ተስፋዬ አ.

ተስፋዬ አ. (tes983398@gmail.com)

ለመግቢያ ያህል
“ሕገ ቤተክርስቲያን”፣ “ፓትርያርክ” እና “ቅዱስ ሲኖዶስ” በዚህ መጣጥፍ ላይ ተደጋጋሚ የተጠቀሱና የመጣጥፉን ሀሳብ የተሸከሙ ቃላት ሲሆኑ ለነዚህ ቁልፍ ቃላት በቅደም ተከተላቸው መሠረት አውዳዊ ትርጓሜ በመስጠት የዛሬውን ጽሑፌን ልጀምር፡፡ “ሕገ ቤተክርስቲያን” የቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዳደርን በሚመለከት የበላይ ሕግ ሲሆን የቤተክርስቲያኒቱ እናት ሕግ በመባል ይታወቃል፡፡ “ፓትርያርክ” ርዕሠ አበው፣ አበ ብዙኃን የሚል ትርጉም ሲኖረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካህናትና ምእመናን መንፈሳዊ መሪና አባት ነው፡፡ “ቅዱስ ሲኖዶስ” ከፍተኛው የቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ሕግ አውጭና ወሳኝ አካል ሲሆን የቤተክርስቲያን የመጨረሻው ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤትም ነው፡፡
የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከሚለያዩበት በርካታ ነገሮች አንዱ የርዕሠ አበው (ፓትርያርክ ወይም ፖፕ) ጉዳይ ነው፡፡ ቫቲካን ፖፗን የማይሳሳት፣ ቀጥተኛ የእግዚአብሔር እንደራሴና የነገሮቿ ሁሉ የበላይ አድርጋ “በእኔነት” የተገለጸ የፖፑን ብቻ የበላይነት በሚያረጋግጥ ሕግ መነሻነት ስራዎቿን ታከናውናለች፡፡ በተነጻጻሪነት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ‹‹እኔ›› ከሚለው ዕሳቤ በመውጣት “እኛ እና መንፈስ ቅዱስ” የሚለውን መርህ በመከተል የነገሮቿ ሁሉ የበላይ ቅዱስ ሲኖዶስን በማድረግ ጉዳዮቿን ትሰራለች፡፡ ለቅዱስ ፓትርያርኳም እንደ ርዕሠ አበውነታቸው ብፁዕ ወቅዱስ ብላ ተገቢውን ክብርና ቦታ እንደ ሥጋ ለባሽ ሰውነታቸውም ከሕግ በላይ እንዳይሆኑባት ተጠየቅ ያላቸው ተግባራትና ኃላፊነቶችን በመስጠት ፓትርያርክ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ብላ ትሾማለች፡፡
በዚህ አጭር መጣጥፍ ስለ ፓትርያርክ ‹‹ሕገ ቤተክርስቲያን ምን ይላል?›› ብዬ ጠይቄ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ፣ ስለ ፓትርያርክ ተግባርና ኃላፊነት እና ስለ ፓትርያርክ ከማዕረግ መውረድ ሕገ ቤተክርስቲያኑ የሚለውን አስተጋባለሁ፡፡ የመጣጥፌ ዓላማም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ በተጠየቃዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ያለ እና ሊሳሳት የሚችል መሆኑን ማሳየት ነው፡፡
የፓትርያርክ ምርጫ
ኑፋቄ፣ ዘረኝነት፣ ሙስና፣ አምባገነን ፓትርያርክ፣ የቄሳር ጣልቃ ገብነት እና የመሳሰሉት ጉዳዮች በህብረትም በተናጥልም የቤተክርስቲያን ፈተናዎች ሆነው በየዘመኑ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በአንደኛው ዘመነ ፕትርክና የነበረው ፈተና በስድስተኛው የፕትርክና ዘመን ሊኖርም ላይኖርም ይችላል፡፡ ወቅት እና ዘመን በራሱ የሚፈጥረው ተግዳሮት ይኖራል፡፡
የሕገ ቤተክርስቲያን ምንጭ ከሆኑት አንዱ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 4 ቁጥር 69 እንደዘመኑ ተግዳሮት ፓትርያርክ ይመረጥ ብሎ ያዛል …“ከሐዲዎች በመብዛታቸው ምክንያት መጻሕፍትን አብዝቶ የተማረው ቢፈለግ መጽሐፍ ዐዋቂውን ይሹሙት፡፡ የተፈለገው መልካም አስተዳዳሪን ለማግኘት ቢሆን በበጎ አስተዳደር የሚያስተዳድረውን ይሹሙት፡፡ ገጽ 35” ፍትሐ ነገሥቱ አክሎም በእዚህ ዘመን እንዳለው ዘርፈ ብዙ ችግር ቤተክርስቲያኒቱ ስትፈተን ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ለቦታው ብቁ የሆነ ሰው መመረጥ እንዳለበት ይናገራል፡፡ “መራጮች ይህችን ሹመት ለሚገባው ሰው መስጠት ይገባቸዋል፡፡ ይህንንም ባያደርጉት ኃጢአት ይሆንባቸዋል፡፡ ገጽ 35”
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሉዓላዊነቷን ካስጠበቀች በኋላ ወጥ የሆነ በራሷ አውድ ላይ የተመሠረተ ቋሚ የፓትርያርክ ምርጫ ሕገ ደንብ ባይኖራትም ፍትሐ ነገሥቱን መነሻ በማድረግ እንደየዘመኑ ሁኔታ ተለዋዋጭ የሆነ የምርጫ ደንብ በማዘጋጀት አምስት ፓትርያርኮችን ወደ መንበሯ አምጥታለች፡፡ አሁን ዘግይታም ቢሆን ቋሚ የፓትርያርክ ምርጫ ሕገ ደንብ በማዘጋጀት ስድስተኛውን ፓትርያርክ ወደ ፕትርክናው ጎራ ቀላቅላለች፡፡ አዲሱ ሕገ ደንብ አስራ ሁለት መመዘኛዎችን እንደ መስፈርት አስቀምጧል፡፡ ከእነዚህ መስፈርቶች ውስጥ “ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ፣ ትምህርተ ኃይማኖትንና ቀኖና ቤተክርስቲያንን ጠንቅቆ ያወቀ፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኃይማኖት ጽኑዕ የሆነና በቅድስና ሕይወቱና በግብረገብነቱ የተመሰገነ፣ ከቤተክርስቲያኒቱ የአብነት ት/ቤቶች በአንድ ት/ት የተመረቀ ወይም ሁለገብ የቤተክርስቲያን ት/ት ያለው ሆኖ ከከፍተኛ የመንፈሳዊ ት/ት ተቋማት ወይም በዘመናዊ ት/ት ቢያንስ ዲፕሎማ ያለው፣ ለሌሎች መልካም ዓርአያ መሆን የሚችል፣ ታማኝና ቃሉን የማይለውጥ ንጹህ ሰው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠባቂና ጠበቃ መሆኑን በተጨባጭ ያስመሰከረ እና መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በመፈጸም በቂ የአስተዳደር ችሎታና ልምድ ያለው፡፡ /ገጽ2-3 / የሚሉት ጎልተው የሚወጡ ተጠቃሽ መመዘኛ መስፈርቶች ናቸው፡፡
ይህንና ሌሎቹን መስፈርቶች ያሟላ አባት ቢገኝ ቤተክርስቲያኒቱ ከሚያጋጥማት እና ካጋጠማት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊያላቅቃት እንደሚችል በማመን አባቶች ሥርዓቱን ከሠሩ በኃላ ይህን ሂደት አሟልቶ የተመረጠው ፓትርያርክ በግራ እጁ አርዌ ብርት በቀኝ እጁ መስቀልና ወንጌል ደራርቦ በመያዝ ከዚህ በታች ያለውን ቃለ መሃላ በእግዚአብሔር ፊት እንዲምል ያዛሉ፡፡ “እኔ አባ እግሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሆኜ ስመረጥ የተጣለብኝን ኃላፊነት እግዚአብሔርን በመፍራትና በማክበር ያለ አድልዎና ያለምንም ተፅዕኖ ሁሉንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካህናት፣ ምዕመናንና ምዕመናት በእኩል አባትነት በቅንነትና በታማኝነት፣ በፍቅርና በትህትና ለማገልገልና በአንዲት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት መሠረት የክርስቶስን መንጋ ለመንከባከብና ከተኩላ ለመጠበቅ በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ቃል እገባለሁ፡፡ ገጽ 9”
ስድስተኛው ፓትርያርክም ፊት አይተው ላይፈሩና ላያደሉ፣ እገሌ የዚህ ብሔር ነው እገሌ ደግሞ ከዚያ ብሔር ነው ብለው ላይሉ፣ በቂም በቀል ላይፈርዱ፣ በቁሳዊ (ሙስናን ከመሳሰሉት) እና በቄሳራዊ ተጽዕኖ ላይወድቁ ቃል ኪዳን ገብተው ነበር ወደ መንበሩ የመጡት፡፡
የፓትርያርክ ተግባርና ኃላፊነት
የቅዱስ ሲኖዶስን የበላይነት በመንጠቅ ለፓትርያርክ ለመስጠት የተደረጉ ሙከራዎች ቢኖሩም መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ የሆነው “ሕገ ቤተክርስቲያን” ግን የፓትርያርኩን ተግባርና ኃላፊነቶች በአንድ አንቀጽ በአስራ አራት ቁጥሮች ወስኗቸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንኳር የሆኑትን ልጥቀስ …“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ኃይማኖት፣ ትውፊትና ቀኖና ይጠብቃል፣ ያስጠብቃል፤ የቅዱስ ሲኖዶስን ምልዓተ ጉባኤንና ቋሚ ሲኖዶስን በሊቀመንበርነት ይመራል፤ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ለኤጲስ ቆጶሳት የሊቀጵጵስና መዓረግ ይሰጣል፤ በቅዱስ ሲኖዶስ የወጡ ሕጎችን የተላለፉ መመሪያዎችን የተሰጡ ውሳኔዎችን ለሚመለከታቸው ሁሉ በፊርማው ያስተላልፋል፣ በተግባር መዋላቸውንም ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፤ በቤተክርስቲያኒቱ ታላላቅ ዓመታውያን በዐላት ላይ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ እየተገኘ ለምእመናን ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ ይሰጣል፤ የቤተክርስቲያንን ጉዳይ አስመልክቶ ከመንግሥት ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችን፣ እንደዚሁም ሌሎች ቤተክርስቲያንን የሚመለከቱ ዐበይት ጉዳዮችን ሁሉ በቅዱስ ሲኖዶስ እያስወሰነ አስፈላጊውን ተግባር ያከናውናል፤ በውጭ ሀገርም ሆነ በሀገር ውስጥ በሚደረጉ ስብሰባዎችና ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ቤተክርስቲያንን በመወከል ይገኛል ወይም ሌላ ሰው ይወክላል፡፡ ስለተከናወነው ተግባርም ለቅዱስ ሲኖዶስ ሪፖርት እንዲቀርብ ያደርጋል፡፡ /ገጽ 28-29/
ሕገ ቤተክርስቲያኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ሳይፈቅድና ሳይወስን ፓትርያርኩ ለብቻቸው ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን አንድም ጉዳይ እንዳይከውኑ ብሎ ቢያዝም በተለያዩ አጋጣሚዎች እና ለበርካታ ጊዜያት ሕግን ጠብቀው እንዲያስጠብቁ በታዘዙ ፓትርያርኮቻችን አማካኝነት ሕግ ሲጣስ ድንበር ሲፈርስ ይታያል፡፡ ሌሎቹ የሕግ ጥሰቶች እንዳሉ ሆነው ለምን ይህን ፈጸሙ ብለን ብዙዎቻችን ከምንጨነቅባቸውና ምክንያቱን ለማወቅ ከምንጓጓባቸው የሕግ ጥሰቶች አንዱ አምስተኛውም ስድስተኛውም ፓትርያርኮች በተመሳሳይ ሁኔታ ቅዱስ ሲኖዶስ ሳያውቀውና ሳይፈቅደው በኃይማኖት ወደማይመስሉን ጣልያኖች /ቫቲካን/ ያደረጉት ጉዞ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ለዚህና ለሌሎቹም ሕገ ወጥ ተግባራት ሕገ ቤተክርስቲያን ፍቱን መፍትሔ አለው፡፡
የፓትርያርክ ከማዕረግ መውረድ/መሻር
ሕገ ቤተክርስቲያን የፓትርያርክን ተግባራትና ኃላፊነቶች ከደነገገ በኋላ ቀጥታ የሚገባው ለአምባገነን ፓትርያርክ መፍትሄ ወደማበጀቱ ሲሆን አንቀጹንም “ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ ከማዕረግ መወረድ” የሚል ርዕስ ሰጥቶታል፡፡ አንቀጹ አንቀጽ 33 ሲሆን ከማዕረጉ የተሻረው ፓትርያርክ ከውግዘቱ በኃላ ወዴት እና እንዴት መቀመጥ እንዳለበትም ይናገራል፡፡ ይህ አንቀጽ ሁለት የውግዘት ምክንያቶችን በጉልህ ካስቀመጠ በኃላ ሌሎቹ የሽረት መንስኤዎች በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 5 ከቁጥር 172-268 ድረስ ባሉት ገጾች ውስጥ ይገኛሉ ብሎ ወደዚያ ይመራናል፡፡
ፍትሐ ነገሥት 25 ጉዳዮችን የውግዘት መንስኤ አድርጎ ያቀርባል፡፡ የውግዘት መንስኤዎቹ ለቅዱስ ፓትርያርክም (ቅዱስ የሚለው ተቀጽላ ለመንበሩ የተሠጠ እንጂ ለግለሰቡ የተሰጠ አይደለም ምክንያቱም በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አንድ ሰው ቅዱስ የሚባለው ከሞተ በኋላ ነው፡፡ ደግሞም መጽሐፉ ሲኖዶስ “በስመ ኃዳሪ ይጼውእ ማኅደር ወበስመ ማኅደር ይጼውእ ኃዳሪ” በማደርያው ስም ያደረው ይጠራል፤ በአዳሪውም ስም ማደርያውም ይጠራል እንዲል)፣ ለጳጳስም፣ ለኤጲስቆጶስም፣ ለቄስም፣ ለዲያቆንም የሚሠሩ ናቸው፡፡
ከእነዚህ መንስኤዎች ውስጥ ሦስቱ የዘመናችን የቤተክህነቱ መገለጫ በሆነው ሙስና ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ “ይህችን ማዕረግ በመማለጃ የተሾመ …ይሻር፤ እስኪሾም ድረስ መማለጃ እሰጣለሁ ብሎ የተሾመ ሹመቱን አይቀበሉት፤ ሳይገባው ገንዘብ ተቀብሎ የሚሾም (“ሾ” ላላ ተደርጎ ይነበብ) ቢኖር ይለይ፡፡ ገጽ 63”
በዘመኑ የፖለቲካ ባለሥልጣናት የተሾመም ሆነ ከእነሱ እገዛ ያገኝና ወደ ሹመትም የመጣ ፓትርያርክ መወገዝ እንዳለበትም ተጽፏል፡፡ “በዚህ ዓለም መኳንንት ቢረዳ ይሻር፡፡ እርሱና ግብረ አበሮቹ ሁሉ ይለዩ፡፡ ገጽ 63፣ ከዓለም መኳንንት ጋር ይረዱት ዘንድ …የተማፀነ ቢኖር ፈጽሞ የተወገዘ ነው፡፡ ገጽ 64”
ከመናፍቃን ጋር አንዳች አይነት ግንኙት ያለው ወይም ኅብረት የፈጠረ ፓትርያርክ ከቤተክርስቲያኒቱ ይለይ ተብሏል …“የሐራ ጥቃን ጥምቀት የተቀበሉ ወይም ቁርባናቸውን የቆረቡ ወይም አብረዋቸው ቢጸልዩ ይለዩ፡፡ ገጽ 68”
በተንኮል በጉልበት ሹመቱን ያገኘ፣ ቂመኛ የሆነ፣ ለተራቡ ችግረኞች የማይራራ፣ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚንቅ፣ እግዚአብሔርን ከማገልገል ይልቅ ቄሳርን ያገለገለ እና እዚህ ላይ ያልጠቀስኳቸው ሌሎች ተግባራት አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪን ከፕትርክናው መንበር የሚያስወርዱ ፈጽሞ የተከለከሉ ተግባራት ናቸው፡፡ /ገጽ 63-70/
ስደመድመው
ከጥቂት ዓመታት በፊት በተጻፈ መጽሐፍ ውስጥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክፉኛ ይተቻል ይሰደባልም፡፡ የአምላካችን መሰደብ ያናደዳቸው ወጣቶች ቤተክህነቱ መልስ እንዲሰጥበት በማለት የስድቡን መጽሐፉ ይዘው ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ወዳሉት ክፍል ይሄዳሉ የክፍሉ ኃላፊዎች የሰጧቸው መልስ የመደምደምያ ሐሳቤን ከማጠንከሩ በላይ እጅግ አሳፋሪ እና አስፈሪ ስለ ነበር እዚህ ልጥቀሰው፡፡ ከጌታችን መሰደብ ይልቅ የፓትርያርኩ መገሠጽ ያንገበገባቸው የቤተ ክህነቱ ኃላፊዎች ለወጣቶቹ እንዲህ የሚል መልስ ሰጧቸው… “እናተ ሥራ አጥታችኋል፣ እኛ ለራሳችን አባታችን (ፓትርያርኩን ነው) ተሰድበው ተጨንቀናል …ብለው አመናጭቀው መለሱን፡፡ (ለምን አልሰለምሁም፡፡ ገጽ 6)
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤተክህነት አካባቢ ፓትርያርኩና እና ሥልጣናቸው አምላክ አከል እና ከሕግ በላይ እየሆነ መጥቷል፡፡ እንደ ብጹአን አባቶች ፓትርያርኩን ከሕግ ውጭ ይህን ይህን ተግባር ፈጽመዋል፣ ይህም ጉዳይ እርሶን አይመለከትም፣ የፈጸሙት ሕገ-ወጥ ተግባር ከአንድ አባት የማይጠበቅ ከመሆኑ በላይ ለመንበሩ አይመጥንም ብሎ ሕገ ቤተክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት የማስተካከያ ብሎም በሕጉ መነሻነት አስፈላጊውን የመጨረሻ እርምጃ መውሰድ የእከሌ ማኅበር ደጋፊ ነህ አሊያም የዚህ ብሔር ተወላጅ ስለሆንክ ነው ወይም ሌላ አያስብልም፡፡ እንደ ልጅነትም ፓትርያርክ ሆይ የቤተክርስቲያናችንን ሉዓላዊነት ደፍረው እያስደፈሩ ነውና ስለክርስቶስ ብለው በአግባቡ ይምሩን ብሎ መናገርም ድፍረትም ኃጢአትም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ፍትሐ ነገሥት ”ክፉ ጠባቂን የሚከተል ሰው ቢኖር ሞቱ በፊቱ የተገለጠ ነው፡፡ ገጽ 58” ይላልና፡፡ ስለዚህ ከዘላለማዊ ሞት ለአባቶች በአግባቡ ሕጉን መተርጎም ለእኛም ለልጆች የሕግ ያለህ ብሎ መጮህ ይሻላል፡፡ ርግጥ ነው፣ ፓትርያርክ ይሳሳታል ለዚህም ምስክሬ ሕገ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ዛሬም ነገም ሕግን መነሻ አድርጌ እጮኻለሁ፡፡
ከጽዮን ምሕረት ለኢትዮጵያ

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *