ፅጌረዳ ጎንፋ

“10 ኢንጂነር፣ 2 ኢኮኖሚስትና 2 ሶሺዎሎጂስት” እሳቸው ባለፈው ሳምንት ከምሁራኑ ጋር በተወያዩበት ወቅት አንድ ድልድይ ለመስራት የሚያስፈልገውን የባለሙያ ምጣኔ የተናገሩት ነው:: ለጥቀውም “ይህ ፖሊሲ የኢትዮጵያን ታሪክ አና የታሪክ ት/ት ምርምርን ያቀጭጫል›› የሚል ጥናት ከቀረበ አልቆረብንበትም፤ ይቀየራል::” ባሉት መሰረትም ላለፉት ቀናት ሰለቸኝ፣ ደከመኝ ሳልል አጥንቼ የደረስኩበትን ውጤት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡-
/በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ/
ከጥቂት ጊዜ በፊት መኖሪያ መንደራችንን አቋርጦ የሚያልፍ አንድ ጅረት ነበረ፡፡ ከጅረቱ ወዲህ ማዶ እና ወዲያ ማዶ የምንኖር ነዋሪዎች “እስከመቼ የቅርብ ሩቅ ሆነን? … እስከመቼስ ተቆራርጠን? …እናንተም ኑ ልጆቻችሁን እኛ ት/ቤት አስተምሩ ….እኛም እንምጣ ጤና ጣቢያችሁ እንታከም (ሆስፒታል ያላልኩት ሆነ ብዬ ነው) …እንናንተም ኑ የእኛን ደብር ተሳለሙ …እኛም እንምጣ እናንተ መስኪድ እንስገድ …ኑ የመረዳጃ እድር ተመዝገቡ …የተዋደዱ ልጆቻችንም ይጋቡ …ይዋለዱ እንዛመድ …እንምጣ …ኑ በአንዲት ጅረት ሳቢያ ምነው ተቆረርጠን መቅረታችን?”
ተባብለን ስናበቃ ድልድይ ለመስራት ተወያየን፡፡ እንግዲህ ለዚህች አስር እርምጃ ለማትሞላ ድልድይ መንግስትንም አናስቸግር …ያሉንን ምሁራን እና የገንዘብ አቅም አዋጥተን እንገነባታለን እንጂ ብለን ተስማማን (መሃንዲስ እኛው፤ የገንዘብ ምንጭ እኛው፣ ቀያሽ እኛው፣ ተቀያሽ እኛው …እንዲሉ!)
ይህን ቅን ሃሳብ እውን ለማድረግ የባለሙያ እና የገንዘብ መዋጮው ጎረፈ …ለጊዜው የገንዘቡን መጠን ልተወውና (ሁሌም የገንዘብ መጠን ለምን እንደሚደበቅ ባይገባኝም … ደመወዝ ድብቅ፤ “ለፊልም ስራ ስንት ተከፈለሽ?” ጭጭ! ወይም “በቂ ነው”) የሆነ ሆኖ ለተሻለ ስራ ወደ ከተማ የኮበለሉ፤ ኮብል ስቶን በማንጠፍ ላይ ያሉ፤ በማኅበር ተደራጅተው ስጋ ቤት እና ግሮሰሪ የከፈቱ …እናም በሌላም በሌላም ምክንያት መገኘት ያልቻሉት ቀርተው ከሁለቱ መንደር የተውጣጡት ምሁራን እና ባለሙያዎች እነኚህ ናቸው …
10 ኢንጂነር
2 ኢኮኖሚስት
2 ሶሺዎሎጂስት …“ይሄው ገንዘቡ በሉ ድልድይ ስሩ” ተባሉ፡፡
የባለሙያዎቹ አጭር የሥራ እና የት/ት ታሪክ …/Curriculum Vitae/
አንደኛው ኢንጂነር, አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዛው ቀዬ ያጠናቀቀ ነው፡፡ መሰናዶ ሲገባ ማኅበራዊ ሳይንስ መማር ቢፈልግም የተፈጥሮ ሳይንስ እንዲማር የተፈረደበት ዩኒቨርሲቲም ሲገባ ፖለቲካል ሳይንስ መማር እንደፈለገ ሲቪል ኢንጂነር የተማረ …የልማት እና የመልካም አስተዳደር ፍላጎቱን ለሟሟላት በየኮሚቴው መሪ፣ አስተባባሪ እንደሆነ፣ የህዝብ አስተዳደር እንዳማረው፣ የተማሪዎች ተወካይ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ …እንዲያውም ፖለቲከኛ ከሆነ ለምርጫ ቅስቀሳ በሚወዳደርበት ወቅት ልዩ ምልክቱን ድልድይ አድርጎ ለመወዳደር ያቀደ (ትርጓሜውም ትውልዱን ከመጪው ጊዜ ጋር ለማገናኘት …ሃሃሃ) “ከመረጣችሁኝ በዚህ ወንዝ ላይ ድልድይ አስገነባለሁ” ብሎ ሊቀሰቅስም ያሰበ …የመንደሩ የጤና፤ የኢኮኖሚ፣ የውጪ ጉዳይና የት/ት ፖሊሲ የሚያሳስበው እንደገና መቀረፅም አለበት ባይ …“ይህ ለድልድይ ስራ አይጠቅምም አርፈህ ፌሮ ጠምዝዝ” አሉት …
ሁለተኛውም እንዲሁ መማር ይፈልግ የነበረው ታሪክ ነበር …ከጥንት ከሜሶፖታሚያ ጀምሮ የተሰሩ ድልድዮችን ታሪክ ሲያጠና …ስንቶቹ ፀኑ? የፀኑትስ እንዴት ፀኑ? ስንቶቹስ ፈረሱ? የፈረሱት ለምን ፈረሱ? ለመፍረሳቸው ድርስና መሠረታዊ ምክንያቶቹ ምን ነበር? የማይፈርስ ድልድይ ለመስራት ምን እናድርግ? ድልድይ ለአንዲት መንደር ያለው ታሪካዊ ፋይዳ …የሁለት ድልድዮች ወግ …የሚል ሃሳብ ሲያመጣ “ታሪክ ለድልድይ አይጠቅምም አርፈህ ኮንክሪት አላቁጥ” አሉት…
ሶስተኛው ፍትሕ የጠማው የህግ ሙያ አፍቃሪ፣ ከልጅነቱ ጀምሮ ለተበደሉት ሲፈርድ፣ በጨዋታ መሃል ዳኛ ሆኖ ሲተውን፤ በደልን ግፍን ሲቃወም፤ ሁለተኛው መንደር ካለ ት/ቤት ትምህርቱን ያጠናቀቀ …ራሱን ዘወትር ካባ ደርቦ ለጭቁኖች ሲከራከርላቸው የሚስል …እጆቹ ከአናፂ መዶሻ ይልቅ የዳኛ መዶሻ ለመጨበጥ የሚሹ …ነፍሱ “ፍትሕ …ፍትሕ …ፍትሕ” የምትል …በድልድዩ ሳቢያ በሁለቱ መንደሮች መካከል እንደታሰበው መቀራረብ ቀርቶ መለያየት እንዳይፈጠር …ፍትሃዊ የድልድይ አጠቃቀም እንዲኖር የሚጥር ጥልቅ አተያይ እና ብያኔን (Critical Judgment) የሚያደንቅ፣ እንዲያውም ለድልድዩ ስራ ከወንዙ ዳር እና ዳር የሰፍረው የነበሩ ገበሬዎች የህልውናቸው መሰረት ከሆነው የጅረት ዳርቻ መነሳት የሚያንገበግበው ተመጣጣኝ ምትክ ቦታ አለማግኘታቸውም …የሚቆረቁረው በግንባታ ስፍራ የሚጎዱ እና የሚሞቱ ሰራተኞች ጉዳይ ጉዳዩ ሆኖ ቁጭ!
አራተኛው ፍልስፍና የነፍሱ ጥሪ ናት …“ለምን?” ይላል፣ “እንዴት?” ይላል፡፡ “ድልድይ ለምን ይሰራል?” ይላል፡፡ “ካለ ድልድይ መሸጋገር የምንችለበት አማራጭ የለም ወይ?” ይላል፡፡ …“ድልድይ ስጋን እንጂ ነፍስን አያሻግርም ይልቅ ነፍሳችሁን ወደ እውቀት ለማሻገር አንብቡ …አሪስቶትል ስለድልድይ እንዲህ ብሎ ነበር፤ ፕላቶ ደግሞ እንደዚህ” ይሄ ሰው እንዲያውም እዛኛው መንደር ካለ ኮሌጅ ገብቶ ፍልስፍናን ለመማር የድልድዩ አለመኖር አግዶት እንጂ እስከዛሬም ባልቆየ ፍልስፍናን በፅንሰ-ሃሳብ ደረጃ መረዳት ማስረዳት እና ማስተማር ከእሱ ወዲያ ላሳር …“ምን እዚህ እብዱን ኢንጂነር አድርገውብን ስራው በየት ይሰራ?” እያሉ ያማርራሉ ባልደረቦቹ …
አንዱ ንግድ ከደሙ የተዋሃደ …ብረቱን ሸጦ ሌላ የሚገዛ “ቁጥሩ አይጉደል እንጂ ብረት እንዲሁ ያው ብረት ነው” ኮንክሪት እንኳ ተቦክቶ ከመድረቁ በፊት ለመሸጥ የሚጎመዥ፤ ባለበት ሁኔታ አጓጉዞ ለሽያጭ ለማብቃት የሚያስችል ሀሳብ የሚያወጣ የሚያወርድ …በድልድዩ እየተረማመደ ከወዲያ ማዶ ሰፈር ሰዎች ሲገበያይ የሚያስብ ሲያተርፍ ሲከብር የሚያስብ የሚያልም …
ሶስቱ ምን መሆን እንደሚፈልጉ ሳያውቁ ምህንድስና ትምህርት ክፍል የገቡ …‹‹ጥሩ ገንዘብ ያስገኛል›› ሲባሉ በርትተው የተማሩ፡፡ …በመጨረሻም ኢንጂነር ሆነው ራሳቸውን ያገኙ፡፡
ሁለቱ ኢንጂነር ለመሆን ይፈልጉ የነበሩ …ሥነ-ህንፃ፣ ምህንድስና ንድፍ የሚመስጣቸው …የሚወዱ ነበሩ፡፡ …ስራውን ጀመሩ፡፡ …እንግዲህ ይህ ድልድይ በአስር ኢንጂነር ፋንታ በአንድ የታሪክ ዝንባሌ ያለው፤ በአንድ የፍልስፍና ወዳጅ፤ በአንድ ፖለቲከኛ፤ በአንድ ነጋዴ፣ በአንድ የፍትህ አስከባሪ፤ በሶስት ምን ለመሆን እንደሚፈልጉ ባላወቁ፤ በሁለት ኢንጂነሮች፤ በሁለት ኢኮኖሚስት እና በሁለት ሶሺዎሎጂስት ሊሰራ ተጀመረ፡፡
ቀድሞ ነገር ሀገር ድልድይ ብቻ መች ሆነችና? ኑሮ ግንባታ ብቻ መቼ ሆኖ? ስንበደል የሚፈርድልን፣ ስንጠቃ የሚሟገትልን ፍትህሳ? ያለፈውን ማንነታችንን የሚነግረን፣ ለነገ እንድንጠነቀቅ የሚመክረን ታሪክሳ? እንዴት? ለምን? ወዴት? እያልን እርምጃችንን እንድናጠራ የሚያነቃን ፍልስፍናሳ?
ገቢ፣ ወጪ፣ የመግዛት አቅም፣ የሀብት ክፍፍል የሚያመጣጥልን ኢኮኖሚክስሳ? ባህል እና ቋንቋሳ? ገንቢዎቹ ተመሳሳይ ቋንቋን ተነጋግረው ካልተግባቡ ግንባታውስ እንደ ባቢሎን መሆኑ አይደል? መዶሻ ሲጠየቅ ቱምቢ እያቀበለ …
መንገዱም ድልድዩም ህንፃውም ይገንባ ጥሩ! …ተጓዳኝ እና ተመጋጋቢ ሙያዎች ግን ችላ አይባሉ፡፡
ምህንድስናን ያለ ኢኮኖሚክስ ማሰብ አይቻልም፡፡ በትንሽ ወጪ፣ በከፍተኛ ጥራት፣ በአጭር ጊዜ ግንባታን ሰርቶ ማስረከብ ያለ ማኔጅመንት እውቀት እንዴት ይሆናል፡፡ ብረት አዋቅሮ ኮንክሪት በመደረብ ሬንጅ በማልበስ ድልድይማ ይሰራል፡፡ ግን ምን ያህል ገንዘብ እና ጊዜ ፈጅቶ? በGeo-tech (Soil Investigation) የአፈሩ አይነት ተጠንቶ …የመሸከም አቅሙ ተጣርቶ ተወስኖ …ርዝመቱ አና ስፋቱ ወርዱ ተለክቶ …ከአካባቢው ጋር ያለው መስተጋብር ተጠንቶ ቢሆን ደግ፡፡ አሁን ግን ችግሩ ጅረት ባየን ቁጥር ድልድይ ካልገነባን ማለታችን፡፡
የእኛ መንደር ምሁራን እንደ አለመታደል ሆኖ አንዳቸውም አካባቢ ጥበቃ አልተማሩም፣ ባይማሩም ጥቅሙን ተረድተው ለመንከባከብ አልሞከሩም፣ እፅዋትን እና እንስሳትን እንዴት እንደሚንከባከቡ አያውቁም …ግድም የላቸውም፡፡ …አባቶቻቸው የተከሏቸውን ዛፎች ቆርጠው ቤት ሰርተውባቸዋል፡፡ የቀንድ ከብቶቻቸው የግጦሽ መሬት አጥተው ፌስታል እና ወረቀት ወደ መመገብ ጀምረዋል …ዱር እንስሳት ወደ አጎራባች ደኖች ተሰደዋል፡፡ እንደው ለፉ እንጂ ጅረቷም ለከርሞ በዚህ ጉልበቷ አልቆየችም፡፡ እንደጠገበ ሰው ሽንት ጭል ጭል ማለት ጀምራለች …እንደው ለፉ እንጂ ድልድዩን ወዲያ ማዶ እያዩ ባገጠጡት አለቶቿ ላይ እንጣጥ …እንጣጥ እያሉ ሊሻገሯትም ይችላሉ፡፡
ድልድዩ በተመረቀ በአመቱ ወንዙም ደረቀ፡፡ …እሱም ሊፈርስ አረገረገ!

About the author

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *