፋትም እንዳይመታቸው ከፊት ከፊት መንገዱ ይጠረግላቸዋል፡፡ መቼም ኢትዮጵያ በጋዜጠኞች ስደት በዓለም ላይ ያላትን ቦታና በአሁኑ ሰዓት ከኢትዮጵያ ምድር የተጋረደውን የነፃ ፕሬስ ጉዳይ ክቡራን የኃይማኖት አባቶች ታጡታላችሁ ብዬ አላስብም፡፡ ራሱን የቻለ ትልቅ ጥራዝ የሚወጣው ጉዳይ ነው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች የራሳቸውን ጋዜጣ በማተም አባላትና ደጋፊዎችን ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ቀደም ሲል በዳሰስነው የገንዘብ ችግር በእጅጉ የተገደበ ነው፡፡ ከዚህ ቅርቃር ወጥተው ቋታቸውን አሟጠው የራሳቸውን ልሳኖች ለመክፈት የሞከሩ የሁለትና ሶስት ፓርቲዎች ጥረት የትም ሊደርስ አልቻለም፡፡ አገዛዙ በሚያስቀምጣቸው አጉራዎች ተሰናክለው ይወድቃሉ፡፡ ይህንን ላስረዳ፡- ለምሳሌ፣ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኜ በምሰራበት ወቅት ‹‹ፍኖተ-ነጻነት›› የተሰኘችውን ልሳናችንን ለማሳተም ከፍ ያለ የማተሚያ ቤት ችግር ገጥሞን ነበር፡፡ አታሚዎች በፍርሃት ቆፈን ውስጥ በመውደቃቸው የተቃዋሚ ፓርቲ ልሳን መሆኑን ስናስረዳቸው ስራቸውን አደጋ ላይ መጣል እንደማይፈልጉ ገልጸው ያሰናብቱናል፡፡ በመጠኑም ቢሆን ደፈር ያሉት ደግሞ ይስማሙና ክፍያ እንድንፈፅም ይጠይቁናል፡፡ ቼክ ይዘን ስንመለስ የማናውቃቸው አይነት ሰዎች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ትርፍ ስለማይፈልጉ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ይሆንባቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ነገሮች ከአቅም በላይ ሲሆን ነገሩን ወደ ግፉ ባለቤት ማዞር ይሻላል ብለን ወደብርሃንና ሰላም ወሰድነው፡፡ ብርሃንና ሰላም የአብዛኛዎቹ የኢህአዴግ ልሳናት ገነት ነው፡፡ ማመልከቻችንን አቀረብን፤ ለቀናት በሰባራ በሰንጣራው እግራችንን አቀጠኑት፡፡ በወቅቱ የመጨረሻው አማራጫችን ነበርና አልተላቀቅንም፡፡ በኋላ ላይ የሆነው ነገር የተዓምር ያህል አስገረመን፡፡ እንድናሳትም ተስማሙ፡፡ ነገር ግን የጋዜጣዋ ህትመት እየጨመረ ሲመጣ በሰላው ጎራዴያቸው ቀሏት፡፡
ክቡራን የኃይማኖት አባቶች፣ የቀድሞ የፓርላማ አባሉ አቶ ግርማ ሰይፉ ጉዳዩን ወደአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቢሮ ይዘውት ተመላለሱ፡፡ አልሆን ሲላቸውም በፓርላማ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ‹‹እባክዎን ልሳናችንን እንድናሳትም ተቸግረናልና አስተዳደርም መላ ይበለን አሉ፡፡›› በግፍ ከታሰርኩበት ጎረኖ ውስጥ ሆኜ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አሳዛኝ መልስ ለመስማት እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በርካታ የግል ማተሚያ ቤቶች እንዳሉ ነገር ግን እርሳቸው ማተሚያ ቤቶቹን የማዘዝ ስልጣን እንደሌላቸው ገለጹ፡፡ ምናልባትም አገዛዛቸው ፍርሃትን በዚህ ደረጃ ሊያሰፍን በመቻሉ ደስታቸው ከፍ ያለ ይመስላል፡፡ እንደ እኔ ምን እንደሚሰራ ነገሮችን በቅርበት ለሚያውቅ ደግሞ ሀዘኑን ያከፋዋል፡፡ ማተሚያ ቤቶች ፓርቲዎችም ሆኑ በሕዝቡ ሊጠቀሙ የሚችሉት የማተም፣ የማሳተምና መረጃ የማግኘት ነጻነት ሲከበር ነው፡፡ ይህ መብት እውን እንዳይሆን የእርሳቸው ደህንነቶች በማን አለብኝነት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ እንዲያትሙ ትዕዛዝ ባይሰጡ እንኳን ደህንነቶቻቸው ማተሚያ ቤቶችን እንዲያስፈራሩ ቢነግሩ በቂ ነበር፡፡ ስለዚህ መልሳቸውን ገለጥ አድርጎ ለሚያየው ማስፈራራታችንን እንቀጥላለን የሚል ነበር፡፡ ደህንነቱ አደብ ሲገዛ ሰዎች በነፃነት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ለአገዛዝ ፍጹም ምቾት አይሰጠውም፡፡ ወይ ነፃነት ወይንም አገዛዝ፤ ሁለቱ ተስማምተው አይቀጥሉም፡፡ ምንአልባት ይኼ ሁሉ አፈና የጠቅላይ ሚኒስትሩ እውቅና ይሆን የሚፈፀመው?
ለመሆኑ በምን አይነት ህግ ይሆን የደህንነት ሰዎች የሚገዙት? እንደኛው አፈር ፈጭተው፣ ጭቃ አቡክተውና ውሃ ተራጭተው ያደጉ ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ ለገዥነት ከሰማየ ሰማያት ተቀብተው የወረዱ ልዩ ፍጡራን ይመስላሉ፡፡ ያም ሆኖ የህዝብ ደህንነት የሚለውን ስም ተጎናጽፈዋል፡፡ በተግባር ግን አገዛዙን የማይደግፍ የህዝብ ክፍል ሁሉ በጥፍሩ ቆሞ እንዲኖር ግድ ብለውታል፡፡ እነ አቶ ግርማም እስከአገዛዙ ጉልላት ድረስ ተጉዘው መብታቸውን ማስከበር አልቻሉም፡፡ ስለዚህ በጥፍርና በጥርሳቸው ቧጠው የማተሚያ ማሽን መግዛት ግድ ሆነባቸው፡፡ የማተሚያ ማሽኑን ለማንቀሳቀስ ግን የተለየ ቆጣሪ ያስፈልግ ነበርና አሁንም ከአፈናው አዙሪት መውጣት አልቻሉም፡፡ የመብራት ኃይል መስሪያ ቤትም ለእኩዩ ተግባር የሚሰንፍ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በመሆኑም ጀነሬተር ለመግዛት ተገደዱ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው አጉራ ወረቀት የሚያገኙበትን መንገድ መዝጋት ይሆናል እያልኩ ሳስብ ሌላ ‹‹በጣም የተሻለ አማራጭ አመጡ፡፡›› ሌላኛውን የአገዛዙን ክንድ ምርጫ ቦርድን ተጠቅመው ፓርቲውን አፈረሱት፤ በሰላማዊ መንገድ በዚህ ሀገር ለውጥ ለማምጣት የሚደረገውን ሙከራ አገዛዙ ህዝብ በሚከፍለው ግብር ምን አይነት ስራ እንደሚሰራበት ፈጣሪ ያስመልክታችሁ፡፡ የፓርቲውን አባላት በየፊናው እንደአውሬ እያደኑ አርፈው እንዲቀመጡ ካልሆነ የነፍሰ-ጡር ሚስቶቻቸውን እምብርት እስከመቅደድ እንደሚደርሱ በመዛት ያሳድዷቸዋል፡፡
በሌላ ወገን ኢህአዴግ አያሌ የህትመት ውጤቶችን በማሰራጨት በዘጠነኛ ጉባኤው ሪፖርት ላይ እንደገለጸው በርካታ ሚሊየን ብሮችን ከህግ ውጪ ያጋብሳል፡፡ በዚህ በግልፅ እንዳስቀመጠው፣ እንደምኞቱ ለሚገዙ ፓርቲዎች ድጎማ ይፈጽማል፡፡ ሬዲዮ ፋናና ድምፀ-ወያኔን በግል ንብረትነት ይጠቀማል፡፡ በሌላ በኩል በስም የኢትዮጵያ ህዝብ በግብር ግን የኢህአዴግ አንጡራ ሀብቶች የሆኑትን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጀትን ያለአንዳች ይሉኝታ በብቸኝነት ይጠቀማል፡፡ እነዚህ ተቋማት ‹‹ለአገዛዙ አይመቹም›› የሚሏቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስም የሚጠቅሱት ጭቃ ሊቀቧቸው ሲፈልጉ ነው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህዝብን ለማንቃት ብሎም ለመድረስ ህዝባዊ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍን ለመጠቀም ይጥራሉ፡፡ አንድ አጭር ነገር ብቻ ላንሣ፡፡ የመድረክ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆኜ ሳገለግል ወደ አዲስ አበባ መስተዳድር ጎራ ብዬ በመስቀል አደባባይ ሰልፍ ለማድረግ ቀን እንደቆረጥን አሳወኩ፡፡ በወቅቱ የሰጡኝ ምላሽ በመስቀል አደባባይ መቼም ማንም ሰልፍ እንዳያደርግ መወሰኑንና ተለዋጭ ቦታ አዘጋጅተው እንደሚያሳውቁን ነገሩን፡፡ ቃላቸውን አምነን ተመለስን፡፡ እጅግ የሚያሳፍረው ግን ለእኛ አንዳች ምላሽ ሳይሰጡን የዴሞክራሲ ፋናው ኢህአዴግ ሁለት ጊዜ ሰልፍ ጠራበት፡፡ ለመሆኑ ‹‹ይህች ሀገር የማን ናት?›› እኛው የኢህአዴግ ወይንስ የራሳችን? ባለፈው ሩብ ምዕተ-ዓመት ይህን መሰል ለቁጥር የሚያታክቱ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ከዚህም የከፉ ብዙ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በእርግጥ ምርጫ ሳምንታት ሲቀሩት ለዓመታት በአገዛዙ ክርን የደቀቁ ፓርቲዎች ትንሽ እፎይታ ያገኛሉ፡፡ ከየጉራንጉሩ በመብራት ይፈለጋሉ፡፡ እነርሱም ጨርሰው ተስፋ አይቆርጡምና ግርግሩን ይወዱታል፡፡ በተለይ ደግሞ የምስክር ወረቀታቸውን እንዳይነጠቁ ፊት ማስመታት አለባቸው፣ ብቅ ብለው ‹‹እስትንፋሳችን አልተቋረጠም›› ይላሉ፡፡ እስከዚህ ድረስ ይፈቀዳል፡፡ ግርግሩ ሲሰክን የማስመሰያዋ ሰርግ ዳስ ሲደርቅና የዝንተ ዓለሙ ሙሽራ ወደጫጉላው ሲገባ አፈናው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ሰርክ መሰደብ፣ መደብደብ፣ መሰደድ፣ መታሰር ካስፈለገም የመጨረሻውን ፅዋ መጠጣት ከአፈና ሜኑው አይጠፋም፡፡ አንድ የማይገባ ጥያቄ እንዳነሳ ፍቀዱልኝ? እናንተ በዚህ ሁኔታ የፖለቲካ መሪዎች ብትሆኑ ምን ታደርጉ ነበር? ብዙዎቻችሁ በህግ የተቀመጡ መብቶቻችሁን በመጠቀም እስከመጨረሻው ህዝቡን ለማንቃት በምታደርጉት የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ተግባር ራሳችሁን እንደ እኔና ጓደኞቼ በሽብርና በሀገር ክህደት ተወንጅላችሁና ተፈርዶባችሁ ወህኒ ቤት ታገኙታላችሁ ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡
በወፍ ዕይታ አንዳንድ ነገሮችን መዳሰሴ ያለነገር አይደለም፡፡ እንደምትረዱትና በህይወታችሁም እንዳያችሁት ለዕሩብ ምዕተ-ዓመት ይችን ሀገር የገዛው እየገዛ ያለው ሃይል ካለፉት አገዛዞች በምን ይሻላል? ኢትዮጵያስ እንደሚነገርላት የነጻነት ምድር ወይንስ የጭቆና ቋያ ናት? አሁን ያለው አገዛዝ በተግባር ሲፈተሽ ወታደራዊ ወይን ሲቪል? የሚለውን ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን በተጨባጭ ያለፍኩባቸውን ወሳኝ ነገሮች ወደተከበረው ህሊናችሁ ሚዛን ለማቅረብ ነው፡፡ ለመሆኑ በ1993 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስንት ንፁሃን ተቀሰፉ? ስንት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተገደሉ? ስንቶች ተደበደቡ? ስንቶችስ ተሰደዱ? ከ1992 ዓ.ም. ምርጫ ጋር ተያይዞ ስንቶች ህይወታቸውን አጡ? የ1997 ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ ስንቶች ህይወታቸውን አጡ? ስንቶችስ አካላቸው ጎደለ? ከ2002 ዓ.ም. ምርጫ ጋር ተያይዞ ስንቶች ስንት መከራን ተቀበሉ? እነማን ህይወታቸውን አጡ? በተለያዩ ዓመታት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ህዝቡ ላይ ምን ደረሰ? የኃይማኖት አባቶችስ ምን አላችሁ? በ2001 ዓ.ም. የዜጎችን መብት ለማፈን ስለወጡ ህጎች ምን አላችሁ? የፓርቲዎችን እግር ለመቁረጥ በውል የሰላው የሽብር ህግ ሲወጣ ሰምታችሁ ይሆን? የዚህን ህግ መውጣት አስመልክቶ አያሌ ወገኖች ሙሾ ሲያሰሙ ድምጻችሁን ምን በላው? ምንአልባት በትክክለኛነቱ አምናችሁበት ይሆን? ለማንኛውም በእነርዕዮት ዓለሙና ውብሸት ታዬ፣ ሩት ክፍሌና ሌሎች ዜጎች ላይ ያረፈው የፀረ-ሽብር ሰይፍ አንዳች ዑዑታ ሳይበግረው እኛም አንገት ላይ አረፈ፡፡ ስመ-ጥሩ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም ለ8ኛ ጊዜ በዚህም የሽብር አንቀጽ ተከሰሰ፡፡ እጅግ አስቸጋሪ በሆነው የሰላማዊ ትግል ሰርጥ ውስጥ የምንመላለስ ዜጎች ልጆቻችንን ከትምህርት ቤት የምንመልስበት ፋታ እንኳን ተነፍገን ከየሻይ ቤቱና ከየመንገዱ ከመንጋ መሀል ለእርድ ተጠምዝዞ እንደሚወሰድ ጠቦት ‹‹አሸባሪዎች›› እየተባልን በህዝባችን መሀል እጆቻችንን ታስረን ተነዳን፡፡ በሰላማዊ ትግሉ ተስፋ ባለመቁረጥ ሲውተረተር የነበረው ፓርቲ አንድነት ላይ የመጀመሪያውን ሰይፍ ሰነዘሩ፡፡ በእርግጥ በሌላ አኳኋን የፓርቲው የመጀመሪያ ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳን ዘብጥያ አውርደው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ህጉ ህዝብን በማያከብሩ፣ እውነትን በናቁና ፈጣሪን በማይፈሩ ሰዎች እጅ ሲወድቅ ትልቅ የጥፋት መሳሪያ እንደሚሆን ከዚህ ወዲያ ማሳያ ከወዴት ይመጣል?
አንደበታችንን በሸበቡበትና ብዕራችንን ባደቀቁበት ሁኔታ ቀድሞውንም በጨረሱት ጉዳይ ላይ ለፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱም እንኳን ስራውን እስኪጨርስ ሌላ ህግ ሳይጥሱ መቀመጥ አልቻሉም፡፡ በተለይ የክርስትና ኃይማኖት አባቶች በቅጡ የምታውቁት “አኬልዳማ” የሚለው ቃል ተመርጦልን በውሸት የተደረተው ዶሴ ላይ በውሸት የደለበ ፊልም ሰሩብን፡፡ በእኔ ላይ ብቻ እንኳን በውሸት ለማስመስከር አራት ሰዎችን “ቶርቸር” አድርገዋል፡፡ ከአራቱ ሁለቱን ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ‹‹በውሸት አንመሰክርም›› ያሉት ደግሞ እንደእኔው የፊልሙም፣ የክሱም፣ የፍርዱም አካል ሆነው እድሜያቸውን በእስር ቤት እየገፉ ነው፡፡ እውነቱን መርገጥ የቻሉት ደግሞ ተፈተዋል፡፡ በዚህ ፊልም መከረኛውን ህዝብ ‹‹በሽብር ሊንጡህ የነበሩትን ከጉያህ መንጥረን ስላምህን አስከበርንልህ›› ብለውታል፡፡ የፈለጋቸውን ህግ ቢያወጡ፣ የፈለጋቸውንስ ፊልም ቢሰሩ ከእነርሱ በላይ የተደረረ ሰማይ እንጂ ሌላ ምን አለ? ብዙ ጊዜ በእኛና በመሰሎቻችን ላይ የሚያሰሙትን የሽብር ቧልት ስሰማ ፈጣሪ እውነተኛውን ሽብር እንዲያርቅልን መጠየቄ አልቀረም፡፡ የሆነ ሆኖ በዚህ አገዛዝ ጭቃ አቡክተው ያደጉና አፋቸውን የፈቱ ልጆችን እንጀራ ፍለጋ በሄዱበት በባዕድ ምድር ለማሰብ እንኳን በሚከብድ አሟሟት አጣናቸው፡፡ የሽብርን ገፈት ተጎነጨን፡፡ አሁንም ከዚህ መሰሉ አደጋ ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ ሀገራችንን ይታደጋት፡፡ እነርሱ ግን አሁንም በህግና በሽብር ስም የጀመሩትን ቧልት ቀጥለዋል፡፡
እውቁ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ቅዱስ ቶማስ አኩናስን በመጥቀስ ስለፍትሃዊና ኢ-ፍትሃዊ ህግ ከበርሚንግሀም እስር ቤት በጻፉት ደብዳቤያቸው ላይ ያነሱትን ሀሳብ በዚህ ቦታ ላይ መጥቀስ ተገቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ኢ-ፍትሃዊ ህግ ‹‹ከዘላለማዊና ተፈጥሯዊ ህግ ያልተቀዳ ነገር ግን ሰዎች ተግባር ላይ የሚያውሉት ህግ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ልዕልና የሚያዋርድ ማንኛውም ህግ ኢ-ፍትሃዊ ህግ ነው፡፡ በተቃራኒው የሰውን ልጅ ልዕልና ከፍ የሚያደርጉ ህጎች ሁሉ ፍትሃዊ ህጎች ናቸው›› ብለው ነበር፡፡ አክለውም ‹‹ሰዎች እንዲያደርጉብህ የማትፈልገውን በሌሎች ላይ አትፈፅም›› እንደማለት ይመስለኛል፡፡ ዶ/ር ኪንግ እንዳሉት በሂትለሯ ጀርመን የተፈፀሙ ግፎች በህግ አንቀፅ ወይንም በህግ ማዕቀፍ ውስጥ እንደነበር አፅንኦት ሰጥተው ተከራክረዋል፡፡ በሌላ ወገን የሀንጋሪ የነፃነት ታጋዮች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ህገ-ወጥ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ አንድን አይሁድ በዘመኑ ከሚደርስበት መከራ ማጽናናትም ወንጀል ነበር፡፡ እኔ ከታሰርኩ በኋላ ባለቤቴን በስልክ ያጽናናት ዳንኤል ሺበሺ ይኸው ወንጀል ሆኖ ተጠቅሶበት ዛሬ እርሱም አሸባሪ ተብሎ ዘብጥያ ወርዷል፡፡ በእኛ ሀገር በህግ ስም የተሰሩ ግፎችና ሸፍጦችን ስንቱን አንስተን ስንቱን መተው እንችላለን? በአሳለፍነው ሩብ ምዕተ-ዓመት ስንቶች በግፍ ተገደሉ? ስንቶችስ ታሰሩ? ስንቶችስ ተሰደዱ?

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *